የሰላማዊ
ትግል አማራጮች ብዙ እንደሆኑ የሰላማዊ ትግል መስመር የመረጡ ዜጎች እንደሚረዱት እሙን ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ፅሁፍ ያቀረበው ጄን
ሻርፕ ከአንሰታይን ኢንስቲትዩት አንዱ ሲሆን ይህም በህዳር 1998 ወደ አማርኛ ተመልሶዋል፤ እርገጠኛ ነኝ ይህ ፅሁፍ እንዲተረጎም
ያደረጉት ሰዎች ድህረ ምረጫ 97 የገጠመንን የሰላማዊ ትግል ክፍተት የተረዱ ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ “የሰላማዊ ትግል 101” በሚል አንድ መፅኃፍ በሰላማዊ
ትግል አቀንቃኙ ግርማ ሞገስ ለገበያ ቀርቦዋል፡፡ ይህ መፅሃፍ የቀረበበት ጊዜም ከምርጫ 2007 መቃረብ ጋር ሰናያይዘው ብዙ እንደምንማርበትና
ስላማዊ ትግል ፈታኝ መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡ የሰላማዊ ትግል ያልገባቸው እንደሚሉትም የፈሪዎች መሰመር አይደለም፡፡ በሁለቱም
መፅሃፎች የቀረቡትን የሰላማዊ ትግል መንገዶች ኢህአዴግ “ነውጥ” ሊላቸው ቢችልም የሀገራችን ተጨባች ሁኔታና የገዢዎችን እና አባሎቻቸውን
ስነልቦና በአገናዘበ መልኩ ሊተገበሩ የሚገባቸው እንደሆኑ ይታመናል፡፡ ከአምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ ለመሸጋገር ሰላማዊ አምቢተኝነት
- ነውጥ አልባ አብዮት እንደሚያስፈልገን ማንም ያምናል፡፡ ለነገሩ አሁን ያሉት ገዢዎች ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ብለው ጠመንጃ
ያነሱ መሆናቸውን ስናሰታውስ እና አሁን ደግሞ የትግል ሰልት መራጭ መሆን ሲያምራቸው ጉዳዩን ምፀት ያደርገዋል፡፡ ከእነርሱ ቀድመው
የነበሩት ንጉሡም ሆነ ደርግ አንባገነኖች ነን አላሉም- ኢህአዴግም አንባገነን ነኝ ብሎ እንዲያምን አናስገድደውም፤ እኛ ግን አንባገነን
መሆኑን እናምናለን፡፡ የትግል ስልት ምርጫም ቢሆን ከኢህአዴግ አናስፈቅድም፡፡ አሁን የመረጥነው “ሰላማዊ ትግል” ኢህአዴግን ስለሚያስደስት
ሳይሆን ዘመኑን የዋጀ አዋጭ የትግል ስልት ነው ብለን ስላመንን ብቻ ነው፡፡
የንጉሡ እና የደርግ ጊዜን ከኢህአዴግ
የሚለየው አሁን ዓለም ካለችበት ሁኔታ በተጨማሪ በስራ ላይ ያልዋለም ቢሆንም እጅግ ብዙ ዓለም አቀፋዊ ሰምምነቶችን ጨምሮ ብዙ ሰብዓዊ
ዲሞክራሲያዊ መብቶች በግልፅ የሰፈሩበት ህገ መንግሰት መኖሩ ነው፡፡ በደርግ ጊዜ “ዲሞክራሲያዊ መብቶች እውቅና ያግኙ” የሚለው
አንዱ ትግል የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ትግሉ ተግባራዊ ይሁኑ ነው፡፡ የዲሞክራሲያዊ መብቶች ተግባራዊ ከሚሆኑበት መንገድ አንዱ
ደግሞ በህዝብ ይሁንታ የሚመረጥ መንግሰት መመስረት ነው፡፡ ይህ ሂደት በሁሉም መስኩ ልምምድ ይጠይቃል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ግን
ምርጫው ይቆይ የሚሉ ድምፆች እየተበራከቱ ነው፡፡ የዛሬው ፅሁፌም መነሻም ይህ እንዲሆን ፈለግሁ፡፡
ለዛሬ
ትኩረቴን የሳቡት ከምርጫው በፊት ሀገራዊ እርቅ ይቅደም እና ከምርጫው በፊት በመስከረም አብዮት ይኑር የሚሉት እንዲሁም በአብዮት
