Sunday, November 30, 2014

ምርጫ መሳተፍ በመርዕ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ወይስ ኢህአዴግን ማጀብ?

 ሰዎች በማንኛውም መንገድ ሸብረክ ሸብረክ የሚሉ ከሆነ መርህ አልባ መሆናቸውን ከማሳየት ውጭ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡ ባለፈው ሳምነት ፍኖተ ነፃነት ላይ ወጣቱ ፀሃፊ ኢዮኤል ፍስሃ ዳምጤ ለምን እንደምንፈራ ቁልጭ አድርጎ አሳይቶን ነበር፡፡ የገዢዎቻችን በትር የበረታብን በእነርሱ ጥንካሬ ሳይሆን ከፍርሃት በመጣ ዝምታችን እንደሆነ አስምሮበታል፡፡ መፍትሔውም ከፍርሃት መላቀቅና ዝምታውን ማፍረስ ነው፡፡ በዛሬው ፅሁፌ ማንሳት የፈለኩት ደግሞ ለምን ሸብረክ ሸብረክ እንደምንል ነው፡፡
ለምንድነው ኮሽ ሲል ደንግጠን ከቆምንበት “መርዕ” ከምንለው አስተሳሰብ የምንሸራተት? እንዲህ ከሆነ ቀድሞውንም መርዕ አልነበረንም ማለት ነው፡፡ መርዕ ብለን የምንይዘው አሰተሳሰብ በእኔ እምነት ለምናደርገው እንቅስቃሴ የማዕዘን ድንጋይ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ መርዕ ሸርተት ስንል ቀጥሎ የምናገኝው ሌላ የተሻለ ማዕዘን የሚሆን ድንጋይ ሳይሆን ድጥ ወይመ ማጥ ነው የሚሆነው፡፡ ብዙዎች መርዕ የሚመስላቸው በአቋራጭ የሚፈልጉትን ግብ የሚያሳካ አጭር መንገድ አድርገው ይወስዱታል፡፡ ይህ አቋራጭ መንገድ ግን ብዙን ጊዜ ወደ ሌላ ውጥንቅጥ ከመውሰድ አልፎ ለስኬት ሲያበቃ አይታይም፡፡
ግልፅ ያልሆነ የህይወት ግብ ያለን ሰዎች የምንሄድበትን ስለማናውቅ ሌሎች በሄዱበት ተከትለን እንነጉዳለን፣ ሌሎች ግባቸውን ሲያሳኩ እኛ የበይ ተመልካች መሆናችን አይቀርም፡፡ ግባችን ግልፅ ያለመሆኑ መድረሻችንን ብቻ ሳይሆን መነሻችንንም ስሚያዛባው ከየት ተነስተን የት እንደምንደርስ፣ እንዴት እንደምንደርስ እንዳናውቅ ያደርገናል፡፡ መርዕ ማለት አሁን ካለንብት ቦታ ተነስተን ወደምንፈልገው ቦታ ለመድረስ የምንጓዝበት ፍኖተ ካርታ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአሰተሳሰብ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ልክ መሆን ያለበት ነው፡፡ አንድ አንድ ሰዎች የምንፈልገውን ግብ ለማሳካት ማነኛውንም መንገድ መጠቀም ችግር የለውም ይላሉ፡፡ ይህ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው /the end justify the means/ የሚባለው ዓይነት መሆኑ ሲሆን፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ሌሎች የምንሄድበት መንገድ እንደ ወጤቱ ሁሉ መርዕ ላይ መመስረት አለበት የሚሉ ናቸው /The means is equally important as the end/:: በግሌ የማምነውም የምከተለውም የኋለኛውን አማራጭ ነው፡፡ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭው የስግብግቦች መንገድ ነው ብዬ በፅኑ ስለማምን፡፡
ሰሞነኛ ወደ ሆነው የምርጫ አጀንዳ እና በመርዕ ላይ የተመሰረተው የአንድነት ፓርቲ ምርጫ እሳተፋለሁ ውሳኔ እንዴት መታየት እንዳለበት በአጭሩ ይህን አቋም ለደገፉም ሆነ ለተቃወሙ ማሰረዳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ አንድነት ፓርቲ ስልጣን የሚገኘው በህዝብ ድምፅ ነው የሚል መርዕ አለው፡፡ የህዝብ ድምፅ የሚገኘው ደግሞ በምርጫ ወቅት መራጩ ህዝብ በሚሰጠው ካርድ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በምርጫ የህዝብ ድምፅ ይገኛል ማለት ነው፡፡ ብዙዎች ምርጫ ለመሳተፍ እኩል ሜዳ ያሰፈልጋል ይላሉ፡፡ ትክክል ነው እኔም አምንበታለሁ፡፡ ሜዳውን ትክክል ከሚያደርገው አንዱ ጉዳይ የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ካልሆነ ማለትም ሜዳው ትክክል ካልሆነ ስልጣን በሌላም መንገድ መያዝ ተቀባይነት አለው የሚል መከራከሪያ ለማቅረብም ሰበብ ይሆናል፡፡
