Saturday, December 27, 2014

አንድነትና ምርጫ ቦርድ


ዛሬ በምርጫ ቦርድ ጉዳይ ለመፃፍ ያነሳሳኝ ነገር ማንም ይረዳዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ፀረ አንድነት ዘመቻ ከተጀመረ ቢቆይም እያለፈ እያለፈ ብቅ ማለቱ ብዥታ ስለፈጠረብኝ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ከአንድነት ጋር የሚያድርግ ያለውን ዝርዝር ከማውራቴ በፊት ግን ለአንባቢ ማስጨበጥ ያለብኝ ነገር አለ፡፡ አንድነት ፓርቲ ምርጫ እሳተፋለሁ ሲል ምን ማለቱ ነው? የሚለውን ብዙዎች እነደፈለጉ ይልቁንም እነሱ ለመረጡት የሰነፍ መንገድ በሚመቻቸው መንገድ እየተረጎሙት ይገኛል፡፡
አንድነት ፓርቲ ምርጫ እገባለሁ ብሎ ሲወስን አንድነት በምንም መመዘኛ ከገዢው ፓርቲም ሆነ ከመንግሰት መዋቅሮች የተለየ ድጋፍ አገኛለሁ ብሎ በማሰብ አይደለም፡፡ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ማለት ነው፡፡ ይልቁንም አሁን ባለው ሁኔታ ማለትም ከዋና አዛዣቸው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እልፈት በኋላ ለመጀሚረያ ጊዜ የሚያካሂዱትን ሀገራዊ ምርጫ ከቀድሞ በተለየ ለመሸነፍ ዝግጁ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ማለትም በ1997 እንዳደረጉት ለሙከራም ቢሆን የጫወታ ሜዳውን ሊከፍቱት አይችሉም፡፡ ባጠቃላይ የአንድነት ፓርቲ ግምገማ ገዢው ፓርቲ ከምን ጊዜውም በላይ ዘግቶ መጫወት እንደሚፈልግ ከግንዛቤ ያሰገባ ነው፡፡ ሰለዚህ መድረኮች በቅርቡ እንዳሉት እንዲሁም አንድ እንድ ፓርቲዎች ሲሉት እንደነበረው ኢህአዴግ በሩን ለውይይት የዘጋው እንደ አንድነት ፓርቲ ምርጫ እንገባለን ስለአልን አይደለም፡፡ ኢህአዴግ አሁን ካለበት ነባራዊ ሁኔታ ተነስቶ ምንም ክፍተት እንደማይሰጥ በመረዳት ከወዲሁ መላውን ህዝብ አንቀሳቅሰን ለማስከፍት የወሰንን መሆኑን ማውቅ ይኖርባቸዋል፡፡
አንድነት ምርጫ እሳተፋለሁ ሲል ደግሞ ለተሳትፎ እንዳልሆነ ደግሞ ሁሉም ያውቀዋል፡፡ የመጀመሪያው በር ማስከፈቻው ደግሞ ህዝቡ አማራጭ የለም ከሚል ፕሮፓጋንዳ እንዲላቀቅ በማድረግ አማራጭ ማሳየት ዋነኛው ሲሆን፣ አማራጭ መኖሩን ከተረዳ ደግሞ በነቂስ ወጥቶ ለመራጭነት እንዲመዘገበ፣ እንዲመርጥ እና ድምፁን እንዲያስከብር ማስተማር ነው፡፡ ይህ ደግሞ በሩን ክፈቱ ከሚል ጉንጭ አልፋ ጭቅጭቅ ተላቀን እንዴት እንክፈተው ላይ ማተኮር የሚል ስትራቴጂ ነው፡፡ ሚሊዮኖች በዚህ መስመር ከተሰለፉ ደግሞ ማንም ውሳኔያቸውን እንደማይቀለብስ እርግጠኞች ነን፡፡ ይህ ደግሞ በህዝብ ኃያልነት መተማመን ነው፡፡ ህዝቡ ከተባበረ ይህን በመንግሰት መዋቅሮች የሚደርሰውን አፈና ሊበጥሰው እንደሚችል ማመን ይኖርብናል፡፡ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የምንለየው በዚህ ነው፡፡ ሌሎች ኢህአዴግ በሩን ይክፈትና እንግባ ሲሉ እኛ ደግሞ ከፍተን እንግባ ብለናል፡፡ ኢህአዴግ ልብ ቢገዛና ሜዳውን ለሁሉም እኩል እንዲሆን ቢያደርገው ምርጫው ፍጥጫ ሳይኖርበት ሊጠናቀቅ እንደሚችል የሁላችንም እምነት ነው፡፡ በነገራችን ላይ በሩን ከፍተን እንግባ ያልነው እኛ ብቻ አይደለንምን የሀይል አማራጭ የሚከተሉትም ይህን ከፍቶ መግባት ይስማሙበታል፡፡ ልዩነታችን እኛ በሰላማዊ መንገድ ህዝብን አስተባብሮ ማሰከፈት እና መግባት ይቻላል ማለታችን ነው፡፡
ወደ ምርጫ ቦርድ ጉዳይ ስንመለስ፣ ምርጫ ቦርድ አንድነትን ምን አድርግ እያለው እንደሆነ ለሁላችን ግልፅ አይደለም፡፡ ከምርጫ ቦርድ ሰዎች ጋር በግንባር ቀርበን ስንወያይ በአክብሮት እንደሚያስተናግዱን መካድ ተገቢ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ በተለያየ ጊዜ በሚዲያ ብቅ እያሉ የሚሰጡት መግለጫ ስንመለከት አንድነት ፓርቲን ለምን በዚህ ደረጃ እንደሚፈታተኑት ለመረዳት ይከብዳል፡፡ በቅርቡ በአንድነት ውስጥ በአመራር አሰያየም ችግር እንዳለ አስመስለው ያቀረቡት ነገር በጣሙን አሳኝ ብቻ ሳይሆን በተለይ አንድነት ፓርቲ የህዝብ ታዛቢዎች ምርጫን በንቃት ለመሳተፍ በቂ ዝግጅት አድርጎ መንቀሳቀስ በጀመረበት ወቅት መሆኑ ጋር ተራ ግጥምጥሞሽ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የምርጫ ቦርድ ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው በሚዲያ ምንም ዓይነት ቅስቀሳ ሳያካሂድ፣ በየሰፈሩም የህዝብ ታዛቢ ምርጫ እንደሚካሄድ በይፋ ጥሪ ሳይደረግ፣ በሚስጥር በደብዳቤ በተጠሩ የቀበሌ ነዋሪዎች የህዝብ ታዛቢ ምርጫ ማድረጉን ስንታዘብ፣ ምርጫው ፕሮፌስር መርጊያ በቃና በተደጋጋሚ ምርጫን በተሻለ ሁኔታ ለማካሄድ አቅም ፈጥረናል ይበሉ እንጂ ሁሉንም እኩል ለማጫወት ዝግጁ ናቸው ብለን ለማለት አቅም እያነሰን፣ እነሱም እምነታችንን እየሸረሸሩት ይገኛል፡፡
