Saturday, April 12, 2014

ኢህአዴግ፣ ምርጫ እና አማራጭ ፓርቲዎች




ግርማ ሠይፉ ማሩ
ባለፈው ፅሁፌ በሀገራችን ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንድ እጅ ጣት ቁጥር ከማይሞሉት ውጭ ያሉት እንዲሁም ምርጫ ቦርድ ተገፍተው እንኳን ለመነሳት ባትሪያቸውን የጨረሱ እንደሆነ ለማሳየት ሞክሬ ነበር፡፡ ይህን ሀሳብ የሚያጠናክር ዜና በጋዜጣ ላይ አነበብኩኝ እና ድጋሚ ስለ ኢህአዴግ፣ ምርጫ እና አማራጭ ፓርቲዎች ግንኙነት ለመፃፍ ወሰንኩ፡፡ ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነው የምርጫ ስነ ምግባር ደንብ የፈረሙ አና በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የሆኑ ፓርቲዎች ኢህአዴግ (ልብ በሉ መንግሰት አላሉም) ከዚህ በፊት ሲሰጣቸው የነበረውን ብር አንድ ሚሊዮን ድጋፍ ወደ ብር ሁለት ሚሊዮን ሊያሳድገው እንደሆነ ነገር ግን እነርሱ ምርጫ ለመሳተፍ ዝግጅት እንዲረዳቸው ወደ ብር አራት ሚሊዮን እንዲያሳድግላቸው ፍላጎታቸው መሆኑን፤ ይህን ጥያቄም በቀጣይ የጋራ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ እንደሚያነሱት ገለፁ የሚል ዘገባ ማንበቤ ነው፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲች ገዢውን ፓርቲ ገንዘብ ጠየቁ የሚለው ፌዝ መሳይ እውነት ለብዙ ሰው እንዲገባ በእግር ኳስ ምሳሌ ማስረዳት ጥሩ ነው፡፡ አቶ ሀይማሪያም ደሳለኝ የክልል ርዕስ መስተዳደር በነበሩ ጊዜ ለክልል ምክር ቤት አባላት ምርጫን በእግር ኳስ ምሳሌ ሲያስረዱ፤ ከከንባታ ዞን፣ ከአንጋጫ ወረዳ የተወከለ ተቃዋሚ አይደለም በሩጫ ይሁን ብሎ ተሰብሳቢውን አሰቆ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ እኔ በእግር ኳስ ላስረዳ የእንግሊዝ ጫወታ ለሚወድ ማንችስተር ሲቲ ወይም ማንችስተር ዩናይትድ ተቀናቃኛቸው አርሴናል ዋናጫ መብላት ስለተቸገረ ቡድኑን ለማጠናከርና ለዋንጫ እንዲበቃ ማሊያ እና ጠንከር ያሉ አዳዲስ ተጫዋቾች መግዣ ብለው ገንዘብ እንደመስጠት የሚቆጠር ነው፡፡ ወይም በሀገራችን ጊዮርጊስ ቡናን ለማጠናከር የገንዘብ ድጋፍ እንደማድረግ ነው፡፡ የልምድ ልውውጥ እንዳይመስላችሁ ጊዮርጊስ ብዙ ዋንጫ ስለበላ በአዘኔታ ቡና ዋንጫ እንዲያገኝ ለማገዝ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ስላቅ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ነብስ ዘርቶ ነው ያለው፡፡
