Wednesday, September 26, 2018

የኦሮሞ ድርጅቶች መግለጫ እና የእኔ ዕይታ!


የኦሮሞ ድርጅቶች ነን ያሉ አምስት ድርጅቶች በኦሮሞ እሴቶችና ጥቅም ላይ በመመርኮዝ የኦሮሞን አንድነት በሚያንጸባርቅ እና እንደ በሚያደርጋቸው ፤ እንዲሁም በወቅታዊ አንገብጋቢ የፖለቲካ ጉዳዮች ናቸው ብለው ባመኗቸው ጉዳዩች ዙሪያ የጋራ ያሉትን አቋም ወስደዋል፡፡ ይህ አቋማቸው ግን በሁሉም ዘንድ በሁሉም ጉዳይ ሰምምነት ይፈጥራል ባይባልም- ጫጫታ ፈጣሪ እንደሆነ ግን የሚካድ አይደለም፡፡ በእኔ ዕይታ ይህ መግለጫ በኦሮሚያ ክልል ለሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ኦዴፓ/ኢህአዴግን ሳይጨምር የምርጫ ማኒፌስቶ ተደርጎ ቢወሰድ ደስ ይለኛል፡፡ ድርጅቶቹ በመግለጫቸው እንዳሉት በምርጫ የሚያምኑ ከሆነ ውጤቱን ሕዝብ የሚሰጠው ሰለሚሆን፡፡ ሲጀመር የኦሮሞ ድርጅቶች ነን ያሉ ያልኩት ያልተመረጡ፤ የያገባናል ስብስቦች በመሆናቸው ነው፡፡ ይህን ሃሳባቸውን ይዘው ለሕዝብ ቀርበው በህዝብ ከተመረጡ የዛን ጊዜ የኦሮሞ ወኪሎች አድረገን እንወስዳቸዋለን፡፡ ለማንኛውም መግለጫው ከጥቂት ማስፈራሪያ ውጭ ብዙ እዚህ ግባ የሚባል ነገር ባይኖረውም አንድ አንዱ ጉዳዮቹ ግን ለውይይት የሚጋብዙ በመሆናቸው የግል ዕይታዬን ማጋራት ወድጃለሁ፡፡

የኦሮሞን ማንነት ለማጥፋት እየተደረገ ያለውን ሙከራ በተመለከተ
በዚህ ርእስ ስር መግለጫው ያቀረበቸው ጉዳዮች የኦሮሞን የሚያክል ትልቅ ሕዝብ የሚመጥን ሳይሆን ጥበቃ ሊደረግለት ለሚገባ አናሳ ቡድን የሚነሱ ጉዳዮች ናቸው ብዬ ለማመን እፈልጋለሁ፡፡ እስኪ ማን ነው የኦሮሞን ሕዝብ ለማጥፋት ሃስቦ በተግባር ሊንቀሳቀስ የሚችል? ይህ ሴረኛ ፖለቲከኞች ከሚያስቡት ውጭ በተግባር ሊውል የሚችል ሃሳብ አይደለም፡፡ እርግጥ ነው ባለፉት አምሳ ዓመታት በተዘራ ዘረኝነት የተለከፉ ሰዎች አንድ አንድ ጥቃቶችን በሀብትና ንብረት ላይ ብቻ ሳይሆን በክቡር የሰው ልጆችም ላይ ስጋት ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ወንጀለኞች ግን በምንም መመዘኛ የኦሮሞን ሕዝብ ሊያጠፋ የሚችል አቅም ሊኖራቸው አይችልም፡፡ እነዚህን ጉዳዮች በተለይ የጨቅላ ሕፃን ግድያ ጨምሮ የፖለቲካ ትኩሳት ለማሰነሻ፤ በተለይ ደግሞ ለተፈፀሙ ዘግናኝ ማንነትን መሰረት ላደረጉ ጥቃቶች እንደ ሰበብ ለመጠቀም የሚሞክሩ ሸፍጠኛ ፖለቲከኞች አገር መሆናችን አሳዛኝ እውነት ነው፡፡ በዚህ መግለጫ “ጸረ ኦሮሞ አቋም ያለው የተደራጀ የፖለቲካ ቡድን ሰለመኖሩ በርካታ መረጃዎች ተገኝተዋል፡፡” የሚል ዐ/ነገር አለው፡፡ ይህ እውነት ከሆነ መረጃውን ለመንግሰት በመሰጠት እርምጃ እንዲወሰድ እኛም እንድናውቅ እና አንድንታገላቸው ያስፈልጋል፡፡ በእኔ እምነት በዚህ መግለጫ የፖለተካ ሴራው በግልፅ ከማሳየት የሚያልፍ ቁም ነገር የለውም፡፡  በዚህ ክፍል መጨረሻ ያስቀመጠው አቅጣጫ ድርጊቱን ማውገዝ እና አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ የሚል በመሆኑ አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ የማይስማማ ሰለማይኖር ተሰማምተን ማለፍ የግድ ነው፡፡ ለህግ ይቅረቡ የሚለው ጉዳይ ለማለት ብቻ ሳይሆን እነዚህ አጥፊዎች ለህግ ያለማቅረብ ሌሎችን ግድ የለም ቀጥሎ ማለት ይሆናል፡፡ ማንኛውም በሕዝብ መካከል እና ጉዳት በደረሰባቸው አካላት የሚደረግ የሽምግልና እና የእርቅ ጉዳዮች አጥፊን ከመቅጣት የሚያስቀር መሆን የለበትም፡፡ ክቡር አቶ ለማ መገርሳ ይህን ጉዳይ አፅዕኖት ሰጥተው ሲናገሩ በሚዲያ ሰለሰማው አድናቆቴ የላቀ ነው፡፡