ምርጫ ቦርድ አንድነት ፓርቲን ከሌሎች ፓርቲ በተለየ ሁኔታ የጠቅላላ ጉባዔ አባላትን ብዛት አሰገቡ ይህም በደንባችሁ ውስጥ ይካተት ብሎ ሲል በግልፅ ባይሆንም በገደምዳሜ ጠቅላላ ጉባዔ ካልጠራችሁ ይህን ማድረግ አትችሉም ማለቱ ነበር፡፡ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ደግሞ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ይህን ማድረግ አይችልም የሚል ታሳቢ ያደረጉ ይመስላል፡፡ አንድነት ግን ይህን ግምት መና ባስቀረ መልኩ ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቶ በደመቀ ሁኔታ ለ2007 ምርጫ መሰረት ጥሎ ሲለያይ ምርጫ ቦርድ እሰይ ተፎካካሪ የሚሆን ፓርቲ መጣ ብሎ መደሰት ሲገባው በተራ የአስተዳድር ስራዎች መሰረት አድርጎ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ በሳምንት ጊዜ እንድታስታውቁ የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት በማስተላለፍ ህዝቡን ግራ ማጋባት ተገቢ እንቅስቃሴ አይደለም፡፡ ይህን ጉልበታቸውን ለፓርቲዎች አቅም ግንባታ ቢያውሉት የሚጠቀሙ ይመስለኛል፡፡ ሀገርም ከዚህ ይጠቀማል፡፡
አንባቢ እንዲረዳ የምንፈልገው ዋና ቁምነገር አንድነት ፓርቲ እንደ ፓርቲ ሁሉንም ህጋዊ መስመሮች አሟልቶ በተደጋጋሚ በሆደ ሰፊነትና በቅንነት በህግ ከሚጠበቅብን በላይ በመሄድ ከግብግብ ግንኙነት ወደ ውይይት ለማምረት ሙካራ እያደረግን መሆኑን አውቆ አንድም የህግ ክፍተት ፈጥረን ከጫወታ ለመውጣት ሰበብ እንደማንሰጣቸው ነው፡፡ ይህ ማለት ግን እንዲያንበረክኩን እድል እንሰጣለን ማለት አይደለም፡፡ ለማነኛውም ምርጫ ቦርድ ህዳር 19 ቀን በፃፈልን ደብዳቤ መሰረት የሚጠበቅብን የጠቅላላ ጉባዔ ቁጥር በደንብ አካታችሁ አምጡ የሚል ሲሆን ይህን ደግሞ ታህሳስ 3 የተሰበሰበው ጠቅላላ ጉባዔ እንዲካተት አድርጎ ሪፖርቱ ታህሳስ 10 2007 ለቦርዱ ፅ/ቤት ገቢ ተደርጎዋል፡፡ ታህሳስ 10 ማለት ቦርድ ስብሰባ ያደረገበት ዕለት እና በሚዲያ የቀረበበት ቀን ስለሆነ ሪፖርቱን ከማየቱ በፊት ያሳለፈው ውሳኔ ነው ብለን በቅን ልቦና በመውሰድ በህዝቡ ዘንድ የፈጠሩት ብዥታ በሚያጠራ መልኩ የፈለጉት ሪፖርት በአንድነት በኩል የቀረበ መሆኑን በሚዲያ ይገልፃሉ ብለን አሁንም በቅንነት እንጠብቃልን፡፡
አንድነት ፓርቲ ላይ ምርጫ ቦርድ ከዚህም የከፋ ጫና ሊያደርስብን እንደሚችል መጠበቅ ትጥቃችንን ጠበቅ ለማድረግ እንደሚረዳን መገንዘብ አለብን፡፡ በቀጣይ በሚኖሩት ተደጋጋሚ ምርጫ ተኮር እንቅስቃሴዎች በቁጥር ብዙ የሚባሉ ለውጤት ሳይሆን ለተሳትፎ የሚገቡ ፓርቲዎች ይህን ጫና ለማድረግ አብረው መሰለፋቸውም የግድ ነው፡፡ ለለውጥ የተነሳው ህዝብ ግን ትኩረቱን ማን ላይ ማድረግ እንዳለበት ግን ጠንቅቶ ያውቃል፡፡ በቅርቡ በምርጫ ቦርድ በተሰጠው የሚዲያ መግለጫም አብዛኛው ሕዝብ ይህ ዘመቻ አንድነት ላይ ለምን በዛ? ብሎ ጠይቆዋል፡፡ መልሱም ግልፅ ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ ቁርጥ አቋም ይዞዋል፣ በቀጣይ ምርጫ ሚሊዮኖች ተንቀሳቅሰው ድምፃቸውን ይስጣሉ፣ የሰጡትን ድምፅ ደግሞ ያስከብራሉ ብሎ ያምናል፡፡ አምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለአምሳ ሰው ጌጡ እንደሚባለው፣ አንድነት ፓርቲ እያንዳንዱ ዜጋ ነፃነቱን ለማስከበር ዘብ ከቆመ የሚሊዮኖች ድምፅ ይከበራል ብሎ በማመን የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ እንዲሰራ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ይገኛል፡፡
ቀኝ ኋላ ዙር ሊሉ የሚፈልጉትን በሙሉ ወደፊት በማለት ለማሸነፍ የስነ ልቦና ዝግጅት እናድርግ እላለሁ፡፡ ምርጫ የገባ ነው ምርጫ ቦርድን አምነን ሳይሆን የህዝብን ሀያልነት ተገንዝበን ስለሆነ ማሸነፋችን ሳይታልም የተፈታ ነው፡፡ መንገዱ ምንም ያህል ጎርባጣ ቢሆንም ለድል የተነሳን መንፈስ ማሸነፍ ይከብዳል፡፡ ይቻላል ብለን እንደጀመርነው ከግብ ለማድረስ ቀበቶዋችንን ጠበቅ ነው፡፡ ቀላል ነው፣ የመጀመሪያው ሰራ ለመራጭነት መመዝገብ ነው፡፡ ቀዳሚ ይሁኑ ካርዶን በእጆ ያስገቡ!!!
ቸር ይግጠመን!!!!