ለውጥ ቢመጣስ ማን ይረከባል የሚሉ ሃሳቦች ናቸው፡፡ የእነዚህ አሰተያየቶች ዋናው ገፊ ምክንያት አስተያየት አቅራቢዎች በገዢው ፓርቲ
መማረራቸው ከማሳየት በተጨማሪ ለለውጥ ያላቸውን ፍላጎት ነው፡፡ ገልብጠን ስናየው ግን ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው የሚያመዝኑ አሰተያየቶች
ናቸው ብዬ ነው የምወሰድው፡፡
ከምርጫ
ሀገራዊ እርቅ ይቅደም አሰተያየት የተደመጠው ከዶክተር ያዕቆብ ሀይለማሪያም ከአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሲሆን
ይህ መልዕክት ምርጫን እንደ የትግል ስልት ይልቁንም የምናገኛቸውን አንድ አንድ ውጤቶችን የምንቋጥርበት(Anchoring
intermediate results) መሆኑንም የዘነጋ አስተያየት ይመሰለኛል፡፡
ዶክተር
ያዕቆብ በፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በንቃት እየተሳተፉ እንደሆነ ሁላችንም የምንረዳው ነው፡፡ በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ ግን በይፋ
የሉበትም ስለዚህ ምርጫን በሚመለከት በግንባር ቀደም ተወዳዳሪነት አንጠብቃቸውም በግል ዕጩ ካልሆኑ በስተቀር፡፡ ስለዚህ አሁን የሰጡት
አስተያየት በቀጥታ የሚጠቅመው ኢህአዴግን ሲሆን ጉዳቱ ደግም በምርጫ ፖለቲካ ዝግጅት ለሚያደርጉ ፓርቲዎች ላይ ነው፡፡ ይህ አስተያየት ደግሞ በቅርቡ አንድነት ከመኢህአድ ጋር ውህደት እንዲፈፅም
ሲያደርጉት ከነበረው ጥረት ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ ውህደቱ የሚያስፈልገው ከእርቅ በኋላ ለሚደረገው ምርጫ ነው ካለሉን በስተቀር፡፡
እንደ ዶክተር ያዕቆብ ኃይለማሪያም ያለ ተደማጭነት ላለው የአደባባይ ሰው እንዲህ ዓይነቱ አስተያየት ቀላል የማይባል ሰው ምርጫ ዋጋ የለውም ብሎ ከመራጭነት፣
ከታዛቢነት ከፍ ሲልም ከዕጩ ተወዳዳሪነት እራሱን እንዲያርቅ ያበረታታል፡፡ ይህ አሰተያየት ኢህአዴግን ካልሆነ ማንን ይጠቅማል?
ኢህአዴግ
የዶክተር ያዕቆብን ምክር የሚሰማ ቢሆን ኖሮ አስተያየቱ ተቀባይነት ሊኖረው ይችል ነበር፡፡ ኢህአዴግ እንዲህ ዓይነት ስልጣኑን በጥያቄ
ምልክት ውስጥ የሚያስገባ አሰተያየት እንዴት ሊቀበል እንደሚችል ማሰብ በራሱ ከባድ ነው፡፡ ዶክተር ያዕቆብ ይህን እርቅ ይቅደም
አስተያየት ሲሰነዝሩ መቼም በዚህ የእርቅ ማዕድ ኢህአዴግ አዳዲስ አባላት አፍርቶ ዕጩ እንዲያፈራ ሳይሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሊደግፉ የሚችሉ ሰዎች ከፍርሃታቸው ተላቀው ተቃዋሚ
ፓርቲዎች እንዲጠናከሩ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ ኢህአዴግ የሚፈልገው ቢሆን ኖሮ የእርቅ ማዕድ ሳይሆን የሚያስፈልገው በ1997 እንደተደረገው
እንከን የለሽ ምርጫ ማድረግ አለብን ብሎ ማወጅ ለዚህም ምቹ ሁኔታዎችን በኢህአዴግ በኩል ሳይሆን በመነግሰት መስመር እንዲከፈት
ማድረግ ነው፡፡ የ1997 ምርጫ ሁሉም እንደሚያስታውሰው ከምርጫ በኋላ እንከን በእንከን ሆኖ ተጠናቆዋል፡፡ ያለብንን የሰላማዊ ትግል
