Wednesday, November 26, 2014

ህዝቡ የሚለው …..


ዛሬ በርዕስነት የመረጥኩት ጉዳይ ለመፃፍ ካሰብኩ ቆይቻለሁ፡፡ መልዕክት ማስተላለፊያው መንገድ ሲዘጋ በጅምር ትቼው ነበር፡፡ ለዛሬ የ “ፍኖተ ነፃነት” ጋዜጣ እንዲሆን ብዬ ሳዘጋጀው የቱን አንስቼ የቱን እንደምጥል ግራ ገብቶኝ ለ “ህዝብ ጥቅም” ሲባል ከሚወሰዱት ህገ ወጥ እርምጃዎች የቅርብ የቅርቦቹን ብቻ ለማንሳት ወሰንኩ፡፡
የ “የፀረ ሽብር ህግ” ከምንጊዜውም በላይ ተግባራዊ እየተደረገ ያለበት ወቅት ላይ እንደምንገኝ ማንም ሰው ይረዳዋል ብለን እናምናለን፡፡ ሀገራት ሽብርን ለመከላከል የሚያስችላቸውን የህግ ማዕቀፍን ጨምሮ ሌሎች አወቃቀራቸውን በማደረጀት ህዝብን ከአደጋ ለመጠበቅ ዝግጁ መሆ እንዳለባቸው ዓለም አቀፍ ጥሪ ከቀረበላቸው ቆየት ቢልም ኢትዮጵያ ሀገራችን ዘግየት ብላም ቢሆን ከዓለም አቀፍ ማዕቀፉ ውጭ የዜጎችን ስብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለማፈን የሚረዳ ህግ አውጥታ ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች፡፡ ለ “ህዝብ ጥቅም” ሲባል በሚል ማስመሰያ ብዙ ኢትዮጵያዊያን የ “ፀረ ሽብር” ህጉ ሰለባ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ በመላው ዓለም ፍተሻ ቢደረግ ዜጎቹን በሽብርተኝነት  በ“ፀረ ሽብር” ህግ የሚያንገላታ መንግሰት የሚገኘው እዚህ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ብቻ ነው፡፡ የሌሎች ሀገሮች የፀረ ሽብር ህግ ትኩረቱና ግብ ሀገርን ከውጭ ሀገር ከሚመጣ የተደራጀ አሸባሪ ቡድን መጠበቅ ነው፡፡
በ “ፀረ ሽብር ህግ” ተከሰው ቅጣት ከተጣለባቸው ውስጥ ቅጣት የሚገባቸው ተከሳሾች የሉም የሚል ጭፍን ዕየታ የለኝም፡፡ እነዚህ ሰዎች በወንጀል ህጉ ሊቀጡ የሚችሉ እንደሆነ ግን መቶ በመቶ እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች እየታደኑ “በፀረ ሽብር” ህግ ስም የሚታጎሩት ግን ለህዝብ ደህንነትና ሰላም ሳይሆን በገዢዎች ወንበር ላይ በሚፈጥሩት ሽብር ነው፡፡ እነ አንዱዓም አረጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ ሽብር የነዙት በአራት ኪሎ ወንበር ላይ ነው፡፡ የእነርሱ ድምፅ ለህዝቡ የነፃነት ድምፅ ነው፡፡ የተሰፋ ድምፅ ነው፡፡ አሁንም በብዞዎች የሚዘመር እና ወደፊትም ለክብር የሚበቃ የነፃነት ድምፅ፡፡