Saturday, December 20, 2014

ጀግኖቻችን እና የፍርድ ቤት ነፃነት!!!

ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com; girmaseifu.blogspot,com
በቅርቡ የሚካሄደውን የ2007 ምርጫን  አስመልክቶ የፓርቲዎችን ዝግጅት ምን እንደሚመስል ለመረዳት ኢህአዴግ፣ አንድነት እና ኢዴፓ የወከሉ ሰዎች በፋና ሬዲዮ ባለፈው እሁድ ውይይት አድርገው ነበር፡፡ መኖሩ ትርጉም ስለአልነበረው ነው እንጂ ሌላም አንድ ፓርቲ ወክያለሁ ያለ ሰው እንደነበር ዘንግቼው አይደለም፡፡ የኢህአዴጉ ወኪል በመጨረሻ ላይ ያቀረቡትን ሃሳብ ሳደምጥ የኢህአዴግ ፓርቲ ወኪል ማንም ቢሆን ተመሳሳይ እንደሆነ መረዳት የምንችለው ነገር አንዳቸውም በተነገራቸው እንጂ በራሳቸው መርምረው ሊደርሱበት የሚፈልጉት ሀቅ ያለ አይመስለኝም፡፡ በፓርቲው ስብሰባ ከሚሰበካቸው ውጭ ዋነኛ የመረጃ ምንጫቸው የኢትዮጰያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ገፋ ሲል ደግሞ ፋና ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት መደምደሚያ ላይ እንድደርስ ያደረገኝ ነጥብ ደግሞ የአንድነት ምክትል ፕሬዝዳንት እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆኖ ሲሰራ የነበረው አንዱዓም አራጌ እና ሌሎች የህሊና እሰረኞች ላይ የተፈረደውን የፍርድ ቤት ውሳኔ መቀበልና አለመቀበል ከፍርድ ቤት ነፃነትና ለፍርድ ቤት እውቅና ከመስጠት ጋር ማያያዛቸው ነው፡፡ በፍርድ ቤት ውሳኔ ባለመስማማት የምንይዘውን አቋም መረጃ የሌለው ነው ብለው የሚያቀርቡት ጉንጭ አልፋ  ክርክር እጅግ አስገራሚ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም አንዱዓለም አራጌ ይፈታ በሚል አንድ ፅሁፍ ፅፌ ነበር አንዱዓለም የታሰረው በ “አሸባሪነት” ነው ለሚሉን መስሚያ የሌለን መሆኑን ብቻ አይደለም የታሰረው የኢህአዴግ ጉምቱ ባለስልጣናት ከእቅዳቸው በፊት ከስልጣን የሚነቀንቃቸው ሰላማዊ ታጋይ መሆኑን በመጠርጠራቸው ነው የሚል ነበር፡፡ ብዙዎች እንደሚስማሙት ደግሞ በምርጫ ሁለት ሺ ሁለት ክርክር ወቅት ተናዳፊ ተከራካሪ ሆኖ በመቅረቡ ነው፡፡ በብዙዎች ዘንድ አንዱዓለም ንቢቱን አስንቆ በስልጣን ሲናገሩ የነበሩትን በመረጃ አስደግፉ ሲያጋልጣቸው ቂም ይዘው እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህን እንድንገምት ያደረገን ደግሞ አንዱዓለም በተከሰሰበት ወንጀል ለዕድሜ ልክ እስር አይደለም ለምክር የሚገብዝ ጥፋት ማጥፋቱን የሚያስረዳ ማስረጃም አልቀረበበትም ምስክርም አልተሰማበትም፡፡ አዳፍኔ ምስክሮችም ቢሆኑ ከእስር ቤት ለመውጣት ቃል የሰጡ ቢሆንም በፍርድ ቤት ገብተው ግን አንዱዓለም ለሸብር ተግባር ወጣት ሲያደረጅ ነበር ብለው ሊመስክሩ አልቻሉም፡፡ የኢህአዴግ ሹሞች በቦታው አልነበሩም፤ እኛ ግን በቦታው ነበርን፡፡
ፍርድ ቤት ውሳኔ የሰጠበት መዝገብ በአሁኑ ወቅት ማንም ሰው ሊያገኘው እንደሚችል ግልፅ ነው፡፡ የኢህአዴግ አባላትና ሹማምንት ደግሞ ይህን መረጃ ለማግኘት ከማነኛችንም በላይ እድሉ አላቸው፡፡ እነዚህ የኢህአዴግ አባላትና ባለስልጣናት ይህን የምናቀርበውን ጩኽት ልክ መሆኑን ለማጣራት ለምን ይህን የፍርድ ቤት መዝገብ መርምረው አቋም አይዙም? የሚል ብርቱ ጥያቄ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ እነዚህ ሹሞች ከላይ እንደገለፅኩት በኢህአዴግ ስብሰባ ወቅት ከሚሰሙት ማብራሪያ እና በመንግሰት ሚዲያ ከሚሰሙት ውጭ ሌላ ነገር አንብበው ለመረዳት ዝግጁ አይደሉም፡፡ የኢህአዴግ ደጋፊዎች ቢሆኑም ከዚህ ጭፍን መስመር ውጭ አይደሉም፡፡ አንዱዓለም ይፈታ በሚል በፃፍኩት ፅሁፍ እንዲ ብዬ ነበር፤
“መደበቅ የሌለብኝ ዕውነት ግን ከአንዱዓለም ጋር ከምናደርገው የሠላማዊ ትግል ውይይት (አንዳንዴም ጭቅጭቅ የሚባል ቦታ ሊደርስ የሚችል) በተቃራኒ አንድ የሆነ ሠይጣን አሳስቶት - ይህ ሠይጣን ኢህአዴግ ሊሆን ይችላል፤ ማለትም የሠላማዊ መንገዱን ሁሉ እያጠበበ ያለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ - አንዱዓለም ተገዶ ሌላ አማራጭ ፍለጋ ሄዶ ይሆን በሚል የመረጃ ፍለጋ ጉጉቴ አልጨመረም ልላችሁ አልችልም፡፡”
