Sunday, May 8, 2016

ቅንጅት ፓርላማ አልገባም አላለም የእኔ ዕይታ ….. (የነፃነጽ ዋጋ ሰንት ነው? ከሚለው መፅሃፍ የተወሰደ)



ቅንጅት ፓርላማ አልገባም፣ አዲስ አበባንም አልረከብም በማለቱ ለዚህች ሀገር የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ላይ አሉታዊ አሰተወፅኦ አድርጎዋል የሚለው ድምዳሜ ትክክል አይደለም እላለሁ፡፡ ይህም የሆነው አንዳንዶች ሳያውቁ በሰህተት አንዳንዶቹ ደግሞ አውቀው በድፍረት የሚነዙት ፕሮፓጋንዳ ውጤት ነው፡፡ ሃቁ ግን ቅንጅት የወሰነው ፓርላማ እንግባ አዲስ አበባንም እንረከብ የሚል ነው፡፡ ይህ በቃለ ጉባዔ የተያዘና የተወሰነ ነው፡፡ በግልባጩ ግን ኢህአዴግ ፓርላማ እንዳይገቡ አጥር ያጠረበትና፤ አዲስ አበባን አላሰረክበም ያለበት መሆኑ ነው፡፡(ይህንን ጉዳይ መረዳት የፈለገ ግማሽ ሙሉ እና ግማሽ ጎዶሎ - HALF FULL AND HALF EMPETY- በሚለው ምልከታ መሆን አለበት)፡፡
ኢህአዴግ ይህንን በህዝቡ ዘንድ ለማሰረፅ በስፋት የተጠቀመው በሞኖፖል በያዘው ሚዲያ አማካኝነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ቅንጅት ፓርላማ አልገባም አለ፣ አዲስ አባባን አልረከብም አለ የሚለውን የተሳሳተ መረጃ እውነት አሰኪመስል ድረስ ህዝቡን ግቶታል፡፡ ከተራው ባተሌ እሰከ ምሁር ተብዬው ድረስ ማለት ነው፡፡
የኢህአዴግ ካድሬዎች የሚያሳዝኑኝ ፓርቲያቸው የሚመራቸው በተሳሳተ መንገድ መሆኑን አለመገንዘባቸው ብቻ ሳይሆን ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲኖራቸው የሚፈልገውን ምስል ሰጥቶ ከዚያ ውጭ ማሰብ እንዳያችሉ ሲያደርጋቸው ነው፡፡ ልጅ ሆነን ጭራቅ እንደሚባለው፤ በእውነታው ዓለም የሌለ ነገር ግን ያለ የሚመስለን ነገር ማለት ነው፡፡ አብዛኞቹ የኢህአዴግ አባላትና ካድሬዎች ከሚነገራቸው ውጭ አለቆቻቸው የሚያነቡትን የግል ሚዲያ እንኳን እንዲያነቡና እንዲከታተሉ አይበረታቱም፡፡ የሚነገራቸውና እንዲያውቁ የሚፈለገው ሰለተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የግል ሚዲያዎቹ አፍራሽነት ብቻ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ጭራቅ ከሆኑ የግል ሚዲያዎች አፍራሽ ከሆኑ እነዚህን መቅረብ ምን ያደርጋል፡፡ ይህ የሚደረገው ግን በግልፅ ማወዳደርና ማነፃፀር እንዳይኖር ነው፡፡ 
የኢህአዴግ መካሪ የሆነው ሪፖርተር ጋዜጣ ሁሌም ከሚያነሳቸው ጉዳዮች አንዱ እና የኢህአዴግ አባላትም በተደጋጋሚ የሚሉት ነገር አለ፡፡ ተቃዋሚዎች (በተለይ ቅንጅት) ምራኝ ብሎ የመረጠውን ህዝብ ተመልሶ እንዴት ልምራቸሁ ብሎ ሊጠይቅ ወደ ህዝብ ወረደ ይላሉ (ፓርላማ እንግባ ወይም አንግባ በሚል ከህዝብ ጋር ሲደረግ የነበረውን የህዝብ ውይይት አስመልክቶ)፡፡ በመጀመሪያ ህዝብን ለውሳኔ ማሳተፍ ለቅንጅት ሲሆን ወንጅል ይሆናል፡፡ ኢህአዴግ ግን ብርቱካን ሚደቅሳን ማስር ተገቢ ነበር በሚል ለህዝብ ግንዛቤ ለማሰጨበጥ በመላው ሀገሪቱ ውይይት ሲያደርግ ነበር፡፡ ይህ ዲሞክራሲያዊ ነው፡፡
