Tuesday, January 28, 2014

የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ለራሱ ሲል ይጣፍጥ ግርማ ሠይፉ ማሩ



የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የስራ እንቅሰቃሴን አሰመልክቶ  አዲሱ የቦርዱ ስብሳቢ አቶ ሬዲዋን ሁሴን ሪፖርት ለምክር ቤት አቅርበው ነበር፡፡ እኔም የበኩሌን አሰተያየት እና ጥያቄዎች አቅርቤ ነበር፡፡ ሪፖርቱ ባጠቃላይ ሲታይ የምናውቀውን ደካማ ተቋም በግልፅ ያሳየን ነበር፡፡ በሪፖርቱ እንደመልካም ስራ የቀረበው ደግሞ ያፈርንባቸው  ዶክመንተሪዎች መሆናቸው ሌላ ነጥብ ነው፡፡ እነዚህ ስራዎቸ ደግሞ በህዝብ የተወደዱ ናቸው ተብለናል፡፡ አስገራሚ ደግሞ በድርጅቱ የሚሰራውን ፕሮግራም የሚወደው ህዝብ ለቴሌቪዥን ኪራይ በዓመት አምሳ ብር ለመክፈል ያለመፈለግ ዝንባሌ ያሳያል መባሉ ነው፡፡ በእኔ አረዳድ የህዝቡ ያለመክፈል አዝማሚያ ምንጭ ህዝቡ በደረሰበት የዕድገት ደረጃ የሚመጥን የቴሌቪዥን አገልግሎት ስለማያገኝ ነው፡፡ አንድ የእግር ኳስ ጨዋታ ለማየት ህዝቡ ስንት እንደሚከፍል እናውቃለን፡፡
በዕለቱ ካቀረቡኩት ጥያቄ ምላሽ የተነፈገው ዋነኛው ጥያቄ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በሪፖርቱ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ከማጠናከር አንፃር ስራዎች ተሰርተዋል በማለት ያቀረበው ልክ አይደለም የሚል ሲሆን፤ ለዚህ ማሳያም አንድነት እና ኢህአዴግ እኩል ፓርቲዎች ቢሆኑም የአንድነት ጠቅላላ ጉባዔ በሚዲያ ሳይዘግብ የኢህአዴግን ጉባዔ ግን ከባህርዳር በቀጥታ ስርጭት ጭምር ሲዘገብ እንደነበረ ያቀረቡክት ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ ክቡር ሚኒስትሩ እንደ ካድሬም ማሳሳቻ ነገር ስለ አልታያቸው በዝምታ ማለፉን እንደ ዘዴ መምረጣቸውን ወድጄዋለሁ፡፡
ሌሎችን አሰተያየቶችን በተመለከተ ደግሞ ሃሳቡን በማሳሳት ተርጉመው ለማሳሳት የሞከሩባቸውን ናቸው፡፡ በሪፖርቱ ውስጥ “ብሔራዊ መግባባት ለማጎልበት ጥረት ተደርጎዋል” ይላል፡፡ እኔ ይህን የሚደግፍ ሰራ በሪፖርቱ ውስጥ የሌለው መሆኑን አመልክቼ ይልቁንም ድርጅቱ ያለመግባባት ለማምጣት ነው የሚሰራ የሚመስለው የሚል ሃሳብ ስሰነዝር፡፡ አቶ ሬድዋን ግን የሚሰሙት መበታተን ብለው ነው፡፡ ኢህአዴግም ሆነ ካድሬዎቹ አንድ ጉዳይ ጠንከር ብሎ ከታያቸው መመሽጊያቸው ይህች ሀገር ልትበተን ነው ወደሚለው ፅንፍ መሄድ ነው፡፡ ኢህአዴግ በፈለገው አስማት ከዚህ ወንበር ቢነሳ፤ ይህች ሀገር ምንም ዓይነት የመበተን አደጋ የለባትም፡፡ ለምን ይህን ካርድ እንደሚወዱት አይገባኝም፡፡
ሌላው አዲስ የሰማሁት ፍልስፍና ደግሞ “መነሻችን ከተለያየ፣ መድረሻችንም ይለያያል” የሚለው ነው፡፡ በየትኛውም ህግ አንድ ቦታ ለመድረስ ከተመሳሳይ ቦታ መነሳት የግድ አይልም፡፡ በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ያሰፈልጋል ብለን ከልብ የምናምን ሰዎች መነሻችን እንደሚለያይ ብቻ ሳይሆን፣ ልንሄድበት የምንፈልጋቸው መንገዶች በአብዛኛው የተለያዩ ቢሆኑ እንኳን መድረሻችን  አንድ ወይም ተመሳሳይ ነው የሚል እምነት አለን፡፡ ይህውም የሀገራችን ዕድገትና ብልፅግና ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚሆነው ሰላም ዲሞክራሲ እና የዜጎች ሰብዓዊ መብት የሚከበርበት ሀገር እና የፖለቲካ ስርዓት ሲፈጠር እንደሆነ ጥርጥር የለንም፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ትግሉ፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ “ትግል” የሚለውን ቃል ከፖለቲካችን ለማውጣት እና ድህነትን በጋራ ለምናደርገው ርብርብ ብቻ እንድንጠቀምበት ለማድረግ ኳሱ ያለው በኢህአዴግ እጅ ነው፡፡ ኢህአዴግ ከቆረበበት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ/ግራ ዘመም ፖለቲካ መውጣት የግድ ይለዋል፡፡ ምክንያቱም የዚህ መስመር ተከታዮች ትንተና የሚያደርጉበት ማዕቀፍ ሁልጊዜ ተቃራኒ ወገን ይፈልጋል፡፡ ምቀኛ አታሳጣኝ ፍልስፍና ነው፡፡ ለውጥ ለማምጣት ደግሞ ይህ ተቃራኒ ወገን መጥፋት አለበት ብለው ያምናሉ፡፡ ለዚህ ነው ገድለው እንኳን እርግጠኛ ስለማይሆኑ መቃብር ላይ ግንብ የሚገነቡት፡፡ በዚህ ዓይነት የትንተና መስመር የሚመራ ፓርቲና መንግሰት የመድበለ ፓርቲ ሰርዓትን ከምር ሊወስድ አይችልም፡፡ ስለዚህ ድምዳሜው “መነሻችን ከተለያየ፣ መድረሻችንም ይለያያል” የሚል ፅንፍ የሚደርሰው፡፡