ይህ የሚያሳየው አንዱዓለም ጓደኛ የትግል ጓዴ ቢሆንም ሊሳሳት ይችላል ብዬ መጠራጠሬ አልቀረም ነበር፡፡ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትርም ክምር ማስረጃ አለ ብለውን ነበር፡፡ ፍርድ ቤት ከቀረበው ማስረጃ እና ከቀረቡት ምስክሮች ግን አንድም ውሃ የሚቋጥር ነገር ስናጣ፤ ክምር ቀርቶ አንድ ገፅ ወረቀት ሲጠፋ ፍርድ ቤት ወስኖዋል ብለን ከህሊናችን ጋር ተጋጭተን እንደ ኢህአዴጎቹ አንዱዓለም አሽባሪ ነው እንድንል መፈለጋቸው አስገራሚ ብቻ ሳይሆን እነዚህ የኢህአዴግ ሹሞች እንዴት አድርገው እንደሚሰሯቸው መረዳት አስቸጋሪ ነው፡፡
ይህን ሁሉ በድጋሚ እንድል ያስባለኝ ኢህአዴግን ወክሎ የቀረበው የውይየት ተሳታፊ “በእስር ቤት የሚገኙትን አመራሮችና አባሎች ጅግኖቻችን ማለታችሁ አሁንም በሁለት ሺ ሰባት ምርጫ ህጋዊና ህገወጥ መስመር እያጣቀሳችሁ ለመሄድ ያላችሁን ዝግጅት የሚያሳይ ነው፡፡” የሚል አስተያየት ሲሰጡ መስማቴ ነው፡፡ የሁለት ሺ ሰባት ምርጫ ሰላማዊ ሊሆን የሚችለው ሀቅን በመደፍጠጥ እና ፍርድ ገምድል ውሳኔን አሜን ብሎ በመቀበል ሳይሆን ኢህአዴግ በስልጣኑ የመጡበትን ያለምንም ይልኝታ እድሜ ልክም ቢሆን እስር ቤት ለመጎር ደንታ የሌለው መሆኑን በማጋለጥ ነው፡፡ ይህንን ሀቅ ለመመርመር ድፍረት ያገኙ የኢህአዴግ አባላትም ሆኖ ሹሞች በዚህ አይነት ስርዓት ማንም ተጠቃሚ እንደማይሆን ለመረዳት አይቸገሩም፡፡ ይህን ስርዓት በመለወጥ የሚገኘው ትንሳኤ ማንም በግፍና በፍርደ ገምድል ውሳኔ ሰጋት ላይ እንዳይወድቅ የሚያድርግ ነው፡፡ የዚህ ደግሞ ትሩፋት ለኢህአዴግ አባላትም የሚሆን ነው፡፡
የኢህአደግ ሹሞች በዚህ ዓይነት ውይይት ወቅት ከፓርቲያቸው በተቃራኒ መስመር ይቁሙ የምል የዋሃ አይደለሁም፡፡ ይልቁንም እነዚህን ነጥቦች መከራከሪያ ሆኖ ቢመጣ እንኳን ችላ ብለው በማለፍ ከትዝብት ሊተርፉ ይቻላሉ የሚል እምነት ስለ አለኝ ነው፡፡ በሀገራችን ያሉትን ተቋሞች የምናከብራቸው በህንፃቸው ግዝፈት ወይም በቀጠሩት የስው ሀይል ብዛት ሊሆን አይችልም፡፡ ፍርድ ቤቶች ሊከበሩ የሚችሉት በሚያሰፍኑት ፍትህ ነው፡፡ ዜጎች መብቴ ፍርድ ቤት ሄጁ አስከብራለሁ የሚል ደረጃ ሲደርሱ ነው፡፡ በሀገራችን ያለው የፍትህ ስርዓት ፖለቲካ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን በቤተስብ ውርስ ጉዳይ እንኳን አፋጣኝ ፍትህ የሚሰጥ አይደለም፡፡ በፍትሃብሔር ጉዳይም ቢሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጠው ደረጃ የወረደ ነው፡፡ ይህ እንዲሻሻል ማሳሰብ እና መታገል ፍርድ ቤቶቸን እውቅና እንደመንፈግ መቁጠር ተገቢ ነው ለማለት አይቻለም፡፡ በተመሳሳይ ፍርድ ገምድል ውሳኔዎችን እንድንቀበል መገደድም የለብንም፤ ብንገደድም ሊሳካ የሚችል አይደለም፡፡ ለዚህ ነው የህሊና እስረኞችን ጅግኖቻችን የምንለው፡፡
እኔም እላለሁ የአንድነት ፓርቲ አባላት ላይ እየተለጠፈ ያለው “የአሸባሪነት” ታፔላ በፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው ደግመን ደጋግመን ማሳሰብ እንፈልጋልን፤ መፍተሔውም ፖለቲካዊ ውሳኔ በመስጠት መፍታት እና ለሰላማዊ ትግል የፖለቲካ ምዕዳሩን ማስፋት ነው፡፡ የሰላማዊ ትግል መድረኩ በጠበበ ቁጥር ደግሞ ዜጎች አማራጭ የትግል ስልት መፈለጋቸው የግድ ነው፡፡ በጠረጴዛ ላይ ያለው ሌላኛው አማራጭ ሀገርን ህዝብን ከመጉዳት ውጭ ገዢዎችንም ሊጠቅማቸው የሚችልበት አንድም መንገድ አይታይም፡፡ ሁሉም አሽናፊ ሆኖ የሚወጣበት ስርዓት መዘርጋት ለፍትህ ስርዓቱም ትንሳኤ ስለሚሆን ጅግኖቻችንን በመፍታት ለፍትህ ስርዓቱ ትንሳኤ በጋራ እንድንቆም መንግሰት ኃላፊነት አለበት፡፡
ምርጫ ሁለት ሺ ሰባት ለለውጥ!!!
ቸር ይግጠመን



Sunday, December 14, 2014

ህገ መንግሰቱን የሚንደው ማን ነው?




ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com; girmaseifu.blogspot.com
በአገባደድነው ሳምንት መጀመሪያ ህዳር 29 ቀን በከፍተኛ የገንዘብ ወጪ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የ “ብሔር ፣ብሔረሰቦች እና ህዝቦች”  ቀን ተክብሮ ውሎዋል፡፡ “ብሔር፣ ብሔረሰቦች፣ ህዝቦች” የሚሉት ሶሰት ቃላቶች ቢሆኑም በህገ መንግስት ውስጥ አንድ ትርጉም የተሰጣቸው ቢሆንም ባለቤቶች ነን የሚሉትም ቢሆኑ በውል ያልተረዷቸው ተምኔታዊ ነገሮች ናቸው፡፡ ወጣም ወረደ ግን እነዚህ ቃላቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልዕ ቦታ ያላቸው እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ እኛም እነዚህን ቃላቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉልዕ ቦታ የያዞ መሆናቸውን አምነን ተቀብለናል፡፡ ይህ ማለት ግን ገብቶናል ማለት አይደለም፡፡ ይህ በየክልሉ በዙር የሚከበረው ባህል ታስቦበት ህገ መንግሰት ከጸደቀበት እለት ጋር የተገናኘ ስለሆነ እለቱን ከህገ መንግሰት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች የሚነሱበት ብናደርገው ክፋት የለውም፡፡ ስለዚህ ባለፉት 20 ዓመታት ይህ ህገ መንግሰት ምን ሰጠን ምንስ ነፈገን ብለን መጠየቅ እና የተወሰኑ ማሳያዎች ማቅረብ ተገቢነት ያለው ይመስለኛል፡፡
ጠበቃ ተማም አባቡልጉ ባለፈው ሳምንት ዕትም በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ እንዳስቀመጠው ህገ መንግሰታችን ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ የህግ ግዴታ ለማይጣልባቸው “ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች” ለሚባል ሃሳባዊ ስብስብ ተሰጥቶ ህገ መንግሰቱ የናንተ ነው ተብለዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ህገመንግሰቱ የማንም እንዳይሆን ተደርጎዋል ብሎናል፡፡ ይህ የሆነው ግን በስህተት የሚመስለው ካለ ተሳስቶዋል፡፡ የማንም ያልሆነን ማለትም ባለቤት የሌለወን ነገር በአደራ ለመጠበቅ በሚል ለረዥም ጊዜ በስልጣን ለመቆየት የተደረገ ደባ እንደሆነ መረዳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ የዚህን ሴራ ማሳያ የሚሆን ምሳሌ ከዚህ በታች ማቅረብ ጉዳዩን ግልፅ ያደርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በፕሬዝዳንትነት የጀመሩትን በታሪክ አጋጣሚ የተገኘ ሀገር የመምራት ተልዕኮ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲያወርዱት በፕሬዘደንታዊ ስርዓት (በቀጥታ የህዝብ ምርጫ ስልጣን የሚይዝ) ፕሬዝዳንት መሆን ጠልተው አይደለም፡፡ በዛን ጊዜ በነበረው ነባራዊ ሁኔታ አቶ መለስ ዜናዊን ማንም ሀገር ወዳድ ተነስቶ ዕጩ ሆኖ ቢቀርብ ሊያሸንፋቻው እንደሚችል ስለሚያውቁ ከዚህ የተለየ አደረጃጀት መከተል ነበረባቸው፡፡ ይህም በድርጅታዊ አሰራር በሚስጥር ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የሚያሰችል ዘዴ መከተል ነው፡፡ ይህ ህውሃት እንደ ቡድን አቶ መለስ ዜናዊ በግል ያለባቸውን ያለመመረጥ ስጋት ካነሱት ነጥቦች አንዱ በ1987 አይደለም ዛሬ ከሃያ ዓመት በኋላ ኢትዮጵያዊያን የባህር በር አጥተው መታነቃቸውን ለመዘንጋት አልተቻላቸውም፡፡
ከዓለም የባህር በር ከሌላቸው ሀገሮች በህዝብ ብዛት አንደኛ መሆናችን ብቻ ሳይሆን በቅርብ ርቀት በባሕር በር ላይ ተገኝተን የበይ ተመልካች መሆናችን ታሪክ ይቅር የሚለው ስህተት አይደለም፡፡ የዚህ ታሪካዊ ስህተት መሃንዲስ ደግሞ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው፡፡ ሌላው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የኢትዮ-ኤርትራ የወንድማማቾች ጦርነት ተከትሎ ህዝቡ ለባንዲራ ያሳየውን ፍቅር ተመልክተው የባንዲራ ቀን እንዲከበር አረንጓዴ መብራት ቢያሳዩም፤ እራሳቸው በስታዲየም ተገኝተው “ጨርቅ” ነው ብለው ያጣጣሉትን ባንዲራ በክብር ቢሰቅሉትም ህዝቡ ባንዲራ “ጨርቅ” ነው የሚለውን የአፍ ወለምታ ሊዘነጋው አልተቻለውም፡፡ በእነዚ እና ሌሎች ብዙ ምክንያቶች የኢትዮጵያ ህገ መንግሰት ዜጎች በቀጥታ የሚመራቸውን መሪ እንዳይመርጡ ያደረገ ህገ መንግስት ነው፡፡
