Monday, June 27, 2016

ለዲሞክራሲ ስርዓት ምን ዓይነት ፓርቲ ያስፈልገናል?



በሀገራችን የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበራት እንዲሁም የሚዲያ ተሳትፎ አጅግ ወሳኝ እንደሆነ ሁሉም ይረዳዋል ማለት ባይቻልም በተለይ የፖለቲካ ፓርቲ አባል አመራር የሆኑ ሰዎች ይጠፋቸዋል ብሎ የሚገምት ላይኖር ይችላል፡፡ እውነቱ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ሰዎች የሚሳተፉት በዋነኝነት በሀገራቸን የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያላቸውን መዋጮ በማስላት ሳይሆን ገዢውን ፓርቲ በማስወገድ ላይ ብቻ ያጣነጠነ ይመስላል፡፡ ይህንንም ማድረግ የሚፈልጉት ደግሞ በትርፍ ጊዚያቸው ከስራ መልስ ወይም በጡረታ ጊዚያቸው ነው፡፡ ይህን ሲያደርጉ ደግሞ የብዙ ወጣቶች ጊዜና ጉልበት መስመር ባልያዘ አቅጣጫ እንደሚመሩ አይረዱም፡፡ ለነገሩ የወጣቶችን ጊዜ በማባከን እና የወጣቶችን ፍሬያማ ጊዜ በከንቱ በማባከን ገዢውን ፓርቲ የሚወዳደር የለም፡፡ በሰራ እናገኛለን ተሰፋ እና እራሳቸውን ከደህንነት ስጋት ለመጠበቅ ገዢውን ፓርቲ በምሽግነት ስለሚጠቀሙበት፡፡ ይህም ቢሆን ገዢው ፓርቲ ይህን ስለሚያደርግ ተቃዋሚዎች የወጣቶችን ጊዜ ያለአግባብ ማባከን አለብን የሚል ክርክር ሊገጥሙ አይገባም፡፡
በእኔ እምነት የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሲኮን በተለይም አመራር ሲኮን በቀጣይ የመንግሰትን ስልጣን ለመያዝ መዘጋጀትን ይጠይቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዚህ ልክ እራሳቸውን ያዘጋጁ የገዢው ፓርቲም ሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ ከሰበሰባቸው ሰባት ሚሊዮን አባላት ምርጥ ብሎ አውጥቶ አመራሩን መቀየር ባለመቻሉ ያሉትን የጡረታ ጊዜ እያራዘሙ 25 ዓመት ሞልቶታል፡፡ አሁንም ቢሆን በገዢው ፓርቲም ሰፈር ከፊት መጥተው ተሰፋ የሚደረግባቸው አይታዩም፡፡
በተቃዋሚ ጎራ ይህን ወሳኝ የፖለቲካ አመራር እና የመንግሰት ስልጣን ቁርኝትን ባለመረዳት ፓርቲ የመሰረቱ እና ለመመስረት የሚራወጡ ሰዎች ግባቸው እንደ ከዚህ ቀደሙ የጡረታ ወይም ደግሞ ከሰራ መልስ ጊዜ ማሳለፊያ ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ከዚህ በፊት ይህን ለማሳካት አንድነት ፓርቲ ያዘጋጀውን ስትራቴክ ሰነድ መሰረት አድርጎ የመድረክ አመራሮችን “ሻዶ ካቢኔ” እናቋቁም ብሎ ጥያቄ ሲያቀርብ በግልፅ ለፖለቲካ ስልጣን የምናደርገውን ትግል በድብቅ ማድረግ የለብንም የሚለውን የአንድነትን ግልፅ አቋም በድብቅ በውስጣቸው ባለ ሰውር የስልጣን ጥም (ማን የካቢነዊ መሪ ይሆናል?) ሳይቀበሉት እና ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በዚህም መነሻ አንድነት ያቀረበውን የስትራቲጂክ ፕላን ሰነድ ሳይቀበሉት ቀሩ፣ቀጥሎም አንድነትን ገፍትረው አስወጡት፡፡ ለነጉሩ አንድነትም በዚህ ትብትብ ውስጥ ድንክ ሆኖ አይቆይም ነበር፡፡
አሁን ደግሞ በድጋሚ ማሳካት የሚፈልገው ዓላማ ምን እንደሆነ የማይታውቅ ከአንድነት ፓርቲ ፍርስራሽ “ነፃነት” የሚባል ፓርቲ መመስረቱን ሰምተናል፡፡ ለምስረታው ከፍተኛውን ሚና ሲጫወት የነበረው አቶ ብሩ ቢርመጂ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይም የፓርቲው መሪ ሆኖ የተመረጠው ዶክተር ንጋት በእርግጥም የጃንሜዳ ልጅ ቢሆንም በሰሜን ሸዋነቱ በቀጣይ መድረክ ውስጥ ለሚታየው የአማራ ፓርቲ ክፍተት ማሟየ እንደሚሆን ግልፅ ነው፡፡
አንድነትን ገፍትሮ ያስወጣው የፕሮፌሰር በየነ አና የዶክተር መረራ መድረክ አሁን ለነፃነት ፓርቲ ምስረታ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የሚያሳየን ኢትዮጵያ የፓርቲዎች እጥረት ስለአለባት የዜጎችን የመደራጀት ዲሞክራሲያዊ መብት ለመደገፍ ካላቸው ቀና አመለካካት ሳይሆን መድረክ የኢህአዴግ “ፎርጅድ ኮፒነቱን” ለማሳካት የጎደለውን የአማራ ፓርቲ ለመሙላት ብቻ ነው፡፡ መድረክ በትግራይ ዓረና ለህውሃት፣ በኦሮሚያ ኦፌኮ ለኦህዴ፣ በደቡብ የፕሮፌሰር በየነ ፓርቲዎች እና የሲዳማው ድርጅት ለደህዲን የተዘጋጁ ሲሆን ለብአዴን ግን የአቻ ፓርቲ ችግር ነበረበት፡፡ ከዚህ በፊት አንድነትን በውስጠ ታዋቂነትም ሲከፋም በይፋ የአማራ ፓርቲ አድርገው ይፈርጁ ሰለነበር ከአንድነት መውጣት በኋላ ይህ ክፍተት “ፎርጅድ ኮፒ” ለመሆን እንኳን አላሰቻላቸውም፡፡ አሁን ግን የነፃነት ፓርቲ መምጣት ከመኢህአድም ሆነ ከሰማያዊ ጋር ያላቸውን ስር የሰደደ ጥላቻ አስወግደው ከመሻረክ ይህን የአንድነት ፍራሽ በማሰገባት ድሮ አንድነት ሊውጠን ነው ከሚለው ስጋታቸው ወጥተው እኩያቸው የሆነ ፓርቲ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል፡፡ ነፃነት ቢሮ የሌለው ማህተምና ፋይል በሰዎች መኖሪያ ቤት የሚገኝ፣ ይህ ነው የሚባል ድርጅታዊ ጥንካሬ የሌለው ፓርቲ ሰለሆነ ለመድረክ አባል ድርጅቶች የእኩዮች ጥምረት ይሆናል፡፡ “የፎርጅድ ኮፒ” ፕሮጀክት ክፍተትም ይሞላል፡፡ እንደሚታወቀው የፓርቲዎች ውህደት እኩል ሳይሆኑ በእኩልነት መንፈስ ይባላል፡፡
ለማነኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ እውነተኛ የዲሞክራሲ ስርዓት እንዲኖር ይፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ የሚሆነው አውነትኛ የድርጅት አቅም ያላቸው አማራጭ የሚሆኑ፤ ህዝቡ ቢመርጣቸው የመንግሰት ሃላፊነት ተረክበው ሊያስተዳድሩት የሚችሉ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይፈልጋል፡፡ በግሌ አንድ ፓርቲ መንግሰት ብሆን የካቢኔ አባሎቼ እነ እገሌ ናቸው ብሎ ብቃት ያላቸው 30 ሰዎች የሚያሳየኝ ካለ አባል ለመሆን ዝግጁ ነኝ፡፡ አንድነት ውስጥ ይህን ማደረግ ስለሚቻል ነበር ለፖለቲካ ስልጣን የምንሰራው፣ ይህ በገዢው ፓርቲ አልተወደደም፡፡ በገዢው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚ ነን በሚሉት ጭምር (ሰማያዊና መድረክን ጨምሮ) በተለይ ሰማያዊ በአንድነት ፍራሽ የሚጠነክር መስሎት ስለነበር፡፡ ነገሩ ግን የተገላቢጦሸ ነው የሆነው፡፡
አሁንም በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ስርዓት እንዲኖር ካስፈለገ፤ የሚፈጠረው ፓርቲ እንደ ኢህአዴግ አመራር የማይወጣው 7 ሚሊዮን አባል በመስብሰብ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጥሩ አባላትን በማብዛት ሳይሆን ምርጦች የሚሰበሰቡበት፣ ለጥቅም ሳይሆን “ለአቅመ መስጠት” የደረሱ፤በአውቀታቸው እና ከራሳቸውና ከቤተሰባቸው አልፈው ለዜጎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ፍትህ የሚጨነቁ ብቻ ሳይሆን አማራጭ መፍትፈሔ የሚያቀርቡ፣ በየደረጃው ለፖለቲካ አመራር የሚሰባሰቡበት መሆን ይኖርበታል፡፡ ሰለዚህ መስጠት የማይችሉ ለአቅመ መስጠት እስኪበቁ በደጋፊነት መቆየት ይኖርባቸዋል፡፡ መረዳት ያለባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባልም ሳይሆኑ በዲሞክራሲ ስርዓት ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ በዚህ የሚጠቀሙት የኢህአዴግ አባለት ጭምር ስለሚሆኑ፡፡
በተመሳሳይ ጠንካራ ሚዲያ እና ሲቪል ተቋማት መኖር አለባቸው፡፡ አርዳታ ለማሰጠት እና ለራሳቸው የስራ እድል ለመፍጠር የተደራጁ ሲቪል ማኅበራት፣ በዕትመት ለመቆየት ለዘብተኛ የሆኑ ሚዲያዎች ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ፋይዳ የላቸውም፡፡ ይፍረሱ!!!!!

Monday, June 6, 2016

መድረክ ንጉሣዊ ነው እንዴ?