ስልጣን በተለያየ መንገድ ለመያዝ እንደሚቻል አማራጭ ማሳየት አንድ ጉዳይ ሆኖ እኛ የመረጥነው ብቻ ልክ ነው ማለትም ተገቢ አይደለም፡፡ በተገኘው መንገድ ለመያዝ መሞከር ግን መርዕ አልባ ያደርገናል፡፡ ሰላማዊ ትግል እከተላለሁ ብሎ በሰላማዊ ትግል መርዕዎች አምናለሁ የሚል ማታ-ማታ ወይም ቅዳሜና-እሁድ በሌላ መንገድ ልሞክር የሚል ከሆነ መርዕ አልባነት ነው፡፡ በእኔ እምነት ችግር ያለው የምርጫ ሜዳ ላይ ከሆነ የምርጫው ሜዳው ለማስተካከል ምን አድርገናል? ከሚለው መነሳት አለበት፡፡ ስልጣን የመያዣው መንግድ ኮሮኮንች በዝቶበታል ማለት ኮሮኮንቹን እንዴት እናሻሽል ወደሚል ሊገፋን ይገባል፡፡
ሁሉም ሰው መረዳት ያለበት ገዢው ፓርቲ የምርጫ ሜዳውን ያጠበበው ወይም ኮሮኮንች እንዲበዛበት ያደረገው አውቆ ነው፡፡ ሜዳው ደግሞ የጠበበን ደግሞ አማራጭ አለን የምንል ፓርቲዎች ነን፡፡ አማርጭ ለማቅረብ እድል ስንነፈግ መጠየቅ ያለብን አንድ መስረታዊ ጥያቄ አማራጭ የተከለከለው ህዝብ ምንም ማድረግ አለበት የሚለው ነው? አማራጭ የሚፈልግ ህዝብ ድንጋይ ወይም ጠብመንጃ ይዞ አማራጭ አትከልክሉን ቢል ነው የሚሻለው ወይስ የምርጫ ካርድ ይዞ? አንድነት የመረጠው መስመር የምርጫ ካርድ ይዞ ቢሆን ይሻላል የሚለውን ነው፡፡ ይህ በምንም ዓይነት ሌሎች የመረጡት መስመር አይሰራም ማለት አይደለም፡፡ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጭውን እንደ መርዕ የተቀበለ ብዙ ሌላ አማራጭ ሊያስብ፣ ሊተገብር ይችላል፡፡ ችግሩ የእኛ ካልሆነ ብሎ የሌሎችን ምርጫ ለማክበር አለመፈለጉ ላይ ነው፡፡
በሀገራችን ኢትዮጵያ በ1997 ከተደረገው ምርጫ ውጭ ህዝቡ በምርጫ እንዲሳተፍ የምርጫ ካርድ እንዲወስድ በተቃዋሚ ፓርቲዎች በተገቢው መልኩና ደረጃ ተቀስቅሶዋል የሚል እምነት የለኝ፡፡ ከ1997 በፊት ምርጫ መወዳድር ወያኔን ማጀብ ነው እያልን ምርጫ የሚወዳደሩትን ብቻ ሳይሆን መራጩንም ተሰፋ እያስቆረጥን ኖረናል፡፡ ይህን ምርጫ የማጣጣል ስትራቴጂያችንን በደንብ የተረዳው ገዢው ፓርቲ የራሱን መራጮችና ተመራጮች እያዘጋጀ ውድድር ሲያድርግ ነበር፡፡ እንደዚያም ሆኖ ህዝቡ በምርጫ ካርዱ ቅሬታውን ሲገልፅ እንደ ነበር የገዢው ፓርቲ የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዴእታ የነበሩት አቶ ኤርሚያስ ለገሠ “የመለስ ትሩፋቶች” በሚለው መፅሃፍ አስነብቦናል፡፡ ስለዚህ የአንድነት ቤተሰቦች ምርጫ እንሳተፋለን ስንል መራጮቻችን እንዲመዘገቡ እናደርጋለን ማለት ነው፡፡ የእኛ መራጮች ሲመዘገቡ፣ ገዢው ፓርቲ የእኔ ብሎ ያስመዘገባቸውም ቢሆኑ እኛን ለመምረጥ እንዲችሉ መሸሸጊያ እንሰጣቸዋለን፡፡
ብዙ ሰው መረዳት ያለበት የምርጫ ቅስቀሳ የሚጀመርበት ወቅት መራጮች ምዝገባ ሊጠናቀቅ ሳምንት ሲቀረው ነው (በ1997 ቀድሞ የምርጫ ቅስቀሳ ተጀምሮ ነበር)፡፡ ለዚህ ነው ገዢው ፓርቲ ሁል ጊዜ የሚጮሁት ካርድ ያልያዙ ናቸው የሚለው፡፡ ያስመዘገባቸውን ስለሚያውቅ ነው፡፡ የእኛ መራጮች ካርድ ባልያዙበት ሁኔታ የፈለገ አማላይ የሆነ ለሀገር የሚጠቅም አማራጭ ብናቀርብ ለማሸነፍ ያለን እድል አነስተኛ ነው፡፡
ማስተላለፍ የፈለኩት ነጥብ ምርጫ እገባለሁ-አልገባም በሚል ዥዋዝዌ ስንጫወት ደጋፊዎቻችን በመራጭነት ሳይመዘገቡ እንዳይቀሩ በአንድነት በኩል የተወሰደው እርምጃ ትልቅ ፖለቲካ ውሳኔ ነው፡፡ የምርጫ ፓርቲ መሆናችን የሚታወቅ ቢሆንም እስከ አሁን በተቃዋሚ ፓርቲዎች መስመር ምርጫ መግባትና አለመግባት በቁርጥ ቀድሞ ስለማይወሰን መራጮች ሁለት ልብ እየሆኑ ከጫወታ ውጭ ሲደረጉ ከርመዋል፡፡ ይህ እንዳይደግም መራጮች እንዲመዘገቡ እና በምርጫው ሙሉ ሂደት በንቃት እንዲሳተፉ ይህን አቋም መያዝ እጅግ አስፈላጊ እና ጠቃሚ ነበር፡፡ ሁሉም እንደሚረዳው ያልተመዘገበ ደግሞ አይመርጥም፣ ያልመረጠ ደግሞ ድምፁ እንዲከበር ዘብ ሊቆም አይችለም፡፡ ድምፃችን ይከበር የሚለው እንቅስቃሴ የሚጀምረው ከህዝብ ታዛቢዎች ምርጫ እሰከ ድምፅ ቆጠራ ድረስ ይዘልቃል፡፡
ጎበዝ ሰላማዊና ህጋዊ ትግል እናደርጋልን ስንል የሰላማዊና ህጋዊ ትግል መርዖዎችን ጠንቅቀን መረዳት የግድ ይለናል፡፡ በስላማዊ ትግል ዋናው ግብ የህዝብን የስልጣን ባለቤትነት ማረጋገጥ ሲሆን፣ ስልጣን መያዝ የሚፈልግ ፓርቲ የህዝብ ይሁንታ ማግኘት የግድ ይለዋል፡፡ ይህ ደግሞ በምርጫ የሚገኝ ነው፡፡ ምርጫውን የህዝብ ፖለቲካ ተሳትፎ መለኪያ አድርገን ለመውስድ ቁርጠኞች መሆን የግድ ይለናል፡፡

