Tuesday, September 16, 2014

ተጠያቂነት የማያረጋግጥ የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ

ባለፈው ሳምንት ማጠናቀቂያ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ሰብሳቢነት የመንግሰት ከፍተኛ ባለስልጣኖች የ2006 የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ሁሉም ሪፖርት አቅራቢዎች “ፖወር ፖይንት” በሚባል የማይክሮ ሶፍት ፕሮግራም የተጠቀሙ ሲሆን አብዛኞቹ ይህን ፕሮግራም በቅጡ ለመጠቀም በግል ያላቸውን ዝቅተኛ ችሎታ ያሳየ ብቻ ሳይሆን በየመስሪያ ቤታቸው ሞያ ያላቸውን ሰዎች መጠቀም ያለመቻልና ያለመፈለግን ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነበር፡፡ የተፈቀደላቸውን አጭር ጊዜ ያመጣጠነ ዝግጅት ማድረግ ሳይችሉ ቀርተው ያዘጋጁትን የፅሁፍ ሪፖርት ሲያነቡ ጊዜ አለቀ እየተባሉ ማስተላለፍ የሚፈልጉትን ቁም ነገር (ካለቸው ማለቴ ነው) ትተው በመግቢያና በሪፖርት ይዘት ጊዜ ሲያባክኑ መታዘብ አሰገራሚ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር የውሃ መስኖ ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ በንፅፅር የተሻሉ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ቴክኖሎጂ የመጠቀም አስፈላጊነቱም ሰዓትን በአግባቡ በመጠቅም ተገቢውን መልዕክት ለማስተላለፍ ነው፡፡ ረፖርት አቅራቢዎች ስዓት በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላቸው ሊያቀርቡ ያሰቡትን በሙሉ ካለማቅረባቸው በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የሰዓት ቁጥጥር ስራ ጨምረውባቸው ነው የዋሉት፡፡ እርግጠኛ ነኝ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆኑ ኖሮ እንዴት ሊበሳጩባቸው እንደሚችሉ፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ሚኒሰቴር ሚኒስትሯ ወ/ሮ አስቴር ማሞ ድርጅታቸው ኢህአዴግ ንቅናቄውን እንደ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ግብዓት ለመጠቀም መወሰኑን በሚያሳብቅ ሁኔታ መሪ ድርጅታችን ኢህአዴግ አና መንግስታችን በሰጡት ትኩረት በሚል ነበር ንግግራቸውን የጀመሩት፡፡ የመሪ ድርጅታችን ኢህአዴግ በንግግሩ መግባት መልዕክት ለተሰበሰቡት የመንግስት ሹሞች ሳይሆን ጥሪ ለተደረገላቸው እና በአዳራሹ በብዛት ለታደሙት በኢህአዴግ አጣራር “የህዝብ አደረጃጀት” በመባል ለሚታወቁት የኢህአዴግ አፍቃሪዎች ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሆን የስብሰባ ታዳሚዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት “ውድ” የሚል ተቀፅላ ያገኙት እነዚሁ የህዝብ አደረጃጀቶች ናቸው፡፡ እርግጥ ነው በቀጣዩ ምርጫ በአሸናፊነት ለመውጣት የእነዚህ የህዝብ አደረጃጀቶች ሚና የላቀ ነው፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ተቃዋሚዎች ተጠናክረው