Tuesday, July 19, 2016

ከግል እና ከመንግሰት ትምህርት ቤት በጥራት ማን ይሻለል?



በዛሬው ፅሁፌ በቅርቡ በዘመቻ መልክ የሚካሄደውን የግል ትምህርት ቤቶች ውግዘት አሰመልክቶ አንድ አንድ ሃሳቦች መሰንዘር እፈልጋለሁ፡፡ ይህ የግል አስተያየት በቅጡ ውይይት ማደረግ የሚፈልግ ካለ በይፋ መድረክ ላይ መነጋገር የምችልበት በፅኑ የማምንበት አቋም ነው፡፡ በተለይ በቴሌቪዥን “ማያ” በሚባል ፕሮግራም ላይ ሲቀርብ የነበረው ተከታታይ የግል ትምህርት ዘርፍ ጠል የሆነ አቀራረብ ፕሮግራሙን አስቀያሚ አድርጎታል ብዬ እንዳምን አድርጎኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የፕሮግራሙ አቅራቢ ልጁን የትኛው የመንግሰት ትምህርት ቤት እንደሚያስተምር በይፋ ለህዝብ እንዲገልፅ እጠይቃለሁ፡፡ ያለበለዚያ ግን ልጁን የግል ትምህርት ቤት እየለካ የዚህን ዓይነት ፕሮግራም ማዘጋጀት አሰነዋሪ ነው፡፡ ልጅ ከሌለው ደግሞ በዚህ ደረጃ በማያውቀው ጉዳይ ባይገባ ይመከራል፡፡ እደግመዋለሁ “ልጆቹን የት የመንግሰት ትምህርት ቤት እንደሚያስተምር ለህዝብ በይፋ መግለፅ እና ምሳሌ መሆን ይኖርበታል”፡፡
በመጀመሪያ ከግልና ከመንግሰት ትምህርት ቤት የቱ ይሻላል? ከባድ ጥያቄ አይደለም፡፡ በብዙ እጥፍ የግል ትምህርት ቤት ይሻላል፡፡ ለምን? ብሎ በመጠየቅ እና ተገቢውን መልስ በመስጠት የመንግሰት ትምህርት ቤቶች ወደ ግል ትምህርት ቤቶች ደረጃ ለማሳደግ የሚደረግ ጥረት ካለ ይህን ለማሳካት ይረዳል የሚል እምነት አለኝ፡፡
በእኔ እምነት የግል ትምህርት ቤቶች በሚከተሉት ሁኔታዎች የተሻሉ ናቸው፤
1)  የወላጅ - ትምህርት ቤት መገናኛ መፅኃፍ ማዘጋጀት እና መጠቀም፡፡ ይህ የግንኙነት መስመር የዕለት ከዕለት ነው፡፡ የልጆች ትምህርት ቤት ወሎን፤ ምን የቤት ስራ እንደተሰጠ፣ ልጆች በዕለቱ በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ፣ ጤናቸውን ጨምሮ፣ ሌሎች ጠቃሚ መረጃዎችን መምህር ለወላጅ መልዕክት ይልካል፡፡ ወላጅ መልዕከቱን ማየቱን በፊርማው ያረጋግጣል፡፡ በዚህ ሁኔታ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲከታተሉ የሚያደርጉ ሲሆን የመንግሰት ትምህርት ቤቶች የዚህ ዓይነት ስርዓት ያላቸው መኖራቸውን አላውቅም፡፡ መንግስት የወላጅ ትምህርት ቤት የግንኙነት የሚያጠናክር ማስታወሻ መፅኃፍ በማዘጋጀት እና ተግባራዊነቱን በመከታተል በቀላሉ ሊያደረገው የሚችል ቀላል ግን እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ወላጆች/የወላጅ ኮሚቴዎች በወርና በሶሰት ወር ከሚያደርጉት ሰብሰባ እጅጉን የተሻለ ነው፡፡

