ግርማ ሠይፉ ማሩ
ኢህአዴግ
በህዝብ ግፊት የመጣበትን ጫና ለመቀነስ በመውሰድ ላይ ከሚገኛቸው እርምጃዎች አንዱ፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ለማድረግ ወስኛለሁ
ማለቱ ነው፡፡ ለውይይት የሚቀርቡ ተቃዋሚዎች ያሉበት ደረጃ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለቴ ነው፡፡ በማንኛውም ሁኔታ ግን ውይይት መጀመሩን
በበጎ መውስድ ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በግሌ ውይይቱን በበጎ መውስድ ብፈልግም ከውይይቱ ምንም ዓይነት ተጫባጭ ውጤት ላይገኝ
ይችላል የሚል ፍርሃቴን ግን መደበቅ አልችልም፡፡ ምክንያቱም በኢህአዴግም በኩል ሆነ በተቃዋሚ በኩል ምንም ዓይነት የባህሪ ለውጥ
ማሳየታቸውን የሚያመላክት ነገር አለመኖሩ ነው፡፡ በዋነኝነት የሰዎቹ አለመለወጥ ብቻ ሳይሆን የተወሰነ የአካሄድ፣ ቢያንስ የንግግር
ለውጥ ማድረግ ያልቻሉ መሆናቸውን ስታዘብ ጥርጣሬዬን ከፍ ያደርገዋል፡፡
ይህ ጨለምተኛ
የሆነው ለውጥ አይታየኝም የሚለውን ነገር ትቼ፤ አሁን ከሚደረገው ውይይት ለዚህች ሀገር ለውጥ እንዲመጣ በዋነኝነት ኳሱ የሚገኘው
በኢህአዴግ እጅና ፈቃድ ነው፡፡ ይህም ማለት አሁን በድርድር ላይ ያሉትን ፓርቲዎች በሙሉ ችላ ብሎ ከዛሬ ጀምሮ ማነኛውም የፖለቲካ
ፓርቲ በህጋዊ መንገድ እስከተንቀሳቀሰ ድረስ ምንም ዓይነት ቀጥተኛም ይሁን ተዘዋዋሪ ጫና አይደርስበትም፤ የሚል መግለጫ ማውጣት
እና እንዲህ ዓይነት ችግር ሲገጥመው በዚህ ቦታ በሚቋቋም ተቋም ሪፖርት በማድረግ ድርጊት ፈፃሚውን በማጋለጥ እርምጃ
ማስወሰድ ይችላል፤ ቢል ብዙ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፡፡ ኢህአዴግ፤ ይህን ማድረግ እየቻለ ፓርቲዎቹን ሰብስቦ ፈርተናችሁ ሳይሆን፤ እኛ
ሰለፈለግን ይህን ውይይት እንዲዘጋጅ አደርገናል፤ በሚል ድባብ የሚደረግ ውይይት በተደራዳሪዎች አቅም ለውጥ ያመጣል ብዬ አላምንም፡፡
እውነቱን ለመናገር ይህን ድርድር ኢህአዴግ የፈለገው፤ በፖለቲካ ስርዓቱ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ፈልጎ፣ ነገር ግን ተቃዋሚዎች ምን
እንደሚፈልጉ ለማወቅ እና ፍላጎታቸውን ለማካተት አስቦ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ኢህአዴግ ውይይቱን የፈለገው ለህዝብ ግንኙነት
እና እንዲሁም ጫና የፈጠረውን ህዝብ በማዘናጋት ጊዜ ለመግዛት ነው፡፡
ተቃዋሚዎች አብዛኞቹ ምንም
ለህዝብ የሚጠቅም የፖለቲካ ፍላጎት የላቸውም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ምንዳ ከኢህአዴግ እንዴት እንደሚሰፈርላቸው
መጠበቅ ብቻ ነው፡፡ በዚህ መስመር ጉድለት ካለ ሊነጫነጩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ምንም ለውጥ አያመጡም፡፡ ጥቂቶቹ ተቃዋሚዎች፤ በተለያየ የውስጥና የውጭ ጫና ተጠልፈው፤
