Wednesday, April 29, 2015

የኦሮሞ ጉዳይ …. መፅሃፍ እና የፀሃፊው የሰለሞን ሰዩም የኦነግ ፍቅር

ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com, girmaseifu.blogspot.com
እውነቱን ለመናገር የሰለሞን ሰዩምን የመጀመሪያ ክፍል መፅሃፍ ሳነብ ትዝ ያለኝ በአንድ ወቅት “ኮንዶም ኤች.አይ.ቪ አይከላከለም” የሚል መፅሃፍ የፃፈውን እብድ ሰው ነው ያስታወሰኝ፡፡ ፀረ ኮንዶም የሆነ አሰተሳሰብ ያላቸው አብዛኞቹ የሀይማኖት አክራሪና “ፕሮ ላይፍ” በመባል የሚታወቅ የአሰተሳሰብ ዘርፍ ደጋፊ ሰዎች የፃፉትን ሰብሰቦ በማስረጃ የተደገፈ በሚል ነበር ኮንዶም ኤች አይ ቪን አይከላከልም እያለ ህዝቡን ለማሳሰት የሞከረው፡፡ አሁንም ሰለሞን ሰዩም ፅንፈኛ የኦሮሞ ነፃነት አቀንቃኞች እና “አማራ ጠል” አስተሳሰብ አራማጆችን እየጠቀሰ ኦሮሞ በእቅድና በዝግጅት ኢትዮጵያ በምትባል ሀገር አማራ በሚባል ገዢ መደብ ስትረገጥ ነበር ሊለን ይሞክራል፡፡ እግረ መንገዱንም በእርግጥ ይህን የሚፅፈው እኔ የማውቀው ሰለሞን ሰዩም ነው? የሚል ጥያቄም ጭሮብኛል፡፡
ሌላው ጥያቄ የጫረብኝ ሰለሞን ስዩም መፅሃፍ ፅፎ ግዙ ካለ በኋላ ሃሳቤን ለመቅረፅ ነው ያለውን ዘመነኞቹ “ላይክ” አድርጌዎለሁ የሚሉት አይነት ፌዝ ይጋብዛል፡፡ ለማነኛውም እኔ ደግሞ የወደድኩለት የፈለገውን ብሎም ቢሆን ኢትዮጵያችን በኦሮሞነት የበለጠ የምታምር መሆኑን ለማሳየት መሞከሩ ነው፡፡ እርሱም የዚሁ አባል እንደሆን በገደምዳሚ የነገረን በጋራ ቤት የመኖራችን ሚስጥር ገልጦልኛል፡፡
ሰለ ኦሮሞ ብሔርተኝነት እና የአማራ ገዢ መደብ
ሰለሞን ሰዩም የአማራ የበላይነት ሲባል ገዢ መደቡን ነው ብሎ በመግቢያ ላይ ቢነግረንም እዚህም እዚያም የአማራ የበላይነት ለመታገል በሚል የኦሮሞ ብሔርተኝነትን የሚገልፅበት መንገድ አማራን እንደማያሸማቅቅ ሊነግረን አይችልም፡፡ የትግራይ ነፃ አውጪዎች ትግል የአማራ ገዢ መደብ ሲሉ ሊደግፋቸው የተሰበሰበው ህዝብ እንዴት አድርጎ “አማራ ጠል” እንዲሆን እንዳደረጉት አብሮን ያለ እውነት ነው፡፡ ሰለሞንም በገፅ 153 ላይ በግልፅ “የሆነው ሆኖ የገዢ መደብ ቡድኑ የተገኘባቸው ዘውጌዎች፣ ቁሳዊ ጥቅም ባያገኙም ሰነ-ልቦናዊ ገዥነት መላበሳቸው ተፍጥሯዊ በመሆኑ ምንም ነገር አልተጠቀመሙ ማለት አይቻልም፡፡” በሚል አስቀምጦታል፡፡ ይህ ደግሞ በመግቢያው ላይ “የአማራ ገዢ መደብ፣ ከአማራ ህዝብ ጋር አንድ አድርጋችሁ አትውሰዱ” ካለው ጋር ይቃረናል፡፡
ሰለሞን በኦሮሞ ላይ የደረሰውን ግፍ ለማጉላት ከ30 ሚሊዮን ኦሮሞ የሶስተኛ ደረጃ ትምህርት ያገኘው 0.01 ከመቶ በታች ነው ብሎ ያልተሟላ ማስረጃ ቢጠቅስም የሌሎች ብሄሮችንም የመቶኛ ድርሻ ማሰቀመጥ ይገባ ነበር ብሎ የሚጠይቅ እንዳለ አልተረዳውም፡፡ በኦሮሞ ላይ የደረሰ በደል ጥልቀት ለማሳየት “ኦሮሞ በአበርክቶው እንዳይኮራ፣ ብሔረተኝነቱ እንዳያብብ፣ ባህሉን የማናናቅ፣ በራስ የመተማመን ሰሜት የመሸርሸር ስራ የተተገበረው በተጠና ዘዴ እንደነበር የሚናገሩ አሉ፡፡” ይልናል፡፡ ነገር ግን ይህን ጥናት ማን አስጠና? ማን አጠና? የጥናቱ ሰነድ አለ ወይ? ተብሎ ሳይጠየቅ ለኦሮሞ ብሔርተኝነት ወደፊት አለማለት የአማራ ገዢ መደብ በሚል አማራን ለመክስስ እጅ መጠንቆል ከሰለሞን የሚጠበቅ አልመሰለኝም፡፡ ለዚህ ደግሞ ፅንፈኛ የኦሮሞ ነፃ ሀገርነት የሚደግፉ ሰዎችን ፅሁፍ መጥቀስ ሚዛናዊ አያደርግም፡፡ የበለጠ ያስገረመኝ “በተለይ እስከ 19983 ድረስ የኢትዮጵያ መንግሰት የአማራ ገዢ ልሂቃን መንግስት ብቻ ነበር፡፡” (ገፅ 22/23) የሚለው የሰለሞን ድምዳሜ ኢህአደግ ተጨፈኑ ላሞኛቹ እንደሚለው ዓይነት ሆኖብኛል፡፡ ሁሉን ትተን ደርግ ዘውጊያዊ ማንነት የነበረው ስብሰብ ነበር ለማለት የምናውቀው ሀቅ ይተናነቀናል፡፡ በሳበ ፊደልም ቢሆን ኦሮምኛ ይፃፍ እንደነበር በግሌ አውቃለሁ፡፡ የኦሮምኛ ሬዲዮ ፕሮግራም ነበር፡፡ በቂ አልነበረም ያስማማናል፡፡ በሰለሞን መፅሃፍ ውስጥ የቁቤ ፊደል ከሳባው ፊደል የተመረጠበትን እውነተና ምክንያት አግኝቻለሁ፡፡ ይህም ክፍሌ ጆቴ “በኦሮሞ ህዝብ የስነ-ልቦና ነፃነት ወሳኝ ነው፡፡” በሚል የቀረበው ነው፡፡ አማራ ገዢ መደብ ጨቋኝ ተደርጎ በተሳለበት አግባብ አማርኛ በሚፃፍበት የሳባ ፊደል ኦሮሚፋን መፃፍ የሚፈለገውን የሰነ ልቦና ነፃነት አይሰጥም ሰሜት ይስጣል፡፡  
የኦሮሞ ጠልነትና የኦሮሞ ጥላቻ በተደራጀ ከላይ በጠየቁት መሰረት በጥናት ባይሆንም በምድር ላይ ያልነበረ ውሸት ነው ብዬ ልሞግት አልችልም፡፡ አንድ አንድ ጓደኞቼ እኔ የኦሮሞ ደም እንዳለኝ ሳያውቁ፣ አንድ አንዶች አውቀው ለነገር ፍላጋ የሚናገሩት ነገር እንዳለ አውቃለሁ፡፡ የግል ገጠመኞቼም ነገር ከማባባስ አልፍ ድምዳሜ ስለማያደርሱ እዚህ መጥቀስ ተገቢ አይደለም፡፡ በተመሳሳይ ግን በኦሮሞዎች ዘንድ ኦሮሞ ከሁሉም የሚበልጥ ምርጥ ነው፣ የተፈጥሮ ሀብት በተለየ ሁኔታ ያለው፣ ሌላው ለዝንብ ማረገፊያ ቅጠል የሌለው እስኪመስል ድረስ ፅንፍ የያዙ ነገሮች አሉ፡፡ አሁንም በግልፅ በኦሮሚያ ክልል የሚታይ “ኦሮሞ ያልሆነን ጠልነት” የምንታዘበው ነው፡፡ ለማነኛውም ሰለሞን ሰዩም “ግማሽ መንገድ የመጣውን ኦሮሞ፣ የአንድነት ሀይሎችም ግማሽ መንገድ ሄደው ይቀበሉት” ቢልም አሁንም ሰለሞን መምጣቱ ልክ ቢሆንም ኦሮሞ እንደ ህዝብ ወደ ግማሽ እንዲመጣ የማይፈልጉ፣ ሌላውም መጥቶ በፍቅር መኖራችን የሚያባንናቸው እንዳሉ መርሳት የለብንም፡፡ እንደ አንደ ኦሮሞ እና እንደ አንድነት ሀይል አቀንቃኝ እኔ በማራምደው አስተሳሰብ አንድ የኦሮሞ ልጅ የሚጎዳ ከሆነ አንገቴን እሰጣለሁ፣ ኦሮሞ ስለሆነ ሳይሆን ሰው ስለሆነ ብቻ፡፡ እርግጠኛ መሆን ያለብን ግን ጉዳዩ የአማራና የኦሮሞ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሁሉም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔሮችና ብሔረሰቦች እና ኢትዮጵያችን ነች፡፡ ይህን የምለው በፍፁም የአማራ ገዢ መደብ ከሚለው አስተሳሰብ ጋር ስለማልስማማ ነው፡፡ አማራም አማራነቱን ሳይተው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ኦሮሞም ኦሮሞነቱን ሳይተው ኢትዮጵያ ነው፡፡ ለእኔ የኢትዮጵያዊነት ሰርተፊኬት የምጠይቀው የሚስጠኝ ምንም ገዢ መደብ የለም፤ ወዘተ ….
ለማነኛውም ሰለሞን ሰዩም ማለት የፈለገው በትክክል ገብቶኝ ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ጥያቄ የሚባል ነገር ተወው ባክህ የሚባል አይደለም፡፡ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት ሊስተናገድ የሚገባው የፖለቲካ አጀንዳ ነው ለማለት ነው፡፡ ዋናው ምሳሌ የኦሮሚያ ጉዳይ ቢሆንም ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ከአንድ ዓይነት ብሎኬት እንደተሰራ ቤት አይደለችም እያለን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ለመሆንም ማንነትን መልቀቅ አያስፈልግም የሚል ነው፡፡ ይህ የገባኝ ቢሆንም በኢትዮጵያ ብሔርተኛ ወይም ደግሞ የአንድነት ደቀመዝሙሮች ያላቸውን ደግሞ ባልተገባ ሁኔታ ለራሱ በገባው ወይም ደግሞ አክራሪ የኦሮሞ ነፃነት አቀንቃኞች የሰጡትን አስተያየት እያጣቀሰ ተገቢ ያልሆኑ ድምዳሜዎች ላይ እንደንደርስ ሊገፋን ሞክሯል፡፡ እኔ የአንድነት ደቀ መዝሙር ነኝ፡፡ በፍፁም የማንንም ማንነት ተለውጦ አንተ ኢትዮጵያዊ ብቻ ነህ እንዲባል አልፈልግም፡፡ አሜሪካዊ ሲባል አይሪሽ መሆኑን፣ አፍሪካ አሜሪካ መሆኑን ደብቅ ተብሎ ያውቃል፣ እኛስ ለምን?
