Saturday, June 2, 2018

አንዳርጋቸው ፅጌ - የገብርኤሉ መንገድ ካህን



ኢትዮጵያ አገራችን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመግባት ብዙ ታሪካዊ አጋጣሚዎች፤ እንዲሁም ደግሞ ሁለት ሰር ነቀል የሚባሉ ለውጦች በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ አሰተናግዳለች፡፡ ከእነዚህ አንዱ የሆነው የዛሬ ሃያ ሰባት ዓመት ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም የነበረው ለውጥ በብዙዎች ዘንድ ብሩዕ ተሰፋ አጭሩ ነበር፡፡ ይህ ተሰፋ ካጫረባቸው ሰዎች አንዱ በቅርቡ ከእስር የተፈታው ከየመን ታግቶ የመጣው የነፃነት ታጋዩ አንዳርጋቸው ፅጌ ነው፡፡በዚያ ክፉ ጊዜ ይህ ሰው እንደ ብዙዎቻችን ተሰፋ መሰነቅ እና ለበረኽኞቹ ዕድል እንስጣቸው ብሎ አልተቀመጠም፡፡ ይልቁንም ላግዛችሁ እችላለሁ፣ ከለውጥ ባቡሩ መሳፈር ብቻ ሳይሆን ልሾፍር ብሎ አዲስ አበባ በመግባት፣ የሽግግር መንግስቱን በአዲስ አበባ ዋና ፀኃፊነት በማገልገል ተሳትፏል፡፡ ይህን ጉዳይ ያነሳሁት አንዳርጋቸው በአሰገራሚ ሁኔታ ይህን ተሳትፎ በክብር ለመሞት እንደውለታ አንዲቆጠርለት፤ ለአሳሪዎቹ ጥያቄ ማቅረቡን ሰለነገረን ነው፡፡ ማሩኝ አትግደሉኝ፣ በክፉ ቀን አብሬያችሁ ነበርኩ፤ አይደለም ያላቸው፡፡ እየሳቁ በክብር ለሞሞት የሚዘጋጅ ጀግና ፊታቸው ሲቆም፤ አሳሪዎቹ ምን እንደተሰማቸው ወደፊት በዝርዝር የማወቅ ዕድሉ ይኖረናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከዚህ የምንማረው ትልቁ ነገር አምነን ለቆምንለት ዓላማ፣ በጠላት ዕጅ ውስጥ ብንሆንም ለክብር ሞት መዘጋጀት እንዳለብን ነው፡፡ ይስማል!!!
አንዳርጋቸው ፅጌ በመሰራችነት የተሰለፈበት ግንቦት ሰባት፣ የጠመንጃ ሱስ እና ወንድም ወንድሙን ገድሎ ጀግንነት የሚመዘገብበት አውድ ለመፍጠር ፍላጎት እንደሌለው ማንም ንፁህ ሕሊና ያለው ይረዳል፡፡ ነገር ግን በመሣሪያ ሀይል ሥልጣን የያዘ የሚመስለው በህወሓት ቁጥጥር ሥር የነበረው መንግሥት (አሁን ህወሓት በዚህ ደረጃ ያለች ስለማይመስለኝ ነው፡፡) ፉከረው ሁሉ መንገዱን ጨርቅ ያርግላችሁ በሚል ትዕቢት ውስጥ መግባቱ፣ ብረት ለማንሳት ዋንኛው ገፊው ምክንያት እንደነበር እንረዳለን፡፡ የማሪያም መንገድ ከተዘጋ፣ የገብሬሉ ይከፈታል ብለን ብንወተውትም የሚሰማን አላገኘንም ነበር፡፡
የገብሬሉ መንገድ ሲከፈት ደግሞ ከካህናቱ አንዱ ሆኖ ብቅ ያለው፣ ህወሓተች በሚያሳዩት ዕብሪት በንዴት በመጦዝ፣ እነርሱ ጫማ ስር ለማጎንበስ እና ለመጫን ፈቃደኛ ካልነበሩት አንዱ ውስጣቸው ሆኖ ገምግሟቸው “ነፃነት የማይውቅ፣ ነፃ አውጪ” ብሎ ስም ያወጣላቸው አንዳርጋቸው ፅጌ ነው፡፡ ይህ ሰው በአንዲት ክፉ ቀን እና አጋጣሚ ምንአልባትም ወደፊት ይፋ በሚወጣ ልዩ ደባ በህወሓት “ደህንነቶች” እጅ ስር ወድቆ ለአራት ዓመት በቁጥጥራቸው ሥር ሆኖ ነበር፡፡ ይህን የጭለማ ዘመን ለማሰብ ይከብዳል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ብለው እየተመፃደቁ፤ አንድ መሰመር የሕገ መንግሥት ድንጋጌ ከማያከብሩ ሀይሎች ቁጥጥር ውስጥ ሲኮን ደግሞ ጨለማው ድቅድቅ ነው፡፡
ባለፉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን የገብርኤል መንገድ ካህን ምን አደረጉት? ምንስ ያደርጉት ይሆን? የሚለው ስጋት ወጥሮት ነበር፡፡ አንዳርጋቸው በመረጠው የገብርኤል መንገድ ባንስማማ፣ ተገፍቶ የገባበት መሆኑን የምንረዳ ሁሉ በዚህ ጭንቅ ውስጥ እንደነበርን ለማንም ግልፅ ነው፡፡ በግሌ አገሩን እንደሚወድ ዜጋ አንዳርጋቸው ላይ በዚህ መንግሥት ሊደርስ የሚችለውን ግፍ በማስብ አገሬ በምን ደረጃ ልትዋረድ እንደምትችል ሳሰበው ይጨንቀኝ ነበር፡፡ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ስልሣዎችን የንጉሡን ሹማምንት፣ አስከትሎም አገሪቱን አሉኝ የምትላቸውን ጄነራሎች ገድሎ በግሉ የፈጠረለትን ደስታ ባላውቅም ለአገሬ ኢትዮጵያ የፃፈላትን ጥቁር ታሪክ ሳስብ ያመኛል፡፡ የህወሓት ሰዎቸም ለአገር በማሰብ ሳይሆን በግል ቂምና በቀለኝነት አንዳርጋቸው ላይ ሊያደርሱ የሚችሉት ግፍ ለአገሬ ኢትዮጵያ አንድ ተጨማሪ ጥቁር ጠባሳ ያለበት ታሪክ እንደሚፃፍ በማስብ በስቃይ ውስጥ የከረመው ሕዝብ እንዲሁ ከአንዳርጋቸው መፈታት ጋር የሠላም አየር መተንፈስ ችሎዋል፡፡ በሕይወትና እና በጤና ማግኘታችን ደስ የሚያሰኝ ነው፡፡