ለነገሩ እነዚህ ፓርቲዎች በኢህአዴግ ተቆራጭ እየተደረገላቸው የሚቆሙ በመሆናቸው ለወጉ ነው እንጂ አማራጭ ናቸው ብለን የምናስባቸው አይደሉም፡፡ እነዚህ ፓርቲዎቸ ከኢህደዴግ ሀጋር ድርጅቶች የሚለያቸው የአብዮታዊና ልማታዊ መንግሰት ፍልስፍና ተቀብለናል ብለው በኢህአዴግ ፕሮግራም ነው የምንመራው ያለማለታቸው ነው፡፡ ከዚህ በሰተቀር በሚባል ደረጃ የፓርቲያቸው ፕሮግራም ስለመኖሩ አይታወቅም እና አማራጭ አላቸው ብለን እኛም አናምንም ህዝቡም በዚህ ጉዳይ አይጠረጥራቸውም፡፡ ሁሌም እንደምለው የእነዚህ ፓርቲዎች መኖር በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ለማገዝ ሳይሆን ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ብዙ ፓርቲዎች አሉ ለማስባል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ገዢው ፓርቲ ለረዥም ጊዜ ያለተቀናቃኝ በስልጣን ለመቆየት ያስቀመጠውን ዕቅድ ለማሳካት ጭምር የሚጠቀምበት ነው፡፡ አማራጭ እንዲሆኑ የሚጠበቅባቸው ፓርቲዎች በተቃራኒው ቆመው ሀገር አማራጭ ያሳጣሉ፡፡
ይህ ተግባር የሞራልና የመርዕ ጥሰት ብቻ ሳይሆን ህገወጥ ድርጊት ነው፡፡ ኢህአዴግ ለእነዚህ ፓርቲዎች የሚያድለውን ገንዘብ የሚያገኘው ከመንግሰት ካዝና ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ዓመት ለምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት መሰረት ለፓርቲዎች የሚሰጠው ድጋፍ በክልልና በፌዴራል ምክር ቤቶች ባገኙት መቀመጫ መሰረት በመሆኑ እነዚህ በፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የሆኑ ፓርቲዎች ደግሞ መቀመጫ ስለሌላቸው ገንዘቡን በሙሉ ጠቅልለው የወሰዱት ኢህአዴግና አጋሮቹ መሆናቸው አስታውቆዋል፡፡ ኢህአዴግ ግን በዚህ መሰረት ያገኘውን ገንዘብ በቸርነቱ ለነዚህ ፓርቲዎች እንዲታደል አድርጎዋል፡፡ ለዚህም ምርጫ ቦርድ ትብብር ማድረጉን በአደባባይ አምኖዋል፡፡
የመጀመሪያው ህገወጥ ተግባር ኢህአዴግ እንዲጠቀምበተ ከመንግሰት ካዝና በምርጫ ቦርድ በኩል የተሰጠውን ገንዘብ ለሌሎች ፓርቲዎች አሳልፉ የሚስጥበት አንድም የህግ አግባብ የለም፡፡ ለምሳሌ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ከመንግሰት የተመደበለትን በጀት ለክልል ጤና ቢሮ ወይም ለትምህርት ሚኒስትር አሳልፎ መስጠት አይችልም፡፡ ካልተጠቀመበት ወደ መንግሰት ካዝና መመለስ ብቻ ነው ያለው አማራጭ፡፡ ይህን ድርጊት ለምርጫ ቦርድ ሃላፊው ፕሮፌሰር መርጊያ በቃና የተነገራቸው ቢሆንም አሁንም ለማረም ዝግጁ የሆኑ አይመስልም፡፡ በሹመት ላይ ሆኖ ህግ የሚተላለፍ ባለስልጣን የሚቀጣበት ሀገር ስለአልሆነ በማንአለብኝነት በህገወጥ ድርጊቱ ቀጥለዋል፡፡ ቀን የጨለመ ዕለት ግን ማጣፊያው እንደሚያጥር ጥርጥር የለኝም፡፡ ይህን ፅሁፍ እያዘጋጀው እያለ ፕሮፌሰር መርጊያ መግለጫ ሲሰጡ ሰማው እንዲህ ብለው “ገለልተኛ አይደላችሁም ይሉናል፤ ለገዢው ፓርቲ ያደላሉ ይሉናል፤ በእውነት ገዢው ፓርቲ የእኛ ድጋፍ ያስፈልገዋል?” እስኪ አንድ ዳኛ ጫወታ ከመጀመሩ በፊት እንዲ ማለት ምን ማለት ነው? ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚዎችን እንደሚበልጥ እርግጠኛ ቢሆኑ እንኳን እንዲህ ዓይነት አስተያየት አይሰጥም፡፡ ቢያንስ በአደባባይ፡፡ ለነገሩ ከኢህአዴግ ጋር ተባብሮ የመንግስት ገንዘብ በማከፋፈል ተግባር መሰማራት ድጋፍ ካልሆነ ምን ይሆናል?
