Tuesday, November 8, 2016

የስርዓት ለውጥ በስርዓት



የሰሞኑን የካቢኔ ሹመት አስመልክቶ ብዙ አስተያየት እየተሰጠ ነው፡፡ አሰተያየት መስጠቱ ትክክል ነው፡፡ በህይወታችን ላይ ከፋም-ለማም ውሳኔ የሚያሳልፉ ሰዎች ምደባ በመሆኑ የመሰለንን አስተያየት መሰንዘር ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በእኔ እምነት ኢህአዴግ ባልሆንን ሰዎች ፣በተለይ ደግሞ የተሻለ አማራጭ ይታየናል፣ አለንም ለምንል ዜጎች ዋናው ጉዳይ የኢህአዴግ ፖሊሲ በምን ዓይነት ካቢኔ በደንብ ተግባራዊ እንደሚሆን መምከር አይመስለኝም፡፡ እኛ በእጃቸን ያለውን አማራጭ ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ የምንችልበት የፖለቲካ ምዕዳር መመቻቸት ጉዳይ ነው የእኛ ጥያቄ መሆን ያለበት፡፡ በእግረ መንገድም ኢህአዴግ ፖሊሲውን እንዲፈፅሙ የተመደቡት ሰዎች መስመር ሲስቱ ማጋለጥ ዋነኛ ተግባራችን ነው፡፡ ብዙዎች እንደሚጠብቁት ፖሊሲዎቹ ያላቸውን በጎ ጎን እየጠቀሱ ኢህአዴግን ማወደስ፣ በአንዳንዶቹ አባባል እውቅና መስጠትም ሃላፊነታችንም ግዴታችንም አይደለም፡፡ ይህን አስተያየት በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንደ ዜጋ በጋራ መቆም ከሚለው መርዕ ጋር ማምታታት በፍፁም ተገቢ ካለመሆኑም በላይ ለኢህአዴግ ተደጋጋሚ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ መሆንን ነው የሚያመለክተው፡፡
አንድ አንድ ሰዎች አሁን በሹመት ወደ ሃላፊነት የመጡት ሰዎች በብዛት አዲስ አድርገው ይገምታሉ (ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከዘጠኙ በስተቀር በሚል አሳሳች መልዕክት እንዳሰቀመጡ ሳንዘነጋ)፡፡ በቁጥር ሁለት ሲበዛ ሶሰት ከሚሆኑት ውጭ የኢህአዴግን ፓርቲ መታወቂያ ከመውሰድ በስተቀር ከጳጳሱ በላይ ካቶሊክ ለመሆን የሚሞክሩ፣ በነበሩበት ተቋም በተገቢ ሁኔታ ኢህአዴግን አሁን ለደረሰበት ውድቀት የዳረጉ ጭምር ናቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ በዝርዝር መግባት ተገቢ አይደለም፡፡ እነዚህ ሹመኞች ደግሞ አሁን ባለው ሁኔታ የፖለቲካ ስልጣን የላቸውም፡፡ ያለ ፖለቲካ ስልጣን የሚኒሰትርነት ቦታ በፖለቲካ አቋም በየመስሪያ ቤቱ ከሚገኙ የፖለቲካ ምድብተኞች ጋራ ለመጋጨት ካልሆነ ትርጉሙ አይታየኝም፡፡ ደርግ በመጨረሻ ዘመኑ የክልል አስተዳደሪዎቹን በተለያየ ዘርፍ ትምህርት የቀመሱ በዘርፋቸው ምርጥ የተባሉ ምሁራንን አድርጎ ነበር፡፡ የዚህ ሹመት ውጤት የሆነው ከኢሠፓ ሹሞች ጋር የዕለት-ከዕለት ግጭት ነበር፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ ፓርቲ መሪ ስለሆነ እነዚህ “አዲስ ተብዬ” ሹሞቾ የፓርቲ መመሪያ ሲጠብቁ ሰራ ተገተሮ እንዳይቀር ስጋት አለኝ፡፡
እነዚህን ሹሞች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በድፍረት ጥያቄ ሊጠይቋቸው ይችላሉ፡፡ በፓርቲ ውስጥ አለቃ ስለአልሆኑ፣ ጠብ እርግፍ አድርገው ሊያብጠለጥሏቸው ይችላሉ፡፡ ወይም ጥፋት ካጠፉ ወደ ዘብጥያ ለማውረድ የፓርቲ ግምገማና አቋም ላይጠየቅላቸው ይችላል፡፡ በዚህ ሁኔታ አሁን ያሉት ሚኒሰትሮች አንዳንዶቹ ሚኒሰትሮች (እነ ወርቅነህ፣ ደብረፅዮን፣ የመሳሰሉት) ከፖለቲካ ጡንቻ ጋር ሲሆኑ የተቀሩት ይህን ዋና የፖለቲካ ጉልበት ባለመያዝ ነው በአንድ መድረክ የተገናኙት፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ጡንቻ ያላቸው ሚኒሰትሮች ደግሞ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ እንደነገሩን በሲኒየር ሚኒስትርነት በውስጠ ዘ- ምክርና መመሪያ የሚሰጡ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ዘለል ባለ መስመር የሚሄድ ሚነሰትር ካለ ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡ ለምሣሌ የአሁኑ የመንግሰት ኮሚኒኬሼን ሚኒስትር ማድረግ ያለባቸው በመዝገብ ታሸጎ ፈቃድ የተከለከሉ ጋዜጠኞች ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ፣ በሽመልስ ከማልና አለቆቹ ትዕዛዝ ወህኒ እንዲወርዱ፣ በየፍርድ ቤቱ የሚንከራተቱ ጋዜጠኞች ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሚያበረክቱትን አስተዋፅኦ ከግምት በማስገባት ከእስር በመፍታት፣ የፍርድ ቤት ምልልሱን