Sunday, June 29, 2014

ምርጫ ይራዘምን ምን አመጣው? ማንን ይጠቅማል?


የሰላማዊ ትግል አማራጮች ብዙ እንደሆኑ የሰላማዊ ትግል መስመር የመረጡ ዜጎች እንደሚረዱት እሙን ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ፅሁፍ ያቀረበው ጄን ሻርፕ ከአንሰታይን ኢንስቲትዩት አንዱ ሲሆን ይህም በህዳር 1998 ወደ አማርኛ ተመልሶዋል፤ እርገጠኛ ነኝ ይህ ፅሁፍ እንዲተረጎም ያደረጉት ሰዎች ድህረ ምረጫ 97 የገጠመንን የሰላማዊ ትግል ክፍተት የተረዱ ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ  “የሰላማዊ ትግል 101” በሚል አንድ መፅኃፍ በሰላማዊ ትግል አቀንቃኙ ግርማ ሞገስ ለገበያ ቀርቦዋል፡፡ ይህ መፅሃፍ የቀረበበት ጊዜም ከምርጫ 2007 መቃረብ ጋር ሰናያይዘው ብዙ እንደምንማርበትና ስላማዊ ትግል ፈታኝ መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡ የሰላማዊ ትግል ያልገባቸው እንደሚሉትም የፈሪዎች መሰመር አይደለም፡፡ በሁለቱም መፅሃፎች የቀረቡትን የሰላማዊ ትግል መንገዶች ኢህአዴግ “ነውጥ” ሊላቸው ቢችልም የሀገራችን ተጨባች ሁኔታና የገዢዎችን እና አባሎቻቸውን ስነልቦና በአገናዘበ መልኩ ሊተገበሩ የሚገባቸው እንደሆኑ ይታመናል፡፡ ከአምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ ለመሸጋገር ሰላማዊ አምቢተኝነት - ነውጥ አልባ አብዮት እንደሚያስፈልገን ማንም ያምናል፡፡ ለነገሩ አሁን ያሉት ገዢዎች ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ብለው ጠመንጃ ያነሱ መሆናቸውን ስናሰታውስ እና አሁን ደግሞ የትግል ሰልት መራጭ መሆን ሲያምራቸው ጉዳዩን ምፀት ያደርገዋል፡፡ ከእነርሱ ቀድመው የነበሩት ንጉሡም ሆነ ደርግ አንባገነኖች ነን አላሉም- ኢህአዴግም አንባገነን ነኝ ብሎ እንዲያምን አናስገድደውም፤ እኛ ግን አንባገነን መሆኑን እናምናለን፡፡ የትግል ስልት ምርጫም ቢሆን ከኢህአዴግ አናስፈቅድም፡፡ አሁን የመረጥነው “ሰላማዊ ትግል” ኢህአዴግን ስለሚያስደስት ሳይሆን ዘመኑን የዋጀ አዋጭ የትግል ስልት ነው ብለን ስላመንን ብቻ ነው፡፡
የንጉሡ እና የደርግ ጊዜን ከኢህአዴግ የሚለየው አሁን ዓለም ካለችበት ሁኔታ በተጨማሪ በስራ ላይ ያልዋለም ቢሆንም እጅግ ብዙ ዓለም አቀፋዊ ሰምምነቶችን ጨምሮ ብዙ ሰብዓዊ ዲሞክራሲያዊ መብቶች በግልፅ የሰፈሩበት ህገ መንግሰት መኖሩ ነው፡፡ በደርግ ጊዜ “ዲሞክራሲያዊ መብቶች እውቅና ያግኙ” የሚለው አንዱ ትግል የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ትግሉ ተግባራዊ ይሁኑ ነው፡፡ የዲሞክራሲያዊ መብቶች ተግባራዊ ከሚሆኑበት መንገድ አንዱ ደግሞ በህዝብ ይሁንታ የሚመረጥ መንግሰት መመስረት ነው፡፡ ይህ ሂደት በሁሉም መስኩ ልምምድ ይጠይቃል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ግን ምርጫው ይቆይ የሚሉ ድምፆች እየተበራከቱ ነው፡፡ የዛሬው ፅሁፌም መነሻም ይህ እንዲሆን ፈለግሁ፡፡
ለዛሬ ትኩረቴን የሳቡት ከምርጫው በፊት ሀገራዊ እርቅ ይቅደም እና ከምርጫው በፊት በመስከረም አብዮት ይኑር የሚሉት እንዲሁም በአብዮት ለውጥ ቢመጣስ ማን ይረከባል የሚሉ ሃሳቦች ናቸው፡፡ የእነዚህ አሰተያየቶች ዋናው ገፊ ምክንያት አስተያየት አቅራቢዎች በገዢው ፓርቲ መማረራቸው ከማሳየት በተጨማሪ ለለውጥ ያላቸውን ፍላጎት ነው፡፡ ገልብጠን ስናየው ግን ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው የሚያመዝኑ አሰተያየቶች ናቸው ብዬ ነው የምወሰድው፡፡
ከምርጫ ሀገራዊ እርቅ ይቅደም አሰተያየት የተደመጠው ከዶክተር ያዕቆብ ሀይለማሪያም ከአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሲሆን ይህ መልዕክት ምርጫን እንደ የትግል ስልት ይልቁንም የምናገኛቸውን አንድ አንድ ውጤቶችን የምንቋጥርበት(Anchoring intermediate results) መሆኑንም የዘነጋ አስተያየት ይመሰለኛል፡፡
ዶክተር ያዕቆብ በፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በንቃት እየተሳተፉ እንደሆነ ሁላችንም የምንረዳው ነው፡፡ በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ ግን በይፋ የሉበትም ስለዚህ ምርጫን በሚመለከት በግንባር ቀደም ተወዳዳሪነት አንጠብቃቸውም በግል ዕጩ ካልሆኑ በስተቀር፡፡ ስለዚህ አሁን የሰጡት አስተያየት በቀጥታ የሚጠቅመው ኢህአዴግን ሲሆን ጉዳቱ ደግም በምርጫ ፖለቲካ ዝግጅት ለሚያደርጉ ፓርቲዎች ላይ ነው፡፡  ይህ አስተያየት ደግሞ በቅርቡ አንድነት ከመኢህአድ ጋር ውህደት እንዲፈፅም ሲያደርጉት ከነበረው ጥረት ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ ውህደቱ የሚያስፈልገው ከእርቅ በኋላ ለሚደረገው ምርጫ ነው ካለሉን በስተቀር፡፡ እንደ ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማሪያም ያለ ተደማጭነት ላለው የአደባባይ ሰው እንዲህ ዓይነቱ አስተያየት ቀላል የማይባል ሰው ምርጫ ዋጋ የለውም ብሎ ከመራጭነት፣ ከታዛቢነት ከፍ ሲልም ከዕጩ ተወዳዳሪነት እራሱን እንዲያርቅ ያበረታታል፡፡ ይህ አሰተያየት ኢህአዴግን ካልሆነ ማንን ይጠቅማል?
ኢህአዴግ የዶክተር ያዕቆብን ምክር የሚሰማ ቢሆን ኖሮ አስተያየቱ ተቀባይነት ሊኖረው ይችል ነበር፡፡ ኢህአዴግ እንዲህ ዓይነት ስልጣኑን በጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚያስገባ አሰተያየት እንዴት ሊቀበል እንደሚችል ማሰብ በራሱ ከባድ ነው፡፡ ዶክተር ያዕቆብ ይህን እርቅ ይቅደም አስተያየት ሲሰነዝሩ መቼም በዚህ የእርቅ ማዕድ ኢህአዴግ አዳዲስ አባላት አፍርቶ ዕጩ እንዲያፈራ  ሳይሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሊደግፉ የሚችሉ ሰዎች ከፍርሃታቸው ተላቀው ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲጠናከሩ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ኢህአዴግ የሚፈልገው ቢሆን ኖሮ የእርቅ ማዕድ ሳይሆን የሚያስፈልገው በ1997 እንደተደረገው እንከን የለሽ ምርጫ ማድረግ አለብን ብሎ ማወጅ ለዚህም ምቹ ሁኔታዎችን በኢህአዴግ በኩል ሳይሆን በመነግሰት መስመር እንዲከፈት ማድረግ ነው፡፡ የ1997 ምርጫ ሁሉም እንደሚያስታውሰው ከምርጫ በኋላ እንከን በእንከን ሆኖ ተጠናቆዋል፡፡ ያለብንን የሰላማዊ ትግል ሠራዊት ዝቅተኝነትና ዝግጁነት ተጠቅሞ ኢህአዴግ የንፁሃን ዜጎች ህይወት እዳ ወሰዶ አፍኖታል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሰለምርጫ ስናሰብ ግን ከምርጫ 97 የምንማረው የመኖሩን ያህል በምርጫ 97 መተከዝ አለብን ብዬ አላምንም፡፡ ምርጫ 97 ታሪካችን እንጂ ምርጫ ድሮ ቀረ እያልን የምናላዝንበት መሆን የለበትም፡፡
እንደ እኔ አምነት የዶክተር ያዕቆብን ሃሳብ ለመቀበል ኢህአድግ ከተዘጋጀ ኢህዴግ መንኩሶዋል ማለት ነው፡፡ እንደ ጳውሎስ ቀደም ሲል የሰራውን ግፍና መከራ ትቶ ወደ መልካምነትና ቅዱስነት ተሸጋግሯል ማለት ነው፡፡ አንባገነን መንግሰታት ባህሪ አይቀይሩም ማለት ባይሆንም ኢህአዴግ በዚህ ደረጃ እንዲያድግ እኛም ተገቢውን ግፊት አላደረግንም የሚል እምነት ስላለኝ ነው፡፡ እሰከ አሁን የሄድንበት መንገድ የተለመደ እና ኢህአዴግ ደግሞ እንዴት እንደይሰሩ ማድረግ እንዳለበት በደንብ ያውቃል፡፡ ሰለዚህ እኛም የተለየ መንገድ ማሰብ ይኖርብና፡፡
ምርጫው ይራዘም የሚል አሰተያየት የቀረበው ከዶክትር ያዕቆብ ብቻ ሳይሆን የፋክቱ ቋሚ አምደኛ ተመስገን ደሳለኝም አቅርቦታል፡፡ የተመስገን ምርጫው ይራዘም ጥያቄ ተግባራዊ የሚሆነው በመስከረም ቢሆን የመረጠው የህዳሴው አብዮት የሚመጣ ከሆነ ነው፡፡ የተመስገንን የህዳሴው አብዮት ማስፈፀሚያ ስትራቴጂ ጥሪ ተቀብለው በተለይ ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አብዮቱን የመሩት ከሆነ የአብዮቱ መሪዎች የምርጫውን ቀን የሚወስኑት ሲሆን፤ መቼም ይህ ከሆነ በእቅድ የተመራ አብዮት ተብሎ በታሪክ የሚመዘገብ ይሆናል፡፡ ይህ ገና ለገና በቢሆን የቀረበ የህዳሴ አብዮት ጥሪ ተግባራዊ ካልሆነ ከዚህ አሰተያየት የሚጠቀመው አሁንም ኢህአዴግ እንጂ ለምርጫ ዝግጅት የሚያደርጉ ፓርቲዎችን ሊሆኑ አይችሉም፡፡ መቼም ተመስገን ደሳለኝ በህዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ሰናሰብ የዚህ አሰተያየት ጉዳት ከፍ ያለ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡
ንጉሡ ቢወርዱ ማን ይተካቸዋል፣ ደርግ ቢወድቅ ማን ይተካል ሲባል እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ከኢህአዴግ በኋላ ማን ሀገር ሊመራ ይችላል የሚል መሞገቻ ይዞ በሸገር ሬዲዮ ዋዘኛ በሚል አዲስ የተጀመረ ፕሮግራም ላይ የተመስገን ደሳለኝን ህዳሴ አብዮት አሰተሳሰብ ሲሞግት ሰምተናል፡፡ ጋዜጠኛው የተመስገንን የህዳሴ አብዮቱን መሞገቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህችን ትልቅ ሀገር ከኢህአዴግ ሌላ ማን ይመራታል? ብሎ አማረጭ የሌለን አድርጎ ማቅረብ ጤነኛ ሃሳብ አድርጌ ለመውሰድ እቸገራለሁ፡፡ ይህን ፕሮግራም የሰማሁት በዛሚ ወይም በፋና ቢሆን አይገርመኝም፤ በሸገር ሲሆን ግን ብዙ ዜጎችን ያሳሰታል ብዬ ሰለምሰጋ ነው፡፡ ሀገራችን ትልቅ ነች ሰንል በቆዳ ሰፋት ብቻ አይደለም ባላት ምርጥ የሰው ሀይል ጭምር ነው፡፡ እነዚህ ዜጎች ለምን ከኢህአዴግ ጎን አይታዩም? ለሚለው ጥያቄ መልሱ ኢህአዴግ የምርጦችና የምጡቃን ስብስብ ቤት ስላልሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ሊመሩ የሚችሉትን ሰዎች በኢህአዴግ አፈና ምክንያት በፊት ለፊት ከተቃዋሚ ጋር ወይም ከኢህአዴግ ጋር ስላላየናቸው የሉም ማለት ግን ትልቅ ሰህተት ነው፡፡
በእኔ እምነት በዚህ ጊዜ የሚያስፈልገው ለምርጭ ዝግጅት ህዝቡ እንዲነቃቃ ማድረግ ለታዛቢዎች አሰፈላጊውን የሞራል ትጥቅ ማስጨበጥ ዕጩዎች በግል ከሚያደርጉት ዝግጅት በተጨማሪ የሚጎድላቸውን በሞራልም በፋይናንስም ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ በተለይ ዶክተር ያዕቆብ እና ተመስገን በኢትዮጵያችን ለውጥ እንዲመጣ ያላቸውን ጉጉት ሰለምረዳ፤ የሚፈልጉት ለውጥ ግን ደረጃ በደረጃም ቢሆንም ሊመጣ እንዲችል  ተጨባጭ ድጋፍ ሊያደርጉ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ በዋነኝነት እነዚህ የአደባባይ ሰዎች ምርጫ ይራዘም ከሚለው አቅጣጫ ወጥተው በቁርጠኝነት ምርጫውን በግላቸው መደገፍ እና አድናቂዎቻቸውም በምርጫ እንዲሳተፉ ግፊት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያገባናል ከሚሉ የአደባባይ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የሚጠበቀው፤
·         ደጋፊዎቻቸው እና አድናቂቆቻቸው በምርጫው ለመሳተፍ በመራጭነት፣ በታዛቢነት ብሎ በዕጩነት እንዲነሳሱ ማበረታታ እና
·         ደጋፊዎቻ   የሚችሉትን ድጋፍ ለማድረግ እንዲችሉ ለማበረታት ደግሞ እራሳቸውን በአራሃያነት ማቅረብ
ነው፡፡ ይህን ካደረግን በሁለት ሺ ሰባት በሚደረግ ምርጫ ቀላል የማይባሉ የምርጫ ክልሎችን ነፃ ማውጣት እንዳለብን ማመን የግድ ይላል፡፡ አማራጭ የለም ብለው ወደኋላ የሚሉትን ለመሳብ ፓርቲዎች የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ባለፈው የምርጫ ፖለቲካን አስመልክቶ የፃፍኩትን አሰተያየት አንብቦ አንድ ወዳጄ አማራጭ ሳይኖር ለምርጫ መመዝገብ ምን ዋጋ አለው ብሎ ጠየቀኝ፡፡ የእኔም መልስ “በእኔ በኩል ኣማራጭ የለም በሚለው አልሰማማም፡፡ በቂ አማራጭ አለመኖሩን ግን መካድ አይቻለም ነገር ግን የምርጫ ካርድ የወሰደ ሰው አማራጭ የለም ብሎ ካመነ የምርጫ ካርዱን ይዞ ያለመምረጥ መብት አለው፡፡” የሚል ነበር፡፡ ይህን ማድረግ ትልቅ የፖለቲካ መልዕክት ያስተላልፋል፤ በገዢው ፓርቲ አፈና ምክንያት አማራጭ አጥተናል ብለን ካመንን የምርጫ ካርዳችን ላይ በምርጫ ያለመሳተፋችንን የሚገልፅ ምልክት አድርገን ምርጫ ቦርድ ጊቢ ወይም ፓርላማ ጊቢ ውስጥ በመወርወር ተቃውሞ ብናደርግ ተቃውሟችን በመረጃ የተደገፈ ለማድረግ ይረዳናል፡፡ ባለፈው ለማሳየት እንደሞከርኩት በምርጫ የተሳተፈ ህዝብ ድምፃችን ይከበር ብሎ መንግሰትን ሊያስገድድ ይችላል፡፡ ያልመረጠ ግን ምን ድምፅ አለው? ምንስ ሞራል ይኖረዋል ድምፃችን ይከበር ለማለት? ድምፃችን ይከበር ለማለት በምርጫ መሳተፍ የግድ ይላል፡፡ ሁላችንም የምርጫውን ግንባር ለመደገፍ እንትጋ ከአደራ ጋር የማስተላልፈው መልእክት ነው፡፡