የሰለሞን ግራና ቀኝ ትንተና
የሰለሞን ግራና ቀኝ ትንተና የራሱ በገባው ያሰመረው እንጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባቦት የተደረሰበቱ አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ፅሁፍ ስል የተለየ ንባብ ሳያስፈልገኝ አሁን ባለው ሁኔታ ቀኝና ግራ ትንተና የማውቀው “ግራ” የሚባሉት ወደ ኮሚኒስት አስተሳሰብ የሚያዘነብሉ ሲሆን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና ፖለቲካ ትንተናቸው ይህንኑ መሰረት ያደረገ ነው፡፡ “ቀኝ” የሚባሉት ደግሞ በካፒታሊሲት ርዕዮት የሚከተሉ ወይም ወደዚያ የሚያጋድሉ ናቸው፡፡ እነርሱም የኤኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የፖለቲካ ትንተናቸው ይህንኑ መስረት ያደረገ ነው፡፡ በእነዚህ ሁለት ጥጎች አማካይ የሚባል ቦታ አለ፡፡ ይህ ማዕከል ግን ሀሳባዊ ነው፡፡ አሁን ባለው የዓለም ሁኔታ የሶሻሊሰት/ኮኒሚኒስት የሚባሉ ሀገሮች በብዛት/በተግባር የሉም ካሉም በእጅ ጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ሰለዚህ በዓለም ላይ የሚደረጉ ቀኝና ግራ ዘመም ትንተናዎች ከአሳባዊው አማካይ ተነስቶ ወደ ቀኝ ነው፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ የእኛው ሀገር አብዮታዊ ዲሞክራሲም ምናልባት በተግባር ሃሳባዊው አማካይ አካባቢ ቢገኝ እንኳን በሀሳባ ግን በአካባቢው የለም፡፡ ምን አልባለት ግራ ሰፈር ሊገኝ ይችላል/አልባኒያ ሶሻሊዝም እያሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በሰለሞን ሰዩም ትንተና ኢህአዴግ ግራ የገባው ግራ አንጂ ቀኝ ሊሆን አይችለም፡፡
ሰለሞን ስዩም በተጨማሪ “የ1960ዎቹን በጅምላ ግራ ዘመም ማለት ልክ አይደለም”(122)ይላል፡፡ ልክ ለመሆን የፈለገ ሁሉም የሶሻሊስት/የኮሚኒዝም አቀንቃኝ ነበሩ ስለዚህ ግራ ዘመም ብቻ ሳይሆን ግራዎች ናቸው፡፡ ሰለሞን እንደ መነሻ የወሰደው ግራኞች ተራማጆች፣ ቀኞች ደግሞ አድሃሪያን (ሪአክሽነሪ) የሚለው ፍረጃን ነው፡፡ ይህ ፍረጃ የግራዎቹ ኮሚኒስት አስተሳሰብ ያላቸው ለራሳቸው ያወጡት የተሳሳተ ሰያሜ ነው፡፡ ሰለሞን በምሳሌ ያቀረባቸው “ኮንሰርቫቲቭ” እና “ሌበር” የሚባሉት ሁለቱም ከሴንተር/ከአማካይ በስተቀኝ ባለው ሰፍር በተወሰነ ርቀት የሚለያዩ ናቸው፡፡ በውስጣቸው ግራና ቀኝ ዘመም ሲባል እንኳን ከአማካዩ ባላቸው ርቀት እንጂ በፍፁም ሶሻሊስት/ኮሚኒስታዊ ርዕዮት ቅርበት አይደለም፡፡ የእኛዎቹ ኢህዴጎች ግን ከአማካዩ በግራ ብቻ ሳይሆን እዛም ውስጥ ግራ የገባቸው መሆኑ ነው፡፡ ግራ መሆናቸው ማሳያው ለመድበለ ፓርቲ ስርዓት ያላቸው ግዴለሽነት/አስመሳይነት፣ ለነፃ ኢኮኖሚ የመንግሰት ጣልቃ ገብነት ፍቅር፣ አጭበርባሪ የሆነ ህዝባዊ ህዝባዊ የሚሉት ምሽግ፣ ብዙ ሊባል ይችላል፡፡
ብሔረተኝነት ግራ ዘመም የሚያሰኘው ነገሩን ከግለሰብ ነፃነት መልስ ከመስጠት ይልቅ እንደ ስታሊን በቡድን ሀስተሳሰብ ውስጥ  ስለተገለፀ ነው፡፡ በራሱ ግን ግራና ቀኝ መመደቢያ ሊሆን አይችልም፡፡ በተለይ አሁን ባለው የሃያ አንደኛ ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ አንፃር የግለሰብ መብት ሲከበር የቡድን መብት ይከበራል ከሚል ድፍን ሎጂክ ዘለል ብሎ የቡድን መብቶች በአንድ አንድ ወሮበሎች እንዳይደፈር ጥበቃ እንዲደረግለት ዋስትና መስጠት ዘመናዊነት እንጂ ቆመ ቀርነት ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህም መነሻ ብሔረተኞች ግራ ወይም ቀኝ ለመባል ሌሎች ተጨማሪ መስፈርቶች መጠየቅ አለባቸው፡፡ ለምሳሌ የሰካንዲኒቪያን ሀገሮች ኮሚኒሰታዊ/ሶሻሊስታዊ አስተሳሰብ የላቸውም ነገር ግን ወደ አማካዩ ከቀኙ የመቅረብና የመራቅ ጉዳይ ነው ግራ ዘመም፣ ቀኝ ዘመም የሚያሰኛቸው፡፡ ብዙዎች የሚሳሳቱትም በዚሁ መስመር አረዳድ ችግር ይመስለኛል፡፡ ሰለሞን “ያ አንድነት” በማለት የጠቀሰው የእኔ እና የሰለሞን አንድነት ይህን በቅጡ የተገነዘበ ፓርቲ ነበር፡፡ በኢህአዴግ ልክ ስለአልተሰፋ አደገኛ ሆኖ ተገኝቶ ፖለቲካ ውሳኔ ባይሰጥበት፡፡
የሰለሞን የኦህዴድ ጥላቻና የአለማየሁ አቶምሰ ፍቅር
ሰለሞን ሰዩም ለኦህዴድ ያለውን ጥላቻ እና ለአለማየሁ አቶምሳ የሚያሳየው ፍቅር እኔና ዳዊት ሰለሞን ክትፎ በፖፖ የምንለውን ያስታወሰኝ፡፡ ይህ አባባል በእርግጥ ያመጣው የአዲስ አበባ ህዝብ ነው፡፡ ኤርሚያስ ለገሰ የሚባል የኢህአዴግ ውስጥ አዋቂ ሰል አርከበ እቁባይ መረጃ እያወጣ ጥርጣሬ ውስት ከመክተቱ በፊት አቶ አርከበ ለአዲስ አበባ ህዝብ ጥሩ ነበሩ ይባል ነበር፡፡ ታዲያ ምን ያደርጋል ኢህአዴግ ናቸው፡፡ ሰለዚህ ክትፎ በፖፖ አይበላም ብሎ የአዲስ አበባ ህዝብ እርሰቸውን እንኳን በ1997 ምርጫ ሳይመረጥ ቀረ፡፡ አሁንም የሰለሞን ሰዮም ስለ አለማየሁ አቶምሳ የሚያቀርበው ተረክ መለስ ዜናዊ ከሙሰና የፀዳች ኦሮሚያ እንድትኖር ይፈልግ ነበር የሚያስብል ይመስላል፡፡ ሰለሞን ሰዩም ለሌንጮ ለታም ያለውን ፍቅርና በተለይ ለአዲሱ ፓርቲ ልቡ ክፍት አንደነበር መረዳት አይገድም፡፡ አለማየሁ አቶምሳም በህይወት ቢኖር የኦዴግ ይሆን ነበር የሚል ነው የሚመስለው፡፡ በእኔ እምነት ሌንጮ ከአዲሱ ፓርቲ ጋር በአዲስ አስተሳሰብ መጥቻለሁ ሲል የድሮ ያስከፈለውን ውድ ዋጋ ተረክ ተርኮልን፤ ካስፈለገም አፉ ብለን መሆን አለበት፡፡ ከኦህዴግ ጋር ተሻርኮ በጓሮ በር ለመግባት መሞክር ቅቡል አይመስለኝም፡፡ ሰለሞን ያንገበገበው በእስር ቤት ኦሮምኛ መስፋፋት የኦነግ ጦስ ጭምር ነው፡፡ ኦነግ እሰሩልኝ ብሎ ባይሆን እንኳን በሰሙ ጭዳ መሆናቸውን ሌንጮ ያጣዋል ብዬ አልወስደውም፡፡
ለማነኛውም የሰለሞን ሰዩም መፅሀፍ በተሟላ ሁኔታ “የኦሮሞ ነፃነት አቀንቃኞችን” የፃፉትን ፅሁፎች  በአማርኛ፣ በእንግሊዘኛም ሆነ በቁቤ የተፃፉትን በሚያስባስብ መልኩ ከዚህ በተሻለ ዝርዝር ቢያቀርበልን በተለይ ቁቤ ለማይገባን ለእኛ ምስኪኖች ጥሩ ድጋፍ ይሆን ነበር፡፡ ከዚህ መለስ ያለውን የመፅሃፍ ክፍል በፋክት ላይ ቀርበው ለነበሩት ሙግቶች የተሰጠው መልስ አልተመቸኝም፡፡ አንደኛ በእርግጥ ያስፈልግ ነበር ወይ? የሚል ሲሆን፤ በማስከተልም መልሱ በእርግጥ በተደራጀ እና በሞጋች መልኩ ለማስተማር የሚረዳ ነበር ወይ? የሚል ጥያቄዎች ያስነሳል፡፡ ሌላው እነዚህ ፀሃፊዎች የአማራ ገዢ መደብ የሚባለውን ይወክላሉ? በሚል ነው ወይስ ርዝራዦች በሚል? አልገባኝም ስለዚህ የመፅኃፉን ይህን ከፍል አልወደድኩትም፡፡ መብቴ ነው!!!!



