Monday, May 30, 2016

የግንቦት 20 ፍሬዎች ሲመዘኑ ….



ዛሬ ግንቦት 22 /2008 ዓ.ም ነው፡፡ ይህን ፅሁፍ ግንቦት 20 በሀዋሳ ከተማ ሆኜ ፃፍኩትና ለመለጠፍ ስል ፅሁፌ ሁሉ የደርግ ደጋፊ የሆንኩ አሰመሰለኝ፡፡ እውነት ከሆነ ደርግ የሰራውን በጎ ነገር መደገፍ አጢያት ባይሆንም እራሴን ከስህተት ለመጠበቅ የፅሁፉን አጭር መደምደሚያ እና የግምገማ ማዕቀፌን ለህዝብ ግምገማ እና ተጨማሪ ግብዓት በአጭሩ በፌስ ቡክ ገፄ ላብለጥፈው በቂ ስድቦች እንጂ ሃሳቦች ማግኘት አልተቻለም፡፡ ሰለዚህ በእራሴ ሚዛን ይህን የግምገማ ውጤት እንደወረደ ማሰቀመጥ እንዳለብኝ ወሰንኩኝ፡፡ ለዚህ ግምገማ የተጠቀምኩበት ማዕቀፍ በብዙ ቦታዎች የተለመደ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ማዕቀፍ ስድስት መለኪያዎች ቢኖሩቱም አንዱ ከአንደኛው ጋር የሚገናኝ እንደሆነ ለመረዳት አያስቸግርም፡፡ በእንግሊሰኛ (PESTEL – Political, Economy, Social, Technology, Environment and legal framework ) የሚባለው ነው፡፡ በእነዚህ መመዘኛዎች የግንቦት 20 ፍሬዎችን እንመዝናለን፡፡ ለማጠቃለል እንዲመቸን ከመጨረሻው እጀምራለሁ፡፡
የህግ የበላይነትና ግንቦት 20
ደርግ በህግ የሚገዛ መንግሰት ነበር የሚል ሰው ሊኖር አይችልም፡፡ የደርግ ስርዓት ሲወድቅ ያየ ወይም እንዲወድቅ ጠብታም ያዋጣ በህግ የሚገዛ ስርዓት መጠበቁ ከእባብ እንቁላል እርግብ መጠበቅ ሊሆንበት አይችልም፡፡ ስህተትም አይደለም፡፡ የደርግ ስርዓት በተለይ የፖለቲካ ተቀናቃኞች ናቸው ያላቸውን ከህግ ስርዓት ውጭ በኮሚቴ እና በአውጫጭኝ እንደገደለ ምስክር መጥራት ወይም ማስረጃ ማቅረብ አይጠበቅብኝም፡፡ ግንቦት 20 1983 ዓ.ም የደርግ ስርዓት ሲቀየር ያለ ህግ ግድያ ይቀራል የሚል ተሰፋ በአብዛኞች ዘንድ ነበር፡፡ ነገር ግን እንደ አንባገነኑ ደርግ ገድሎ ፉከራው ቢቀርም ያለ ህግ ግድያ፣ እስራት እና ግፍ  ለኢትዮጵያዊያን የእለት ከእለት ጉዳይ መሆኑ አልቀረም፡፡ አንድ እውነትም አለ ደርግ ፍርድ ቤቶችን ለፖለቲካ ቲያትር መስሪያ አልተጠቀመባቸው፡፡ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት የፍትህ ስርዓቱን ባጠቃላይ ለፖለቲካ ግብ ማስፈፀሚያ በማዋል ደርግን አስከንድቶታል፡፡ ሁሉም እንደሚረዳው በጥናትም እንደተረጋገጠው ዜጎች ፖለቲካው ሊበላቸው ሲመጣ “በህግ አምላክ” ብለው የሚጠለሉበት የፍትህ ስርዓት በግንቦት ሃያ ፍሬነት ያለማገኘታችን ነው፡፡ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ዜጎች በፍርድ ቤት ውሳኔ እምነት ያጡባት ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ትሆናለች ብዬ እገምታለሁ፡፡ ግንቦት ሃያ ይህን ሊያረጋግጥልን አልቻለም፡፡ ዕውቀት ያላቸው የህግ ባለሞያዎች ከዳኝነት ይልቅ ጥብቅና ብለው፣ ለፖለቲካ ላለማጎብደድ ወሰነው በችሎታ ከማይመጥኗቸው ዳኞች ፊት ይቆማሉ፡፡ በእውቀት የላቁ ዳኞችን ከዳኝነት ወንበር መግፋት ፍሬ ከሆነ የግንቦት ሃያ ፍሬ አድርገን ልንወሰደው እንችላለን፡፡
ፍርድ ቤቶቻችን የሰጡት ውሳኔ እንኳን ለማሰፈፀም አቅም እንደሌላቸው በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የህሊና እስረኞች ካሉባቸው ሀገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ደርግ ያሰራቸውን ሰዎች መጠየቅ አይከለክልም ነበር፡፡ ይህን ፅሁፍ ከማጠናቀቄ በፊት በዝዋይ የሚገኘውን ጓደኛችንን ተመስገን ደሳለኝን መጠየቅ አይቻልም ተብለን ተመልሰናል፡፡ በህገመንግሰት የተቀመጠን መብት ማንም በመመሪያና ደንብ ሲሸረሸር አቤት የሚባልበት ቦታም ሰርዓተም የሌለበት ሀገር ኢትዮጵያ ነች፡፡ ይህን ማሻሻል የማይችል መሰዋዕትነትን ለማክበር ግንቦት 20 አደባባይ ልንወጣ የምንችልበት ምክንያት አልታይህ ብሎኛል፡፡ የሚገርመው ይህንን የግንቦት 20 ፍሬ ተብሎ እነዚሁ ታሳሪዎች እንዲያከብሩት ይገደዳሉ፡፡
ግዴታን በተመለከተ እንግዲህ ከየመስሪያ ቤቱ እየሾለከ የወጣው ግንቦታ ሃያ ካላከበርክ/ሽ ወዮልህ ማስፈራሪያ መስከረም 2 ለአብዮት በዓል ውጡ ግዴታ በምን እንደሚሻል እና ኢህአዴግ ከደርግ በምን እንደሚሻል የሚያስረዳን ቢገኝ ለመረዳት መዘጋጀት አለብን፡፡ በጭፍኑ ከደርግ እንሻላለን የሚያዋጣ አይመሰለኝም፡፡ ግንቦት 20 አላከብርም ያለ ዜጋ ምን እንደሚደርስበት እና ጉዳት እንዳይደርስበት አፋጣኝ የፍትህ ስርዓት ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡
ሲጠቃለል ግንቦት 20 “በህግ አምላክ” የሚባለውን ኢትዮጵያዊ የህግ አክባሪነት ባህል ያጣንበት ነው፡፡ ፍትህን ለደህንነታችን መሸሸጊያ ሳይሆን ለፖለቲካ መሳሪያነት የበለጠ እንድናውቃት የተደረገበት መሆኑ ጎልቶ የታየተበት ነው፡፡ ከህገ መንግሰት ድንጋጌ ይልቅ የግለሰቦች ቁጣና ግልምጫ የሚፈራበትና የሚከበርበት ሀገር ላይ መኖራቸን ነው፡፡ በተለይ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ቃላቸው ህግ ሊሆን የተቃረበበት ወቅት ነበር፡፡
ቴክኖሎጂ እና ግንቦት 20
