“በኢትዮጵያ
ወሰጥ ላለው ችግር ተጠያቂው ወያኔ የሚመረው መንግሰት ነው፡፡” አቶ ኢሣያስ አፈወርቄ በቅርቡ ከአሰመራ ከሰጡት መግለጫ ዋንኘው
ነጥብ ነው፡፡ አቶ ኢሣያስ ይህን ማለታቸው ስንሰማ አዎ ልክ ናቸው፤ ግን ምን አገባቸው ብለን የምንተወው ጉዳይ አልመሰለኝም፡፡
ሰሞኑን ኢትዮጵያና ኤርትራ የግብፁ ፕሬዝደናት ጋር ቀርበው (ይህ ነው የሚሻለው ቃል ብዬ ነው፡፡ በአኩል በአገራዊ ኩራት ተገናኝተዋል
የሚል ነገር በውስጤ ሰለሌለ፡፡) አለን በሚሉት ጉዳይ ላይ ተነጋግረዋል፡፡ ለአቶ ኢሣያሳ አፈወቄ አልሲሲ የሚነግሯቸው ቁም ነገር
ቢኖር ኢትዮጵያ የምትባል አገር ቀና እንዳትል ለሚፈለገው ማንኛውም ድጋፍ አንደማይለየቻው ነው፡፡ ለአቶ ሀይለማሪያም ደሣለኝ ደግሞ
የሚነግሩት የዚህ የግድብ ጉዳይ ችግር ቢኖርም፤ የግብፅን ሕዝብ ችግር ላይ የሚጥል መሆኑ እውነት ቢሆንም፣ በኤኮኖሚና ማህበራዊ
መስክ ያለንን ትስሰር አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ በኢንቨሰትመንትም እንሳተፋለን፡፡ አፍሪካም በዓለም መድረክ ላይ ያላትን ተሰሚነት
ከፍ ለማድረግ ሁለቱ መንግሰታት አብረን እንሰረራለን፤ ወዘተ የሚል
ነው እንጂ “ከኢሣያስ ጋር አያሴርኩላችሁ ነው አይሉንም፡”፡ እስኪ የግብፅን ጉዳይ በግብፅ ቦታ ሆነን እንፈትሽ፡፡
ግብፅ
የምትባል አገር ለመኖር አባይ የሚባል ወንዝ የግድ ይላታል፡፡ ሌሎች አመራጮች ቢኖርም ውድ ናቸው፡፡ ግብፅ የአባይ ጉዳይ የአገር
ደህንነት እና ህልውና ጉዳይ እንጂ የአንድ ሚኒሰትር መሰሪያ ቤት የውሃ ወይም የተፋሰስ ልማት ጉዳይ አድርጋ የምታየው ነገር አይደለም፡፡በግብጽ
ጥሩ የሚባል መንግሰት ይህን ጉዳይ በበላይነት የሚመራ ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም ቢሆን አስተማማኝ መሰረት የሚጥል መሆን አለበት፡፡
ስለዚሀም ለማንኛውም ተረኛ የግብፅ መንግስት “ታሪካዊ ጥቅማቸውን” ማስጠበቅ ትንሹ ስራው ነው፡፡ ለግብፅ ታሪካዊ የሚባለው መብትና
ጥቅም አሁን ከሚያገኙት የውሃ መጠን ጠብታም ቢሆን የሚቀንስ መሆን የለበትም፡፡ ይህ ደግሞ ሊሆን የሚችለው የላይኛው ተፋሰሰ አገሮች
(ኢትዮጵያን ጨምሮ) አንድ ጠብታ ውሃ እንዳይንኩ ቢቻል በውድ፣ ካልሆነ በእጅ አዙር በዘዴ በሚደረግ ጫና ሲሆን፤ ዘለግ ሲልም በግድ
በማስፈራራት ማድረግ ነው፡፡ ይህ ለአንድ ግብፃዊ ተገቢና ትከክል ብቻ ሳይሆን ለመስዋዕትነት የሚዘጋጅለት የአገር ሉዓላዊነት ጉዳይ
ነው፡፡ እንደ አገር የመቀጠል ወይም ያለመቀጠል ጉዳይ ነው፡፡ በታሪክም ይህን የማራል፤ በትውፊትም እንዲሁ ተበሎ ይነገረዋል፡፡
እንዲህ ትውልድ መቅረፅ ማለት፡፡
ግብፅ