አንዳርጋቸውን ሳገኘው የተሰማኝ ደስታ ከሁሉም በላይ ከፍ ያደረገው በሠላም፣ በጤና መገኘቱ ብቻ አይደለም፣ እንዲህ ዓይነቱ ልዩ እስር በሚፈጥረው የመረጃ ክፍተት ያልተወናበደ መሆኑ ጭምር ነው፡፡ አንዳርጋቸው ሰል ከሆነ ጭንቅላቱ ጋር በጤና ሰላገኘሁት ደስ ብሎኛል፡፡ በአገሬም ተጨማሪ ጥቁር ጠባሳ የሚፈጥር ታሪክ አለመፃፉ በተጨማሪ አስደስቶኛል፡፡
በዚህ አጋጣሚ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግሰት በዓለም ልዩ የሆነ ቶርች ሲስተም በመፍጠሩ በታሪክ ሊመዘገብለት የሚገባ ይመስለኛል፡፡ በፖለቲካ ጉዳይ የሚያስራቸውን ሰዎች በተለይ ቀንደኞች ብሎ ለሚፈርጃቸው በሃያ አንደኛው  ክፍለ ዘመን መረጃ እንዳያገኙ ማድረጉ ነው፡፡ ብርቱካን ሚደቅሳ ከደካማ እናቷ እና ሕፃን ልጇ በስተቀር ማንም እንዳይጠይቃት በማድረግ ዕለት ከዕለት ፕሮፓጋንዳ የሚነዛበት የገዢውን ሥርዓት ቴሌቪዥን ፈቅዶ በትግል ላይ ናቸው ብላ የምታስባቸው የፓርተ አባላት ሲደባደቡ ማሳየት ዋና ተግባሩ ነበር፡፡ በተመሣሣይ አንዳርጋቸው ፅጌ ከዘጠና ዓመት አረጋዊ አባቱ በስተቀር ማንም አንዳይጎበኘው በማድረግ የፈፀሙት ግፍ፤ የፈለጉትን ወጤት አለመጣም፡፡ በፈለጉት መንገድ አንዳርጋቸውን ባለማስጎንበሱ ደስተኛ ነኝ፡፡ ባለፉት ጥቂት ሣምንታት አንዳርጋቸው ቴሌቪዥን አንዲገባለት መደረጉ ደግሞ ከመውጣቱ በፊት ተሰፋ እየዘሩብን ያሉትን አዲሱን ጠቀላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይ አህመድን ለመተዋወቅ እንደሚረዳው እና ተስፋም እንዲሰንቅ ረድቶታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከተፈታ በኋላ ጠቅላይ ሚኒሰትር አብይ አንዳርጋቸውን ለማግኘት መወሰናቸው በራሱ አንድ ትልቅ እርምጃ ነው፡፡ ያለፈውን ትተን ወደፊት ለአገራችን ሠላምና ብልፅግና፤ ለሕዝቦች ክብር የምንቆምበት ቀን የተቃረበ ይመስለኛል፡፡
ግርማ ሠይፉ ማሩ