በማቋረጥ የሚዲያ ምእዳሩን ክፍት እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ይህን ካልቻሉ እስኪባረሩ ሳይጠብቁ ምክንያታቸውን ለህዝብ ገልፀው ከሹመት መልቀቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ከላይ እስከ ታች የተንቀሳቀሰው ዶ/ር ቴዎድሮስ አደሃኖም፣ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ፣ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ ወ/ሮ ዘነቡ ታደሠ፣ ኦቶ መኩሪያ ሀይሌ ወዘተ … ከስልጣን ይውረዱልን የሚል ጥያቄ አንስቶ አይደለም፡፡ በመስረታዊነት እነዚህ ሰዎች የኢትዮጵያን ፖለቲካ ምዕዳር ለማፈን ያላቸው ሚና ዜሮ ነው፡፡ የአንድ አንዶቹ ሚና ከተላላኪነት የሚዘልም አይደለም፡፡ የእነዚህ ሚኒሰትሮች ከስልጣን ተነስቶ እዚህም እዚያም ስርዓቱን ሲያገለግሉ በነበሩ ቴክኖክራቶች በመተካት የሀገራቸውን ኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ አያመጣም፡፡ ከቴክኖክራት ሚኒሰትሮች የሚጠበቀው የቴክኒክ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱ ህዝብ የሚጠብቀውን የፖለቲካ ሪፎርም እንዲመጣ ማድረግ ነው፡፡ ይህን ማድረግ አቅም አላቸው ወይ? ብለን ስንጠይቅ ጥርጣሬ እንደሚያጭር እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ አዲስ ሹሞች የፖለቲካ ስልጣን የላቸውም፡፡ በኢህአዴግ ቤት ደግሞ ስልጣን ያለው ፓርቲ ነው፡፡ ከፓርቲም በህውሃት እጅ ነው፡፡ በአማራም በኦሮሚያም የነበረው እንቅስቀሴ ውስጥ ጎልቶ የወጣው የአንድ ፓርቲ/የህወሃተ የበላይነት ይቁም የሚለው ነው፡፡ ይህን ምላሽ በሚሰጥ መልኩ ምለሽ አልተሰጠም፡፡
በመግቢያዬ ላይ እንዳልኩት ኢህአዴግ የፈለገውን ካቢኔ ሚኒሰትር የመሾም መብት አለው፡፡ በኢትዮጵያችን የተፈጠረው ችግር በኢህአዴግ ካቢኔ የሞያ ሰብጥር ምክንያት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ችግር የፖለቲካ ምዕዳሩ ኢሕአዴግና ለኢህአዴግ ለገበሩ ብቻ በሚሆን መልኩ የተደረጃ መሆኑ ነው፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ መንግሰት ከሚፈልገው ውጭ መናገርም ሆነ መስራት በመከልከሉ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በህገ መንግሰት በግለፅ የተደነገገን የመደራጀት መብትን፣ ተደራጅቶም ሃሳብን የማቅረብ መብትን መተገበር ባለመቻሉ ነው፡፡ በኢትዮጵያችን የመንግስት ተቋማት ዜጎችን አገልግሎት የሚሰጡት በህግ አግባብ ሳይሆን የየትኛው ብሔር አባል ነው በሚል መመዘኛ መሆኑ ነው፡፡ በኢትዮጵያችን መንግሰት የሚባው አካል ተጠያቂ ያለመሆን ብቻ ሳይሆን ማንነታቸው የማይታወቅ አካላት የተለያዩ የመንግሰት ተቋማት በስውር ያዛሉ፡፡ የሚጠሉትን ፓርቲ ከህግ አግባብ ውጭ ያፈርሳሉ፡፡  የግል አግልግሎት መስጫዎችን፣ ማተሚያ ቤቶችን በስልክና በግንባር እየቀረቡ ያስፈራራሉ፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ የደንብ ልብስ የለበስ ፖሊስ አባላት ከነ ማዕረጋቸው ማንነቱ ያልታወቀ ሰው ዜጎችን ለማፈን ሲሞክር መታወቂያ መጠየቅ የማይቻልባት ሀገር ነች፡፡ ስንቱን ዘርዝሮ ይቻላል፡፡ ይህን ችግሩን የሚያሰማበት መድረክ ያጣ ህዝብ በብሶት ተነሳስቶ የዜጎች ህይወትና ንብረት እንዲወድም አድርጎዋል፡፡ ይህ ውድመት የአፈና ውጤት ነው፡፡ አፈናን በማፈን ማስታገስ ደግሞ አይቻለም፡፡
አሁንም በሀገራችን የስርዓት ለውጥ በስርዓት እንዲመጣ ፍላጎት ብዙዎች አለን፡፡ ፍላጎት በራሱ ግን በቂ አይደለም፡፡ በእኔ እምነት ስርዓት በሌለው ሁኔታ ለውጥ እንዲመጣ ከማንም በላይ ፍላጎት እያሳዩ ያሉት መንግሰት እና ገዢው ፓርቲ ናቸው፡፡ መንግሰት በስርዓት ለውጥ እንዲመጣ የመሪነቱን ሚና መጫወት ይኖርበታል፡፡ በቅድሚያ ማነኛውም ከመንግሰት ጋር ያልተግባባ ኃይል ከመፈረጅ መታቀብ አለበት፡፡ በዋና ዋና የሀገር ዕልውና ላይ የማይደረዳሩ መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ ማድረግ የሚከለክል አስራር ሊዘረጋ ይችላል፡፡ ከዚህ በመለስ ኢህአዴግ እራሱን “በጥልቅ ማደስም ይሁን አፍርሶ መስራት”  የራሱ የቤት ስራ ሲሆን “መንግሰት” በግልፅ ከፓርቲው መለየቱን ለማስመስከር ባለበት ሃላፊነት ኢህአዴግን አውራ ፓርቲ የማድረግ ተግባሩን በማቆም በሀገራቸን የሃሳብ ልዮነትን መስረት ያደረጉ ፓርቲዎች ምድር እንድትሆን ለማድረግ ቁርጠኛ እርምጃ መውስድ ይኖርበታል፡፡ ከእነዚህም ዋና ዋናዎቹ