ታዛቢ ካስቀመጡ ምርጫ ቦርድ ያለነዚህ የህዝብ አደረጃጀት ንቁ ተሳትፎ ቢሮ ቁጭ ብሎ ኢህአዴግን ብዙ ሊረዳው አይችልም፡፡ ጠቅላይ ሚኒሰትሩም ሆነ ፓርቲያቸው ይህ በቅጡ የገባቸው ይመስለኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ እዚህና እዚያ የጎደሉ አግልግሎቶችን በማስተካከል ብቻ የሚያበቃ እንዳልሆነ ይልቁንም የመልካም አስተዳደር ችግር በቀጣይ የሚያመጣው “መዘዝ” ብዙ መሆኑን አበክረው ገልፀዋል፡፡ እርሳቸው “መዘዝ” ያሉትን እኛ አብዮት ስንለው የመንግሰት ሚዲያዎች ደግሞ ተቀብለው “የቀለምና የፍራፍሬ አብዮት” ይሉታል፡፡ ተመስገን ደሳለኝ አብዮት ብቻውን የማይጥም ከሆነ ብሎ ይመስለኛል “የህዳሴው አብዮት” ብሎታል፡፡ ለማነኛውም በዚህች ሀገር የተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር ችግር መዘዙ ብዙ መሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ከታመነ ይህ መዘዝ የተባለው ነገር ስሙ ብዙ አያስጨንቀንም፡፡ የሚያስጨንቀን ይህ መዘዝ እንዳይከተል ምን ማድረግ ይኖርብናል ነው፡፡ በተለይ መንግሰት ይህን መዘዝ ለመከላከል ብሎ ለናይጄሪያ ሽብርተኝነትን ለመከላከል ልምድ ይሆናል ተብሎ የተነገረለትን “የፀረ ሽብር” ህግ እንደመፍትሔ አሰቦት ከሆነ ከመዘዙ እየራቀ ሳይሆን ወደ መዘዙ በፍጥነት እየተጠጋ መሆኑን መረዳት ይኖርበታል፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኖ ሌሎች ሚኒሰትሮች በተደጋጋሚ ያነሱት ሌላ አብይ ነገር የኪራይ ሰብሳቢነት የሚመለከት ሲሆን ይህን የኪራይ ሰብሳቢነት የገለፁት የኪራይ ስብሳቢነት መረብ በሚል ነበር፡፡ በዕለቱ ያነበብኩት ጋዜጣ ደግሞ በኮንትሮባንድ ሊገባ የነበረ ወተት በኬላ መያዙን የሚገልፅ ክፍል ነበረው፡፡ ታዲያስ ስብሰባ ላይ ቁጭ ብዬ “የሰው ለሰው ድራማ” አስናቀ እና ኢህአዴግ ቁልጭ ብለው ይታዩኝ ጀመር፡፡ ይህን መረብ ለመበጠስ እሰከ አሁን እንዳልተቻለ እና ከፍተኛ ትግል እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒሰትሩን ጨምሮ ሚኒስትሮቹ  እየገለፁ ኢቲቪ ደግሞ አሰናቀ ለፍርድ ሳይቀርብ ለምን ሞተ ብሎ ዶክመንተሪ ይሰራል፡፡ የኪራይ ስብሳቢነት መረብ እስኪበጣጠስ ድረስ አስናቀ መኖር እና ማጋለጥ ነበረበት የሚል አቋም አለኝ፡፡ እናንተስ ምን ትላላችሁ ጎበዝ? አሁን አንድ የቴሌቪዥን ድራማ አጨራረስ እንዴት መሆን እንዳለበት ዶክመንተሪ ያስፈልገዋል? ለማንኛውም የሰው ለሰው ድራማ ደራሲና አዘጋጆች የህዝቡን እንጂ “ባለሞያ” ተብዬዎች በኢቲቪ ያቀረቡትን አስተያየት እንደማትሰሙ እርግጠኛ ነኝ፡፡
ዶክተር ደብረፅዮን በዕለቱ ሪፖርት ከሚያቀርቡት ሚኒስተሮች ቀዳሚውን ቦታ ያገኙ ነበሩ፡፡ ሪፖርት ያቀረቡት በዋነኝነት የቴሌኮሚኒኬሽን ሴክተሩን  በሚመለከትነው፡፡ ከሚመሩት መስሪያ ቤት አንፃር ሲታይም ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተሻለ መሆን ሲጠበቅባቸው ማድረግ አልቻሉም፡፡ የቀረበው ሪፖርትም በፍፁም በመሬት ላይ ካላው የቴሌ ችግር ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ በሪፖርቱ መስረት ሁሉም ችግሮች በእቅድ ከተያዘው