ቸር ይግጠመን

Wednesday, November 26, 2014

ህዝቡ የሚለው …..


ዛሬ በርዕስነት የመረጥኩት ጉዳይ ለመፃፍ ካሰብኩ ቆይቻለሁ፡፡ መልዕክት ማስተላለፊያው መንገድ ሲዘጋ በጅምር ትቼው ነበር፡፡ ለዛሬ የ “ፍኖተ ነፃነት” ጋዜጣ እንዲሆን ብዬ ሳዘጋጀው የቱን አንስቼ የቱን እንደምጥል ግራ ገብቶኝ ለ “ህዝብ ጥቅም” ሲባል ከሚወሰዱት ህገ ወጥ እርምጃዎች የቅርብ የቅርቦቹን ብቻ ለማንሳት ወሰንኩ፡፡
የ “የፀረ ሽብር ህግ” ከምንጊዜውም በላይ ተግባራዊ እየተደረገ ያለበት ወቅት ላይ እንደምንገኝ ማንም ሰው ይረዳዋል ብለን እናምናለን፡፡ ሀገራት ሽብርን ለመከላከል የሚያስችላቸውን የህግ ማዕቀፍን ጨምሮ ሌሎች አወቃቀራቸውን በማደረጀት ህዝብን ከአደጋ ለመጠበቅ ዝግጁ መሆ እንዳለባቸው ዓለም አቀፍ ጥሪ ከቀረበላቸው ቆየት ቢልም ኢትዮጵያ ሀገራችን ዘግየት ብላም ቢሆን ከዓለም አቀፍ ማዕቀፉ ውጭ የዜጎችን ስብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለማፈን የሚረዳ ህግ አውጥታ ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች፡፡ ለ “ህዝብ ጥቅም” ሲባል በሚል ማስመሰያ ብዙ ኢትዮጵያዊያን የ “ፀረ ሽብር” ህጉ ሰለባ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ በመላው ዓለም ፍተሻ ቢደረግ ዜጎቹን በሽብርተኝነት  በ“ፀረ ሽብር” ህግ የሚያንገላታ መንግሰት የሚገኘው እዚህ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ብቻ ነው፡፡ የሌሎች ሀገሮች የፀረ ሽብር ህግ ትኩረቱና ግብ ሀገርን ከውጭ ሀገር ከሚመጣ የተደራጀ አሸባሪ ቡድን መጠበቅ ነው፡፡
በ “ፀረ ሽብር ህግ” ተከሰው ቅጣት ከተጣለባቸው ውስጥ ቅጣት የሚገባቸው ተከሳሾች የሉም የሚል ጭፍን ዕየታ የለኝም፡፡ እነዚህ ሰዎች በወንጀል ህጉ ሊቀጡ የሚችሉ እንደሆነ ግን መቶ በመቶ እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች እየታደኑ “በፀረ ሽብር” ህግ ስም የሚታጎሩት ግን ለህዝብ ደህንነትና ሰላም ሳይሆን በገዢዎች ወንበር ላይ በሚፈጥሩት ሽብር ነው፡፡ እነ አንዱዓም አረጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ ሽብር የነዙት በአራት ኪሎ ወንበር ላይ ነው፡፡ የእነርሱ ድምፅ ለህዝቡ የነፃነት ድምፅ ነው፡፡ የተሰፋ ድምፅ ነው፡፡ አሁንም በብዞዎች የሚዘመር እና ወደፊትም ለክብር የሚበቃ የነፃነት ድምፅ፡፡