ሠራዊት ዝቅተኝነትና ዝግጁነት ተጠቅሞ ኢህአዴግ የንፁሃን ዜጎች ህይወት እዳ ወሰዶ አፍኖታል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሰለምርጫ ስናሰብ
ግን ከምርጫ 97 የምንማረው የመኖሩን ያህል በምርጫ 97 መተከዝ አለብን ብዬ አላምንም፡፡ ምርጫ 97 ታሪካችን እንጂ ምርጫ ድሮ
ቀረ እያልን የምናላዝንበት መሆን የለበትም፡፡
እንደ
እኔ አምነት የዶክተር ያዕቆብን ሃሳብ ለመቀበል ኢህአድግ ከተዘጋጀ ኢህዴግ መንኩሶዋል ማለት ነው፡፡ እንደ ጳውሎስ ቀደም ሲል የሰራውን
ግፍና መከራ ትቶ ወደ መልካምነትና ቅዱስነት ተሸጋግሯል ማለት ነው፡፡ አንባገነን መንግሰታት ባህሪ አይቀይሩም ማለት ባይሆንም ኢህአዴግ
በዚህ ደረጃ እንዲያድግ እኛም ተገቢውን ግፊት አላደረግንም የሚል እምነት ስላለኝ ነው፡፡ እሰከ አሁን የሄድንበት መንገድ የተለመደ
እና ኢህአዴግ ደግሞ እንዴት እንደይሰሩ ማድረግ እንዳለበት በደንብ ያውቃል፡፡ ሰለዚህ እኛም የተለየ መንገድ ማሰብ ይኖርብና፡፡
ምርጫው
ይራዘም የሚል አሰተያየት የቀረበው ከዶክትር ያዕቆብ ብቻ ሳይሆን የፋክቱ ቋሚ አምደኛ ተመስገን ደሳለኝም አቅርቦታል፡፡ የተመስገን
ምርጫው ይራዘም ጥያቄ ተግባራዊ የሚሆነው በመስከረም ቢሆን የመረጠው የህዳሴው አብዮት የሚመጣ ከሆነ ነው፡፡ የተመስገንን የህዳሴው
አብዮት ማስፈፀሚያ ስትራቴጂ ጥሪ ተቀብለው በተለይ ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አብዮቱን የመሩት ከሆነ የአብዮቱ
መሪዎች የምርጫውን ቀን የሚወስኑት ሲሆን፤ መቼም ይህ ከሆነ በእቅድ የተመራ አብዮት ተብሎ በታሪክ የሚመዘገብ ይሆናል፡፡ ይህ ገና
ለገና በቢሆን የቀረበ የህዳሴ አብዮት ጥሪ ተግባራዊ ካልሆነ ከዚህ አሰተያየት የሚጠቀመው አሁንም ኢህአዴግ እንጂ ለምርጫ ዝግጅት
የሚያደርጉ ፓርቲዎችን ሊሆኑ አይችሉም፡፡ መቼም ተመስገን ደሳለኝ በህዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ሰናሰብ የዚህ አሰተያየት ጉዳት
ከፍ ያለ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡
ንጉሡ
ቢወርዱ ማን ይተካቸዋል፣ ደርግ ቢወድቅ ማን ይተካል ሲባል እንደነበረ ሁሉ ዛሬም ከኢህአዴግ በኋላ ማን ሀገር ሊመራ ይችላል የሚል
መሞገቻ ይዞ በሸገር ሬዲዮ ዋዘኛ በሚል አዲስ የተጀመረ ፕሮግራም ላይ የተመስገን ደሳለኝን
ህዳሴ አብዮት አሰተሳሰብ ሲሞግት ሰምተናል፡፡ ጋዜጠኛው የተመስገንን የህዳሴ አብዮቱን መሞገቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህችን ትልቅ ሀገር
ከኢህአዴግ ሌላ ማን ይመራታል? ብሎ አማረጭ የሌለን አድርጎ ማቅረብ ጤነኛ ሃሳብ አድርጌ ለመውሰድ እቸገራለሁ፡፡ ይህን ፕሮግራም
የሰማሁት በዛሚ ወይም በፋና ቢሆን አይገርመኝም፤ በሸገር ሲሆን ግን ብዙ ዜጎችን ያሳሰታል ብዬ ሰለምሰጋ ነው፡፡ ሀገራችን ትልቅ
ነች ሰንል በቆዳ ሰፋት ብቻ አይደለም ባላት ምርጥ የሰው ሀይል ጭምር ነው፡፡ እነዚህ ዜጎች ለምን ከኢህአዴግ ጎን አይታዩም? ለሚለው
