ለዚህ
ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ፤ በሳምንቱ መጨረሻ አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ የሚገመግም የፖለቲካ ውይይት የሚደረግበት ቦታ ላይ ነበርኩ፡፡
“አንድ አንድ ኃይሎች መስከረም 30! እያሉ አደጋ ደቅነውብናል!” የሚሉ ብዙ አስተያየቶች አድምጫለሁ፡፡
አስተያየቶቹ እነዚህ ሃሣቦች አገርን ስጋት ላይ ይጥላል የሚል መደምደሚያ ላይ ለመድረስ መግቢያ ያደርጉታል፡፡ ከዚህ አልፎ ግን
አንድ ወዳጄ በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ‘I can’t breathe` በሚል ርዕስ መፃፉን ተመለከትኩ፡፡ ሰለ አሜሪካው ጥቁር፣ የነጭ ዘረኝነት
ሰለባ በመሆኑ ምክንያት ሰሜቱን ሊያካፍለን መስሎኝ ማንነብ ጀመርኩ፤ እንዲህ ይላል፤
“I
can't Breath አንድ ሰው በጠና ታመመና ሆስፒታል ገባ። ሰውዬው አፉና አፍንጫው ላይ የመተንፈሻ መሣሪያ ቢገጠምለትም ህመሙ
እጅግ በመበርታቱና ለህይወቱ አስጊ እየሆነ በመምጣቱ ፓስተሩን ለመጨረሻ ጊዜ እንዲጠሩለት ዘመዶቹን ጠየቀ። ፓስተሩ ሆስፒታል እንደደረሰ
በቀጥታ ከህመምተኛው ራስጌ ሄዶ ቆመ። በዚህ ጊዜ ህመምተኛው ህመሙ የባሰ ጠና። እንዲያውም የባሰ መተንፈስ አቃተውና እጆቹን አንስቶ
በምልክት እስክሪብቶና ወረቀት እንዲሰጡት ጠየቀ። ዘመዶቹ ፈጠን ብለው እስክሪብቶና ወረቀት ሲሰጡት እሱም ፈጠን ብሎ የሆነ ነገር
ጽፎ ወረቀቱን ለፓስተሩ ሰጠው። ፓስተሩም ወረቀቱን ተቀብሎ ኪሱ ውስጥ ከተተው። ህመምተኛው ወረቀቱን ለፓስተሩ ከሰጠ በኋላ ትንፋሽ
አጥሮት ወዲያው ሞተ። ሰውዬው ከሞተ ከጥቂት ወራት በኋላ ፓስተሩ ኮቱን ለላውንደሪ ለመስጠት ኪሱን ሲፈትሽ ያኔ ህመምተኛው የሰጠውን
ወረቀት አገኘው። ወረቀቱ ላይ የተጻፈው ፅሁፍ እንዲህ ይላል "እባክህ መተንፈስ አልቻልኩም። የኦክስጂን ቱቦዬ ላይ ቆመሀል"
I can’t breathe you are standing on my oxygen tube. የሚል ነበር፡፡ ወገኔ! ኧረ ስንቱ ቱቦአችን ላይ ቆሞ ፈጀን? አሁንም የእነ ጃዋርና
የወያኔ ቡድኖች በሰላማችን ቱቦ ላይ ቆመው እንዳንተነፍስ ከልክለውናል። እነዚህ ቡድኖች ይባስ ብለው “መስከረም 30” እንገናኝ
ብለው የሞት ቀጠሮ ቀጥረውልናል። መተንፈስ አልቻልንም። መንግሥት እንደ ጆርጅ ፍሎይድ በጉልበታቸው አንገታችን ላይ የቆሙትን ቡድኖች
ምን ሊያደርግልን አስቧል? ኧረ የአየር ያለህ! we can't breathe.”የዚህ ፅሁፍ ጥያቄ ግልፅ ነው፡፡ ደመቅ ብሎ የተሰመረበት ነው፡፡
ይህ ብቻም አይደለም፤ በምክር ቤት
ለጠቅላይ ሚኒሰትሩ በቀረበ ጥያቄ ላይ “መስከረም 30 ቁርጥ ነው፤ መከላከያም ደህንነትም አልታዘዝም ይላል፤ የሚሉ ሀይሎች እንዳሉ
ተጠቅሶ እነዚህን ሰዎች አደብ ለማስገዛት ምን ታስቧል?” የሚል ጥያቄ
መቅረቡን ሰምተናል፡፡ በፖለቲካ መድረክ፤ በማህበራዊ ሚዲያ እንዲሁም በምክር ቤት ልዩ ስብሰባ ጥያቄ ሆኖ የቀረበው ጉዳዩ፤ እንዴት
በዚህ ደረጃ አሳሳቢ ሊሆን ቻለ? ወይስ የተጋነነ ነገር አለ ብሎ ማየት አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡
በእርግጥ
አገራችን እንደሚባለው “መስከረም 30” በዚህ ልክ ልንሰጋበት የምንጨነቅበት ጉዳይ ነው? እኔ ግን አይመስለኝም፡፡ አይመስለኝም