ለማነኛውም ፓርላማ እንግባ ወይስ አንግባ የሚል ውይይት የተካሄደበት መሰረታዊ ምክንያት ትክክል ነበር፡፡ የህዝብ ድምፅ በተሟላ ሁኔታ ይከበር የሚል ይህም የሆነው ድምፃቸውን ለቅንጅት ስጥተው በጠራራ  ፀሐይ የተዘረፉ ዜጎች ሰለነበሩ ነው፡፡ ውይይቱ ለህዝብ በመከፈቱ የኢህአዴግ ሴረኞች መግቢያ ቀዳዳ አግኝተው ፓርላማ መግባት አይገባም የሚል አጀንዳ በስፋት አራምደዋል፡፡ እነርሱ ብቻም አይደለም ከምር የህዝብ ድምፅ መከበር አለበት የሚሉ ደጋፊዎችም ፓርላማ መግባት ትክክል አይደለም ብለው ሞግተዋል፡፡ በማይጠበቅ ሁኔታም ለደሞዝ ከሆነ እኛ እንከፍላችኋለን እሰከ ማለት የደረሱ ሰዎች ነበሩ፡፡ በቅንጅቱ የተወከሉት የመድረክ መሪዎች ግን ሲያስተላለፍ የነበረው መልዕክት ግን ውሳኔውን ፓርቲው እንደሚያደርግ ነገር ግን የፓርቲውን ውሳኔ ምንም ይሁን ምን ግን ህዝቡ ውሳኔውን በፀጋ እንዲቀበል ነበር፡፡
ይህ አካሄድ ያልጣመው ኢህአዴግ/መንግሰት ግን ቀጣይ ህዝብን የማወያየት ዕቅዶችን አገዱ፤ እንደዚያም ሆኖ ግን ቅንጅት ላዕላይ ምክር ቤት ታሪካዊ ውሳኔ ነው ያስተላለፈው የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ ወደ ፓርላማ አትግቡ ያለውን የህብረተሰብ ድምፅ ከግምት ውስጥ ያሰገባና ኢህአዴግ ፓርላማ እንዲገቡ ከፈለገ ደግሞ ዕድል የሚሰጠው ነበር፡፡ ኢህአዴግ ግን የዚህ ዓይት ታሪካዊ ዕድሎችን የመጠቀም በዓል ሰለሌለው አንባገነንቱን ይፋ ያደረገ ጨካኝ እርምጃ መሰረት ያደረገውን ስትራቴጂውን ተግባራዊ አደረገ፡፡ የህዝብ ተመራጮችን ማሰርና ደጋፊዎችን በጠራራ ፀሐይ በአልሞ ተኳሾች መግደል፡፡
የቅንጅት ላዕላይ ምክርቤት ፓርላማ እንግባ የሚል ውሳኔ ነው የወሰነው ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ግልፅ ለማድረግ፡፡ ይህ ውሳኔ ሲወሰን የተለያዩ አሰቦች ሲንሸራሸሩ ሰለነበር ጉዳዮችን ነጥብ በነጥብ ለይቶ በማየት በመጨረሻ ውሳኔው የተወሰነው በሙሉ ድምፅ ነው፡፡ ልደቱን ጨምሮ ማለት ነው፡፡ ከየት አምጥቶ እኔ እንጋብ ስል እነርሱ /አክራሪ የቅንጅት አመራሮች/ አንግባ አሉ እንደሚል ግልፅ አይደለም፡፡ ፓርላማ ለመግባት ግን ለኢህአዴግ የቀረበለት ቀላል ጥያቄዎች የሚከተሉት ነበሩ፤ (በቅንፍ የተጨመሩት የህገ መንግሰት አንቀፆች የኔናቸው)
  1. ነፃ፣ገለልተኛና ጠንካራ የማሰፈፀም ብቃት ያለው የምርጫ ቦርድ (ህገ መንግሰት አንቀፅ 102/
  2. ነፃና ገለልተኛ ፍርድ ቤት፤/ህገ መንግሰት አንቀፅ 79/
  3. የፖሊስ፣ የደህንነትና የመከላከያ ከፖለቲካ ጣልቃገብነት መራቅ፣(ህገ መንግሰት አንቀፅ 87/5፣)
  4. ሰኔ1/1997 ዓ.ም የተገደሉ ኢትዮጵያዊያንን ጉዳይ የሚያጣራ ገለልተኛ ኮሚሽን እንዲቋቋም፣ ግድያውን በፈፀሙ ላይም ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፤