ሌላ የሰሞኑ ወሬ የግል ሚዲያዎች ህዝቡን ለብጥብጥ ህገመንግሰታዊ ሰርዓቱን በሀይል ለመናድ እየተንቀሳቀሱ እንዴት ዝም ተባሉ የሚለው ነው፡፡ የመንግሰት የፖሮፓጋንዳ ሚዲያዎች የህዝብ ጥያቄ እነዚህ ሚዲያዎች ለፍርድ ይቀረቡ የሚል ነው፡፡ ይህ በእውነት የህዝብ ጥያቄ ከሆነ ይህን ጥያቄ ያቀረበ ህዝብ ለምን አዲስ ዘመን ተሯሩጦ አይገዛም? ለኢቲቪም ያለምንም ውትወታ፣ ማስታወቂያና ማስፈራሪያ ዓመታዊ ኪራይ አይከፍልም? ለምን የግል ሚዲያ ህትመቶችን ተሻምቶ ይገዛል? ነገሩ ግን አንዲህ አይደለም፡፡ አንድ ቅምጥል የንጉስ ዘር የህዝብ ብዛት 20 ሚሊዮን ደርሶዋል ብትባል ምናምንቴውን ቆጥረው ይሆናል እንጂ እኛ ከአምሰት መቶ አንበልጥም ብላለች ተብሎ የሚበላ ወሬ አለ፡፡ ሕዝብ ለዚህች ቅምጥል ትርጉሙ የተለየ ነው፡፡ ለእኛዎቹ ቅምጥሎች ደግሞ ህዝብ የሚባለው ሌላ ትርጉም ካልተሰጠው እና አሁን በብዛት የግል ሚዲያ ሰርጭት ያለበት አዲስ አበባ ከሆነ እኛ ነን ህዝብ የምንባለው ካላሉን በስተቀር ነገሩ ለየቅል ነው፡፡ ህዝቡ እያለ ያለው ቅዳሜ ምን ልናደርግ እንውጣ? ነው፡፡ ቅዳሜ ተወዳጇ ፋክት መፅሔትን ጨምሮ ሌሎች ብዛት ያላቸው ህትመቶች ለገበያ ቀርበው የሚያነብበት ቀን ስለነበር ነው፡፡ በዚህ እለት አዲስ ዘመን በገበያ ላይ ብትውልም የሚመለከታት እንደሌለ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ለጨረታ ማስታወቂያ ከሚፈልጉት ውጭ ማለቴ ነው፡፡
ሌላው የህዝብ ጥያቄ በእሰር ላይ የሚገኙትን ፍቱልን የሚል እንደሆነ ለመረዳት ፈላስፋ መሆን አያስፈልግም፡፡ በቅርቡ ቂሊንጡ እስር ቤት ሄጄ የታዘብኩት አንድ ነገር እጅግ ብዛት ያለው እስረኛ መኖሩን ነው፡፡ ተቃዋሚዎች እስር ቤት የሌለው መንግስት እንደማይመሰርቱ የታወቀ ቢሆንም በአሁኑ ሰርዓት ከህግ ውጭ ታስሮ መንገላታት ግን በግልፅ የሚታይ ሀቅ ሆኖዋል፡፡ ህዝቡ በግፍ የታሰሩትን ፍቱልን ሲል የቅምጥሎቹ ወገን የሆኑት ደግሞ እነዚህ ታሳሪዎች አሸባሪዎች ናቸው ይሉናል፡፡ እውነት እነዚህ ሰዎች አሸባሪ ከሆኑ ሰፍር ቁጥር የሌለው ህዝብ በየፍርድ አደባበዩ እና በየማጎሪያ ሰፍራ ለምን ይገኛል? እነዚህ በመንግሰት አሸባሪ የተባሉ ሰዎች ህዝቡ ለምን በፈቃዱ ይጎበኛቸዋል? እነዚህ ታሳሪዎች መጎብኘት የሚፈልግ ሁሉ በነፃነት እንዳይጎበኝ ለምን የተጠና እገዳ ይጣልባቸዋል? እዚህ ጋ ምፀት የሚሆነው ጉብኝት እግድ የሚጣለው “አሸባሪ” ብለው ያሰሯቸው እስረኞች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ነው የሚለው ነው፡፡ የሚያገላቱዋቸውም ለእነርሱ ደህንነት ብለው ነው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ህዝቡ እያለ ያለው መሰረት የሌላቸው ሲከፋም ህገወጥ የሆነ የአቃቢ ህግ ክስና ይህን መሰረት አድርጎ የሚሰጥ የፍርድ ቤቶች ውሳኔ ይቁም ነው የሚለው፡፡ በመንግሰት በተጠና ጥናት እምነት የማይጣልባቸው ተቋማት የተባሉት እነዚህ ተቋማት በዚህ ድርጊት አሁን ባለው ጥልቀት መሳተፋቸው የተዓማኒነት ጉድለታቸውን ከማሳደግ ውጭ የህዝብ ጥያቄን አይመልስም የጊዜ ጉዳይ እንጂ የገዢዎችንም ወንበር አያፀናም፡፡
