Sunday, March 22, 2015

ምረጫ ክርክር 2፡ “የፌዴራል ስርዓተ በኢትዮጵያ”-የግል ዕይታ

ተከራካሪዎች፤
·         ካሳ ተክለብርሃን እና አባዱላ ገመዳ                           ኢህአዴግ
·         በኃይሉ ሸመክት እና ደረጀ ጣሰው                         “ድንኩ አንድነት”
·         ተሾመ ወልደሐዋሪያት  እና ሰማቸውን ያልያዝኩት አዛውንት            መኢብን
·         ኤርሚያስ ባልከው እና ሰሙን ያልያዝኩት ወጣት                ኢዴፓ
·         አበባው መሃሪ እና አንድ ሰማቸውን ያልያዝኩት አዛውንት         መኢአድ                 
የሁለት ሺ ሰባት ምርጫ ክርክር ሁለተኛ ክፍል “የፌዴራል ስርዓተ በኢትዮጵያ” በሚል ነው፡፡ በዚህ ክርክር ዙሪያ ስናወራ አንድ ወዳጄ አንድ ቀልድ ቢጤ ነገረኝ፡፡ በዚሁ ቀልድ ብጀምረው ወደድኩ፡፡ በቅርቡ የእንግሊዝ፣ የአሜሪካ እና የኢትዮጵያ ምርጫ አስፈሚዎች ለልምድ ልውውጥ ተገናኝተው ነበር አሉ፡፡ የአንግሊዙ ተወካይ በቅድሚያ አሁን እኛ ምርጫ በብቃት አካሂደን በዚያው እለት ምርጫ ውጤት መግለፅ ችለናል ብለው የደረሱበትን ደረጃ ሲናገሩ፤ የአሜሪካው ተወካይ ደግሞ እኛ ደግሞ ውጤቱን በቀጥታ ማሰራጨት ችለናል ብለው ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ተወካይ (ፕሮፌሰር መርጊያ በቃና ይሁኑ አቶ ነጋ ዱፊሳ አልተገለፀም) ይህ ምን ያስገርማል ብለው በኩራት በእኛ ሀገር ውጤቱ ከምርጫ በፊት ይታወቃል ብለው አረፉት፡፡ የዘንድሮ ምርጫ የዋንጫው ባለቤት የታወቀበት ውድድር መሆኑ ከግንዛቤ እንዲያዝ እኛም እንደ ህዘብ እንደተረዳን ቀልዱ ያሰረዳል ብዬ አምናለሁ፡፡
በዛሬው ክርክር በእውነቱ ያዘንኩት በክርክሩ ፓርቲያችውን ወክለው ለቀረቡት ለአቶ ካሳ ተክለ ብርሃን እና ለአቶ አባዱላ ገመዳ ነው፡፡ በረጅም ዓመት በትጥቅ ትግል እንዲሁመ 24 ዓመት በመንግሰትነት የፖለቲካ አመራር ሲሰጡ የነበሩ ሰዎች የዚህ ሁሉ “ድካም” እና መስዋዕትነት ውጤት ዛሬ ከጎናቸው ሆነው በደህንነት መስሪያ ቤት ፈቃድ ያገኙ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ የደረሰበትን የፖለቲካ ደረጃ የማይመጥኑ የፓርቲ ወኪል ነን የሚሉ ሰዎች ጋር ያደረጉት ክርከር ነው፡፡ ማለት የፈለኩት ኢህአዴግ የዚህን ያህል የፖለቲካ ልምድ አለኝ እያለ ልኩ የዚህን ያህል የወረደ እንዲሆን በአንድነት እና በመኢአድ ፓርቲ ላይ ያደረገው ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ እንደ እነርሱ አባባል ለሰማዕታት ክብር ለመስጠት የሚያስችል ደረጃ ዲሞክራሲውን ሊያደርሱት አልተቻላቸውም፡፡ ህወሃት ትግል ከጀመረበት ቢቆጠር ከአርባ ዓመት በላይ ተደክሞ የተደረሰው እዚህ መሆኑ አሳፋሪ ነው የሚል የግል እይታ አለኝ፡፡