ጊዜ ቀደም ብሎ የተተገበረ ሲሆን በአሁኑ ስዓት በተለይ በአዲስ አበባ ይህ ነው የሚባል ችግር እንደሌለ ነው ያበሰሩን፡፡ ይህ ግን በምንም መመዘኛ ተቀባይነት እንደሌለው ለመረዳት ከሪፖርታቸው በኋላ በሻይ እረፍት የተሰበሰቡት ሹመኞች ሳይቀሩ ሲያፌዙ እንደነበር ልነግራቸው እወዳለሁ፡፡ ዶክትር ደብረፅዩን ከአቀረቡት ሪፖርቱ ውስጥ የቴሌን ሰራ ለመስራት የፈጠሩት አደረጃጀት አንድ ጥሩ ነገር ጠቆም አድርጎን አልፏል፡፡ ይህም ፓርላማው ማፅደቅ የማያስፈልገው የቴሌን አገልግሎት በአሰራ ሦስት ክበቦች ወይም ክልሎች መከፋፈላቸው ነው፡፡ ይህም የተደረገው ለአሰራር ቅልጥፍና ሲባል እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ተቀባይነት ያለው በጎ ጅምር ነው፡፡ በዚህ አደረጃጀት ሀረሪ ወይም ድሬዳዋ በምንም መለኪያ አንድ ክልል ሊሆን አይችሉም፡፡ አዲስ አበባ እንኳን አንድ ክልል ሊሆን አልቻለም፡፡ ሌሎችም በተመሳሳይ እንዲሁ፡፡ ይህ ለቴሌ አገልግሎት ምቹ የሆነ አደረጃጀት ለሌሎች የመልካም አስተዳደር እንዲሁም ማህበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ በሚመች መልኩ የፌዴራል ስርዓቱ ይዋቀር ለምንል ሰዎች እንደ ጥሩ መግቢያ ሊያገለግል ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይህን ሀሳብ ከዶክተር ደብረፅዮን ወስዶ የህዝቦችን ቋንቋ እና ስነ ልቦና መሰረት ባደረገ ሁኔታ ቢየጠናው ጥሩ ሀሳብ ይመስለኛል፡፡ እሰኪ አንዴ ከያዝነው አስተሳሰብ ወጣ ብለን በተለየ መንገድ ለማሰብ እንሞክር፡፡ ዶክተር ደብረፅዩን ያቀረቡት ሀሳብ በሌሎች ፌዴራል መስሪያ ቤቶችም ሊሞከር ይችላል፡፡ ይህ የምክር ቤት ውሳኔ አይጠይቀም ብለዋልና፡፡
የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ባለፈው ዓመት ሰኳር እና ስንዴ እጥረት እንደነበረ በይፋ አምነዋል፡፡ ያቀረቡት ምክንያትም ሰኳር ይደርሳል ተብሎ ተገምቶ በፊንጫ እና ተንዳሆ ሰኳር ፋብሪካ በእቅዱ መሰረት ባለመድረሱ ችግር መከሰቱን ነው፡፡ እኛም ሰንል የነበረው ችግር አለ በእቅድ መስራት አልቻላችሁም እንዲሁም አትችሉም ነው፡፡ የሰንዴም የሰኳርም እጥረት የለም ሲሉን እንዳልነበር አሁን ችግር መኖሩን አምነው ከውጭ ግዥ እየተፈፀመ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ ይህች ሀገር በሌላት የውጭ ምንዛሪ በሀገር ውስጥ ሊመረት የሚችልን ምርት ከውጭ እንድታሰገባ እያደረገ ያለን ፖሊሲና ፈፃሚዎቹ ተጠያቂ ሊያደርግ አልቻለም፡፡ ሰኳርና ስንዴ ማቅረብ ያልቻለ የሃያ ዓመት አገዛዝ መዘዝ ሊመጣበት እንደሚችል ቢፈራ ተገቢ ነው፡፡ አንድ በግብርና ላይ የተሰማሩ ባለሀብት ፈራ ተባ አያሉ “ስንዴ ከውጭ ታዞ የሚመጣበት ገዜ እና በሀገር ውስጥ ቢመረት የሚወሰደው ጊዜ ተቀራራቢ ነው፡፡” ብለዋል፡፡ አስከትለውም “ኢትዮጵያ ሰንዴና ሰኳር ኤክስፖርት የምታደርግ ሀገር እንጂ ከውጭ የምታስገባ መሆን የላባትም፡፡” በማለት ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡ ግብርና ግን መሬት ይፈልጋል መሬት ደግሞ በመንግሰት እጅ ሆኖ እንደልብ የሚገኝ አይደለም፡፡ የመሬት ፖሊሲያችን ይፈተሸ ስንል ለምን ጫጫታ ይበዛል?