2)  የግል ትምህርት ቤቶች የእንግሊዘኛ ቋንቋን በተሸለ ሁኔታ ሰለሚያስተምሩ ቋንቁ የሚችሉ ልጆች ደግሞ ማነኛውንም የመረጃ ምንጭ በቀላሉ እንዲጠቀሙ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህ ዘመን ደግሞ መረጃ የእውቀት መሰረት ነው፡፡ ይህንን እጅግ አስፈላጊ የእውቀት መሰረት የሆነን ቋንቋ ወላጆች ለምን ትኩረት ሰጡት ብሎ ክስ የሚያቀርቡ የመንግሰት ትምህርት ቤቶች ዳይሬክተሮች ትምህርት ምን ማለት እንደሆነ የገባቸው አይመሰለኝም፡፡ እዚህ ነጥብ ላይ አንድ የግል ምሳሌ መግለፅ እፈለግጋለሁ፡፡ ልጆቼን ከማስተምርበት ትምህርት ቤት ልጆቾ “በአማርኛ” ወይስ “በእንግሊዘኛ” እንዲማሩ ይፈልጋሉ? ምክንያቶን ያስቀምጡ የሚል እና ሌሎች መጠይቆች ቀረቡልኝ፡፡ ይህን ጥያቄ ከልጄ ጋር መወያየት ስለነበረብኝ ተነጋገርን፡፡ በእንግሊዘኛ መማር እንደሚፈልግ አስረግጦ ነገረኝ - በወቅቱ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነበር፡፡ ለምን ብዬ ሰጠይቀው “ዓለም አቀፍ” መሆን ሰለምፈልግ አለኝ፡፡ ከዚህ የተሸለ መልስ እኔም አልነበረኝም እና ይህንኑ ሞልቼ ላኩኝ፡፡ አሁን በዘማቻ የተያዘው ነገር “በአፍ መፍቻ ቋንቋ” በሚል ፈሊጥ ልጆቻችን በአማርኛ ይማሩ የሚል የጥቂቶች ጩኽት በመርዝ የተቀባ መሆኑን ለማወቅ ነብይ መሆን አያሰፈልግም፡፡ አዲስ አበባ የአፍ መፍቻ ቋንቋ አማርኛ ነው ያለው ማነው? ወላጆች የአፍ መፍቻ ቋንቋ የሚሉት ካላቸው ልጆችን የት ማስተማር እንዳለባቸው መወሰን ያለባቸው እነርሱ ናቸው፡፡ ከላይ በጠቀስኩት የቴሌቪዝን ፕሮግራም ላይ አንድ የግል ትምህርት ቤት ተወካይ ፈራ ተባ እያለች “የአፋር ልጅ” በምን ይማር? አማርኛ አይችልም ብላለለች፡፡ እኔም እላለሁ በአዲስ አበባ “ሶማሌም” አለ፣ “ኦሮሞ” አለ፣ “ትግሬ” አለ፣ ወዘተ ለምን ሲባል አማርኛ ብቻ እንባላለን፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በግል ትምህርት ቤቶች ተለጠፈ የሚባሉት ማስጠንቀቂያዎችን ይመለከታል፡፡ “አማርኛ መናገርና  …… ያስቀጣል” የሚለው ሲሆን መልዕክቱ በዚህ መልክ ባይለጠፍ ጥሩ ነው፡፡ ልጆቻችን ግን የእንግሊዘኛ ቋንቋ ለማዳበር ያላቸው አንዱና ዋነኛው ቦታ በትምህርት ቤት ውስጥ እንግሊዘኛ ቋንቋን እንዲጠቀሙ በማበረታት/በማስገደድም ነው፡፡ ይህን በጎ ነገር አይቶ ማስጠንቀቂያው እንዲስተካከል ከመምከር ይልቅ ይህንን በመጥፎ ጎኑ በመተረክ የግል ትምህርት ቤቶችን ማሸማቀቅ ምን ያህል ይጠቅማል? ስንት ወላጆች ልጆቻቸው ቋንቋ እንዲለምዱ ቤት ውስጥ መርዳት ይችላሉ? ለማነኛውም ወላጆች በፍፁም ያልተሳሳትነው፤ ነገር ግን የመንግሰት ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ነን ብለው በቴሌቪዥን