በውዴታ ከአገራቱ ጋር የምትወስደው እርምጃ ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ዓይናቸውን ከዓባይ ላይ አንስተው በሌሎች
አመራጭ ወንዞች እንዲጠቀሙ መምከርና ማግባባት፣ አገሮች ይህን ሊገዳደር የሚችል እና በእውቀት ላይ የተመሰረተ የውሃ አጠቃቀም እንዳይኖራቸው
ማፋዘዝ በግብፅ በኩል ዋና ዋና ተግባራቶች ናቸው፡፡ ለዚህ ጉዳይ በዓለም የልማት ተቋሞች ጭምር የውሃ ኤክስፐርት የሚባለው ሁሉ
ከግብፅ ጎን እንዲሰለፍ በማድረግ አገራቱን ማፋዘዝ ትልቁ ስራ ነው፡፡ ይህ ለረጅም ጊዜ በስራ ላይ የዋለ ስትራቴጂ ነው፡፡ለምሣሌ
በዓለም ባንክ ድጋፍ የሚሰሩ ማንኛውም ዓይነት ስራዎች ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ መሰራት አይቻልም፡፡
ሌላኛወው
በእጅ አዙር/በዘዴ የሚደረገው የላይኛው ተፋሰስ አገሮች እርስ በእርስ እንዳይስማሙ ማድረግ፣ በተጨማሪ አገራቱ በውስጣቸው ባለው
የውስጥ ጉዳይ ሌላኛው ጣልቃ እንዲገባ ማድረግ (ኢትዮጵያና ሱዳን በዚህ ቅርቃር ውስጥ ለረጅም ጊዜ ቆይተዋል)፣ የአገራት የውስጥ
ችግር መፍትሔ እንዳያገኝ በተለያየ መስመር ስምምነት እንዳይደርሱ በማድረግ ጥቅመኞችን መግዛት ነው (ሻቢያና ወያኔ የዚህ ስትራቴጂ
ዋነኛ ተጠቃሚዎች ነበሩ)፡፡
የመጨረሻው
የግድ የሚባለው በመሣሪያም ቢሆን አስፈራርቶ አባይን ጥቅም ላይ እንዳያውሉ ማድረግ ነው፡፡ የመጨረሻው አማራጭ የመጨረሻ ብቻ ሳይሆን
ከሱዳን ጋር ካልሆነ ሊተገበር የማይችል አማራጭ ነው (ሱዳን ይህን ሁሉ አልፋ ከግብፅ ይሁንታ ውጭ “መረዋን” የሚባል ትልቅ ግድብ
ገንብታ በስራ ላይ አውላለች)፡፡ ይህ የመጨረሻው ስትራቴጂ ለወሬ እና ፕሮፓጋንዳ የሚጠቀሙበት ብቻ ነው፡፡ ግድብ በአውሮፕላን እናፈርሳለን፣
አገሪቱን እንዲህና እንዲያ እናዳርጋለን በሚል ዛቻ ማስፈራራት የተሞላ ስትራቴጂ ነው፡፡ የስነ ልቦና ጦርነት ልንለው እንችላለን፡፡
ግብፅ ትወረናለች፣ የዘህ ዓይነት አውሮፕላን አላት የሚለው በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው፡፡
ለግብፃዊ
ዜጋ ሁሉም አማራጮች በጠረጴዛ ላይ መኖራቸውን አውቆ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲኖሩ፣ መንግሰታቸውም በስራ ላይ እንዳለ ማሳያ ሲሆን፣
ዜጎችም የበኩላቸውን የሚወጡበት ነው፡፡ ሌሎች የላይኛው ተፋሰስ አገር ዜጎች ደግሞ በተለያየ መንገድ መረጃው ደርሷቸው በፍርሃት
እንዲርዱ ማድረግ ነው፡፡ የግብፅ ሚዲያዎች እና ሲቪል ማህበራት የሚባሉት ደግሞ ይህን ተግተው ይስራሉ፡፡ የዜግነት ግዴታቸውን ይወጣሉ፡፡
