Tuesday, November 8, 2016

የስርዓት ለውጥ በስርዓት



የሰሞኑን የካቢኔ ሹመት አስመልክቶ ብዙ አስተያየት እየተሰጠ ነው፡፡ አሰተያየት መስጠቱ ትክክል ነው፡፡ በህይወታችን ላይ ከፋም-ለማም ውሳኔ የሚያሳልፉ ሰዎች ምደባ በመሆኑ የመሰለንን አስተያየት መሰንዘር ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በእኔ እምነት ኢህአዴግ ባልሆንን ሰዎች ፣በተለይ ደግሞ የተሻለ አማራጭ ይታየናል፣ አለንም ለምንል ዜጎች ዋናው ጉዳይ የኢህአዴግ ፖሊሲ በምን ዓይነት ካቢኔ በደንብ ተግባራዊ እንደሚሆን መምከር አይመስለኝም፡፡ እኛ በእጃቸን ያለውን አማራጭ ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ የምንችልበት የፖለቲካ ምዕዳር መመቻቸት ጉዳይ ነው የእኛ ጥያቄ መሆን ያለበት፡፡ በእግረ መንገድም ኢህአዴግ ፖሊሲውን እንዲፈፅሙ የተመደቡት ሰዎች መስመር ሲስቱ ማጋለጥ ዋነኛ ተግባራችን ነው፡፡ ብዙዎች እንደሚጠብቁት ፖሊሲዎቹ ያላቸውን በጎ ጎን እየጠቀሱ ኢህአዴግን ማወደስ፣ በአንዳንዶቹ አባባል እውቅና መስጠትም ሃላፊነታችንም ግዴታችንም አይደለም፡፡ ይህን አስተያየት በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንደ ዜጋ በጋራ መቆም ከሚለው መርዕ ጋር ማምታታት በፍፁም ተገቢ ካለመሆኑም በላይ ለኢህአዴግ ተደጋጋሚ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ መሆንን ነው የሚያመለክተው፡፡
አንድ አንድ ሰዎች አሁን በሹመት ወደ ሃላፊነት የመጡት ሰዎች በብዛት አዲስ አድርገው ይገምታሉ (ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከዘጠኙ በስተቀር በሚል አሳሳች መልዕክት እንዳሰቀመጡ ሳንዘነጋ)፡፡ በቁጥር ሁለት ሲበዛ ሶሰት ከሚሆኑት ውጭ የኢህአዴግን ፓርቲ መታወቂያ ከመውሰድ በስተቀር ከጳጳሱ በላይ ካቶሊክ ለመሆን የሚሞክሩ፣ በነበሩበት ተቋም በተገቢ ሁኔታ ኢህአዴግን አሁን ለደረሰበት ውድቀት የዳረጉ ጭምር ናቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ በዝርዝር መግባት ተገቢ አይደለም፡፡ እነዚህ ሹመኞች ደግሞ አሁን ባለው ሁኔታ የፖለቲካ ስልጣን የላቸውም፡፡ ያለ ፖለቲካ ስልጣን የሚኒሰትርነት ቦታ በፖለቲካ አቋም በየመስሪያ ቤቱ ከሚገኙ የፖለቲካ ምድብተኞች ጋራ ለመጋጨት ካልሆነ ትርጉሙ አይታየኝም፡፡ ደርግ በመጨረሻ ዘመኑ የክልል አስተዳደሪዎቹን በተለያየ ዘርፍ ትምህርት የቀመሱ በዘርፋቸው ምርጥ የተባሉ ምሁራንን አድርጎ ነበር፡፡ የዚህ ሹመት ውጤት የሆነው ከኢሠፓ ሹሞች ጋር የዕለት-ከዕለት ግጭት ነበር፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ ፓርቲ መሪ ስለሆነ እነዚህ “አዲስ ተብዬ” ሹሞቾ የፓርቲ መመሪያ ሲጠብቁ ሰራ ተገተሮ እንዳይቀር ስጋት አለኝ፡፡
