Friday, April 13, 2018

ለክቡር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ አገራችን መድበለ ፓርቲ ስርዓት ለመገንባት ከገዢው ፓርቲ/መንግስት ምን እንደሚጠበቅ ለመጠቆም የቀረበ የመነሻ ሃሣብ ከግርማ ሠይፉ ማሩ girmaseifu@gmail.com girmaseifu.blogspot.com



ከብር ጠቅላይ ሚኒሰትር ይህን ከባድ ሃላፊነተት በተረከቡ ዕለት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባደረጉት  አነቃቂ ንግግር “የሃሣብ ልዩነት መርገምት አይደለም፣ ይልቁንም በረከት ነው፡፡” ባሉት መነሻ፣ ከኢህአዴግ ጋር የሃሣብ ልዩነት ያለን ዜጎች በተናጥል ይሁን በተደራጀ መልክ ሃሣባችንን ለሕዝብ ማቅረብ እንደሚገባን መረዳቶን ተገንዝቢያለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር ክቡር ጠቅላይ ሚንሰትር መወሰድ አለባቸው፤ ይገባልም ብዬ የማስባቸውን ነጥቦች በግሌ በዚህች አጭር ፅሁፍ የማቀርብ ሲሆን፤ ከዚያ ቀድሜ ግን አንድ ጠቃሚ እውነት ማሰጨበጥ ይኖርብኛል፤
በኢትዮጵያ አገራችን አብዛኞቹ ተቃዋሚዎች በሚያሳዝን ሁኔታ ምንም ለህዝብ የሚጠቅም የፖለቲካ ፍላጎት/ሃሣብ የላቸውም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ምንዳ ከኢህአዴግ እንዴት እንደሚሰፈርላቸው መጠበቅ ዋንኛ ሥራቸው ነው፡፡ በዚህ መስመር ጉድለት ካለ ሊነጫነጩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ምንም ለውጥ አያመጡም፡፡ ተገቢ የሆነ ጠበቅ ያለ የስርዓት ማስከበር እርማጃ ቢጀመር እና በህይወት እንዲቆዩ እንደ ኦክስጅን የሚደረግላቸው ምንዳ ቢቋረጥ ለመኖር እንደማይችሉ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ጥቂቶቹ ተቃዋሚዎች፤ በተለያየ የውስጥና የውጭ ጫና ተጠልፈው፤ ከገዢው ፓርቲ ጋር በሚደረግ ምንም ዓይነት ግንኙነት፤ ምን ማግኘት እንዳለባቸው ሳይሆን፤ በግንኙነት ወቅት የህዝብ ግንኙነት ስራ በመስራት የውስጥና የውጭ ጫናውን ለማለዘብ እና ለህዝብ ቋሚ ተጠሪ መሆናቸውን ለማሳየት የሚውተረተሩ ናቸው፡፡ ሰለሆነም ተቃዋሚዎች ለመንግስት ቀላል እና ለመፈፀም የሚቻል፣ ፍላጎታቸውን ያማከለ ጥያቄ በማቅረብ ሊፈትኑት አልተዘጋጁም፡፡ የሚያቀርቡት ጥያቄ ለህዝቡ በሚገባው ቋንቋ፤ መንግሰት ይህን ማድረግ ከቻለ ሌላውን ስራ ለእኛ ተዉት በሚል ደረጃ ለማቅረብ አልተዘጋጁም፡፡ በዚህ አውድ ውስጥ ሆኜ ነው የግል ሃሣብ የምሰነዝረው፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እርሶ የሚመሩት መንግሰትና/ኢህአዴግ በግሌ ተግባራዊ እንዲያደርጉት የምፈልገው ቀላል ጥያቄ አንድ ብቻ ነው፡፡ ይህም ኢህአዴግ በመንግሰትነት በያዘው ሀይል ተጠቅሞ፤ የፖለቲካ ምህዳሩን አጥብቦታል እና ይህን ይክፈትልን የሚል ነው፡፡ ይህን ሲያደርግ አብዛኞቹ ከጫወታ ይወጣሉ፤ ጥቂቶቹ አማራጫቸውን ለህዝብ በተደራጀ መልክ የሚያቀርቡበት እድል ያገኛሉ፡፡ ይህ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብና መስፋት ጉዳይ ለጥቂት ፖለቲከኞች የሚገባ ቢሆንም ለአብዛኛው ህዝብ ጥቅል ሃሣብ ነው፡፡ ይህ ለህዝቡ እንዲገባው ማድረግ በሚችል መልኩ በዝርዝር መቀመጥ ይኖርበታል፡፡ እርሶም ምን ምን ማድረግ እንደሚገባው መነሻ ሆኖ ያገለግለዎታል የሚል እምነት ሰላለኝ፡፡ በአጭሩ ለማቅረብ እሞክራለሁ፤