ሕዝቡ እያለ ያለው በየአምሰት ዓመት ምርጫ ቢመጣም አማራጭ አሳጣችሁን፡፡ አፈናውን አቁሙና ፍላጎት ያለው ተደራጅቶ አማራጭ ያምጣ ነው፡፡ የመደራጅት መብት ያለምንም ገደብ ይከበር!! ሕገመንግሰት ላይ በተቀመጠው መሰረት ተግባራዊ ይሁን!!! ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ህዝቡ ያለው አሁንም የሚለው፡፡ እዚህ ላይ ገዢው ፓርቲም የመንግሰት መዋቅርን ተጠቅሞ የሚያደርገው አፈና አማራጭ አሳጣን እንጂ ደግ አደረጋችሁ የሚል ድምፅ አይሰማም፡፡ በቅርቡ በመንግሰት ድጋፍ በገዢው ፓርቲ አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ መስመርና ልማታዊ መንግሰት ፍልስፍና ዙሪያ የተደረጉት ከ-እሰከ የማይገልፃቸው ስብሰባዎች ያረጋገጡት ሀቅ ኢትዮጵያዊያን አማራጭ እንደሚፈልጉ እና የመንግሰት ህገወጥ አካሄድ እንዲቆም ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን እንደ ህዝብ ያቀረቡት ጥያቄ ከልማት እኩል ነፃነት ይገባናል ነው፡፡ ነፃነት ልማትን ያሳልጣል እንጂ የልማት ደንቃራ የሚሆንበት አንድም በቂ ምክንያት እንደሌለ ህዝቡ ተገንዝቦዋል፡፡ ህዝቡ የሚለው ነፃነታችንን አትንኩ ነው፡፡
ህዝቡ አሁንም እያለ ያለው የእምነት ነፃነት ይከበር የመንግሰት ጣልቃ ገብነት ይቁም ነው፡፡ ባለፈው ሰሞን ኢሳት የሚባል ለኢህአዴግ እሣት የሆነ ሚዲያ በቅርቡ ይፋ ያደረገው የሰብሰባ ውስጥ ውይይት መንግሰት በምን ያህል ጥልቀት በሙስሊሞች ጉዳይ ጣልቃ እንደሚገባ ብቻ ሳይሆን የሙስሊሙን ማህበረሰብ ለመምራት በሚል የአመራር ቦታ “የቀሙት” ሰዎች ግብ ምን እንደሆነ አጋልጧቸዋል፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ እያለ ያለው እምነታችን በካድሬ አይመራም ነው፡፡ የኢሳትን ተደማጭነት ያጎላው የሀገር ውስጥ አፈና መሆኑን ለመረዳት ነብይ መሆን ያስፈልግ ይሆን? ህዝቡ እያለ ያለው አፈና ይቁም!!! ሀሳብ በነፃነት ማንሸራሸር የሚፈቅደው ህገመንግሰታዊ ድንጋጌ ይከበር ነው፡፡
ለማጠቃለል መንግሰት በህዝብ የመደራጀትና ሃሳብን በነፃነት የማንሸራሸር መብት ላይ በህዝብ ስም ገደብ እያደረገ ቢሆንም ህዝቡ ግን በተቃራኒ እየጠየቀ ያለው እነዚህ መብቶች ያለምንም ገደብ ይከበሩ ነው፡፡ እነዚህን መብቶች ተጠቅሞ በህዝብ ጥቅም ላይ ጉዳት የሚያድርስ ቡድንም ሆነ ግለሰብ ቢመጣ ህዝብ ለመቅጣት የሚያስችለው አቅም አለው እያለ ነው፡፡ የህዝብ ድምፅ ይሰማ፡፡
ቸር ይግጠመን!!!!