ቸር ይግጠመን

Sunday, June 22, 2014

የ2007 የመንግሰት በጀት ሚስጥር …….



የኢትዮጵያ በጀት በደንብ አድርጎ ለመረመረው ሀገሪቱ ያለችበትን ፖለቲካ ሁኔታ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህም ማለት በበጀቱ ውስጥ የቻይና፣  ምዕራባዊያን ሀገሮች እንዲሁም የምዕራብ ሀገሮች ይዞታ የሚባሉት አለም አቀፍ ባንኮች እጅ በግልፅ የሚታይ ነው፡፡ እንደምታውቁት መንግሰት ለ2007 ዓመተ ምህረት ያቀረበው በጀት ብር 178.6 ቢሊዮን ነው፡፡ ዘጠኝ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር አካባቢ ማለት ነው፡፡ መደበኛው ወጪ እና የክልሎች ድጋፍ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ የሚሸፈን ሲሆን ዋና ዋና የካፒታል በጀት ደግሞ ከመደበኛ ወጪ እና ክልሎች ድጋፍ ከሚተርፈው አነሰተኛ የሀገር ውስጥ ገቢ እና ለበጀት ጉድለት ለመሸፈን ከታሰበው ከሀገር ውስጥ ባንኮች ብድር ይሸፈናል ተብሎ የሚጠበቅ ነው፡፡ ከአጠቃላይ በጀቱ 19.2 በመቶ ከእርዳታና ብድር ይሸፈናል በዝርዝር ሲታይ ግን የመደበኛ በጀቱ 21.8 ከመቶ፣ የካፒታል በጀቱ ደግሞ 36.5 ከመቶ የሚሸፈነው ከብድርና እርዳታ ነው፡፡
ስንት ሰው እንደሚያስታውስ ባላውቅም የቀድሞ አዲስ ጉዳይ ጋዜጣ (ሁሌም ጋዜጣ ሳስብ የሚናፍቀኝ) በአንድ ወቅት የቀረበን በጀት ይህ በጀት ኢትዮጵያዊ በጀት ነው ወይ? የሚል ጥያቄ አንሰቶ ነበር፡፡ የበጀትን ዜግነት የጠየቀበት ገፊ ምክንያት በዚያን ሰሞን መወያያ፤ በአሁኑ ጊዜ ጠርናፊ ህግ የሆነውን የሲቪል ማህበራት ህግ ነበር፡፡ ይህ አፋኝ ህግ ማነኛውም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀስ ሰቪል ማህበር በጀቱ ከአስር በመቶ በላይ ከውጭ ከሆነ ኢትዮጵያዊ አይደለም ነው የሚለው፡፡ አሁን በሀገራችን የሚንቀሳቀሱት ብዙዎች መንግሰታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተመዘገቡት በኢትዮጵያዊነት ሳይሆን “ረዚደንት” በሚል ቅፅል ነው፡፡ አዲስ ጉዳይ ጋዜጣ ይህን በጠየቀበት ወቅት የሀገሪቱ በጀት ከ40 በመቶ በላይ ከውጭ እርዳታ ሰለነበር ይህ መንግሰት ይህን ያህል ከውጭ የሚያገኝ ከሆነ ኢትዮጵያዊ አይደለም የሚል መከራከሪያ ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡ ይህን ሰፋ አድርገው በመተርጎም አንድ አንድ ሰዎች የገቢ ምንጭ ዜግነት የሚወስን ከሆነ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ከውጭ ከሚኖሩ ዘመዶቻቸው በሚላክላቸው ገንዘብ የሚተዳደሩ ስለሆነ ዜግነታቸው ኢትዮጵያዊ መሆን የለበትም ብለው ነበር፡፡ ስላቅ መሆኑ ነው፡፡ ያለበለዚያ ደግሞ የሚልኩላቸው ዘመዶቻቸው ዜግነት ያልቀየሩ በመኖሪያ ፍቃድ (ረዚደንት) የሚኖሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡
የሰዎችን ወይም የድርጅቶችን ዜግነት ኢትዮጵያዊ ወይም የውጭ ለማድረግ የገቢ ምንጭ መስፈርት መሆን የለበትም የሚለውን መከራከሪያ መንግሰት በዋዛ ያለፈው እንዳይመስላችሁ፡፡ መፍትሔ ብሎ የያዘው በተቻለ መጠን መንግሰት በጀቱን በመከፋፈል እና የተወሰኑት ወደ ጎን በማድረግ የብድርና የእርዳታ ገንዘቡ እንዳይታይ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ነው መንግሰት  ከፍተኛ መዋለ ንዋይ ከሚፈስባቸው የመሰረተ ልማቶች ውስጥ ዋና ዋና የሆኑትን ለምሳሌ እነ ቴሌ፣ መብራት ሀይል፣ ባቡር፣ የመሳሰሉት በሪፖርት ውሰጥ በስፋት እንደሰኬት ተካተው በበጀት ውስጥ ግን አይታዩም፡፡ ሉሎች ፋብሪካዎች ለምሳሌ ስኳር ፋብሪካ፣ ማዳበሪያ ፋብሪካ የመሳሰሉት ትልልቅ የመንግሰት ፕሮጀክቶቸ በበጀት ውስጥ የሉም፡፡ እነዚህ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ የፈሰሰላቸው የመንግሰት ኢንቨስትመንቶች ከበጀት ውሰጥ እንዲወጡ የተደረጉት ደግሞ ብዙዎች በብድር የሚሰሩ ናቸው፡፡ የእነዚህ ፕሮጀክቶች የብድር ሂሣብ በበጀት ውስጥ ቢደመር የመንግሰትን በጀት ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ ላይሆን ነው ማለት ነው፡፡ ለነገሩ በሲቪል ማህበራት ትርጉም እነዚህ ሁሉ ተቀንሰው አሁን የቀረበው የመነግሰት በጀት ኢትዮጵያዊ በሚያደርገው ደረጃ ላይ አይለም፡፡ ምክንያቱም ከአጠቃላይ በጀቱ 19.2 በመቶ ከውጭ ብድርና እርዳታ የሚገኝ ስለሆነ ማለት ነው፡፡
መንግስት በበጀት ውስጥ ያካተታቸው በእርዳታና ብድር የተገኙ አብዘኞቹ የካፒታል ወጪዎች ለኤኮኖሚ ሴክተር መንገድ፣ ግብርና እና ውሃ ሲሆን፤  እርዳታው ደግሞ ለጤናው ሴክተር የተመደበ ነው፡፡ የእነዚህ ገንዘቦች ዋናኛ ምንጮች ደግሞ የኒዎ ሊብራል አራማጆች የሚባሉት መንግሰታት እና የእነዚሁ መንግሰታት ይዞታ ናቸው የሚባሉት ባንኮች የሰጧቸው ብድሮች ናቸው፡፡ እነዚህ መንግሰታት እና በቁጥጥራቸው ስር ያሉት የፋይናንስ ተቋማት ኢትዮጵያዊያን ጤናቸው እንዲጠበቅ የተሻለ መንገድ እንዲኖረን፣ ምርታማ ግብርና እንዲሁም ንፁህ ውሃ እንዲኖረን ዕርዳታና ብድር እየሰጡን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ብጥብጥ እንዲነሳ የቀለም አብዮት ይደግፋሉ ብሎ ስጋት ውስጥ መውደቅ አይቃረንም ወይ? ይህ በእውነት የአብዮታዊ ዲሚክራሲ ወይም የልማታዊ መንግሰት ቅዠት ይመስለኛል፡፡
በጣም የሚያስገርመው ደግሞ በዋነኝነት ከፍተኛ እርዳታ የሚሰጡን መንግሰታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በኩል አድርገው በቀለም አብዮት ሊያጠፉን ነው የሚባሉት የኒዎ ሊብራል አራማጅ ተብለው የተፈረጁት ሀገሮች መንግሰታት ናቸው፡፡ ከነዚህ ውሰጥ ቻይና እንደ መንግስት የምትሰጠን እርዳታ በሀገር ውስጥ ከውጭ ሀገር ዜጎች ምዝገባና የስራ ፈቃደ ከምናገኛው ያንሳል፡፡ ከሌሎቹ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ ከአንድ መቶኛ ያነሰ ነው፡፡ ቻይና ሀገራችን በበጀት ውስጥ ከተካተተው ብድር ከ59 በመቶ በላይ ሰጥታናለች፡፡ ይህ ቻይና የሰጠችን ብድር ብዙ ስለሆነ ሳይሆን መንግሰታት ለኢትዮጵያ የሰጡት ብድር እጅግ ዝቅተኛ ከመሆኑ የመጣ ከፍተኛ የመቶኛ ድርሻ ነው፡፡ ቻይና በጀት ውስጥ ባልገባው ብድር ከፍተኛ አበዳሪያችን ነች፡፡ የቻይና ብድር በዋነኝነት በበጀት ውስጥ ባለተካተቱት ከፍተኛ የመንግሰት የመሰረተ ልማቶች እና የኤኮኖሚ ሴክተሮች ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ ከበጀት እንዲወጣ የተደረገውን የቴሌን ማስፋፊያ ብቻ ብንወሰድ ወደ 32 ቢሊዮን ብር ወይም 1.6 ቢሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር በ2007 በጀት ተብሎ የተያዘውን 18 ከመቶ ይሆናል፡፡ ይህ ገንዘብ በጀት ውስጥ ቢታይ እና የመንግሰትን የዜግነት መስፈርት ብንጠቀም መንግሰት ኢትዮጵያዊ ነው ለማለት ይቻላል ወይ? በጀት የመንግሰትን አቅም የሚያሳይ መለኪያ ነው በሚለው ልማዳዊ መለኪያ ለመጠቀም ለሚፈልግ ለቀጣይ ዓመት የቀረበው በጀት ትክክለኛውን የመንግስት ጡንቻ የሚያሳይ ነው ብለን ለመውሰድ እንቸገራለን፡፡
የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒሰትሩ አቶ ሶፊያ አህመድ በዚህ ጉዳይ በተደጋጋሚ በግንባር ቀደምነት የሚያነሱት የኢትዮጵያ አየር መንገድን ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዕዝ ኢኮኖሚ በሚባለው በደርግም ጊዜ ቢሆን ሪፖርቱን በይፋ ያቀርባል አቶ ሶፊያ ግን ይህን እንዲያደርግ ያለበትን ዓለማ አቀፋዊ ጫና የምንረዳ አይመስላቸውም፡፡ ያለበለዚያ ቦይንግ መግዣ ገንዘብ ሊገኝ እንደማይችል ግልፅ ነው፡፡ አሁን እኛ የግልፅነት ችግር አለባቸው እያልን ያለነው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪን የሚባለው አስማተኛ ድርጅት የሚሰራው ሰራ የሚያገኘው ገቢና ወጪው በግልፅ አይታወቅም ነው፡፡ እጅግ ብዙ ሀብት ፈሶበትም የሚያመጣው ትርፍ ተመጣጣኝ አይደለም እያልን ነው፡፡ በቅርቡ ከመንግሰት ድርጅቶች ይገዛው የነበረውን የወዳደቁ ብረቶች ግዢ እንዲያቆም መታዘዙ ይታወቃል፡፡ ለምን? የፀረ ሙስና እና ሰነምግባር ኮሚሸን እነዚህ ተቋማት ለምዝበራ የተጋለጡ እንደሆነ ሪፖርት አቅርቧል፡፡ ለነገሩ ይህ ድርጅት ተጠሪነቱም ለመንግሰት የልማት ድርጅት አይደለም፡፡ ሌሎቹም ኮርፖሬሽኖች ለምሳሌ የሰኳር ኮርፖሬሽን ስር ነው የሚባለው ተንዳሆ የሰኳር ፕሮጀክት ያለበትን ጉድ የማያውቅ ያለ አይመስለኝም፡፡
በጀት ውስጥ የገባውን የመከላከያ በጀት ስንመለከት ደግሞ በየሳምንቱ እሁድ በሚያቀርበው የቴሌቪዥን ፕሮግራ በነፃ ገበያ ሰርዓት እየተወዳደረ መነገዱን ቢነግረንም፡፡ በግልፅና በሰውር የሚሰራቸው የገቢ ማስገኛ ገንዘቦች እንዳሉት እየታወቀ ከውስጥ ገቢ የሚባል አንድም የገቢ ርዕስ በጀቱ ላይ አይታይም፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ የመከላከያ በጀት ይህ ብቻ ነው ብሎ ለመውሰድ አይቻልም፡፡ የመንግሰት ጡንቻ በመከላከያ በኩል ከዚህ እንደሚበልጥ ለማወቅ ደግሞ ልዩ እውቀት አይጠይቅም፡፡ ለዚህ ነው የመንግሰትን ትክክለኛ ቁመና የሚያሳይ በጀት አይደለም የምንለው፡፡
እነዚህ እርዳታ እየሰጡን ብድር የማይሰጡን መንግሰታት ምክንያታቸው ምንድነው? ብሎ መጠየቅም ተገቢ ይመሰለኛል፡፡ በኒዮ ሊብራል አሰተሳሰብ ተፈርጀው ሀገራችን ላይ የቀለም አብዮት ሊያመጡ ያሴራሉ የሚባሉት ሀገራት በዋና ዋና የንግድ እና ኢንቨስትምነት ውስጥ እጃቸውን ለማስገባት ወደኋላ ያሉት ለምንድነው? በተቃራኒው ደግሞ ቻይና በእነዚህ ወሳኝ የኤኮኖሚና የንግድ ኢንቨስትመንት ውስጥ እጇን በሰፊው የምትዘረጋው ለምንድነው? ብሎ መጠየቅ እና መልስ መሻት ግድ ይላል፡፡
በእኔ እምነት የምዕራባዊያን መንግሰታት በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የኢኮኖሚ መስኮች ውስጥ ለመሳተፍ ውሳኔ የሚሰጡት መንግሰታት ሳይሆኑ በየሀገሮቻቸው ያሉት የግል ባለሀብቶች ናቸው፡፡ የመንግሰታት ድርሻ ለባለሀብቶች ትክክለኛ መረጃ እንዲደርሳቸው ማድረግ እና ተገቢውን ከለላ መስጠት ነው፡፡ የግል ባለሀብቶች ደግሞ መረጃ የሚያገኙት ከኢቲቪ አይደለም፡፡ በተለያየ መልኩ በሀገራችን ያለውን ሁኔታ አብጠርጥረው ያውቁታል፡፡ እንደ ምሳሌ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተከሰተው ዓይነት ብሔርን መሰረት ያደረገ ብጥብጥ ከፍተኛ ትርጉም አለው፡፡ አንድ አንዶች እንደሚያስቡት በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ያሉ ከተሞች የተቀናጀ ማሰትር ፕላን ዝግጅት ነው ብለው አይወስዱትም፡፡ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችና የሰጋት ደረጃ የሚተነትኑ ድርጅቶች የሚያወጧቸው ሪፖርቶች ትርጉማቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ በሀገሪቱ ውሰጥ ያለው የዲሞክራሲያዊ ሰርዓት በተለይም በየምርጫ ወቀት የሚፈጠሩ ሰጋቶች፤ መንግሰት የሚያወጣቸው አዋጆች፣ ደንቦች እና መመሪያዎች ተገማችነት፤ በአጠቃላይ ለኢንቨስትመንት ያለው ምቹ ሁኔታ ወሳኝ ግብዓቶች ናቸው፡፡ ዝም ብሎ በኢቲቪ የሚለፈፍ የገፅታ ግንባታ ፕሮፓጋንዳ ተጠቅመው የኢንቨስትምነት ውሳኔ አይሰጡም፡፡
በተቃራኒው የቻይና መንግሰት በከፍተኛ ደረጃ አፍሪካን ለመቆጣጠር ባለው ፍላጎት መነሻ እንዲሁም ውሳኔ የሚሰጡት የግል ባለሀብቶች ሳይሆን የቻይና መንግሰት በመሆኑ ውሳኔዎች በአብዛኛው ኤኮኖሚያዊ አዋጭነት ብቻ ሳይሆኑ የፖለቲካ ጭምር ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቻይና በዓለም ላይ ከፍተኛ ብድር ሰጪ ሀገር ነች፡፡ ለአማሪካ ጭምር፡፡ በቻይና የግል ሴክተሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢንቨስት ለማድረግ ገና አልደረሱም፡፡ ቻይና እንደ ሀገር ያላትን ከፍተኛ ቁጠባ በዓለም ላይ ኢንቨስት ለማድረግ እየተጠቀመችበት ነው፡፡ ቻይና በሙሉ በሚባል ደረጃ የምትሰጠንን ብድር የሚጠቀሙበት የቻይና ኩባንያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ያለውን ስጋት በሚያካክስ ደረጃ ትርፋቸውን በአጭር ጊዜ ለማግኘት ይገባሉ በአሁኑ ሰዓት ቴሌን የወሰዱት ሁለት የቻይና የመንግስ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ በተለያየ ስም የሚሰሩ፡፡ ቻይና የምታስገርመው እነዚህ የመንግሰት ኩባንያዎች ጉቦ የመሰጠት ጭምር አቅም አላቸው፡፡
እንደ ማጠቃለያ ለኢትዮጵያ የተበጀተው በጀት ብር 178.6 ቢሊዮን በጀት እንደ ሀገር ሲታይ አጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያ 90 ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርባት ከመሆኗ አንፃር እና በቅርቡ ደግሞ ዓመታዊ የነብስ ወከፍ ገቢያችን ብር 11 ሺ (550 የአሜሪካ ዶላር) ደርሶዋል ከተባልን ይህ በጀት ከእያንዳንዱ ሰው በወር የገቢውን 1.5 ከመቶ መዋጮ ሊሸፍነው የሚችለው ነው፡፡
ቸር ይግጠመን

Sunday, June 15, 2014

ለጅቡቲ ውሃ በነፃ ለምን? የባህር በር ሸቀጥ ነው ወይ?



የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሌጋሲ እናስቀጥላለን ያሉ ሰዎች …. የሰውዬውን ሌጋሲ እየሸረሸሩት እንደሆነ ያወቁ አይመስለኝም፡፡ አውቀውት የራሳቸውን ሌጋሲ ለማኖር ከሆነም እሰዬው የሚያሰኝ ነው፡፡ ሰሞኑ ለጅቡቲ መንግሰት ውሃ አቅርቦት በሚመለከት አንድ አዋጅ ምክር ቤት መቅረቡን ተከትሎ ትንሽ ጫጫታ መነሳቱ የሚታወስ ነው፡፡ የዚህ ነገር ደግሞ አንጓ ያለው ደግሞ የመንግሰት ተጠሪ ሚኒሰትሯ ወ/ሮ ሮማን ገ/ስላሴ ጥቅሙ ፖለቲካ ነው ያሉት ላይ ነው፡፡ ከምክር ቤት አባላት ኢትዮጵያ ምን ጥቅም ታገኛለች? በሚል ለቀረበ ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ ጥቅሙ ፖለቲካ ነው የሚል ነበር፡፡ ከዓለም የባህር በር/ወደብ ከሌላቸው ሀገሮች በህዝብ ብዛት አንደኛ የሆነችውን ኢትዮጵያ የባህር በር እንዳይኖራት የተደረገው ደባ እየዋለ እያደር ብዙ ዕዳ እንደሚያስከፍለን ምልክቱ እየታየ ነው፡፡
በእኔ እምነት ህወሃት/የትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅት ከሻቢያ ጋር በመተባበር በዕቅድ ይዞት ነበር ለሚባለው የትግራይ-ትግረ መንግሰት ምስረታ አንፃር ሲታይ ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል የባህር በር እንዳይኖረው ማድረግና በሚመሰርቱት የትግራይ-ትግረ መንግሰት ጥገኛ ማድረግ ተገቢ ሊመስል ይችላል፡፡ በ1980 መጀመሪያ ኢህአዴግ የሚባል ግንባር ሲመሰርቱ ግን የአማራው ክንፍ ኢህድን/ብአዴን በመጨረሻም ኦህዴድ እና ደኢህዴን የተቀላቀለው ግንባር ለዚህ እቅድ ገብሮ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ በመጀመሪያ በዚህ ደረጃ ማን ያወያያቸዋል ካልተባለ በስተቀር፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ቢሆን ከኢሳያስ ጋር ያጣላቸው የሚመስለኝ ብዙ ሰው እንደሚለው በኢትዮ-ኤርትራ ቅጥ ያጣ ግንኙነት የትግል ጓዶቻቸው ተበሳጭተው ባደረጉባቸው ግፊት ብቻ ሳይሆን የሚኒሊክ የሚሏት ኢትዮጵያ ቤተመንግሰት ውስጥ ቁጭ ብሎ ከአሰመራ ትዕዛዝ ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ጭምር ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ በሁሉም መስፈርት ትልቅ ሀገር ነች፡፡ የሚያሳዝነው ግን ይህችን ትልቅ ሀገር ለመምራት እድል አግኝተው ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት እድል ያለመፍጠር፤ እድል ሲገኝም ለመጠቀም ፈቃደኛ ያለመሆናቸው ነው፡፡ አሰበውት የነበረ ነገር ካለም ይዘውት ሄደዋል፡፡
አሁን ባለው አለማዊ ሁኔታ እንዲሁም አሁን በምድር ላይ ባለው ተጨባጭ እውነት ትግራይ- ትግረ ቅዥት ነው፡፡ ሊሳካ የሚችልበት ሁኔታ የለም፡፡ ለምን? እያልን ደጋግመን መጠየቁን እናቁምና በዚህ ሃሳብ መነሻ ግን ኢትዮጵያን የምታክል ትልቅ ሀገር በተለይ ትግራይን በቅርብ ርቀት የባህር በር እንዳይኖር ተግቶ መስረት ምን ዓይነት ልክፍት እንደሆነ የሚያሰረዳን እንፈልጋለን፡፡ ባህር እንዲኖረን ጥረት እናድርግ ሲባል ጦር ናፋቂዎች እንደሚሉን እምነቴ ነው፡፡ ይህ መልስ ግን ካፈርኩ አይመልሰኝ በሚል፣ጥፋትን መሸፈኛ ነው፡፡ አሁን ያለው ጥፋት ጥፋትን በጥፋት ማረሙ ላይ፡፡
ይህ ግትር አቋም እንደ አፍ ወለምታ ብቻ ሳይሆን ቋሚ የገዢው ፓርቲ መርዕ አድርገው ወደብ ሸቀጥ ነው ያሉን ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር በህይወት እያሉ ነው ወደብ ሽቀጥ ብቻ እንዳልሆነ ምልክቱን ያዩት፡፡ በመስከረም 2004 ህይወታቸው ከማለፉ በፊት ከጅቡቲ ጋር የነፃ (እንዲሁም ከፍለን) ውሃ ለማቅረብ የተስማሙት፡፡ ሁለት ዓመት አስቆጥሮ ደግሞ ይህ ሰምምነት ህግ ይሆን ዘንድ ለምክር ቤት ቀርቦዋል፡፡
ዛሬ ጅቡቲ በምትባል አንዲት ትንሽ ሀገር በፀባይ ለመያዝ ውሃ በነፃ ለዚያውም ከነሙሉ የደህንነት ጥበቃው ጋር መስጠት ጥቅሙ ወደብ ሽቀጥ ነው ብለው ያሰተማሩን ትምህርት ትክክል ያለመሆኑን ከማረጋገጥ በላይ ነው፡፡ ወደ ዘለገ ያለ የፖለቲካ ጥቅም አለው ለሀገር ደህንነትም ወሳኝ ነው፡፡ ዛሬ የዚህ የተሳሳተ ወደብ ሸቀጥ ነው ፍልስፍና ለወደብ ኪራይ ከምንከፍለው ገንዘብ በተጨማሪ በነፃ ውሃ ልናቀርብ መሆኑ ነው፡፡ በእኔ እምነት በቅርባችን ያለችው መሪዋ አማርኛ አቀላጥፈው የሚናገሩት ጅቡቲዎች ውሃ ቢያገኙ ደስ ይለኛል፡፡ የሃረሪ ክልል ከድሬዳዋ፣ አዲስ አበባ ከኦሮሚያ ክልል ውሃ እንደሚያገኘት ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ችሮታ ደግሞ ሁሌ ቤት ሞልቶ ሲተርፍ ከሆነ ስጦታው ብዙም ላያስገርም ይችላል፡፡ ያለን በማካፈል ስሜት ሲሆን ደስ ይላል፡፡ እነካ በንካም ትክክል አይደለም፡፡
የሚቆጨው እና የሚያንገበግበው ግን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ወጪ አድርጋበት የገነባቸውን አሰብ የግመል ውሃ መጠጫ እንዲሆን ፈቅደውና ተስማምተው፤ እንደ ሸቀጥ እንገዛዋለን ብለው ያሰቡትን የጅቡቲ ወደብ ከፈተኛ ዋጋ እያሰከፈለ ቢሆንም አሁንም በዓይነት ደግሞ የምንከፍልበት ፖለቲካው ሁኔታ መፈጠሩ ነው፡፡ ለጅቡቲ ከጫት እስከ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ከመብራት እሰከ መጠጥ ውሃ የማቅረብ ፍቅራችን ጥቅሙ ፖለቲካ መሆኑ መታመኑ ትልቅ ነገር ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ወደብ ሸቀጥ ነው ብለውን ነበር እኮ፡፡ ለባቡር ግንባታ የሚያስፈልገውን ብድር ዋስትና የሰጠች ሀገር አሁን ደግሞ የመጠጥ ውሃ ቢያገኙ ምን ይላቸዋል በሚል የህግ ረቂቅ ቀርቧል፡፡ በነገራችን ላይ በመሃል ሀገር የጅቡቲ መንግሰት የእርሻ መሬት እንዳለው መዘንጋት የለብንም፡፡
ብዙ ሰው ያልተረዳው ነገር ኢትዮጵያ ነዳጅ ብታመርትና በጅቡቲ በኩል ለመላክ ከወሰነች ነዳጅ በነፃ የምንሰጥበት ግዴታ ውስጥ ልንገባ እንችላለን፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታሰብ ማነኛውም ወደ ወጭ የሚላክ ምርትን ዋጋው እጅግ በጣም ውድ ነው፡፡ ዋጋ ውድ እንዲሆን ያደረገው ደግሞ የሎጀስቲክ ስርዓቱ ነው እያሉ ሊያታልሉን ይሞክራሉ እንጂ ከሎጀስቲክ ስርዓቱ ውስጥ ዋነኛው የባህር በር የሌለን መሆኑ ነው፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ለመወዳደር ዋጋ ትልቁ መስፈርት ነው፡፡ የባህር በር ናፍቆታችን መቼም ቢሆን በደረቅ ወደብ ምስረታ እንደማይሳካ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ የግመል መጠጫ እንዲሆን የፈረድንበትን የአሰብ በር ኢትዮጵያዊያን በአማራጭነት የምንጠቀምበት ሁኔታ አጀንዳ መሆን አለበት፡፡ እሰከዚያ ድረስ ከጅቡቲ ጋር ያለንን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ከዚህም በላይ አጠናክረን መቀጠል ምርጫ አይደለም ግዴታ ነው፡፡
ወደብ ተራ ሽቀጥ አይደለም! ወደብ ለአንድ ሀገር ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካው እድገት ወሳኝ የሆነ ግብዓት ነው፡፡ ለሀገር ደህንነትም ጭምር፡፡ ኤርትራዊያን ሞልቶ ከተረፈ የባህር በሮቻቸው አንዱን በተለይም በኢትዮጵያ ብብት ውስጥ የሚገኘውን የአሰብ ወደብ በነፃነት ሰሜት መጠቀም መቻል ይኖርብናል፡፡ ይህ ማለት በጅቡቲ ወደብ መጠቀም ይቆማል ማለት አይደለም፡፡ መተንፈሻችን ይሰፋል ማለት ነው፡፡
የነፃነት ዋጋ ስንት ነው? በሚል መፅሃፌ ላይ “ጅቡቲ ያለ ኢትዮጵያ ሀገር ነች ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ …. ኢትዮጵያ አሁን እያቀረበችው ያለውን መሰረታዊ አቅርቦት በማሻሻል የጅቡቲ ዜጎች በኢትዮጵያ የትምህርት ዕድል የሚያገኙበትን እና ድሬዳዋን እና አካባቢዋን ተመራጭ ሀገራቸው እንዲያደርጉት መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ኢትዮጵያዊያንም በጅቡቲ የኤኮኖሚ ትስስር ፈጣሪ እንዲሆኑ መንግሥት ቀጥተኛ ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል፡፡” ብዬ ነበር፡፡ በማስከተልም “በእኔ ዕይታ ኢትዮጵያ ለሁሉም ጎረቤት ሀገሮች ቅድሚያ መስጠት ይኖርባታል፡፡ በተለይ ኤርትራ፣ ጅቡቲ እና ሱማሊያ የመሰሉት የሰሜንና ምስራቅ አጎራባች ሀገሮችን በጋራ በመሆን ልናሸንፋቸው የምንችላቸው ብዙ ጉዳዮች አሉን፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ለማጠናቀቅ ግን ኢትዮጵያ በግንባር ቀደምነት ከታሪካዊ ጠላትነት ፍልስፍና ወጥታ ለታሪካዊ አጋርነት መመሥረት መሥራት ይኖርባታል፡፡ እነዚህ የሰሜንን እና ምስራቅ አጎራባች ሀገሮች ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ በመሥራት አንድ ሰጥተው ሁለት የሚያገኙበት መሆኑን ማስጨበጥ ሲሆን ለኢትዮጵያዊያን ደግሞ እነርሱ ሁለት ያገኙት ከኛ ተቀንሶ ሳይሆን አብረን በመሆናችን ከተገኘ ትርፍ መሆኑን አብረን ካልሆንን እኛም አንድ እነርሱም ሁለት አያገኙም የሚለውን ማስጨበጥ ይኖርብናል፡፡” ብዬ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ሲመዘን የሰሞኑ ለጅቡቲ የተሰጠው ውሃ እጅግ ጠቃሚ ጅምር አድርገን መውሰድ ይኖርብናል፡፡ ትግሉን አሁን ባለ ነባራዊ ሁኔታ ትክክል የሆነን ውሳኔ በመቃወም ሳይሆን ዘላቂ ጥቅም ልናረጋግጥ የምንችልበትን ነፃ የባህር በር የማግኘት መብታችንን ማረጋገጡ ላይ ይመስለኛል፡፡
ልክ ነው ጅቡቲ ትንሽ ሀገር ነች፡፡ ለኢትዮጵያ ግን የመተንፈሻ በር ነች፡፡ ዋነኛ መተንፈሻችን ጅቡቲ እንድትሆን ያደረጉን ደግሞ በትግራይ ነፃ አውጪ ስም ተደራጅተው ኢትዮጵያ የሚመሩ ያሉት ቡድኖች ናቸው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በመቶ እጥፍ ከምንበልጣት ጅቡቲ ጋር በእኩል ደረጃ ልንደራደር አንችልም፡፡ በእኩል እንዳንደራደር ሀገራችንን ባህር በር አልባ ያደረጉን የትግራይ ነፃ አውጪዎች የሚያስከፍሉን ዕዳ ወደፊትም በዚህ የሚያበቃ አይመሰለኝም፡፡ በእኔ እምነት በምስራቅ አፍሪካ በሚገኙት ሀገሮች ሁሉ ባለ ራዕይ መሪዎች በተመሳሳይ ወቅት መፈጠር ይህን ዕዳችንን ሊያሳጥረው ይችላል የሚል ቅን አመለካከት አለኝ፡፡
ቸር ይግጠመን
ግርማ ሠይፉ ማሩ



Monday, June 9, 2014

“ስለ ….. ሲባል ምርጫ ይቅር” …. ትግሉም ይቁም ወይ?