ሌላ የሰሞኑ ወሬ የግል ሚዲያዎች ህዝቡን ለብጥብጥ ህገመንግሰታዊ ሰርዓቱን በሀይል ለመናድ እየተንቀሳቀሱ እንዴት ዝም ተባሉ የሚለው ነው፡፡ የመንግሰት የፖሮፓጋንዳ ሚዲያዎች የህዝብ ጥያቄ እነዚህ ሚዲያዎች ለፍርድ ይቀረቡ የሚል ነው፡፡ ይህ በእውነት የህዝብ ጥያቄ ከሆነ ይህን ጥያቄ ያቀረበ ህዝብ ለምን አዲስ ዘመን ተሯሩጦ አይገዛም? ለኢቲቪም ያለምንም ውትወታ፣ ማስታወቂያና ማስፈራሪያ ዓመታዊ ኪራይ አይከፍልም? ለምን የግል ሚዲያ ህትመቶችን ተሻምቶ ይገዛል? ነገሩ ግን አንዲህ አይደለም፡፡ አንድ ቅምጥል የንጉስ ዘር የህዝብ ብዛት 20 ሚሊዮን ደርሶዋል ብትባል ምናምንቴውን ቆጥረው ይሆናል እንጂ እኛ ከአምሰት መቶ አንበልጥም ብላለች ተብሎ የሚበላ ወሬ አለ፡፡ ሕዝብ ለዚህች ቅምጥል ትርጉሙ የተለየ ነው፡፡ ለእኛዎቹ ቅምጥሎች ደግሞ ህዝብ የሚባለው ሌላ ትርጉም ካልተሰጠው እና አሁን በብዛት የግል ሚዲያ ሰርጭት ያለበት አዲስ አበባ ከሆነ እኛ ነን ህዝብ የምንባለው ካላሉን በስተቀር ነገሩ ለየቅል ነው፡፡ ህዝቡ እያለ ያለው ቅዳሜ ምን ልናደርግ እንውጣ? ነው፡፡ ቅዳሜ ተወዳጇ ፋክት መፅሔትን ጨምሮ ሌሎች ብዛት ያላቸው ህትመቶች ለገበያ ቀርበው የሚያነብበት ቀን ስለነበር ነው፡፡ በዚህ እለት አዲስ ዘመን በገበያ ላይ ብትውልም የሚመለከታት እንደሌለ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ለጨረታ ማስታወቂያ ከሚፈልጉት ውጭ ማለቴ ነው፡፡
ሌላው የህዝብ ጥያቄ በእሰር ላይ የሚገኙትን ፍቱልን የሚል እንደሆነ ለመረዳት ፈላስፋ መሆን አያስፈልግም፡፡ በቅርቡ ቂሊንጡ እስር ቤት ሄጄ የታዘብኩት አንድ ነገር እጅግ ብዛት ያለው እስረኛ መኖሩን ነው፡፡ ተቃዋሚዎች እስር ቤት የሌለው መንግስት እንደማይመሰርቱ የታወቀ ቢሆንም በአሁኑ ሰርዓት ከህግ ውጭ ታስሮ መንገላታት ግን በግልፅ የሚታይ ሀቅ ሆኖዋል፡፡ ህዝቡ በግፍ የታሰሩትን ፍቱልን ሲል የቅምጥሎቹ ወገን የሆኑት ደግሞ እነዚህ ታሳሪዎች አሸባሪዎች ናቸው ይሉናል፡፡ እውነት እነዚህ ሰዎች አሸባሪ ከሆኑ ሰፍር ቁጥር የሌለው ህዝብ በየፍርድ አደባበዩ እና በየማጎሪያ ሰፍራ ለምን ይገኛል? እነዚህ በመንግሰት አሸባሪ የተባሉ ሰዎች ህዝቡ ለምን በፈቃዱ ይጎበኛቸዋል? እነዚህ ታሳሪዎች መጎብኘት የሚፈልግ ሁሉ በነፃነት እንዳይጎበኝ ለምን የተጠና እገዳ ይጣልባቸዋል? እዚህ ጋ ምፀት የሚሆነው ጉብኝት እግድ የሚጣለው “አሸባሪ” ብለው ያሰሯቸው እስረኞች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ነው የሚለው ነው፡፡ የሚያገላቱዋቸውም ለእነርሱ ደህንነት ብለው ነው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ህዝቡ እያለ ያለው መሰረት የሌላቸው ሲከፋም ህገወጥ የሆነ የአቃቢ ህግ ክስና ይህን መሰረት አድርጎ የሚሰጥ የፍርድ ቤቶች ውሳኔ ይቁም ነው የሚለው፡፡ በመንግሰት በተጠና ጥናት እምነት የማይጣልባቸው ተቋማት የተባሉት እነዚህ ተቋማት በዚህ ድርጊት አሁን ባለው ጥልቀት መሳተፋቸው የተዓማኒነት ጉድለታቸውን ከማሳደግ ውጭ የህዝብ ጥያቄን አይመልስም የጊዜ ጉዳይ እንጂ የገዢዎችንም ወንበር አያፀናም፡፡