ለማነኛውም ወደ ክርክሩ ዝርዝር ስንገባ ካለፈው በተቃራኒ መጥፎውን የክርክር ጀማሪነት የወሰዱት “ድንኩን አንድነት” ወክለው የተገኙት አንድነትን በማፍረስ ቀንደኛ ተዋናይ የነበረው ደረጀ ጣሰው እና በኃይሉ ሽመክት የሚባል አንድነት ውስጥ የማላውቀው ወጣት ነው፡፡ በኃይሉ ሽመክትን በእውነት የት ወረዳ የተደራጃ አባል እንደነበር አላውቅም፡፡ ለማነኛውም ሁሉንም የማወቅ ፍላጎትም ሁኔታም የለኝም፡፡ እርግጡ ግን ለክርክር ካዘጋጀናቸው ሰዎች ውስጥ አልነበረም፡፡ አንድነትን ወክለው እንዲከራከሩ በዝገጅት ላይ የነበሩት የአንድነትን ፕሮግራም ጠንቅቆ ማወቅ የግድ ስለሚል ነው፡፡ ለዚህ ዋነኛው ማሳያ “የኮሚሽነር ጄነራል” ትዕግስቱ አወሉ “ድንኩ አንድነት” ፓርቲ ፕሮግራም ለውጥ ካለደረገ በስተቀር የአንድነት የፌዴራሊዝም አማራጭ “ጂኦግራፊ መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝም” የሚል አይደለም፡፡ በኃይሉ ስለ ፌዴራሊዝም ጎግል ሲያደረግ ስራ በዝቶበት የአንድነትን የፌዴራሊዝም ግልፅ አማራጭ ለማቅረብ አልቻላም፡፡ የበሀይሉን ለአንድነት ፓርቲ እንግዳነት የሚያሳብቀው ሌላው አንድነት “ሀብታሙ ሰዩም” የሚባል እሰረኛ የሌለው መሆኑ ነው፡፡ ደረጀ ጣሰው ከዚህ አንፃር  ጥቁር እንግዳውን በሀይሉ ሸመክትን በመራጃ ማቀበል እንዲረዳው የሚጠበቅ አይመስለኝም፡፡ በክርክር አብሮት ስለተገኘ ምሽት ክለብ ወሰዶ እስክስታ/ዳንስ ሊጋብዘው ይችል ይሆናል፡፡ ሌላው የበሀይሉን እንግዳነት የሚያሳየው “ራዕያችን ዋንጫ ነው” የሚለው የቃላት ግድፈት ዋንጫውን እንደ ምርጫ ምልክት የመረጥን ሰዎች በዋንጫው ዙሪያ ያደረግነውን ዝርዝር ውይይት ስለአላገኙት ዋንጫው ከምርጫ ውድድር ምልክትነት አልፎ “ራዕይ” እሰከመሆን የሚደርስ የቃላት ግድፈት ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡ ለማነኛም በኃይሉ ከፎረም የመጣ፣ በአንድነት ወጣቶች ውስጥ ራሱን የደበቀ የቀበሮ ባሕታዊ መሰለኝ፤ ለማነኛውም በሀይሉ ሊማር የሚችል ወጣት እንደሆነ ለመገንዘብ አልተቸገርኩም፡፡ አንድነትን ወክሎ ለክርክር ይመጥናል የሚባል ተከራካሪ አይደለም፡፡ ለ”ድንኩ አንድነት” ግን ከበቂ በላይ ነው፡፡ በሀይሉ የአንድነት አባል ከሆነ ወረዳውን እና የወርሃዊ ክፍያ የከፈለበትን ፌስ ቡክ ላይ ቢለጥፈው “ከፎረም” የመጣ ከሚለው ጥርጣሬ እተርፋለሁ፡፡