ጥያቄ መልሱ ኢህአዴግ የምርጦችና የምጡቃን ስብስብ ቤት ስላልሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ሊመሩ የሚችሉትን ሰዎች በኢህአዴግ አፈና ምክንያት
በፊት ለፊት ከተቃዋሚ ጋር ወይም ከኢህአዴግ ጋር ስላላየናቸው የሉም ማለት ግን ትልቅ ሰህተት ነው፡፡
በእኔ
እምነት በዚህ ጊዜ የሚያስፈልገው ለምርጭ ዝግጅት ህዝቡ እንዲነቃቃ ማድረግ ለታዛቢዎች አሰፈላጊውን የሞራል ትጥቅ ማስጨበጥ ዕጩዎች
በግል ከሚያደርጉት ዝግጅት በተጨማሪ የሚጎድላቸውን በሞራልም በፋይናንስም ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ በተለይ ዶክተር ያዕቆብ እና ተመስገን
በኢትዮጵያችን ለውጥ እንዲመጣ ያላቸውን ጉጉት ሰለምረዳ፤ የሚፈልጉት ለውጥ ግን ደረጃ በደረጃም ቢሆንም ሊመጣ እንዲችል ተጨባጭ ድጋፍ ሊያደርጉ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ በዋነኝነት እነዚህ የአደባባይ
ሰዎች ምርጫ ይራዘም ከሚለው አቅጣጫ ወጥተው በቁርጠኝነት ምርጫውን በግላቸው መደገፍ እና አድናቂዎቻቸውም በምርጫ እንዲሳተፉ ግፊት
ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያገባናል ከሚሉ የአደባባይ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የሚጠበቀው፤
·
ደጋፊዎቻቸው እና አድናቂቆቻቸው
በምርጫው ለመሳተፍ በመራጭነት፣ በታዛቢነት ብሎ በዕጩነት እንዲነሳሱ ማበረታታ እና
·
ደጋፊዎቻ የሚችሉትን ድጋፍ ለማድረግ እንዲችሉ ለማበረታት ደግሞ እራሳቸውን በአራሃያነት
ማቅረብ
ነው፡፡ ይህን ካደረግን
በሁለት ሺ ሰባት በሚደረግ ምርጫ ቀላል የማይባሉ የምርጫ ክልሎችን ነፃ ማውጣት እንዳለብን ማመን የግድ ይላል፡፡
አማራጭ የለም ብለው ወደኋላ የሚሉትን ለመሳብ ፓርቲዎች የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ባለፈው የምርጫ ፖለቲካን አስመልክቶ
የፃፍኩትን አሰተያየት አንብቦ አንድ ወዳጄ አማራጭ ሳይኖር ለምርጫ መመዝገብ ምን ዋጋ አለው ብሎ ጠየቀኝ፡፡ የእኔም መልስ “በእኔ
በኩል ኣማራጭ የለም በሚለው አልሰማማም፡፡ በቂ አማራጭ አለመኖሩን ግን መካድ አይቻለም ነገር ግን የምርጫ ካርድ የወሰደ ሰው አማራጭ
የለም ብሎ ካመነ የምርጫ ካርዱን ይዞ ያለመምረጥ መብት አለው፡፡” የሚል ነበር፡፡ ይህን ማድረግ ትልቅ የፖለቲካ መልዕክት ያስተላልፋል፤
በገዢው ፓርቲ አፈና ምክንያት አማራጭ አጥተናል ብለን ካመንን የምርጫ ካርዳችን ላይ በምርጫ ያለመሳተፋችንን የሚገልፅ ምልክት አድርገን
ምርጫ ቦርድ ጊቢ ወይም ፓርላማ ጊቢ ውስጥ በመወርወር ተቃውሞ ብናደርግ ተቃውሟችን በመረጃ የተደገፈ ለማድረግ ይረዳናል፡፡ ባለፈው
ለማሳየት እንደሞከርኩት በምርጫ የተሳተፈ ህዝብ ድምፃችን ይከበር ብሎ መንግሰትን ሊያስገድድ ይችላል፡፡ ያልመረጠ ግን ምን ድምፅ
አለው? ምንስ ሞራል ይኖረዋል ድምፃችን ይከበር ለማለት? ድምፃችን ይከበር ለማለት በምርጫ መሳተፍ የግድ ይላል፡፡ ሁላችንም የምርጫውን
ግንባር ለመደገፍ እንትጋ ከአደራ ጋር የማስተላልፈው መልእክት ነው፡፡
ቸር ይግጠመን