ከውይይቱ ምን ማግኘት እንዳለባቸው ሳይሆን በውይይቱ ወቅት የህዝብ ግንኙነት ስራ በመስራት የውስጥና የውጭ ጫናውን ለማለዘብ እና
ለህዝብ ቋሚ ተጠሪ መሆናቸውን ለማሳየት የሚውተረተሩ ናቸው፡፡ ተቃዋሚዎች ለኢህአዴግ ቀላል እና ለመፈፀም የሚቻል፣ ጥያቄ በማቅረብ
ለማሳጣት አልተዘጋጁም፡፡ የሚያቀርቡት ጥያቄ ለህዝቡ በሚገባው ቋንቋ፤ ኢህአዴግ ይህን ማድረግ ከቻለ ሌላውን ስራ ለእኛ ተዉት በሚል
ደረጃ አልተዘጋጁም፡፡
በዚህ
ውይይት ወቅት ለኢህአዴግ በግሌ እንዲቀርብለት እና እንዲፈፅመው የምፈልገው ቀላል ጥያቄ አንድ ብቻ ነው፡፡ ይህም ኢህአዴግ በመንግሰትነት
በያዘው ሀይል ተጠቅሞ የፖለቲካ ምዕዳሩን አጥብቦታል እና ይህን ይክፈትልን የሚል ነው፡፡ ይህ ለጥቂት ፖለቲከኞች የሚገባ ቢሆንም
ለአብዛኛው ህዝብ ጥቅል ሃሣብ ነው፡፡ ይህ ለህዝቡ እንዲገባው ማድረግ በሚችል መልኩ በዝርዝር መቀመጥ ይኖርበታል፡፡ ለምሣሌ፤
1. የፖለቲካ ፓርቲዎች ለቢሮ የሚሆናቸውን
ደረጃውን የጠበቀ ቤት በኪራይ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ቢያንስ አንድ የተሟላ ፅ/ቤት የሌለው ፓርቲ እንደ ፓርቲ ሊቆም የሚችልበት
ሁኔታ የለም፡፡
2. የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሚያደርጉት
የአዳራሽ ስብሰባ ማነኛውም አዳራሽ በኪራይ የሚያቀርብ ተቋም ያለምንም የዋጋ ጭማሪ አገልግሎቱን እንዲሰጥ፤
3. የህትመት አገልግሎት የሚሰጡ
ድርጅቶች ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን ማንኛውንም የህትመት አገልግሎት መስጠት፣
4. ማንኛውም የፓርቲ አባላት የፓርቲውን
ሰነዶች (የድምፅ፣ የምስል፣ የህትመት፣ ወዘተ) በሚያሰራጩበት ወቅት ምንም ዓይነት ጫና በፖሊስም ሆነ በሌላ አካል እንዳይደርስበት
ማድረግ፤
እነዚህ ተግባራት አሁንም የሚቻሉ
በሕገ-መንሥት እውቅና ያገኙ ናቸው፤ የሚል የድርቅና ሙግት እንደሚቀርብ ይታወቃል፡፡ ትልቁ ችግር እነዚህን መብቶች፤ በውስጥ አስራር
በመንግሰት መዋቅር እንዲታፈኑ መደረጋቸው ነው፡፡ ስለዚህ፤ ከላይ በተዘረዘሩት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ህገወጥ ተግባር ተፈፅሞ ቢገኝ
አግልግሎት ሰጪዎች ወይም ዝርዝር የፓርቲ ተግባር የሚፈፅሙ አባላት ምንም ዓይነት ተጠያቂነት የሌለባቸው ሲሆን፤ ሙሉ ሃላፊነቱን የሚወስደው የፓርቲ አመራር መሆኑን በህግ መደንገግ ይኖርበታል፡፡
በተጨማሪ አገልግሎት ሰጪዎች በማንኛውም ሁኔታ፤ የመንግሰት አካል ነኝ ብሎ በግንባር ቀርቦ፣ በቃል፣ በስልክ ወይም በሌላ ሁኔታ
አገልግሎት አቋርጡ የሚል ትዕዛዝ ቢሰጥ፤ ይህን ትዕዛዝ መቀበል እንደሌለባቸው በህግ መደንገግ ይኖርበታል፡፡ ፓርቲዎች በተከራዩት
አዳራሽ፣ በሚያሰራጩት ህትመት፣ ወይም ሌላ እንቅስቃሴ ጥፋት መፈፀማቻው በፍርድ ቤት ተረጋግጦ በህግ ሲታገዱ ብቻ አገልግሎት አለመስጠት