መኢብን በእርግጥ የመሳፍንት/መስፍን መኢብን ነው ወይ? ያስብላል፡፡ እኔ መሳፍንት/መስፍን የሚባል ግለሰብ የሚመራው ፓርቲ በሀገር ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚረዱ አባላት አሉ ብዬ አላምንም ነበር፡፡ ይህን ለማለት የሚያስደፍረኝ በግሉ የፈለገውን ከማለትና ከማድረግ አልፎ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በጠራራ ፀሃይ ከገዢዎች ጎን ተሰልፎ ሲዘልፍ ተው የሚለው አባል በፓርቲው ውስጥ መኖር አለበት ብዬ ስለማምን ነው፡፡ ለማነኛውም የመኢብን ተወካዮች በተደራጀ መልክም ባይሆን በዚህች ሀገር ያለውን ፌዴራሊዝም ዕፀፆች ለማሳየት ሙከራ አድርገዋል፡፡ ተከፋፍሎ የተሰጣቸው 19 ደቂቃ አንሶዋል ቢሉም በሁሉም ክፍሎች ግምሻ ላይ ሃሰብ አጥሮዋቸው ፈተና ውስጥ ሲገቡ ታዝበናል፡፡ ለማነኛውም ኢህአዴግ ከ24 ዓመት ወዲህ ያመጣው ኦሮሞ፣ ትግሬም፣ ሀዲያም፣ ወዘተ የሌለ መሆኑን በመግለፅ ይህ የኢህአዴግ የአፋዊ ፌዴራሊዝም ተቀባይነት የለውም ማለታቸው እውነት ነው፡፡ ይህ ግን በምንም መመዘኛ መኢብን የሚባል ፓርቲ ለምርጫ መቅረብ ያለበት ፓርቲ ነው ማለቴ አይደለም፡፡ ህዝብ ወክሎ ለምርጫ ለመቅረብ የሚያስችል የፓርቲ አቋም ያለው ፓርቲ ነው ብዬ ከምር ልወስደው አልችልም፡፡ የመሳፍንት ዓይነት ሰው የሚመራው ፓርቲ የፈለገ ጠንካራ ሰው ውስጡ ቢኖር የትም ሊደርስ አይችልም፡፡ እነዚህም ለክርክር የመጡ ሰዎች መሳፍንትን ያላስታገሱ እንኳን ሀገር፣ ቀበሌ ማስተዳደር የሚችሉ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ መሳፍንት የሚመጥነው ኢህአዴግ ስለሆነ ከተቀበሉት ፎርም ሞልቶ እዚያው ቢገባ የሚል አስተያየት መሰጠት ስህተት አይመሰለኝም፡፡
በዚህ ክርክር እንደ ኢዴፓ ውጤታማ ክርክር ለመከራከር የሚያስችል መረጃ ያለው ፓርቲ በግሌ አልገምትም ነበር፡፡ ለዚህ አስተያየቴ መነሻ  የኢዴፓው ልደቱ አያሌው መፅሃፍ ለማጣቀሸ የሚሆን እንደሆነ ስለማውቅ ነው፡፡ ለክርክሩ የቀረቡት ወጣቶች ግን ከልምድም ሆነ ከዝግጅት ማነስ አዚህ ግባ የሚባል ክርክር ማድረግና ነጥብ ማስቆጠር አልቻሉም፡፡ የልደቱን መፅሃፍ እንደ ማጣቀሻ ሳይሆን እንደ ቅዱስ መፅሃፍ ነው የወዱት፡፡ አሁን በኢዴፓ ውስጥ ፊቱን እየለመድነው የመጣነው ወጣት ኤርሚያስ ባልከው ያባከናቸውን ጊዜዎች ለጓደኛው/ከይቅርታ ጋር ሰሙን አልያዝኩትም/ ቢተውለት የተሻለ ይሆን ነበር ብዬ እገምታለሁ፡፡ ለማነኛውም ኢህአዴጎች ለኢዴፓ ባላቸው ቅን ልቦና እና አሁን ለክርክር የቀረቡት ሰዎች ተናዳፊ ያለመሆን ካልሆነ በስተቀር ኤርሚያስ ባልከው በተደጋጋሚ የኦሮሚያ መገንጠል በሚል በቀጥታ ከልደቱ መፅሃፍ የወሰደውን ሃሰብ እንደወረዳ እያቀረበ ለጥቃት እራሱን ሲያጋልጥ ነበር፡፡ ሰሙን ያልያዝኩት የኢዴፓ ተከራካሪ ህገመንግሰት ለማሻሻል አስቸጋሪ መሆኑ ግልፅ ሆኖ እያለ አሁን ኢዴፓ ባቀረበው ዕጩም ሆነ በሌላ መስመር ሊያሳካው የማይችለውን የህገ መንግሰት ማሻሻል ጉዳይ አንስቶ ጊዜ ሲያባክን ነበር፡፡ የዚህ ክርክር ፋይዳ የሚኖረው ለምርጫ ሳይሆን ለእውቀት በሚደረግ ክርክር ቢሆን ነበር፡፡ የኢዴፓው ተከራካሪ ሊብራል ዲሞክራሲ በሚከተሉ ሀገሮች ያለ ፌዴራሊዝም ተፈትኖ የወደቀ በሚል በኢህአዴግ የቀረበውን መሰረተ ቢስ ክስ ተፈትኖ የወደቀ ሳይሆን ተፈትኖ ያለፈ መሆኑ በደንብ ለማስረዳት ሞክሮዋል፡፡ ፈተና ያላለፈው እንኳን 70 ዓመት 24 ዓመት በቅጡ መቆም ያቃተወ ግራ ዘመም ሀገሮች ውስጥ ያለው ፌዴራሊዝም በተለይም አምሳያ የሌለው አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን ለዓለም ያበረከትነው ብለው የተመፃደቁበት ፌዴራሊዝም በእግሩ መቆም ያለመቻሉ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ፌዴራሊዝም ልዩ እያሉ የሚያሞካሹ ምሁር ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ አቶ ካሳ ተክለብርሃንም ሆነ ድርጅታቸው ኢሀአዴግ ሁሌም የሚያሰቡትን የሚነግሯቸው ምሁራን ስለሚመርጡ ነው፡፡
በኢዴፓ እምነት አሁን ያሉት ክልሎች ስልጣን ያላቸው ፌዴራል መንግሰት አባላት ሳይሆኑ፣ የሰራ ድልድል የተደረገላቸው ምድብ ሰራተኞች መሆናቸው ትክክለኛ ምልከታ ነው፡፡ በእኔ ዕይታ ለዚህ ማሳያ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ርዕስ መስተዳደር ከነበሩት ከአቶ ያረጋል አይሽሹም የተሻለ ማሳያ የሚገኝ አይመስለኝም፡፡ ከእርሳቸውም ሌላ በተፈለገ ጊዜ ከክልል ርዕሰ መሰተዳደርነት ተነሰቶ መጥቶ ወደ ፌዴራል መንግሰት የሚመጡበት ሁኔታ በተደጋጋሚ የታየ ነው፡፡ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒሰትራችን በብቃት ማነስ በሚል ከደቡብ ክልል መምጣታቸው፣ እርሳቸውን በብቃት ይተካሉ የተባሉት አቶ ሸፈራው ሽጉጤ ከመለስ ዜናው ሞት በኋላ ከክልል ርዕሰ መስተዳድረነት መነሳት፣ የጋምቤላው ርዕስ መስተዳድር ተነስተው ፌዴራል መስሪያ ቤት ቢሾሙም አድብተው ስደት መምረጣቸው፣ የድሬዳዋ የዙር አመራር፣ የሀረሪ ሀደሬዎችን ማዕከል ያደረገው የመንግሰት አሰያየም፤ ወዘተ እየተመለከትን በምን መመዛኛ የአንድ ፌዴራል አካል የሆነ የክልል መንግሰታት ናቸው ብለን ተጨፍነን ልንሞኝ አንችልም፡፡ የኢዴፓዎች መፈክር በተሳሳተ መስመርም ሆነው - “ዛሬም ይቻላል” የሚል ነው፡፡