Monday, April 27, 2015

ክርክር 6፡ ኢህአዴግ እና 1997 ስብርባሪዎች!!!!

በዛሬው ሰድስተኛ ዙር የምርጫ ተብዬ ክርክር ጉዳዩ በመሰረተ ልማት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ኢህአዴግ ጎምቱ ያላቸውን ሹሞቹን ለክርክር ይዞ የቀረበበት ቢሆንም ለእኔ ግን ትኩረቴን የሳበው የተከራከሩበት ርዕስ ሳይሆን ተከራካሪዎቹ ሰዎች እና ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ማለት የፈለኩት የመሰረተ ልማት በሚል ርዕስ ክርክር ስመለከት የተገነዘብኩት ጉዳይ ቢኖር ኢህአዴግ ክርክር እያደረገ ያለው የዛሬ አስር ዓመት ለሚዲያ ክርክር ድመቅት ይሰጥ ከነበረው ከቅንጅት ስብርባሪ ጋር አንደሆነ ተረዳሁኝ፡፡ ህብረትም ቢሆን አሁን በመድረክ በኩል በድሮ ግርማ ሞገሱ አይታይም፡፡ እውነቱን ለመናገር አሁን በክርክሩ ላይ የሚገኙት ሰዎች ኢህአዴግ በልኩ የሰራቸው፤ በእግራቸው ገመድ የተበጀላቸው ጭምር ናቸው፡፡ ምንም ቢሉ ማንም ምንም የማይሰማቸው፡፡
ኢዴፓ በ1997 ከተቀናቃኙ መኢህአድ ጋር ያለውን የውስጥ ግብ ግብ ቅንጅት የሚባል ፓርቲ እውን እንዳይሆን በማድረግ፣ አንድ አንዶቹን በግል ታሪካዊ የፖለቲካ ዋጋ አስከፍሎ አሁን ባለበት ደረጃ ይገኛል፡፡ ይህ የኢዴፓ አመራር ውሳኔ ኢትዮጵያ ሀገራችንም በመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ ዋጋ እየከፈለች እንድትገኝ አድርጓል፡፡ በሁለት ሺ ሰባት ምርጫ ኢዴፓ እንደ ፓርቲ መንግሰት እንደማይሆን ቢታወቅም ወደፊት ፓርቲስ ይሆናል ወይ? የሚል ጥያቄ ሁሉ ማንሳት የግድ የሚል ነው፡፡ ይህ በፍፁም ሟርት አይያደለም በምድር የሚታይ ሀቅ ነው፡፡ ለማነኛውም ኢዴፓ የዛሬ አሰር ዓመት በ1997 ክርክር የቅንጅት ፈርጥ ሆኖ ክርክሩን ያደመቀ ቢሆንም ዛሬ ይህን ሊያደርግ አልተቻለውም፡፡ ኢህአዴጎች በጥርስና ጥፍራቸው ቅንጅትን ሲያፈርሱ ያተረፉት ሽራፊ ኢዴፓ አሰር ዓመት አፈር ልሶ መነሳት ሳይችል ቀርቷል፡፡ አሁንም በምድር ላይ እየዳከረ ይገኛል፡፡
ኢዴፓ ማህተም አላደርግም በማለት ያፈረሰውን ቅንጅት ቢያንስ በፍረስራሽ በቅጡ እንዳይሰራ ያደረገው ደግሞ አቶ አየለ ጫሚሶ ነው፡፡ መቼም ይህን ሰም የማያውቅ ያለ አይመስለኝም፡፡ “ቅንጅት”  በአቶ አየለ ጫሚሶ ተወክሎ ቅንጅት ቢመረጥ እንዲህ ያደርጋል ይህን ይፈጥራል ሲሉን እኛ የምናወቀው የ1997 ቅንጅት የሌለ መሆኑን፤ የፈለግነው ቅንጅት እንዳይኖር የተሰራው “ቅንጅት” እንኳን ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅም አጀንዳ አይደለም እንደ ድርጅትም ቁመናውን አስተካክሎ የሚሄድ እነዳልሆን እናውቃለን፡፡ እውነቱን ለመናገር እነርሱም በሚዲያ ቀርበው አይተናቸዋል፡፡ ለማነኛውም ይሉሹን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ የሚባለው የዚህ ዓይነቱ ድርጊት ነው፡፡ የቅንጅት ምልክት የነበረው ሁለት ጣት አሁንም “ቅንጅት” ለሚባው ድርጅት ቢሰጥም በተግባር ግን በስራ ላይ እንደሌለ ይታወቃል፡፡ ትዝ ይላችሁ እንደሆን “ጣት እንቆርጣለን” እስክንባል ድርስ ይህች አስማተኛ ምልክት የዛሬ አስር ዓመት የሰራቸው ስራ በእውነት ግሩም ድንቅ ነበር፡፡ የእኛን ቅንጅት ነብስ ይማር ብለናል፡፡
መድረክ አሁን ባለው ቁመና የ1997 ህብረት ሰዎች በተወሰነ ደረጃ ቢይዝም ህብረትን የሚያክል አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ከምርጫ በኋላ ቅንጅት የሚባል እንዳይኖር የአሁኖቹ መድረኮች ያላቸው ጥላቻ ቀላል አይደለም፡፡ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ አሁንም ቢሆን ከቅንጅት መንፈስ ጋር ግብ ግብ ላይ እንዳለ ማወቅ የፈለገ የ1997 ጫወታ አንስቶ መሞከር ነው፡፡ በሌሎቹም የህብረት አባል ድርጅቶች እሰከ ፓርላማ የደረሰ ደባ በቅንጅት ላይ እንደሚሰራበት የሚታወቅ ነው፡፡ የዚህ ደባ ባለቤቶች አሁንም የመድረክ አባሎችና አመራሮች ናቸው፡፡ መድረክ አንድነትን ከሚጠላበት አንዱ ምክንያት በአንድነት ውስጥ የሚታየው የቅንጅት መንፈስ ጭምር ነው፡፡ የአሁኖቹ አመራሮች ከአንድነት ጋር ሲነነጋገሩ የሚሰማቸው ሰሜት በ1997 ህብረት ሆነው ከቅንጅት ጋር የሚያደርጉት ውይይት/ክርክር ነው፡፡ በክርክሩ ውስጥ ሁሌም ጠልፉ መጣል አለ!! የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ልዬ ችሎታ፡፡
አሁን ደግሞብ በብረት ሰንሰለት ተይዞ የሚገኘው ሰማያዊ ፓርቲ ነው፡፡ ሰማያዊ የት ድረስ ይጓዛል? አላውቅም፡፡ ሰማያዊ ፓርቲም ቢሆን የቅንጅት አብዛኛውን አመራርና አባል ይዞ የተመሰረተው አንድነት ፓርቲ ስባሪ ነው፡፡ ስለዚህ የቅንጅት አካል እንደነበር ማወቅ ያስፈልጋል፡፡  በሁለት ሺ ሁለት ምርጫ አንድነትን ምርጫው ላይ ውጤታማ እንዳይሆን ከኢህአዴግ ባልተናነሰ ገትረው የያዙት ልጆች ሳይዘገዩ በአምስተኛ ዓመቱ የምርጫ ፈተና ከኢህአዴግ ጋር እንዴት እንደሆነ እየቀመሱት ነው፡፡ በሆነ ባልሆነው ሰማያዊ የሚለው መንግሰትም ከሰማያዊ አልላቀቅ ብሎ ምን ሊያደርግ እንደሚችል እየተጠበቀ ነው፡፡ የኢህአዴግ ትልቅ ግብ በዚህ ምርጫ መንግሰት መመስረት የሚመስለው ካለ ተሳስቷል፡፡ ሰማያዊን ለማዋረድ ነው የሚሰራው፡፡ በኢቲቪ በሰማያዊ ላይ የተያዘው ዘመቻ የአንድ አንድ የህግ ባለሞያዎች ተብዬ አስተያየት ጥፍራችን ውስጥ እንድንደበቅ የሚያደርግ ነው፡፡ እረ በህግ መባል ያለባቸው ናቸው፡፡
ሌሎች ተሳታፊ ፓርቲዎችን ትተን ከላይ የዘረዘርናቸው ፓርቲዎችን ስንመለከት ኢህአዴግ የዛሬ አስር ዓመት ሰንገው ይዘውት ከነበሩ አሁን ግን ምንም ማድረግ ከማይችሉ ደካማ ስብርባሪ ፓርቲዎች ጋር ተራ ገብቶ እየተጫወተ ነው፡፡ ሁሌም እንደምለው ኢህአዴግ ብጤዎቹን በትክክል መርጦዋል፡፡ ከዚህ ከፍ ያለ ጫወታ አይችልም፡፡ ከዚህ ከፍ ካለ ኢህአዴግ ቀልድ አያውቅም ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ሲል ታንክም ባንክም ለመጠቀም ወደኋላ የሚል አይደለም፡፡ አሁን ለጊዜው በቁጥጥር ስር ያሉ ሚዲያዎች እና ሆዳሞች ይበቁታል፡፡ ታንክ አያስፈልግም ማለቴ ነው፡፡ ሚዲያና ሆዳሙን ለመጥቀም ያህል ባንክ ይጠቀም ይሆናል፡፡

ቸር ይግጠመን!!!!!

Friday, April 24, 2015

በዚህ ጊዜ እንኳን ኢትዮጵያዊያን በጋራ እንቁም …. ማለትም የፖለቲካ ቁማር ይቅር

ወዳጄ ከበደ ካሰ ዘወትር ወዳጄ ስልህ በግል ጠብ የሌለን የሀሳብ መስመራችን ግን አንድ አለመሆኑን በማስታወሰ ነው፡፡ ይህን አንተ እንደምትረዳው አውቃለሁ፡፡ አንድ አንድ አብረውህ በቡድን በሚመስል መልኩ የሚሳደቡትን ግን እንዳተ በግንባር ባላውቃቸውም ወዳጅነት ግን የሚኖርኝ አይመስለኝም፡፡ የሃሳብ ሳይሆን እነርሱ ጥቁረቴን ሁሉ የሚጠሉት ይመስለኛል፡፡ እጥረቴም ኢህአዴግን ለመቃወም ሆን ብዬ ይመስላቸዋል፡፡ ለማነኛውም በሪፖርተር ላይ  “ከአይኤስ” እኩል የማወግዛቸው …” በሚል ርዕስ ያሰፈርከውን ፅሁፍ አንብቤ በተረዳሁት መልክ መልስ ልሰጥህ ወደድኩ፡፡ ይህ በአስራ ሰድስት አንቀፅ ተክፍሎ የተፃፈን ፅሁፍ እንዲህ አድርጌ አየሁት፡፡
አንቀፅ አንድ ላይ በሰፈረው በሙሉ ተሰማምቻለሁ፡፡ በአንቀፅ ሁለት ላይ “በየትኛውም ሁለተኛ ሀገር በሰደት መኖር በሰላም ወጥቶ በሰላም ለመግባት ዋስትና አይሰጥም” በሚል መደምደሚያ የጀመርከው ግን በፍፁም ትክክል አይደለም፡፡ ለማሳያ ያቀረብካቸው ሀገሮች ላይ ትክክል ነህ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት አይቻልም፡፡ በዓለም ግን እጅግ በጣም ብዙ ሀገሮች የሰው ዘር በሰላም ወጥቶ በሰላም የሚገባባቸው ናቸው፡፡ በተለይ እናነትተ አብዮታዊ ዲሞክራቶች፤ ኒዎ ሊብራል እያልችሁ በምትሰድቧቸው ሀገሮች “ዜጋ” አይደለም ባጠቃላይ የሰው ልጅ በሰላም ወጥቶ በሰላም የሚገባባቸው ሀገሮች ናቸው፡፡ ይልቁንም ብዙዎቻችን በሀገራችን በሰላም ወጥተን በሰላም እንድግገባ ሃላፊነት ያለባቸውን የደህነነትና የፖሊስ ሀይሎች የምንፈራበት ሀገር ውስጥ የምንኖር መሆናችን ትንግርት የሚያሰኝ በምድር ላይ ያለ ሀቅ ነው፡፡ ይህ አስተያትህ ከልምድ ማነስ ነው ብዬ ለመውሰድ ፈቃደኛ ነኝ፡፡ አንድ ወዳጄ በውጭ ሀገር የሚኖር በአሜሪካን ሀገር የነጮች ዘረኝነት በግልፅ ይታየኛል፣ ነገር ግን በሀገሬ እንደሚሰማኝ ዓይነት በፖሊስና ደህንነት ክትትል እየተደረገብኝ አደጋ ላይ እወድቃለሁ የሚል ስጋት የለበኝም ነው የሚለው፡፡ በሀገራችን ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው የሚል ህገመንግሰታዊ ድንጋጌ ቢኖርም ከቤ አንተ እና አለቆችህ በህግ ፊት እኩል ናችሁ? በስልክ የሚያሳስሩ፣ በስልክ የሚያስፈቱ አለቆች አታውቅም? እውነት ብቻ ተናገር መወሻሸት አያስፈልግም፡፡
በሶሰተኛው አንቀፅ ላይ አሁን በሊቢያ የተፈጠረውን ጉዳይ የሙስሊም ጉዳይ አድርገው ሊያጣሉን ከሚፈልጉ ሀይሎች መጠበቅ እንዳለብን ያስቀመጥከው ትክክል ነው፡፡ ከዚህ የከፋም ሊመጣ ስለሚችል በፅናት በአንድነት መኖር ይኖርብናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የእነዚህ ሰማዕታት ደም ለአንድነታችን ማጠናከሪያ በማድረግ ጠላቶቻችንን ማሳፈር ይኖርብናል፡፡ ከአይኤሰ እኩል የማወግዛቸው ያልከው እነዚህን ስለሆነ ተሰማምቻለሁ፡፡ በማስከተል የፖለቲካ ቁማርተኞችን እንደምታወግዝ በትክክል አስቀምጠህ ቁማርተኛውን መረጣ ላይ ግን አድልዎ አሳየተሃል፡፡ ለአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር ተገዥነትህን በግልፅ አስቀመጥክ፡፡ አሁን ድረስ በእነዚህ ወንድሞቻችን ደም የፖለቲካ ቁማር እየተጫወተ ያለው ማን ነው?
በዚህ ፅሁፍ በግልፅ የተረዳሁት ነገር ብዕር ያነሳኽው የአሁኑ የምታገለግለውን ድርጅት ኢህአዴግን/ገዢውን ፓርቲ እና የቀደሞ መስሪያ ቤትህ ኢቲቪን ለመከላከል ነው፡፡ ይህ ግን በፍፁም አልተሳካልህም፡፡ በመጀመሪያ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ላጣራ ያለው መንግሰት እስከ አሁን እንዳላጣራ የሚያሳብቀው ሟቾች ኢትዮጵያዊያን መሆናችው ቢታወቅም አሁንም ሁሉም ክርስቲያን መሆናቸው የሚያረጋግጥ መረጃ አልወጣም ብለሃል፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆናቸው በሆነ መንገድ ከተጣራ እነዚህ ሰዎች ሙስሊም ይሁን ክርስቲያን እንዴት መለየት ያቅታል? ሌላው በፍፁም መሸሽ የፈለከው የፖለቲካ ቁማር እየተጫወተ ያለው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ መሆኑን መግለፅ ነው፡፡ ይህን በፍፁም አታደርገውም፡፡ ሰደተኝነት ምንጩ በ24 ዓመት ለብሔራዊ ውርደት የዳረገንን ድህነት ማስወገድ ያልቻለው ኢህአዴግ እንጂ በ17 ዓመት በጦርነት ተወጥሮ የነበረው ደርግ ሊሆን አይችልም፡፡ አሁን በስደት የሞቱት ደግሞ የኢህአዴግ ትውልዶች ናቸው፡፡ ሀገር ጥላችሁ አትሂዱ ሰራ በሀገር ሞልቶዋል እያለ የልማት ፖለቲካ የሚነዛ ያለውም ኢህአዴግ እና መንግሰት ነው፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ቁማርተኞች መሆናቸውን ማመን አልፈለክም፡፡ በቅርቡ በስደት ላይ ሜዲትራኒያን ባህር ከገቡት ሰዎች ውስጥ ሶሪያ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ፣ ወዘተ በዋነኝነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በእነዚህ ሀገሮች የፖለቲካ ጉዳይ ሆኖ በእኛ ሀገር የህገወጥ ደላላ ጉዳይ ብቻ የሚሆንብት ምክንያት ልታስረዳኝ ትችላለህ
ኢቢሲ/ኢቲቪን ለመከላከል የሄድክበት መስመር ከቤ አንባቢዎችን እንደመናቅ ነው፡፡ መንግሰትን መግለጫ ነው ያነበበው ኢቢሲ ብትል ያዋጣህ ነበር፡፡ ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን አይለቅም እንደሚለው፣ እነዚህ የሞቱት ኢትዮጵያዊያን ቢበዛም በአሁኑ ቋንቋን ኤርትራዊ ወንድሞቻችን እንደሆኑ እየታወቀ ይህን ስብራት እንዴት እንቻለው መባል ሲገባው፣ ህገወጥ ስደተኞች ትምህርት የሚወሰዱበት ይሆናል እየተባለን፤ ዳግም የሳውዲ ቁስላችን እየተቀሰቀሰ፤ ይህን የሚያቀርብ ኢቲቪን ከሌሎች ዓለም አቀፍ ዜና አውታሮች ጋር ለማነፃፀር መሞከር ተገቢ አልመሰለኝም፡፡ ለማነኛውም እኔም እንደፖለቲከኛ ከዚህ ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚገኝ ፖለቲካ ትርፍ ይኖራል የሚል እምነት ባይኖረኝም፡፡ የፖለቲካ ጦስ ያመጣውን ሰደት ግን በህገወጥ ደላላ ላይ ብቻ ደፍድፎ እራሰን ነፃ ማውጣት አይቻልም፡፡ ይህ የሰብዓዊነት ጉድለት ያመጣ ፖለቲካ ደግሞ ጥንብ እርኩሱ ቢወጣ ምንም ቅር አያሰኝም፡፡ በነገራችን ላይ ከቤ ፖሊስ አውጪ እና ተግባሪ ፖለቲከኞች ተጠያቂነታቸውም ይለያያል፡፡ አንተ ለአቅመ ፖሊሲ አውጭነት ያልደረስክ ስለሆነ ይህ እንደ ኢህአዴግ አባል አይመለከትህም አትጨነቅ፡፡
ለማነኛውም አህአዴግ በ24 ዓመት ጉዞ በቂ ስራ መፍጠር ያልቻለ ፓርቲ ነው፡፡ እራሱ ባመነው ስሌት ብንሄድ የዛሬ 10 ዓመት ከድህነት መውጣት ከቻልን፣ ዛሬ ከድህነት ያልወጣነው ኢህአዴግ ከ1983-1993 ባሉት አሰር ዓመታት ምንም ስራ ባለመስራቱ ነው፡፡ ብተፈልግ እነ ገብሩ እነ ስዬ አላሰራም ብለዋቸው ነው ማለት ትችላለህ፡፡ አሁንም ቢሆን ገዢዎች የራሳቸውን አቅም ለማጎልበት እንጂ ትኩረታቸው የህዝብ ችግር ለመፍታት አይደለም፡፡
ባጠቃላይ ወደጄ ከበደ ካሳ “ከአይኤስ እኩል የማወግዛቸው ….” ብለህ ርዕስ የሰጠህው ፅሁፍ በዋነኝነት ይህን አሳዛን ክስተት ህዝብ ከህዝብ በእምነት መስመር የሚያጋጩትን እና በዚህም የፖለቲካ ቁማር የሚጫወቱ ፖለቲከኞችን ማውገዝ እንደሆነ ብረዳም፡፡ ዋነኛ የፖለቲካ ቁማርተኞቹ አለቆችህ እና አንተው እራሰህ መሆናቸውን የዘነጋህ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ በዚህ የሀዘን ጊዜ አብረን እንዳንቆም አንድ አንድ ሀይሎች እያላቸሁ መከፋፈላችሁን ትታችሁ እኛ ኢትዮጵያዊያን በሚል እንዲተካ አደራ ጭምር እጠይቃለሁ፡፡ አሁን ለተፈጠረው ችግር ሰደት አንዱ መፍትሔ ሲሆን አሳዳጁ ደግሞ ፖለቲካ ስለሆነ የፖለቲካ መሪ የያዙ ሰዎች ተጠያቂነት እንዳለባቸውም መዘንጋት የለበትም፡፡ ከቤ ይህን ያህል ካልኩ ይበቃል፡፡ ከምስጋና ጋር ለዝርዝር www.girmaseifu.blogspot.com.


