Tuesday, March 31, 2020

“ኮቪድ 19” እና ምርጫ በኢትዮጵያ


ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ የወቅት የዓለም መነጋገሪያ የሆነው “ኮቪድ 19” በመባል የሚታወቀው ወረርሽኝ ነው፡፡ ዓለማችን እንደሆነች ለበሽታ ብርቅ የሆነች ይመስል፤ በሚዲያ ጡዘት የሞቀውን “ኮሮና ቫይረስ” በዓለም ላይ ፕሮግራም የተያዘላቸው ከፍተኛ ኩነቶች እንዳልነበሩ እያደረገ ይገኛል፡፡ በዓለማችን ከፍተኛ ኩነት ተብሎ በየአራት ዓመቱ የሚከወነው ኦሎምፒክ ጭምር መሰረዝ የሚያስችል ሀይል ያለው ወረርሽኝ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ኦሎምፒክ በዓለማችን ከሚደረጉ ትልቁ ምን አልባትም ውድ ከሆኑ ከንውኖች አንድኛው ነው፡፡ ጃፓንን የሚያክል የዓለማችን ባለ ትልቅ ኢኮኖሚ፤ ከዘጠኝ ዓመት በፊት የደረሰባትን የኢኮኖሚ ድቀት ለማካካስ መፍትሔ አደርጋ የተዘጋጀችበትን ኦሎምፒክ መሰረዙ አይቀሬ መሆኑ ተነግሯል፡፡ የኦሎምፒክ ችቦ አቀባበል ሥነ ሰርዓት ይህን ከማመላት የሚዘል አልነበረም፡፡ ብዙ አገሮች ምርጫ የሚባለውን “ፖለቲካ ካርኒቫል” በቀላሉ በአንድ አጭር መግለጫ፤ ያለ ብዙ ማብራሪያ እንዲዛወር አደርገዋል፡፡ ምንም ጫጫታ አልተሰማም፡፡ አንድ አንዶች ምንአልባት ከዚህ ፅሁፍ ይሆናል፤ አገራት ምርጫ ማራዘማቸውን የምትሰሙት፡፡ ምክንያቱም በኮሮና ዘመን ምርጫ መግፋት ትልቅ ክስተት አይደለም፡፡ ይህ ግን በምስኪኗ አገራችን ኢትዮጵያ እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡
ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መከበር አለበት፤ መገለጫውም በተቀመጠለት የጊዜ ሠሌዳ ምርጫ ተካሂዶ በምርጫ መንግሥት መመሰረት አለበት የሚሉ እና ምርጫ በምንም ሁኔታ መካሄድ የለበትም፤ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ፖለቲካዊ ሁኔታ በአገሪቱ የለም በሚሉ ፅንፎች መካከል ሲካሄድ የነበረው መጓተት አሁን ቢያንስ ማስቢያ ጊዜ የሚሰጥ ምክንያት ተገኝቷል፡፡ ይህም “ኮሮና ቫይረስ” የሚባል የመግደል አቅም ያለው ወረርሽኝ በዓለማችን ተከስቶ እኛም የዚሁ ክስተት ተጠቂዎች መሆናችን በመረጋገጡ ነው፡፡
በአገራቸን ኢትዮጵያ ምርጫ ሊገፋ የሚችልበት ሁኔታ ኮሮና መፍጠሩን ከበቂ በላይ ማሳያ ማቅብ ይቻላል፡፡ በዝናብ እንዴት አደርገን ቀስቅሰን ነው ምርጫ የምንወዳደረው? ሲሉ የነበሩ ተቃዋሚዎች፤ እንዴት አድርገው በኮሮና ዘመን ምርጫ መወዳደር እንደሚችሉ መንገድ ማገኘት ሰለማይችሉ ምርጫው መራዘሙ አይቀሬ ነው፡፡ ቀደም ምርጫው ይራዘም በክርምት አይሆንም ስለ ነበር ምክንያቱ አሁን ምርጫው ከክረምት በኋላ እንደሚሆን ለማወቅ ነብይ መሆን አይጠይቅም፡፡ ኦሎምፒክን የሚያክል ትልቅ ዓለም አቀፍ ክንውን፤ የጃፓን የኢኮኖሚ ማንሰራሪያን እድል ተደርጎ በእቅድ ሲከወን የነበረን ጉዳይ የገፋ ኮረኖ ቫይረስ፤ ምንአልባት ለብጥብጥ መነሻ ሰበብ ለመሆን የተዘጋጀን የኢትዮጵያን አገር አቀፍ ምርጫ ቢገፋው ለምን ይገረመናል?