ኢህአዴግ እና አባላቱ አብዮታዊ ዲሞክራሲ አመለካከት መያዝ ምርጫቸው ከሆነ መከበር ያለበት መብት ነው፡፡ ልናከብርላቸው ይገባል፡፡ ሆኖም ግን ልማታዊና ዲሞክራሲያዊ አመለካከት መገንባት እያሉ በየሲቪል ሰርቪሱ እና መንግሰት ተቋማት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ማጥመቅ፤ ህገ መንግሰታዊ ስርዓቱ የፈቀደውን የሃሳብ ልዩነትን መድፈር ነው፡፡ ለዚህ ሁነኛ ምሳሌ ደግሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት አንዱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህገ መንግሰት አንቀፅ 29/5 “በመንግስት ገንዝብ የሚካሄድ ወይም በመንግስት ቁጥጥር ስር ያለ መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አሰተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችል ሁኔታ እንዲመሩ ይደረጋል፡፡” ይላል፡፡ ይህን ህገ መንግሰታዊ ድንጋጌ ጥሰው የመንግሰት ሚዲያዎች ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ መንገድ ውጭ ሌሎች አመለካከቶችን ለማስተናገድ ለዜጎችም ሆነ ቡድኖች አንድም ክፍት ቦታ ለመስጠት ዝግጁ አይደሉም፡፡ ይልቁንም አቋም ይዘው የስም ማጥፋት ዘመቻ ይሰራሉ፡፡
በቅርቡ በተደጋጋሚ እየሰማነው ያለው “ልማታዊና ዲሞክራሲያዊ መንግሰት” የሚለው ፍልስፍና መሰረቱ አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ የሚባለው የት መጤው የማይታወቅ ፍልስፍና እንደሆነ ቢታመንም አብዮታዊ የሚለውን ትተነዋል ማለት ጀምረዋል የሚል ነው፡፡ ይህ ጥሩ ሽግሽግ ይመስለኛል፡፡ ግልፅ መሆን ያለበት ግን ልማትና ዲሞክራሲ ግቦች ሲሆን እዚያ ለመሄድ የምንከተለው የፖለቲካ ፍልስፍና በግልፅ ነጥሮ መውጣት እና ለህዝብ ይፋ መሆን ይኖርበታል፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ የፖለቲካ ፍልስፍና አባታቸው በህይወት ስለሌሉ ይህ መንገድ ለኢህአዴጋዊያን ግራ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አንድ ጓደኛዬ ከኢህአዴግ ሰፈር አዳዲስ ቃላት ጠፍቶዋል ነገሩ ምንድነው ብሎኝ ነበር፡፡ ይህን ነገር ልብ ብላችኋል?
ሌላው በኢህአዴግ ሰፈር ድንገት ከሚመዘዙት ካርዶች አንዱ ህገ መንግሰት መጣስ፣መናድ ወይም አለማክበር የሚለው ነው፡፡ ህገ መንግስቱን እንደ ቅዱስ መፅሃፍ የማይመለከቱ ብዙ ወገኖች አሉ እኔም አንዱ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ሊሻሻሉ የሚችሉ ጉዳዮች እንዳሉት ሰለምናምን፡፡ ይህም ህገ መንግስታዊ ስለሆነ ነው፡፡ የህገ መንግሰቱ አንቀፅ 104 እና 105 ህገ መንግሰት እንዴት እንደሚሻሻል የሚገልፁ ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው አሁን ባለው ህገ መንግሰት ከምር በማክበርና በማስከበር ረጅም ርቀት ልንሄድ እንችላለን ብለን ገዢውን ፓርቲ እና መንግሰትን ህገመንግስቱን ለማክበር እና ለማስከበር በፅናት እንዲቆሙ የምንሞግተው፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ህገ መንግሰታዊ ድንጋጌዎችን በማክበር ሚዲያዎቹ የሁሉም ዜጎች የጋራ መጠቀሚያ መድረክ እንዲሆኑ መስራት የሚኖርባቸው፡፡ ይህ ግን በቅረቡ የሚሆን አይመስልም ምክንያቱም የድርጅቱ የቦርድ ስብሳቢ አቶ ሬድዋን በጀመሩት መስመር እንደሚቀጥሉ አበክረው ለምክር ቤቱ ገልፀዋል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ስለ አቶ ሬድዋን የቦርድ ስብሳቢነት ስናወራ አንድ የማክያቶ ቡድን አባል የመንግሰት ቦርዶች መብዛት አንስቶ ካጫወተኝ በኋላ ውስጥ ለውስጥ በቦርድ አባልነት ሽኩቻ እንዳለ እና ምክንያቱም ከቦርድ አባልነት ጋር ተያይዞ ከግብር ነፃ የሆነ ከፍተኛ ገቢ እና ሌሎች ጥቅሞች እንዳሉ ገለፀልኝ፡፡ ለነገሩ ሚኒስትሮቻችን በቦርድ አባልነት በሚያገኙት ድጎማ ጭምር እንጂ በመንግሰት በሚከፈል ደሞዝ መኖር እንደማይችሉ ማን ያጣዋል በሚል ወሬው ተቋጭቶዋል፡፡ እሰኪ አንባቢያን የምታውቁትን በቦርድ የሚተዳደር መስሪያ ቤት እና የቦርድ አባላት ጥንቅር የሚከፈላቸውን አበል ጭምር ዘርዘር አድርጉና አስረዱን፣ ስለ ፍትሃዊነቱ ግልፅነት እንዲኖረን ብዬ ነው፡፡