Tuesday, April 21, 2015

ክርክር አምስት መልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነት ግርማ ሠይፉ ማሩ



girmaseifu32@yahoo.com; girmaseifu.blogspot.com
ተሳታፊዎች
·         ወልዴ ዳና  እና ሰለሞን ታፈስ             ከአትፓ  
·         ዋሰይሁን ተሰፋዬ ወንዶሰን ተሾመ        ከኢዴፓ
·         ይድነቃቸው  ከበደ                          ከሰማያዊ
·         ብርሃኑ በርሄ እና ደጀኔ                     ከመድረክ
·         አሰቴር ማሞ እና አባይ ፀሓዬ              ከኢህአዴግ
የሚያዚያ ዘጠኝ ቀን 2007 ክርክር እንዳበቃ አንድ አንድ ነዋሪዎች አስተያየት በሚል በኢትቪ የቀረበው ዜና አስቂኝ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ፕሮግራሙ በተላለፈ እለት እንዴት አድርገው ይህን ሊሉ ቻሉ? የሚለው ዋነኛ ጥያቄ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ፓርቲ ነው (ተሳስቼ አይደለም ሃሳብ የሰጠች የአዲስ አበባ ነዋሪ ነች እንዲህ ያለችው)፣  ሰማያዊ ፓርቲ የአባይ ግድብን ማጣጣል ተገቢ አይደለም ተብሎዋል.፤ የብሔሮችን እኩሉነትን የማይቀበል ሰማያዊ ፓርቲ፤ ወዘተ የሚሉ አስተያየቶች የሚያሳዩት ሰማያዊ ፓርቲ ላይ የተያዘው ዘመቻ ግቡ ምን እንደሆነ እየቆየን እንደምናየው ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የሚከረፋው ኢቲቪ የሚባል የመንግሰት የሚዲያ ተቋም ይህን ያህል መውረዱ ብቻ ሳይሆን ለዚህ ተሳታፊ የሚሆኑ ሰዎች ያለማጣታችን ነው፡፡ ቢፈልጉ ፎረም የፈለጉትን ሊሆኑ ይቸላሉ ….. ይህች ሀገር ትንሳኤ የምታገኘው የዚህ ዓይነት ውርድት አንቢ የሚል የሀቅ፣ የነፃነት ሠራዊት ሲበዛ ነው፡፡
ከመንግሰቱ ሀይለማሪያም ቀጥሎ በኢትዮጵያ ከፍተኛውን ስልጣን የያዘው ማን ነው? ቢባል መለስ ዜናዊ ያለ ልክ ሊሆን ቢችልም አሁን ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ናችው ብሎ ማንም ስህተት አይሰራም፤ ከጠቅላይ ሚኒሰትሩ በለይ ፈላጭ ቆራጭ የሆነ ስልጣን ያለውን ሰው የመድረኩ ተከራካሪ በይፋ ተናግረዋል፡፡ የስልጣኑን ዝርዝር የሚታወቅ ስለሆነ መዘርዘር አያሰፈልግም ብሎኛል አንድ ወዳጄ፡፡ ይደር በሚል!!!!
ኢህአዴግ ለክርክር ይዞ የቀረበው አቶ አባይ ፀሃዬ የመልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነት ክርክር ላይ በግንባር ቀደምነት ይገኛሉ ብዬ አልገመትኩም፡፡ እነዚህ ሁለት ጥንድ ርዕሶች የራሳቸው ጌቶች አላቸው፡፡ አንደኛው እንደገመትኩት ወ/ሮ አስቴር ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ የፍትህ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ ይሆናሉ ብዬ ነበር፡፡ ብአዴን በዚህ ቦታ የሚያስቀምጣቸው ሰዎች የተሳካላቸው አልመሰለኝም፡፡ በአምስት ዓመት አንዴ በሚመጣ በህዝብ ፊት አንደበተ ርዕቱነት፣ታጋሽነትን፣ ወዘተ ሊፈተንበት የሚችል የአደባባይ መድረክ የፍትህ ሚኒሰትሩ ሊያገኙት አልቻሉም፡፡ የዚህ ውስጠ ወይራ አቶ ጌታቸው አይችሉም ብቻ ሳይሆን እርሳቸው በህግ የበላይነት ዙሪያ ከህውሃት ኢህአዴግ የበለጠ የማስረዳት የባለቤትነት ጉዳይም ጭምር ነው የሚመስለው፡፡
ሌላው ውስጠ ወይረ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ሚኒስትር የሆኑት የኦህዴድ “ዋና” ሰው ወ/ሮ አስቴር ማሞ ቀደም ሲል የኮርፖሬሸን ስራ አስኪያጅ አሁን በተፈጠረው የቡድን አመራር የጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ ዋና ተከራካሪነት እርሳቸው በምክትልነት ተከራካሪነት ቀርበው አይተናቸዋል፡፡ አንድ አንድ ጊዜ የኦሮሞ ልጆች ለምሳሌ ወዳጄ ሰለሞን ስዩም ትልቅ ህዝብ ትንሽ ፓርቲ የሚለውን ኦህዴድ አግኝቼዋለሁ፡፡ ለማነኛውም የጎንደር አማርኛ የሚናገሩት ወ/ሮ አስቴር ማሞ ይህ የደረጃ ጉዳይ ነው ለምን? እንዲህ ይሆናል አላሉም አይሉምም፡፡ ፓርቲያቸው በመደባቸው ቦታ ይስራሉ፣ ይታዘዛሉ፡፡ እምቢ የሚባል ነገረ ቦታ የለውም፡፡
እስከ አሁን ባሉት ክርክሮች ያሰጠላኙ ነገሮች መካከል ኢህድግም ሆኑ ተቃዋሚዎች እንኳን አደረሳችሁ ለአምስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚሉት ቀልድ፣ ኢህአደግ በግሉ አማራጭ የሌላቸው ተቃዋሚዎች እና ተቃዋሚዎች በሙሉ ደግሞ ብንመረጥ እንዲህ እናደርጋለን ብሎ መዋሸት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
በዚህ ክርክር ነጥብ ያሰቆጠሩት ተከራካሪዎች የኢዴፓው ዋስይሁን እና የሰማያዊ ይድነቃቸው ቢሆኑም የኢህአዴግ ተከራካሪዎች ትኩረት ያደረጉት ግን በሰማያዊ እና በመድረክ ላይ ነበር፡፡ ለምሳሌ ሰማያዊና መድረክ ሀገር የመምራት ብቃት አላችሁ? የሚል ጥያቄ በኢህአዴግ ሲቀርብባቸው ኢዴፓ ይህ ጥያቄ ሊቀርብለት አልቻለም፡፡ ከዚህ ተደጋጋሚ ኢዴፓን በለውሳስ የማለፍ ሰሜት ኢህአዴግ በሚቀጥለው ምርጫ የኢዴፓ ውጤት ምንም ይሁን ምን ለኢዴፓ የሆነ ቦታ ለማጋራት ፍላጎት ያለው ይመስላል፡፡ ተራ ግምት ሊሆን ይችላል፡፡ ብሳሳትም ልክም ብሆን ምንም የተለየ ነገር አይኖርም፡፡ ኢዴፓዎች በልደቱ በኩል ያተረፉት ነገር ቢኖር በእንደዚህ ዓይነት ህዝባዊ መድረኮች በኢህአዴጎች አለመዘርጠጥን ነው፡፡ ይህ ለነገሩ የፓርቲዎች ምክር ቤት አባላት በሙሉ የጋራ ጥቅም ሳይሆን አይቀርም፡፡ አትፓ መቼም ከዚህ ዘለፋ የሚድነው ሀገር ለመምራት ባለው ብቃቱ አይመስለኝም፤ የፓርቲዎች ምክር ቤት አባል በመሆኑ ይመስለኛል፡፡
የአትፓ ባለቤት አቶ አስፋው ጌታቸው ከዚህ በፊት የለገስኩትን ምክር ብጤ ሰምቶ ከክርክሩ ዞር ቢልም የተለወጡት ሰዎች ፓርቲው ሲገለጥ ያሉትን አባላት ጥንካሬ ለማወቅ የሚረዳን ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ የአትፓ ተወካይ ከፖለቲካ ይልቅ እንዲሁ ከአምሳያ ወዳጆቻቸው ጋር በመሆን በፀሎት ሊረዱን ቢሞክሩ የተሻለ ነበር የሚል የግል አስተያየት አለኝ፡፡ ለነገሩ ፀሎት ቅን ልቦና ይጠይቃል፡፡ የፀሎት ትሩፋት ከራስ አልፎ ለሌላው እንዲተርፍ ካሰፈለገ ማለቴ ነው፡፡ ያለበለዚያ እንኳን አደረሳችሁ ለ2007 ምርጫ ለመባባል አይመስለኝም፡፡ የአትፓ ተወካይ ሰፋ ያለ የአድሎዎ ዝርዝር የገለፁ ሲሆን እርሳች አባል የሆኑበት የዓይማኖት ድርጅት ለስራ ቅጥር አንኳን ችግር እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ሌላውን ሁሉ ትተው የአትፓ ተወካይ ሌቦችና ወንጀለኞች ጌታ በሆኑበት እስር ቤት፤ የፖለቲካ እሰረኞች ላይ የሚደርሰውን ግፍ ማንሳታቸው ለወሰዱት 19 ደቂቃ ከፓርቲው ከሚጠበቀው በላይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ከማርሸ ቀያሪ ነኝ ከሚለው አትፓ ምንም ስለማልጠብቅ፣ ይህን እንደጥሩ ነጥብ አድርጌ ዘገባዬን አብቅቻለሁ፡፡
ኢዴፓ የመልካም አስተዳደር መመዘኛ ነጥቦችን አስቀምጦ አቶ አባይ ፀሀዬንም በዚሁ መስፈርት መሰረት እንዲፈሱ አድርጎዋቸዋል፡፡ ኢዴፓ የእነዚህ መሰፈርቶች ፈልሳፊ ባይሆን እንኳን ኢህአዴግ በነዚህ ዓለም አቀፍ መስፈርቶች መውደቁን ለማሳየት ተጠቅሞበታል፡፡ ወደ ዝርዝሩ መግባት ባልፈልግም ኢህአዴግ እነዚህን መሰፈርቶች በየመስሪያ ቤቱ መግቢያ ላይ የለጠፋቸው ቢሆንም አንዳቻውንም በተግባር አንደማያውል የአገልግሎት ፈላጊው ህዝብ ምስክር ነው፡፡
ለሲቪል ሰርቪስ ሰራተኛ ግልፅ ወገንተኝነቱን በተደጋጋሚ የሚገልፀው ኢዴፓ የሲቪል ሰርቪሱን ድክመት በግልፅ አስቀምጦዋል፡፡ ሲቪል ሰርቪሱ በእውነትም የአቅመ ቢሶች መጠራቀሚያ እንደሆነ በግልፅ ተከራካሪው ለማሰቀመጥ ሞክሮዋል፡፡ የሰቪል ሰርቪስ ሰረተኛው አቅም በፈቀደ ድጋፍ የሚደረግለት እንጂ በሰራበት ልክ የሚከፈለው እንዳልሆነ ጭምር የተመሰከረለት ነው፡፡ ተደጓሚ አንጂ በስራው ልክ የማይከፈለው፣ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መፍስስ ግዴታው የሆነ እንደሆነ መረዳት የሚያስችል ክርክር ነበር፡፡ ኢዴፓ እነዚህ ክርክሮች ይህን መስመር እንዲይዙ እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትር ማዕረግ ያሉት የኢህአዴግ ተከራካሪ እንዲፎርሹ እድል ስጥቷቸዋል፡፡ ምን ዋጋ አለው ሲቪል ሰርቪሱ ይህን ክርክር መሰረት አድርጎ ይወስናል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሁለም እንደሚያቀው የሲቪል ሰርቪስ ጠንካራው ሰራተኛ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር አልገባም ብሎ መንግሰታዊ ያልሆኑ ተቋሞች ውስጥ ሲገባ እነዚህን ተቋሞች የኪራይ ስብሰቢ መታጎሪያ ተብለው ተፈርጀዋል፡፡
ኢዴፓዎች የሱማሌን ጦርነት ከኢህአዴግ ጎን ቆመው ከደገፉበት ቀን ጀምሮ አንገት ያስደፋቸውን የሀገር መረጋጋት በሚቃረን መልኩ ይህች ሀገር የተረጋጋች ነች ማለት አይቻለም ብለው ወደ ትክክለኛው ግምገማ ቀርበዋል፡፡ እዚህም እዚያም የታጠቀ ሀይል እየተንቀሳቀሰ ነው በሚል ሙግት አቅርበዋል፡፡ ኢህአዲጎች እዚህም እዚያም ያለ ቡድን ብለው ለማጣጣል ቢሞክሩም ችግሩን ማመናቸው ግን አልቀረም፡፡ ህወሓት በደርግ ጥቂት ወንደበዴዎች ይባል እንደነበረው ማለት ነው፡፡