የፍትሕ ሚኒሰትር ሪፖርት በጥቅምት ወር ባቀረቡት እቅድ በግርፊያ ምርመራ ያደርጋሉ ያሉዋቸውን ፖሊሶች እንዴት እንደተቆጣጠሩ ሳይነግሩን ቢጫ ታክሲ ማህበራት ጋር ስብሰባ አድርገናል እና የመሳሰሉትን ሪፖርት ማድረግ ምን ፋይዳ እንዳለው መረዳት ከባድ ነው፡፡ አስገራሚው ደግሞ ፍትህ ሚኒስትር የሚያዘጋጀው የዜጎች ቻርተር ነው፡፡ በእኔ እምነት ፍትህ ሚኒስትር ከህገ መንግሰቱ የተሻለ ሌላ የዜጎች ቻርተር የሚያስፈልገው አይመስለኝም፡፡ በፍትህ ሰርዓቱ እምነት እንዲኖረን ህገ መንግሰቱን ማስከበር ላይ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከሌሎች የመንግሰት አካላት ጋር ተባብሮ የህገ መንግስቱን መስረታዊ ድንጋጌዎች መናድ ማቆም አለበት፡፡ ለዚህም ማሳያው በቅርቡ በመፅሔቶች እና ጋዜጦች ላይ በመንግሰት ሚዲያ የተጀመረውን ስም ማጥፋት ተከትሎ በፍትህ ሚኒስትር መሪነት ወደ ፍርድ ቤት ማምራቱ ነው፡፡ ዘጠና ሚሊዮን ለሚሆን ህዝብ ቢበዛ 20 ሺ ኮፒ ለሚያትም  አንድ መፅሔት ሀገር ሊያጠፉ ነው የሚል መዓት ማውራት ምን አመጣው? ለነገሩ የፈሪ ዱላ የሚባለው ብዒል አንደሆነ መገመት አያሰቸግረም፡፡ ግለሰቦችን እያሳደዱ በማሰር እና አሰሮ ማሰረጃ እያፈላለኩ ነው ከሚል ፌዝ  መውጣት ይኖርብናል፡፡ መንግሰት “የፀረ ሸብር ህግ” ያሰፈልገናል ሲል የነበረው ሰዎችን ሳይዝ በቂ ማሰረጃ ለመሰብሰብ ይጠቅመኛል በሚል እንደነበር እናስታውሳለን፡፡
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ ይህ ነው የሚባል ነገር ሳያቀርቡ ሰዓት ሰዓት አልቋል ቢባሉም በከተማው የተንሰራፈውን የቤት ችግር ለመቅረፍ በተለይ በማሕበር ለመገንባት ገንዘባቸውን ባንክ ላስገቡ፣ ቅድሚያ ታገኛላችሁ ተግለው ከሚፈለገው 40 ከመቶ በላይ ባንክ ያስገቡ በ40/60 የተመዘገቡ እና በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊየን በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን የቤት አቅርቦት ማሳካት አለመቻል አንድም ነጥብ ሊያነሱ አልቻሉም፡፡ ዜጎች ቤት እናገኛለኝ ብለው ተብደረው ባንክ ያሰቀመጡትን ገንዘብ የመንግሰት ባንክ እየነገደበት ትርፍ በትርፍ ሲሆን ዜጎች ቀጣይ ተሰፋቸው ምን እንደሆነ እንኳን ማሰረዳት አልቻሉም፡፡ አዲሱ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ምዝገባ የተጀመረ ሰሞን አንድ ፅሁፍ አቅርቤ እንደ ነበር ይታወሳል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት የቤቶች ግንባታን አስመልክቶ ሂሳብ ማውራረድ ስለሚኖር ለዛሬው በዚሁ ማለፍ ይሻላል፡፡ ዜጎች ግን አሁንም ተሰፋ እያደረጉ ነው?