ባንዲራን በሚመለከት የኢትዮጵያ ህገ መንግሰት በግልፅ የኢትዮጵያ ባንዲራ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ነው ብሎ ደንግጓል፡፡ በተጨማሪም አርማ እንደሚኖረው ይደነግጋል፡፡ አርማው ላይ ካልተስማማን በሚያስማማን የባንዲራው ይዘት ላይ አብረን መቆም እንችላለን፡፡ በግሌ ከዚህ ቀደም ከነበሩት አርማዎች የአሁኑ የተሻለ ነው የሚል እምነት ቢኖረኝም ሁሉም ዜጋ ይህ አርማ የሌለበት ባንዲራ መያዝ አለበት የሚለውን ህገ ወጥ የህግ ድንጋጌ ግን ለመቀበል እቸገራለሁ፡፡ መንግሰት በኤምባሴዎች፣ በመንግሰት ተቋማት አርማዬ ያለውን የማድረግ ግዴታ ቢጥል ግድ የለኝም፡፡ በግል አርማ ካላደረጋችሁ የሚል አስገዳጅ ህግ ማውጣት ግን መንግሰት ጉልበተኛነቱን ለማሳየት ካልሆነ በስተቀር ይህ አርማ ከልብ የሚፃፍ እና በፍቅር ሊወደቅለት የሚችል ሊያደርገው አይችልም፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ህገ መንግሰት ከማነኛውም ጊዜ እና ምን አልባትም በፅሁፍ ደረጃ ከማንም ሀገር በተለየ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ህገ መንግስታዊ ዕውቅና የሰጠ ነው ቢባል ማገነን አይሆንም፡፡ ምን ያደርጋል እነዚህ ድንጋጌዎች በወረቀት ላይ የቀሩ ናቸው፡፡ በደም የተፃፈ የሚባለው ህገ መንግሰት በቾክ እንደተፃፈ መቁጠር የተሳናቸው የመንግስት ሹሞች እንደ አፈተታቸው ሲደፈጥጡት ይታያሉ፡፡ ዜጎችን በአደባባይ ከመደብደብ ጀምሮ በዓለም ላይ የቀረ ቶርች የሚደረግባት ሀገር ኢትዮጵያ ነች፡፡ በህገ መንግሰት እውቅና ያገኘን የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች በ “ፀረ ሽብር ህግ” ተደምስሶዋል፡፡ የሰው ልጅ ክቡርነት ዋጋ አጥቶ በህዝብ ስም ስልጣን ለማቆየት ምንም ዓይነት እርምጃ የሚወሰድባት ሀገር ሆናለች፡፡ ይህ ደግሞ ባለበቤት የሌለው ህገ መንግሰት ያመጣው ትሩፋት ነው፡፡ የህገ መንግሰት ባለቤት የተባሉት “ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች” የህግ ተጠያቂነት የሌለባቸው ብቻ ሳይሆኑ ሰብዓዊነትም የሌላቸው ስለሆኑ መብታችን ተነካ ሊሉ አይችሉም፡፡ እስር ቤት አይገቡም፡፡ የሚታሰረው ሰው ነው፤ ሰብዓዊ መብቱ የሚጣሰውም ሰው ነው፡፡ ዜጋው የህገ መንግስት ባለቤት ለመሆን በቡድን ውስጥ መገኘት የግድ ይለዋል፡፡ እኔ ለምሳሌ እነዚህ ቡድኖች ውስጥ ለመገኘት ፍላጎትም ምኞትም ስለሌለኝ ይህ ህገ መንግሰት የእኔ ነው ብዬ በግድ የራሴ ለማድረግ ከመታገል ውጭ ሌላ አማራጭ የለኝም፡፡
ገዢው ፓርቲ በቡድናዊ አስተሳሰቡ በመወጠሩ የእኔ ዓይነት አመለካከት ያላቸውን ሰዎች ህገ መንግሰቱ የእኛ እንዲሆን የምናደርገውን ጥረት ህገ መንግሰት መናድ ነው ብሎ የቡድን ጠብ ለማስነሳት ይታትራል፡፡ በዚህ ዓይነት የቡድን አስተሳሰብ ውስጥ ለሚገኙ የኢህአዴግ አባላትም ሆነ አጋሮች ማረጋገጥ የምፈልገው አንድ ቁም ነገር አለ፡፡ ይህም ቁም ነገር፤
“ይህ ህገ መንግሰት ከነ እንከኑም ቢሆን እንዲከበር የምንፈልግ መሆኑን ብቻ ሳይሆን   ለማሻሻል የተቀመጡት ድንጋጌዎች ምንም ዓይነት አስቸጋሪ ቢሆኑም በዚሁ መስመር ብቻ እንዲሰተካከል እንደምንታገል ማወቅ አለባቸው፡፡”
ይህ ማለት ግን በህገ መንግሰቱ በተቀመጠው መሰረት እንዳይሻሻል ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ የለም ማለት አይደለም፡፡ ለዚህም ዋነኛው ተጠያቂ ገዢው ፓርቲና መንግሰት ብቻ ናቸው የሚሆኑት፡፡ ገዢው ፓርቲ እና መንግሰት በዚህች ሀገር ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ሊኖር የሚችልበት እድል ዘግተው በነውጥ ወይም በጠመንጃ ለውጥ ከመጣ ይህ ህገ መንግሰት ከዚህ ቀደም እንደነበሩት ህገ መንግሰቶች ታሪክ ሊሆን ይቸላል፡፡ ይህ እንዲሆን ፍላጎት የሌለን ሰዎች ህገ መንግስቱ ያሉበትን ችግሮች በህግ ስርዓት ብቻ እንዲሻሻል እንፈልጋለን፡፡ ይህ ባልተሟለበት ሁኔታ አንድ ፊደል በፍሉድ ሳይጠፋ ህገ መንግሰቱ እንዲከበር እንፈልጋለን፡፡
ከዚህ በተቃራኒው ግን መንግሰት ህገ መንግሰቱ እንዲናድ እና ወደ መቃብር እንዲወርድ ተግቶ እየሰራ ነው፡፡ ይህን ስንታዘብ  ህገ መንግሰቱ እንዲናድ የሚሰሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአሁኑ ሰዓት እየጠየቁ ያሉት በህገ መንግስት በግልፅ የተቀመጡት ሰብዓዊና ዲሞክራሲ መብቶች ይከበሩ ነው፡፡ መብቱ የተከበረለት ዜጋ ለልማት ግብዓት እንጂ ዕዳ ሊሆን አይችልም፡፡ በቁስ በሚገለፁ እድገቶች መብታችንን አሳልፈን አንሰጥም ማለት ህገ መንግሰቱን ማስከበር እንጂ መናድ ሊሆን አይችልም፡፡ ዜጎች ህገ መንግሰታዊ መብታችንን ለማስከበር ነቅተን በምርጫ እንሳተፍ የመዝጊያ መልዕክቴ ነው፡፡
ቸር ይግጠመን