በመጨረሻም አቶ ሬድዋን በሳውዲን ስለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የመንግስታቸውን አቋም የገለፁበት ቁርጥ አቋም ከአንድ ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር የሚጠበቅ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ በህገ ወጥ መንገድ ሳውዲ የገቡትን ዜጎች ህገወጥ ብሎ በስማቸው መጥራት ምንም ችግር እንደ ሌለው ይልቁንም በሌላ ስም ቢጠሩ ወይም ዝም ቢባል ልክ እንዳልሆነ አስረድተውናል፡፡ ይህ ደግሞ የፓርቲያቸውና መንግሰታቸው እውነት መሸፋፈን እንደማይወድ ማሳያ እንጂ ሌላ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት አስመረውበታል፡፡ በእኔ አረዳድ በመኪና አደጋ ጉዳት የደረሰበትን ሰው በአደጋው ቦታ ተገኝቶ ለምንድነው ግራ ቀኝ አይተህ የማትሻገረው ብሎ እንደማላጋጥ ነው፡፡ በሳውዲ ሀረቢያ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖቻችን አብዛኞቹ ልክ በመሰላቸው መንገድ ከሀገር ስራ ፍለጋ መውጣታቸው የሚካድ አይደለም፣ ይህም በሳውዲ መንግሰት ዕይታ ሕገወጥ ለሆን ይችላል፡፡ የእኛ ሚዲያ በሳዊዲ መንግሰት ጎን ቆሞ ዜጎቹን ህገወጥ እያለ ማሸማቀቅ ተገቢ ነው ብሎዋል፡፡ ስለዚህም በሚዲያ በተደጋጋሚ “ህገ ወጥ” መሆናቸውን መንገር ተገቢና ትክክል ከደረሰባቸው ጉዳት የሚያገግሙት በስማቸው “ህገ ወጥ” ተብለው ሲጠሩ ነው ተብለናል፡፡ ስምተናል!! ግን መስማት መስማማተ አይደለም፡፡
ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን እንደ ድርጅት ልሳን እየተጠቀመበት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ይህ ደግሞ ኢህአዴግ ከህግ አግባብ ውጭ የያዘውን የፓርቲ ሚዲያ ማለትም ፋና ብሮድካስትን ጨምሮ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን ትልልቅ ሚዲያዎች ተቆጣጥሮ ሀገሪቱን የአብዮታዊ ዲሞክራቶች መንደር ለማድረግ ነው፡፡ እርግጠኛ መሆን ያለብን ግን የፈለጉትን ያህል ሚዲያውን ቢቆጣጠሩት የኢትዮጵያ ህዝብ ሌሎች አማራጮችን ተጠቅሞ ከዓለም እኩል ይሆናል እንጂ በእነርሱ መንደር ውስጥ ሲርመጠመጥ አይገኝም፡፡ ይህን የአፈና መረብ ሊበጥሱ የሚችሉ ዜጎች እንደ አሽን እየፈሉ ይገኛሉ …….. ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ነው፡፡


Thursday, January 23, 2014

ዲታ መንግሰትና ምስኪን ህዝብ



የ “አባት ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” የሚባል አባባል አለ፡፡ ይህን አባባል ሰረዳው ዘራፊዎችን ማስቆም ካልቻልክ በዘረፋወ በመሳተፍ የድርሻህን ማንሳት ችግር የለውም የሚል እንደምታ እንዳለው ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ይመስለኛል በአብዛኛው የመንግሰት በሚባለው ንብረት ላይ በዘረፋ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ድርሻቸውን እንደወሰዱ እየተሰማቻው ይህን በማድረጋቸው አንድም ቅሬታ አይታይባቸውም፡፡ ይልቁንም የጀግንነት ሰሜታቸው ሀይሎ ይህን ዘረፋ የሚጠየፉትን እንደ ጅል መቁጠር እየተለመደ መጥቶዋል፡፡ በዘረፋው ላይ ያልተሳተፉም ቢሆኑ ይህ የመንግሰት የሚባለው ንብረት ሲዘረፍ ከመመልከት ዘለው ለምን አይሉም፡፡ አንድ አንዶች ደግሞ በመዝረፍ ባይሳተፉም በማዘረፍ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ለመዝረፍም ለማዘረፍም ጥሩ ማሳያ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡
የአዲሰ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አሰርቶት ከአገልግሎት ውጭ ሆኖ የነበረው ከመሰቀል አደባባይ ቃሊት ያለው መስመር አሰፋልቱ እየፈረሰ ሰፊ ጉድጓድ እየተማሰ አደሲ ቁፋሮ እየተካሄደ ሰመለከት ከባከነው ገንዘብ ይልቅ ያብከነከነኝ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ፣ ካልቻሉም እራሳቸው የሚጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትራችን የሰጡት ማብራሪያ ትውስ ብሎኝ ለምን መዋሸት ያስፈልጋል ብዬ ጉዳዩን ማንሳት ወደድኩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመዝረፍ ተሳትፈዋል ለማለት መረጃም ማስረጃም የሌለኝ ቢሆንም ሲዘረፍ ዝም ብሎ በመመልከት እና ሲከፋም ለማዘረፍ ከለላ እየሰጡ መሆናቸው ግን የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡
ከመስቀል አደባባይ ቃሊቲ ድረስ ያለው መንገድ አንድ ዓመት እንኳን ሳያገለግል በመንገዱ አሰፋልት መሆን ምክንያት የተማሪዎችን ህይወት መቅጠፍ ሳይበቃው ይህን ሊከላከል ይችላል የተባለ የብረት አጥር ግንባትን ጨምሮ ከፍተኛ ገንዘብ ከንቱ ቀርቶዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ ዋነኛ ተጠያቂ መሆን ያለበት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ሲሆን፤ የባለስልጣኑ መስሪያ ቤት ሃላፊ ጉዳዩን፤ የባቡር መስመሩ ድንገት በመምጣቱ ነው የሚል አስተያየት መስጠት ዕቅድ አልባ መንግስት መሆኑን ማሳያ ነው፡፡ ይህ በሚመለከት ሃሳቡን ያጋራኝ በመንገድ ዘርፉ ኃላፊ የሆነ ሰው የነገረኝ ደግሞ፤ በባቡር ኮርፖሬሽን ቦርድ ውስጥ የአዲስ አበባ መንገዶች መስሪያ ቤት ኃላፊ ያሉበት መሆኑን አስተያየታቸውን አሰገራሚ ያደርገዋል ነው ያለኝ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ኃላፊው ባቡር መስመሩ መንገዱን ሊጠቀምበት ይችላል የሚል ግምት ነበር ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችንም የዚህ ሰበብ አውቀው ይሁን ሳያውቁ ሰለባ የሆኑ ይመስለኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ማስተባበያ በሰጡበት ወቅት ባለ ሞያ መሐንዲስ መሆናቸውን ጠቅሰው ከላይ ያለው አሰፋልት ብቻ ስለሚነሳ ከሰር ያለው ሙሊት ስራ ላይ ይውላል በዚህ የተነሳ ብክነቱ ዝቅተኛ ነው ብለው ለኢትዮጵያ ህዝብ ገልፀው ነበር፡፡ የነበራቸው መረጃ ይህ ከሆነ አሁን እያየን ያለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ሳይሆን እንደ አዲስ ተቆፍሮ ሌላ እየተሞላ ነው፡፡ አሁንም ጉዳዩ ቀላል ነው ሊሉን አይችልም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዋሽተውናል፤ አልዋሸውም የሚሉ ከሆነ ደግሞ በሹሞቻቸው ተታለዋል፡፡ ሰለዚህ የተሳሳተ መረጃ የሰጧቸውን ይጠይቁልን ወይም እራሳቸው ኃላፊነቱን ይውሰዱ፡፡ ይህ የጠቅላይ ሚኒሰትሩ አሰተያየት የህዝብ ሀብት ብክነት ሲነገራቸው እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ከለላ መስጠታቸው ተባባሪነታቸውን ነው የሚያሳየው፡፡ አሁንም አሰቸኳይ እርምጃ እንዲወስዱልን እንጠይቃለን፡፡
በቅርቡ ደግሞ ከፍተኛ ወጪ የተደረገበት ግንባታ ከተከናወነ በኋላ መፍረሱን አስመልክቶ መስሪያ ቤቱ ኃፊዎች የሰጡት አሰተያየት አሁንም ያስገርማል፡፡ ዲዛይን ለውጥ በመደረጉ የተነሳ ግንባታው መፍረሱን አረጋግጠው፤ እንደዚያም ቢሆን ወጪው የሚመለከተው ግንባታውን የሚያከናውነው የቻይና ድርጅት ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ኮንትራቱ ሰሰጥ ዲዛይንም ግንባታንም የሚጨምር የኮንትራት ዓይነት ስለሆነ ነው ብለውናል፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ይህ ኮንትራት የተሰጠበት ዋጋ እንደፈለጉ አባክነውም ቢሆን አትራፊ ያደርጋቸዋል የሚል እንደምታ በጆሮዋችን ያቃጭላል፡፡ ድሮም ቢሆን ገንዘብ ይዞ መጥቶ ዲዛይንም ግንባታም ለመስራት የሚገባበት ውል ሰላማዊ እንደማይሆን ልባችን ያውቀዋል፡፡ ለማነኛውም ይህ የባቡር ፕሮጀክት ተጠናቆ ሰራ ሲጀምር ወጪውን በግራም በቀኝ አሰበን በወቅቱ ካለው ዋጋ አንፃር ማየታችን የግድ የሚል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ዋነኛ ዘራፊው የቻይና መንግሰት ሲሆን አዘራፊው ደግሞ የብድር ስምምነት የገባው የፌዴራል መንግሰትና የባቡር ኮርፖሬሽን ነው፡፡ የእነዚህ አካላት ሀለቃ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡
ከመንገድ ጋር በተያያዘ የማንረሳቸው በባቡር ግንባታ ስም የህዝብን ሃብት ያባከኑት ከሾላ ገበያ፣ በለም ሆቴል ወደ ቀለበት መንገድ ማቋረጫ መንገድ፤ በደሳለኝ ሆቴል ሳርቤት የሚወስዱት መንገዶች አገልግሎት ሳይሰጡ መፍረሳቸው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ሃላፊዎችን እንቅልፍ ይሰጣቸው እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ምን ችግር አለው ለዘመናዊ ባቡር ሲባል ነው ብለው በሚዲያ የሚሰጡት መልስ ውሃ የሚቋጥር አይሆንም፡፡ አሁንም በድፍረት ሚዲያ እየወጡ ይህን መልስ የሚሰጡ ሰዎች ትዝብት ላይ ከመውደቅ ባለፈ ይህ ሰበብ ግብር ከፋዩን ዜጋ እንደማያሳምነው መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን የሚዲያ ዘማቻ አሁንም አላቆሙም፤ ልብ ማለት ግን የተሳናቸው ይመስለኛል፡፡