ይህን ሚዛን ኢህአዴግ እና የፕሮፓጋንዳ አውታሮቹ የሚጠቀሙበት ቁጥር በማነፃፀር ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ የዛሬ 25 ዓመት 24 ዓመቴ ነበር ዛሬ 49 ስሆን ይህን በምንም መለኪያ የግንቦት 20 ፍሬ አድርጌ ለመቁጠር አልችልም፡፡ በተመሳሳይ በሚኒሊክ ጊዜ ይሁን በደርግ ጊዜ የነበረ የስልክ መስመር ቁጥር ብዛት፣ አሁን ካለው ጋር በማነፃፀር የግንቦት 20 ፍሬን ማግኘት አይቻልም፡፡ በኢትዮጵያ አሁን አሉ የምንላቸው ቴክኖሎጂዎች በተለይ የማህበራዊ ድረ ገፅ መጠቀሚያ የሆኑት መሰረተ ልማቶቸ፣ የሞባይል ስልክ፣ ኮምፒውተር፣ወዘተ ደርግ በስልጣን ቢቀጥል የኢትዮጵያ ምድር ሊረግጡ የሚችሉበት መንገድ አይኖርም ብሎ ማሰብ ይቻላል ወይ? ብሎ መጠየቅ የተሻለ ትክክለኛ ሚዛን ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ደርግ በስልጣን ቢቀጥል ኢትዮጵያ ውስጥ ቴክኖሎጂ እንዳይገባ ያደርግ ነበር? ብዬ ለማሰብ ግን አቃተኝ፡፡
አንድ ነገር ማሰብ ቻልኩ ህወሃት እና ሻቢያ እንዲሁም ኦነግ እና ሌሎች ለመገንጠል የሚሰሩ ድርጅቶች ውጊያ ካላቆሙ፣ አሁን ይገኝ የነበረው እርዳት በገፍ የማይግኝ ቢሆን መሰረተ ልማቶቹ ሊኖሩ አይችሉም ነበር፡፡ ሰለዚህ ደርግ ይህን ሊሰራው የማይችል የነበረው አሁን በመንግሰት ላይ ያሉት ኃይሎች እንዳይስራ የማደናቀፍ ስራ ከሰሩ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ማክተም በኋላ የውክልና ጦርነቶች ስለማይኖሩ በሌሎቸ ሀገራትም ያሉት በመክሸፋቸው ጦርነቶቹ የሚቀጥሉበት እድል ጠባብ ነበር፡፡ እርዳታና ብድር ደግሞ እንደ ኤርትራ እንቢ ያላለ ይልቁንም በዓለም ከሚገኙ ከምስራቅም ከምዕራብም ለመውሰድ ዝግጁ የሆነ ብድር ማግኙት አይቀርም ነበር፡፡ ሰለዚህ በቴክኖሎጂ በኩል ኢትዮጵያ ከዓለም ተለይታ እንደ ኩባ እና ሰሜን ኮሪያ ትሆን ነበር ብሎ ማሰብ አይቻለም፡፡ ይልቁንም በቅይጥ ኢኮኖሚ ጅማሮ የታየው የግል ባለሀብት መስፋፋት በመቀጠል ወደ ተሻለ መሰመር ሊኬድ ይችል ነበር፡፡ ማለትም ተጨማሪ ቴክኖሎጂ የሚያቀርቡ የግል ሴክተሮች ሊኖሩ የሚችሉበት እድል ይኖር ነበር፡፡ ይህን ለማድረግ የደርግ ቅይጥ ኢኮኖሚ ከኢህአዴግ ቅጥ አንባሩን ካጣው “አብዮታዊ ዲሞክራሲ መር ኢኮኖሚ” እንደሚሻል በግሌ አምናለሁ፡፡ ሰለዚህ ግንቦት 20 በቴክኖሮለጂ መስክ ያመጣው ለውጥ ኢህአዴግ ስልጣን ባይዝ እናጣው ነበረ ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡
ሲጠቃለል በዓለም ላይ ሆኖ ከቴክኖሎጅ እራሱን ማራቅ አይቻልም፡፡ ሰለዚህ እኛም አሁን ካለንበት በተሻለ ልንሆን የምንችልባቸውን ወርቃማ 10 ዓመታት (1983-1993) ከተሜ ጠል በሆነ የኢህአዴግ አስተሳሰብ አምልጦናል፡፡ ከዚያም ቀጥሎ ያሉት ዓመታት ከውድድር ይልቅ የግል ዘረፋን በህዝብ ስም ለማድረግ በሚያስችል አሰራር የህዝብ ሀብት ማባከኛ ሆኗል፡፡ በቴሌ መሰረተ ልማት ብንወሰድ ዘላቂ ለመቶ ዓመትና ከዚያ በላይ ማሰብ ባለመቻል፣ በተደጋጋሚ የመሰረተ ልማት ለውጦችና ውድመቶች የደረሱባት ሀገር ነች፡፡ ስለዚህ ግንቦት 20 የሰርዓት ለውጥ ባይመጣ የምናጣው ነገር ሳይሆን ያጣነው ብዙ ነገር እንዳለ ይሰማኛል፡፡ ኢትዮጵያ የዜጎቿን ሙሉ ሀይል መጠቀም ብትችል ከዚህ የተሻለ መሆን እንደሚቻል ይስማኛል፡፡