ኢዴፓዎች ኢህአዴግ ሰለ መልካም አስተዳድርና የህግ የበላይነት ለማውራት የሞራል ልዕልና እንደሌለው ከማሳሰብ በተጨማሪ  በህግ አምላክ ብሎ የሚያምን ህዝብ በህግ ላይ እምነት ያጠበት ወቅት መሆኑን በጥድፊያ አስቀምጠዋል፡፡ ፍትህ አደጋ ላይ የወደቀበት ከደርግም ከንጉሱ ጊዜ የባሰ ነው በሚል ነው የገለፁት፡፡ ይህ አገላለፅ አቶ አባይ ፀሃዬን ከምንም በላይ ያስቆጣቸው ቢሆንም፡፡ ፍርድ ቤት አሽንጉሊት ከመባል ያለፈ ምን ይባል? ከዚህ በላይ የት ይውረድ? ብለው ሞግተዋል፡፡ መንግሰት ደግሞ ፍርድ ቤት የፈታውን የሚያስር ከሆነ ከዚህ በላይ ምን ዓይነት ጣልቃ ገብነት ነው የፈለገው? ብለውም ለህዝብ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ ባጠቃላይ ሲታይ የህግ የበላይነት ሳይሆን የፖለቲካ እና የገንዘብ የበላይነት የነገሰበት ነው፡፡ ፖለቲካና ገንዘብ ያለው የፈለገውን ለማድረግ የሚችልበት ሀገር ነው፡፡ የሙስና ዜናዎች ዘግናኝ ሆኖዋል፡፡ ስንት ትከፍላለህ ጉዳይ ለማስፈፀም መደበኛ የስራ ሂደት ሆኖዋል ሲሉ ለህዝቡ አቅርበዋል፡፡ ለዚህም ነው ኢህአዴግ ስለ ህግ የበላይነት እና መልካም አስተዳደር ለማውራት የሞራልም ሆነ የህግ ልዕልና የለው የምንለው ብለው ትንፋሽ እያጠራቸው አሰረድተውል፡፡ ለዚህ ነው እኛም ቤት ሆነን ምርጫችን ያልሆነውን ኢዴፓ ኮፍያ አንስተን ልክ ልክ ነገረልን ያልነው፡፡  ኢዴፓ ቢመረጥ ይህን ይህን እናደርጋለን የሚለውን ፌዝ ትተን ማለት ነው፡፡ ኢዴፓ ግን ከሁሉም በተሻለ እንደዚህም የምር ተናግሮ በቀጣዩ መንግሰት አንድ ነገር ሊያገኝ የሚችል ነው የሚል ተሰፋ አለኝ፡፡ በችሎታ ሳይሆን በችሮታ፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ክርክር የነበረበት ከተሰጠው ርዕስ ጋር ብቻ ሳይሆን ከአወያዩ ጋዜጠኛ ጭምር እንደነበር ለመረዳት አሰቸጋሪ አልነበረም፡፡ ይህን ጋዜጠኛ በቀጣዩ ቀን ደግሞ በሌላ አንድ ለአንድ በሚል ፕሮግራመ ከኢዴፓ የህዝብ ግንኙነት ጋር ክርክር ሲያደርግ አድምጨው ዶክተር መረራ ተማሪዬ የሚሉት ጋዜጠኛ ሊብራል ዲሞክራሲን በዚህ ደረጃ አስረድተው ከሆነ ያስመረቁት ለትምህርት ክፍሉም ነው ያዘንኩለት፡፡ የሰማያዊ ተከራካሪ ከዚህ ጋዜጠኛ አረዳድ ጋርም ጭምር ነበር ክርክር የገባው የሚል እምነት አለኝ፡፡ አንባቢ ይፍረደኝ ሊብራል ዲሞክራሲ ለጥቂት ባለሀብቶች የቆመ ነው የሚል መፅኃፍ የት ነው ያነበበው? የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መፅሃፍ እንዲህ የሚል እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ይህ ደግሞ እውነት አይደለም፡፡ ይህ ጋዜጠኛ አነስተኛ ደሞዝ ወለል መወሰን ከሊብራል ዲሞክራሲ አስተሳሰብ የወጣ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ጋዜጠኛው 2 ከመቶ የሚሆኑ ሀብታሞች ያሉበት ዓለም ብርቅ ለምን እንደሆነበት አይገባኝም፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ጥቂት ነገሮች ሀብታሞች ብቻ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በዓለም ላይ ያሉ ባለስልጣኞች ዜሮ ነጥብ አንድ አይሆኖም፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ፓይለቶችም እንዲሁ ትንሽ ናቸው፡፡ እንዲህ ብሎ መቀጠል ይቻላል፡፡
ለሰማያዊ ፓርቲ የኢዴፓ ከፊት ቀድሞ የመልካም አስተዳደር መስፈርቶች እና የኢህአዴግ ድክሞቶች ማቅረቡ ሰማያዊ ፓርቲ ቀሪውን የኢህአዴግ ዘባተሎ ለማስረዳት እድል የሰጠው ይመስለኛል፡፡ የይድነቃቸው ጮሌነትም ይህን ለመጠቀም የረዳው ይመስለኛል፡፡ ይህን ክርክር ከህግ አግባብ ውጭ በእስር የሚማቅቁ ወንድሞችና እህቶች ካልተነሱቡት፣ ለደሞዝ እንጂ ለውጤት የሚሰራ ሲቪል ሰርቪስ እንደሌለን ካልተዘከረበት ምን ክርክር ሊባል ይችላል? ሰማያዊ ፓርቲ ተወካይ ይድነቃቸው እነዚህን ነጥቦች በማንሳት ተሳክቶለታል፡፡ በማግሰቱ በጋዜጣዊ መግለጫ የታጀበው “የድንኩ አንድነት” መግለጫንም የጠራው አስተያየት የተገኘው ከሰማያዊ ፓርቲ ነው፡፡ ኢቲቪዎች ካሜራ ይዘው ድንገት “ድንኩ አንድነት” ሰፈር ተገኝተው አቶ ትዕግሰቱ አወሉን የማሪያም ብቅል እንደበላ ሲያንተባትቡት ውለዋል፡፡ ፍርድ ቤትም እንደሚሄዱ ነግረውናል፡፡ ሌባን ሌባ ብለን ፍርድ ቤት መሄድ የምንፈራ እንዳልሆንን አቶ ትዕግሰቱ አጉሉም ቢሆን በደንብ ያውቀናል፡፡ አንድነት የፈሪ ሰፈር እንዳልሆነ ብቻ ሳይሆን የአጉል ጀብደኛም ሰፈር እንዳልነበር፡፡ አጉል ጀብደኛ ቢኖረን ትዕግሰቱ በየመሸታ ቤቱ ሲያንቃርር ሊገጥመው የሚችለውን ያውቅ ነበር፡፡ መርዕ እንዳለን ያውቃል ስለዚህ ማሰፈራሪያ እንደማንፈራ ብቻ ሳይሆን እንደማናሰፈራራም ያውቃል፡፡
ሰማያዊ ሰለብሔራዊ መግባባት ያነሳው ጉዳይ አቶ አባይ ፀሃዬን ቢያበሳጭም አሁንም እውነት መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ከደርግ ጊዜ በላይ ታጣቂ ያለባት ሀገር ኢትዮጵያ ብቶሆንም የቀዝቃዛው ጦርነት በዓለም ላይ አለመኖር እና የፀረ ሸብር ህብረት በኢትዮጵያ ዙረያ ባሉ ሀገራት ተመሳሳይ መሆን ለመንግሰት የፈጠረለት ምቹ ሁኔታ መግባባት አለ እንድንል የሚያሰገድድ አይደለም፡፡ ይህ በፍፁም ኢህዴግን ሊያበሳጭ አይገባም፡፡ በዕትመት ምክንያት ዘግይቶ የደረሰኝ ሪፖርተር ጋዜጣ 11 ሰዎች ከጋምቤላ አካባቢ የህዳሴ ግድብ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ሲሉ ተይዘው ተፈረደባቸው የሚል ነበር፡፡ ይህ መልዕክቱ ምን ማለት ነው? ልማት ሊያፈርስ የሚፈልግ ጥቅሙ የተነካበት ቡድን አለ ማለት ነው፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ብትመርጡን እንዲህ እናደርጋለን የሚል ፌዝ ውስጥ መግባቱን አልወደድኩለትም፡፡ በተለይ ወዳጄ ይድነቃቸው አንድነት ፓርቲ ሰለ ምርጫ ሲሰብክ በማህበራዊ ድረ ገፅ ያወርድብን የነበረውን የጭቃ ጅራፍ ሳስታወሰ እና አሁን ምረጡን ብሎ እስክስታ በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ዓይነት ነው የሚመስለው፡፡ ለማነኛውም ይድነቃቸው ማዕከላዊ ትሄዳለህ የሚል ዳኛ ባለበት ሀገር የህግ የበላይነት አለ እንድንል አያስብልም ያላትን ነጥብ በደንብ በአደባባይ ሲያቀርብ አንጀቴን ቂቤ አርሶታል፡፡ ይህች ነጥብ መቼም የኢህአዴጎችን ወዳጅ ዳንኤል ብርሃኔን እንኳን ጥፍር ስር ለመሸሸግ የገፋፋች ናት፡፡ ይህ ዳኛ በዚህ አባባሉ ፋውል ነጥብ የሚያዝበት ይመስለኛል፡፡
ለማነኛውም ይድነቃቸው  ምርጥ ምርጥ ነጥቦች አንስቶዋል፡፡ ከፓርቲ ገደብ ወጥቶ ተከራክሮዋል፡፡ ይድነቃቸው ከኢህአዴግ ጋር ብቻ ሳይሆን ከአወያዩ ጋርም ጭምር ነበር ግብ ግብ የገጠመው፡፡ ውሳኔ የተሰጠበትን ጉዳይ ሁሉ በፍርድ ቤት ተይዞዋል እያለ ለማቋረጥ ያደረገውን ጥረት አክሽፎበታል፡፡ ሰለ አባይ ግድብ መዋጮ ያነሳት ነጥብ ወደፊት ሰለማዊ ሰልፍ በሰማያዊ ላይ ልታስጠራ ትችላለች፡፡ ይህ የአንድ አንድ ነዋሪዎች አስተያየት ነው፡፡
መድረክ በአቶ ብርሃኑ በርሄ ዓለም አቀፍ ሪፖርት እንደማስረጃ በማቅረብ የጀመረ ሲሆን ይህ አቀራረቭ ህዝቡ ይህች ሀገር በመልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነት ያለችበትን ደረጃ ከዓለም አቀፍ መስፈርት ደረጃ አንፃር እንዲያውቅ፣ የሚያውቀውም እንዲያስታውስ የረዳ ነው፡፡ አንደ ጠንከር ያለ ሃሰብም አንሰተዋል ይህች ሀገር ሰው እንደሌላት አንድ ሰው ይህን ሁሉ ስልጣን የያዘበት ሁኔት ለምንድነው? በሚል ጠይቀዋል፡፡ ይህ ግለሰብም በምክር ቤት ስብሰባ ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚያውቁት የአቶ መለስ አጃቢ ጋርደ አድርገው የሚያውቁት ቢሆንም በትክክል ግን ከአቶ መለስ ዜናዊ ጀርባ የሚቀመጠው አቶ አስመላሽ ገ/ስላሴ የምክር ቤቱ ዋነኛ መሃንዲስ ነው፡፡
የመድረኩ ሌላኛው ተከራካሪ በገቡበት ጥቂት ደቂቃም ቢሆን የኢህአዴግን ታንክና ባንክ በደንብ አድርገው በጥድፊያ ገልፀዋል፡፡ ይህ ነው የሚባል የተማረ ሰው ሳይዝ ታንክና ክላሽ ይዞ ሀገር ለመምራት የቻለው ኢህአዴግ፣ መድረክን ሀገር ልትመሩ አትችሉም ማለቱን አጣጥለውታል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ኢህአዴግ ሀገር የሚመራው ኢትዮጵያዊ ከሆነ መሪው የፖለቲካ ፓርቲ ማንም ቢሆን ሀገር የሚመራበትን መንገድ የሚቀይስ ይጠፋል ማለቱ ሁሉም እንደራሱ በር ዘግቶ ለሌብነት ይመክራል ብሎ ስለሚያስብ ነው፡፡ ለመስረቅ ካልሆነ ሀገር ለመምራት ኢትዮጵያዊያን ከየትም ከኢህአዴግም ሰፈር ጨምሮ እንደሚኖሩ ያለማወቅ ነው፡፡
የኢህአዴግ ጉምቱ ፖለቲከኛ አቶ አባይ ፀሀዬ የኢዴፓው ጎረምሳ በተደረጃ መልክ ባቀረበው የመልካም አስተዳድር መመዘኛ መስመር እንዲቀርቡ ያስገደዳቸው ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት ተዘጋጅተው የመጡበትን ዋና ዋና ነጥብ ማቅረብ አልቻሉም፡፡ የተዘጋጁት የኢህአዴግን ስኬት እና አሁን የሚታየውን ጉድለት በማቅረብ ጉድለቱን እንዴት አርመው ለቀጣይ እንደሚገዙን ህዝቡን ለማማለል ቢሆንም እንደቀልድ የጀመሩት የመልካም አስተዳድር መስፈርቶች ብሎ የኢዴፓ ተከራካሪ ያቀረበላቸውን ነጥብ በማብራራትና በመከላክል ጊዜውን ጨርሰውታል፡፡ ኢህአዴግ በእነዚህ መመዘኛወች ከአሰር ሁለት የሚያገኝበት አንድም ቦታ ሳይኖር ለቀጣይ ምርጫ እራሱን ማጨቱ እረሱ አስገራሚ ነው የሆነብኝ፡፡
ኢህአዴግ ሀገራዊ መግባባት ደርሰናል ያለባቸው ነጥቦች በሙሉ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ህዝብ የተጣላባቸው አልነበሩም፡፡ ድህነት ሰርዓቶች የጫኑብን እንጂ እንደህዝብ ተሰማምተን ይዘነው አናውቅም፡፡ የብሔር ግጭትም ለግል የፖለቲካ ስልጣን የሚሮጡ ፖለቲከኞች እንጂ የህዝብ አጀንዳ አይደለም፡፡ ሰላምን የማይሻ በሽፍትነት የሚጠቀም የነበረ ሲሆን ሽፍታ መንግሰት ሆኖ መዝረፍ ከቻለ ሽፍትነት ሊያምረው አይችለም፡፡ ለማነኛውም ኢህአዴግ ያመነው የሙስና መስፋፋት ብቻ ከስልጣኑ በፈቃደኝነት እንዲለቅ የሚያደርገው ቢሆንም ይህን ለማድረግ ፍላጎት የሌለው ብቻ ሳይሆን ምን ላድርግ? እነዚህም ሰዎች ከማህበረሰቡ የመጡ ናቸው፡፡ ኢህአዴግ የመላዕክት ስብስብ አይደለሙ በሚል ፌዝ አልፈውታል፡፡
ሃያ አራት ዓመት መልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነት ማረጋገጥ ያልቻለ ቡድን በስልጣን ለመቀጠል ፍላጎቱ ለከት ማጣቱን ስንታዘብ እና ባለፉት ሰድስት ዓመታት ቦኮአራምን ማስታገስ አልቻለም ተብሎ ስልጣን እንዲለቅ የተደረጉትን የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ስናይ ቅናት እርር ድብን ቢያደርገን አይገርምም፡፡ ለማነኛውም ኢህአዴግ በቀጣይ ምርጫ ብቻውን እሮጦ ብቻውን እንደሚገባ ቢረጋገጥም ይህም ደግሞ እንደ ህዝብ አማራጭ ከለከልከን ብሎ ሆ ብሎ የሚነሳ ህዝብ ከሌለ ተገቢው መንግሰት ነው ብለን ለመቀበል አንቸገርም፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚመጥነው መንግሰት ለጊዜው ኢህአዴግ እና ኢህአዴግ ብቻ ነው፡፡ ለማንኛውም የእለት ፍጆታ ችግር አስመልክተው ወ/ሮ አስቴር ማሞ ስለ ውሃ ችግር ሲያወሩ እንስራ የያዘች አንዲት ኢትዬጵያዊ ምሰኪን ሴት ታየችኝ፣ በሁለት ሺ ሁለት 3000 ሜጋ ዋት አለን ያለው ኢህአዴግ በሁለት ሺ ሶሰት መጀመሪያ 2000 ሜጋ ዋት ነው ያለው በቀጣዩ አምስት ዓመት 10000 ይደርሳል ብለው ዛሬ በአሰር ዓመት 3000 ሜጋ ዋት ያለመኖሩን ሊያስተባብሉን ይሞክራሉ፡፡ ታዲይ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ውሸት ከተቀበለ ኢህአዴግ ይመጥነዋል ማለት ሰህተት ይሆናል፡፡
ከዚህ በላይ የኢህአዴግን ዘባተሎ የተጠና ፕሮፓጋንዳ ማቅረብ ተገቢ አልመሰለኝም እና የዛሬውን በዚሁ ላብቃ፡፡