“ስለ …. ሲባል ምርጫ ይቅር” በሚል እንድ ፅሁፍ ፋክት ላይ ወጥቶ አንብቤ ለምን? ብዬ ልፅፍ አስቤ ተውኩት፡፡ ምክንያቱም በፋክት መፅሔት ላይ አምደኞች የሃሣብ ፍጭት ማድረግ የተለመደ ቢሆንም ሰሞኑን ግን የበዛ ይመስላል ከሚል ነበር፡፡ ይህ አንድ ዘርፈ ብሉ ጥሩ ጎን አለው፡፡ አንዱ አምደኞቹ ከአንድ ፋብሪካ የወጡ ሳሙና ዓይነት ያለመሆናቸውን ያሳያል፡፡ሌላው የፋክት መንፈስ ብለው ለሚቃዡትም ሆነ፤ ከመሬት ተነስተው ለሚፈርጁት የሚያስተላልፈው መልዕክት አለው፡፡ ጉዳቱ ደግሞ በሳምንት አንዴ ብቅ ለምትል መፅሄት የተወሰነ ሃሳብ በተወሰኑ ሰዎች የሚቧቀሱባት ከሆነች ደግሞ አንባቢን አማራጭ እንዳያሳጣ የሚል ፍርሃት ስለአለኝ፡፡ ይህ ሁሉ ዳር ዳርታ እኔም ተውኩት ወዳልኩት የሃሣብ ፍጭት ለመቀላቀል ሰበብ ፈልጌ ብቻ አይደለም፡፡ በቅርቡ “ሰለ … ሲባል ምርጫ ይቅርብን” በሚል በወዳጄ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ያቀረበውን ሃሳብ ባልቀበለውም በፋክት ላይ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት እናደርጋለን ብዬ እያሰብኩ ሳለ በፌስ ቡክ የውስጥ መዘገቢያ እንዲሁም በግል የሚያገኙን ሰዎች ምርጫ እንዳትወዳደሩ የሚል አንዳንዱ ምክር አንድ አንዱ ደግሞ ትዕዛዝ መሰል መልዕክቶች በብዛት ይደርሱኝ ጀምረዋል፡፡ ውሳኔው ልከም ይሁን አይሁን የምርጫ ጉዳይ የሚወሰነው በፓርቲ መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት የግል አስተያየቴን መስጠት እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህም ነው “ሰለ … ሲባል ምርጫ ይቅር” ከተባለ እኔም እንደቅድመ ሁኔታ ትግሉም ይቁም ወይ? በሚል ጥያቄ የጀመርኩት፡፡
በእኔ እምነት ምርጫ መወዳድር ያለመወዳደር የሚባል አማራጭ የለም፡፡ የአንድ ፓርቲ ስራ ምርጫ መወዳድር ነው፡፡ የሰው ልጅ ሞት እንዳለ እያወቀ ሞትን ረስቶ በህይወት እንደሚኖረው ማለት ነው፡፡ ለፓርቲዎች ያለመወዳደር የሚባል ነገር እንዳለ ረስተው ለምርጫ ውድድር መዘጋጀት ዋናው ስራቸው መሆን አለበት፡፡ ፓርቲዎች ምርጫ ላለመወዳደር የሚያበቃ ነገር እንዳይኖር ተግተው መስራትን ትተው፤ ላለመወዳድር ሰበብ የሚፈልጉ ከሆነ እንደ አሸዋ የበዛ ሰበብ ማቅረብ አይገድም፡፡ ከዚህ ሰበብ ውስጥ ግን አንድም ተሰፋ አይገኝም፡፡ ምርጫውም የሰነፍ ነው የሚሆነው እንጂ ባስቸገሪ ሁኔታ ጀግና ለመሆን ለሚታትር ታጋይ የሚመጥን አይደለም፡፡
በሀገራቸን ኢትዮጵያ ለምርጫ የእኩል መወዳደሪያ ሰፍራ ሳይኖር ምርጫ መወደዳር አስቸጋሪ እንደሆነ መረዳት ለማንም የሚገድ አይደለም፡፡ ትግል የሚባለው ነገርም የመጣው ይህ አስቸጋሪ ሁኔታ በመኖሩ ነው፡፡ በአሜሪካን ወይም በሌሎች በዲሞክራሲ በዳበሩ አገሮች የሚደረግ የፖለቲካ ተሳትፎ ትግል አይባልም፡፡ ታጋዮች ማድረግ ያለባቸው ታዲያ ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ ለማስወገድ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመክፈል የሚያስፈልገውን ማድረግ ነው፡፡ ክቡር የሆነውን የስው ልጅ ህይወት ከማጥፋትና ንብረት ከማውደም በመለስ ማለቴ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ምን ምን ሊሆኑ ይችላሉ ቢባል በምርጫ ሂደት ውስጥ ወሳኝ ናቸው ብዬ የማምናቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች በማንሳት ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡
የዕጩ ተወዳዳሪ ዝግጅት አንዱ መስረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ በምርጫ ለመወዳድር የወሰነ አንድ ፓርቲ በምንም ዓይነት መልኩ ምርጫው ሲደርስ ዕጩ ለማዘጋጀት ደፋ ቀና የሚል ከሆነ ለመሸነፍ መዋጮ ማድረጉን ማመን አለበት፡፡ ለምርጫ ውድድር የሚመለመሉ ዕጩዎች በሁሉም መልክ በተለይ ከገዢው ፓርቲና መንግሰት ሊደርስባቸው የሚችለውን ጫና ለመቋቋም ዝግጁ የሆኑ መሆን አለባቸው፡፡ በዋነኝነት እነዚህ ዕጩዎች እንደ ገዢው ፓርቲ ወጪያቸው በፓርቲ የሚሸፈን ባለመሆኑ ተገቢውን ፋይናንስ ከደጋፊዎቻቸው ለማግኘት የሚያስችል ስልት መቀየስ የግድ ይላቸዋል፡፡ ውድድሩ በእኩል ሁኔታ ላይ እንዳልሆነ ከሚያስረዱት ሁኔታዎች አንዱ ይህ ነው፡፡ የገዢው ፓርቲ ዕጩዎች በዚህ ጉዳይ ቅንጣት ሃሣብ የለባቸውም፡፡ ይህ ጉዳይ የምርጫ ትግል ከሚደረግባቸው አንዱ መሆኑን ተረድተን መፍትሔ መሻት የእኛ እንጂ አንድ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ነን የሚሉ ፓርቲዎች እንደሚሉት ለዚህ መፍትሔ ኢህአዴግ/መንግሰት የገንዘብ ድጋፍ ያድርግልን የሚለው አይደለም፡፡ በሀገራችን ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና መንግሰት የማይለያዩ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ከሚባለው በላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ መንግሰት ድጋፍ ያድርግልን ሲባል ኢህአዴግ ያድርግ እንደማለት እየሆነ ነው፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ ይህን አድርጎ ለመሸነፍ ዝግጁ አይደለም ሰለዚህ ታግለን ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በፍትሃዊነት የሚታዩበት ስርዓት እንዲመጣ በትግል ውስጥ ያለን መሆኑን መረዳት የግድ ይለናል፡፡ ይህ ከባድ ከሆነ አማራጩ ትግሉ ይቅር ወይ? የሚለው ነው፡፡
ከዕጩ ዝግጅት በኋላ በዋነኝነት የሚያስፈልገው በየደረጃው ያሉ ታዛቢዎችን ማዘጋጀት ነው፡፡ የታዛቢዎች ዝግጅት በሁለት ይከፈላል፡፡ የመጀመሪያው በምርጫ ቦርድ አስተባባሪነት የሚዘጋጁት ታዛቢዎች ማለትም “የህዝብ ታዛቢ” የሚባሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ታዛቢዎች በሚመረጡበት ጊዜ ኢህአዴግ ቀደም ብሎ በአንደ-ለአምስት፣ በጥቃቅንና አነስተኛ፣ በወጣትና ሴቶች ፎረም ያደራጃቸውን በተለይም የፋይናንስ አቅማቸው ደከም ያሉ የአካባቢ ነዋሪዎችን በማዘጋጀት በህዝብ እንደተመረጡ በማስመሰል ይመድባቸዋል፡፡ ይህ ሲፈፀም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በዝምታ በማለፍ አንድ ደጋፊያቸው እንኳን እንዲገባ ሳያደርጉ ያልፋሉ፡፡ ትግሉን በትክክል ተረድተን ከሆነ በየምርጫ ጣቢያዎች እነዚህ ታዛቢዎች ሲመደቡ እኛም ደጋፊዎቻችን እንዲኖሩ ለማድረግ መስራት ይኖርብናል፡፡ ልክ ነው ይህን ለማድረግ ኢህአዴግ የዘረጋው ዓይነት የመንግሰት መረብና ድጋፍ አናገኝም፡፡ ይህ ነው የውድድር ሜዳው ልክ አይደለም የሚያስብለው እና ትግል የሚያስፈለገው፡፡ ይህን ለመለወጥ ትግል ማድረግ ካለብን የማይቻል አይደለም፡፡ ሁሉተኛው በዕጩ ተወዳዳሪዎች በራሳቸው የሚመደቡ ታዛቢዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ታዛቢዎች የመምረጥ መብት የዕጩ ተወዳዳሪው ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ያለው ፈታኝ ነገር ታዛቢዎችን ማስፈራራት፣ በገንዘብ መደለል ሲበዛም አፍኖ መውሰድ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እነዚህ በሙሉ የትግሉን አስፈላጊነት የሚያሳዩ እንጂ እንዲህ ከሆነማ ምርጫ ይቅር የሚያስብሉ አይመስለኝም፡፡ የማይፈራ፣ በገንዘብ የማይደለል ታፍኖ ለሚደርስበት ፈተና የተዘጋጀ ታዛቢ ማዘጋጅት ትግሉ የሚጠይቀው መሰዋዕትነት ነው፡፡ ለዚህ የሚመጥን ታዛቢ ማዘጋጀት የዕጩ ተወዳዳሪዎችና የፓርቲዎች ሲሆን ይህን በታዛቢዎች ላይ የሚፈፀም ህገወጥ ድርጊት ማሰቀየር ነው በሀገራችን ፖለቲካ ከሌሎች ዲሞክራሲ ከሰፈነባቸው ሀገሮች ለየት የሚያደርገው እና ትግል ያሰፈለገው፡፡ ምርጫቻን የቱ ነው? ታግለን እንቀይር ወይስ ኢህአዴግ በቃኝ እስኪል እንጠብቅ ነው፡፡
