Friday, September 25, 2015

የኢህአዴግ መንታ መንገድ




ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com
ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ በእሁድ መስከረም 2/2008 ሪፖርተር ላይ የወጣው የኢህአዴግ የግንባርነት ጉዞና ቀጣይ ፈተናዎች በሚል የቀረበው ፅሁፍ ነው፡፡ ይህ ፅሁፍ ጠቅለል አድርጎ በሰንጠረዥ ያሰፈረው መረጃ ስለ ግንባሩ አባል ድርጅቶች አቻ ያለመሆን ብዙ የሚያስረዳ ሲሆን ለይሰሙላ በምክር ቤት የሚታየው መለያየት በዋና ዋና ወሳኝ ቦታዎች ላይ በእኩልነት ፍልስፍና እኩል ድምፅና እኩል ውሳኔ ሰጪ ወደ መሆን ቀይሮታል፡፡ ዛሬ ማንሳት የምፈልገው በእኔ እይታ በቀጣይ ግንባሩ ያለበት ፈተና በወሳኝ መልኩ ምን እንደሆነ የግል ምልከታዬን ማቅረብ እና በመጨረሻም ተቃዋሚዎች በዚህ መንታ መንገድ ላይ ሚናቸው ምንድነው? የሚለው ነው፡፡
ኢህአዴግ ይህችን ሀገር ሊገዛበት የሚችለው አደረጃጀት መስርቶ ላለፉት ሃያ አራት ዓመታት በስልጣን ላይ እንደቆየ ይታወቃል፡፡ ግንባሩን ከመሰረቱት ድርጅቶች በተጨማሪ ደግሞ በግንባሩ ሳንባ የሚተነፍሱ “አጋር” የሚባል ታርጋ የተለጠፈላቸው መኖራቸው ደግሞ እሙን ነው፡፡ ለማነኛውም ግን የግንባሩ አባል ድርጅቶች እና የአጋር ድርጅቶች ጥምረት ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ባይታወቅም፣ ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት በኋላ ደፍሮ ይህን ግንባር አፈርሶ ወይም አሳድጎ ወደ ውህድ ህብረ ብሔር ፓርቲ የሚያደርስ አቅም ያለው ቡድንም ሆነ ግለሰብ ማየት እየተቸገርን ነው፡፡ ይህ ግንባሩን መንታ መንገድ ላይ ሀገራችንንም ሰጋት ላይ የሚጥል ነው፡፡
በአብዛኛው በግንባሩ አባል ድርጅቶችም ሆነ በአጋር ድርጅቶች ውስጥ በአመራርነት ቦታ የያዙት ሰዎች በምንም መመዘኛ ሀገር ለመምራርት የሚያስችል የግል ብቃትና ስብዕና ያስመዘገቡ አይደለሙ፡፡ ይልቁንም አሁን የያዙትን ቦታ ያገኙት በተደራጁበት የብሔር/የጎሣ መዋቅር ወኪል በመሆን ነው፡፡ ግንባሩ ህብረ ብሔራዊ ፓርቲ ወይም ንቅናቄ ቢሆን ብቃት ዋነኛው መመዘኛ ሆኖ ሌሎች ተዋፅኦ የሚመለከቱ ጉዳዮች ተከታይ መስፈርት ስለሚሆኑ ብዙ ጥገኞች ይራገፋሉ፡፡