በመጨረሻ ሁሉም ሪፖርት አድራጊ መስሪያ ቤቶች እንደ ችግር ያነሱት “የከፍተኛ አመራር እና ፈፃሚዎች የአመለካከት ችግር መኖር” የሚለው ይገኘበታል፡፡ ይህ ችግር ሁሌም በኢህአዴግ ሰፈር እንዳለ የምንረዳው ስለሆነ መፍትሔው በየአዳራሹ እየመሸጉ ሰልጣና፣ ስልጣና እየተባለ የሀገር ሀብትና ንብረት ከማባከን ተጠያቂነት የሚያሰፍን ሰርዓት በመዘርጋት ኃላፊነቱን ብቃት ላለው ዜጋ ማስረከብ ነው፡፡ አሁን በኢህአዴግ አባልነት በመንግሰት ስልጣን ላይ የሚገኙት በአብዛኛው ከዝቅተኛ ደረጃ እስከ ማስተርስ እና ከዚያም በላይ በርቀትም ሆነ በመደበኛ ይህች ሀገር አስተምራለች፡፡ እነዚህ ኃለፊዎች ባለፉት ሃያ ዓመታት የሰለጠኑ ቢሆንም ለህዝብ መልካም አስተዳደር ለማስፈን የሚያስችል አመለካከትና ክዕሎት ማደበር አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ቦታውን መልቀቅ ግድ ይላቸዋል ብንል ድፍረት ሊሆን አይችልም፡፡ ቦታውን የማስለቀቅ ኃለፊነት ደግሞ የህዝብ ነው፡፡ የህዝብ ድምፅ ይከበር ዘንድ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት፡፡ ማንም የማንም ነፃ አውጪ አይደለም፡፡

ቸር ይግጠመን!!!

Thursday, September 4, 2014

የኢቲቪ ጥያቄዎች እና የእኔ መልሶች


በሰሞኑ ሰለ ግል ሚዲያው ትንሽ ለማለት ሞክሬ ነበር፡፡ የዚሁ ተከታታይ የሆነውን ይህ ፅሁፍ ደግሞ በዋነኝነት የአሁኑ የኢትዮጵ ብሮድካሰት ኮርፖሬሽን ለዘጋቢ ፊልም መስሪያ ብሎ ያዘጋጀውን ጥያቄ መሰረት አድርጌ አቀርብላችኋለው፡፡ ከጥያቄው መረዳት እንደምትችሉት ጥያቄዎቹ ለውንጀላ በሚያመች መልኩ የተዘጋጁ ሰለሆነ በግልፅነት ጥያቄውን ለመመለስ የሚሞኩሩ ሰዎች እንደ አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ መጠለፋቸው አይቀርም፡፡ ሚዲያ ብላችሁ አዲስ ዘመንን ስትከሱት ኢቲቪ ከሌላ ቦታ ካመጣው ጋር ቆርጦ ቀጥሎ ዘጋቢ ፊልም የግል ሚዲያውን ለመክሰስ ግብዓት ያደርጋችኋል፡፡ ይህን ለመከላከል ኢቲቪን በሩቁ ማለት ሳይሻል አይቀርም፡፡ ለዚህም ነው የቀረቡልኝን ጥያቄዎች ለኢቲቪ ብመልስ ምን ሊሆን እንደሚችል በምትረዱት ሁኔታ ከዚህ በታቸ የማቀርብላችሁ፡፡