ፊንፊኔን በተመለከተ

እነዚህ ድርጅቶች ያወጡት መግለጫ ፊንፊኔ “`የእነ እገሌ ጎሳ የእምነት የባህልና የኤኮኖሚ ማዕከል እንደነበር ማንም የሚክደው አይደለም፡፡” በሚል አደገኛ እና የተሳሳተ መነሻ መሰረት ያደረገ ነው፡፡  አደገኛነቱ በዚህ አያቆምም “እነዚህ ጎሳዎች በሀይል እንዲጠፉ ተደርገዋል፡፡” በማለት አንድ ዘር አጥፊ አካል/ቡድን ያፋልጋል፡፡ በፊንፊኔ አሳቦም በኦሮሞ የአገር ባለቤትነት ጥያቄ  በሚል ኢትዮጵያ የምትባል አገርን በጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡ ለማንኛውም ፊንፊኔ/አዲስ አበባ የኢትዮጵያዊያን የእምነት የባህል የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማዕከል ናት፡፡ ማንም በተለየ የእኔ የሚላት እና በሕግም በታሪከም ባለይዞታ ነኝ ሊል የሚችልበት ነባራዊ ሁኔታ የለም፡፡ ነዋሪዎቿ መብታቸውን የሚያስከብሩት ደግሞ ለማንም ድርጅት ሃላፊነት በመስጠት ሳይሆን በሚመርጡት ተወካይ በመተዳደር፣ የመረጡት አካል በተገቢው ሳይከውን ሲቀር በማውረድ ነው፡፡ አዲስ አበባችን በማንም የብሔር ማዕቀፍ ባለቤትነት እንድትወድቅ መፍቀድ አንችልም፡፡ ምንም ዓይነት ማስፈራሪያም ሆነ ማባበያ የሚመልሰው አይደለም፡፡ ይህ ክፍል የፖለቲካ አሻጥር መገለጫ የሆነ የመግለጫው መጥፎ ፀያፍ ክፍል ነው፡፡ መግለጫው ላይ በሚታየው እብሪት እና ማን አለብኝነት፣ በቅርቡ በአዲስ አበባ በአፈሳ መልክ የሚታየው “ጭጭ” የማሰኘት እርምጃ አኳያ የሚሸተው ነገር ጥሩ አይደለም፡፡ በአንድ ወቅት አርሲ ተወልዶ ቦረና የሚሰራ ጎረምሳ ከአምሳ አመት በላይ ተወልጄ በኖርኩበት አዲስ አበባ ምን አገባህ? ያለኝን አስታውሶኛል፡፡ እኔ አያገባኝም- በቀለ ገርባና ጓዶቹ ያገባቸዋል፡፡ የምጸት ሳቅ የሚያስቅ ነው፡፡