ይህን ለድርድር የሚያቀርብን የፖለቲካ አመራር ቁም ስቅሉን ያሳዩታል፡፡ ወደ መስመር ሳይውድ፤ በግድ እንዲገባ ይደረጋል፡፡ ለአገር
ጥቅም ሲባል፡፡
በግብፅ
ቦታ ሆኖ ለሚመለከት ይህ ለአገር ህልውና ሲባል የሚደረግ መሆኑን ያለመረዳት ግብፅን እና የፖለቲካ አመራሩን እንዲህ አደረጉ ብሎ
መክስስ ጅል ከመሆን አያልፍም፡፡ በአንድ ወቅት ለኦነግ አመራሮች በግብፅ የተደረገላቸውን ዝግጅት የኢትዮጵያ መንግሰት እንደ ትልቅ
ነገር በሚዲያ ሲያቀርብ ቆይቶ ጠቅላይ ሚኒሰትሩም የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩም ይህን ያደረጉትን የግብፅ ተቋማት የግብፅ መንግስት እርምጃ
እንዲወስድ መጠየቃቸውን እና ምላሽ እየጠበቁ እንደሆነ በሚዲያ ተከታተልን፡፡ የግብፅ መንግስት ዜጎች በግል ይሁን ተደራጅተው ለአገራቸው
ጥቅም የሚቆሙ ዜጎችን ሊነካ አይችልም፡፡ ይልቁንም በውስጥ መስመር በርቱ ተበራቱ ብሎ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ይህ በእኛ አገር መንግስት
ቢሆን ይህን ያደረጉ ድርጅቶች ይዘጋሉ፣ ይህን በዜግነት ስሜት ያደረጉ ደግሞ ወህኒ ይወርዳሉ፡፡
በኤርትራዊ
ቦታ ሆኖ ለሚመለከት ማለት አይቻለም፡፡ በኢሣያስ ይልቁንም በሻቢያ መሪዎች ቦታ ሆኖ ማየት ቢባል ይሻላል፡፡ የኤርትራ ህዝብ መንገድ
ቢያገኝ አብዛኛው ኢትዮጵያ ገብቶ ቢያድር ይወዳል፡፡ ይህ እምነት የእኔ ብቻ አይመሰለኝም፡፡ ቢያንስ ወደ ሌላ አገር በሰደት ለመሸጋገር
ሲሉ ብዙ ኤርትራዊ ወንድም እህቶቻችን አብረውን በአገራችን ይገኛሉ፡፡ የኤርትራ መንግሰት/ሻቢያ ለምን ይህን ያደርጋል/? ከግብፅ
ጋር ተባብሮ ከላይ ያስቀመጥናቸውን የግብፅን ጥቅም ለማሰጠበቅ ለምን ይስራል? ተብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጵያ
ጋር አሁን የገባበትን ቅርቃር ለመውጣት መንገድ ያጣ መንግሰት ነው፡፡ ጦርነት ብሎ ቢነሳ ብቻውን አይችልም፡፡ የሰላም መንገድ የሚባል
በዚህም በዚያም በኩል የሚታወቅ አማራጭ አይደለም፡፡ ሁለቱም ቡድኖች በደፍጣጭነት ተወልደው ያደጉ ናቸው፡፡ ተሸንፎ ማሸነፍ የሚባል
ነገር በመዝገባቸው የለም፡፡ የእስከ አሁኑን ትተው ከአሁን በኋላ ህዝብ በሰላም ሊኖርበት የሚችልበትን እድል ለመፍጠር ታሪክ የሰጣቸውን
አጋጣሚ ከመጠቀም ይልቅ በድሮ መንገድ መጓዝ የተሻለ አድርገው ወስደውታል፡፡ ሰለዚህ ኢትዮጵያ አሁን በውስጥ ቸግር የተወጠረችበት
ወቅት በመሆኑ፣ በዚህ ጊዜ ዘወትር ከጎናቸው የምትገኘው ግብፅ ደግሞ ይህን እድል ለመጠቀም ወደኋላ እንደማትል የረጅም ጊዜ ተመክሮ
ያላቸው አቶ ኢሣያስ አፈወርቄ ወደ ግብፅ ጎራ ብለው ምን ልታዘዘ? ቢሉ ብርቅ አይደለም፡፡ አሁንም በኤርትራ መንግሰት ጫማ ውስጥ