ቀጠዩ አምስት ዓመት ኢህአዴጎች ተቃዋሚው እንዳያንሰራራ አድርገው ህዝቡም ይህን በፀጋ ተቀብሎ የሚጠናቀቅ ከሆነ፣ የኢህአዴግ ተግዳሮት የሚጀምረው ሌላ ምርጫ ሲደረግ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ይሁን? የሚለው ነው፡፡ በእርግጠኝነት ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ከአጋር ድርጅቶች ለማግኘት የሚቻልበት እድል በፍፁም በግንባሩ መስመር ዝግ ነው፡፡ የግንባሩ እና የአጋሮች ግንኙነት ይህን አይፈቅድም፡፡ ይህች ሀገር ነች እንግዲህ ዜጎች እኩል ናቸው የሚባልባት፡፡ አፋር፣ ሶማሌ፣ አደሬ፣ ቤኒሻንጉል፣ ጋምቤላ፣ ወዘተ ሆኖ የጠቅቀላይ ሚኒትርነት ቦታ የሚያዝበት ስርዓት የለም፡፡ ግንባሩ ለአጋሮች መች የክልል ስልጣን አነሳቸው የሚል ትምክት ላይ እንዳለ አሁንም ያሳያል፡፡
ግንባሩን መስቀለኛ መንገድ ላይ የሚያቆመው ወሳኙ ጉዳይ ቁልፍ የሚባለው ስልጣን በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ቦታ አሁንም ቢሆን ለግንባሩ አባል ድርጅቶች አለመዳረሱ ነው፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒሰትር ያለምንም ይሉኝታ ከሃያ ዓመት በላይ ስልጣኑን ጠቅለለው በመያዛቸው እና ድንገት ጉዳዩን ፈር ሳያሲዙት በሞት መለየታቸው፤ አሁን ላሉት የግንባሩ እኩዮች ትከሻ ለመለካካት በር የከፈተ ሲሆን ፈተናውም ከባድ ሆኖባቸዋል፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትር የሚል ማዕረግ እስከ መስጠት የደረሰ፡፡ በዘጠነኛ የግንባሩ ድርጅታዊ ጉባዔው ግንባሩ አንድ ውሳኔ አሳልፎዋል፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ በሌሉበት የተካሄደ በመሆኑ ድርጅቱን ከሁለት ዙር በላይ አንድ ሰው አይመራውም የሚል አቋም ለመያዝ ብዙ አልተቸገሩም፡፡ አቶ መለስ ቢኖሩ በእጅ አዙር ልክ አልነበሩም እንደማለት ስለሚሆን የሚደፍረው አይገኝም ነበር፡፡ ከዚህ ስንነሳ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ከዚህ አምስት ዓመት በኋላ የድርጅቱም ሆነ የሀገሪቱ መሪ የሚሆኑበት እድል ዜሮ የሆነ ይመስለኛል፡፡ እኔ እንደሚገባኝ “የአክሱም ሀውልት ለወላይታ ምኑ ነው?` በሚባልበት ድርጅት ውስጥ በአቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒሰትርነት የደቡብ ንቅናቄ አባላት ሁሉ ይደሰታሉ ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ በብሔር ፖለቲካ ስልጣን ለሚፈልጉ ስብስቦች የሀይለማሪያም ደሳለኝ ከወላይታ ጠቅላይ ሚኒሰትር መሆን ለሲዳማ፣ ለጉራጌ፣ ለጋሞ፣ ወዘተ ምኑ ነው? ይህ የሚያሳየው ይህ ቦታ ለደቡብም ንቅናቄ ደስታና እርካታ አልፈጠረም ማለት ነው፡፡ ቢሆንም አሁን ባለው የግንባሩ ቀመር ደቡብ ድርሻውን አግኝቶዋል እንበል …. ልክ ባይሆንም ….