Monday, April 6, 2015

ክርክር 4፡ ኢንዱስትሪ እና ከተማ ልማት- በእኔ ዕይታ

ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com; girmaseifu.blogspot.com
ተከራካሪዎች
·         እያሱ መኮንን እና አዳነ ታደስ                  ኤዴፓ
·         ተሸመ ወልደ ሓዋሪያት                       መኢብን                 
·         ትዕግሰቱ  ደበላ እና ግዑሽ ገ/ሰላሴ              ኢድአን
·         ካሳሁን አበባው እና ተሰፋሁን አለምነህ          መኢሕአድ
·         መኩሪያ ኃይሌ እና አህመድ አብተው            ኢህአዴግ
በግንቦት 2007 የሚካሄደው “ምርጫ” አማራጭ በሌለበት መሆኑ በዋነኝነት የጎዳው ለምርጫ ከምር የተዘጋጁትን ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን መራጩን ህዝብ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ይህ አሁን በገዢው ፓርቲ ላይ ለምንመለከተው የፀጥታ ስጋት ምንጭ የሆነ ይመስለኛል፡፡ ዘንድሮ የፕሮፓጋንዳ ማሽን የሆነው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ ምርጫ ቦርድ የሰጠው ውሳኔ ፍትሐዊ ነው፣ የምርጫ ቦርድ ታጋሽነት ያስደስታል፣ ወዘተ ከሚሉ አንድ-አንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዘገባ፤ ምርጫ ክርክሩ በመረጃ ላይ ተመስርተን እንድንመርጥ የሚያስችል ነው “አሉ” አንድ-አንድ ነዋሪዎች ወደሚል አድጓል፡፡ ይህ መልዕክት አማራጭ አለ የሚል የተሳሳተ መልዕክት ለማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን ከአማራጮቹ “ምርጡ ኢህአዴግ” ነው ወደሚለው ቀጣይ ዘመቻ መግቢያ ነው፡፡ በዚህ አሰቀያሚ የማስመሰል ድራማ ውስጥ አውቀው በድፍረት ሳያውቁ በስህተት የሚሳተፉ እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን በዚህ ድራማ ውሰጥ አውቀው በድፍረት ከሚሳቱፉት አንዱ ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ክፍል ነው፡፡ ምርጫው አማራጭ እንደሌለው እየታወቀ “የሚዲያ ሚና በመርጫ” ምናምን እያለ ድራማውን ያዳምቃል፡፡ በዚህ ጉዳይ ሌላ ቀን መመለስ ይቻላል እና ወደ መጋቢት 25 እና 26 የምርጫ ክርክር ትኩረት እናድርግ፡፡
ኢህአዴግ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱም ቢሆን ከግብርና ወደ ኢነዱስትሪ የሚደረግ ሽግግር የማድረግ ሃሳብ አልነበረውም፡፡ በዋነኝነት እድገቱ መሰረት ያደርጋል ተብሎ ታሳቢ የተደረገው በአነስተኛ ማሳ ላይ በሚደረግ ምርታማነት ማሳደግ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በዋነኝነት የሰራ እድል በመፍጠርም ሆነ የተለየ ምርታማነት ማሰደጊያ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም የሚያስችል አይደለም፡፡ ለምሳሌ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል ከግማሽ ሄክተር በታች ማሳ ያላቸው ገበሬዎች ከበሬ የዘለለ የእርሻ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ያስቸግራቸዋል፡፡ ሰለዚህ ዋነኛው የምርት ማሳደጊያው ግብዓት ማደበሪያ አጠቃቀምም ነው የሚሆነው፡፡ ይህም ቢሆን የመሬቱን የማዳበሪያ ፍላጎት መሰረት ያደረገ ሳይሆን “ለሁሉም አንድ ጃኬት” በሚመስል መልኩ ለሁሉም ዩሪያና ዳፕ የሚባሉ ማዳበሪያዎች የሚቀርቡበት አሰራር ነው ያለው፡፡ የማዳበሪያ ንግድ በሀገራችን የማንን ኪሲ እንደሚያደልብ እያወቅን ተጨፈኑ እናሞኛችሁ ይሉናል፡፡ የግብርና ምርት ማሰደጊያ ግብዓቶች ማቅረብ በዋነኝነት ግቡ የተወሰኑ ኩባንያዎች ኪስ ማደለቢያ እንጂ በወሬ እንደሚባለው ምርታማነት ለመጨመር አይደለም፡፡ አማልጋሜትድ የሚባል በኢትዮጵያዊ የሚመራ የግል ኩባንያ ለምን ከዚህ ሀገር ተገፋ?
መጋቢት 25 እና 26 በተደረገው የፓርቲዎች ክርርክር ርዕሱ “ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት” የሚል ነበር፡፡ ኢህአዴግን ባለፉት 24 ዓመት ብቻ ሳይሆን ባለፉት አምሰት ዓመታት አሳካዋለሁ ብሎ የቀረበውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እንኳን ለማሳካት የማይችል ብቻ ሳይሆን እነዚህን በቁጥር ያስቀመጣቸውን ግቦች ያለ ማሳካቱን ግልፅ ሆኖ እያለ በኩራት አሳክቻለሁ ይላል፣ ጥሩ ጅምር ነው እያለ ሲፎክር በመረጃ አስደግፎ ሊሞግተው የሚችል ፓርቲ አላገኘም፡፡ በግሌ ይህ ክርክር በኤዴፓው ተከራካሪ እያሱ መኮንን እና በኢህአዴግ ተወካዮች ብቻ ቢሆን ምርጫዬ ነበር፡፡ ለኢዴፓ ካለኝ ፍቅር ሳይሆን አቶ እያሱ በተረጋጋ ሁኔታ በነጥብ ሲሞግት ስላየሁት ነው፡፡ አብሮት ለክርክር የገባው አቶ አዳነ ታደሰ ሊረዳው በሚገባው ልክ ከመርዳት ይልቅ ኢዴፓዎች አንፈልገውም የሚሉትን ሰሜታውነት መቆጣጠር ሳይቻለው ቀርቶ ታዝበነዋል፡፡
ወደ ዝርዝሩ ስንገባ የመጀመሪያ ቅድሚያ እድል ያገኘው ኢዴፓ በአቶ እያሱ መኮንን ተከራካሪነት ነው፡፡ እያሱ በመግቢያው ላይ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የከተማ ታሪክ ያላት መሆኗን በጨረፍታ አንሰቷል፣ ከአፍሪካ አንፃርም ቢሆን ከተሜነት በዝቅተኛ ደረጃ እንደምንገኝ፤ በዚህ ዝቅተኛ ደረጃ ባለ ከተሜነት አስፈላጊ የሆኑ አግልግሎቶች ማቅረብ ያለመቻሉን፣ ኢህአዴግ ወዳጄ ያለው ግብርናም ቢሆን ይህን አነስተኛ ቁጥር ያለውን ከተሜ መመገብ አቅቶት ስንዴ፣ ሰኳር የመሳሰሉ መሰረታዊ ፍጆታ ከውጭ በግዥ እንደሚገባ አሰረድተዋል፡፡ የኢህአዴጉ ተወካይ ግብርና ባፈራው ጥሪት ነው ሰንዴና ሰኳር የተገዛው የሚል አስቂኝ መልስ የሰጡ ቢሆንም፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ልካ በምታመጣው ገቢ ከነዳጅ ውጭ ሌላ ነገር ለመግዛት የሚያስችል አቅም እንዳልፈጠረች፣ አብዛኛው የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከእርዳታ፣ በውጭ ከሚኖሩ ዜጎች የሚገኝ ገቢ፣ ወዘተ እንደሆነ ለኢህአዴጉ ተወካይ ማስታወስ ያስፈልግ ነበር፡፡
ከከተሜነት አንፃር አሁን የተፈጠረውም ሽግግር በኢዴፓው ተወካይ በኢንዱስትሪ ነው የሚል አቀራረብ የነበራቸው ቢሆንም እውነታው ግን አብዛኛው ወደ አገልግሎት የመጣ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ዘርፍ በሰራ ፈጠራ አሁን ወደ ከተማ የገባውን ሁለት ከመቶ ህዝብ አልተቀበለም ምክንያቱም ኢንዱስትሪ የሚባለው እዚህ ግባ በሚባል ደረጃ የለም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ 70 ከመቶ በሀገር ውስጥ ባለሀብት ተይዞዋል የሚባለው ኢንዱስትሪ በቤተሰብ ደረጃ የሚሰሩ የጎጆ ኢንዱስትሪዎች መሆናቸው መታወቅ አለበት፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ የከተሜንት ታሪክ ብቻ ሳይሆን ለዓለም የምታጋራው ልምድ የነበራት/ያላት ሀገር ነች፡፡ እንደ ብራዚሊያ ያሉ ከተሞች የሚኒሊክ ሞዴል ተከትለው ዋና ከተማቸውን በሀገሪቱ አማካይ ቦታ ለማድረግ ችለዋል፡፡ አዲሰ አበባ በሀገራችን አማካይ ቦታ መገኘቷን ልብ ይሏል፡፡ ሌሎችም የረጅም የከተማናት ታሪካችንን መጥቀስ አለመቻላቸው ቅር አስኝቶኛል፡፡ የአፍሪካ ከተሜነት ከ40 በመቶ በላይ ሲሆን በዓመት በአማካይ ላለፉት 20 ዓመታት 3 በመቶ እያደገ ሲሆን ኢህአደግ የሚመራት ኢትዮጵያ ግን በ24 ዓመት 3 ከመቶ ዕድገት ማምጣት አልቻለም፡፡ ኢህአዴግ ቢዘህ ሊያፍር አልቻለም የሚያሳፍረውም ተከራካሪም አላገኘም፡፡
የኢዴፓው እያሱ መኮንን በኢትዮጵያ ከተሞች “ለምን ዕድገት አላሳዩም? ተብሎ ሲጠየቅ ኢህአዴግ ሳይፈልግ ቀርቶ ሳይሆን በፖሊስ ችግር ነው፡፡ ግብርናን መሰረት አድርጌ ለውጥ አመጣለሁ ይላል፤ ግን አይችለም” የሚል አስተያየት አስቀምጦዋል፡፡ ይህ አተያየ በኤዴፓ የፖለቲካ ቅኝት ልክ ቢመስልም፣ “ከተሞች አድገው ስልጣን ከማጣ፤ ከተሞች ባያድጉ ይሻላል” የሚል ፖሊስ የነደፈ ገዢ ፓርቲ አንፃር ለምን የከተሞች ዕድገት አልታየም? ለሚለው ጥያቄ የሰጡት መልስ እንዴት ሊተረጎም እንደሚችል አይገባኝም፡፡ ይህን ውሳኔ ለአንባቢ መተው ይሻላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ኢህአዴግ ከተሜነት እንዲያድግ ይፈልጋል?