ሆኖ ማየት ያሰፈልጋል፡፡ በተለይ በኢሣያስ አፈወርቄ ቦታ ሆኖ ማየት አሁን የሚሰጡትን መግለጫ እንዲሰጡ እንደገፋፋቸው ለመረዳት
አያስቸግርም፡፡ ሰለዚህ የኢሣያስ አፈወርቄ እርምጃ እንደ ግብፁ ለዜጎች ህልውና የሚደረግ ሳይሆን ይልቁንም በዜጎች ጥቅም ላይ ሁሉ
ሆነው በእልዕ፣ የቸገረው እርጉዝ ያገባል የሚባለው ዓይነት ነገር ሆኖባቸው ነው፡፡
ኢትዮጵያዊ
ሆነን ሰንመለከተው ግብፅና ኤርትር መርዕ አልባ ግንኙነት ማድረጋቸው በእኛ ቁጥጥር ውስጥ ያለ ነገር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊያን
አብረን ለመቆም፣ ያለብንን የሃሣብ ልዮነት ለህዝባቸን በመንገር በህዝብ የምንዳኝነበት ምዕድር መፍጠር አልቻልንም፡፡ ሰለዚህ አሁን
ኢትዮጵያ ላለችበት ችግር ዋንኛ ተጠያቂዎች ሆነናል ማለት ነው፡፡ ይህን ምዕዳር አውቆ እንዳይፈጠር ያድረገው ደግሞ ህወሓት/ኢህአዴግ
ነው፡፡ ሰለዚህ የውስጥ ችግራችን ገበናችን በግብፅና ኤርትራ መጫወቻ እንዲሆን ተደርጎ ቀርቧል፡፡ አቶ ኢሣያስ አፈወርቄ ኢትዮጵያ
አሁን ላለባት ችግር ተጠያቂው ገዢው ፓርቲ መሆኑን ሲነግረሩን እውነት ነው ማለት ይኖርብናለ፡፡ አስከትለንም በግብፅ ድጋፍ በኤርትራ
በኩል የሚመጣ መድሃኒት ዘላቂ መፍትሔ እንደማይሆን እናውቃለን፡፡ ግብፆች መንግሰታቸውም ሆነ ሕዝቡ በጋራ ቆሞ ጥቅሙን ያስጠበብቃል
እንጂ ለኢትዮጵያዊያን የሚቆሙበት ምክንያት የላቸውም፡፡ ኢትዮጵያ የግብፅ ዓይነት መንግሰት እንደሌላት መወራረደድ ይቻላል፡፡ ለምሣሌ
ኢትዮጵያዊያን የሲቪል ማህበራት በግብፅ ጥቅም በተቃራኒ፣ ለአገራቸው ሲሉ ቢቆሙ፣ የኢትዮጵያ መንግሰት ተብዬው ይህ የመንግሰት አቋም
አይደለም ብሎ በግል ይህን ማራመድ መብታቸው ነው ብሎ ለዜጎች ጥቅም ሊቆም ይችላል? አይቆምም!! ለምሣሌ የግራዢያኒን ሀውልት ግንባታ
የተቃወሙና ሰልፍ የወጡ፣ የሳውዲን መንግሰት በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚውስደውን እርምጃ የተቃወሙ ወጣቶች ላይ መንግሰት ምን እርምጃ
እንደወሰደ እናውቃለን፡፡ ግብፃዊያን ከመንግስታቸው አቋም በተቃራኒ የፈለጉትን አቋም ቢያራምዱ ማንም ምንም አይላቸውም፡፡
የግብፅ
ሚዲያዎች በተለያየ መንገድ የድርድር ሰነዶችን እንዲያገኘ እና ወሬ እንዲያናፍሱ የሚያግዛቸው መንግሰታቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን
ከግብፅ ሚዲያ ተቀብለው ከመጮኽ የዘለለ ነገር ማድረግ አንችልም፡፡ አገራዊ ጥቅም የሚያስጠብቀው መንግሰት ብቻ ተደርጎ የተወሰደበት
አገር ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አትቀርም፡፡ በአንፃራዊነት በህዳሴ ግደብ ግንባታና ጥናት አሁን ባሉ ድርድሮቸ ምርጥ ኢትዮጵያዊያን