1.      የፖለቲካ ፓርቲዎች ለቢሮ የሚሆናቸውን ደረጃውን የጠበቀ ፅ/ቤት በኪራይ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ቢያንስ አንድ የተሟላ ፅ/ቤት የሌለው ፓርቲ እንደ ፓርቲ ሊቆም የሚችልበት ሁኔታ የለም፡፡
2.      የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሚያደርጉት የአዳራሽ ስብሰባ ማነኛውም አዳራሽ በኪራይ የሚያቀርብ ተቋም/ሆቴል ያለምንም የተለየ የዋጋ ጭማሪ አገልግሎቱን እንዲሰጥ፤
3.      የህትመት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን ማንኛውንም የህትመት አገልግሎት ያለምንም ቅድመ ሁኔተታ መስጠት፣ እና
4.      ማንኛውም የፓርቲ አባላት የፓርቲውን ሰነዶች (የድምፅ፣ የምስል፣ የህትመት፣ ወዘተ) በሚያሰራጩበት ወቅት ምንም ዓይነት ጫና በፖሊስም ሆነ በሌላ አካል እንዳይደርስበት ማድረግ፤
ያስፈልጋል፡፡ እነዚዚ ከላይ የተዘረዘሩት ጉዳዮች ለአንድ ፓርቲ ወደ ሕዝብ ቀርቦ አማራጩን ለማቅረብ ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እነዚህ ተግባራት አሁንም የሚቻሉ በሕገ-መንሥት እውቅና ያገኙ ናቸው፤ የሚል የድርቅና ሙግት ሲቀርብልን ለረጅም ዓመተት መቆየታችን ይታወቃል፡፡ ትልቁ ችግር እነዚህን መብቶች፤ በውስጥ አስራር በመንግሰት መዋቅር እንዲታፈኑ መደረጋቸው ነው፡፡ የፖለቲካ ምዕዳሩ ጠፍቷል ያስባለው እና ይህን ሕገ መንግሰታዊ ድንጋጌ ለመተግበር የተንቀሳቀሱ ደግሞ ለእስርና እንግልተ የተዳረጉት በዚህ ኢ-ሕገመንግታዊ አሰራር ነው፡፡ ክቡርነትዎም በንግግሮ ሕገ መንግሰቱ ያሰቀመጣቸው ዴሞክራሲያዊና ስብዓዊi መብት የተመለከተቱ ድንጋጌዎች በተሟላ ሁኔታ መከበር እንዳለበተት አፅዕኖት ሰጥተውታል፡፡ መፍትሔውም፤
የቢሮ ችግር ለመፍታት ብዙ አማራጭ ሊታይ እንደሚችል ባስበውም ለዚህ ምላሽ ለመስጠት እንደመነሻ በየወረዳው የተገነቡ የወጣት ማዕከላት አሁን በተለያየ አግልግሎት በአብዛኛው ተከራይተው ምግብ ቤት እና ታይኳንዶ ማሰልጠኛ የሆኑት ሊታሰቡ ይችላሉ፡፡ ጠንከር ያለ መመዘኛ ወጥቶ ለፓርቲዎች ፅ/ቤት እንዲሆኑ ማሰብ ይቻላል፡፡
በሆቴሎች በሚደረጉ ስብሰባዎች የሚተላለፍ መልዕክት፤ ማተሚያ ቤቶች በሚያትሙት መልዕክት ወይም የፓርቲ አባላት በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ ህገወጥ ተግባር ተፈፅሞ ቢገኝ አግልግሎት ሰጪዎች ወይም ዝርዝር የፓርቲ ተግባር የሚፈፅሙ አባላት ምንም ዓይነት ተጠያቂነት የሌለባቸው መሆኑ ታውቆ በይፋ መነገር እና በዚህ ጉዳይ ሙሉ ሃላፊነቱን የሚወስደው የፓርቲ አመራር መሆኑን በህግ መደንገግ ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪ አገልግሎት ሰጪዎች በማንኛውም ሁኔታ፤ የመንግሰት አካል ነኝ ብሎ በግንባር ቀርቦ፣ በቃል፣ በስልክ ወይም በሌላ ሁኔታ አገልግሎት አቋርጡ የሚል ትዕዛዝ ቢሰጥ፤ ይህን ትዕዛዝ መቀበል እንደሌለባቸው በህግ መደንገግ ይኖርበታል፡፡ ፓርቲዎች በተከራዩት አዳራሽ፣ በሚያሰራጩት ህትመት፣ ወይም ሌላ እንቅስቃሴ ጥፋት መፈፀማቻው በፍርድ ቤት ተረጋግጦ በህግ ሲታገዱ ብቻ አገልግሎት አለመስጠት እንደሚችሉ እንዲያውቁት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ በአገልግሎት ሰጪዎች እንዲሁም ዜጎች ላይ የተዘራውን ፍርሃት ለመግፈፍ መወሰድ ያለበት እርምጃ ነው፡፡
