የአስቸኳይ ጊዜው ሴክፌታሪያት አዋጁ ግቡን መቷል ብለው መግለጫ
መስጠታቸውን ሰምተናል፡፡ ይህ አዋጅ በአጭሩ ዝም ጭጭ አድርጎ ለመግዛት የተቀየሰ ዘዴ ነው ለምንል ሰዎች ዜጎች ዝም ጭጭ እንዲሉ
ተደርጓል ማለት ነው፡፡ አሰገራሚው ነገር መስከረም 1967 “መለኮታዊ ንጉስ” የሚባሉትን አውርዶ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደርግ ለምን
አወጀ ብለው የሚከሱ፣ ሲከፋም በዚሁ ምክንያት ነው ጫካ የገባነው ብለው የሚፎክሮ የዲሞክራሲ አርበኞች በህይወት እያሉ አሁን “ዲሞክራሲያዊ”
የተባለ የአስቸኳይ ጊዚ አዋጅ አውጀውልናል፡፡ ይህ አዋጅ በቴሌቪዥን ሲነበብ አደመጥኩት ክልከላዎቹ በሙሉ ድሮም በህግ የተፈቀዱ
በተግባር ግን የማይቻሉ የነበሩ ናቸው፡፡ ለማረጋገጥ በጋዜጣ የወጣውን በጥሞና ደግሜ ደግሜ አነበብኩት ብዙዎች መመሪያው “ክልክል”
ያላቸው ድሮም ወደፊትም ክልክል ናቸው፡፡ ለምሣሌ ንብረት ማውደም፣ ሰው መግደል፣ ያልተፈቀደ የሠራዊት ዩኒፎርም መልበስ፣ ህገወጥ
ቅስቀሳዎች፣ ወዘተ በሙሉ መቼም ያልተፈቀዱ ወደፊትም የማይፈቀዱ ክልከላዎች ናቸው፡፡ ተፈቅደው ነገር ግን በተግባር ያልነበሩት የአደባባይ
ሠልፍ እና ስብሰባ ዋነኛዎቹ ሲሆኑ፣ እጅግ ብዙዎቹ ክልከላዎች በሀገሪቱ በነበረው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ወቅት ገዢዎችን አንጀት ያሳረሩ
ድርጊቶቸን ዝርዝር ለማወቅ ከመጥቀማቸው ውጭ ፋያዳቸው አይታየኝም፡፡
በአዋጁ ውስጥ አስደናቂ ሊባሉ የሚችሉት ግን ማየት መስማት የሚከለክሉት
የመጀመሪያዎቹ አንቀፅ ላይ የሰፈሩት ክልከላዎች ናቸው፡፡ መለኮታዊ ንጉስ አውርዶ እንዴት ሰልፍ ተከለከልን ያሉ ታጋዮች ለዚህ ነው
ዓይናችን የጠፋው አካላችን የጎደለው ያሉ ሁሉ በተገኙበት ስብሰባ ይህን ማድረግ አስገራሚ ሆኖ በታሪክ ይመዘገባል፡፡
አዋጁን ተከትሎ በሚዲያ የሚተላለፉት ነገሮች ደግሞ የበለጠ አስደማሚ
ናቸው፡፡ አንድ አንድ ነዋሪዎች በመባል የሚታወቁ አስተያየት ሰጪዎች አዋጁ ዘገየ፣ ለልማታችን ያስፈልገናል፣ ወዘተ የሚሉ አሰተያየቶች
ሰጥተዋል፡፡ ማለት የፈለጉት ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለአስተያየት ሰጪዎችም ሆነ አስተያየት ሰብሳቢዎች ግልፅ አይመሰለኝም፡፡ ሕገ መንግሰታዊ ስርዓት ይከበር እያልን፣ በአስቸኳይ አዋጅ መብታችን
ተገድቦ ይኑር ማለት ትርጉሙ አይገባም፡፡ ግራ ገብቷቸው ግራ የሚያጋቡ የዚህ ዓይነት አስተያየት ሰጪዎችና ሰብሳቢዎች ያሉበት ሀገር
ውስጠ ነው የምንገኘው፡፡
ተንታኞች ተብዬዎቹ ደግሞ አዋጁ ምንም አያስገርምም ሁሉም ሀገሮች
የሚያደርጉት ነው በሚል ፈረንሳይን፣ ቱርክን፣ አሜሪካን የመሳሰሉ ሀገሮችን በመጥቀስ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብርቅ ነው እንዴ!! እያሉን
ይገኛሉ፡፡ ይህን አዋጅ ልዩ የሚያደርገው ደግሞ አዋጁ ሲዘጋጅ ልምድ የተወሰደበት ሀገር አለመጠቀሱ ነው፡፡ ይህን እኛም እንዳንጠረጥር