በከተማችን በከፍተኛ ወጪ እየተገነቡ ያሉት የትራፊክ መብራቶች ለመፍረስ አንድ ወር ሲቀረው የሚሰሩ መሆናቸው የዚህ መብራት ባለቤት ማን ነው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል:: የመንገድ ማካፈያዎች፣ አደባባዮች የሚሰሩት በጥቃቅን በተደራጁ ይሁን በኮንትራክተር መፍረሳቸው እየታወቀ የሚገነቡበት ምክንያት ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ የጥላሁን ገሠሠ አደባባይ የሚባለው የተጠናቀቀው እንደሚፈርስ ታውቆ ሌሎች መንገዶች መፍረስ ከጀመሩ በኋላ ነው፡፡ ይህን ተግባር ለማከናወን ውል ተገብቶ እንኳን ቢሆን ገንብቶ ከማፍረስ ተደራድሮ ሀብት እንዳይባክን ማድረጊያ “አስገዳጅ ሆኔታዎች” የሚል የውል አንቀፅ  እንዳለ ይታወቃል፡፡ ይህ የኮንትራት አስተዳደር ሀሁ ነው፡፡ በግርግር የሚባክነው ግን ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ሀብት መሆኑ ተዘንግቷል፡፡ ህዝብና መንግሰት የተለያዩበት ሀገር የመንግሰት ሀብት የሚባለውን መዝረፍ ለፅድቅ እንደሚደረግ ተግባር ይወሰዳል፡፡
 በነገራችን ላይ በመርዕ ደረጃ የመንግሰት የሚባል ነገር የለም፡፡ መንግሰት ህዝብ በመወከል ለህዝብ የጋራ ጥቅም የሚውል የጋራ የሚባሉ ንብረቶች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ ከዚህ ጋር ተሰማሚ የሆነው የህገ መንግሰት አንቀፅ 89፡3 “መንግሰት መሬትንና የተፈጥሮ ሀብትን በህዝብ ስም በይዞታው ስር በማድረግ ለሕዝብ የጋራ ጥቅምና እድገት እንዲውሉ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡” ይላል፡፡ በተቃራኒ ደግሞ የሚቆመው አንቀፅ 40፡3 “የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግስትና የህዝብ ብቻ ነው”  በማለት መንግሰት እራሱን ከህዝብ የተለየ ሌላ አካል አድርጎ ያስቀምጣል፡፡ አሁን በተግባር ያለውም የመንግሰት ባለቤትነት እንጂ የህዝብ ባለቤትነት አይደለም፡፡ ለመንግሰት ንብረት ዜጎች የማይቆረቆሩት የመንግሰት የሆነ የእነርሱ ባለመሆኑ ነው፡፡ የእኛ መንግሰት ከህዝብ ይበልጣል፤ ለዜጎች የሚያስፈልገውን እየነፈገ ለራሱ ጡንቻ ማደበሪያ የሚሆነውን ሀብት፣ ንብረት ያፈራል፡፡ በዚህም ህዝብን ይጨቁናል፡፡ ይህም ሆኖ የመንግሰት የሆነ የማንም ስለአልሆነ ቀዳዳ ያገኘ ሁሉ ይዘርፋል ያዘርፋል፡፡
አሁን እዚህም እዚያም የሚባክነው ገንዘብ በእኔ እምነት የህዝብ ንብረት ነው፡፡ መንግሰትም በህዝብ ስም የማስተዳደር ስራ እንዲሰራ የተቀመጠ እንጂ ንብረት እንዲያፈራ የተቀመጠ አካል አይደልም፡፡ የህዝብን ንብረት ሲያስተዳድር የሚያባክን ደግሞ ሃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ ምንም ዓይነት ሰብብ ሳያቀርብ ቦታውን መልቀቅ ይኖርበታል፡፡ እንቢ ካለም ባለቤት የሆነው ህዝብ ማስለቀቅ ይኖርበታል፡፡ ምን ያደርጋል ህዝቡ ይህ የሚሰራው ስራ በገንዘቡ ወይም በስሙ ልጆቹና የልጅ ልጆች በሚከፍሉት ዕዳ መሆኑን እንዲዘነጋ እና መንግሰት በቸርነት የሚሰራው እስኪመስል ድረስ የተሳሳተ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ እየሆነ ነው፡፡ የዚህ ፕሮፓጋንዳ ዓላማ አንድና አንድ ነው፡፡ መንግስትን ከተጠያቂነት ማሽሽ፤ ንብረት ሲያባክንም የራሱን ንብረት እንዳባከነ እንዲቆጠር ማድረግ፡፡ ከተቻለም የመንግሰት ንብረት መዝረፍ ነውር እንዳልሆነ ማስጨበጥ ናቸው፡፡
ልብ በሉ የባቡር መስመር፣ የመንገድ. የቴሌ፣ የመብራት መሰረተ ልማቶች የሚገነባልን ዲታ መንግሰት ነው ያለን፡፡ መንግሰት ቸርነቱ የበዛ፣  እንዲሁም ደግ ሲሆን መንግሰት ለህዝቦቹ የሚያስብ አንድ አካል ነው፡፡ ህዝብ ደግሞ  እነዚህ ሁሉ የመሰረተ ልማቶች የሚያስፈልጉት ምሰኪን ከመንግሰት እጅ የሚጠብቅ፡፡ የሚገርም ነው!!  የገዛ ንዘቡን እና ንብረቱን እንዲያስተዳድር የተቀመጠ አካል አዛዥ ናዛዥ ሲሆን፤ ባለ ገንዘቡ ደግሞ ምስኪን ተመፅዋች የሚኮንበት ጥቂት ሀገሮች ካሉ አንዷ ምስኪኗ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ናቸው፡፡
ቸር ይግጠመን!!!!