ክበር ጠቅላይ ሚኒስትር በቁጥጥር ስር የነበሩ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ በመፍታት በጎ ጅምር ታይቷል፡፡ በቀጣይም ሁሉም እስረኞች እንደሚፈቱ እምነታችን ነው፡፡ ይህም በአገር ውስጥ ለመንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ በአገር ውስጥ በሚፈጠረው አዎንታዊ እርምጃ መሠረት ላይ፤ በማንኛውም መንገድ መንግሰትን መጣል አለብን ብለው ለተነሱት ሀይሎች ጥሪ ማቅረብ እና በሀገራቸው በሰላማዊ መንገድ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉበት ምህዳር መፈጠሩን ማሳየትና ማስተማመኛ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን ተግባራት ለመፈፀም ክቡርነትዎ አንድ ገለልተኛ ኮሚሽን ማቋቋም ያስፈልጎታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በተቋም ላይ ተቋም ማቋቋም አያስፈልግም፤ የሚል ጎንጭ አልፋ ክርክር ሲነሳ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ መንገድ ገዢው ፓርቲ ቁርጠኛ ያለመሆኑን ከማሳየት ውጭ ሌላ ነገር አላስተማረንም፡፡
የሚቋቋመው ኮሚሽን ዋናው ተግባሩ በጥርጣሬ የሚተያዩ ሀይሎች እንዲተማመኑ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር በተጨማሪ አሁን ያሉት ተቋማት በመፈተሸ በሚጠበቅባቸው ደረጃ ከወገንተኝነት ተላቀው እንዲሰሩ ማስቻል ነው፡፡ ይህ ኮሚሽን አፋኝ የምንላቸውንም ሕጎች መፈተሸ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ፤ ኮሚሽኑ ለዴሞክራሲው ስርዓት ግንባታ አዎንታዊ ሚና ያላቸው ሚዲያና ሲቪል ማህበራት ህዝቡን በማንቃትና በነፃነት እንዲንቀሳቀስ የሚሰሩበት ሁኔታ እንዲፈጠር መስራት ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ሁሉ ግን ሊሆን የሚችለው እርሶዎ በሚመሩት መንግስት እና ግንባር በጎ ፈቃድ ብሎም ለአውነተኛ አገራዊ ለውጥ ባለው ፍላጎት ነው፡፡ ገዢው ግንባር እንዲህ እንዲያደርግ ሊያስገድድ የሚችል ተቃዋሚ ፓርቲ አደረጃጀት በሚያሳዝን ሁኔታ የለም፡፡ አማራጭ ሆኖ የቀረበው ሕዝባዊ እንቢተኝነት መሆኑ ቀጣዩን ተግባር ከባድ ያደርገዋል፡፡ እርሶ የሚመሩት ግንባርና መንግስት የተደራጀ ሀይል አማራጭ እንዲያቀርብ ካላደረጋችሁ፤ ይዋል ይደር እንጂ የተዳፈነው የህዝብ ቅሬታ ይፈነዳል፡፡ አሁን በተያዘው የኢህአዴግ ብቸኛ መስመር ወይም “ጥልቅ ተሃድሶ” ሊፈታ እንደማይችል መታወቅ ይኖርበታል፡፡ መደመር ይኖርበናል፣ ተባብረንም ረጅም ጊዜ ሊወስድብን ይችላል፡፡ ይህ የዜጎች ቅሬታ በተለይ የ30 ሚሊዮን ወጣት ብሶት፤ መንግሰት መደብኩት ባለው ብር 10 ቢሊዮን የሚለዝብ እንዳልሆነ እርግጠኛ ሆኜ መናገር እችላለሁ፡፡
ከብሩነትዎ እርሶም ሆኑ የሚመሩት ግንባር ኢህአዴግ በዚህች ሀገር ውስጥ አዎንታዊ ታሪክ እንዲኖርዎ ፍላጎቴ ነው፡፡ ይህ ከተፈለገ፣ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በሚል የተሰዉት ክብር እንዲያገኙ ከተፈለገ፤ እስከዛሬ የተከናወኑ በጎ ተግባራት ለቀጣይ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባት እርሾ እንዲሆን ከተፈለገ፣ ወዘተ….ድርጅቶ በፈቃደኝነት የቀረበለትን ቀላል የፖለቲካ ምህዳር ማሻሻያዎቹን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ድርጅቶ ቀላሉን ከመለስ ከባዱን አብረን ለመስራት እድል ይገኛል፡፡ ይቻላልም፡፡
አመሰግናለሁ!!!
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጊዜ ያለፈበት እና መነሳት እንዳለበት ሳልዘነጋ ነው፡፡