ኢቲቪ እንደ መግቢያ በመጀመሪያ ያቀረበው ጥያቄ “ብሄራዊ ጥቅም ማለት ከኢትዮጵያ አንፃር መገለጫዎቹ ምንድናቸው?” የሚል ነው፡፡ የዚህ ጥያቄ ዓላማ በመጨረሻ ላይ ከሚቀርቡት ጥያቄዎች አንፃር ስታዩት የግል ሚዲያዎቹ እነዚህን ብሔራዊ ጥቅሞች እየተጋፉ ነው የሚል መደምደሚያ ለመስጠት እንዲመቸው ያቀረበው ነው፡፡ በእኔ እምነት በቅርቡ እየሰፋ የመጣውን ሀገር ማለት? የሚለው  ተጠየቅ መሬት ሲደመር ሰው (አንድ እና አንድ ሁለት እንደሚባለው) ማለት አይደለም፡፡ ለምሣሌ የዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ሀገር ማለት የእኔ ልጅን ልብ ይሏል፡፡ የመለስ ዜናውንም ሀገር ማለት ህዝብ ነውም የሚረሳ አይደለም፡፡ የዶክተር ሀይሉ ኃርሃያን የሀገር ልክፍት ግጥምም ትዝ ይለኛል፡፡ የዚህን ጥያቄ መልስ እንደ እልም ፈቺ፤ ለእልም ፈቺ እንተውው እና በእኔ እምነት ብሔራዊ ጥቅም ወይም የሀገር ጥቅም ማለት በአጭሩ የዜጎች ጥቅም ብዬ ነው የማስበው፡፡ የሀገረ ኢትዮጵያ ጥቅም የሚባል ነገር ሁሉ የኢትዮጵያዊያን ጥቅም ማለት ነው ብዬ ነው የምረዳው፡፡ ኢትዮጵያዊያኖች እንዴት ነው የሚጠቀሙት ብለን ወደ ዝርዝር ሰንገባ ደግሞ በሠላም ወጥቶ መግባት/መኖር፤ የሰውነት መብት መከበር፤ የህግ የበላይነት መኖር፤ ወዘተ ሲሆኑ መንግሰት እነዚህን ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስችለው መዋቅር እንዲኖረው ማደረግ ደግሞ የህዝቡ ዋነኛ ኃላፊነት ይሆናል፡፡ አንድ አንድ ሰዎች ጥቅም የሚባለውን ነገር ከራሳቸው በላይ ዘለግ አድርገው ማየት ስለማይችሉ ለልጅ ልጆች ሀገርን እንደ ሀገር አስጠብቆ ማለፍ የእነርሱ ድርሻ አይመስላቸውም፡፡ ለዚህም ነው ድንበር ማስከበርም፣ ዛፍ መትከልም፣ ወንዝ ተራራውም እንዲጠበቅ ማድረግ የመሳሰሉት አብይ ጉዳዩች ባለቤት ያጣሉ፡፡ ንቁ ዜጎች ግን ይህን በፍፁም አይዘነጉትም፡፡ ዛፉ ጥላው አድጎ ባይጠቀሙበት እንኳን ችግኝ መትከል ሀገራዊ ሃላፊነታቸው እንደሆነ ይረዳሉ፡፡ ድንበር ማስከበርም እንዲሁ ለልጅ ልጆቻቸው የሚተላለፍ መሆኑን ስለሚገነዘቡ ሀገር ቆርሰው አይሰጡም፡፡ ለኢቲቪ ይህን መልስ ብሰጠው የት ሰፈር እንደሚቆርጠውና ከምን ጋር እንደሚቀጥለው መገመት አያሰቸግርም፡፡