  5. ፍትሐዊ የመንግሰት ሚዲያ አጠቃቀም እንዲኖር የግል ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ እንዲቋቋም፤(ህገ መንግሰት አንቀፅ 29/5)
  6. ከግንቦት ሰባት በኋላ በተወካዮች ምክር ቤት አሰራርና የአዲሰ አበባ መሰተዳድርን በተመለከተ የወጡትን ህጎች ቀድሞ ወደነበሩበት መመለስ፤
  7. በፖለቲካ አመለካከታቸው የታሰሩ አባላትን መፍታት የታሸጉ ቢሮዎቻችንን መክፈት እንዲሁም በተቃዋሚ ፖርቲ አባላት ላይ ያለው ማሳደድ እንዲቆም፤
  8. እነዚህን ጥያቄዎች በተግባር መዋላቸውን የሚከታተልና የሚያስፈፅም ነፃ ኮሚሽን ይቋቋም፤
የሚሉት ናቸው፡፡
የተጠየቁት ጥያቄዎች እነዚህ ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ በህገ መንግሰት ላይ ከዚህ በተሻለ ዝርዝር የተቀመጡ ነገር ግን ገዢው ፓርቲ ሊያከብራቸው ያልቻላቸው፣ በተራ ቁጥር አራት የተጠቀሰው ደግሞ ተቃዋሚዎች ወንጀል ሰርተዋል ካለ ለራሱ ለመንግሰት መረጃ የሚያገኝበት ነበር፡፡ ይህም ሆኖ በጥቅምት ከተፈፀመው ድጋሚ ጭፍጨፋ በኋላ የተቋቋመው ኮሚቴ የግድያውን ምክንያት እንዳያጣራ (መንግሰት የወሰደውን እርምጃ ተመጣጣኝ ነው አይደለም የሚለው ብቻ እንዲያይ) ተደረገ፡፡
ከላይ የተዘረዘሩትን ነጥቦች መንግስት ተቀብሎ የቅንጅት መሪዎች ፓርላማ እንዲገቡ ማድረግ ቀላል የሚባል ስራ ነበር ለመንግሰት(በተለይ ለህዝብ ክብር ሲባል የቀረቡ ከመሆናቸው አንፃር - ፓርላማ አትግቡ ሲል የነበረውን የህብረተሰብ ክፍል ጥያቄ ለማስታመም ሰለሆነ)፡፡ ፓርላማ እንዲገቡ ሳይሆን እስርቤት ማስገባት በሚል በቂመኝነት ላይ ተመስርቶ የተነደፈን ስትራቴጂ ለመፈፀም የሚተጋን መንግሰትና/ፓርቲ ለካድሬዎቹ ቅንጅት ፓርላማ አልገባም አለ ብሎ ይነግራል፡፡ ካድሬዎችም ይህንኑ ይደግማሉ፡፡ ጉዳዩም ካለፈ በኋላ ለግል ግንዛቤ እንኳን እንዲሆናቸው በማለት ነገሩን በጥልቀት ከማየት ይልቅ ክሱን ወደ ማይመለከተው ቅንጅት ለማድረግ ይጥራሉ፡፡ እነዚህ ታዳ ምድባቸው አውቀው በድፍረት ከሚያጠፉት ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
ለዚህ ማሳያ አቶ በረከተ ሰምዖን በመፅሐፋቸው እንዲህ ብለው ገልፀውታል፤
“ከቅንጅት ኢዴፓ፤ ከሌሎች ተቃዋሚ ድርጅቶች ደግሞ ህብረትና ኦፌዴን መሰከረም ላይ የተሰመረው ቀይ መሰመር የምር እንደሆነ ተገንዝበው አቤት ወዴት ሲሉ ሰንብተዋል፡፡ …….. በመቀጠልም የህብረት መሪዎች … በአድርባይነት ከምንጠላው ከአቶ ልደቱ ጋር አብረን በአንድ ጠረጴዛ አንቀመጥም አሉን፡፡ በበኩላችን አንዱ ሌላውን በአድርባይነት ሊከስ እንደማይችል እናውቃለን፡፡ እነርሱም ያውቃሉ፡፡ ሁለቱም ወገኖች (ህብረትና ኢዴፓ መሆናቸው ነው) ፀጋዬ ገብረመድህን እሳት ወይ አበባ በሚለው የግጥም መድብሉ በተስለምላሚነት የገለፃትን ቢራቢሮ ያስንቁናል፡፡” ገፅ 182 እና 183……………..
አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በኢቲቪ/በሬዲዮ በሚቀርቡ ታቅደው ለማሳሳት በሚቅርቡ መረጃዎች ቢሳሳት ችግር የለውም ሊባል ይችላል፡፡ የተማረ የሚባለው ክፍል ግን እንደፈለገ የተሳሳተ መደምደሚያ መስራት አግባብ አይመስለኝም፡፡ የተማረ የሚለው መጠሪያ የተጨመረለት የተነገረን ለመስማት ብቻ ሳይሆን፣ ያሉትን መረጃዎች መርምሮ ለማየት የሚችል ነው በሚል ይመስለኛል፡፡
የታሪክ ተመራማሪዎች በተለይ ቅንጅት ለአቅመ ፓርቲ ሳይበቃ/ሳይቀናጅ መፍረስ ዋና ዋና ምክንያቶቸ፤ በተለይም ደግሞ በቅንጅት ጊዜ የተወሰዱትን የሠላማዊ ትግል አካሄዶች ጠንካራና ደካማ ጎኖቹን በዝርዝር እንዲፈትሹት እጠይቃለሁ፡፡ ይህ ሲሆን ከኢህአዴግም ሆነ ከቅንጅትም ግንኙነት የሌላቸው ቢሆኑ(ግንኙነት የለንም በሚል ሳይሆን የምር የሌላቸው ቢሆኑ ይመረጣል) ለታሪካችን እጅግ ጠቃሚ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በግሌ ቅንጅት በወቅቱ  በነበረው ነባራዊ ሁኔታ ኃላፊነት የሚሰማው ውሣኔ እንደወሰነ ይሰማኛል፡፡ ምንም ሰህተት የለውም ልል ግን አልችልም፡፡ አንድ አንድ ጉዳዮች ከኩነት በኃላ ሲታዩ እንዲህ ቢሆን ማለት ይቻላል፡፡ ለምሣሌ ቅንጅት ያሰቀመጣቸውን ሰምንት ነጥቦች ባያነሳ ሊባል ይችላል፡፡ ይህንን ግን ማነፃፀር የሚኖርብን በዚያን ጊዜ ከነበረው የህብረተሰቡ ድምፃችን ይከበር ከሚለው ሰሜት ጋር በቅጡ መታየት ይኖርበታል፡፡
አዲስ አበባን በተመለከተ ፓርላማ አልገባም አሉ ካሉ በኋላ በመጨረሻም ከንቲባ ሆኖ የተመረጠውን ዶክተር ብርሃኑን ካሰሩ በኋላ እንደ አሸንጉሊት የሚያሽከረክሯቸውን ሠዎች (በተለይ እነ አየለ ጫሚሶን) ይዞ አዲስ አበባን ለማስረከብና የአዲስ አበባን ህዝብ ሊቀጡት ወስነው ነበር፡፡ ይሄን ጊዜ ከእስር ቤት ውጭ የሚገኙ የቅንጅት አባላት ይህ ሴራ እንዳይሳካ አድርገዋል፡፡ እኔንም ጨምሮ ይህ ደግሞ ትክክለኛ ውሳኔ ነበር፡፡ ሰለ አዲስ አበባ መረከብ ዶክትር ብርሃኑ በነፃነት ጎህ ሲቀድ በሚለው ከቃሊቲ በፃፈው መፅሐፉ በደንብ አስቀምጦታል፡፡ ይሀንን አንብቦ የቅንጅት ውሳኔ ምን አንደነበር መረዳት የባለቤቱ ይመስለኛል፡፡
ለማጠቃለል ቅንጅት ፓርላማ አልገባም አዲስ አበባንም አልረከበም የሚል አቋም አልወሰደም ሰለዚህ የቅንጅት አመራሮች እስር ቤት ከመግባት ፓርላማ ይሻላቸው ነበር የሚለው ምርጫ በኢህአዴግ የተወሰነ እንጂ በቅንጅት የተወሰነ ያለመሆኑን መረዳት ያሰፈልጋል ባይ ነኝ፡፡ ይህንን ውሳኔ በአቶ በረከት ሰምዖን የሁለት ምርጫዎች ወግ አንዲህ ተብሎ ተቀምጦዋል
“… የፌዴራል ፓርላማ ውስጥ እሰከገባችሁ ድረስ አዲሰ አበባን ትረከባለችሁ እንጂ    አንዱን ነጥላችሁ (አዲስ አበባን መረከብ ማለቱ ነው) እንድትወስዱ አይፈቀድም አለ፡፡” ገፅ 157
ሰለዚህ አዲሰ አበባን ቅንጅት አንረከብ አለ ነው መልሱ ሁይስ መንግሰት/ኢህአዴግ አላስረክብም አለ ነው የሚቀርበው፡፡ ወይም ሚዛናዊ ለመሆን ኢህአዴግ አዲስ አበባን ለማስረከብ ቅድመ ሁኔታ አሰቀምጦ ነበር እንበል፡፡ አሁንም ዳኝነቱን ለገለልተኛ አካል መተው ይሻላል፡፡


No comments:

Post a Comment