ይቻላል፡፡
ኢህአዴግ አሁን በመንግሰትነት
የያዘውን ስልጣን መከታ አድርጎ፤ በህግ ማስከበር ስም በቁጥጥር ስር ያደረጋቸውን ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ በመፍታት ለመልካም ግንኙነት
ሲባል ያለምንም ተንበርከኩ ጥያቄ መፍታት ይጠበቅበታል፡፡ በሀገር ውስጥ በሚፈጠረው አዎንታዊ እርምጃ መሠረት ላይ፤ በማንኛውም መንገድ
መንግሰትን መጣል አለብን ብለው ለተነሱት ሀይሎች ጥሪ ማቅረብ እና በሀገራቸው በሰላማዊ መንገድ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉበት ምዕዳር መፈጠሩን
ማሳየትና ማስተማመኛ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን ተግባራት ለመፈፀም አሁንም ኢህአዴግ የሚመራው መንግሰት ቁርጠኛ ከሆነ አንድ
ገለልተኛ ኮሚሽን ማቋቋም ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በተቋም ላይ ተቋም ማቋቋም አያስፈልግም፤ የሚል ጎንጭ አልፋ ክርክር
ከተነሳ አሁንም ኢህአዴግ ቁርጠኛ ያለመሆኑን ከማሳየት ውጭ ሌላ ነገር ሊሆን አይችልም፡፡
የሚቋቋመው ኮሚሽን ዋናው ተግባሩ
አሁን ያሉት ተቋማት በመፈተሸ በሚጠበቅባቸው ደረጃ ከወገንተኝነት ተላቀው እንዲሰሩ ማስቻል ነው፡፡ ይህ ኮሚሽን አፋኝ የምንላቸውንም
ሕጎች መፈተሸ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ፤ ኮሚሽኑ ለዴሞክራሲው ስርዓት ግንባታ አዎንታዊ ሚና ያላቸው ሚዲያና ሲቪል
ማህበራት ህዝቡን በማንቃትና በነፃነት እንዲንቀሳቀስ የሚሰሩበት ሁኔታ እንዲፈጠር መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ሁሉ ግን ሊሆን የሚችለው
በኢህአዴግ በጎ ፈቃድ እና ለለውጥ ባለው ፍላጎት ነው፡፡ ኢህአዴግ እንዲህ እንዲያደርግ ሊያስገድድ የሚችል ተቃዋሚ ፓርቲ አደረጃጀት
የለም፡፡ ኢህአዴግ ይህን በፈቃዱ ካላደረገ፤ ይዋል ይደር እንጂ የተዳፈነው የህዝብ ቅሬታ አሁን በተያዘው መስመር “ጥልቅ ተሃድሶ”
ሊፈታ አይቻለም፡፡ ይህ የዜጎች ቅሬታ በተለይ የ30 ሚሊዮን ወጣት ብሶት፤ መንግሰት መደብኩት ባለው ብር 10 ቢሊዮን የሚለዝብ
እንዳልሆነ እርግጠኛ ሆኜ መናገር እችላለሁ፡፡
ኢህአዴግ በዚህች ሀገር ውስጥ
አዎንታዊ ታሪክ እንዲኖረው ከፈለገ፣ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በሚል የተሰዉት ክብር እንዲያገኙ ከፈለገ፤ እስከዛሬ የተከናወኑ
በጎ ተግባራት ለቀጣይ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባት እርሾ እንዲሆን ከፈለገ፣ ወዘተ በፈቃደኝነት የቀረበለትን ቀላል የፖለቲካ ምዕዳር
ማሻሻያዎቹን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ቀላሉን ከመለስ ከባዱን አብረን ለመስራት እድል ይገኛል፡፡ ይቻላልም፡፡
መልካም የአስቸኳ ጊዜ!!!