·         በኢትዮጵያ ውስጥ የሚጀመረውን የፖለቲካ ሪፎርም ሊመራ የሚችል ኮሚሽን በማቋቋም በሀገሪቱ ያሉት ችግሮች ደረጃ በደረጃ በውይይት የሚፈታበትን ተግባር እንዲያከናውን ስልጣን መስጠት፣ ይህን ሃላፊነት የሚወስድ ማነኛውም ሰው በሁሉም ወገኖች ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ማድረግ፡፡ ፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲስ መልክ እንዲደራጁ መፍቀድ፣ ሚዲያ በነፃነት እንዲሰሩ መፍቀድና ማገዝ፣ ህዝቡ የመስለውን የፖለቲካ አቋም እንዲያራምድና እንዲደግፍ ማበረታታትና ማገዝ፣
·         በማነኛውም ሁኔታ ከመንግሰት መዋቅር ውጭ መመሪያ የሚሰጡና የሚያስተገብሩ አካላትን ድርጊት በግልፅ ማስቆም (ለምሳሌ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር መስሪያ ቤትን በሚኒስተርነት ደረጃ ለማቋቋም የተጀመረውን ስራ ማጠናቀቅ ተጠያቂ የሆነ የደህንነት ጉዳዮች ሚኒስትር በይፋ መሾም)፣ኢትዮጵያዊ ደህንነት መስሪያ ቤት ማቋቋም፤
·         ከሃያ አምስት ዓመት በኋላም በመከላከያ ውስጥ የሚታየውን ያልተመጣጠነ የሃላፊነት ቦታ ምደባን ለማስተካከል አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ፡፡ ብቃትን መሰረት ያደረግ ምደባ በማድረግ ተሰናባቾችን በክብር ማስናበት፡፡
የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ እነዚህ እርምጃዎች መላው የሀገራቸን ዜጎች በህጋዊ መንገድ ድምፁን ለማሰማት እድል የሚፈጥሩ ስለሆነ ከግብታዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴ የሚገታው ይሆናሉ፡፡ የሚወሰዱት ተግባራዊ የፖለቲካ ምዕዳር የማስፋት እርምጃዎች ለቀጣይ በተረጋጋ ሁኔታ በሀገር ፍቅር ሰሜት እና በባለ ሀገርነት ሰሜት በነፃነት የእለት ተግባሩን ከማከናወን በዘለለ፣ ከፍ ወደሚል ሀገራዊ ሃላፊነት ሰሜት እንዲያድግ ያግዘዋል፡፡
ነፃነት ባለበት ዲሞክራሲ ያብባል፡፡ ይህን ጊዜ ዘላቂ ሰላምና እድገት ለትውልድ ይተላለፋል፡፡ ለዚህ ሲባል ገዢው ፓርቲ/መንግሰት አሁን ያላቸውን ህገወጥ ቁርኝት በመለየት ፓርቲውም እንደ ፓርቲ መንግሰትም እንደ መንግሰት ሃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ በምንም ሁኔታ የመንግሰት ስልጣን ገዢውን ፓርቲ በተለይ ሁኔታ መጥቀም አይኖርበትም፡፡ የካቢኔ ሽግሽግ የፓርቲው ጉዳይ ነው፡፡ በስርዓት የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ ትክክለኛውን እርምጃ በትክክለኛው ጊዜ መውሰድ ይኖርብናል፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራችን እና ህዝቧን እግዝአብሔር በበረከቱ ይጎብኝልን!!!!
ቸር ይግጠመን!!!

Monday, October 31, 2016

የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብርቅ ነው!!!




የአስቸኳይ ጊዜው ሴክፌታሪያት አዋጁ ግቡን መቷል ብለው መግለጫ መስጠታቸውን ሰምተናል፡፡ ይህ አዋጅ በአጭሩ ዝም ጭጭ አድርጎ ለመግዛት የተቀየሰ ዘዴ ነው ለምንል ሰዎች ዜጎች ዝም ጭጭ እንዲሉ ተደርጓል ማለት ነው፡፡ አሰገራሚው ነገር መስከረም 1967 “መለኮታዊ ንጉስ” የሚባሉትን አውርዶ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደርግ ለምን አወጀ ብለው የሚከሱ፣ ሲከፋም በዚሁ ምክንያት ነው ጫካ የገባነው ብለው የሚፎክሮ የዲሞክራሲ አርበኞች በህይወት እያሉ አሁን “ዲሞክራሲያዊ” የተባለ የአስቸኳይ ጊዚ አዋጅ አውጀውልናል፡፡ ይህ አዋጅ በቴሌቪዥን ሲነበብ አደመጥኩት ክልከላዎቹ በሙሉ ድሮም በህግ የተፈቀዱ በተግባር ግን የማይቻሉ የነበሩ ናቸው፡፡ ለማረጋገጥ በጋዜጣ የወጣውን በጥሞና ደግሜ ደግሜ አነበብኩት ብዙዎች መመሪያው “ክልክል” ያላቸው ድሮም ወደፊትም ክልክል ናቸው፡፡ ለምሣሌ ንብረት ማውደም፣ ሰው መግደል፣ ያልተፈቀደ የሠራዊት ዩኒፎርም መልበስ፣ ህገወጥ ቅስቀሳዎች፣ ወዘተ በሙሉ መቼም ያልተፈቀዱ ወደፊትም የማይፈቀዱ ክልከላዎች ናቸው፡፡ ተፈቅደው ነገር ግን በተግባር ያልነበሩት የአደባባይ ሠልፍ እና ስብሰባ ዋነኛዎቹ ሲሆኑ፣ እጅግ ብዙዎቹ ክልከላዎች በሀገሪቱ በነበረው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ወቅት ገዢዎችን አንጀት ያሳረሩ ድርጊቶቸን ዝርዝር ለማወቅ ከመጥቀማቸው ውጭ ፋያዳቸው አይታየኝም፡፡
በአዋጁ ውስጥ አስደናቂ ሊባሉ የሚችሉት ግን ማየት መስማት የሚከለክሉት የመጀመሪያዎቹ አንቀፅ ላይ የሰፈሩት ክልከላዎች ናቸው፡፡ መለኮታዊ ንጉስ አውርዶ እንዴት ሰልፍ ተከለከልን ያሉ ታጋዮች ለዚህ ነው ዓይናችን የጠፋው አካላችን የጎደለው ያሉ ሁሉ በተገኙበት ስብሰባ ይህን ማድረግ አስገራሚ ሆኖ በታሪክ ይመዘገባል፡፡
አዋጁን ተከትሎ በሚዲያ የሚተላለፉት ነገሮች ደግሞ የበለጠ አስደማሚ ናቸው፡፡ አንድ አንድ ነዋሪዎች በመባል የሚታወቁ አስተያየት ሰጪዎች አዋጁ ዘገየ፣ ለልማታችን ያስፈልገናል፣ ወዘተ የሚሉ አሰተያየቶች ሰጥተዋል፡፡ ማለት የፈለጉት ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለአስተያየት ሰጪዎችም ሆነ አስተያየት ሰብሳቢዎች ግልፅ አይመሰለኝም፡፡ ሕገ መንግሰታዊ ስርዓት ይከበር እያልን፣ በአስቸኳይ አዋጅ መብታችን ተገድቦ ይኑር ማለት ትርጉሙ አይገባም፡፡ ግራ ገብቷቸው ግራ የሚያጋቡ የዚህ ዓይነት አስተያየት ሰጪዎችና ሰብሳቢዎች ያሉበት ሀገር ውስጠ ነው የምንገኘው፡፡
ተንታኞች ተብዬዎቹ ደግሞ አዋጁ ምንም አያስገርምም ሁሉም ሀገሮች የሚያደርጉት ነው በሚል ፈረንሳይን፣ ቱርክን፣ አሜሪካን የመሳሰሉ ሀገሮችን በመጥቀስ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብርቅ ነው እንዴ!! እያሉን ይገኛሉ፡፡ ይህን አዋጅ ልዩ የሚያደርገው ደግሞ አዋጁ ሲዘጋጅ ልምድ የተወሰደበት ሀገር አለመጠቀሱ ነው፡፡ ይህን እኛም እንዳንጠረጥር አዋጁን ያዘጋጀው ማንም ይሁን ማን ደረጃውን ያልጠበቀ ዝርክርክ መሆኑን ግን አለመግለፅ ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡ ይህን አዋጅ ሰመለከት ይህ ካቢኔ ተብዬው ሀገሪቱን የሚገዛው ቡድን ያለውን አቅም ለመረዳት ችያለሁ፡፡ በምንም ሁኔታ በአስቸኳይ ደረጃውን የጠበቀ መግለጫ ማውጣት እንደማይችል፤ ይህን ዓይነት የባለሞያ ስራ ሊያግዝ የሚችል የባለሞያ ስብስብ እንደሌለው ጭምር ተረድቻለሁ፡፡ አዋጁን መታወጁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁ ዕለት ዝርዝሩን እንደደረስን እናቀርባለን የሚለው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተደጋገመ ማስታወቂያ የሰለቸው ልጄ ስብሰባውን በእንግሊዘኛ ነው እንዴ ያደረጉት? ብሎኛል:: ይህ በሙሉ የሚያሳየው አሰቸኳይ ጊዜ አዋጁ፣ ደንብ፣ መመሪያ፣ ፕሮግራም እየተባለ የሚወጡት በሙሉ ደረጃቸውን ያልጠበቁ መሆናቸው ነው፡፡ “ነበር” በሚል መፅኃፍ ውስጥ ደርጎች መግለጫ እንዴት ያወጡ እንደነበር የተፃፈውን ስመለከት በዚያ ቀውጢ ወቅት ከዚህም ከዚያ የተሰባሰቡ ወታደሮች የሰሩትን መስራት የማይችል ሃያ አምሰት ዓመት በስልጣን ላይ የቆየ መንግሰት እንዴት አሳዛኝ እንደሆነ አንባቢ ሊፈርድ ይችላል፡፡
በነገራችን ላይ ከቅዳሜ ጀምሮ የሚፀና አዋጅ እሁድ ለምን ታወጀ? ሰኞ ምክር ቤቱ ሰለሚከፈት በዝርዝር አዘጋጅተው ለምን ምክር ቤቱ ሲከፈት አላቀረቡትም? የሚሉና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ማንሳት ይቻላል፡፡ በእኔ እምነት ከቅዳሜ ጀምሮ የፀና ይሆናል የሚል ህገወጥ አካሄድ የመረጡት ምክር ቤት በሌለበት የታወጀ በማሰመሰል፣ በአርባ ስምንት ሰዓት ውስጥ ለምክር ቤት አቅርቡ የሚለውን ህገ መንግሰታዊ ድንጋጌ ለመጣስ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ይህን በማድረግ በሁለተኛው አማራጭ አሰራ አምስት ቀን ማግኘት የቻሉ ሲሆን ባገኙት አስራ አምስት ቀን የዝግጅት ጊዜ ውስጥም የሚሰሩትን ሰራ ጥራት ለማስጠበቅ አልቻሉም፡፡
አዋጁ ዋና ዓላማው አስፈራርቶ መግዛት ስለሆነ ከሞላ ጎደል ሊሳካለት ይችላል የሚባለው ለመፍራት በተዘጋጁት ላይ ብቻ ነው፡፡ ነፃነት ወይም ሞት ብሎ ለተነሳ ግን ይህ አዋጅ ምን ይቀንሰበታል? ብዬ ጠይቄ መልሱ ምንም የሚል ነው የሆነብኝ፡፡ ለማነኛውም ይህ አሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ ህወሃት/ኢህአዴግ በውስጡ እፈጥራለሁ ላለው “ጥልቅ ተሃድሶ”  ይሁን “ፈርሶ መሰራት” በአባላቱ መካከል ሊፈጠር ለሚችል ቀውስ መቆጣጠሪያ ለማድረግ ነው በሚል በተሰፋ ለመሞላት ለሚፈልጉት ተሰፋ ከሰጣቸውም ተሳስቼም ቢሆን ይህ ተሰፋ ዕውን ቢሆን ደስ ይለኛል፡፡
መልካም የአስቸኳይ ጊዜ ይሁንልን!!!!

ለኢትዮጵያ ፖለቲካ መሪነት ተቃዋሚ መሆን ብቻ አይበቃም!!!