የኢትዮጵያ ምርጫ “በኮቬድ 19” ምክንያት መራዘሙ የግድ የሚሆንባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች፤
ምርጫችን በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ድጋፍ ጥገኛ መሆን፤
ቀደም የነበረው ምርጫ ቦርድ ላለፉት 25 ዓመታት አምስት ተከታታይ ምርጫዎችን ያካሄደ ሲሆኑ፤ ልምዱ ተቀምሮ ወደ ቀጣይ ለማሻገር በሚሆን መልኩ የተደራጀ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ለአዲሱ ምርጫ ቦርድ አቅም ሳይሆን መጥፎ ሰም አስቀምጦለት መቆየቱ የጎለ ነበር፡፡ በዚህ መነሻ አደረጃጀት ይሁን አሰራር፤ በአጠቃላይ ከሕግ ማዕቀፍ እስከ ዝርዝር ተግባራት መከለስ የግድ የሚል ነበር፡፡ በአገር አቀፍ የሚቀመር ልምድ ያለማዳበራችን ደግሞ ከውጭ እንድናማትር የግድ የሚለን ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ሰለዚህ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከነበረበት የአቅም ልምሻ ተላቆ፤ አገራዊ ተልዕኮዎን በብቃት ይወጣ ዘንድ በዓለም አሉ የተባሉ የምርጫ ኤክስፐርቶችን በማሳተፍ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ እነዚህም ኤክስፐርቶች በዚህች ደሃ አገር በጀት ሊከፈላቸው የሚችል ባለመሆኑ ከውጭ አገራት ከፍተኛ የበጀት ድጋፍ እየተገኘ ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም ለምርጫ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ግዢ እና ዕትመት ጭምር ከውጭ የሚከወን መሆኑን ሰምተናል፡፡ ዓለም በኮሮና ቫይረስ በሮቿን ጥርቅም አደርጋ በዘጋችበት ወቅት ኢትዮጵያ ለምትባላ አገር ከፍታ ይህን የምትከውንበት አንድም ምድራዊ ምክንያት አይታየኝም፡፡ ብዙዎቹ የውጭ ባለሞያዎች ለድጋፍ ወደ አገራችን የመጡ ቢሆንም የተለያዩ ድጋፎችን ደግሞ ከውጭ ከመጡበት እናት መስሪያ ቤት እንደሚያገኙ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ሰራተኞች በሙሉ ከቤታቸው እንዳይወጡ በተደረገበት፤ ከውጭ የመጡትም ቢሆኑ ወደ አገራችው እንዲመለሱ እየተመከሩ ባለበት ሁኔታ በተረጋጋ መንፈስ ምርጫ ማዘጋጀት የሚቻልበት ሁኔታ የለም፡፡ ሰለዚህ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለው የኮሮና ቫይረስ ሰርጭት ሁኔታ መስመር ሳይዝ የተረጋጋ የውጭ ድጋፍ ማግኘት ሰለማይቻል፡፡ በውጭ ድጋፍ ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ምርጫ መራዘሙ የግድ የሚል ይመስለኛል፡፡
በአገር ውስጥ ለምርጫ የተዘጋጁ ፓርቲዎች ለምርጫ ሥራ የሚያስችል ሁኔታ አለመኖሩ፤