እነዚህን ሹሞች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በድፍረት ጥያቄ ሊጠይቋቸው ይችላሉ፡፡ በፓርቲ ውስጥ አለቃ ስለአልሆኑ፣ ጠብ እርግፍ አድርገው ሊያብጠለጥሏቸው ይችላሉ፡፡ ወይም ጥፋት ካጠፉ ወደ ዘብጥያ ለማውረድ የፓርቲ ግምገማና አቋም ላይጠየቅላቸው ይችላል፡፡ በዚህ ሁኔታ አሁን ያሉት ሚኒሰትሮች አንዳንዶቹ ሚኒሰትሮች (እነ ወርቅነህ፣ ደብረፅዮን፣ የመሳሰሉት) ከፖለቲካ ጡንቻ ጋር ሲሆኑ የተቀሩት ይህን ዋና የፖለቲካ ጉልበት ባለመያዝ ነው በአንድ መድረክ የተገናኙት፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ጡንቻ ያላቸው ሚኒሰትሮች ደግሞ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ እንደነገሩን በሲኒየር ሚኒስትርነት በውስጠ ዘ- ምክርና መመሪያ የሚሰጡ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ዘለል ባለ መስመር የሚሄድ ሚነሰትር ካለ ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡ ለምሣሌ የአሁኑ የመንግሰት ኮሚኒኬሼን ሚኒስትር ማድረግ ያለባቸው በመዝገብ ታሸጎ ፈቃድ የተከለከሉ ጋዜጠኞች ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ፣ በሽመልስ ከማልና አለቆቹ ትዕዛዝ ወህኒ እንዲወርዱ፣ በየፍርድ ቤቱ የሚንከራተቱ ጋዜጠኞች ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ ከግምት በማስገባት ከእስር በመፍታት፣ የፍርድ ቤት ምልልሱን በማቋረጥ የሚዲያ ምእዳሩን ክፍት እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ይህን ካልቻሉ እስኪባረሩ ሳይጠብቁ ምክንያታቸውን ለህዝብ ገልፀው ከሹመት መልቀቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ከላይ እስከ ታች የተንቀሳቀሰው ዶ/ር ቴዎድሮስ አደሃኖም፣ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ፣ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ ወ/ሮ ዘነቡ ታደሠ፣ ኦቶ መኩሪያ ሀይሌ ወዘተ … ከስልጣን ይውረዱልን የሚል ጥያቄ አንስቶ አይደለም፡፡ በመስረታዊነት እነዚህ ሰዎች የኢትዮጵያን ፖለቲካ ምዕዳር ለማፈን ያላቸው ሚና ዜሮ ነው፡፡ የአንድ አንዶቹ ሚና ከተላላኪነት የሚዘልም አይደለም፡፡ የእነዚህ ሚኒሰትሮች ከስልጣን ተነስቶ እዚህም እዚያም ስርዓቱን ሲያገለግሉ በነበሩ ቴክኖክራቶች በመተካት የሀገራቸውን ኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ አያመጣም፡፡ ከቴክኖክራት ሚኒሰትሮች የሚጠበቀው የቴክኒክ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱ ህዝብ የሚጠብቀውን የፖለቲካ ሪፎርም እንዲመጣ ማድረግ ነው፡፡ ይህን ማድረግ አቅም አላቸው ወይ? ብለን ስንጠይቅ ጥርጣሬ እንደሚያጭር እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ አዲስ ሹሞች የፖለቲካ ስልጣን የላቸውም፡፡ በኢህአዴግ ቤት ደግሞ ስልጣን ያለው ፓርቲ ነው፡፡ ከፓርቲም በህውሃት እጅ ነው፡፡ በአማራም በኦሮሚያም የነበረው እንቅስቀሴ ውስጥ ጎልቶ የወጣው የአንድ ፓርቲ/የህወሃተ የበላይነት ይቁም የሚለው ነው፡፡ ይህን ምላሽ በሚሰጥ መልኩ ምለሽ አልተሰጠም፡፡