የቀረቡት ሰዎች እና አቅራቢው ጭምር የተሳሳቱት “እንግሊዘኛ ቋንቋ” ልጆቻችን እንዲማሩ ስንወስን ይህ ችሎታ ለማህበራዊም ሆነ ለተፈጥሮ ሳይንስ አውቀት ለማግኘት መሰረት ሰለሆነ ነው፡፡ በግሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ዩኒቨርስቲዎች የሚያስተምሩት በአማርኛ ቢሆኑ ልጆቼን በአማርኛ ብቻ ለማስተማር፣ በኦሮምኛ ቢሆን ኦሮምኛ ለማስተማር ብዙ ላልቸገረ እችላለሁ፡፡ ግን ልጄ ዓለምአቀፍ እሆናለሁ ሲለኝ በፍፁም አይቻልም ብዬ ልሞግተው አልችልም፡፡ ምርጫ የልጆች ሲሆን ይህን ምርጫ ማገዝ የእኛ የወላጆች መሆኑን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ እስኪ ባለፉት 20 ዓመታት በአፍ መፍቻ ቋንቋ ተምረው ምደርን ያንቀጠቀጡ ልጆች በምሳሌነት አቅርቡልን፡፡
3)  የግል ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ተጨማሪ የመርጃ መፅኃፍት ያቀርባሉ(ከህንድ፣ ከእንግሊዝ፣ ከአሜሪካ ወዘተ)፡፡ በዚህ መስመር የሚታየው ነገር መሰረቱ ምቀኝነት የሚመስል ነው፡፡ በግል እምነቴ ሰታንዳርድ ማለት ዝቅተኛው እንጂ ከዝቅተኛው የሚበልጥ ክልክል ነው ማለት አይመስለኝ፡፡ የግል ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች የሚሰጡት ትምህርት ከተቀመጠው ስታንዳርድ አንሶ ከተገኘ ተጠያቂነት መኖር አለበት፡፡ ከዚያ ከበለጠ ግን ያነሰውን እንዴት ከፍ እናድርግ ከሚለው ሃሳብ ይልቅ እንዴት ከፍ ያለውን የግል ትምህርት ቤት ውጤት እናውርድ አሳፋሪ የሆነ ነገረ ነው፡፡ እያዩ ፈንገስ “ርሃብህ የሚነሳው፣ የጎረቤትህን መጥገብ ሲያይ ከሆነ ርሃብህ ምቀኝነት ነው” ብሎናል፡፡ አሁንም በቅጡ ተጨማሪ የትምህርት መርጃ መፅሃፍት እና ሌሎች ቁሶችን ማቅረብ መከልከል ተገቢ አይደለም፡፡ ወላጆች ልጆቻቸው በመንግሰት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ያነሰ ትምሀርት እያገኙ ተጨንቀው ተጠበው በውድ ዋጋ ያስተምራሉ ማለት የወላጆችን ውሳኔ እና የውሳኔ መስጠት አቅም መናቅ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ በጣም የሚያስገርመው የትምህርት ቢሮ ተወካይ፣ ሃላፊ ሆነው የሚፎክሩብን ሰዎች አለቆቻቸው ልጆቻቸውን የት እንደሚያስተምሩ የማያውቁ ይመስላል፡፡ ከዚህ አንፃር በመግቢያዬ ላይ ያቀረብኩ ጥያቄ ለትምህርት ቢሮ ሃላፊም ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ክብሩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የትምህርት ቢሮ ሃላፊ ልጆን የትኛው የመንግሰት ትምህርት ቤት እንደሚልኩ ቢነግሩን?