የኢዴፓ ተወካዮች ጥቃቅን እና አነስተኛ በመባል የተደራጁትን እንደሚደግፉ ነገር ግን እነዚህ አደረጃጀቶች ከፖለቲካ ሴል ወደ ኢኮኖሚ ሴል መለወጥ እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ያሰቀመጡ ሲሆን ከጥቃቅን እና አነስተኛ አባላት ጋር ግብ ግብ መፍጠር እንዳልፈለጉ ያሰታውቅባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ትክክል የፖለቲካ አያያዝ ይመስለኛል፡፡ ይህን ነጥብ ብዙዎቹ ተከራካሪዎች የተጋሩት በመሆኑ ኢህአዴግ ከዚህ አንፃር ነጥብ እንዳያሰቆጥር አድርገውታል፡፡ በሀገራችን አለ የሚባለው እድገት ከተሜው በዋጋ ንረትና በኑሮ ውድነት ሰቃይ ውስጥ ሆኖ የተገኘ ሲሆን ይህ ደግሞ ዘላቂነት እንደማይኖረው አስረድተዋል፡፡ ይህ ለአብዛኛው አድማጭ በምን ያህል ደረጃ እንደሚረዳው አላውቅም፡፡ ከተሞቻችን ጥቂት የሚባሉ ባለ ሀብቶች እጅ የወደቀች ሲሆን ዋናው መንግሰት የሚቆጣጠረው ሀብት ነው፡፡ በተለይ አዲስ አበባ ለድሃ ምቹ ያልሆነች ከተማ ነች፡፡ አዲስ አበባ ፓርክ የሌላት፣ መዝናኛ የራቃት ከተማ ብቻ ሳትሆን ለወጣቶች ያዘጋጀችው መዝናኛ ትውልድ ገዳይ የሆነ ሱስ ማዘውተሪያ ቦታዎችን ነው፡፡ የስራ እድልን በተመለከተ ከኢህአዴግ የተነገረን የስራ እድል ቁጥር የተጋነነ ነው፡፡ በጡረታ የሚደጎም ወጣት የሚኖርበት ሀገር ይህ ሁሉ የሰራ እድል ተፈጠረ ማለት ምፀት ነው፡፡ ኢዴፓ በበኩሉ በዓመት 1.7ሚሊዮን በላይ የስራ እድል ለመፍጠር እንደሚሰራ ነገሮናል፡፡ ኢዴፓዎች ይህን ቃል ሲገቡ እንደሌሎች ፓርቲዎች ሁሉ መንግሰት የመሆን እድል እንደሌላቸው እየታወቀ አጉል ተሰፋ ሊመግቡን እየፈለጉ እንደሆነ ማወቃችንን ማወቅ አለባቸው፡፡
የኢዴፓው አቶ አዳነ ታደሰ ካነሱት ሃሳብ የከተሞች እድገት ላይ ዋነኛው እንቅፋት የሆነው ከተሞች በካድሬ መመራታቸው ብቻ ሳይሆን የከተማ ህይወት የማያውቁ ሰዎች በመሆናቸው የተፈጠረ ነው ብለውታል፡፡ ይህ በአዲስ አበባ ከላይ እስከታች ባለው መዋቅር የሚታይ አዲስ አበቤዎችን የገፋ፤ ይልቁን የአዲስ አበባ ልጆችን በጠላትነት የሚያይ ሰርዓት መሆኑን ማሳያ ነጥብ ነው፡፡ በኢንዱስትሪ ዘርፍም ቢሆንም በሀገራችን አሁን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እየወጣ ወደ ሀገር የሚገቡት ጁስዎች በሀገራችን የጥሬ እቃዎች ምርት በሚበላሸበት ሁኔታ እንደሆነ እያወቅን ይህን መለወጥ የማይችል የኢህአዴግ ፖሊስ አይሰራም ብለው ነጥብ አስቀምጠዋል፡፡ ሰልጡን ፖለቲካ ከፈለጋችሁ ኢዴፓን ምረጡ ብለውን ተሰናብተዋል፡፡
መኢብን የሚባው የአቶ መሳፍንት ፓርቲ ዛሬም አቶ ተሾመ ወልደ ሓዋሪያትን በድጋሚ ይዞ የመጣ ሲሆን በኢህአዴግ ፖሊሲ ምክንያት የከተሜነት ችግር ለመፍታት አለመቻሉን የከተሜውን ችግር በሚያሳይ ሁኔታ ዘርዝረውታል፡፡ በምርጫ ውድድርም ውስጥ የገቡት መንግሰት ለመሆን ሳይሆን እና የዘረዘሩትን ችግሮች ለመፍታት ሳይሆን ይህን ብሶቱን ለማሰማት እንደሆነ በግልፅ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ልናከብራቸው ይገባል (ፓርቲያቸውን ሳይሆን አቶ ተሸሞን በግል)፡፡ አቶ ተሾመ ትውልዳቸው ዱራሜ አካባቢ እንደሆነ በሚያሳይ መልኩ ፓርቲያቸውን በሚመጥን መልኩ የተሰጣቸውን ጊዜ በቀበሌኛ ጉዳዮች አባክነው “በከተማና ኢንዱስትሪ” ጉዳዮች ነጥብ ሳይሰጡን አልፈዋል፡፡ ነጥብ አገኛለሁ ብዬም ስለአልጠበኩ አልገረመኝም፡፡ ምርጫ ቢኖረን መኢብን የሚባል ፓርቲ ከአሁን በኋላ በቤታችን ቴሌቪዥን ባይመጣ በመረጥን ነበር፡፡ ምርጫ ቦርድ ከሚንከባከባቸው ፓርቲዎች አንዱ ብቻ ሳይሆን በማነኛውም ሀገራዊ ጉዳዮች ተቃዋሚ ፓርቲን ወክሉ በግንባር ቀደም ከሚገኙት አንዱ ነው፡፡ ለውርደታችን ምሳሌ ይሆን እንደሆነ እንጂ የተቃዋሚ ፓርቲን የሚወክል ቁመና ያለው ፓርቲ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡
ኢድአን ባለፈው ክርክር ወቅት እንቅልፍ ሲያሰቸግራቸው በነበሩት በአቶ ትዕግሰቱ ደበላ የተወከለ ቢሆንም “አዲሰ አበባ የመቶ ዓመት እድሜ ያላት ሀገር ናት” ብሎ በስህተት ጀምሮ በቅጡ እንዳንከታተለው አድርጎናል፡፡ በመጀመሪያ አዲስ አበባ ሀገር አይደለችም፣ ሲከተል መቶ ዓመት ብቻም አይደለችም፡ ኢህአዴግ ኢትዮጵያ የመቶ ዓመት ታሪክ ነው ያላት ብሎ ጫካ ገባ ጫካ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ 40 ዓመት ሙሉ የመቶ ዓመት ታሪክ ያወራል፡፡ ኢህአዴግ ስዓትና ጊዜው ቆሞበት ከሆነ አቶ ትዕግሰቱ ደበላም ይህንኑ መቀበላቸው ትክክል አይደለም፡፡ በሌላ በኩል አቶ ትዕግሰቱ ደበላ ባለፈው ፓርቲያቸው በገጠር መንደር ምስረታ ሲያነሳ የነበረውን ሃሳብ ወደፊት ለከተማ ምስረታ እንደሚውል የሚጠቁም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ “ፅድቁ ቀርቶ በወጉ በኮነነኝ” እንደሚባለው በየክልሉ ያሉት ከተሞች ከተማ ቢሆኑ ብዙ ለውጥ እንደሚኖር ኢድአን የገባው አይመስልም፡፡ የኢድአን ከመንደር መስረት የሚመጣ ከተሜነት፤ ከኢህአዴግ ከገጠር በኋላ ከተሜነት ከሚለው አተያይ ልዩነቱ አልታየኝም፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ትዕግሰቱ ደበላ ያለችውንም አጭር ጊዜ ሳይጨርሱ ትንፋሽ ይሁን ሃሳብ አጥሯቸው ለአቶ መኩሪያ ኃይሌ የሚወዱትን የኮብል ሰቶን ጉዳይ አቀብለው ክርክሩን አቁመዋል፡፡
በአቶ ትዕግሰቱ ደበላ አቀራረብ ያልተደሰቱ የሚመስሉት አቶ ግዑሽ ገ/ስላሴ ቀጣዮችን ክፍሎች በሙሉ ይዘውታል፡፡ ዛሬም እኛ ከተመረጥን እንዲህ እናደርጋለን የሚል ከልብ ያልሆነ ቃል በተደጋጋሚ እየገቡ መግቢያ በሚመስል ነገር ጊዜ ሲያባክኑ ነበር፡፡ ከአቶ ግዑሽ ነጥብ አርጌ ልይዝላቸው የቻልኩት የኢህአዴግ “የፓርቲ አክራሪነት” በሚል የገለፁት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ጥቃቅን እና አነስተኛ በሚል የተደራጀው በአብዛኛው የፓርቲ አባል ነው በሚል እቅጩን ተናግረዋል፡፡ ለማነኛውም አቶ ግዑሽም ቢሆን ሰዓት በአግባቡ ለመጠቀም ሳይችሉ ጊዜው አልቆዋል፡፡ ከዚህ የበለጠ ጊዜም ቢሰጣቸው ምን ማድረግ እንደሚችሉ አላውቅም፣ አቅማቸውም ከዚህ የሚዘል አይደለም፡፡
ዋሊያው መኢአድ አቶ ካሳሁን አበባው በተባሉ አዛውንት የመጀመሪያውን ክፍል የጀመረ ሲሆን፣ የከተማ መልሶ ማልማትን አስመልክትው በተለይ ከማህበራዊ ኑሮ አንፃር በሰፈር ያሉ አሉባልታዎች ጭምር የያዙ ቅሬታዎችን አቅርበዋል፡፡ እንደ ፓርቲ ለአዲስ አበባ ህዝብ፣ በሌሎች ከተሞች ለሚኖር ከተሜ እና ርዕሱ የሚጠይቀውን “ኢንዱስተሪና ከተማ ልማትን” የሚመለከት አልነበረም፡፡ የመኢህአዱ አቶ ካሳሁን ከመኢብን አቶ ተሾመ ግልፅነት መማር ሰልአልፈለጉ አልተማሩም፤ መንግሰት መሆን የሚያስችል ዕጩ እንዳላቀረቡ እያወቁ መንግሰት ብንሆን ብሎ ማላገጥ ተገቢ አልመሰለኝም፡፡ በደርግ የተወረሱ ቤቶቸ አብዛኞቹ ፈረስው ማለቃቸውን ዘንግተው፤ የተወረሰ ቤት እንመልሳለን፡፡ የመንግስት የገቢ ምንጭ ውስን መሆኑን ዘንግተው፤ ይሁን ሳያውቁት ቤት በነፃ እየሰራን እንሰጣለን፡፡ እንደ ፓርቲ አማራጭ ማቅረብ እየተጠበቀባቸው ህዝብ እናማክራለን፡፡ እና ሌሎች ተመሳሳይ ፋውል ሰርተው ጊዜያቸውን አጠናቀዋል፡፡
ሌላኛው ተከራካሪ ተሰፋሁን አለምነህ መኢአድን  ወክሎ ለክርክር መመጣቱ በራሱ አስገራሚ ነው፡፡ ከምርጫ በግሌ እራሴን አግልያለሁ ማለቱን ካልቀየረ በስተቀር ማለቴ ነው፡፡ ተሰፋሁን ያለውን የሀገር ፍቅር ሰሜት አደንቀዋለሁ፡፡ በፌስ ቡክ በሚሰጣቸው አስተያየቶቹም ቢሆኑ ሰሜታዊነት እንደሚታየበት ያስታውቃል፡፡ በክርክሩም ይዞት የቀረበው ይህን ሰሜታዊነቱን ነው፡፡ የደም ሰሩ እስኪገተር ድረስ እየተጨነቀ በምርጫ ወቅት የፖለቲካ ጥቅም የማያስገኙ ለምሳሌ “ጥሬ እቃው ዲላ፤ ፋብሪካው አድዋ” የመሳሰሉ አስተያየቶች ለተንኮለኞቹ የህውሃት ካድሬዎች የሚመች ነው፡፡ በ1997 የበድሩ አደምን ንግግር እንዴት አድርገው እነደተጠቀሙበት ማሰተዋል ያስፈልጋል፡፡
ተሰፋሁን አብረውት ክርክር ከመጡት ሰው ጋር ተመካክረው እንዳልገቡ ግለፅ ነው፡፡ ተሰፋሁን በፌስ ቡክ ካሰራጨው አቋሙ ጋር የሚሄደው የኢትዮጵያ ህዝብ ከመኢህአድ ጋር እንዲሰለፍ እንጂ መኢህአድን እንዲመርጥ እና መንግሰት እንሆናለን የሚል መልዕክት የለውም፡፡ መጨረሻ ላይ በችኮላ የመኢህአድ አቋም ብሎ የገለፀው “ለባለ ሀብቶች ብድር ከወለድ ነፃ ይሰጣል” ያለው ግን በስህተት እንደሆነ አድርገን መውሰድ ይኖርብናል፡፡ በማጠቃለየውም ቢሆን ተሰፋሁን ያስተላለፈው መልዕክት “ነፃነት በነፃ ስለማይገኝ ለመሰዋዕትነት እንዘጋጅ” የሚል ነው፡፡ ለማነኛውም መኢህአድ ድሮ የምናውቀው ባለ ግርማ ሞገሱ አይደለም፡፡ ረጅም እድሜ አለው የሚለው ብቻ ነው አብሮት ያለው፡፡ ኢ/ር ሀይሉ ሻወል በህይወት እያሉ መኢህአድ እንዲህ ሲሆን ማየታቸው ምን ሰሜት እንደሚሰጣቸው እና የእርሳቸው ሚናም ምን እንደሆነ የሚነግሩን አይመስለኝም፡፡ ለማነኛውም የመኢህአድ አወራረድ “ጎፈርያም ውሻ” የሚያስንቅ ነው፡፡