በዚህ ክርክር የመኢህአድ ተወካይ አቶ አበባው መሐሪ አንድ ሀቅ ተናግረዋል፡፡ ህዝቡን በዚህ ምርጫ ምረጡን እና እንዲህ እናደርጋለን ብለው እስከመጨረሻው ለማሳሳት አልሞከሩም፡፡ በስተመጨረሻም ቢሆን በግልፅ ያሉተ “ምረጡን እና ምክር ቤት ከገባን ወክለን እንከራከርላችኋለን” ነው፡፡ ለወጉም ቢሆን መንግሰት እንሆናለን አላሉም፡፡ በዚህ አባባላቸው የኢህአዴግን ቀጣይ መንግሰትነትን አምነው ተቀብለውታል፡፡ በክርክሩ ከአንድ ፖለቲከኛ በማይጠበቅ ደረጃ የሰሩት ስህተት እና አቶ አባዱላንም ያሳሳቱት “ህዝቡ በአሰር ብር እንዳይታለል” በሚል የሰጡት አስተያየት ነው፡፡ አቶ አበባው መሃሪ በምድር ላይ ያለውን ሀቅ ገዢው ፓርቲ በኢኮኖሚ ደካማ የሆኑተን ዜጎች በተለያየ መንገድ እንደሚያማልል ለመግለፅ ነው፡፡ ይህን ሀሳብ በቅጡ መግለፅ ካልቻሉ በዚህ ደረጃ ባይሉት ጥሩ ነበር፤ አቶ አባዱላም ይህን በዚሁ መንፈስ ከህዝብ ጋር ለማጋጨት ባይሞክሩ ጥሩ ነበር፡፡ ይህን የአቶ አበባው መሃሪን ስህተት ተከራካሪው አቶ ሬድዋን ሁሴን ወይም ሽመልስ ከማል ቢሆኑ ኖሮ አንድ ዶክመንተሪ የሚወጣው ስድብ ይገጥማቸው ነበር፡፡ አሁንም ኢህአዴግ በቀጣይ በኢቲቪ በሚያቀርበው ዶክመንተሪ ከህዝብ ጋር በሚያጋጭ መልኩ ቅስቀሳ አይደረግባቸውም የሚል እምነት የለኝም፡፡ ለማነኛውም “ከፍትፍት እና ከእሳት” ምርጫ ቀርቦዋል አሰበህ ምረጥ ብለው ክርክሩን አጠናቀዋል፡፡
አቶ አበባው መሃሪ በአማካሪነት ያመጧቸው አዛውንት አስተያየት ካልሰጡ ለምን እንዳደከሟቸው አይገባኝም፡፡ አሁንም እንዚህ ጎምቶ የሀገር አዛውንቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛ ተዋናይ ለመሆን የሚያደርጉትን ፍላጎት ለመግታት ካልተቻለ በቀጣይ ዋነኛ ተዋናይ የሚሆነው አዲስ ትውልድ እንዴት እድል እንደሚያገኝ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ አቶ አበባው መሀሪም ቢሆን በዚህ ክርክር ደረጃውን የጠበቀ የቀድሞውን መኢህአድ ወክለው ሊቀርቡ አልቻሉም፣ ወደፊትም አይችሉምና በጊዜ ቢያስቡበት ጥሩ ነው የሚል ምክር መለገስ አለብኝ፡፡ አንተን ብሎ መካሪ የሚልም ቢኖር ማለቴ ነው፡፡
ኢህአዴግ ባለፈው እንዳልኩት አዲስ ሀሳብ ሆነ አዲስ ሰው እንደሌለው አሁንም በድጋሚ አሳይቶናል፡፡ ፌዴራሊዝምን በሚመለከት ኢህአዴግ እየደጋገመ ሲናገረው ለራሱም እውነት እየመሰለው የመጣው አሁን የተዘረጋው ፌዴራሊዝም ስርዓት ባይኖር ይህች ሀገር ትበታተን ነበር የሚለው ነው፡፡ መሳሪያ ይዘው ይህችን ሀገር ሲቆጣጠሩ እነርሱ እንደ ፈለጉ ካላደረጓት ይህችን ሀገር ለመበታተን ፍላጎት ነበራቸው የሚባል ከሆነ እውነት ነው፡፡ እነሱ ስልጣን ሲይዙ እኛ በህይወት ያለን ምስክሮች ሀገራችን ቋንቋን በዋነኝነት መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝም ካልመጣ እንበታተናለን ብለን ተማምለን አናውቅም፡፡ ልክ ነው ህውሃት ለመገንጠል ሃሳብ ነበረው፣ ኦነግም እንደዚሁ የነፃ ኦሮሚያ ሀሳብ እሰከ አሁን አልተወም፡፡ ኦነግ እንደ ድርጅት ይህን ሀሳብ ባይተወውም መሪዎቹ እነ ሌንጮ ለታ ለአርባ ዓመት በኦነግ ሰም የተከፈለውን መሰዋዕትነት እንዴት እንደሚያወራርዱት ሳናውቅ፤ የመገንጠል ሀሳቡን ትተውት አዲስ አበባ ገብተዋል የሚል ወሬ ነፍስ ዘርቶዋል፡፡