የአካባቢ ጥበቃና ግንቦት 20
ሀገራችን ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ የደን ሸፋን እየተራቆተ ሄዶ ሁለትና ሶሰት በመቶ ቀርቶዋል ስንባል ልጆች ነበርን፡፡ አሁን ደግሞ ድንገት ተነስተን ከአስራ ሁለት እስከ አስራ አምሰት በመቶ መድረሱ እየተነገረን ነው፡፡ እኔ በእድሜዬ አዲስ አበባ ከተማ ጫካ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ሰፈራችን መሳለሚያ አካባቢ ድረስ ጅብ ይመጣ እንደነበርም አውቃለሁ፡፡ ኮልፌ ከሚኖሩ ዘመዶቼ ከሄድኩ ከመሸ ማደር ግዴታ ነበር፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ አዲስ አበባ ውስጥ በደብሮች እና በዮኒቨርሲቲ እንዲሁም በቤተ መንግሰት እንመለከት የነበረው ደን ወደ ሲሚንቶ ክምርነት እየተቀየረ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ዋና ጊብ ልብ በሉልኝ፡፡ በክልልም ያለው ተመሳሳይ ሁኔታ ነው፡፡ በደርግ በተፈጥሮ ሀብት ልማት በሚኒሰትር ደረጃ አደራጅቶ በእርዳታ የሚገኝ ገንዘብን በነፃ ከመስጠት የአካባቢ ልማት በተለይ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እንዲሰሩ በማድረግ እሰከ አሁን የሚታዩ ውጤቶች ተመዝግበው ነበር፡፡ አሁን ኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ፅ/ቤት የሚባለው ቦሌ ፍላሚንጎ አካባቢ ያለው ህንፃ የዚህ ተቋም ውጤት ነበር፡፡ ከግንቦት 20 በኋላ ይህ መስሪያ ቤት ፈርሶ አሁን ከ20 ዓመት በኋላ እንደ አዲስ እንዲቋቋም ተደርጎዋል፡፡ ይህ የሚያሳየን ደርግ የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅ የተሻለ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ከስራውና ከተገኘው ፍሬ በመነሳት ማለት ነው፡፡ በተወሰኑ አካባቢዎች የተሻለ ሰራ በኢህአዴግ እንደተሰራ አውቃለሁ፣ እነዚህ ስራዎች ግን ደርግ ሃያ አምስት ዓመት ቢቆይ አይስራውም ብዬ ለማመን ግን እቸገራለሁ፡፡ አሁንም ቢሆን በተለይ ከአባይ ግድባ ጋር ተያይዞ መሰራት ያለበት የአባይ ተፋሰስ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት እንዳለበት ባለሞያዎች ቢናገሩም አሁንም ያለው ስራ ከወረቀት እና የውሸት ሪፖርት ከማምረት የሚዘል እንዳልሆነ በአባይ ተፋሰስ ጎግል በማድረግ ማየት ይቻላል፡፡ የሌለ ጫካ አለ ማለት በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን አይቻለም፡፡