Saturday, November 22, 2014

የነፃነቴ ዋጋ ነብሴ ነው!!!


 መረጃ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ጠቃሚ ነው ብሎ መንገር ለቀባሪ እንደማርዳት ነው፡፡ የተሟላ መረጃ የሰውን ልጅ ሙሉ ያደርገዋል፡፡ መረጃን አጣሞ ማቅረብ ደግሞ የሰውን ልጅ ውሳኔ ለማጣመም ካልሆነ በስተቀር ግቡ ምን ሊሆን እንደሚችል አይገባኝም፡፡ በሰሞኑ ሰው በላው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በጥርሱም በጥፍሩም ዘመቻ የጀመረው እኔ ላይ ነው፡፡ ዓላማው ግልፅ ነው፡፡ በነፃነት የማሰብ መብቴን ለድርድር እንዳቀርብ ነው፡፡ ለነፃነቴ ያለኝን ዋጋ የማያውቁ ሰዎችን ይህንን ለማድረግ ቢሞክር ካላቸው የመረጃ እጥረት ወይም ማወቅ ባለመፈለጋቸው ነው፡፡ አንዳንድ ቅን ሰዎች ሰህተት እንደሰራው አድርገው ይቅርታ እንድጠይቅ፤ ይቅርም እንድባል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በቅን ልቦና ላደረጋችሁት ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡ ነገር ግን በሰጠሁት አስተያየት ያልተስማማ ሰው በሃሰብ ልዮነት መለያየት እያለ ይቅርታ ጠይቄ፤ ይቅርታም ተደርጎልኝ ወደ እነሱ ሃሳብ እንድገበ መፈለጉ ምን ዓይነት ከፍተኛ ችግር ያለበት አስተሳሰብ እንደሆነ የተረዱት አይመሰለኝም፡፡ ይህ ደግሞ በጣም አስገራሚ የሚሆነው የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ደጋፊ፣ ለግለሰብ ነፃነት እንቆማለን የሚሉ ወገኖች መሆናቸው ነው፡፡ ለሃሳብ ነፃነት የማይቆም እንዴት አድርጎ ለመድበላ ፓርቲ ስርዓት ግንባታና የግለሰብ ነፃነት እንደሚያከብር አይገባኝም፡፡
ጫጫታ ወደ ፈጠረው አጃንዳ ስገባ፡፡ አንድነት ፓርቲ የምርጫ ግብረ ሀይል ማቋቋሙን ለህዝብ በይፋ ለማሳወቅ እና በቀጣይ ሳምንት ስለሚያደርገው የህሊና እስረኞች ስለሚታሰብበት ፕሮግራም መግለጫ በሰጠንበት ወቅት በፍፁም ጠቃሚ ያልሆነ የተቃዋሚ ጎራውን በተለይ በሀገር ውስጥ ለምንገኝ ሰዎች የማይጠቅም (በኢቲቪ ቢቀርብ የማይገርም) ጥያቄ ቀረበ፡፡ ጥያቄው በእስር ላይ የሚገኙ የቀድሞ አንድነት አባል የነበሩ ታሳሪ ስም ጠርቶ በአንድነት አቋም እኝህ ሰው የህሊና እስረኛ ናቸው ብላችሁ ታምናላችሁ ወይ? የሚል ነበር፡፡ የሰጠሁት መልስ የማንንም ታሳሪ ስም ማንሳት ሳያስፈልግ የአንድነት ፓርቲ አባል ሆኖ የሌላ ፓርቲ አባል መሆን ትክክል እንዳልሆነ፣ ከአንድነት ጋር በትግል ስትራቴጂ ከማይመሳሰሉት ጋር ብቻ ሳይሆን በትግል ከሚመሳሰሉትም ጋር ቢሆን የተሻለ ወደሚለው መጠቃለል እንጂ ሁለት ቦታ መሆን ትክክል እንዳልሆነ አስረድቻለሁ፡፡ በማስከተልም “በፀረ ሽብር” ህግ መንግሰት እየከሰሰ የሚያስራቸው ሰዎች አንዳንዶቹ በወንጀል ህግ ሊያስጠይቅ የሚችል ሰህተት አልሰሩም የሚል ድምዳሜ እንደሌለኝ አሰረግጬ ተናግሬያለሁ፡፡ ለምሳሌ በፈንጂ ስው የገደለ ሰው በወንጀለኛ ህግ መጠየቅ እና መቀጣት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ እምቴ አሁን ፅኑ ነው፡፡ የ “ፀረ ሽብር” የሚባለውን ህግ በይፋ አሸባሪ ህግ ነው፡፡ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች አሸባሪ እየተባሉ የሚታሰሩ ያሉት የአራት ኪሎን ወንበር ስለሚያሸብሩ ነው የሚል አቋሜን ከብዙዎቹ ተችዎቼ በላይ እና ከማንም በማያንስ መልኩ ሃሳቤን በነፃነት አራምጃለሁ፡፡ ይህን ሳራምድ ማንንም ለማስደስት ሳይሆን አምኜበት ነው፡፡ አንድነት የ “ፀረ ሽብር” የሚባለው ህግ እንዲሰረዝ የተገበረውን “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” ዘመቻ በቁርጠኝነት ከመሩት አንዱ ስሆን፤ በተለይ በደሴ ከተማ የተደረገውን የሚሊዮኖች ድምፅ ዘመቻ በቦታው ተገኝቼ የመራሁት እኔ ነኝ፡፡ ይህን ሁሉ የምዘበዝበው በዚህ ህግ ላይ ያለኝን ግልፅ አቋም በድጋሚ ለማረጋገጥ ነው፡፡
በእኔ በኩል የአቋም ለውጥ ሳይኖር እሳት ጭረው ቤንዝን እያርከፈከፉ ያሉት ግለሰቦችና ቡድኖች ለምን ተፈጠሩ?  የሚለው ነው፡፡ በእኔ እምነት የአንድነት በምርጫው የመሳተፍ ውሳኔ በትግል ስልታቸው ላይ የሚፈጥረው ጫና ስለሚያስጨንቃቸው ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ምርጫ መሳተፍ ትክክል አይደለም ብሎ መሟገት ሲያቅታቸው የፈጠሯት ስልት ነች፡፡ አንድነት ምርጫ መሳተፍ ሲወስን በምንም መመዘኛ የመወዳደሪያው ሜዳ ምቹ ነው የሚል ግምገማ ላይ ደርሶ አይደለም፡፡ የፖለተካ ምዕዳሩ ጠበበ ብቻ ሳይሆን ዝግ ነው የሚል ግምገማ ላይ ደርሶዋል፡፡ ልዩነቱ ማስከፈቻ መንገዱ ምን ይሁን የሚለው ነው፡፡ በህዝብ ድምፅ የተዘጋው የፖለተኪ በር ይከፈታል ነው አንድነት ያለው፡፡ በዚህ ውሳኔ የማይስማማ ሊኖር እንደሚችል ይገመታል፡፡ በዚህ ደረጃ ወርዶ ግን በጥርስና በጥፍር ለመናከስና ለመቧጨር መሞከር ግን ያስተዛዝባል፡፡

የግል ሰሜቴን ለመግለፅ እሰከ ዛሬ ድረስ ለሚቀርብልኝ ሙገሳና የማጀገኛ ቃለቶችን ተመርኩዥ ልቤ አላበጠም፡፡ አንድ ቀን ያለአግባብ ከፍ አድርገው ከሰቀሉ ቦታ ላይ አውርዶ የሚከሰክስ ማህበረሰብ አባል መሆኔን አውቃለሁ፡፡ ያለ አግባብ በእራሳቸው ስሜት ሊወስዱኝ የፈለጉት ከፍታ ላይ ስለአልሄድኩኝ አሁን ሊያወርዱኝ አይችሉም፡፡ እደግመዋለሁ ለነፃነቴ የምሰጠውን ዋጋ የማያውቁ ሰዎች ምንም ሊሞክሩ ቢችሉም ነፃነቴን ለኢህአዴግ አሳልፌ አልሰጥም ስል በተቃዋሚ ጎራ ለተሰለፈ አሳልፌ እሰጣለሁ ማለት አይደለም፡፡ ለነፃነቴ የመደብኩት ዋጋ ነብሴን ነው፡፡ ስም፣ ዝና፣ ክብር፣ ገንዘብ፣ ወዘተ እንዳይመስላችሁ!!!!! ነብሴን ነው፡፡

Monday, November 17, 2014

በኢትዮጵያችን በጥርስና በጥፍር የሚደረግ ትግል እንዴት ይቁም?


አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ/አንድነት አሳዛኙን የ2002 ምርጫ ውጤት ተከትሎ ፍራሽ አንጥፎ ኢህአዴግን ምርጫ ዘረፈ ከሚል መደበኛ ለቅሶ መውጣት አለብኝ ብሎ ቁርጠኛ ውሳኔ በመወሰን ውስጣችንን መፈተሸ ተገቢ አቅጣጫ ነው ብሎ በማመን በእኛ በኩልስ የነበረው ችግር ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ አንስቶ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት አድርጎዋል፡፡ ይህ ነገሮች ወደ ውጭ ከማላከክ በዘለለ ሙሉ ቁጥጥር ባለን በራሳቸን ላይ የውስጥ ፍተሻ ማድረግ ጠቃሚና ተገቢ ነው ከሚል እምነት የመነጨ ነበር፡፡ ይህ ማለት ግን የውጭ ጫናዎች በተለይም የኢህአዴግ አፈና የነበራቸውን ተፅዕኖ አሳንሶ ማየት እና የኢህዴግን አፋኝነትን ዝቅ አድርጎ መመልከት አድርገው የሚውስዱ ሰዎች አይጠፉም፡፡ ዋናው ጉዳይ እና ቅድሚያ መሰጠት ያለበት የውሰጥ ጥንካሬና ድክመትን ማወቁ ነው የሚለው ነበር፡፡ በዚህም መነሻ አንድነት በተቃዋሚ ፓርቲዎች ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የአምስት ዓመት ሰትራቴጂና ዕቅድ አዘጋጅቶ ለህዝብ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ሪፖርተርን የመሰሉ ጋዜጦች ተቃዋሚዎችን በጅምላ የሚመሩበት አቅጣጫ የሌላቸው አድርገው መፈረጃቸወን አላቆሙም፡፡ ሌሎችም ቢሆኑ ይህን ተከትለው ከማሰተጋባትና ተቃዋሚዎችን በጅምላ ከመክሰስ ወደኋላ አላሉም፡፡ ለማነኛውም ፍረጃው እንደተጠበቀ ሆኖ አንድነት ያለፉትን አራት ዓመታት ጎዞዉን ባስቀመጠው ሰትራቴጅና አምስት ዓመት ዕቅድ መሰረት አድርጎ ቀጥሏል፡፡ የእቅዱ ማጠቃለያ ዘመንም ከምርጫ ሁለት ሺ ሰባት ምርጫ ጋር የሚገጣጠም ነው፡፡
ይህ የአምስት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ወደፊት እንደሚካሄድ ታሳቢ ተደርጎ የመጨረሻው ዓመት ሊኖረን የሚገባው ዋነኛ ሰራ ምርጫን መሰረት ያደረገ እንደሚሆን ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንፃር ገዢው ፓርቲ በጥርሱም በጥፍሩም ምርጫን ለማሸነፍ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን እግረ መንገዱን ደግሞ የተቃዋሚዎችን በተለይም ደግም የአንድነትን ጥርስ ማውለቅና ጥፍር ማዶልደሙን ተያይዞታል፡፡ የጫወታው ህግ በጥርስም በጥፍርም መጫወት የሚፈቅድ ከሆነ ተወዳደሪዎች በተመጣጣኝ ጥርስም ጥፍርም ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በቦክስ ጫወታ ደረጃ የሚወጣው በኪሎ ነው፡፡  አጫዋቹም/ዳኛውም ጫወታው ከመጀመሩ በፊት ቅድሚያ ሰጥቶ ማረጋገጥ ያለበት ይህን ጉዳይ ሁሉም ተወዳዳሪዎች ማሟላታቸውን ነው፡፡