4)  የግል ትምሀርት ቤቶች በአብዛኛው በዲግሪ ደረጃ የተመረቁ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ለትምሀርት ጥረት ወሳኝ ግብዓት ነው፡፡ የመምህራን ጥራት በተመለከተ ትምህርት ቢሮ መምህራን በሙሉ ከመምህራን ማስልጠኛ መውጣት አለባቸው ይላል፡፡ በሀገራችን መመህራን ማስልጠኛ የሚገቡት በትምህርት ውጤታቸው በምን ዓይነት ደረጃ ያሉት እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ እነዚህ መምህራን በሌሎች ዮኒቨርሲት ከሚመረቁት ምሩቃን በተወሰኑ የፔዳጎጂ ትምህርት ልዩነት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ይህን ክፍተት በአጭር ጊዜ ስልጠና በመሙላለት ምሩቃኑን አስተማሪ ማድረግ ግን ይቻላል፡፡ ለዚህ ትክክለኛ ማሳያው በዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ውጤት የሚያመጡ (ሰቃይ) ተማሪዎች በአስተማሪነት አይሰለጥኑም ነገር ግን ዩኒቨርስቲ በአስተማሪነት አሰቀርቶ አስተማሪ ያደርጋቸውል፡፡ በዩኒቨርሲት እያሰተማሩ ሌላ ቦታ ማስተማር አይችሉም ማለት ሰህተት ነው፡፡ እነዚህን ተመራቂዎች በተወሰነ ደረጃ ማስልጠን ያስፈልጋል በሚለው መስማማት ይቻላል፡፡
5)  በግል ትምህርት ቤቶች የሚማሩ በአንድ ክፍል የሚገኙ ሁሉም ተማሪዎች ተመሳሳይ ትምሀርት መማራቸውን ለመከታተል የሚረዳ እና ተከታታይ ምዘና ለማድረግ የሚያግዝ ወርክ ሽቶች በየዕለቱ ያገኛሉ፡፡ ወላቸጆችም ይህን ለመከታተል የሚችሉበት አስራር አለ፡፡ ይህ አስራር ለተማሪዎች እጅግ ጠቃሚ የማጥኛ ዘዴም ጭምር ነው፡፡ ይህ በወላጆች ተሳትፎም ቢሆን በመንግሰት ትምህርት ቤቶች ቢተገበር እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ይህን ማንም ሲቃወም አላያሁም ግን ወደ መንግሰት ትምህርት ቤት እንዴት ይምጣ ? የሚለው ሲነሳ አልሰማሁም፡፡
6)  በግል ትምህርት ቤቶች እሰከ አሁን ባለኝ መረጃ በአንድ ክፍል ውስጥ ከ30 ተማሪ በላይ የለም፡፡ ይህ መምህሩ ተማሪዎቹን ለመከታተል እና ለመርዳት ያግዘዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ረዳት መምህራን አሉ፡፡ በመንግሰት ትምህርት ቤት እሰከ አሁን ያልተሳካው በክፍል 50 ተማሪ ማድረግ ነው፡፡ ይህ በመምህሩ ላይ የሚፈጥረው ጫና እንደተጠበቀ ሆኖ ለክትትልም አይመችም፡፡
7)  በግል ትምህርት ቤቶች ተማሪ ከትምህርት ቤት በፍፁም መቅረት አይቻለም፡፡ ታሞ የቀረ የህከምና ማስረጃ ማቅረብ ግዴታ ሲሆን ወላጆች የልጃቸውን ከትምህርት ቤት መቅረቱን በእለቱ በስልክ ተደውሎ ምክንያት ይጠየቃሉ፡፡ ይህ ክትትል ልጆች በመሃል አልባሌ ቦታ እንዳይውሉ ያግዛል፡፡ በተደጋጋሚ የሚቀር ተማሪ ከትምህርት ቤቱ ይባረራል፡፡ ሰለሚከፍል ተብሎ ትምህርት ቤት አይቆይም ይህ ክትትል መቼም በመንግሰት ትምህርት ቤት ለማድረግ የሰልክ በጀት ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡

ከላይ የዘረዘርኳቸው ነጥቦች በጎ በጎዎች ናቸው፡፡ ብዙ ችግሮች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ወደዚያ ዝርዝር ያልገባሁት የፕሮግራም አቅራቢዎች በበቂ ለመክሰሻነት ያቀረቡት በመሆኑ ነው፡፡ እዚህ ግን መነሳት ያለበት የግል ትምሀርት ቤቶች እጅግ አሳሳቢ የሆነ የቦታ ችግር አለባቸው፡፡ ሰፊ ቦታ ለማግኘት አጅግ ውድ የሆነ የቤት ኪራይ መክፈል ስለሚኖርባቸው የትምህርት ክፍያዎች በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከመክፈል አቅም በላይ እየሆኑ ሲሆን ወላጆች ይህን ለማሟላት ሲሉ በከፍተኛ ጭንቀት ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ መንግሰት የምር ለዜጎች ጭንቅና ለአዲሱ ትውልድ መፍትሔ ለማምጣት የሚጨነቅ ከሆነ ለመንገሰት ትምህርት ቤቶች እንደሚያደርገው ሁሉ ለግል ትምህርት ቤቶችም በዝቅተኛ ዋጋ ወይም ደግሞ በነፃ የትምህርት ቤት መገንቢያ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ለምሳሌ በነፃ ለትምህርት ቤት ግንባታ የተሰጠ ቦታ በምንም መልኩ ወደሌላ ቢዝነስ የማይለወጥ እንዲሆን የሚያስችል ህግ ሊያወጣ ይችላል፡፡ ከዚህም በላይ በነፃ ቦታ ያገኙ የግል ትምሀርት ቤቶች የተወሰኑ ተማሪዎችን ከዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍል በነፃ እንዲያስተምሩ ሊያስገድድ ይችላል፡፡ ይህ መንግሰት በእጁ ያለ የግል ዘርፉን ሊያግዝበት የሚችልበት ነው፡፡ ተመቸኝ ብሎ በቴሌቨዠን ቀርቦ ግን ተገቢ ያልሆነ ክስ መስጠት ግን ብዙ ጥቅም የለውም፡፡ አሁን በግል ትምህርት ቤቶች ላይ የተያዘው ዘመቻ በምንም መልኩ የመንግሰት ትምህርት ቤቶችን አያጠናክርም፡፡ ይልቁንም ወላጆች በመንግሰት ቁጥጥር ወደማይደረግባቸው “ኮሚኒቲ” ትምህርት ቤቶች እንዲያዘነብሎ፣ ካልሆነም ውጭ ልከው እንዲያስተምሩ ከመገፋፋት ውጭ ትርፍ የሚኖረው አይደለም፡፡ ለማነኛውም ሁላችንም የመንግሰት ትምህርት ቤቶች እንዲት ወደ ግል ትምህርት ቤቶች የጥራት ደረጃ ይድረሱ ለሚለው ጠጠር ብንወረውር የተሻለ ነው፡፡ የግሎቹን እንዴት ወደ መንግሰት ትምህርት ቤቶች ደረጃ እናውርዳቸው ከማለት ይልቅ፡፡

Tuesday, July 5, 2016

ኮንዶሚኒየም፣ የዜጎች መኖሪያ ቤት ጉዳይ እና ፖለቲካ



አንድ ጊዜ አሜሪካን ሀገር በነበረ ስብሰባ ኮንዶሚኒየም ቤት ለማግኘት የተመዘገበው በውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ትክክል እንዳልሆነ ትንሽ ጠንከር ያለ ሃሳብ ሰጠው፡፡ በቂ ምክንያት ነበረኝ፣ አሁንም ልክ እንደሆንኩ ይስማኛል፡፡ ኮንዶሚኒየም የሚሰረው በመንግሰት ልዩ ድጋፍ “ለድሆች” በሚል ነበር፡፡ ነበር ያልኩት እየገቡ ያሉት እንማን እንደሆኑ በብዛት ስለሚታወቅ ነው፡፡ ስለዚ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ በአንፃራዊነት የተሻሉ ናቸው፡፡ ሰለዚህ በዚህ ውድድር ውስጥ መግባት የለባቸውም የሚለው አንዱ ለሰጠሁት ሃሳብ መነሻ ሲሆን፡፡ ዋነኛውም ግን መንግሰት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን/ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለማገዝ ፈልጎ ሳይሆን በዚሁ መስመር የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ነው፡፡ የሚሉ ሃሳቦች ነበሩኝ፡፡ ነገር ግን ሁሉም ከእውነቱ እና ከቀረበው አምክንዮ ይልቅ የግል ጥቅሙ በልጦበት እጅጉን ቅር ተሰኘ፡፡ ድሮም እኔ በውሸት ለማስደስት ሰለአልተዘጋጀሁ በግሌ ደስ አለኝ፡፡ ተዋወቅን ብል ነው ደስ የሚለኝ፡፡ ይህን አስመልክቶ በግል እንዲህ ዓይነት አቋም አትያዝ ውጭ ያሉት ሰዎች ቅር ይላቸዋል፣ ድጋፍም አይሰጡህም የሚሉ ምክር አዘል መልዕክቶች ደርሰውኛል፡፡ እውነቱ ግን ይህው ነበር፡፡ በግሌ የተለየ ድጋፍ ሰለማልፈልግ እውነቱን መናገር ምርጫያ ነበር፡፡
ሰሞኑን ደግሞ በሀገር ውስጥ ያሉ በመንግሰት ፍርጃ “ጥቅመኞች፣የኒዎ ሊብራል አቀንቃኞች፣ ወዘተ” የሚባሉት የእኔ ቢጤዎች ኮንዶሚኒየም ቤት ለማግኘት በ40/60 ቤት ተሰርቶ እንደሚሰጣቸው እንዲሁም በማህበር ተደራጅተው ሃምሳ ከመቶ (50/50) የግንባታ ወጪ በዝግ ሂስባ ካስቀመጡ በከተማው መሃል ለልማት ከሚነሱት ቦታዎች ቦታ ይሰጣችኋል ተብለው እጅግ ብዙ ገንዘብ እንዲቆጥቡ አማላይ ሃሳብ ቀረቦላቸው ተግባራዊ ሲያደርጉ ነበር፡፡
አብዛኛው ያለምንም ማንገራገር የመንግሰትን መግለጫ ሰምቶ ቁጠባ ጀመረ- ቁጠባ ከሚባል ያለውን ጥሪት ተበድሮ ጭምር ወደ ንግድ ባንክ አዞረ ማለት ይቀላል፡፡ በእሩጫ ውድድር አሯሯጭ እንደሚመደበው አንድ አሯሯጭ ዜናም አብሮ ቀረበ፤ “ቀድሞ ሙሉ የከፈለ ቅድሚያ ያገኛል” የሚል ወሬ ሚዲያውን ጨምሮ በልዩ ልዩ መስመር ተወራ፡፡ በእውነትም በአስር ሺዎች ሙሉ በሙሉ ከፈሉ፡፡ ለመክፈል ያልቻሉም የቻሉትን ያህል ለመክፈል ተረባረቡ፤ በተለይ አርባ ከመቶ ለማሟላት የሚችሉትን ሁሉ አደረጉ፡፡ አብዮታዊው ዲሞክራሲው መንግሰታችን “የእነዚህን ጥቅመኞች እና የኒዎ ሊብራሎችን” ገንዘብ ሰብሰቦ በእጁ አስገባ፡፡ በእጅ አዙር በቁጥጥር ስር አዋላቸው ነው መባል ያለበት፡፡
መንግሰት ገንዘቡን ለመሰለውና ለፖለቲካ ጥቅሜ ያዋጣኛል ባለው መስመር ተጠቀመበት፡፡ ይህን እውነት ከማመን ይልቅ ሁለት ሺ ለማይሞላ ቤት አሰር ሺዎች ይራኮታሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚ መንግሰት በሚቀጥሉትም አምስት አመታት ቤት ሰርቶ እንደማያስረክብ የታመነ ነው፡፡ ለምሳሌ ባለፉ አስር ዓመታት መንግሰት መገንባት የቻለው 175 ሺ የማይበልጥ ሲሆን በቀጣይ አምስት ዓመታት የታቀደው ደግሞ 450 ሺ ቤት ለመገንባት ነው፡፡ እንደምታውቁት ፉከራ ነው፡፡ በመጨረሻው ልምድ አግኝተንበታል ነው የምንባል፡፡ ሚሊዮኖች ተመዝግበው እየጠበቁ ሌሎች ሚሊዮኖች ደግሞ የቤት ፈላጊ ሆነው በዚህ መስመር ቤት አገኛለሁ ማለት የእልም እንጀራ ይመስለኛል፡፡ ጥቂቶች ቤት አያገኙም እያልኩ እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ውጤቱን ግን ወደፊት እናየዋለን፡፡