እንደሚሳተፉ እና የተሻላ ውጤት አንደተመዘገበ ይታወቃል፡፡ ከኤርትራ ጋር በነበረው የድንበር ውዝግብ በዝረራ ተሸንፈን የወጣነው
በውጭ ሰዎች እና የኢትዮጵያን ታሪክ አጣመው ባጠኑ ፖለቲከኞች ስለተመራ ነው፡፡ በወቅቱ አንደኛ የነበሩ የህወሓት ሰዎች፣ የኢትዮጵያ
ታሪክ እና የባህር በር ጉዳይ የገባቸው ከስልጣን መንበራቸው ከተፈናቀሉ በኋላ መሆኑ ነግረውናል፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ
አሁን ላለንበት ቸግር ተጠያቂ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን ካለንበት አዙሪትም ልንወጣ የምንችልበት ቁልፍ በእጁ ይገኛል፡፡ ቁልፉን
በአግባበ ለሚመለከተን ዜጎች ካልሰጠን አቶ ኢሣያስ እንዳሉት ቁልፉን በግብፅ ድጋፍ ከየትም መስመር በሚመጣ የጊዜው ጉልበተኛ መቀማቱ
አይቀርም፡፡ ይህን መንገድ አሁን በሰልጣን ላይ ያሉት ሰዎች እንዲሁም ደጋፊዎቻቸው አገርን ለጠላት አሳልፎ መስጠት ነው በሚል ሊያጣጥሉት
ይሞክራል፡፡ የዚህን መንገድ አዋጭነት የሚያውቀቱ በዋነኝነት ህወሓትና ሻቢያ መሆናቸው ነው፡፡ በአንድ ወቅት ከግብፅ ባገኙት ሁሉን
አቀፍ ድጋፍ ዛሬ የመንግሰትነት ወግ አግኝተዋል፡፡ ጨቋኝ ደርግን ለመጣል በተደረገ ትግል የሚል መከራከሪያ ዘወትር ይቀርባል፣ በዛሬይቱ
ኢትዮጵያ ከደርግ በላይ የሚጠላው ህወሓት/ኢህአዴግ መሆኑን ማሰታወስ ያስፈልግ ይሆናል፡፡ የቁቤ ትውልድ ደርግን አያውቅም፣ አሁን
ቄሮና ፋኖ ተሰማራ እያለ ያሉት ወጣቶች ደርግን አያውቁም፡፡ ነፃነቱን የቀሙት ይህን ነፃነት ለማሰመለስ ከማንም ጋር እሻረካለሁ
እያለ ያለው ትውልድ ደርግን አያውቀውም፡፡ ሰለዚህ ይህ መንገድ እንዳይሰራ ዋንናኛውን የዜጎች መሳተፊያ የሆነውን የሀገር ውስጥ
መስመሩን ክፍት አድርጉልን፡፡
ሰለዚህ
ህወሓት/ኢህአዴግ የህዝብን ጥያቄዎች በአገር ውስጥ የሚሰተናገድበትን ምዕዳር መፍጠር ትቶ አልሲሲ ቤተ መንግስት ደጅ መጥናት ግብፅን
የሚያሰቀይራት አንደም ነገር የለም፡፡ ይልቁንም ጊዜ መግዛትና፣ ማዘናጋት ብቻ ነው፡፡ ተጎጂዎችም እኛው ነን፡፡ በዋነኝነት የውስጥ
ችግራችንን በራሳችን በመፍታተት ጠንካራ ኢትዮጵያን በመገንባት በኤርትራ ከሚኖሩ ወንድምና አህቶች ጋር ቡና ብንጣጣ ይሻለናል፡፡
ለማይቀረው የጋራ ጥቅማችን ጠላትነት ማጠናከር ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ ግብፆች ከጠብታ ውሃ አይነካም ወደ ፍትሓዊ አጠቃቀም የሚመጡት
እኛ ይህን የማድረግ አቅም ያለን መሆኑን አሰረግጠን ስናሳያቸው ነው፡፡
ቸር
ይግጠመን!!!
ግርማ
ሠይፉ ማሩ