አንድነት በዚህ ዓይነት የጥርስና የጥፍር ጫወታ ውስጥ ገዢው ፓርቲ ለማድረግ እንደሚፈልገው የተወዳደሪን ጥርስ ማርገፍና ጥፍር ማዶልዶም ተመጣጣኝ ምላሹ የገዢውን ፓርቲ ኢህአዴግ ጥርስ ማርገፍና ጥፍር ማዶልዶም መፍትሔ ይሆናል ብሎ አያምንም፡፡ ለውድድሩ ጥርስም ጥፍርም አስፈላጊ ከሆነ የአንድነት ፓርቲ ጥርስና ጥፍር እንዳይጎዳ መጠበቅ ቅድሚያ ይሰጠው ነው፡፡ ይህ ነው በቁጥጥራችን ስር የሚገኘው እና ዋና ትኩረታችን ሊወስድ የሚገባ እንዲሁም ተገቢ ጊዜ መስጠት አለብን የምንለው፡፡ የገዢውን ፓርቲ ጥርስ ለማርገፍና ጥፍርሩን ለማዶልዶም የምናባክነው ጊዜ የራሳችን በመጠበቅ ብሎም በቁርጠኝነት ባለማስደፈር ቢሆን የበለጠ አዋጭ ነው ብለን እናምናለን፡፡
በገዢው ፓርቲ መንገድ የምንሄድ ከሆነ ግን ወደፊት ለሚደረግ ውድድር በሁለቱም ወገን የሚኖሩ ተወዳደሪዎች በድድ እና በዱልዱም ጥፍር የሚወዳደሩ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የጫወታውን ህግ መለወጥ የሚጠይቅ ይሆናል፡፡ በዛሬው የጥርስና ጥፍር ተምሳሌት ዋነኛ ወካይ ባህሪዎች በሁለቱም ጎራ የተሰለፉ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ነው፡፡ ኢህአዴግ የተቃዋሚዎችን በተለይ የአንድነትን ጥርስና ጥፍር ላይ አደጋ አደረሰ ማለት በየደረጃው ያሉ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች ላይ የሚወስዳቸው ቅጥ ያጡ ህገወጥ እርምጃዎች ማለታቸን ነው፡፡ በአፀፋው አንድነት ይህን ያድርግ ሲባል ደግሞ በኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ላይ ቅጥ ያጡ ሕገ ወጥ እርምጃዎች እንውሰድ ማለት ነው፡፡ የእነዚህ ድምር ውጤት ኢትዮጵያዊያንን በፖለቲካ አቋማቸው ከመጉዳት የሚተናነስ አይደለም፡፡ በዚህ ሁኔታ በተጎዳ ህዝብ ውስጥ ወደፊትም ቢሆን የተሸለ እና የሰለጠነ አማራጭ ይዞ በፖለቲካ መወዳደር ይቻላል የሚል እምነት አይኖርም፡፡ ለዚህም ነው ጉልበታችንን የኢህአዴግ አባላትን ለመጉዳት ወይም ለመበቀል ሳይሆን የአንድነት አባላትና ደጋፊዎችን አቅም በማሳደግ የአይደፈሬነት ሰነልቦና ማዳበር መሆን ይኖርበታል የምንለው፡፡
በአንድነት በኩል የአባላቶቻችንን አቅም እናሳድጋለን ብለን ስንነሳ በዋነኝነት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረግ ውድድር የሚመነጨው አንዱ ሀገር ወዳድ ሌላው ጠላት ነው ከሚል መንፈስ፣ ወይም በግል በደረሰብን በደል በቁጭትና ለበቀል መሆን እንደሌለበት በማሰተማር ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚለያዩት በሚመርጡት የርዕዮተ ዓለም፣ ይህን ለመተግበር በሚያወጡት ፖሊሲና የማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎች መሆኑን በማስረዳት በማስከተለም እነዚህ ልዩነቶች ሀገርን ሊጎዱ እንደሚችሉ ለህዝብ በማሰየት ህዝብ ለሚሰጠው ብይን ተገዢ ለመሆን ዝግጁ ሲኮን ነው፡፡ ይህን ልዩነታችንን ከጠባብ ቡድናዊ/የፓርቲ ወይም ሌላ ስብስብ ፍላጎት ከመነሳት “ሀገር ወዳድ እና የሀገር ጠላት” በሚል እንድንፈራረጅ ምክንያት ከሆነ የጋራ ሀገር እንዲኖረን እየሰራን ነው ማለት አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን ለሁሉም ፓርቲዎች የጋራ መኖሪያ ከመሆን በዘለለ የሁሉም ፓርቲዎች አባላት የሚኖሩባት ብቻ ሳትሆን ለልጅ ልጆች በተሻለ ደረጃ ልናስተላልፋት ትልቅ ራዕይ ሰንቀን የምንቀሳቀስ መሆኑ በሁሉም ዘንድ መታወቅ አለበት፡፡ ኢትዮጵያችን እንድትኖር እኛም በእርሷ እንድንኮራ በሁሉም ጎራ የተሰለፍን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ከፍተኛ ሀገራዊ ኃላፊነት እንዳለብን አውቀን መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡
በኢህአዴግ በኩል የሚገኙ አባላት ብሎም ከፍተኛ አመራሮች ጭምር የተቃዋሚ ፓርቲዎችን “ኪራይ ሰብሳቢ” ከሚል ቅጥ አንባሩ ከጠፋው ፍረጃ በላይ ግልፅ ሆኖ በወጣ መልኩ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፍን ዜጎች በፍፁም ለሀገር ደንታ የሌለን አድርገው መሳል የተለመደና አስልቺ ፕሮፓጋንዳ ከሆነ ቆይቶዋል፡፡ ይህ በእውነቱ የኢህአዴግ በጥርስም በጥፍርም ለመጫወታ እንዲመቸው የሌላውን ጥርስ ማርገፍና ጥፍር ማዶልዶሚያ ስትራቴጂው ነው፡፡ ይህ መንገድ ግን ብዙ ርቀት የማያስኬድ ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም የሚበጅ ነው የሚል እምነት የለንም፡፡
በተቃዋሚ መስመር የተሰለፍን ሰዎች መካከልም ኢህአዴግን መሳደብ እንደ ዋና የትግል ሰልት የተያዘ እስኪመስ ድረስ ጥግ እንደምንሄድ አምኖ መቀበል ስህተታችንን ለማረም ጉልዕ ድርሻ አለው፡፡ አንዳንዴም የሃሳብ ልዩነትን በሰለጠነ መንገድ ከመግለፅ ይልቅ ሰነምግባር በጎደለው ሁኔታ በተለይ የግለሰቦችን ስብዕና የሚነኩ አላስፈላጊ የቃላት ጫወታዎች እንዳሉ እንረዳለን፡፡ “ቅኔው ሲጣፋበት ቀረርቶ ሞላበት” የሚለው አባባል በሁለቱም ጎራ የመከራከሪያ ሃሰብ ድርቀት ምልክት ሊሆን ይቻላል፡፡ ይህንን ከመሰረቱ ለመቅረፍ ከላይ እንደተገለፀው አባላትን በስነምግባር መኮትኮት እና ዋነኛው የፓርቲዎች ልዩነት መሰረት መሆን የሚገባው የፖሊሲና የስትራቴጂ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ሲሆን በከፍተኛ ሀገራዊ መግባባት ሰሜት መንቀሳቀስ ይቻላል የሚል ፅኑ እምነት ይዳብራል፡፡