በነገራችን ላይ መንግሰት ይህን ማድረግ የማይችል መሆኑን በደንብ ተረድተው በሪል ሰቴት ልማት ውስጥ የሚሰማሩ ኢንቨሰተሮችን በሆነው ባልሆነ እንዳይሳካላቸው መንገድ የሚዘገው መንግሰት መሆኑን ብዙዎች አይረዱም፡፡ ይልቁንም ከቤት አልሚዎች ጋር ከመንግሰት ጋር ተባብረው ፈጣሪ ኢንቨሰተሮችን ያዋክባሉ፡፡ ይሰቀል፣ በድንጋይ ይወገሩ የሚሉ ሞልተዋል፡፡ መንግሰት በዚህ ጊዜ ደግሞ ቤት እንዲያገኙ ፍላጎት እንዳለው መስሎ ቀርቦ ድብቅ ተልዕኮውን ያሳካል፡፡ መንግሰት ይህን የሚያደርገው የግል አልሚዎች በተሻለ መፈፀም ከቻሉ መሰታውት ሆነው እንደሚያጋልጡት ስለሚረዳ ነው፡፡ ቀደም ሲል የመሬት ዋጋ በማሰወደድ የግል አልሚዎችን ማሰወጣት በቂ ነው በሚል እየሰራ የነበረ ሲሆን፣ ይህ ግን በቂ አለመሆኑን በመረዳት በአሁኑ ጊዜ የግል አልሚዎች በፍፁም እንዳይሳካላቸው እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህን ለመመልከት ግን በፍፁም ከግል ጥቅማችን እና ጉዳታችን ወጥተን ጉዳዩን በእውነት ለመመልከት ስንወሰን የሚገባን ሚስጥር ነው፡፡
መንግሰት ለቤት አልሚዎች መሬት በነፃ ሰጥቶ አልሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ቤት እንዲያቀርቡ ለምን አይደራደርም? ይህማ የኒዎ ሊብራል አስተሳሰብ ነው፡፡ መንግሰት የእኔ ነው በሚለው መሬት ግለሰቦች ሊከብሩበት የሚል የምቀኛ አስተሳሰብ በውሰጣችን አለ፡፡ መንግሰት ይህን እየኮተኮተ ያሳድጋል፡፡ እኛ ከስር ከስር ውሃ እናጠጣለን፡፡ ተቃቅፈን በድህነት የመንግሰት ጥገኛ ሆነን እንኖራለን፡፡ መንግሰትም የሚፈልገው ሁላችንንም ግቡ-ውጡ በሚለን መስመር እንድንገኝ ነው፡፡ የምርጫ ሰሞን ኮንዶሚኒየም ጊቢዎች ውስጥ ያለውን ውክቢያና ጥርነፈ የተመለከተ ነፃነቱን በገንዘቡ አሳልፎ እንደሰጠ ይረዳል፡፡ ኮንዶሚኒየም ቤት ደርሶት ያከራየ ሁሉ ተከራይም ኢህአዴግን መምረጥ እንዳለበት ማሳሰቢያ የሚሰጡበት ወቅት ነው፡፡
በነገራችን ላይ በዚህ አጋጣሚ የአያት የመኖሪያ መንደር መስራች በግሌ በግፍ እንደተሰቃዩ ይሰማኛል፡፡ ባደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በሀገራችን የቤት ልማት ውስጥ ማንም በሸፍፅ የማይሽርው አሻራ አኑረዋል፡፡ እጅግ ብዙዎችን ባለቤት/ባለሀገር አድርገዋል፡፡ ይህን የሚያክል የከተማ ክፍል ሲገነቡ ምንም ስህተት አልሰሩም ብዬ መከራከር የምችልበት መረጃ ባይኖረኝም፣ መንግሰት ይህን የሚያክል ከተማ ክፍል የመገንባት ሰራ ቢሰራ ሊያጠፋ የሚቸለውን ሳሰበው ይዘገንነኛል፡፡ ሰራ እና ሃሳብ ፈጣሪዎቻችንን ከመሸለም እና እውቅና ከመስጠት ይልቅ ወህኒ ማውረድ በፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ ክብር ለሚገባው ክብር እንስጥ!!!!
ቸር ይግጠመን!!!!