ዶክተር አብይ የሚመራውን የለውጥ ሂደት እንደግፋለን እያሉ ጠብ አጫሪ መግለጫ ማውጣት እና በመዲናው ውጥረት የሚያነግስ፤ ነዋሪውን መጤ ሌላውን ባለቤት የሚያደርግ አካሄድ እብሪት እንጂ አመክንዮ በአጠገቡም እንደሌለ ያስረዳልና ልብ ማለት የግድ የሚል ይመስለኛል፡፡


ሕዝብን ለሕዝብ የሚያጋጩ ሚዲያዎችን በተመለከተ
ትኩረቱ ኢሳት ላይ ቢሆንም ዋና ነጥቡ ግን ቄሮን አትንኩ ነው፡፡ ማስፈራራት ጭምር ያለበት ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ኢሳት የእጁን ያገኘ ይመስለኛል፡፡ ኢሳት በማንም የተለያ ብሔር ላይ በፖሊሲም ይሁን በአሰራር ጥላቻ አለው ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን በሰላማዊ ትግል ላይ የነበረው ጥላቻ እና በሰላማዊ መንገድ ለሚደረግ የቁርጥ ቀን ትግል ፊቱን አዙሮ አሁን የክስ ናዳ ላወረዱበት ወገኛ የትጥቅ ትግል አፍቃሪ ብሔረተኞች ዋንኛ መድረክ ሆኖ መክረሙን የሚዘነጋው አይመስለኝም፡፡ በምርጫ 2007 የደረሰብንን የተቀናጀ የሚዲያ ዘማቻ የምንረሳው አይደለም፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ቄሮን የመላዕክት ስብስብ በማድረግ ለማስፈራሪያነት መጠቀም ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ለመጣው ለውጥ ሙሉ ባለቤት የማድረግ ፍላጎት በግልፅ ይታያል፡፡ ቄሮ በኦሮሚያ ለነበረው ለውጥ የማይናቅ አሰተዋጾ ማድረጉ አይካድም፡፡ በቀጣይም ፀረ ጭቆና ላይ አሰፈላጊ ሀይል ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ማለት ግን በቄሮ ሰም ወንጀለኞች ወንጀል እየሰሩ አይደለም ማለት አይደለም፡፡ በቡራዩ በተግባር የታየው በሌሎች አካባቢዎች ምልክቱ ግልፅ የነበረው አደጋ በምንም ሰበብ የሚፈለግለት ሳይሆን አጥፊዎች በስም ተጠርተው ለህግ መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ሚዲያዎች ይህን በማጋለጥ ሂደት ስህተት ሰርተው ከሆነ ማስተካከል እንጂ ማሸማቀቅ በፍፁም መታሰብ የለበትም፡፡ በኢትዮጵያ እየነፈሰ ያለው የነፃነት መንፈስ ለቄሮ እና ለኦሮሞ ብቻ አይደለም፡፡ በአራቱም ማዕዘን እንቢ ለነፃነቴ የሚል ወጣት ተነስቷል፡፡ ይህን ወጣት የወያኔን አገዛዝ አስወግዶ በሌላ ወያኔ ለመተካት መሞከር ከንቱ ሙከራ ብቻ ሳይሆን ማንም የማያተርፍበት አገር የማፍረስ ሙከራ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን ደግሞ መስዋዕትነቱ ውድ ሊሆን ቢችልም የምትፈርስ አገር አለመሆኗ ማሳሰብ ግድ ይላል፡፡ በጊዚያዊ የፖለቲካ ትኩሳት ዘላቂ ሰላማችንን ማግኛውን መንገድ ውድ ባናደርገው የሚል ምክር አለኝ፡፡