በሀገሩ ጉዳይ  እገሌ ያገባዋል እገሌ አያገባውም ማለት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን መሃንዲሰ ሀኪም መሆን እንደሌለበት ሁሉ የሚያገባን በምን በምን ጉዳይ መሆኑ ተለይቶ መታወቅ እና የበለጠ ውጤታማ የምንሆንበትን መምረጥ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በኢትዮጵያ ሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ ሁሉም ያገባዋል ነገር ግን በምን ደረጃ ሃላፊነት ሊወስድ ይችላል በሚባለው ጉዳይ ግን ዝርዝር መታወቅ ይኖርበታል፡፡ እገሌ ማን ነው? ተብሎ መጠየቅ ይኖርበታል፡፡ ይህ መጠይቅ ደግሞ በተለይ መቅረብ ያለበት በአንድ ቡድን ውስጥ ሆኖ በአንድ ማዕቀፍ ለመስራት ለሚፈልግ ሰው የግድ ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራር ችግር አለባት፡፡ ተቃዋሚ መሆን ብቻ ለፖለቲካ መሪነት አያበቃም፡፡ ብቃት ያለው የፖለቲካ መሪ እንዳይኖረን ካደረጉት ነገሮች ዋነኛው እስከ ዛሬ በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ለመሳተፍ እራሳቸውን ያዘጋጁ ሁሉ ከስሜት አልፈው የፖለቲካ አመራር ማፍራት ትክክለኛ የፖለቲካ ፓርቲ ተግባር ነው ብለው አምነው ያለማወቃቸው ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ይህ ትልቅ ኃላፊነት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የተተወ እንደሆነ የሚረዱ አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰልፍ መጥራት፣ መግለጫ ማውጣት እና ከፍ ሲል ጋዜጣ ማሳተም ትልቁ የፓርቲ ስራ ይመስላቸዋል፡፡ የሚገርመው አንዳንዶቹ መደበኛ ትምህርታቸውን እንኳን ፓርቲ እንደያስተምራቸው የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ለዛሬው መደበኛ ትምህርታቸውን ፓርቲ እንዲያስተምራቸው የሚፈልጉትን ምስኪኖች ሳይሆኑ እራሳቸውን የፖለቲካ መሪ አድርገው ያስቀመጡ ልሂቃን ላይ ብቻ ማተኮር ነው የምፈልገው፡፡
ሁሉም እንደሚረዳው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲ ምስረታ በእነ ኢህአፓ እና መኢሶን የተጀመረ ሲሆን ከዚያ በኋላ ብዙ ፓርቲዎች በወቅቱ የነበረውን የስልጣን ክፍተት ለመሙላት መደራጀት በሚል ሲደራጁ እንደ ነበር ይታወሳል፡፡ የዚህ ታሪክ ባለቤቶች አሁንም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ዋናዎቹ ተዋናዮች ናቸው፡፡ ሲደክማቸው እያረፉ፣ መልካም አጋጣሚ የተገኘ ሲመስላቸው ብቅ እያሉ ዛሬ ደርሰናል፡፡ በቅርቡ ትዝታችን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ከፍተኛ ንቅናቄ የፈጠረው የቅንጅት መንፈስ ነው፡፡ ይህ መንፈስ ምን ዓይነት እንደነበር ለታሪክ እንዲተው የምንፈልግ ብንኖርም አሁንም የዚህ መንፈስ ተከታዮች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቀሴ ውስጥ ከኢህአፓ መንፈስ ቀጥሎ ከፍተኛ ህዝባዊ ንቅናቄ የፈጠረ መንፈስ የቅንጅት መንፈስ ነው ቢባል የሚቀየም አይኖርም፡፡
ቅንጅትን ከሁሉም በላይ በህዝቡ ዘንድ ተደማጭነት እንዲኖረው ካደረጉት ነገሮች አንዱ ህዝቡ በግንባር የሚያያቸው መሪዎች ከጥቂቶቹ በስተቀር ፕሮፌሰር፣ ዶክተር፣ ኢንጅነር፣ ወዘተ በሚባሉ ማዕረጎች የሚጠሩ ነበሩ፡፡ የተማረ ይግደለኝ የሚባለው ዓይነት መሆኑ ነው፡፡ ይህ መንፈስ ታዲያ ዛሬም የሞተ አልመሰለኝም፡፡ ኢንጀነር የሚል ማዕረግ ከዩኒቨርሲቲ ውጭ በእለት ከእለት ኑሮ መጠሪያ ሲሆን ይህ ዘመን የመጀመሪያ ይመስለኛል፡፡ ይህን ፉርሽ ነገር “መንግሰት” ተብዬውም ተከትሎ “ኢንጅነር” እገሌ እያለ መጥራት ሙያ አድርጎታል፡፡ የተማራ ይግደለኝ መንፈስ አልሞተም ያልኩበት ምክንያት ዛሬም ከዚህ በፊት በተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲካ አፍራሽ ሚና የነበራቸው ሁሉ ድንገት ክፍተት ከተገኘ ብለው ጥፋታቸውን ለማረም ሳይሆን ጥፋታቸውን አድሰው ለመድገም እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ በመስማቴ ነው፡፡
በሀገራችን በሚፈጠር ችግር ከእድሜያቸውም አንፃር ሸምግልና የሚገባቸው ሁሉ ዛሬም በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ ሆነው እራሳቸውን ለስልጣን ሲያጩ ማየት የእውነት ያማል፡፡ ያለፈውን ፓርቲያችሁን ምን አደረጋችሁት? የሰባሰባችሁትን ወጣት ምን በላው? ወዘተ ብሎ የሚጠይቃቸው ያለ አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም እነርሱ ከሰሻ እና ፈራጅ ሆነው መድረኩን የክፋታቸውን ጥላ አጥልተውበታል፡፡