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ፓርቲ የሚጠበቅባቸውን ተግባር እየከወኑ ነው የቆዩት ብሎ በድፍረት መናገር አይቻለም፡፡ ይልቁንም ምርጫ እንዴት በሰበብ አስባብ ላለመሳተፍ “የእናቴ ቀሚስ” የሚል ሰበብ ሲፈልጉ ነበር ቢባል ስህተት አይሆን፡፡ ለማንኛውም ግን ለምርጫ የተዘጋጁ ፓርቲዎች የሚከውኑዋቸው የተለያዩ ተግባራት ያሉ ሲሆን በዋነኝነት ለውድድር በሚዘጋጁበት ምርጫ ክልሎች ቢሮ መክፈት፣ አባላትን ማደራጀት፣ ዕጩዎችን መመልመል፣ መራጮችን መቀስቀስ ማስተማር፣ ወዘተ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ ኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል ሲባል በሚጣሉ ገደቦች ጫና ይደርስባቸዋል፡፡
በምርጫ ክልል ቢሮ መክፈት፤
ሁሉም እንደሚረዳው በምርጫ ክልል ፓርቲዎች በዘላቂነት ቢሮ የሚከፍቱበት ሁኔታ የለም፡፡ ፓርቲዎች አቅም ቢኖራቸው ይህ ቢሆን ክፋት የለውም፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ፓርቲዎች በየምርጫ ክልሉ የምርጫ ዘመቻውን ለመምራት የሚያስችል ቢሮ መክፈት ብቻ ነው የሚፈልጉት፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው፡፡ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ምርጫው በትክክል የማይታወቅ ከሆነ ፓርቲዎች ለተራዘመ አላስፈላጊ ወጪ የሚዳረጉ ሰለሚሆን የምርጫ ቢሮ መክፈት ይቸገራሉ፡፡ ሰለዚህ ምርጫው ሠሌዳ ላይ የሚደረግ ለውጥ በውል ታውቆ ወደ እንቅስቃሴ መግባት ይቸገራሉ፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ፓርቲዎች ሥራቸውን መስራት ይቸገራሉ ማለት ነው፡፡
በምርጫ ክልል አባላት አባላት ማደራጀት፤
ፓርቲዎች በተለይ ሁኔታ የምርጫ ወቅትን ተከትለው አባላትን በስፋት ያደራጃሉ፡፡ ኮሮና ቫይረስ ማንኛውንም የሕዝባዊ ስብሰባዎች ማካሄድ የማያስችል ከመሆኑ አንፃር ፓርቲዎች ይህን ተግባር ከባድ ያደርግባቸዋል፡፡ በቂ አባላትን መመልመል ያልቻ ፓርቲ ደግሞ፤ በምርጫው ዕለት በቂ ታዛቢዎችን ማቅረብ የማይችል ሲሆን በምርጫው ቅስቀሳ ወቅትም በቂ ፈቃደኛ የቤት ለቤት ቀስቃሾችን ማሰማራት አሰቸጋሪ ይሆናል፡፡ ሰለዚህ ይህ ባልተደረገበት ሁኔታ ምርጫ ማድረግ ትርጉም የሚኖረው ፖለቲካዊ ተግባራ ሊሆን አይችልም፡፡
ዕጮዎችን መመልመል፤
ፓርቲዎችን ወክለው የሚወዳደሩ ዕጩዎች መለየት በዚህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ከባድ ይሆናል፡፡ ዕጩዎች ሊያድርጉት የሚፈልጉት የምርጫ ቅስቀሳ ብዥታ ውስጥ ባለበት ሁኔታ ዕጩ የመሆን ፍላጎታቸው ይደበዝዛል፡፡ በዚህ ሁኔታ በቂ ዕጩ ቢገኝ እንኳን በበቂ ሁኔታ ተነቃቅቶ የሚያነቃቃ ሳይሆን “የግብር ይውጣ” ሊሆን የሚችልበት እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ምርጫ ባልተነቃቃ የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩ እየተመራ ሲከወን ሰሜት አይሰጥም፡፡
መራጮችን መቀስቀስና ማስተማር ያለመቻል፤