በመግቢያዬ ላይ እንዳልኩት ኢህአዴግ የፈለገውን ካቢኔ ሚኒሰትር የመሾም መብት አለው፡፡ በኢትዮጵያችን የተፈጠረው ችግር በኢህአዴግ ካቢኔ የሞያ ሰብጥር ምክንያት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ችግር የፖለቲካ ምዕዳሩ ኢሕአዴግና ለኢህአዴግ ለገበሩ ብቻ በሚሆን መልኩ የተደረጃ መሆኑ ነው፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ መንግሰት ከሚፈልገው ውጭ መናገርም ሆነ መስራት በመከልከሉ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በህገ መንግሰት በግለፅ የተደነገገን የመደራጀት መብትን፣ ተደራጅቶም ሃሳብን የማቅረብ መብትን መተገበር ባለመቻሉ ነው፡፡ በኢትዮጵያችን የመንግስት ተቋማት ዜጎችን አገልግሎት የሚሰጡት በህግ አግባብ ሳይሆን የየትኛው ብሔር አባል ነው በሚል መመዘኛ መሆኑ ነው፡፡ በኢትዮጵያችን መንግሰት የሚባው አካል ተጠያቂ ያለመሆን ብቻ ሳይሆን ማንነታቸው የማይታወቅ አካላት የተለያዩ የመንግሰት ተቋማት በስውር ያዛሉ፡፡ የሚጠሉትን ፓርቲ ከህግ አግባብ ውጭ ያፈርሳሉ፡፡  የግል አግልግሎት መስጫዎችን፣ ማተሚያ ቤቶችን በስልክና በግንባር እየቀረቡ ያስፈራራሉ፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ የደንብ ልብስ የለበስ ፖሊስ አባላት ከነ ማዕረጋቸው ማንነቱ ያልታወቀ ሰው ዜጎችን ለማፈን ሲሞክር መታወቂያ መጠየቅ የማይቻልባት ሀገር ነች፡፡ ስንቱን ዘርዝሮ ይቻላል፡፡ ይህን ችግሩን የሚያሰማበት መድረክ ያጣ ህዝብ በብሶት ተነሳስቶ የዜጎች ህይወትና ንብረት እንዲወድም አድርጎዋል፡፡ ይህ ውድመት የአፈና ውጤት ነው፡፡ አፈናን በማፈን ማስታገስ ደግሞ አይቻለም፡፡
አሁንም በሀገራችን የስርዓት ለውጥ በስርዓት እንዲመጣ ፍላጎት ብዙዎች አለን፡፡ ፍላጎት በራሱ ግን በቂ አይደለም፡፡ በእኔ እምነት ስርዓት በሌለው ሁኔታ ለውጥ እንዲመጣ ከማንም በላይ ፍላጎት እያሳዩ ያሉት መንግሰት እና ገዢው ፓርቲ ናቸው፡፡ መንግሰት በስርዓት ለውጥ እንዲመጣ የመሪነቱን ሚና መጫወት ይኖርበታል፡፡ በቅድሚያ ማነኛውም ከመንግሰት ጋር ያልተግባባ ኃይል ከመፈረጅ መታቀብ አለበት፡፡ በዋና ዋና የሀገር ዕልውና ላይ የማይደረዳሩ መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ ማድረግ የሚከለክል አስራር ሊዘረጋ ይችላል፡፡ ከዚህ በመለስ ኢህአዴግ እራሱን “በጥልቅ ማደስም ይሁን አፍርሶ መስራት”  የራሱ የቤት ስራ ሲሆን “መንግሰት” በግልፅ ከፓርቲው መለየቱን ለማስመስከር ባለበት ሃላፊነት ኢህአዴግን አውራ ፓርቲ የማድረግ ተግባሩን በማቆም በሀገራቸን የሃሳብ ልዮነትን መስረት ያደረጉ ፓርቲዎች ምድር እንድትሆን ለማድረግ ቁርጠኛ እርምጃ መውስድ ይኖርበታል፡፡ ከእነዚህም ዋና ዋናዎቹ