የመራጮች ምዝገባ ዘወትር ተገቢ ትኩረት የማይሰጠው በተወዳዳሪ ፓርቲዎች በኩል ነው፡፡ በ1997 ምርጫ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ቅስቀሳ ተደርጎ ብዙ መራጭ የተመዘገበ ቢሆንም መምረጥ የሚገባቸው ያልተመዘገቡና ባለመመዝገባቸው የቆጫቻ እንደነበሩ የቅርብ ጊዜ  ትውስታችን ነው፡፡ የ1997 በተለየ ሁኔታ ትተን በሌሎች ምርጫዎች ተቃዋሚዎች እንዲመርጡን የምንፈልገው ኢህአዴግ ጎትጉቶ ባስመዘገባቸው መራጮች ነው፡፡ ሁሉም ማወቅ ያለበት ኢህአዴግ በመራጭነት እንዲመዘገቡ ቤት ለቤት እየሄደ የሚቀሰቅሰው ባለው መረጃ መሰረት ደጋፊዎች ብሎ ያመነባቸውን ወይም በቀላሉ ደጋፊ ላደርጋቸው እችላለሁ ብሎ የሚገምታቸውን ነው፡፡ በተለይ በትምህርት ደረጃ ዝቅተኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እናቶች ከአባለት ቀጥለው ለምዝገባ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ ፓርቲዎች በምርጫ ትርጉም ያለው ለውጥ ማየት የምንፈልግ ከሆነ የመራጭ ምዝገባ ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ ደጋፊዎች እንዲመዘገቡ መቀስቀስ፣ ማበረታት እንዲሁም የመመዝገብን ጥቅም ማስተማር ይኖርብናል፡፡ ፓርቲዎች ላለመወዳደር ቢወስኑ እንኳን ደጋፊዎቻቸው ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዳይሄዱ ማድረግ በምርጫው ላይ ትርጉም ያለው መልዕክት ያስተላልፋል፡፡ ያለመወዳደር ምርጫ ከሆነ ማለቴ ነው፡፡ መራጮችን ለማሰመዝገብ በምናደርገው እንቅስቃሴ በአብዛኛው ችግር ባይኖርም መዝጋቢ የለም፣ መታወቂያ አልታደሰም፣ እሰከ ዛሬ የት ነበርክ፣ በቀበሌ ተሳትፎ የለህም፣ የመሳሰሉት የሚጠበቁ የማደናቀፊያ መንገዶች ናቸው፡፡ ይህን ሊቋቋም የሚችል መራጭ እንዲኖር ቅስቀሳ ማድረግ ከትግሉ አንዱ አካል ነው፡፡ መራጮች በወኔ እንዲመዘገቡ ካደረግናቸው ከተመዘገቡ በኋላ መራጭ ብቻ ሳይሆን ቀስቃሽም በመሆን የምርጫ ምዕዳሩ እንዲስተካከል ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ ህዝብ የተሳተፈበት አፈናን እንቢ የማለት ተግባር ደግሞ በጥቂት ካድሬዎች ቁጥጥር ስር እንዲውል የተውነውን ምርጫ በትግላችን የእኛም ይሆናል ማለት፡፡ ለመምረጥ ያልተመዘገበ መራጫ የምርጫ ምዕዳር ለማስፋት አላፊነት ያለበት አይመስለውም፡፡ ትክክልም ነው፡፡ የምርጫ ምዕዳር የማስፋት አላፊነት ያለበት ዜጋ መፍጠር የትግሉ አካል ነው፡፡ ቆጠራ ሳይጠናቀቅ ካደረ አብረን ስንጠብቅ እናድራለን የሚል መራጭ ማዘጋጀት የግድ ይላል፡፡ ምርጫ 97 ትዝ አይላችሁም፡፡
መራጮች የሰጡትን ድምፅ፣ ታዛቢ ተከታትሎ ቆጥሮ፣ ደምሮ  የተቀበለውን፣ ምርጫ ቦርድ ሊለውጠው አይችልም ባይባልም ለመለወጥ የሚገጥመው ፈተና ከባድ ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ እንደመፃፍ ቀላል እንዳልሆነ ይገባኛል፣ ኢህአዴግ ሲጨንቀው በታጣቂ ኮሮጆ እንደሚገለብጥ ዘንግቼው አይደለም፡፡ ይህን ድርጊቱን በተደራጀ መከላከል የትግሉ አንድ አካል እንደሆነ አፅዕኖት ለመስጠት ነው፡፡ ፓርቲዎች አሁን ባለው ደረጃ ይህን ለማድረግ ሙሉ ለሙሉ አልተዘጋጀንም የሚሉ ከሆነ ከምርጫ ለመውጣት ሳይሆን በተደራጁበት ልክ ለመወዳደር መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሀሉም ቦታ ለመሆን ሲከጀል አንድም ቦታ ያለመሆን የሚመጣው በዚህ ምክንያት ነው፡፡
በታዛቢዎች የተፈረመ የምርጫ ውጤትን በምርጫ ቦርድ በኩል በሚፈፀም ሸፍጥ ወይም በጉልበት መሣሪያ ጭምር ተደርጎ በሚደረግ ንጥቂያ ሌላ ፈተና ላይ የሚወድቀው አካል የፍትህ ስርዓቱ ነው፡፡ የተደራጀ መረጃ ይዘን የፍትህ ስርዓቱን መሞገትም አንዱ የትግል አካል እንደሆነ መዘንጋት የለበትም፡፡ ይህን ሁሉ አድርገን ኢህአዴግ እነዚህን የህዝብ ድምፆች ገፍቶ ማነኛውንም ዓይነት ጉልበት ለመጠቀም ቢወስን ህዝብ የተሳተፈበት ስለሚሆን መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ምርጫን ተከትሎ ለሚመጣ አብዮትም ጠሪ የሚሆነው የዚህ ዓይነት ድርጊት ነው፡፡ በምርጫ መሳተፍ ሂደት ውስጥ ህዝብ ካልተሳተፈ የተወሰኑ ሰዎች የሚያደርጉት መፍጨርጨር ሰለሚሆኑ ህዝቡ ድምፁ እንዲከበር የሚያደርገው ግፊት እምብዛም ነው፡፡ እነደከዚህ ቀደሙ ኢህአዴግ ወትውቶ ያስመዘገባቸው ሰዎች ለምን አልመረጡንም ብለን መጠየቅ ተገቢ አይደለም፡፡ በሚስጥር ድምፅ ሰጥተውን ቢሆን እንኳ በይፋ ድምፃችን ይከበር ሊሉ ይችላሉ ብሎ መጠበቅ የዋህ መሆን ነው፡፡ በሚስጥር የካዱትን በአደባባይ እንዲያረጋግጡ መጠየቅ ነው የሚሆነው፡፡
በዚህ ደረጃ ሳንዘጋጅ ቀርተን ምዕዳሩ ጠቧል ብለን “ሰለ …ሲባል ምርጫው ቢቀር” የምንል ከሆነ ኢህአዴግ ደስተኛ ነው፡፡ በግልፅ የሚሰብከውን አውራ ፓርቲ ስርዓት ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ ኢህአዴግ ምዕዳሩን በህዝብ ተሳትፎ ሳናስገድደው ያሰፋዋል ብለን የምንጠብቅ ከሆነ በቅርቡ የሚሆን ስለአልሆነ የትግል ስልታችንን መፈተሸ ሊኖርብን ይገባል፡፡ አንዱ አማራጭ አንድ ሺ ትንታግ ታዛቢ ከማዘጋጀት፣ አንድ ሺ ተኳሽ ተዋጊ ሀይል ማዘጋጅት ሊሆን ይችላል፡፡ እንግዲህ ዘመኑ የሚዋጀውን፣ ለሰው ልጅ ከፍተኛ ክብር የሚሰጠውን፣ በወጪ አንፃርም አዋጭ ሊሆን የሚችለውን የትግል ስልት መምረጥ በፓርቲ ውስጥ ያሉ ስትራቴጂሰቶች ሃላፊነት ነው፡፡ በሃላፊነት ሰሜት የሚወሰን፡፡
እርግጠኛ ነኝ “ስለ …. ሲባል ምርጫው ቢቀር” የሚለው ሃሳብ የቀረበው በባርነት እንቀጥል በሚል ወይም የኢህአዴግ አውራ ፓርቲ ፍልስፍና ተስማምቶናል የሚል አይደለም፡፡ በእኔ አረዳድ ሌላ አማራጭ የትግል ስልት እንመልከት የሚል መሆን አለበት፡፡ ለጊዜው የምርጫው መንገድ ገና ብዙ ያልተሄደበት መንገድ ስለሆነ ተሰፋ መቁረጥ ያለብን አይመስለኝም፡፡ ምርጫ መሳተፍ የሰላማዊ ትግል ማሳኪያ አንዱ መንገድ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን በፍፁም የምርጫ ሰሞን ደርሶ በሚፈጠር ሆይ ሆይታ ውስጥ ውጤት ለማግኘት መከጀል አይደለም፡፡ ከላይ በአጭሩ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት በሁሉም የምርጫ ደረጃዎች በንቃት በመሳተፍ እና ህዝቡን በማሳተፍ ነው፡፡
ቸር ይግጠመን