የአቶ አዲሱ ለገሠ ሚዛናዊነት የጎደለው ሚዛናዊ ሁኑ ጥያቄ



የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ አዲሱ ለገሠ በአደባባይ ድንገት ጡረታ ውጡ ተብለው በጡረታ ላይ ናቸው ብለን ስናስብ፣ አንድ አንዱ ደግሞ መተካካት አለ ብሎ እያሰበ ባለበት ወቅት እርሳቸው ግን በጓሮ በር የተለያየ መንግሰታዊ ተቋም ቦርድ ኃለፊ በመሆን ብቅ ብቅ ማለት ከጀመሩ የቆየ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መጥቀስ ይቻላል፡፡ አሁን ግን ከእነ ሙሉ ክብሩ እና ጥቅሙ ጋር ብቅ ብለዋል፡፡ የመንግሰት ሹሞች ጥቅማ ጥቅምን አስመልክቶ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት ምክትል ጠቅለይ ሚኒስትር መሆን ከመደበኛ ጡረታ ውጭ ብዙም ትርጉም አልነበረውም፡፡ የአሁን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ግን ትርጉም ያለው ጥቅም አለው፡፡ እንደ “ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር” የተባሉትን አይጨምረም፡፡ በነገራችን ላይ በስልጣን ላይ ካለ ሚኒስትር በጡረታ ያለ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚበልጥም ትምህርት አግኝተናል፡፡
አቶ አዲሱ በፌዴራል ልዩ ድጋፍ ቦርድ ስብሳቢነት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ያቀርባሉ ብለን ስንጠብቅ፤ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትሩን ሪፖርት እንዲያነቡ አድርገው በሪፖርቱ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የቦርዱ ስብሳቢ አቶ አዲሱ ምላሽ ይሆና ያሉትን ስጥተዋል፡፡ አቶ አዲሱ ለገሠ ያለ አግባብ ጡረታ ውጡ የተባሉ እንደሆነ የተሰማኝ በመልስ አሰጣጣቸውም ሆነ በሚጠቀሙባቸው ቃላት ጥንካሬ እንዲሁም ምክር ቤቱን በማሳቅ ሟቹን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን ለመተካት የበለጠ ቅርብ እንደነበሩ ስመለከት ነው፡፡ አማራ ባይሆኑ የአማራ ገዢ መደብ ተመልሶ መጣ ያስብላል የሚባለውን ፈረተው ሟቹ ለእንዲህ ዓይነት ሀሜትና ፈተና የማያጋልጥ ዕጩ ባያዘጋጁባቸው ኖሮ አቶ አዲሱ አቶ መለስን ለመተካት የተሻሉ ነበሩ የሚል ግምት ወስጃለሁ፡፡ ጥሩ ጠቅላይ ሚኒስትር አላልኩም - አቶ መለስን ለመተካት ነው ያልኩት፡፡
አቶ አዲሱ መልስ መመለስ የጀመሩት እነዚህ ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች እራሳቸውን የቻሉ መንግሰት መሆናቸውን አስረግጠው ነግረውን ነገር ግን አመራር የሌላቸው መሆኑን ማወቅ እንዳለብን ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ በእኔ አረዳድ አጋር ክልሎች አመራር የሌላቸው ሰለሆነ አሁን በሞግዚት የሚተዳደሩ ናቸው፡፡ ፌዴራሊዝም የሚባለው ፌዝ ነው ለሚሉ ተቺዎች አቶ አዲሱ በአደባባይ ማስረጃ የሰጡ ነው የሚመስለኝ፡፡ በራሱ አመራር የማይሰጥ ፌዴራሊዝም ከፌዝ ውጭ ምን መልስ ይኖረዋል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች እና ሌሎች ጠጠር ያሉ ጥያቄዎች ከአጋር ድርጅቶች ይቀርባል ብዬ ስጠብቅ የነበረ ቢሆን ምንም መስማት አልቻልኩም፡፡ ጥፋቱ የአፈ ጉባዔው አይመስለኝም፡፡ በምክር ቤቱ አሰራር ጥያቄ ማቅረብ የሚፈልግ ሰሙን ማስመዝገብ ስለሚኖርበት እነዚህ የሀጋር ክልል ወዳጆቼ ሳይመዘገቡ ቀርተው ዕድሉ አመለጣቸው ፤ እንደዛም ሆኖ በቀረበው ሪፖርት መናደዳቸውን ታዝቢያለሁ፡፡