ዋናውን ወንበር ጠባቂ ቀሪ የግንባሩ ደርጅቶች “የአማራው” ብአዴን እና “የኦሮመ” ኦህዴድ ናቸው፡፡ የኦሮሞ ብሔረተኞች ለላንቲካ ከሚሰጠው የፕሬዝዳንትነት ቦታ በላይ ይገባናል የሚል ቅሬታ አላቸው፡፡ ይህ ከባድ ጥያቄ ባለበት ጊዜ በሚቀጥለው ዙር የጠቅላይ ሚኒሰትርነት ቦታ ለአማራ መስጠት በግንባሩ ውስጥ ጡዘት ይፈጥራል የሚል የግል ግምት አለኝ፡፡ ጡዘቱ ከኦህዴድ ብቻ ሳይሆን ከህወሃት ጭምር የሚመጣ ይመስለኛል፡፡ አማራ/ነፍጠኛ በደለህ ተብሎ ሲዋጋ የነበረው የትግራይ ብሔረተኛ መልሶ ለአማራ ዋናውን ቁልፍ የስልጣን ቦታ ይስጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒሰትር የመሆን እድሉ የሚታወቀው የፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ አንድ የስራ ዘመን ከቀጣዩ ምርጫ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ሲጠናቀቅ ቦታውን ለአማራ እንዲሰጥ በማድረግ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒሰትር ኦሮሞ እንዲሆን ሊደረግ ይቻላል፡፡ ይህ ኦህዴድ ከአሁን ጀምሮ ዝግጅት ያደረገበት እንደሆነ የሚሳካ የቤት ስራ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ነገር ግን ፕሬዝዳንት ሙላቱ በመንበሩ ላይ ከቀጠሉ ግን ካርታው በውድም ሆነ በግድ የፖለቲካ ጡዘቱን ለመሸከም ተዘጋጅቶ ግንባሩ ጠቅላይ ሚኒሰትርነቱን ለአማራ ያስረክባል ማለት ነው፡፡ ብዙዎች እንደሚገምቱት ሁሉም የግንባሩ አባል ድርጅቶች ይህ ወሳኝ የስራ አስፈፃሚ ቦታ ሳይደርሳቸው መልሰው ለህወሃት ይለቃሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ህውሃት አሁን ባለው ሁኔታ ከጠቅላይ ሚኒሰትርነት በመለስ ወሳኝ የሚባሉትን ቦታዎች ለማስከበር በትጋት የሚሰራ ይመስለኛል፡፡
ይህ ሁሉ ስንክሳር የመጣው ወግ በሌለው የብሔር ፖለቲካ የተደራጁ ቡደኖች የፈጠሩት ግንባር ቀጣይነት ያልታሰበበት ብቻ ሳይሆን ሌሎች አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎችም እንዳይጎለብቱ እየተደረገ በመሆኑ ነው፡፡ ግንባሩ ከዚህ ስንክሳር የሚወጣበት አንዱ መንገድ አጋሮቹን ጨምሮ የግንባሩ አባል ድርጅቶች በፖለቲካ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ፓርቲ/ንቅናቄ ለመሆን የመወሰን አቅም ሲፈጥር ለዚህም ሃሳብን ለማንሸራሸር እድል የሚፈጥር ውስጠ ዲሞክራሲ ሲኖረው ነው፡፡ ከዚህ ውጭ አንድ ቀን በስልጣን ጥም የሚነሳ የውስጥ ግጭት የሚያፈነዳው እሳተ ገሞራ ጦሱ ለእኛም ሊተርፍ ይችላል፡፡ ኢህአዴግ ይህችን ቀጣይ አምስት ዓመት ህዝቡን በልማት ስም ለማደናገር በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተውጦ በመስቀለኛ መንገድ ላይ መሆኑን ከዘነጋው ጦሱ ለብዙዎች የሚተርፍ ነው የሚሆነው፡፡ ዛሬ ኢህአዴግ የሚያስፈልገው አሁንም በጎጥ የሚሰበሰቡና ስልጣን የሚቀራመቱ ኪራይ ስብሳቢዎች ሳይሆን ከዚህ ቀደም አቶ ተፈራ ዋልዋ አቅርበውት የነበረውን እና ብቻቸውን ድምፅ የሰጡለት የአዋሳ ጉባዔ ሃሳባቸውን አቧራውን አራግፎ የሚያነሳ ጎበዝ ነው፡፡ ይህ ሃሳብ ደግሞ እነ ሀብታሙ አያሌውን የመሰሉ ምርጥ ወጣቶች ተሰፋ አስንቆ ኢህዴግ አባል እንዲሆኑ ያደረገ ነው፡፡