ለመድረክ ቅርብ የሆነ አንድ ወዳጄ የመድረክን የእሁድ ግንቦት 28/2008 ጉባዔን አስመልክቶ የነገረኝ ነገር መድረክ ንጉሣዊ ነው እንዴ? የሚል ጥያቄ እንዳነሳ አድርጎኛል፡፡ መቼም በመድረክ ስም ፓርላማ ስለነበርኩ ለመድረክ ቅርብ የምመሰላቸው ካሉ ተሳስተዋል፡፡ የመድረክ ስብሰባ እንደሚታወቀው ውሣኔ የሚሰጠው የጉባዔ አባላት ተሰብሰበው በውይየት አቋም ይዘው በነፃነት በሚሰጥ ድምፅ አይደለም፡፡ አባል ድርጅቶች አድማ መተው የሚመጡበት ነው፡፡ ሌላው በመድረክ ውስጥ ኃላፊነት የሚያዘው በአባል ድርጅቶች በዙር ነው፡፡ ከአባል ድርጅቶቹ ደግሞ የሚልኩትን መሪ ቀይረው የማያውቁት ደግሞ ፕሮፌስር በየነ እና ዶክተር መረራ ናቸው፡፡ አሁን ባለኝ መረጃ መሰረት መድረክን የመምራት ተራው የሀረና ነበር፡፡ ይህ ማለት ግን የስብሳቢነት ቦታው ለሀረና እንዲሲጠው ሀረና ለቦታ የሚያቀርበው ዕጩ ወሳኝነት አለው፡፡ ሰለዚህም ሀረና ያቀረበው ዕጩ ለመድረክ ሊቀመንበርነት አይደለም፣ ለምክትልም አይሆንም በሚል ቦታው በቃኝ ለማያውቁት ለፕሮፌሰር በየነ አንዲሰጥ ተደርጎ ዶክተር መረራም ምክትል ሆነው ቀጥለዋል፡፡
አቶ አስፋ ጫቦ በቅርቡ ባሳተመው መፅኃፍ ውስጥ የሸዋ ንግስና ከተመለሰ የእኛም መመለስ አለበት የሚል ስላቅ አቅርቦ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር በየነም ቤተሰቦቻቸው በአካባቢው እንዲህ ዓይነት የንግሰና ጥያቄ ከመጠ ከሚጠይቁት ወገን ናቸው ስለሚባል፤ ይህ እስኪመጣ ድረስ መድረክን የንግስና መለማመጃ ያደረጉት መስለኝ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ብዙ ሙከራ አድርገው ያልተሳካላቸውን የአመራር ቦታ ቢቻል ፖለቲካውን ጭምር መተው ለምን ተቸገሩ?
ከወዳጄ ጋር ሰለምርጫው ስናወራ የፕሮፌሰሩ በተደጋጋሚ ከሚቀርብባቸው ከተቃዋሚ መሪነት እራሳቸውን ያግልሉ ጥያቄ ችላ ማለት ብቻ ሳይሆን ሃያም ሆነ ሰላሣ ሰዎች ድምፅ ሰጥተዋቸው በሃላፊነት የሚቆይቱ ባለፈው የሃላፊነት ዘመናቸው ምን ሰርተው ነው? የሚል ጥያቄ ለምን አያነሱም ነው፡፡ በፕሮፌሰር በየነ አመራር ወቅት መድረክ ምን ውጤት አስገኝቶ ያን ውጤት ለማስቀጠል ሲባል ነው የተሰጠው ሊባል የሚችል ውጤት አልታየም፡፡ በኦሮሚያ ለነበረው ህዝባው ንቅናቄ እንኳን በቂ ድጋፍ መስጠት ያልቻለ ስብሰብ እንደሆነ በስብሰባው ወቅት ጥያቄ ተነስቶበታል፡፡
የተነሳው ጥያቄም “በኦሮሚያ ለነበረው እንቅስቃሴ ኦፌኩ ብቻውን ለምን ተንቀሳቀሰ?” በሚል ነበር፡፡ መልሱ ግን የበለጠ አስደማሚ ነበር፡፡  “ኦሮሞዎች የተለየ ጉዳይ ስለነበረን ነው” የሚል እንደምታ ያለው መልስ ተሰጥቷል፡፡ አስገራሚው ነገር በአንድ ወቅት ሀብታሙ አያሌው  “ሰለ ኦሮሞ ችግር ለመናገር ኦሮሞ መሆን አያስፈልግም ሰው መሆን ይበቃል” ብሎ በሰጠው አስተያየት