አቶ አዲሱ ጥያቄ ሲመልሱ በሙሉ ልብ ነው፡፡ መንግሰት አቅጣጫ ብሎ አስቀምጦ ለአመታት ሲዳክርበት የከረመውን የቢፒራ እና የቢ.ሴሲ እንዲሁም የልማት ሠራዊት ግንባታን በደንብ አላግጠውበታል፡፡ እውነቱን ለመናገር እዚህ ጋ አንጀቴን ነው ያራሱት፡፡ “እነዚህ ድጋፍ የሚደረግላቻው ክልሎች ከጎሳ አሰተሳሰብ ሳይወጡ፣ ስለ ሠራዊት ግንባታ እና ሌሎች ወሬዎች ማውራት ቦታው አይደለም ነው” ያሉት፡፡ በማስከተልም “በክልሉ ያሉት መሪዎችም አንዳንዴ ሠራዊት ገንብተናል ይሉናል፡፡ የታለ የሠራዊቱ መሪ? ስንላቸው የለም ይላሉ፤ ያለ መሪ ሰራዊት ምን ማለት ነው?” ብለው ሊጠየቁበት የቀረበውን ምክር ቤት በጥያቄ አፋጠዋል፡፡ እንዲህ ነው ልበ ሙሉነት፡፡ ጥያቄው “ሰራዊት እንዲገነቡ እገዛ አድርገሃል ወይ? ከሆነ አላደረኩም” ብለዋል፡፡ አንዳንዶች ሠራዊት ግንባታ ሲሉም አቁም ነው ያለኩት ነው ያሉን፡፡ ጎበዝ እንዲህ ያለ አቁም የሚል ልባም ባለስልጣን አላማራችሁም፡፡
የቤቶችና ህዝብ ቆጠራ የሚባለውን መስሪያ ቤት አፈር ድሜ ነው ያስገቡት፡፡ የሚገርመው ይህን መስሪያ ቤት በበላይነት የሚመራውን ኮምሽን እርሳቸው የሚጠቅሱትን ሪፖርት ሲያወጣ ስብሳቢ የነበሩት እራሳቸው መሆናቸው ነው፡፡ ሴንሰሱን (የህዝብና ቤት ቆጠራ ማለታቸው ነው) መሰረት አድርገን ዕቅድ አወጣን መሬት ላይ ሲከድ የተባለውን የሚያክል ህዝብ የለም፡፡ በሌለ ሰው ምን እናድርግ? ብለውናል፡፡ ምንም ነው መልሱ፡፡ የሚገርመው በእንስሳት ቆጠራውም ይኽው ነው በመሬት ላይ ያለው ሀቅ ብለውናል፡፡ ሀቅ ይውጣሉት ማለት ነው የእኛ ድርሻ ለእንዲህ ያለ ደፋር ታጋይ፡፡ ምን ዋጋ አለው ታዲያ ከዚህ በማስከተል፤ ሌላ ደፋር እንዴት ብሎ ህዝብ ሲቆጥር አምስት መቶ ሺ ህዝብ በብልጫ ተቆጠረ ብሎ ጥያቄ የሚያነሳ እና ተጠያቂ የሚያገኝ ያስፈልግ ነበር፡፡ እንደው ለነገሩ ባለፈው ቆጠራ ከአማራ የጎደሉት ሰዎች አፋርና ሶማሌ ሄደው ይሆን እንዴ? የአማራ ነገር እኮ አይታወቅም፡፡
አቶ አዲሱ የክልሎች ስም ሲጠሩ እንደ ፖለቲከኛ ብዙም አይጠነቀቁም፡፡ የደቡብ ብሔራዊ ክልል መንግስት ይላሉ፡፡ በእውነቱ እራሳቸውም ቢሆኑ ይህን ልዩነቱ ለትርጉም እንኳን የማይገባን ወይም ለብዙ ቃል አንድ ትርጉም ያለውን ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የምትለዋን በአቅጣጫ መጠቆሚያው ደቡብ አጠቃለውታል፡፡ ይህ ለሲዳማዎች ከፍተኛ ቅሬታ የሚፈጥር አጠራር እንደሆነ አንድ ወዳጄ አጫውቶኛል፡፡ በቅርቡ ከምክር ቤት ሹመት ያገኘ አንድ ስው ደቡብ አቅጣጫ ነው፤ ትግራይ መባል እንደምትፈልጉ እኛንም በሰማችን ጥሩን በሚለው ሙግቱ ይታወቃል፡፡ ይህ የአጠራር ስህተት ለሌሎች ሹሞች ቢሆን ትልቅ የፖለቲካ ስህተት እንደሆነ መገንዘብ ያስፈለጋል፡፡ ደቡቦች አልተጠራንም ብለው ዝም ማለት ይችላሉ፡፡
አንድ የምክር ቤት አባል እነዚህ ክልሎች በጠረፍ ከመገኘታቸው አንፃር ለህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ካላቸው ተጋላጭነት አንፃር ምን እየተሰራ ነው? በሚል ላቀረቡት ጥያቄ አቶ አዲሱ ሰፋ አድርገው ለመመለስ ሲሉ ወደ ውጪ ለማስወጣት ብቻ ሳይሆን እነዚህ ክልሎች ሌሎች የፀረ ሰላም ሀይሎችና አክራሪዎች የሚንቀሳቀሱበት በመሆኑ ክልሎች ይህን እንቅሰቃሴ ተቋቁመው ነው ይህን የልማት ድል ያሰመዘገቡት፣ ሰለዚህ ይህን በልማት የተገኘውን ድል ካለባቸው የፀጥታ ፈተና አንፃር ሚዛናዊ ሆኖ ለሚመለከት ኃይል ከፍተኛ ሰራ እንደተሰራ ይረዳል ብለዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ሚዛናዊነትን የጠየቁት አቶ አዲሱ የቀድሞ መንግሰታት አሁን እሳቸው አለ ከሚሉት በላይ ፀረ ህዝብ እንዲሁም ገንጣይ አስገንጣይ የሚሉዋቸውን ኃይሎች ተቋቁመው ነው ይህችን ሀገር አሁን እርሳቸው እና ጓዶቻቸው አዲሲቱ የሚሏትን ኢትዮጵያ ያቆዩት፡፡ ስለዚህ ሚዛን በትክክል ከስራ በእረሳችው ሰፈር ያለውን ሚዛን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡
ለነገሩ ኢህአዴግ ሚዛኑ በትክክል እንዲሰራ ስለማያፍለግ በተመቸው ጊዜ ሁሉ እራሱን ከራሱ ጋር እያነፃፀረ መቶ ለማግኘት የሚጥረው፡፡ የኢህአዴግ መንግሰት በእነዚህ ታዳጊ ክልሎች እሰከ 2000 ዓ.ም ድረስ ምንም ስለ አልሰራ (የክልሉም የፌዴራሉም) ማወዳደር የሚፈልጉት ከ1983 ጋር ነው፡፡ ደርግ በስልጣን ላይ የቆየው ለአሰራ ሰባት ዓመት ነው፡፡ ኢህአዴግም በስልጣን እስከ 2000 ድረስ ያለው ሲቆጠር አሰራ ሰባት ነው፡፡ ስለዚህ ከደርግ ጋር እራሱን ማወዳደር ነውር ነው፡፡ ደርግም ሆነ ንጉሱ በሱማሌ ክልል ያላቸው ወታደር በምንም መለኪያ አሁን ኢህአድግ ካለው ጋር ተመጣጣኝ አይደለም፡፡ ተጨፈኑ ላሞኛችሁ ልንባል አይገባም፡፡ ለዚህ ነው ሚዛኑ ይስተካከል፤ ውድድሩ ከዜሮ ጋር አይሁን የምንለው፡፡