Saturday, December 6, 2014

የምርጫ ስትራቴጂ እንዴት ይሁን?



የምርጫ ስትራቴጂ እንዴት ይሁን?
ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com; www.girmaseifu.blogspot.com
በስታራቴጂክ ዕቅድ ዝግጅት ወቅት ከተለመዱት የአካባቢ ሁኔታ ትንታና መሳሪያዎች አንዱ የውጭ እና የውስጥ ሁኔታን የምተነትንበት በእንግሊዘኛ ስዎት/ (SWOT/SLOT Analysis) የሚባለው ነው፡፡ ወደ ውስጣችን ስንመለከት አንዱ ጥንካሪያችን ምንድነው የሚለው ጥያቄ መመለስ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ያሉብን ድክመቶች ወይም ውስኑነቶች ምንድናቸው የሚለው ነው፡፡ ወደ ውጭ ስንመለከት ደግሞ ምን ምቹ ሁኔታ አለ አንዱ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ተግዳሮቶቹ ምንድናቸው ብለን በዝርዝር ማየት ይኖርብናል፡፡
አንድ ስትራቴጂክ ዕቅድ የውስጥና የውጭ ትንተና ሰርቶ የሚከተሉትን ማድረግ የግድ ይለዋል፤
·         በውስጣዊ ጥንካሬ ላይ ያተኮሩ እና በውጭ ያሉትን ምቹ ሁኔታዎችን ለመጠቀም ላይ ያተኮረ፤
·          በውጭ ያሉ መልካም አጋጣሚዎች ለመጠቀም  እና የውስጥ ድከመቶችን በማስወገድ ላይ ያተኮረ፤
·         በውስጥ ጥንካሬዎችን በመጠቀም የውጭ ተግዳሮቶችን በማሸነፍ ላይ ያተኮረ፤ አና
·         የውስጥ ድክመቶች እና የውጭ ተግዳሮቶች የሚያደርሱትን ጉዳቶች በመቀነስ ላይ ያተኮሩ
ስልቶችን መንደፍ የግድ ይላል፡፡ አነዚህን በዝርዝር ከሰለማዊና ህጋዊ ትግል በተለይም ከምርጫ ስትራቴጂ ዕቅድ ዝግጅት ጋር እንዴት ማየት እንዳለብን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ እነዚህን ስልቶች አንድ አንድ ምሳሌ እያነሳን ማየት እስከ ዛሬ የሄድንበትን መንገድ ከመፈተሸ በዘለለ ወደፊት እንዴት መሄድ እንዳለብን የመወያያ ርዕስ ይከፍታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከላይ የተቀመጡትን ስልቶች የተገኙት በዚህ መልክ ከተቀመጠ ሰንጠረዥ ውስጥ ነው፡፡
                                             