አዋጁን ያዘጋጀው ማንም ይሁን ማን ደረጃውን ያልጠበቀ ዝርክርክ መሆኑን ግን አለመግለፅ ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡ ይህን አዋጅ ሰመለከት
ይህ ካቢኔ ተብዬው ሀገሪቱን የሚገዛው ቡድን ያለውን አቅም ለመረዳት ችያለሁ፡፡ በምንም ሁኔታ በአስቸኳይ ደረጃውን የጠበቀ መግለጫ ማውጣት እንደማይችል፤ ይህን ዓይነት የባለሞያ ስራ
ሊያግዝ የሚችል የባለሞያ ስብስብ እንደሌለው ጭምር ተረድቻለሁ፡፡ አዋጁን መታወጁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለፁ ዕለት ዝርዝሩን እንደደረስን
እናቀርባለን የሚለው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተደጋገመ ማስታወቂያ የሰለቸው ልጄ ስብሰባውን በእንግሊዘኛ ነው እንዴ ያደረጉት? ብሎኛል::
ይህ በሙሉ የሚያሳየው አሰቸኳይ ጊዜ አዋጁ፣ ደንብ፣ መመሪያ፣ ፕሮግራም እየተባለ የሚወጡት በሙሉ ደረጃቸውን ያልጠበቁ መሆናቸው
ነው፡፡ “ነበር” በሚል መፅኃፍ ውስጥ ደርጎች መግለጫ እንዴት ያወጡ እንደነበር የተፃፈውን ስመለከት በዚያ ቀውጢ ወቅት ከዚህም
ከዚያ የተሰባሰቡ ወታደሮች የሰሩትን መስራት የማይችል ሃያ አምሰት ዓመት በስልጣን ላይ የቆየ መንግሰት እንዴት አሳዛኝ እንደሆነ
አንባቢ ሊፈርድ ይችላል፡፡
በነገራችን ላይ ከቅዳሜ ጀምሮ የሚፀና አዋጅ እሁድ ለምን ታወጀ? ሰኞ ምክር ቤቱ
ሰለሚከፈት በዝርዝር አዘጋጅተው ለምን ምክር ቤቱ ሲከፈት አላቀረቡትም? የሚሉና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ማንሳት ይቻላል፡፡ በእኔ
እምነት ከቅዳሜ ጀምሮ የፀና ይሆናል የሚል ህገወጥ አካሄድ የመረጡት ምክር ቤት በሌለበት የታወጀ በማሰመሰል፣ በአርባ ስምንት ሰዓት
ውስጥ ለምክር ቤት አቅርቡ የሚለውን ህገ መንግሰታዊ ድንጋጌ ለመጣስ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ ይህን በማድረግ በሁለተኛው አማራጭ
አሰራ አምስት ቀን ማግኘት የቻሉ ሲሆን ባገኙት አስራ አምስት ቀን የዝግጅት ጊዜ ውስጥም የሚሰሩትን ሰራ ጥራት ለማስጠበቅ አልቻሉም፡፡
አዋጁ ዋና ዓላማው አስፈራርቶ መግዛት ስለሆነ ከሞላ ጎደል ሊሳካለት ይችላል የሚባለው
ለመፍራት በተዘጋጁት ላይ ብቻ ነው፡፡ ነፃነት ወይም ሞት ብሎ ለተነሳ ግን ይህ አዋጅ ምን ይቀንሰበታል? ብዬ ጠይቄ መልሱ ምንም
የሚል ነው የሆነብኝ፡፡ ለማነኛውም ይህ አሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ ህወሃት/ኢህአዴግ በውስጡ እፈጥራለሁ ላለው “ጥልቅ ተሃድሶ” ይሁን “ፈርሶ መሰራት” በአባላቱ መካከል ሊፈጠር ለሚችል ቀውስ መቆጣጠሪያ
ለማድረግ ነው በሚል በተሰፋ ለመሞላት ለሚፈልጉት ተሰፋ ከሰጣቸውም ተሳስቼም ቢሆን ይህ ተሰፋ ዕውን ቢሆን ደስ ይለኛል፡፡
መልካም የአስቸኳይ ጊዜ ይሁንልን!!!!