የኢቲቪ ተከታዩ ጥያቄ “የግል ፕሬሶች የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅሞች በማሰጠበቅ ረገድ ምን ያህል እየሰሩ ነው?” የሚል ሲሆን ከመጀመሪያው ጥያቄ ጋር ያለው ዝምድና ፍንትው ብሎ ይታያችኋል፡፡ በግሌ ለዚህ ጥያቄ ያለኝ መልስ “አንድም የግል ፕሬስ” የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ ለአሜሪካ፣ ለአውሮፓ፣ ለሀረብ ወይም ለሌላ አካል አሳልፎ ይሰጣል የሚል እምንት ሊኖረኝ አይችልም፡፡ በሀገራችን እንዳለመታደል ሆኖ መንግሰት የሚባለው አካል ከላይ የዘረዘርኳቸውን የህዝብ ጥቅሞች ማስጠበቅ ሲያቅተው እና ይህን ችግሩን በሌላ ማለከክ ሲፈልግ የግል ሚዲያዎቹ ቅርብ ሆኖ ያገኛቸዋል፡፡ ስለ መንግሰት በጎ በጎውን መዘመር እንጂ የመንግሰትን ኃላፊነት ያለመወጣት እና ደካማነት ሲነሳ “የሀገር/የህዝብ ጥቅም” ተነካ ብሎ ቡራ ከረዩ ማለት ይቀናዋል፡፡ እውነቱን ስንመለከተው ግን ጥቅም የተነካ ከሆነ ወይም ሊነካ ከሆነ የተነካው የሹሞች ጥቅም ነው፡፡ እርሱም እንደ ዜጋ ከሚያገኙት ሳይሆን በወንበር ተገን የሚዘርፉት ነው፡፡ የግል መልሴ ለኢቲቪ ይህ ነበር የሚሆነው፡፡

ሶሰተኛው ጥያቄ “የግል ፕሬሶቹ መሰረታዊ የሆኑ የግለሰብ መብቶቸን በሚጋፋ መልኩ እየሰሩ ይገኛሉ ይባላል፤ በዚህ ላይ እርሶ ይስማማሉ ወይ?” የሚል ነው፡፡ እነዚህ የግል ፕሬሶች ማሰረጃ የሌለው  ነገር አትመው የግል መብት ነክተው ከሆነ በማስረጃ ፍርድ ቤት ማቅርብ ይቻላል፡፡ የግለሰብ መብት የሚሉት ግን ሹመኞቹን እንደሆነ መረዳት አይከብድም፡፡ አንድ አንድ ሹመኞች የህዝብ ማስተዳደሪያ የሆኑትን የሹመት ቦታዎች ሲረከቡ አብሮ የሚመጣውን የግል መብትና ነፃነት ገደብ ይዘነጉታል፡፡ የመንግሰት ንብረት ሲያስተዳድሩ በትክክል ካልተጠቀሙ ሚዲያው ይህን ለልጆቻቸው ብሎ ዝም ብሎ ሊያልፋቸው አይችልም፡፡ ይህ በመንግሰት ሹመኞች ላይ ብቻ ሳይሆን የህዝብ ህውቅናን ያገኘ ማነኛውም አይነት ታወቂነት ደረጃ ላይ የሚገኝ አርቲስት፣ ባለሀብት፣ ሯጭ፣ ወዘተ ሊሆን ይቸላል፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን የግል ሚዲያዎች የግለሰቦችን መብቶች ሊጥሱ የሚችሉበት ምክንያት የለም፡፡ ማንነቱ ስለማይታወቅ ሰው ቢፅፉ ማንም ሊያነብላቸው አይችልም፡፡ ትርፉ ኪሳራ ነው የሚሆነው፡፡ በእርግጥ እነዚህን የግል መብቶች ከላይ እሰከታች የሚጣሱት ጡንቻና መዋቅር ባለው መንግሰት ነው፡፡ መንግሰት ደግሞ እነዚህን ድርጊቶች የሚፈፅመው ለህዝብ ጥቅም ስል ነው ይላል፡፡ እኛ ደግሞ በህዝብ ስም መብታችንን አትጣስ እያልን ለትግል የወጣነው በግል ሚዲያ ላይ ሳይሆን በመንግሰት ላይ ነው፡፡