በአገሪቱ ያለውን ለውጥና የሽግግሩን ሂደት በተመለከተ
መግለጫው አሁን ያለው የለውጥ ሂደት እንደሚደግፍ  እና ለዚህም የበኩሉን እንደሚወጣ አሰቀምጧል፡፡ ነገር ግን የሽግግር መንግስት እንዲኖሩ የሚፈልጉ ሀይሎች አሉ ብሎ በሰም አይጠሬ ክስ ያቀርባል፡፡ እነዚህ ስም አይጠሬዎች ደግሞ ሀሰተኛ የብር ኖት የማዘጋጅት አቅም አላቸውም የሚል የመንግሰት የሚመስል ሃሳብ አለው፡፡ መንግሰትም በሚዲያ ይህንኑ እየገለፀ ይገኛል፡፡ ለማንኛውም ወቅቱ የሽግግር መሆኑን መቀበል ጥሩ ሆኖ ሸግግሩን ግን ለጠብ ያለህ በዳቦ በሚመስል መግለጫ መደገፍ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ለምሣሌ የሽግግር ብሄራዊ አንድነት መንግሰት ይመስረት የሚለው አንዱ ኦፌኮ የሚባለው የዚሁ መግለጫ ቡድን አባል በመሆኑ ምክራችሁን በዛው ለግሱት፡፡ ሌሎችም በሃሳብ ደረጃ ቢሉት ክፋቱ አይታየኝም፡፡ ለማንኛውም በዶ/ር መረራ አገላለፅ ልጠቀምና “የቡዳ ፖለቲካ” ትተን ሌሎች ለምርጫ ዝግጁ አይደለም  የሚለውን ክስ ወደ ጎን በመተው አሁን አለን የምትሉትን ሁሉ ይዛችሁ ለምርጫ ተዘጋጁ፡፡ ወጤት በምርጫ ብቻ ይወሰን፡፡ አዲስ አበባ የኦሮሞ ሕዝብ ነው የሚለውም ቢሆን ለአዲስ አበባ ሕዝብ ይቅረብለት እና ይወስን፡፡ ምርጫ ከአማራጭ ጋር እንደግፍ ዘመናዊ እንሁን፡፡


በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም በተመለከተ
እነዚህ የኦሮሞ ድርጅቶች በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው አስምረውበታል፡፡ አሁን ያለው ችግርም ምንጩ የፌዴራል ስርዓቱ ሳይሆን አፈፃፀሙ ነው የሚል አቋም አራምደዋል፡፡ አንድ ያልገባቸው ነገር ኢትዮጵያ አሁን ያላት ፌዴራል አወቃቀር ቋንቋን መሰረት ያደረገ ብቻ ያለመሆኑን ነው፡፡ በምናባቸው ካለው የኦሮሚያ ክልል ውጭ ላለማሰብ ሰለወሰኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለመመልከት አልፈቀዱም እንጂ “ደቡብ” በሚል የተካለለው ክልል ከአምሣ ስድስት በላይ ብሔር/ብሔረሰብ/ሕዝብ በሚል የታጨቀበት አከላለል ሲሆን ቋንቋ በምንም ሁኔታ መስፈርት አይደለም፡፡ ለማንኛውም ይህን እንደ ምርጫ ማንፌስቶ ወስደን ለሕዝብ ውሣኔ የሚቀርብ የሚሆን እንጂ ለግጭት መንስዔ ሆኖ ማገልገል የለበትም፡፡ በኦሮሚያም ቢሆን እጅግ ብዙ የሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች መኖራቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ መፍትሔውም በመግለጫው እንደተጠቀሰው ሕገ መንግሰቱን መሰረት አድርጎ የሚወሰን ይሆናል፡፡ ኦሮሚያን በኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ውስጥ መመልከት የሚችል ግን ኦሮሚያ በአንድ ብቻ ሳይሆን ከሶሰት በላይ በሆኑ የፌዴራል ስቴት ተወክላ ሕዝቡም በአካባቢው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮን ቢፈፅም ክፋቱ አይታየኝም፡፡ ይህም ቢሆን የድርጅቶች ሳይሆን የሕዝብ ውሳኔ መሆን ይኖርበታል፡፡

በመጨረሻም መግለጫው ሠላምና ነፃነት ለሁሉም ሕዝቦች! በሚል መፈክር ያጠናቀቀ ሲሆን ኢትዮጵያ ላለማለት የሄደበትን የፖለቲካ ቁማርተኝነት የሚያሳይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ እኔ ግን እላለሁ ሰላም ብልፅግና የአንድነት መንፈስ በመላው አገራችን ኢትዮጵያ እና በህዝቦቿ ይስፈን፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን በሕዝቦቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች፡፡

ፈጣሪ ኢትዮጵያ አገራችንን እና ሕዝቦቿን በበረከቱ ይጎብኝልን

መሰከረም 16 2012
ግርማ ሠይፉ ማሩ