ሲጠቃለል ግንቦት 20 መሬትን ዜጎች የኢኮኖሚ መሳሪያ አድርገው እንዲጠቀሙበት ማድረግ ባለመቻሉ ዜጎች ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ የደን ልማቶችን ሊያስራ አልቻለም፡፡ በመንግሰት የደን ጥበቃ ስራ በአግባቡ እየተሰራ አይደለም፡፡ ይልቁንም ያሉትን ባለቤት እንዳይኖራቸው በማድረግ ከህዝብ ቁጥረ መጨመር ጋር ተያይዞ ደን መመንጠር የበለጠ እየሆነ መጥቷል፡፡ ለማነኛውም ማነኛውም ኢትዮጵያዊ የሆነ መንግሰት ቢመጣ በደን ልማት ከዚህ የተሻለ ፖሊሲና ስትራቴጂ በመንደፍ የህዝብ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡ ሰለዚህ በግንቦት ሃያ ካገኘነው ይልቅ ያጣናው ያማዝናል፡፡
ማህበራዊ ልማትና ግንቦት 20
ማህበራዊ ልማትና በጤና በትምህርት መስክ ተወስኖ ይታይ ቢባል አሁን ያሉት ሸፋኖች ከደርግ ጋር ሲነፃፀር ከመቶ እጥፍ እንደሚበልጡ ይታወቃል፡፡  ይህ ግን የግንቦት 20 ፍሬ ሊሆን የሚችለው የጤና ተቋማትን እና ትምህርት ቤቶች የሚያፈርስ ኃይል በሌለበት ነው፡፡ ደርግ ትምህርት ቤት መገንባት አቅም ቢያንሰው ሁሉም ትምህርት እንዲያገኝ በሶሰት ፈረቃ እንዲማር አድርጎዋል፡፡ ይህ ደርግ ዜጎች እንዳይማሩ የሚፈልግ መንግስት ነው ብዬ ለመውሰድ ይቸግረኛል፡፡ ያለምንም የእድሜ ገደብ ወንድ ሴት ሳይባል ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄድ በአካባቢውም የመሰረተ ትምህርት ጣቢያዎች እንዲኖሩ የተደረገበት ነው፡፡ የእኔ እናት ከመሰረተ ትምህርት ተነስታ መደበኛ ትምህርት መግባት የቻለችው ሰርዓቱ በፈጠረው በጎ ተፅዕኖ ነው፡፡ ትምህርቶች ደግሞ ይሰጡ የነበሩት ሁሉም በቋንቋው እንደነበረ ማንም ያውቃል፡፡ ከዚህ አንፃር ተገኘ የሚባል ለውጥ ካለ በኢትዮጵያ “ቁቤ” በግዕዝ ፊደል ፋንታ በኦሮሚያ እና አንዳንድ አካባቢዎች ተግባራዊ ማድረግ መቻሉ ነው፡፡ “በሬሳ” በግዕዝ ፊደልም ቢሆንም በአዲስ አበባ ከተማ ይሸጥ እንደነበር መካድ አይቻልም፡፡ በግሌ ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች እስር ቤት ነበረች ብሎ ተረክ ሊገባኝ አይችልም፡፡ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝም እኔም በደርግ የተማርን እንደነበረ መመሰከር ግድ ይላል፡፡ ዶክተር አሸበርወ/ጊዮርጊሰ ይህን ኢትዮጵያ የብሔሮች እስር ቤት ነበረች ተረክ ይወደዋል፡፡ ሩሲያ ለትምህርት የላከው ግን የደርግ ሰርዓት ነበር፡፡ ሌሎችም እንደዚሁ፡፡