Tuesday, June 3, 2014

የመቀሌ ጉራማይሌ



ጉብኝት አዋሳ ላንጋኖ ብቻ ነው ያለው ማነው? ያልን ሰዎች ትግራይ መቀሌ ለጉብኝት ጎራ ብለንለ ነበር፡፡ አንድ አንዶች ኤርትራ ሊሄዱ ነው ሲሉን ተመስገን ደሳለኝን ኤርፖርት ያዩት ሰዎች ደግሞ ተሰደደ ማለታቸውን ሰማን፡፡ አውሮፕላን ልትጠልፉ ነው ወይ ያሉንም ፌዘኞች ነበሩ፡፡ ስደትና ጠለፍ የትግላችን አካል አለመሆኑን የተረዱት ቢሆኑ ይህን ግምት ይተዉት ነበር፡፡ በቁጭት የተነጋገርንበት ግን አሰመራ የሰው ሀገር ሆኖ መሄድ ያለመቻላችን እንዲሁም ምፅዋ ከመሄድ ሞምባሳ መሄድ መቅለሉን ነው፡፡ ይህ የገዢዎች አጥር ፈርሶ አሰመራ ምፅዋ እንደምንሄድ ፅኑ እምነት አለኝ፡፡
በመቀሌ ባሰለፉክት ቆይታ የተረዳሁት ጥቂት ሰዎች በቁርጥና ውስኪ ቤት የሚገኙ ሲሆን፣ አብዛኛው ህዝብ ደግሞ የእለት ኑሮ ለመግፋት የሚውተረተር መሆኑ ነው፡፡ በሰራ ቀን በቡና መጣጫ ሰፈሮች የሚገኘው ወጣት ብዛት የሚያሳዝን ነው፡፡ ከሁሉም የሚያሳዝነው ግን ከአንድ የወዳጃችን ዘመድ ጋር የነበረን ቆይታ ነው፡፡ ሌላው ካስፈለገ በሌላ ቀን እመለስበታለሁ፡፡
ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ሰሙን ጥበቡ ብለነዋል፡፡ ጥበቡ በዚህ ጉዳይ ሰሙ እንዲነሳ ፈቃደኛ ሊሆን አይችልም፡፡ ጥበቡን ያገኘነው ከሰማዕታት ሀውልት ጉብኝት በኋላ 16 በሚባለው መዝናኛ ሰፈር ነው፡፡ ባንኮኒ ላይ ሆነን ስንጫወት ፈንጠር ብሎ ብቻውን ተቀምጦ ይተክዛል አብሮን ቢሆንም ልቡ ከእኛ ጋር አልነበረም፡፡ አንድ ሌላ ጓደኛውን ጠርቶት ሲቀላቀለን ከብቸኝነቱ ተገላገልን ብለን አርፈን እራት በልተን ሌላ ቤት ለማይት ጎራ አለን፡፡ ብቸኝነቱ ፍላጎት ስለመሰለን አላሰጨነቀንም፡፡ አብረውን ያሉት እነ አርሃያ እና ክብሮም በጫወታ ወጥረው ስለያዙን የጥበቡ ነገር ብዙም ልብ አላልነው፡፡ አርሃያና ክብሮም ትክክለኛ ሰማቸው ነው፡፡

ጥበቡና እኔ ጎን ለጎን ቁጭ ብለን በሙዚቃ መሃል አንድ አንድ ነገር እንጫወታለን፤ ከፊት ለፊታችን ተመስገን ደሳለኝ እና የጥበቡ ጓደኛ ቁጭ ብለዋል፡፡ ድንገት ከእኔ እና ጥበቡ ፊት ለፊት አንዲት ሴት በምሽት ዳንስ አለባበስ የሆነች እና አንድ የቪዲዮ ካሜራ የያዘ ወጣት ቁጭ አሉ፡፡ ጥበቡ እነዚህ ሰዎች እየቀረፁን ነው ወይ? ብሎ ሲጠይቀኝ አዎ አልኩት እንደቀልድ፡፡ ጥበቡ ከእኔ ጋር የነበረው ጫወታ ጠፋበት ይርበደበድ ጀመር፡፡ ሰዎቹ ተነስተው ወጡ፡፡ ቀስ ብሎ በጆሮዬ ግርማ አንተ ታወቂ ስለሆንክ ምንም አትሆንም እኔን ግን አያኖሩኝም አለ፡፡ ቀልዱን መስሎኝ ምን ያደርጉሃል? ሰለው ፍርሃት ያመጣለትን ሁሉ ነገረኝ፡፡ ፍርሃቱ ገባኝ፡፡ ሰቀልድ ነው እየቀረፁን አልነበረም ካሜረው እኮ አልበራም ብዬ ለማረጋገት ሞከርኩ፡፡ እጁን ሰጥቶኝ መታሁለት እንድምልለት ጠይቆኝ ማልኩለት፡፡ እጁን ጭኔ ላይ አድርጎ ለመረጋጋት ሞከረ፡፡ እጁ ሲንቀጠቀጥ ይሰማኛል፡፡ ግርማ ልብ አላልክም እንጂ ድሮም ከእናንተ ጋር መሆን አልፈለኩም ለዚህ ነው ራቅ ብዬ ቁጭ ያልኩት ብሎ የፍርሃቱን መጀመሪያ ነገረኝ፡፡
ሳቅም አዘንም ተሰማኝ፡፡ ቤት እንቀይር ብለን ስንወጣ ባለካሜራው ሰራውን እየሰራ ነው፡፡ አብራው የነበረችውን ልጅ ከምሽቱ ድባብ ጋር ይቀርፃታል፡፡ ሌሎችም ታዳሚዎችም አብረው አሉ፡፡ በግምት በፊልም ቀረፃ ላይ ናቸው፡፡ የጥበቡን ልብ ግን ሳያውቁ እሰኪጎን ድረስ በፍርሃት አርበድብደውት፡፡ ጥበቡን ጠርቼ እመነኝ ይኽውልህ ሰዎቹ በሌላ ስራ ላይ ናቸው፤ ብዬ እንዲረጋጋ መከርኩት፡፡ የምታውቀው የደህንነት ሰው ቢኖር እንኳን እየጠበቁን ነው ብለህ አስብ፤ ግፋ ቢል ነገ ጠርተው ከእኛ ጋር ምን ምን እንዳደረክ ይጠይቁሃል በትክክል ያደረከውን ተናገር አልኩት፡፡ የተረጋጋ መስሎ ወደ ቀጣዩ ቤት እርሱ ባመጣልን  ጓደኛው መሪነት ገባን፡፡ ጥበቡ ድንገት ተሰወረብን እምጥ ይግባ ስምጥ ማወቅ አቃተን ጓደኛው ደውሎ መሄዱን አረጋገጠ፣ ጥበቡም በማግሰቱ ጠዋት ደውሎ ይቅርታ ማታ ተረብሼ ስለረበሽኳቹ ብሎን በዝርዝር ፍርኃቱን ነገረን፡፡ ይህንን ፍርሃት ቀን ስንጎበኘው የነበረው የሰማዕታት ሀውልት ላይ ያየነው ተጋድሎ ያመጣው ሳይሆን በዚህ ትግል ጀርባ ለድል የበቁት እና በስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ዘርተውት መሆኑን መረዳት አያሰቸግርም፡፡ ስንት የትግራይ ልጆች በእንደዚህ ያለ ፍርሃት ስር እንደወደቁ ማሰብ አያሳቸግርም፡፡

Sunday, June 1, 2014

ሚዛናችን ለምን ተዛባ?



የልክነት ሚዛናቸን የጠፋብን ወይም ደግሞ ሁለትና ከዚያ በላይ መለኪያ አስቀምጠን በምናደርገው ተግባር ሳይሆን በውጤት መመዘን የምንፈልግ ብዙዎች ነን፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያለው ስርዓት ደግሞ የዚህ ዓይነት ሚዛን አልባነትን ጎሽ በርቱ ብሎ ቡራኬ የሰጠ ነው የሚመስለው፡፡ እንደአስፈላጊነቱ ይጠቀምበታል፤ እንድንጠቀምበትም እያበረታታን ይገኛል፡፡
መንግሰት “አሸባሪ” ብሎ ከፈረጀው ግንቦት ሰባት ከሚባል ድርጅት አባሎች ጋር የአባልነት ፎርም ሲለዋወጥ፣ ሌሎችንም ለማደራጀት ጥረት ሲያደርግ የነበረ አንድ ግለሰብ በኋላ ላይ አዳፍኔ ምስክር  ሆኖ ቀርቦ እርሱ ነፃ ዜጋ ሆኖ ከዚህ ጋር አንድም ግንኙነት እንዳላቸው ሊያሳዩን ባልቻሉበት መልኩ እነ አንዱዓለም እና ናትናኤል በእስር ቤት ይገኛሉ፡፡ “ነፃነት” የሚሰማው ከሆነ ይህ ግለሰብ በነፃነት “የዞን ዘጠኝ” ታሳሪ/ነዋሪ ሆኖ ቀጥሎዋል፡፡ በቅርቡ “ዞን ዘጠኝ” የሚለው ስያሜ አሰጣጥ ነፃነታቸውን ለማስከበር ዳተኛ ለሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተሰማሚ ሆኖ ስላገኘሁት ነው፡፡ ይህ ለታሪክ የተመዘገበ ሃቅ መስካሪ የሆነውንም ሆነ ተመስክሮባችኋላ ተብለው በግፍ በእስር ቤት ለሚገኙት ዜጎች ወደፊት ታሪክ የሚፋረዳቸው ይሆናሉ፡፡ ይህ ውርስ በባንዳነትም ይሁን በጀግንነት ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ ሰለሆነ እንደ ቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ለመግቢያ ያህል በግፍ በእስር የሚገኙትን ጓዶቼን ካስታወስኩዋችሁ ይህ ጉዳይ ውስብስብ የፖለቲካ ቋጠሮ ስላለው እንለፈው እና ወደ ሌሎች ቀጥታ ፖለቲካ ያልሆኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታችን የሚያወሱ ጉዳዮች ብንሻገር መረጥኩ፡፡
በእለት ከእለት ግንኙነታቸን ጎቦ ሰጪና ተቀባይ እያለ ጣታችን የሚጠነቁለው ተቀባዩ ላይ ብቻ አድርገናል፡፡ ጠንቋይና አስጠንቋይ ባለበት ሀገር የጠንቋዩን ክፋት እንጂ የአስጠንቋይ እኩይ ተግባር እንደቅንነት ተወስዶዋል፡፡ የአራጣ አበዳሪና ተበዳሪ ድራማ በድፍኑ በአበዳሪ ላይ ተደፍድፎ አራጣ ተበዳሪዎች ቅን ኢንቨሰተሮች ተብለው በይፋ ሲሞካሹ መሰማት መደበኛ ነገር ሆኖዋል፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች በአንድ ወቅት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ወንድ አዳሪዎች እያሉ ትኩረታችን በሴቶቹ ላይ መሆኑን ባሳየው መስመር ማየት ፈለጉህ፡፡ ሜሪኩሪ ሸጦ ያለ አግባብ ለመክበር የፈለገን ግለስብ ወይም ብርን ዶላር አድርግልሃለው ተብሎ የተጃጃለን ማነኛውንም ስው በውጤቱ ጉዳት ስለደረሰበት ማዘን የፈለገ መብቱ ቢሆንም ህገወጥ መሆናቸውን በግልፅ ያለመንገር ግን ተገቢ ነው ብዬ ለመውስድ ስለተቸገርኩ ነው፡፡

ጎቦ ስጪና ተቀባይ
ከህግ አንፃር ጉቦ መስጠትም ሆነ መቀበል ወንጀል ነው፡፡ ከሞራል አንፃርም ቢሆን መስጠትም መቀበልም አሰነዋሪ ድርጊት ነው፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ ግን ጠቅላላ መግባባት የተደረሰ በሚመስል መልኩ ስናወግዝ የምንሰማውም ሆነ የምንታየው ጉቦ ተቀባይ ላይ ብቻ ነው ባይባል እንኳን ከልክ በላይ ነው፡፡ ለምሳሌ ትራፊክ ፖሊሶች አብዛኞቹ ጉበኞች ናቸው ብለን የተሰማማነውን ያህል፣ መኪና አሽከርካሪዎች ጎቦ ሰጪዎች ናቸው ሲባል አይሰማም፡፡ አንድ ሺ ትራፊክ ጉቦ ቢቀበል መቶ ሺ ጎቦ ሰጪ መኖሩን ዘንግተን በአንድ ሺ ትራፊክ ላይ እንረባረባለን፡፡ ጎቦ ሰጥቶ መንጃ ፈቃዱን ወይም ታርጋውን ያስመለሰ አሸከርካሪ በኩራት በአደባባይ ሲያወራ ምንም ነውር የለውም፡፡ ገቢዎችና ጉምሩክ ስራተኞች ላይ ጣታችንን ስንቀስር ለእነዚህ ሰዎች ጎቦ የሚሰጡትን ነጋዴዎች ሁል ጊዜ ተገደው የሞት ሽረት ሕይወት ለመምራት አድርገን እንቆጥርላቸዋለን፡፡ የትራፊክ ህግ የጣሰ ግለሰብ በህግ በተቀመጠው አግባብ ቅጣቱን መክፈል ሲገባው ለመንግሰት መግባት ያለበትን ብር ሁለት መቶ ተደራድሮ በማስቀረት አንድ መቶ ጉቦ ሲሰጥ አንድ መቶ መስረቁን ልብ የሚለው አይደለም፡፡ ለመንግሰት መከፈል ያለበትን ግብር ላለመክፈል ከግብር አስከፋይ ጋር ተደራድሮ ግማሹን ጉቦ ሰጥቶ ግማሹን “ሲያድን” እንደ ሌብነት ሳይሆን ጮሌነት መቁጠር እየተለመደ የመጣ የተሳሳተ ሚዛን ውጤት ነው፡፡ እረ ጎበዝ ሚዛናችንን ምን ነካው?