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከአሁን በኋላ የከዚህ ቀደም የፖለቲካ ሂሳቡን ሳያወራርድ ኢንጂነር፣ ዶክተር የሚል ማዕረግ ይዘው ለጡረታ ጊዜ የሚንቀሳቀሱትን አቤት የሚላቸው ካገኙ ይገርመኛል፡፡ የኢህአዴግ መተካካት ምኞት ሆኖ ቢቀርም፣ በተቃዋሚ ጎራ መሪዎች መተካት ባይችሉም በራሳቸው ተነሳሸነት ሃላፊነት ለመውሰድ ለሚመጣ አዲስ ኃይል ቦታ መልቀቅ የግድ ነው፡፡ ቦታ ልቀቁ ሲባል ስልጣኑን ብቻ አይደለም፣ ትግሉንም ጭምር ነው፡፡ እሰከ ዛሬ ላደረጉት ሙከራ ክብር በመስጠት የነበራቸውን ረጅም የትግል ታሪክ በመፅኃፍ መልክ ለትውልድ በታሪክ መልክ በታማኝነት ማሰቀመጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ለራሳቸውም ቢሆን ምን ያህል ታማኝ እንደሆኑ ሌላው እንዲረዳቸው እድል ይስጣል፡፡
ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ጡረታ መውጣት ካለባቸው ሰዎች አንዱ እና ዋነኛው ግዛቸው ሸፈራው (ኢ/ር) ነው፡፡ በፌስ ቡክ ላይ “በቅንጅት መንፈስ በሚል ፓርቲ ለመመሰረት መንገድ ላይ ያለው ግዛቸው ለአንድነት መፍረስ ያሰቀመጠውን የመሰረት ድንጋይ እረስቶት ፓርቲ በማፍረስ ኢህድግን ብቻ ይከሳል፡፡ እሱ ቢረሳው እኛ ግን አንረሳውም እና ……. ከአሁን በኋላ የፓርቲ ፖለቲካ ቢቀርበት ምከሩት” ብዬ ለጥፌ ነበር፡፡ ፌስ ቡክ ላይ ባያየውም በደንብ እንደሰማው መረጃው አለኝ፡፡ ግዛቸው በቅንጅት ጊዜ የተጫወታቸው ሚናዎች በወቅቱ በነበረበት ጊዜ የሚገመገም ቢሆንም አንድነትን በመስራችነት እና በመሪነት ሲያገለግል ምን ሰርቶ ምን አድርጎ ፓርቲውን እንዳፈረሰ ማስረዳት ይኖርበታል፡፡ ይህን በቅጡ ሳይወጣ ዛሬም የፖለቲካ ፓርቲ መስርቶ መሪ ሊሆን ያሰባል፡፡ የሚገርመው “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዳለቸው አህያ አንድነትን በመሪነት ከሚያፈርስ ሚዲያ ጋር ቀርቦ እራሱን ሲከስ የነበረ ጀግና፣ በአንድነት ንቅናቄ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ መቸለሱን ረስቶ ዛሬም ፖለቲካ መጫወት ያምረዋል፡፡ ግዛቸው ፓርቲ ካማረው ከትዕግሰቱ አወሉ ጋር ተሰማምቶ መሰራት ነው ያለበት፡፡ ይህን ለማድረግ የሬዲዮ ፋናው ብሩክ ሊረዳው እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ምክንያቱም የትዕግሰቱ አወሉ ቡድን ከምርጫ ቦርድ ድጋፍ ያገኘው “ግዛቸው ከስልጣን የተነሳው በህጋዊ መንገድ አይደለም” የሚለው መከራከሪያ አቅርቦ ነው፡፡ ግዛቸው “በፈቃዴ ነው የለቀቅሁት” ብሎ ቃሉን ለመስጠት ዳተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን “በሀሰት ከኃላፊነቴ እንደለቅ የተገደድኩት ፋይናንስ በባንክ ይሁን ስላልኩ ነው” ብሎ ራሱን ጭምር በሬዲዮ ፋና ቀርቦ ከሶዋል፡፡ አንድነት ፓርቲ ከማንም ፓርቲ በተሻለ የፋይናንስ ስርዓት እንዳለው እያወቀ ቢሆንም ክፋቱን እወነት ሊያሸንፈው አልቻለም፡፡ ከዚህ ዓይነት ክፉ ሰው ጋር የፖለቲካ ማህበር አይደለም እንዴት ሌላ ማህበራዊ ኑሮ ይታሰባል፡፡ ያለፈውንም ይቅር ይበለን!!
ከግዛቸው ጋር የፓርቲ ምስረታ ጥንስስ ላይ ያለ ሁሉ /ለጊዜው ስም አልጠራም/ በዝርዝር እራሳችሁን ማየት ይኖርባችኋል፡፡ ከደርግ የማይሻል የለም ተብሎ የመጣው ህወሃት/ኢህአዴግ ደርግን በአፈና አስንቆታል፡፡ እናንተም ከዚህ መሻላችሁን በእውነት ቀድማችሁ አስመስክሩ፡፡ ሀገራችን የወላድ መሃን የሆነችበት ወቅት ላይ እንገኛለን እና በጥንካሬ መሪ ለመፍጠር አስበን መስራት እንዳለብን ማወቅ ይኖርብናል፡፡
ቸር ይግጠመን!!


Monday, October 24, 2016

የፕሬዝዳንት ሙላቱ ሪፖርት እና የፋና ውይይት……..



ታሪከኛው የ2007 ምርጫ ተጠናቆ ገዢው ፓርቲ `መንግሰት` መስርቻለሁ ባለ ማግስት በተጀመረ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ሲናወጥ የከረመው መንግስት የሁለተኛ ዓመት ስራውን ለመጀመር ማሟሻ ንግግር የሚያደርጉት ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ መሰከረም 30/2009 ንግግር አድርገዋል፡፡ ተከትሎም የግንባሩ ልሣን ፋና ብሮድካሰቲንግ ማስመሰያ ውይይት አዘጋጅቷል፡፡ ከፕሬዝዳንቱ ሪፖርት እና ከፋና ውይይት ምን እንጠብቅ የሚል ጥያቄ ለራሴ አቅርቤ ትዝብቴን አሰቀምጫለሁ፡፡ የፕሬዝዳንቱ የመክፈቻ ንግግር እና የፋና የውይየትት ፕሮግራም በተለመደው መስመር ማዘናጋት እና አሁንም ገዢው ፓርቲ ህወሃት/ኢህአዴግ መሆኑን አረጋግጦ ማለፍ ነው፡፡ የተወሰኑ ነጥቦችን አንስተን ለመመልከት እንሞክር፡፡