ውስጣዊ ሁኔታዎች
ውጫዊ

ሁኔታዎች

ጥንካሬ
ድክመት/ውሱንነት
መልካም አጋጣሚዎች/
ዕድሎች

በውስጣዊ ጥንካሬ ላይ ያተኮሩ እና በውጭ ያሉትን ምቹ ሁኔታዎችን ለመጠቀም ላይ ያተኮረ


በውጭ ያሉ መልካም አጋጣሚዎች ለመጠቀም  እና የውስጥ ድከመቶችን በማስወገድ ላይ ያተኮረ



ተግዳሮቶች

በውስጥ ጥንካሬዎችን በመጠቀም የውጭ ተግዳሮቶችን በማሸነፍ ላይ ያተኮረ

የውስጥ ድክመቶች እና የውጭ ተግዳሮቶች የሚያደርሱትን ጉዳቶች በመቀነስ ላይ ያተኮሩ

ከላይ የተዘረዘሩትን ስልቶች ከታች ወደ ላይ እንመልከታው፡፡
እሰከ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በተቃዋሚ ጎራ የምንገኝ አካላት ትኩረት ሰጥተን ስንሰራ የነበረው የውስጥ ድክመቶቻችንን እና የውጭ ተግዳሮቶች የሚያደርሱብንን ጫናዎቸና ጉዳቶች በማጉላት ላይ ነበር፡፡ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ያሉትን ችግሮች ማወቅ ተገቢ ቢሆንም እነርሱም ደጋግሞ ማንሳት መፍትሔ ሊያመጣ እንደማይችል አልተረዳንም፡፡ በስትራቴጅክ እቅድ ዝግጅት እነዚህ ጉዳታ የሚያደርሱ ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታዎች እንዳሉ ተረድቶ እነርሱን ለመቀነስ የምነወስዳቸው እርምጃዎች ቅድሚያ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይ ምንም ማድረግ የማንችላቸው ለውጫዊ ሁኔታዎች ትኩረት ስጥቶ እነርሱን ማግዘፍ ከጥቅሙ ጉዳቱ ነው የሚበልጠው፡፡ ከዚህ አንፃር ከምርጫ ጋር የተገናኙ ውስጣዊ ችግሮች ከምንላቸው አንዱ ለምርጫ ለመወዳደር ያለብን የፋይናንስ ችግር ሲሆን ይህን ችግር ማሰቀረት ባይቻል እንኳን ለመቀነስ ስልት ነድፈን ከመንቀሳቀስ ይልቅ የገዢው ፓርቲ ድጋፍን እንደ አማራጭ እንወስደዋለን፡፡ ገዢው ፓርቲ ከዚህ አኳይ ሊረዳን ሳይሆን እንዴት ችግራችን ተባብሶ እንድንወድቅ እንደሚሰራ አንረዳም፡፡ ገዢው ፓርቲ የሚያደርሰውን ጫና ከመቀነሻ መንገዶች አንዱ ከመንግሰት የሚጠበቅን የገንዘብ ድጋፍ መብትም ቢሆን ትኩረት አለመስጠት ነው፡፡
ይልቁንም ከመንግሰት የሚመጣን የዚህን ዓይነት ተግዳሮት ትንሸም ብትሆን ካለችን የውስጥ ጥንካሬ በመጠቀም እነዚህን ተግዳሮቶች ማሸነፍ ይኖርብናል፡፡ ከፋይናንስ አንፃር ባነሳነው ምሳሌ ብንቀጥል ተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች አምሰት መቶ አርባ ሰባት ምርጫ ክልል ለማሸነፍ የሚያስችል የፋይናንሲንግ ሰትራቴጂ ልንጠቀም እንችላለን፡፡ ይህም እያንዳንዱን ዕጩ ሰፖንሰር የሚያደርግ አንድ ደጋፊ መመልመል ሲሆን፤ ድጋፉ ለአንድ ሰው ይበዛል ከተባለ ለአስር ማካፈል ይቻላል፡፡ አንድ ዕጩ አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ አስር ደጋፊዎች ሰፖንሰር ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ አንድ ፓርቲ አምስት ሺ ደጋፊዎች ያስፈልጉታል ማለት ነው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ካላቸው የውስጥ ጥንካሬ አንዱ ገንዘብን በቁጠባና መጠቀም፣ ይልቁንም በነፃ የሚያገለግሉ ሰፍር ቁጥር የሌላቸው ወጣቶች መኖራቸው ትልቅ ውስጣዊ ጥንካሬ ነው፡፡ ይህንን አጠንክሮ መሄድ ያለብንን የፋይናንስ ችግረ ለመፍታት ይረዳናል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ውጭ ያሉ አመቺ ሁኔታዎች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ መንግሰት በሚወስዳቸው የተለያዩ የተሳሳቱ ፖሊሲዎች እና አፈፃፀም ዙሪያ ያሉትን ችግሮች በመገንዘብ ህዝቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለመደገፍ ዝግጅቱን እያሳየ ይገኛል፡፡ ይህንን የህዝብ ዝግጁነት ወደተግባር ለመለውጥ በውስጥ ያሉብንን ወደ ህዝብ የመቅረብ ችግር አሰወግደን ለውጤት ማብቃት ይኖርብናል፡፡ እኛ ወደ ህዝቡ በመቅረብ ያሉንን አማራጮች ካላቀረብን እና ከህዝቡ ምን እንደምንጠብቅ ካላስረዳነው ፓርቲዎች ከህዝቡ ጋር ሳይገናኙ ይቀራሉ፡፡ ገዢው ፓርቲ በአንድም በሌላም የሚሰራቸው ስህተቶች ለተቃዋሚዎች የተዘጋጁ ዕድሎች ሲሆኑ ተቃዋሚዎች ደግሞ ወደ ህዝቡ ለመቅረብ ያለባቸውን ችግር በማሰወገድ ለድል የሚያበቃ ሰልት መንደፍ የግድ ይላቸዋል፡፡ እዚህ ነጥብ ላይ ሊነሳ የሚችለው ወደ ህዝብ መቅረቢያውን መንገድ ኢህአዴግ ዘግቶታል የሚለው ነው፡፡ ትክክል ነው ተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ህዝቡን ማግኘት ያለብን ሰብሰበን በአዳራሽና በአደባባይ ብቻ ነው ከሚለው አቋም ወጥትን የአንድ ለአንድ የሰው ለሰው ግንኙነት በየሰፈራችን መጀመር ይኖርብናል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያዎች እንደተጠበቁ ሆነው ማለት ነው፡፡
ዋነኛውና አውራ/ግራንድ የሚባለው ስትራቴጅ ግን መሆን ያለበት ጥንካሬዎቻችን ላይ መሰረት ማድረግና በውጭ ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን አሟጦ መጠቀሙ ላይ ነው፡፡ ላለፉት 23 ዓመታት ችግሮችን እና ተግዳሮቶችን ከበቂ በላይ ተናግረናል እነርሱ የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ ከመስራት ይልቅ መኖራቸው እንዲታወቅ ጩኽናል፡፡ አሁን ጊዚው መለወጥ አለበት ያሉትን እድሎች ለመጠቀም ቆርጦ መነሳት መሆን ይኖርበታል፡፡ ምንም ትንሽ ቢሆኑ በውሰጣችን የሚገኙትን ጥንካሬዎች መፈተሸ እና ዕድሎችን የምንጠቀምበት እድል ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ አሁን በሀገራችን ያሉት ወጣቶች ከሞላ ጎደል ፊደል የቆጠሩ ናቸው እነዚህ ወጣቶች በእውቀት ላይ የተመሰረተ አማራጭ ከቀረበላቸው ያለምንም ፍርሃት በመራጭነት ለመሳተፍ አያቅማሙም፡፡ ይህ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ በተቃዋሚ በኩል የበለጠ የሰራ እድል መፍጠር የሚያስችሉ የፖሊሲ አማራጮች ወጣቶችን ከመንግሰት ጥገኝነት የሚያላቅቅ የመኖሪያ ቤት ፖሊሲ፣ ወጣቶችን የመሬት ባለቤት ሊያድርግ የሚችል የመሬት ፖሊሲዎች እንዳሉን ግልፅ ነው፡፡ ይህ ወጣቱን ከፍተኛ የምርጫ ሀይል ሊያደርግ የሚችል በውጭ ያለ ዕድል እና በፓርቲዎች ውስጥ ያለ ጥንካሬ ነው፡፡
ሌላው ለምሳሌ በከተማ ውስጥ ያለው ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት የሚችል አማራጭ ፖሊሲ ብቻ ሳይሆን አሁን በተገነቡ ኮንዶሚኒየም ቤት አግኝተው የሚኖሩ ዜጎች የገጠሩን ህዝብ በመሬት እንደያዘው ሁሉ የከተሜውን የኮንዶሚኒየም ጠርንፎታል፡፡ የኮንዶሚንየትም ቤቱን ለአምስት ዓመት እንዳይሽጥ፤ እንዳይለውጥ፤ በባንክ እንዳያሲዝ የሚያደርግ ፖሊሲ አለው፡፡ ይህ በእርግጠኝነት የአንድነት ዓይነት ፓርቲ ስልጣን ቢይዝ በወራት ውስጥ ቀይሮ ሁሉንም የቤቱ ባለቤት የሚያደርግ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት የሚታይና የሚጨበጥ እርምጃዎችን የሚያሳዩ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ይኖርብናል፡፡ አንድነት ከዩኒቨርሲቲ ስትመረቁ ኮብል ሰቶን /ድንጋይ ፈለጣ/ ትገባላችሁ አይልም፡፡ ድንጋይ ለመፍለጥ አራት ዓመት ዩኒቨርሲቲ መቆየት አያስፈልግም፡፡ እንደ አማራጭ የስራ መስክ ሆኖ ለሌሎች ይቆያል፡፡ የተማሩ ዜጎች ስራ እንዲይዙ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ የግል ባለሀብቶች ግልፅ በሆነ አስራር እንዲሰፋፉ ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ ሀገር ማለት ህዝብ ነው ስንል ዜጎች ለዜጎች የስራ እድል የሚፈጥሩበት ማለታችን ጭምር ነው፡፡
ለዛሬ በዚሁ ይብቃኝ!!!!! ቸር ይግጠመን!!!!