አራጣ አበዳሪና ተበዳሪ
የከተማችን ኢንቨስተሮች በአራጣ ብር እንደሚነግዱ መረጃ መውጣት ከጀመረ ሰነባብቶዋል፡፡ አሁንም ግን ዘመቻው ያለው አራጣ አበዳሪ የተባሉት ላይ ያመዘነ ነው፡፡ ለአራጣ ብድር ባዶ ቦርሳ ይዘው የሄዱት ሰዎች ለምን እንዲህ እንዳደረጉ የሚጠይቃቸው ያለ አይመስልም፡፡ ለአራጣ የሚሆነውን ወለድ የዜጎችን ደም በሚመጥ የዋጋ ጫና ወደ ዜጎች አስተላልፈው ሊከብሩ እንዳሰቡ የሚነግራቸው ደፋር የተገኘ አይመስልም፡፡ ዛሬ በአራጣ መደህየታቸው እንጂ ስንቱን ለማደህየት ታጠቀው ተነስተው የነበሩ መሆናቸው ተዘንግቶዋል፡፡ አራጣ አበዳሪዎች ብቻ ሳይሆን አራጣ ተበዳሪዎች እኩል ጥፋተኞች መሆናቸውን አምነን መቀበል ይኖርብናል፡፡ አንድ አራጣ አበዳሪ እንዲከብር ብዙ አራጣ ተበዳሪዎች የመኖራቸው ሀቅ በፍፁም ሊሰወርብን አይገባም፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ በመንግሰት ፖሊሲ ምክንያት መስሪያ ካፒታል እጥረት እንደሚኖር ሀቅ ነው፡፡ የመስሪያ ካፒታል ዕጥረት በህገወጥ መንገድ መሸፈን ግን በምንም ሚዛን ልክ ሊሆን አይችልም፡፡ የፖሊሲ ስህተት ግለሰቦች በሚሰሩት ስህተት አይሰረይም፡፡ በተለይ ከእለት ኑሮው አልፎ ለሌሎች ዕድል ልፈጥር ነው የሚል “ኢንቨስተር” የሚጠበቅበት ህገ ወጥ ወይም ኢ-ሞራላዊ መሆን ሳይሆን የስራውን ስፋት መቀነስ ነው፡፡ ስኬት በውጤት ሳይሆን የሚለካው ውጤቱን ለማምጣት በተሄደብት ህጋዊነት ጭምር ነው፡፡ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው አይስራም፡፡ የስራ ዕድል ለመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት፣ ባለሀብት ለመባል የተሄደበት መንገድ ከተደረሰበት ውጤት እኩል ወይም በላቀ ሁኔታ ግልፅና በሃቅ ላይ የተመሰረተ ሊሆን ግድ ይላል፡፡ ከላይ የተዘረዘሩትን ውጤት ለማሰመዝገብ ወንጀል ውስጥ መዘፈቅ ተቀባይነት የለውም፡፡
ጠንቋይና አሰጠንቋይ
አንድ ሰሞን ታምራት የሚባል ጠንቋይ የከተማችን ዋነኛ አጀንዳ እንደ ነበር የሚዘነጋ አይመስለኝም፡፡ በዚህ ጉዳይ ከእምነት ነፃነት ጋር አያይዤ የግል ምልከታዬን አቅርቤ እንደ ነበር አስታውሳለሁ፡፡ በአብዛኛው ግን ታምራት ቤታችው ሄዶ ሳይሆን ቤቱ ድረስ እየሄዱ ያለ አግባብ ለመበልፀግ ወይም “የቸገረው እርጉዝ ያገባል” በሚል ብሂል ለጤናችን መሻሻል ብለው ከህክምና ተቋም ይልቅ ጠንቋይ ቤት መርጠው የሄዱትን ሰዎችን በግልፅ ጥፋተኛ መሆናቸው ሳይነገራቸው ይልቁንም ተበድለዋል በሚል ከንፈር ተመጦላቸው ተገቢ ያልሆነ ድርጊት አብረው ማድረጋቸው ተዘንግቶ ምስክርና ከሳሽ ሆነው መቅረባቸው አሳፋሪ ነው፡፡ እኔ በምንም ሚዛን ለጠንቋይ ጥብቅና እንደማልቆም የታወቀ ቢሆንም ለአሰጠንቋዮችም የምቆምበት ልብ የለኝም፡፡ አንድ ጠንቋይ ቤት በካዳሚነት ይሰራ የነበረ ሰው ጠንቋዮች የሚባሉት የደንበኞቻቸው ስግብግብነት የገባቸው የሰነ ልቦና አዋቂዎች ናቸው ይለኛል፡፡ ጠንቋያቸው ካዘዛቸው የሰውን ልጅ ክብር ነብስ ለገንዘብ ሲሉ ከማጥፋት ለማይመለሱ አስጠንቋዮች በግልፅ ቋንቋ በእኩል ደረጃ ጥፋተኞ መሆናቸው ሊነገራቸው ይገባል፡፡ ለዚህ ነው ሚዛናችን በውጤቱ ሳይሆን ሂደቱንም ከግንዛቤ ያሰገባ መሆን ይኖርበታል የምለው፡፡ ምንም ጥርጥር የሌለው ጤናቻውን ለማስመለስ ህይወት የከፈሉ፤ እንከብራለን ብለው የደኸዩ እንሚኖሩ እርግጥ ነው - ይህ ውጤት ነው፡፡

የሎተሪ ቁጭበሉና ባለመታወቂያዎቹ/ሜሪኩሪና ዶላር
ሎተሪ አሰር ሺ ብር ደርሶኝ መታወቂያ ስለሌለኝ ያለህን/ያለሽን ሰጡኝና ቀሪውን ውሰዱት ብሎ ለሚያታልል ቁጭ በሉ ንብረቱን ያስረከበ ሰው ሊታዘንለት ይገባል ብዬ አላምንም፡፡ አንድ ሺ ብር ንብረት ወይም ጥሬ ገንዘብ ሰጥቶ የሰው ዕድል አሰር ሺ ለመውሰድ የተዘጋጀ መታወቂያ ያለው ሰው ይህ ሳይሳካለት ቢቀር ቁማር እንደተበላ ቁማርተኛ እንጂ ሎተሪ የደረሰውን ሰው ለመርዳት የተነሳ ቅን ሰው አድርጌ ለመውሰድ ልብ የለኝም፡፡ ተማሪ እያለሁ “ቀይዋን ያየ በሚባል የካርታ ጨዋታ” ተሣታፊ ሆኜ ለጫማ መግዣ የተሰጠኝን ሃምሣ ብር ኮልፌ ታይዋን የሚባል ገበያ ውስጥ ተብልቻለሁ፡፡ ከዚህ መማርና ከቁማር መራቅ የእኔ ፋንታ እንጂ የካርታ አጫዋቾቹ አይመስለኝም፡፡ ትርፍ ለማግኘት ብዬ ተበላው፡፡ ቁማር ህገ ወጥ ከሆነ ካርታ አጫዋቹ ብቻ ሳይሆን እኔም አለሁበት፡፡ በፖሊስ ፕሮግራም እንባቸውን እያወረዱ የሚቀርቡት ሰዎች እንባቸውን ማበስ የእነሱ ፋንታ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ እርግጠኛ ባልሆንም ፖሊስ እነዚህን አትርፍ ባይ አጎዳዮች  የሚያቀርባቸው ሌሎች በተመሳሳይ አተርፍ ብለው በቁጭ በሉ እንዳይወናበዱ ከተማሩ በሚል ይመስለኛል፡፡ በሌላ በኩል በብዙ ሚሊዮን ብር የሚሽጥ ሜሪኩሪ አለ ተብሎ በእጅ ያለን መቶ ሺ ተጠቅመን ገዝትን እንሽጥ ሲባል እሺ ብሎ ሚሊየነር ለመሆን የወሰነ ሰው ጤነኛ ነው ማለት ይቻላል? በተመሳሳይ በእጅ የያዝከውን ብር መቶ ሺ በመቶ ሺ ዶላር ይቀየራል ተብሎ መቶ ብር የማያወጣ ወረቀት ተሸክሞ ቤቱ የገባን ሰው ምን ልንለው እንችላለን? ይህ በምድራዊ ህግም ሆነ በሞራል ተቀባይነት የሌለው የሀብት ማጋበስ አባዜ ከየት ነው ያመጣነው? ይህን አባዜ ትክክል አይደለም የደረሰብ ጉዳት ለሰራህ ተመጣጣኝ ቅጣት ነው ለማለት ለምን ድፍረት አጣን? በእኔ እምነት ይህን ድፍረት የምናጣው በአንድ ወይም በሌላ መስመር ይህችን ጫወታ ለመጫወት በየግላችን ሳናስብ የምንቀር አይመስለኝም፡፡ ልክ ነኝ?
ሴት አዳሪነት ወንድ አዳሪነት
ሴት አዳሪነትን የምንፀየፍ ወንድ አዳሪወች በብዛት አለን፡፡ ወንዶች የሴቶችን አገልግሎት ባይፈልጉት ሴቶቹ በብርድ እራቃናቸውን ለመቆም ምንም ገፊ ምክንያት አይኖራቸውም፤ የፍላጎቱ መኖር ነው አቅርቦቱ እንዲኖር እያደረገ ያለው፡፡ በዚህ ጉዳይ በልዩ ችሎታው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት መክሮናልና መድገም አልፈልግም ይህን የሴት አዳሪዎችን ጉዳይ ካነሳው አይቅር አንድ ጉዳይ ሳላነሳ ማለፍ ግን አልፈለኩም፡፡ በሴት አዳሪነት የተሰማሩት ሴት እህቶች የመንግሰትን ድጋፍ አግኝተው ከዚህ ኑሮ ለመውጣት ሳውዲ ሀረብያ ሄደው በግፍ  ተባረው መምጣት ይኖርባቸው ይሆን? የሚል ጥያቄ አለኝ፡፡ በዚህ ጉዳይ በቂ መረጃ ባይኖረኝም በከተማችን አንድ ድንክ አልጋ ዘርግተው ደጃቸው ላይ ቆመው ደንበኛ የሚጠብቁ ሴቶች ቁጥር የሳውዲ ሰደተኞችን እንደማያክሉ እርግጠኛ ነኝ፡፡ እነዚህን እህቶች ከዚህ ስራ ማውጣት ቀላል ባይሆንም የማይቻል ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ በባቡር ዝርጋታ ሰበብ መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት የቀድሞ አራተኛ ክፍለ ጦር ጀርባ ወይም መሸዋለኪያ አካበቢ በምሽት ሰመላለስ የማየው ነገር በፍፁም ሰላም አይሰጠኝም፡፡ የዚህች ሀገር እድገት ትሩፋት መቼ ነው የሚደርሳቸው የሚል ምፀት ይመጣብኛል፡፡ እነዚህን እህቶች የወረዳው ጥቃቅን እና አነሰተኛ ተቋም አደራጅቷቸው ይሆን ይህን ስራ የሚሰሩት? ካልሆነ ለእነዚህ ሴቶች የሚሆን የስራ ምክረ ሃሳብ አለው?

እነዚህን ሁሉ ደምረን ለምንድነው የዚህ ዓይነት ሰግብግብ ሰዎች እየተበራከቱ ከሚገባቸው በላይ ጥቅም ለማግኘት የሚደራጁት ብለን ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ በሙሉ ከላይ ያነሳዋቸው የተበላሸ ስርዓት መገለጫዎች ናቸው፡፡ የአባት ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ የሚል የተሳሳተ ብሂል ውጤት ናቸው፡፡ ሕግ ያለማክበር፤ ግብር ለመክፈልም ሆነ በተገቢው ሁኔታ ፈቃደኝነት ማጣት፣ በህገ ወጥ ገንዘብ መክበርና ከዚህም የተገኘውን ገንዘብ ወደ ውጭ ማሻሽ፣ ሰካርና ዝሙት የስርዓት መበስበስ በግለሰብ ደረጃ ደግሞ የሞራል ውድቀት ማሳያ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በስርዓቱ ውስጥ የምንገኝ ብንሆንም በቁጥጥራችን ስር ያለውን የግልና የቤተሰብ ሞራላችን በመጠበቅ ይህን ስርዓት ማስወገድ ይኖርብናል፡፡ ስህተት በስህተት አይታረምም፡፡ ሚዛናቸን ትክክል ይሁን!!!!