የጤና ሸፋን በሀገራችን በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ እንደጨመረ ይታወቃል፡፡ ልብ ማለት ያለብን ግን ከግንቦት 20 1983 በፊት በቅጡ ተደራጅተው የነበሩ “የወባ መቆጣጣጠር”፣ የኤች፣አይ ቪ፣ የመሳሰሉ ገዳይ በሸታዎችን በትጋት ይሰሩ የነበሩ ተቋማትን በማፍረስ በወረርሽኝ መልክ የተስፋፉበት ወቅት እንደ ነበርም የምንዘነጋው አይደለም፡፡ ያለፉት ሰርዓቶች ኢትዮጵያዊ ዜጎችን አደንቁረውና በበሸታ አማቀው ሊገዙ ፖሊሲ ነበራቸው ብዬ ለማመን አልችልም፡፡
ሲጠቃለል በማህበራዊ ልማት ግንቦት ሃያ የስርዓት ለውጥ ባይደረግ የሚቀርብን ነገር ምን አልባት “ቁቤ” ብቻ ነው፡፡ እርሱም ቢሆን በህዝበ ውሳኔ ሊደረግበት የማይችል ነገር አልነበረም፡፡
ኢኮኖሚ ልማትና ግንቦት 20
ኢህአዴግ ብዙ እንዲዘመርለት የሚፈልገው እና ሌሎች ነገሮቻችን በተለይ ነፃነታችንን አሳልፈን እንድንሰጠው የሚፈልገው ተመዘገቡ የሚላቸውን የኢኮኖሚ እድገቶች ብቻ እዪ በማለት ነው፡፡ አሁንም ደርግ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ እንዳታድግ፣ ዜጎች በድህነት እንዲማቅቁ የሚፈልግ ሰርዓት ነበር ወይ? ብዬ እራሴን ሰጠይቅ በፍፁም እንዳልሆነ እረዳለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ የቅይጥ ኢኮኖሚ በደርግ የመጀመሪያ ዘመን የሚያስቀስፍ እንደነበረ ሁሉ በመውደቂያው ጊዜ ደግሞ “ገንዘብ ገንዘብ ያለው ያውጣ፣ ይስራ ያሰራበት” መመሪያው ሆኖ ነበር፡፡ ደርግ የጥቂት ሰዎች መጠቀሚያ ሀገር ለመመስረት ፍላጎት ያለው መንግሰት አልነበረም፡፡ በቅርቡ ከጓደኞቼ ጋር ሆነን በቀድሞ ስርዓት ብር 500 ይከፈለው የነበረ አንድ ጀማሪ ባለዲግሪ (በዶላር 240) ማለት እንደሆነ እና አሁን ግን 240 ዶላር የሚከፈለው 10 እና 20 ዓመት የስራ ልምድ ያለው ተቀጣሪ እንደሆነ ስናስብ ነበር፡፡ ይህ በምንም ህግ እድገት ሊሆን አይችልም፡፡ የመግዛት አቅሙ የተዳከመ ብር የሚመሰረት ኢኮኖሚ ጠንካራ ኢኮኖሚ ሊሆን አይችልም፡፡ ወደፊትም በውጭ ንግድ የተሻል መሆን ካልቻልን በስተቀር የብር ምንዛሬ እየወረደ የዜጎች ሸክም እየከበደ የሚመጣበት ጊዜ እሩቅ አይደለም፡፡ ይህ ማለት ግን በዶላር ሲለካም ቢሆን የተንደላቀቀ ኑሮ የሚኖሩ ባለ ሚሊዮን ዶላር ጥቂቶች ማፍራት የቻለች ሀገር ሆናለች፡፡ ችግሩ እነዚህ ጥቂት ባለሚሊዮን ዶላር ዜጎች በግልፅ ለህዝብ የሚታወቁ እና የገቢ ምንጫቸውም የሚታወቅ ባለ ሚሊዮን ዶላር በሆኑበት ልክ ግብር የከፈሉ መሆኑን የሚረጋገጥበት ስርዓት አልተዘረጋም፡፡