እንደ መነሻም በሰሞኑ ለነበረው የህዝባዊ እንቅስቃሴ ሞተር ለነበረው ወጣት ትውልድ ማዘናጊያ የሚሆን 10 ቢሊዮን ብር መመደቡን አብሰረዋል የዚህ ዓመት በጀት ጉዳይ በሰኔ 30 መጠናቀቁን የሚያስታውስ ሰው ያለ አልመሰላቸውም፡፡ ቀደም ሲል የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ሙክታርም ለኦሮሚያ ቀወስ 3 ቢሊዮን በጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ ሶሰት ወር ሲቀረው ለወጣቱ ሰራ ፈጠራ መድነበናል ብለው ነበር፡፡ ይህ በጀት የኦሮሚያን ችግርም አላበረደም አቶ ሙክታርንም በስልጣን ሊያቆይ አልቻለም፡፡ 10 ቢሊዮን ብር በጀት የወጣቱን ጥያቄ ለመመለስ የወሰዱትን እርምጃ በአስገራሚነቱ ተወዳዳሪ ሊኖረው አይችልም፡፡ ምን ማለት ነው “ወያኔ ይውደም!!” ብሎ መፈክር ለሚያሰማ ወጣት መልሱ “አርፈህ ወደ ስራ ግባ!!” እንደማለት ነው፡፡ ወጣቱ የጠየቀው የስርዓት ለውጥ ነው፡፡ የስርዓት ለውጥ የሚያመጣውን ማነኛውንም እድል የስራ ዕድልን ጨምሮ ለማየት ይፈልጋል፡፡ 25 ዓመት ተሞክሮ ያልተሳካለት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ትንተና መልስ እንደማይሰጠው ነው ወጣቱ የተናገረው፡፡ ለዚህ መልስ መስጫው መንገድ ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ ተዘጋጅቶዋል የሚል ፌዝ ያዘለ መልስ ያስቃል፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ ጉዳዩን የምር እንዳልያዙት የሚያስታውቀው በቅርቡ ሬዲዮ ፋና በጠራው ስብሰባ ላይ የተጋበዙት የወጣቶች ተወካይ የኢህአዴግ አደረጃጀት ወጣት ናቸው፡፡ እነዚህ ወጣቶች ሰልፍ አልወጡም ጥያቄም አላቀረቡም፡፡ ይልቁንም ጥያቄ ያነሱትን ወጣቶች ፀረ-ሰላም እያሉ የሚከሱ ቡድን ተወካይ ናቸው፡፡ ምን አልባትም የተመደበው በጀት ለዚህ ቡድን ሊያገለግል ይችላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ስናወራ ይህ የስርዓቱ ትክክለኛ መገለጫ ነው፣ ችግሮች የሚፈቱት በገንዘብ ይመስላቸዋል፡፡ ሙሰኛ ስርዓት ህዝብንም ሙሰኛ አድርጎ በማየት በገንዘብ ለመደለል ይሞክራል ነው ያለኝ፡፡ እኔም ተሰማምቼበታለሁ፡፡ ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ ከሚል የዘራፊዎች ቡድን ከዚህ የተሻለ የመፍትሔ አቅጣጫ አይገኝም፡፡ የወጣቱ ጥያቄ የስርዓት ለውጥ ነው፡፡ መልሱም እንዴት በተረጋጋ ሁኔታ የስርዓት ለውጥ እናምጣ የሚለው ነው፡፡ መልሱን ከወጣቱ ጋር በግልጽ መወያየት ነው፡፡ ወጣቱ ተወካይ የለውም እንዳትሉን ከዚህ በፊት እንደዳልኩት እኔ ዞን ዘጠኝ የሚባሉትን ወጣቶች ወክያለሁ ……. ሌላም መጨመር ይቻላል፡፡ ከፎረም ውጭ ……
በፕሬዝዳንቱ ንግግር ውስጥ ትኩረት አግኝቶ በተለያየ መንገድም ትኩረት የሳባው የምርጫ ህግ ማሻሻል የሚመለከተው ነው፡፡ የምርጫ ህግ ማሻሻል ሲባል ብዙ ሰው “ህገ መንግሰት ማሻሻል” መሆኑንም ዘንግቶታል፡፡ ከብዙዎቹ አንዱ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ህገ መንግሰት አንቀፅ 54/2 በአንድ ምርጫ ክልል አብላጫ ድምፅ ያገኘ ያሸንፋል በሚለው መስረት ይመረጣል ነው የሚለው፡፡ ሰለዚህ ሌላ የምርጫ ስርዓት ማድረግ አይቻልም፡፡ ህገ መንግሰቱ ሳይሻሻል ማለት ነው፡፡ ሌላው ህወሃት/ኢህአዴግ ማስተላለፍ የፈለገውን መልዕክት ብዙ ሰው የተቀበለው ይመስለኛል፡፡ ይህ መልዕክት “ህውሃት/ኢህአዴግ እና አጋሮች አሸንፈዋል” የሚለው ነው፡፡  ይህ ማለት ግን “ሁሉም ሰው መርጦናል ማለት አይደለም” የሚለውን መልዕክት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ምርጫው ነፃ፣ ፍትሃዊና ታማኝነት ነበረው ለማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያስፈልገው ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ግልፅነት ያለው ምርጫ እንጂ የምርጫ ስርዓት ለውጥ አይደለም፡፡ የምርጫ ስርዓት ለውጥ የሚጠቅመው በቢሮ ቁጭ ብለው የፓርቲ ሰርተፊኬት እና ማህተም በፌስታል ይዘው የብሄር ተወካይ ነን በሚል የውክልና ስልጣን ለማግኘት ለሚፈልጉ ጥቂት ግለሰቦች ነው፡፡ አሁን ባለው ምርጫ ስርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ የብዙሃን ፓርቲ ስርዓትን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ከዚህ የተለይ የምርጫ ህግ የሚመክሩን የውጭ አማካሪዎችም ሆኑ ኢትዮጵያዊያን ልሂቃን በኢህአዴግ ምርጫ አሸንፊያለሁ ችግሩ የምርጫ ስርዓቱ ነው በሚለው መታለላቸውን ማስታወስ ይኖርብኛል፡፡ በመደራጅት መብት ስም ማንም ሱሰኛ የፓርቲ ሰርተፊኬት ይዞ ዕጩ የሀገር መሪ ቡድን ነኝ ሲል ዝም ሊባል አይገባም፡፡ በምርጫ ስርዓት ማሻሻል ሰምም የህዝብ ውክልና ማገኘት ዕድል ሊመቻች አይገባም፡፡