·         በኢትዮጵያ ውስጥ የሚጀመረውን የፖለቲካ ሪፎርም ሊመራ የሚችል ኮሚሽን በማቋቋም በሀገሪቱ ያሉት ችግሮች ደረጃ በደረጃ በውይይት የሚፈታበትን ተግባር እንዲያከናውን ስልጣን መስጠት፣ ይህን ሃላፊነት የሚወስድ ማነኛውም ሰው በሁሉም ወገኖች ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ማድረግ፡፡ ፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲስ መልክ እንዲደራጁ መፍቀድ፣ ሚዲያ በነፃነት እንዲሰሩ መፍቀድና ማገዝ፣ ህዝቡ የመስለውን የፖለቲካ አቋም እንዲያራምድና እንዲደግፍ ማበረታታትና ማገዝ፣
·         በማነኛውም ሁኔታ ከመንግሰት መዋቅር ውጭ መመሪያ የሚሰጡና የሚያስተገብሩ አካላትን ድርጊት በግልፅ ማስቆም (ለምሳሌ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር መስሪያ ቤትን በሚኒስተርነት ደረጃ ለማቋቋም የተጀመረውን ስራ ማጠናቀቅ ተጠያቂ የሆነ የደህንነት ጉዳዮች ሚኒስትር በይፋ መሾም)፣ኢትዮጵያዊ ደህንነት መስሪያ ቤት ማቋቋም፤
·         ከሃያ አምስት ዓመት በኋላም በመከላከያ ውስጥ የሚታየውን ያልተመጣጠነ የሃላፊነት ቦታ ምደባን ለማስተካከል አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ፡፡ ብቃትን መሰረት ያደረግ ምደባ በማድረግ ተሰናባቾችን በክብር ማስናበት፡፡
የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ እነዚህ እርምጃዎች መላው የሀገራቸን ዜጎች በህጋዊ መንገድ ድምፁን ለማሰማት እድል የሚፈጥሩ ስለሆነ ከግብታዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴ የሚገታው ይሆናሉ፡፡ የሚወሰዱት ተግባራዊ የፖለቲካ ምዕዳር የማስፋት እርምጃዎች ለቀጣይ በተረጋጋ ሁኔታ በሀገር ፍቅር ሰሜት እና በባለ ሀገርነት ሰሜት በነፃነት የእለት ተግባሩን ከማከናወን በዘለለ፣ ከፍ ወደሚል ሀገራዊ ሃላፊነት ሰሜት እንዲያድግ ያግዘዋል፡፡
ነፃነት ባለበት ዲሞክራሲ ያብባል፡፡ ይህን ጊዜ ዘላቂ ሰላምና እድገት ለትውልድ ይተላለፋል፡፡ ለዚህ ሲባል ገዢው ፓርቲ/መንግሰት አሁን ያላቸውን ህገወጥ ቁርኝት በመለየት ፓርቲውም እንደ ፓርቲ መንግሰትም እንደ መንግሰት ሃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ በምንም ሁኔታ የመንግሰት ስልጣን ገዢውን ፓርቲ በተለይ ሁኔታ መጥቀም አይኖርበትም፡፡ የካቢኔ ሽግሽግ የፓርቲው ጉዳይ ነው፡፡ በስርዓት የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ ትክክለኛውን እርምጃ በትክክለኛው ጊዜ መውሰድ ይኖርብናል፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራችን እና ህዝቧን እግዝአብሔር በበረከቱ ይጎብኝልን!!!!
ቸር ይግጠመን!!!