ኢህዴግ በሚወደው የቁጥር ጫወታ ብንጫወት ከአምሳ ሚሊዮን ህዝብ የዛረ 30 ዓመት 2 ሚሊዮን ቢራብ 4 ከመቶ መሆኑ ነው፡፡ ከዘጠና ሚሊዮን ህዝብ አሁን 10 ሚሊዮን ሲራብ ከ10 በመቶ በላይ ነው፡፡ የተሻለ የኢኮኖሚ ሰርዓት አለኝ የሚለው ኢህአዴግ ከፖሮፓጋንዳ አልፎ ዜጎችን ባስተማማኝ ሊቀልብ የሚችል ስርዓት አልዘረጋልንም፡፡ ያለ እርዳታ ዜጎች ከሞት ሊድኑ የሚያስችል ስርዓት መገንባት አልተቻለም፡፡
ሲጠቃለል ኢትዮጵያ ውስጥ በኢኮኖሚ በተለይ ሁኔታ ሊጠቀሙ የሚችሉ ቡድኖችን መፍጠር ተችሏል፡፡ አብዛኛው ህዝብ የሀገር ሀብት በፍትሃዊነት ሊጠቀም የሚችልበት አልሆነም፡፡ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በዜጎች መካከል በብሔር በዘር መጠቃቀም ብቻ ሳይሆን፣ ከኢትዮጵያዊ ይልቅ ለውጭ ሰዎች የበለጠ ምቹ እንዲሆን የተደረገ ሰርዓት ነው፡፡ ኤኮኖሚው “በዘረኝነት” የተለከፈ ከመሆኑ የተነሳ የብዙ ሌሎች ፖለቲካ ችግሮች ነፀብራቅ ነው፡፡ ዜጎች ሰርተው ለማደግ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ይልቅ ተከታትሎ ለማጥቃት የተደራጀ መሰረቱ “ምቀኝነት” የሚመሰል የኢኮኖሚ ሰርዓት ነው፡፡ የመንግሰት የገቢ መሰረት ታክስ መሰብሰብ መሆኑ ቀርቶ ከዜጎች ጋር ፉክክር የያዘ ያስመስልበታል፡፡

ፖለቲካና ግንቦት 20
ከላይ የዘረዘርኳቸውን መለኪያዎች ለኢህአዴግ በሚያደላ መልኩ ሊሆን ያልቻሉበት ዋናው ምክንያት ፖለቲካው፣ በመበላሸቱ ነው፡፡ በዓለም ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ተሞክሮ ያለፈ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት በመገንባት በህገ መንግሰት ላይ የተቀመጡትን እጅግ አስደማሚ መብቶች ለማክበር ያለመቻል ውጤቶች ናቸው፡፡ ህገመንግሰትን በሚመለከት ከዚህ በፊት የነበሩ መንግሰታትም ቢሆኑ በወቅቱ የነበረውን ስርዓት የፊውዳል ይሁን፣ የኮሚኒሰት የሚመጥን ህገመንግሰት ነበራቸው፡፡ ችግራቸው መተርጎሙ ላይ ነው፡፡ አሁን ያለውም ቢሆን የፖለቲካ ሰነድ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በፍፁም ከመድበለ ፓርቲ ስርዓት ጋር የሚቃረን የአንድን ፓርቲ ብቻ ፍላጎት የሚያሟላ ተደርጎ መቀረፁ ትክክል አይደለም፡፡ ለማነኛውም ህገ መንግሰቱ ይህ ነው፣ ይህ አይደለም ከማለት ይልቅ የተፃፈውን ቢያከብሩልን ብዙ ደስታ ሊፈጥሩ የሚችሉ እና ከላይ የዘረዘርናቸውን የሌሎች መለኪያዎች የታየውን ውድቀት ማከም የሚችል ይሆን ነበር፡፡ በፖለቲካ ሰነድ ውስጥ መሬትን አስመልክቶ የተቀመጠው ድንጋጌ በአካባቢ ጥበቃም ሆነ በኤኮኖሚ መስክ ማሰመዝገብ የሚገባንን ውጤት እንዳናስመዘግብ ያደረገ ማነቆ ነው፡፡