ሕዝቡ እያለ ያለው በየአምሰት ዓመት ምርጫ ቢመጣም አማራጭ አሳጣችሁን፡፡ አፈናውን አቁሙና ፍላጎት ያለው ተደራጅቶ አማራጭ ያምጣ ነው፡፡ የመደራጅት መብት ያለምንም ገደብ ይከበር!! ሕገመንግሰት ላይ በተቀመጠው መሰረት ተግባራዊ ይሁን!!! ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ህዝቡ ያለው አሁንም የሚለው፡፡ እዚህ ላይ ገዢው ፓርቲም የመንግሰት መዋቅርን ተጠቅሞ የሚያደርገው አፈና አማራጭ አሳጣን እንጂ ደግ አደረጋችሁ የሚል ድምፅ አይሰማም፡፡ በቅርቡ በመንግሰት ድጋፍ በገዢው ፓርቲ አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ መስመርና ልማታዊ መንግሰት ፍልስፍና ዙሪያ የተደረጉት ከ-እሰከ የማይገልፃቸው ስብሰባዎች ያረጋገጡት ሀቅ ኢትዮጵያዊያን አማራጭ እንደሚፈልጉ እና የመንግሰት ህገወጥ አካሄድ እንዲቆም ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን እንደ ህዝብ ያቀረቡት ጥያቄ ከልማት እኩል ነፃነት ይገባናል ነው፡፡ ነፃነት ልማትን ያሳልጣል እንጂ የልማት ደንቃራ የሚሆንበት አንድም በቂ ምክንያት እንደሌለ ህዝቡ ተገንዝቦዋል፡፡ ህዝቡ የሚለው ነፃነታችንን አትንኩ ነው፡፡
ህዝቡ አሁንም እያለ ያለው የእምነት ነፃነት ይከበር የመንግሰት ጣልቃ ገብነት ይቁም ነው፡፡ ባለፈው ሰሞን ኢሳት የሚባል ለኢህአዴግ እሣት የሆነ ሚዲያ በቅርቡ ይፋ ያደረገው የሰብሰባ ውስጥ ውይይት መንግሰት በምን ያህል ጥልቀት በሙስሊሞች ጉዳይ ጣልቃ እንደሚገባ ብቻ ሳይሆን የሙስሊሙን ማህበረሰብ ለመምራት በሚል የአመራር ቦታ “የቀሙት” ሰዎች ግብ ምን እንደሆነ አጋልጧቸዋል፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ እያለ ያለው እምነታችን በካድሬ አይመራም ነው፡፡ የኢሳትን ተደማጭነት ያጎላው የሀገር ውስጥ አፈና መሆኑን ለመረዳት ነብይ መሆን ያስፈልግ ይሆን? ህዝቡ እያለ ያለው አፈና ይቁም!!! ሀሳብ በነፃነት ማንሸራሸር የሚፈቅደው ህገመንግሰታዊ ድንጋጌ ይከበር ነው፡፡
ለማጠቃለል መንግሰት በህዝብ የመደራጀትና ሃሳብን በነፃነት የማንሸራሸር መብት ላይ በህዝብ ስም ገደብ እያደረገ ቢሆንም ህዝቡ ግን በተቃራኒ እየጠየቀ ያለው እነዚህ መብቶች ያለምንም ገደብ ይከበሩ ነው፡፡ እነዚህን መብቶች ተጠቅሞ በህዝብ ጥቅም ላይ ጉዳት የሚያድርስ ቡድንም ሆነ ግለሰብ ቢመጣ ህዝብ ለመቅጣት የሚያስችለው አቅም አለው እያለ ነው፡፡ የህዝብ ድምፅ ይሰማ፡፡
ቸር ይግጠመን!!!!


No comments:

Post a Comment