መራጮችን መቀስቀስ ማስተማር በማይቻልበት ሁኔታ ምርጫ የሚባለው ነገር ሊኖር አይደለም ሊታሰብ አይችልም፡፡ በቂ አማራጭ ቀርቦ ካልመረጡ ምርጫ ቀልድ ይሆናል፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታዎችን ኮሮና ቫይረስ የማይቻል አድርጎታል፡፡ መራጮች ሰለ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያየ ሁኔታ መስማት ይችላሉ የሚል ታሳቢ ቢወሰድ እንኳን፤ መራጮች ወጥተው ለመምረጥ ፍላጎት በሚያጡበት የምርጫ ድባብ ውስጥ ምርጫ ትርጉም ማጣቱ አይቀሬ ነው፡፡
በአጠቃላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች “በኮቬድ 19” ድባብ ውስጥ ሆነው ምርጫ መወዳደር አይችሉም፡፡ ምርጫ ቦርድም ቢሆን በዚህ ድባብ ውስጥ ሆኖ ምርጫ ለማወዳደር የሚችልበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ ሰለዚህ ምርጫው “በኮቬድ 19” አስገዳጅነት ይራዘም እንላለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ “ኮቬድ 19” የገፋውን ምርጫ ሰሌዳ እንደ አንድ እድል መጠቀም የሚችሉ፤ በዝግጅት ክፍተት የነበረባቸው ፓርቲዎች እንዳሉ ከግምት ማስገባት ይቻላል፡፡ እንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ወደ እድል የሚቀይሩ ግን ጥቂቶች ለዚህ ተሰጥኦ ያላቸው ብቻ ናቸው፡፡ በዚህ መስመር የሚገኝ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲ ከተገኝ እሰየው የሚያስብል ነው፡፡ አሰቂኝ ነገር የሚሆነው ግን ኮሮና ቫይረስ ያስቆመውን/ያገተውን ምርጫ ሠሌዳ ለሌላ የግል ርካሽ ፖለቲካ መጠቀም መፈለግ መኖሩ እንደማይቀር ስንገምት ነው፡፡
በግሌ ምርጫ መካሄድ አለበት ብዬ የማምን ቢሆንም፤ ማንም ይህን ምርጫ የሚራዘምበት አሳማታዊ ምክንያት ካመጣ ቢራዘም ግድ የሌለኝ መሆኑን ደጋግሜ ገልጫለሁ፡፡ ምርጫ ከተራዘመ አይቀር ግን በሚኖረን ጊዜ ኮኖና-ኮሮና ስንል ከርመን ወደነበርንበት ንትርክ ለመመለስ ሳይሆን፤ ቀጣዩ ምርጫ የእውነተኛ ዴሞክራሲ ማዋለጅ እንዲሆን ተጨማሪ ጊዜ ወስደን በጎ ስራ የምንሰራበት እንዲሆን ምኞቴ ነው፡፡
ይህን በጎ ሥራ ለመስራት ምክክር የሚጠይቅ ሲሆን፤ ምክክሩ አንዱ አንዱን በዝረራ አሸንፎ ለቀረርቶ የሚወጣበት ሳይሆን፤ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት እንዲሆን ማድረግ የሚፈልግ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል አገራችንን እንወዳልን የምንል ከሆነ ለበጎ ስራ ማዋል ያለብንን ጊዜ፤ በተቃራኒው “የቱኒዚያ እና የሱዳን ዓይነት ምስቅልቅል ተፈጥሮ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም የሚያስችል ሁኔታ የሚፈጥር ሕዝባዊ ንቅናቄ በተቀናጀ ሁኔታ ሊያስተባብርና በመንግሥት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችል የተጽዕኖ ፈጣሪ ዜጐች ስብስብ መድረክ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአስቸኳይ መቋቋም አለበት” ብሎ የአመፅ ጥሪ ማቅረብ ከእብደት የሚለይ ጥሪ ሊሆን አይችልም፡፡
እጃችንን በሣሙና መታጠብ አንዘንጋ!!
ቸር ይግጠመን!!