በሀገራችን የሚደረጉ የይስሙላ ምርጫዎች ፖለቲካ በዜጎች ፍላጎት ሳይሆን በጥቂት አውቅላችኋለሁ ባዩች ብቻ እንዲመራ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን የገንዘብ ማባከኛም ጭምር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምርጫ አለ ከማለት ምርጫ የለም የተሻለ የሚገልፃት ሀገር ሆናለች፡፡ ሀገር የሚመሩ ሰዎች ተምረው በአገኙትና በያዙት እውቀት ሳይሆን ሀገር እየመራን ነው እያሉ እየተሳሳቱ የሚማሩባት ቤተ ሙከራ አድርገዋታል፡፡ ከስህተታችን ተመክሮ ወሰደናል እያሉ የሚመፃደቁበት ቦታ የፖለቲካ ስልጣን ሆኖኋል፡፡ ለማነኛውም …… የኢህአዴግ ፖለቲካ ክስረት የክስረታቸው፣ ብሎም የጋራ ክስረታችን መንስዔው እንደሆነ መረዳት ሊቅ መሆን አያስፈልገውም፡፡
ሲጠቃለል ሀገራችን ኢትዮጵያ በፖለቲካው መስረመር ዜጎች የአመለካከት ልዮነታችን ለስጋት ሳይሆን ለዜጎች ምርጫ ለማቅረብ እንደሚያስችል ምርጥ እድል አድርጎ ከመጠቀም ይልቅ፣ ዜጎች በሚይዙት የፖለቲካ አቋም በእስር፣ በግርፋት፣ ቶርቸርን ጨምሮ የሚደረግባት ሀገር ሆናለች፡፡ ግንቦት ሃያ የደርግን ቶርች ሊያስቀርልን ሳይሆን በተሻሻለ ሁኔታ ሊተገብርልን የመጣ እስኪመስለን ድረስ ዜጎች በመሃል አዲስ አባባ ውስጥ ይገረፋሉ ይስቃያሉ፡፡ ሰቃያቸውን ለፍርድ ቤት ሲናገሩ የሚያደምጥ ያለመኖሩ ሳይሆን በዚህ ዓይነት ምርመራ የተገኘን ማስረጃ ተቀብለው ዘግናኝ ውሳኔ በመስጠት የፍትህ ስርዓቱን የፖለቲካ አጋርነት ያረጋግጣለሁ፡፡ ይህ አልበቃ ብሏቸው በቁጥጥር ሰር ያዋሏቸውን እስረኞች በወዳጅ ዘመድ እንዳይጠየቁ፣ በማድረግ ማህበረሰቡን እንዳለ ለማሸማቀቅ ይጠቀሙበታል፡፡ ግንቦት 20 ያስገኘልን አዲስ ነገር ይልቅ ያጣናው ማመዘኑ የሚያስቆጭ ብቻ ሳይሆን በተለያየ ጎራ ተሰልፈው በሀገራችን ማህበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን፣ የፖለቲካ እኩልነት እንዲኖር ዜጎች በሀገራችው ያለምንም ገደብ ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ፣ ወዘተ ለማደረግ መስዋዕትነት የከፈሉትን ኢትዮጵያዊያን ደምና ህይውት ከንቱ እንደቀረ የሚያስቆጥር ነው፡፡ በእኔ እምነት በሀገራችን ለብዙ ዘመናት የተከፈሉት መስዋዕትነቶች ጥቂቶችን ሚሊዮኒየር፣ ጥቂቶችን ደግሞ በስልጣን ማማ ላይ ለመስቀል አልነበረም፡፡ ግንቦት 20 1983 ተከትሎ የመጣውም ለውጥ ሀዲዱን ስቶ ያረጋገጠው ነገር ቢኖር ጥቂት ሚሊኒየሮች እና ጥቂት እምብርት አልባ የስልጣን ጥመኞችን ነው፡፡
ቸር ይግጠመን!!!

No comments:

Post a Comment