ኢህአዴግ የሚባል ድርጅት ይህችን ሀገር ካልመራ ሀገር ትበተናለች ሰላም የሚባል ነገር የለም የሚባል ቅጥ ያጣ ሟርት ምንጩ ምን እንደሆነ ባይገባኝም፤ ይህን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ደጋግመው ሲያወሩት ለራሳቸውም እውነት እየመሰላቸው መጥቶዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ልዩ በሆነ ሁኔታ ብዙ ቋንቋ እንዳለ አድርገው የሚነግሩን ለምን እንደሆነ እሰከ አሁን ለማንም ግልፅ አይደለም፡፡ በሌሎች የዓለም ሀገራት ብዙ ቋንቋ ብዙ ባሕል እያለም ተፋቅሮ መኖር የሚባል ነገር፣ ሀገር የሚባል የጋራ ቤት መስራት እንደተቻለ በፍፁም እንድናውቅ አይፈልጉም፡፡ በአንድ ቋንቋ እየተናገሩም በሰለምና በፍቅ መኖር አቅቷቸው በጎሳ እየተቧደኑ መገዳደል እንደሚቻል በቅርብ ያለች ሀገር ሶማሌ መፍረስ እንዳለም እንደምናውቅ አያውቁም፡፡ ስለዚህ ኢህአዴጎች ተጨፈኑ ላሞኛችሁ እያሉን ነው የሚገኘው፡፡ ይህንኑ መፈክር ነው አሁን ከ24 ዓመት በኋላ ይዘው ለምርጫ ክርክር የቀረቡት፡፡ ለዚህ ነው አዲስ ነገር የላቸውም የምለው፡፡
ለማነኛውም አስገራሚ ሆኖ ያገኘሁት የመከራከሪያ ነጥብ ከአቶ አባዱላ የቀረበው ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ወደ ትጥቅ ትግለ የገባው በቋነቋ መናገር ሲከለከል፣ ባህሉን ማሳደግ ሲያቅተው ነው የሚለው ነው፡፡ ይህ ክርክር በተለይ አቶ አባዱላ ገመዳ ላይ የሚያምር ሆኖ አላገኘሁትም፡፡  ልክ እንደ ትግራይ ልጆች ይህን ብለው ከአዲስ አበባ የኦሮሞ ልጆችን አደራጅተው ቢሄዱ ይህን ሃሳብ ልናከብረው እንችል ነበር፡፡ ለደርግ ሰራዊት ለመዋጋት ወታደር ሆነው በጦር ሜዳ ተማርከው፤ በምርኮ ወቅት ባገኙት የብሔርተኝነት ምክር በሰማኒያዎች መጀመሪያ ጀምረው ባደረጉት የጠመንጃ ትግል አማርኛ አስጠልቶኝ ነው ጫካ የገባሁት የሚመስል አሰተያየት ውሃ አልቋጥር ብሎኛል፡፡ ኢህአዴግ ፌዴራሊዝምን የመረጠው ብዝዓነትን ለማስተናገድ የቻለ ስርዓት ባለመኖሩ ነው ይሉናል፡፡ ይህ ባይሆን ልንበተን ነበር ሲሉን እኔ የሚገባኝ ግን ሊበትኑን ጫካ የነበሩት ግን እነርሱ ራሳቸው መሆናቸው ነው፡፡