መድረክ አጀንዳ አድርጎት ኦሮሞ ያልሆነ የኦሮሞ ችግር አይገባውም የሚል መልስ ተሰጥቶ አንድነት እና ሀረና ታዲያ እዚህ ምን እንሰራለን? በሚል ስብሰባው ተቀውጦ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ አሁንም መድረኮች አብረን ነን ይበሉ እንጁ የትግሬው ችግር የሀረና፣ የኦሮሞ ችግር የኦፌኮ አድርገው በመያዝ ዳር ይዘው ተቀምጠዋል፡፡ በነገራችን ላይ መድረኮች አንድነትን ካስወጡ በኋላ የአማራ ተወካይ የሚያደርጉት ወይም የሚመስልላቸው ሳያገኙ እስከ አሁን አሉ፡፡ በቅርቡ የተመሰረተው የአንድነት ሽራፊ “ነፃነት” የሚባለው ፓርቲ ይህን ቀዳዳ ለመሙላት ተሰፋ ሳያደርጉ አይቀሩም፡፡ ወይም “ሰመያዊ” ፓርቲ ዓይኑ በጨው ታጥቦ ሊቀላቀላቸው ይችላል፡፡ የመድረክ አመራሮች ይህ ያለባቸውን የአማራ ወኪል ክፍተት በመሙላት “ፎርጂድ” የኢህአዴግ ኮፒ አደረጃጀት እንዲሳካ መጣራቸው የማይቀር ነው፡፡ ለህወሃት-ሀረና፣ ለኦህዴድ-ኦፌኮ፣ ለደህዴን-የበየነ ፓርቲዎች፣ ለብአዴን- ? ? ? ? - ፡፡ ክፍቱን ቦታ ለመሙላት እንግዲ ነፃነትና ሰማያዊ እድሉ አላቸው፡፡
የሀረና ልጆች በመድረኮች ፊት ዓይን የማይሞሉ ሆነው የተገኙት በመተካካት ፖሊሲ የቀድሞውን መሪ አቶ ገብሩ አስራትን ለዕጩነት ባለማቅረባቸው ነው፡፡ አስገራሚው ነገር በመድረክ አንፃር የተሻለ የውጭ ደጋፊ ያለው ሀረና ለክፉም ለደጉ በሚል የፋይናንስ ኮሚቴ ሃላፊነት እንደተሰጠው ተሰምቷል፡፡ በእርግጥ ዶክተር መረራም ከውጭ ድጋፍ ያለው ቢሆንም ድጋፉን በግል ከፈለገ ለኦፌኮ ካልሆነ ለመድረክ የማድረግ ፍላጎት የለውም፡፡ ለማነኛውም ፕሮፌሰሩ ሲመሩት ከነበሯቸው ድርጅቶች የተወሰኑትን “ምርጫ ቦርድ” ተብዬው ቢሰርዘውም በንግሰና በሚመስል መልኩ የመድረክን ሃላፊነት አለቅ ብለው ቀጥለው፡፡ ወይም ደግሞ አባላቱ በግድ ጭነውባቸዋል፡፡ በዚህ የሃላፊነት ዘመናቸው መቼም በቀጣይ ሊያድርጉት ያሰቡትን መርዓ ግብር በሆነ መልኩ ይፋ ያድርጋሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ በእኔ ግምት የመድረክ ሰዎች ይህን ኃለፊነት ይዘው መቆየት የፈለጉት በአንድ አጋጣሚ ኢህአዴግ ሸብረክ ቢል አለን!!! ለማለት ካልሆነ በስተቀር በተጠና ሰትራቴጂ ትግሉን መርተው መንግሰት ለመሆን አይደለም፡፡ እራሱን ለመንግሰትነት ያላዘጋጀ ፓርቲ/ሰብሰብ፣ ህዝቡን ለማድራጀት የማይተጋ ስብስብ ፋይዳው አይታየኝም፡፡
ሀገራዊ ሰብስብ ነኝ የሚል መድረክ ጠቅላላ ጉባዔ ሲያካሂድ በማህበራዊ ድረ ገጽ እንኳን የውይይት አጀንዳ አለመሆኑ አሳዝኖች ይህችን አካፈልኳቹ፤ እናንተስ ምን ታዘባችሁ፡፡ ከመድረክ ስብሰባ ተካፋዮች ዝርዝር እንጠብቃለን ….. ዘላለማዊ ስልጣን ….