በኢትዮጵያ ሀገራችን ውይይት አጅግ በጣም አስፈላጊ እና በእጅጉ የጎደለን የሰልጣኔ መንገድ እንደሆነ ይስማኛል፡፡ ውይይት ሲባል ደግሞ ገዢዎች ንግግር ሲያደርጉ የሚያዳምጣቸውን የፎረም ተወካዮች ሰብሰቦ ሲሞጋገሱ መዋያም መድረክ አይደለም፡፡ ውይይት ሲባል ሃሳብ ተለዋውጦ የሃሳብ ሽግሽግ ለማድረግ መዘጋጀትንም ይጠይቀል፡፡ የሃሳብ ሽግሽግ የሚደረግበት የውይይት መድረክ ሀገራችን በእጅጉ ያስፈጋታል፡፡ በሰብሰባ ውስጥ የህዝብ ሰሜት የሚኮረክሩ ንግግሮች ከተደረጉ በኋላ ሹሞች ያሻቸውን በማጠቃለያነት ተናግረው፣ ሲፈልጉም ዘለፋ አክለውበት ምን ታመጣላችሁ፣ ከቻላችሁ ተደራጅታችሁ እራሳቸሁን አጠናክራችሁ መጥታችሁ ግጠሙን በሚል ፉከራ የሚጠናቀቅ መሆን የለበትም፡፡ ይህ ዓይነቱ መድረክ የውይይት ሳይሆን የፉከራና ቀረርቶ ነው ሊባል የሚችለው፡፡ ተጠናክሮ መጥቶ ለመጋጠም የሕወሃት/ኢህአዴግ ምክር አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ መጋጠሚያ ቦታውን እና የመጋጠሚያ ህጉን ማስተካክል ነው፡፡ የብረት ቦክስ ይዞ ሜዳ እየገቡ ባዶ እጅ ያለን ተጋጣሚ ማድማትና ማቁሰል ጉብዝና ሳይሆን ህገወጥ መሆን እና ውንብድና ነው፡፡
ሌላው የሪፖርቱ አስገራሚ ነጥብ የዜጎች መፈናቀል የሚመለከተው ነው፡፡ ዜጎችን ማፈናቀሉ ትክክል እንዳልሆነ ተገንዝቢያለሁ ያለ የሚመስለው ገዢው ፓርቲና መንግሰት በተዘዋዋሪ ማፈናቀል እቀጥላለሁ ነገር ግን የሚሰጠውን ካሳ ከጊዜው የዋጋ ንረት፣ የምርት ዋጋ እና ምርታማነት እድገት ጋር ተገናዝቦ ይሻሻላል የሚል መግለጫ እየሰጠ ይገኛል፡፡ አታፈናቅሉኝ ያለን ዜጋ ዋጋ ጨምረን እናፈናቅልህ እያሉት ነው፡፡ ህውሃት/ኢህአዴግ ችግሩን ከመስረቱ መፍታት ሳይሆን አሁንም ዙሪያ ጥምጥም መሄድ መርጠዋል፡፡ የህዝቡ ጥያቄ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ መልስ ያግኝ ነው፡፡ የያዘውን መሬት ለልማት ሲባል እንዴት እና በምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚለቅ በኋላ የሚደረስበት የውይይት ነጥብ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ እንደ ምርጫ ሰርዓቱ ህገ መንግሰታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ገዢው ፓርተ የመሬት ነገር በመቃብሬ የሚለውን ነገር ወደ ጎን ትቶ መሬት ለባለመሬቱ ማስተላለፍ ይኖርበታል፡፡ ቀሪውን ስንደርስ የምንጫወታው ይሆናል …… ድልድዩን ሰንደርስ እንሻገራለን እንደሚባለው መሆኑ ነው፡፡
የህወሃት/ኢህአዴግ ጥልቅ ተሃድሶ ፍልስፍና ፈርሶ እስከ መሰራት እንደማይደርስ አቶ አባይ ፀሃዬ ነግረውናል ባይነግሩንም የሚታወቅ ሀቅ ነው፡፡ ፈረሰው ይሁን፣ በአሸዋ ላይ ፓርቲያቸውን መስራት የእነርሱ ምርጫ ነው፣ ይህን ምርጫቸውን የምናከብርላቸው ቢሆንም አሁንም የኢትዮጵያን ህዝብ በካበኔ ሹም ሽር ለመሸንገል ተጨፈኑ እናሞኛችሁ ብሎ ማሰብ መፍትሄ ፍለጋ እና ችግሩን መረዳት ላይ እጅግ ልዮነት እንዳለን ማሳያ ነው፡፡ የኢህአዴግ ካቢኔ ማንንም ይዞ ቢመጣ መስመሩን እስከ አላስተካከለ እና በመድበለ ፓርቲ ስርዓት ውስጥ ቁጥጥር የሚደረግበት ካልሆነ ትርጉም የሌለው ድካም ነው፡፡ ምን አልባትም በራሳቸው ስር ሌላ አኩራፊ ከመጨመር ውጭ የተለየ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ አቶ ጁነዲን ሳዶን የመሰለ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፈላስፋ (በሀገር ውስጥ እያለ) አሁን በግልፅ ምንም ስልጣን አልነበረኝም ስልጣኑ የህወሃት ነው ማለቱን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ተራው የማን ነው? መጠበቅ ነው፡፡
በመጨረሻ በቅርቡ ይወጣል የሚባለውን “የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ” የሚመለከት አዋጅ ነው፡፡ ይህ አዋጅ ምን ያህል የተደከመበት ቢሆን ህወሃት/ኢህአዴግ በለመደው መልኩ አዋጅ አድርጎ ካወጣ በኃላ ንትርክ የሚፈጥር እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ቢያንስ በቅርቡ ይወጣል ሲባል እንኳን ለህዝብ ለውይይት የሚረዱ አንኳር ነጥቦችን ማጋራት አልቻሉም፡፡ ጉዳዮንም የኦሮሚያ ክልል ብቻ በማድረግ የአዲስ አበባ ነዋሪ ግብር ከፋይ ምንም መረጃ እንዲኖረው እየተደረገ አይደለም፡፡ ሰለዚህ ይህ አዋጅ ምን ይዞ ይመጣል ወደፊት የምናየው ነው፡፡ ፕሬዝዳንቱ ግን በቅርቡ ይታወጃል ብለዋል ….. ቅርብ መቼ ነው? በነገራቸን ላይ ሀረሪ ክልል በሚባለው ውስጥስ ቢሆን ኦሮሚያ ልዩ ጥቅም አያስፈልጋትም ትላላችሁ፡፡ ወይም ክልሉ ለኦሮሚያ ተሰጥቶ የሀረሪ ልዩ ጥቅም የሚባል ነገር በሃሳባችሁ መጥቶ አያውቅም፡፡ እጅግ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ ሀረሪዎች ሁልጊዜ አሸናፊ የሚሆኑበት ምርጫ ኢትዮጵያችን ውስጥ ላለው አሳፋሪ የምርጫ አፈፃፀም ጉልዕ ማሳያ ነው፡፡ ሰለምርጫ ከላይ ያነሳሁትን ነጥብ እዚህም ማስታወስ የግድ ይላል፡፡ አዲስ አበባ መቼ ነው በነዋሪዎች ቀጥተኛ ምርጫ ከንቲባ የምትመርጠው የሚል ጥያቄ አሁንም አለኝ፡፡
ይህ ፅሁፍ በምንም መልኩ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር እንደማይጋጭ እራሴን ሳንሱር አድርጌ ነው የፃፍኩት፣ቢጋጭም ይጋጭ ብዬ ለጥፌዋለሁ፡፡
ቸር ይግጠመን!!!!