ለማነኛውም ሁሉም የሚስማሙበት እኛም ቤታችን ሆነን ሰምምነታችንን የምንሰጥበት ጉዳይ ኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሰርዓት ብቸኛውም አማራጭ የሚለውን ትተን ጥሩ አማራጭ ነው በሚለው ሰምምነት ያለበት መሆኑን ነው፡፡  ሰምምነት የሌለበት እና በህዘብ ይሁንታ ሊታረም የሚገባው ደግሞ ምን ዓይነት ፌዴራሊዝም? የሚለው ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአንድ ጊዜ ተሰርቶ የሚያልቅ ሳይሆን ህዝቦች በሂደት እያዳበሩት የሚሄዱት በዓለም ላይ ያለ የአስተዳደር ዘይቤ ነው፡፡ ፌዴራሊዝም በህዘብ ብዛትና በመሬት ሰፋት እኩል የሆኑ የፌዴራል ግዛቶች የሚያዋቅሩትም አይደለም፡፡ አንድ ዓይነት ቋንቋም ሰለሚናገሩ በአንድ የፌዴራል ክልል ውስጥ መሆን አለባቸው የሚል ፎርሙላም አይሰራም፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያሉት ክልሎች መቼም ቢሆን በራሳቸው መንግሰት ሆነው የራሳቸው የተለየ የአስተዳደር ዘይቤ የመሰረቱበት ሁኔታ ሰለአልነበረ፤ በኢትዮጵያ የሚያስፈልገው ምርጥ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያመጣ እና በተለይ ደግሞ ዜጎች ባልተማከለ አስተዳደር ፍትህና መልካም አስተዳደር የሚያገኙበት፣ በሀገሪቱ ፖለቲካ በቀጥታ ለመሳተፍ የሚያስችል ብቻ ሳይሆን የአካባቢያቸውን ልዮ ሁኔታ ያገናዘበ የእድገትና የፖለቲካ ተሳትፎ ለማደረግ ነፃነት የሚሰጥ ነው፡፡ ይህን ያገናዘበ የፌዴራል ሰርዓት ቢያንስ፤
·         የተለያዩ ህጎች በፌዴራል ክለሎች በሚገኙ መንግሰታት መካከል ሊኖር ይቸላል፡፡ ለምሳሌ የሞት ፍርድን ቀድመው የሚያስቀሩ ክልሎች ሊኖሩ ይችላሉ፤
·         ኦሮሚያን የመሰሉ ትልልቅ ክልሎች ውስጥ ለምሳሌ ቦረና ጅማ የመሳሰሉት አካባቢዎች የገዳ ስርዓት ሞዴል የክልል አስተዳደር እንዲኖር የሚያደርግ አሰራር፤
·         መሬትን ለኤኮኖሚ ጥቅምና ለክልሉ ፈጣን ልማት ሲሉ በነፃ ለኢንቨስትመንት ማቅረብን ጨምሮ ታክስ ክፍያን በተለያየ ምጣኔ ማስከፈል፤
·         የሰለጠነ የሰው ኃይል ወደ ክልላቸው ለመሳብ ሲባል የሚወሰዱ የተለያዩ እርምጃዎች ለምሳሌ የክፍያ ሰርዓት እና የሰራ ቋንቋን ከአንድ በላይ ማድረግ፤ወዘተ
በግልፅ የሚታዩ ልዩነቶች ሊሆኑ ይቸላሉ፡፡
የሁለት ሺ ሰባት ምርጫ አማራጭ ባይኖርም ወጪን ይዞ ገዢውን ፓርቲ ለማንገስ በሁሉም መስክ እየተውተረተረ ይገኛል፡፡ እኔም ሰራ እንዳልፈታ ያለኝን የግል ዕይታ ወርውሪያለሁ፡፡ ሁሉም ላይስማማ ቢችልም ተመዝግቦ እንዲቀመጥ በሚል ያሰፈርኩትን ሀሳብ ተወያዩበት፤ ኢህአዴግ ለውድድር የተዘጋጀበት ዐውድ ግን በእውነት አሰደማሚ እንደሆነ ይቀጥላል፡፡ ይህም ፍርሃቱን ካልሆነ ምን ሊያሳይ እንደሚችል አልገባኝ ብሎ አለሁኝ፡፡

ቸር ይግጠመን!!!

No comments:

Post a Comment