ኢህአዴግ ይህን እርምጃ እንዲወስድ የምንመክረው ፓርቲ ከሀገር በላይ መሆኑን በማሰብ እና በእነርሱ ዝርክርክነት የሚመጣው ጦስ ለእኛም ስለሚተርፍ ነው፡፡ ግንባሩ በዚህ መስመር እራሱን ከቃኘ ሌሎች በህብረ ብሄራዊ አደረጃጀት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲደራጁ ፍርሃትና ብርክ አይዘውም፡፡ከሌሎች ጋር ለመወዳደርም ቢሆን ድፍረት ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስብዕናቸው የተፈተኑ ሰዎች በተቃዋሚም ሆነ በገዢ ፓርቲ ውስጥ ጎልተው እንዲወጡ ማድረግ የሚያስችል ስርዓትም የሚፈጠረው ይህን መስቀለኛ መንገድ መሻገር ከቻለ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ስርዓት በሃሳብ የተሻሉ ሰዎች ወደ መድረክ የሚመጡበት እንጂ በጎጥ በኮታ ሹመትና ጥቅም የሚሰባሰቡበት እንዳይሆን ገደብ ያበጃል፡፡
ከዚህ በፊት በተለያየ አጋጣሚ እንደተናገርኩት በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለውን አውራ በሚል አውሬ የሆነውን ግንባር ለመገዳደር የሚችል ተቃዋሚ መኖር የግድ እንደሚል ጥርጥር የለኝም፡፡ ይህ ጠንካራ ተቃዋሚ በእኔ እምነት አሁን ካሉት ተቃዋሚ ነን በሚል ስርተፊኬት ይዘው ከሚንቀሳቀሱት ቡድኖች ውስጥ አይገኝም፡፡ ይህ ማለት ግን በእነዚህ ፓርቲዎች ውስጥ ለዚህ የሚሆን እርሾ የሚያበጁ በግለሰብ ደረጃ ሰዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ እንደ ስብስብ ግን የትኞቹም ቡድኖች በተለየ አደረጃጀት እራሳቸውን ለማፅዳት ቢያስቡ ከውስጥ በሚነሳ እሳት ጉልበትና ጊዜያቸውን መጨረስ ብቻ ነው ትርፉ፡፡ ይህ ደግሞ ተሰፋችንን ያርቀዋል፡፡ በቀጣይ ይህን ከባድ ሀገራዊ ሃላፊነት የሚወጣ ማንኛውም ቡድን ይፈጠራል የሚል ተሰፋ አለኝ፡፡ የዚህ ቡድን ሃላፊነት አባላቶቹ ለአቅመ መስጠት የደረሱ መሆናቸውን ማረጋገጥ የግድ ይለዋል፡፡ ሰጦታቸውም በቸርነት እንጂ ለጉራ እና ነገ በውለታው ምን አገኛለሁ በሚል ስሜት እንዳይሆን ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉም በላይ አባላቶቹ ለፖለቲካ መሪነት እራሳቸውን በቁርጠኝነት ያዘጋጁ እና  ሀገር የመምራት ሃላፊነታቸው በህዝብ ዘንድ ይሁንታ እንደሚያገኝ እርግጠኞች መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ማለት አባላቱ እራሳቸውን ከማሳመን አልፈው የህዝብ ታዓማኒነት ለማግኘት የማይቸገሩ እንደሆነ እርገጠኛ መሆን አለባቸው፡፡
ኢህዴግም መስመሩን ካስተካከለ ተቃዋሚ የሚሆን ቡድን ማግኘት ከቻለን ውድድሩ በተመሳሳይ ኪሎ እና በሃሰብ ልዮነትና የበላይነት ላይ ይሆናል፡፡ ይህን ተሰፋችንን እውን ለማድረግ ቁጭ ብለን በመቆዘም አይመጣም፤ ወይም ደግሞ ሌላ ነፃ አውጪ ቁጭ ብሎ በመጠበቅ፡፡ ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል፡፡
ቸር ይግጠመን