ለኢህአዴግ መንደር ምስረታ ዳገት የሆነበት እንደሚለው ተቃዋሚዎች እና አክራሪ ኒዎሊብራሎች ስለ አስቸገሩት ሳይሆን በትግል ጊዜ መንደር ምሰረታን አሰመልክቶ ይሰራው የነበረው አሉታዊ ቅስቀሳ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ውሃ፣ መብራት እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ከተሟሉ ለማሰባሰብ ችግር ፈጣሪ አይኖርም፣ ቢኖርም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ነገር ግን እነዚህ መሰረታዊ ነገሮች ባልተሟሉበት ዜጎቸን ስትሰባሰቡ ይሟላል ማለት አስቸጋሪ ፈተና ነው፡፡ ከተሰባሰቡ በኋላም ተመልሰው የሚሄዱት ለዚህ መሆኑ መረዳት ጥሩ ነው፡፡
አቶ አዲሱ ከጡረታ በኋላ ቆለኛ የሆኑ ይመስላሉ መቼም እንደ እርሳቸው ብረት ይዘን ዱር ገደል ባንልም ይህችን ሀገር ግን ብዕርና ወረቀት ይዘን ከሳቸው በላይ እንደምናውቀው እድሉ በተገኘ እና በነገርናቸው ጥሩ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ በሱማሌ ክልልም ቢሆን እሳቸው በኮንቮይ ስለሚሄዱ እንጂ ጅጅጋ መግባት እንኳን ክልክል ነበር ባለፈው ሰሞን፡፡ ደርግ እኮ ጎዴ ሆኖ ነበር ክልሉን የሚያስተዳድር፤ እረ ጎበዝ ጅጅጋ ሆኖ ይህ ሁሉ ፉከራ አያስፈልግም፡፡ በዚህ ጉዳይ ማለት የምፈልገው የአቶ አዲሱ “ለነገሩ ማን ሄዶ አይቶዋቸው?” ምፀት አውነት ወይም ውሸት መሆኑ ለማጣራት ይህን ፅሁፍ ድንገት ካነበቡት በኋላ በቦርድ በሚመሩት ክልል የስራ ጉብኝት ለማድረግ ዝግጁ ስለሆንኩ እባክሆትን ሁኔታዎችን ያመቻቹልን፡፡ እንደ አርቲስቶቹ … በእርግጥ እኛ እንደ አርቲስቶቹ እናንተ የምትፈልጉትን ብቻ ሳይሆን ያየነውን የሰማነውን በሙሉ ነው የምንናገረው፡፡ ምክንያቱም እኛ ነፃ … ነፃ ዜጎች ነን፡፡
ባለፈው በጅጅጋ የብሔር ብሐረሰቦች ዕለት ማስታወሻዬ አቶ አዲሱ ለምን …. እንደሚሉ በግርምት አካፍያችሁ ነበር፡፡ አሁንም በምክር ቤት ቀርበው “አብዛኛው ሰው ሱማሌ ክልል ነዳጅ ብቻ የሚገኝበት ነው ሲል ነው የምሰማው፡፡ የክልሉ የግብርና መሬት ግን እጅግ ከፍተኛ መሆኑን አይረዳም” ብለዋል፡፡ አቶ አዲሱ ለገሠ ሱማሌ ክልልን አስመልክቶ የሚያናግሯቸው ሰዎችና አስተያየት የሚስጡዋቸው ግለሰቦች ችግር እንዳለባቸው መረዳት አያስቸግርም፡፡ እርሳቸውም ቢሆን ከዚህ ዓይነት አሰተያየት ሰጪዎች መራቅ አለባቸው፡፡ የመረጡት እራሳቸው ከሆኑም የምርጫ ስሕተት ፈፅመዋል ማለት ነው፡፡ እኔ የማውቃቸው ሰዎች ከዋቢ ሸበሌ ጋር  ተያይዞ ያለውን መሬት የማልማት አቅም በከርሰ ምድር ያለውን ዕምቅ ሀብት ነው፡፡ በተሳሳተ አስተያየት ሰጪ ወይም የግል የተሳሳተ ምልከታን የብዙዎች ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ የሱማሌ ገበሬ እንዳለም እርሶ ከበረሃ ሳይመጡ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ብዙ አይደሉም አብዛኛው አርብቶ አደር ነው፡፡ ይህችም እውቀት ነች ብሎ ፌዝ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ነዳጅም ሆነ የእርሻ መሬት ክልሉን የምንፈልገው ለሀብት ሲባል አይደለም፡፡ ደረቅ ምድረ በዳም ቢሆን የኢትዮጵያ አካል ነው እያልን ነው፡፡ እዚህ ጋ የዶክተር በድሉ ዋቅጅራን “ሀገር ማለት ልጄ” የሚለውን ግጥም መጋበዝ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
በመጨረሻ እሰኪ አሁን ታዳጊ ተብሎ ድጋፍ ከሚደረግላቸው ክልሎች ሰማቸው የማይታወቅ የነበረው ሱማሌ፣ ጋምቤላ፣ ጉሙዝ፣ አፋር የትኛው ነው? እረ እየተሰተዋለ ይሁን፡፡ የአፋርኛ እና የሱማልኛ ሬዲዮ ፕሮግራም እንደነበረ ማስታወስ ይኖርብን ይሆን?
መልካ በዓል አመሰግናለሁ!!!!!