የኢህአደግ ተወካይ አቶ መኩሪያ ኃይሌ ክርክር የጀመሩት የቀድሞ ስርዓት በመክሰስ ነው፡፡ ከተሞችን የከሰሱበት ድህነት እና የፀጥታ ችግር ምንጩ አሁን በመንግሰት ሹም እንዲሆኑ ያደረጋቸው የአሁነ መንግሰት የዛን ጊዜ “ወንበዴ” የሚባለው ነበር፡፡ ኢህአዴግ ከተማ የሚባል ነገር ለዕድገት ወሳኝ መሆኑን ለማወቅ ከአሰር ዓመት በላይ አንደወሰደበትም የማናውቅ አስመስለውታል፡፡ የከተማውን ችግር መፍታት ሲያቅተው የጀመረው “የአደገኛ ቦዘኔ” አዋጅ የበለጠ አደገኛ ሲሆንበት የተወው መሆኑን ከአቶ መኩሪያ ይልቅ እንደምናውቅ የሚነግራቸው አላገኙም፡፡ የመኢህአዱ ተወካይ አቶ ተሰፉሁን አለምነህ በስሜት ተውጦ ሰለ ቁጥር የነገራቸውን የውሸት ቁጥሮች እንደወረደ የምንቀበል እስኪመስለን ድረስ 8 ሚሊዮን ሰራ ፈጥረናል ሲሉ፣ ሰምንት ሚሊዮን ችግኝ መትከል እስኪመስለን ድረስ ነው፡፡ ኢህአዴጎች ምንም ዓይነት የፖሊሲ ለውጥ እንደሌላቸው በጀመሩት የተሳሳተ መሰመር ልክ ነው ብለው በድርቅና እንደሚቀጥሉ ለማረጋገጥ ነው መድረኩን የተጠቀሙበት፡፡ ያመኑት የመልካም አሰተዳደር ችግር፣ የአገልግሎት አቅርቦት ችግር በቁልምጫ ኪራይ ስብሳቢ በማለት የሚጠሩትን ጉበኝነትና ዘራፊነት ስልጣናቸውን ስጋት ላይ የሚጥል ሳይሆን ተራ ሊሻሻል የሚችል ነገር አድርገው አቃለው አይተውት፤ እኛም በዚሁ ልክ እንድናይ ይፈልጋሉ፡፡
የኢህአዴጉ አቶ አህመድ አብተው ብዙ ሰው የማያውቃቸው የኢንዱስትሪ ልማት ለማሰረዳት የቀረቡ የኢህአዴግ ሹም ናቸው፡፡ ተናዳፊ ሆነው አላገኘኋቸውም፡፡ እንደማነኛውም የኢህአዴግ ሹም የድሮ ሰርዓት በመክሰስ ነው ክርክሩን የጀመሩት፡፡  እንዲህ እያሉ “የኢህአዴግ ኢንድስቱሪ ልማት ፖሊሲ ሲቀረፅ - ድህነት በተንሰረፋበት፣ የግል ባለሀብት በሌለበት፣ ሁሉም ነገር በመንግስት ቁጥጥር ስር በሆነበት፣ ማህበራዊ ልማት በሌለበት፣ ካፒታል በሌለበት ወዘተ ነው” ብለው ጀምረው፤ በማስከተልም “ፖሊሲው ሲቀረፅ መሬትና ጉልበት ብቻ ነበር ያለን፡፡ ለዚህ ነው ግብርና መር መሆን አለበት ያልነው፡፡” ብለዋል፡፡ ይህን ሲሉ የፖለቲካ መሰረቴ አርሶ አደሩ ነው በሚል ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል ፖሊሲው እንደተቀረፀ የሚያውቅ ዜጋ አለ ብለው አይገምቱም፡፡ የኢህአዴጎች ዋነኛው ችግር መረጃም ሆነ ማስረጃ ከተፈቀደላቸው አንድ ምንጭ ብቻ የማግኘት አባዜ እና ሌላውም እንዲሁ እንዲሆን ማሰብ ነው፡፡
አቶ አህመድ አብተው የኢንዱስትሪ 20 ከመቶ እድገት ያስታወሰኝ አንድ ፋብሪካ ባለበት ሀገር አንድ ሲጨመር እድገቱ መቶ እንደሚሆን ያለማወቃቸው ነው፡፡ እዚህ ግባ የሚባል ኢንዱስትሪ በሌለበት ሀገር 20 ከመቶ አይደለም መቶ ከመቶ እድገትም ብዙ ለውጥ አያመጣም፡፡ በ24 ዓመት የኢህአዴግ ጉዞ ሰንት ሰው ከገጠር ግብርና ወጥቶ ኢንዱስትሪውን ተቀላቀለ የሚለው ትርጉም ያለው መከራከሪያ ሊያቀርቡልን አልቻሉም፡፡ በ24 ዓመት አሁንም “ጅማሮ ታይቶዋል” የሚል ገዢ ፓርቲ ነው ያለን፡፡ በሃያ አራት ዓመት የውጭ ባለሀብት ተነሳሽነት እና ፍላጎት በማሳይት ላይ ይገኛል፤ መቼ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ አይታወቅም፡፡ 80 ከመቶ ኢንዱስትሪ በግል ባለሀብት የተያዘ ነው በአሁኑ ስዓት 70 ከመቶ በሀገር ውስጥ ባለሀብት የተያዘ ነው ይሉናል፡፡ መንግሰት በሜጋ ፕሮጀክት በመሳተፍ መሰረት በመጣል ላይ ይገኛል፡፡ ግብርና መር ኢንዱስትሪ ልማታችን ፍሬ እያፈራ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ኢህአዴግ ከሃያ አራት ዓምት በኋላ የሚመግበን ተሰፋ ነው፡፡
አቶ አህመድ ከሌሎች የኢህአዴግ ተወካዮች የሚለዩት በማንበብ ማጠቃለላቸው ብቻ ሳይሆን ሰዓትም ሳያልቅ አቁመዋል፡፡ ለማነኛውም አቶ መኩሪያም ሆኑ አቶ አህመድ ተናዳፊነት አልታየባቸውም፡፡ ይህ ኢህአዴጎች ያመጡት በጎ አቀራረብ ነው ብለን ልንወስደው እንችላለን፡፡ ለነገሩ ቀድመው ያፈዘዙትን ተቃዋሚ አሁን ቢነድፉት ሌላ ስህተት ከመሆን አልፎ ጥቅም አያመጣም፡፡ ኢህአዴጎች በሌሎች የሚዲያ ቅስቀሳዎች ተቃዋሚዎችን ተላላኪ እያሉ መሳደባቸውን ባያቆሙም በፊት ለፊት ይህን ማቆማቸው አንድ በጎ እርምጃ አርገን መውሰድ ይኖርብናል፡፡ አማራጭ ለሌለው ምርጫ ከዚህ በላይ መዘጋጀትም አያሰፈልጋቸውም፡፡ ይህም እነርሱ ሆነው ፍርሃታቸው ልክ አጥቶ ነው እንጂ በምድር ላይ ያለው ሀቅ ይህን የሚያሳይ አይደለም፡፡ ፍርሃታቸው ልክ ማጣቱን ለመረዳት ግን በፖሊሲ ጣቢያዎች የቁሙትን አዳዲስ ፒክ ሀፕ የፖሊስ መኪኖች መመልከት ይበቃል፡፡ አሁን ይህ ምርጫ ምርጫ ሆኖ ይህ ሁሉ ዝግጅት ያስፈልገዋል ወይስ ያልገባኝ ነገር አለ?
ቸር ይግጠምን