አራተኛው ጥያቄ “አሁን በገበያ ላይ ያሉት የግል ፕሬሶች የጋዜጠኝነትን መሰረታዊ የስነ ምግባር መርሆዎችን ጠብቀው በመሰራት ረገድ ምን ዓይነት አዎንታዊና አሉታዊ አስተያየት አለዎት?” የሚል ነበር፡፡ ይህ በተደጋጋሚ ጋዜጠኛ ነኝ የሚሉት ሁሉ የሚያነሱት ነጥብ ሲሆን ሰምምነት ተደርሶበት ሁሉም ሊገዛለት ይገባል የተባለ የሰነ ምግባር መርሆ ግን በዓለም ላይ የለም፡፡ አብዛኞቹ የሚስማሙበት ግን ጋዜጣኛ መርዕ ማድረግ ያለበት ነገር ካለ “ተጠያቂነቱን ለህዝብ” ማድረግ ነው፡፡ ይህም ማለት የህዝቡን የመረጃ ፍላጎት ማርካት ነው፡፡ ከዚህ ተከትሎ የሚመጡ የመረጃ ትክክለኝነት፣ግብረገባዊነት፣የመሳሰሉት ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ይህን ጋዜጠኛው ማሟላት ካቃተው ደግሞ ተጠያቂነቱ ለህዝብ ይሁን ካልን ፍርድ ሰጪውም ህዝብ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ህዝብ ዓይንና ጆሮ ሲከለክላቸው ከገበያ ይወጣሉ፡፡ ብሎም ይጠፋሉ፡፡ በዚህ ጊዜ “አከፋፋዮች” ናቸው እንዲህ የሚያደረጉት የሚል ክስ ውሃ አይቋጥርም፡፡ በውጭ ሀይል ግፊት ነው የሚለውም ክስ የትም የሚያደርስ አይሆንም ማለት ነው፡፡

በመጨረሻ የቀረበው ጥያቄ “የፖለቲካ ፓርቲዎችና ፕሬስ አንዱ በሌላው ላይ ያላቸው አዎንታዊና አሉታዊ ተፅህዕኖ እንዴት ይታያል?” የሚል ነው፡፡ የዚህ ጥያቄ ዓላማ የግል ፕሬሶቹ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ልሣን ሆኑ የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ ነው፡፡ በእውነቱ ግን ሁልጊዜ ፕሬስ  “የWatch Dog - የህዝብን ጥቅም የመጠበቅ” ስራውን መዘንጋት የለበትም - ፓርቲዎች በየተራ ስልጣን የሚይዙ ስለሆነ የፕሬስ ይሁንታን ለማግኘት መጣጣራቸው አይቀርም፡፡ ተገቢም ነው፡፡ በእኛ ሀገር ገዢው ፓርቲ “የህዝብ/የመንግስት” የሚባሉትን ሚዲያዎች ጠቅልሎ የያዘና መረጃም የማይስጥ ስለሆነ፤ የግል ሚዲያዎች ደግሞ በመንግሰት በኩል የተነፈጉትን መረጃ ለማግኘት እና የገዢው ፓርቲ ተግባርም ትክክል እንዳልሆነ ለማሳየት በተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ቢወግኑ ክፋት የለው፡፡ ለነገሩ መንግስት መረጃ እየሰጣቸውም ቢሆን መንግሰት መደገፍ የማይፈልግ የግል ሚዲያ ማቋቋም ነውር የለውም፡፡ ነውር የሚሆነው በመንግሰት ሚዲያ ገዢውን ፓርቲ ብቻ ማገልገል ነው፡፡