ስለዚህ ሌላኛው ህገወጥ ተግባር ምርጫ ቦርድ ከመንግሰት ካዝና ወስዶ ለኢህአዴግ የሰጠውን ገንዘብ በህጉ መሰረት ለታለመለት ዓላማ ብቻ ማዋሉን ማረጋገጥ ሲገባው ይልቁንም በዚህ ጉዳይ ኢህአዴግ ለሚፈልጋቸው ፓርቲዎች የማሰራጨት ተግባርን መስራቱ ቦርዱ ከተሰጠው ኃላፊነት እና ተግባር ውጭ ህገወጥ ድርጊት መፈፀሙን የሚያሳይ ነው፡፡ ኢህአዴግ ለፈፀመው ህገወጥ ተግባራም ቦርዱ ተባባሪ ነው፡፡ ይህ ቦርዱ አድሎዋዊ መሆኑን ያሳያል፡፡ ቦርዱ በግፊም አይነሳም ወይም በግፊ የሚነሳው ኢህአዴግ ሲገፋው ነው ያልኩት ለዚህ ነው፡፡
ሌላ አስቂኙ ነገር ደግሞ ኢህአዴግ ለሰጣቸው ገንዘብ የኦዲት ሪፖርት እንዲያቀርቡ ከተጠየቁት ውስጥ የኦዲት ሪፖርት ማቅረብ የቻሉት ሶሰቱ ብቻ ናቸው የሚለው መረጃ ነው፡፡ የሚያስቀው የኦዲት ሪፖርት ያለማቅረባቸው ወይም የኦዲት ሪፖርት ያቀረቡት ትንሽ መሆናቸው አይደለም፡፡ የኢህአዴግ ሪፖርት ጠያቂነት እና እነርሱም ሪፖርት ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸው ነው፡፡ ለነገሩ እነዚህ ፓርቲዎች መሞታቸው የተረጋገጠው ገንዘብ ከኢህአዴግ ለመቀበል የወሰኑ ዕለት ነው፡፡ የዛን ዕለት አለቃቸው ማን እንደሆነ ተጠሪነታቸውም ለማን እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች እንዴት ብለው አማራጭ ያቀርባሉ? ሌላው አስገራሚ ነገር የተጠበቀባቸውን አማራጭ ያለማቅረባቸው ብቻ ሳይሆን የኢህአዴግንም ፖሊሲ በቅጡ ሊደግፉ የሚችሉ ያለመሆናቸው ነው፡፡ ከሁለቱም የሌሉ ጉዶች ናቸው፡፡ የእነዚህ ፓርቲዎች ስብስብ አባል ነው እንግዲህ ሰሜን አጣፋችሁ እያለ ክስ መስርቶ ዜጎችን በየጣቢያው እያስጠራ የሚያንገላታው፡፡ ሰም ሲኖር መስሎኝ የሚጠፋው!!
ፓርቲዎች በዋነኝነት የገቢ ምንጫቸው መሆን ያለበት ከአባላት የሚያገኙት መዋጮ ነው፡፡ አባላት ከሌሏቸው ደግሞ ፓርቲ ናቸው ብሎ ከምር መውሰድ አይቻልም፡፡ በዚህ ፅሁፍ ያነሳሁትን ሃሳብ የሰጠሁት ኢህአዴግ ለነዚህ ፓርቲዎች የሚያድለው ገንዘብ ከምርጫ ቦርድ የወሰደውን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን የኢህአዴግ የገንዘብ ምንጭ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በህገወጥ መንገድ ከያዛቸው የንግድ ድርጅቶች በሚስጥር ከሚያገኘው በተጨማሪ የፓርቲውን አቅም ለማሳደግ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የመንግሰትን ሀብትና ንብረት ያለአግባብ ይጠቀማል፡፡ የተወሰኑ ማሳያዎችን ለመግለፅ፤
·         በቅርቡ ኢህአዴግ ያሰለጠናቸውን ካድሬዎች ለምሳሌ የመንግሰት ተቋም በሆነው የሲቪል ሰርቪስ ዮኒቨርሲቲ ሲያስመርቅ፣ በተከታታይ በዩኒቨርሲቲው ጊቢ ውስጥ ውለው አድርው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሲሰለጥኑ ማየትና መስማት የተለመደ ነው፡፡ ይህ ገንዘብ ፓርቲው በተዘዋዋሪ ከመንግሰት የሚወስደው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ኢህአዴግ ከመንግሰት በተዘዋዋሪ የሚወስዳቸው እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ የፓርቲ አባላት በተደራጁበት መዋቅር አይደለም ወርሃዊ መወጮ የሚከፍሉት፤ በመንግሰት መዋቅር በኩል ነው መዋጮ የሚሰበሰበው፡፡
·         በቅርብ በማውቀው የተወካዮች ምክር ቤት ከላይ እስከ እታች ያለው መዋቅር በመንግሰት የስራ ሰዓት ሁሉ የፓርቲ ስብሰባ ይደረጋል እንዲሁም ሌሎች ልዩ ልዩ ተግባራትንም ያከናውናሉ ለነዚህ ተግራራት ሁሉንም አስተዳደራዊ መዋቅር ይጠቀማል፡፡
·         የኢህአዴግ ቢሮዎች በሙሉ የመንግሰት ናቸው፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ከመንግሰት ቢሮዎች ጋር ብዙ ሀብት በሚጋሩበት ሁኔታ ነው ቢሮዎቹን የሚከፈቱት፡፡
·         በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ፅ/ቤቶች በዋና ዋናዎቹ የክልል ፖሊሶች ጥበቃ ሲያደርጉ ብታዩ በፍፁም መገረም አይኖርባችሁም፤ አሁን እርግጠኛ አይደለሁም እንጂ ሬዲዮ ፋና በፌዴራል ፖሊስ ነበር የሚጠበቀው፡፡ ሸገር ኤፍ ኤምን ፌዴራል ፖሊስ የሚጠብቀው አይመስለኝም፡፡
·         የመንግሰት መኪና ያለምንም እፍረት ለፓርቲ ስራ ሲያውሉ ማየት በፍፁም የሚያሸማቅቅ ሳይሆን፣ በኩራት ልብ የሚያስነፋ ነው፡፡ ለፓርቲ ስብሰባ ከመንግሰት ነዳጅ ሞልተው ነው የሚንቀሳቀሱት፡፡
ይህን ሁሉ ስታሰቡት ኢህአዴግ ለአነዚህ ፓርቲዎች ያሰበውን ብር ሁለት ሚሊዮን ወይም እነርሱ የፈለጉትን ብር አራት ሚሊዮን ቢሰጣቸው በእጅ አዙር ከመንግሰት የሚቀበለው ነው፡፡ አሉኝ ከሚላቸው ስባት ሚሊዮን አባሎችም ሃምሳ ሳንቲም ቢሰበስብ ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ የገንዘቡ ምንጭ ሳይሆን መርዕ ያለመከበሩን ስናስብ ነው ጉዳዮን ጉዳይ ብለን እንድናነሳው የሚያስገድደን፡፡
በነገራችን ላይ እነዚህ ከኢህአዴግ ድርጎ/ደሞዝ የሚቆረጥላቸው ድርጅቶች ከመንግሰት ለፅ/ቤት የሚሆን ቢሮ አላቸው፡፡ አንዳንዶቹ አከራይተው እንደሚጠቀሙበት እና ለግል ጥቅም እንደሚያውሉት እርስ በራስ ሲካሰሱም ሰምተናል፡፡ ለማነኛውም ገንዘብ ሰጪው ኢህአዴግ፣ ገንዘብ ተቀባይ ፓርቲ ተብዬዎችም ሆኑ ምርጫ ቦርድ ይህን በማድረጋቸው ምንም ቅር የሚላቸው አይመስልም፤ ዶክትር በድሉ ዋቅጅራ ባለፈው ሳምንት ባቀረበው መጣጥፍ ላይ በተጠቀመው አባበል ብዘጋው ወደድኩ፡፡ እነዚህ ተዋንያን ተግባራቸው ለአስደሳች ህልም ካልሆነ በቀር ለአሰፈሪ ቅዠት አይዳርጋቸውም፡፡ ይህ ሲሆን ስታዩ አንድ የጎደላቸው ነገር ያለ አይመስላችሁም፡፡
ቸር ይግጠመን!!!

No comments:

Post a Comment