ያልኩበትን መከራከሪያ ላስረዳ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ኑሮዋችን፤ ከሁሉም በላይ ሰላማችን እና ደህንነታችን፤ የተመሰረተው በሕጋዊ መንገድ
በተመረጠ መንግሥት እና የመንግሥት አካላት አልነበረም፡፡ ሰለዚህ እስከ ቀጣዩ ምርጫ ድረስ፤ ያልተመረጠ መንግሥት፤ ለተወሰነ ወራት
መቀጠሉን መዓት አድርገን ለምን መመልከት ፈለግን? በዴሞክራሲ የተመረጠ መንግሥትና፤ የሕዝብ ውክልና ያለው ምክር ቤት መመሰረት
የዜጎች ሉዓላዊነት መገለጫ ነው፡፡” ብለን ዘመናችንን ለትግል ሰጥተን መክረማችን እውነት ነው፡፡ መልካም ጅምር ታይቶ፤ ጫወታው
ሊጀመር ሲል “ኮቪድ 19” የሚባል ዓለም አቀፍ ችግር ደንቃራ ሆኗል፡፡ ይህንን ችግር እስክንሻገር ያልተመረጠ መንግሥት መቀጠል
የለበትም! እስከ ምርጫው ሥልጣን አጋሩን! የሚሉ መሻቶችን ለምን አየር አጠረን እንድንል አደረገን? በዚህ ምክንያት በእርግጥ አየር
ያጥረናል ወይስ እኛ በዚሁ ሰበብ አየር ልናሳጣው የፈለግነው ኃይል አለ?
ኢትዮጵያ
አገራችን ተቀባይነት በሌለው በምርጫ በተመረጠ መንግሥት ላለፉት 40 ዓመታት፤ ከዚያ በፊት በሴራና በዘር ቆጠራ በመጡ ነገስታት
ስትመራ እንደ ነበር እናውቃልን፡፡ ይህ ልክ አይደለም ብለው የተነሱ ሀይሎች የዘውዱን ሥርዓት አስወግደዋል፡፡ እነርሱም በተራቸው
ያስወገዱትን ሀይል በምን እንደሚተኩ በውሉ ያላሰቡበት ጉዳይ ሰለነበር፤ ደርግ ተተካልን፡፡ በምትኩ የመጣው ደርግም ጠብመንጃ ባነገቶ
ሀይሎች ተገፍትሮ ሄዷል፡፡ የጉዞ ሂደቱ ቀጥሎ ባለ ጠብመንጃዎቸም፤ በሕዝብ አመፅ ተገፍተው፤ ለጥገናዊ ለውጥ እንዲዘጋጁ ተገደዋል፡፡
በዚህ ሁሉ ሂደት፤ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥትም ሆነ፤ ሰምምነት ያለው ሕገ መንግሥታና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓት ልንዘረጋ አልቻልንም፡፡
ይህ ስላልሆነ፤ ወደፊትም ኢትዮጵያ አገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አያስፈልገንም የሚል እንደምታ ሊኖረው አይገባም፡፡ በጨለማ መክረማችን እውነት ሆኖ፤ ሊበራልን ተቃርቦ ባለበት የመጣን ችግር እንዴት
እንፍታ ብለን መወያየት ሲገባ፤ እንዲህ ካልሆነ እንዲህ ይሆናል ብሎ ፉከራና ቀረርቶ ምንጩ ምን እንደሆነ ሰለ አልገባኝ ብቻ ሳይሆን፤
በዚህ አሳበን፤ ሃሣብን የመገደብና የማቀጨጭ ፍላጎታችንም በውስጡ የሚታይ ስለመሰለኝ፤ ይህን ርእስ መወያያ ማድረግ ፈልጊያለሁ፡፡
በእኔ
እምነት እነዚህ መሻቶች ዴሞክራሲያዊ ልምምዶች ለማዳበር ብቻ ብንወስደው ምርጫዬ ነው፡፡ ማንኛውም የተለየ
ሃሣብ በመጣ ቁጥር ታፈንን፤ መንግሥት አንድ ነገር ያደርግልን የሚለው ኡኡታ! ብዙም ምቾት የሚሰጥ አይደለም፡፡ መስከረም 30 መንግስት
በህግ የተሰጠው ገደብ የሚያበቃ በመሆኑ፤ ቀጣዩ ጊዜ በጋር የምንገዛበት መንገድ ይከፈት የሚል መሻት ያሰዩ ሰዎች አሉ፡፡ ይህን
መሻታቸውን የገለፁት ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች ያሉት ነገር ቢኖር፤ መስከረም 30 የገዢው ፓርቲ እድሜ ሰለሚያበቃ ሕዝቡ በዝምታ አይመለከተም
ነው፡፡ ይህን ግምታቸውን ባለን የእለት ከእለት ግንኙነት ስንፈትሸው ምን ይመስላል? በእኔ ግምገማ ይህ የማይሆን ነው፤ ከሆነም ሲደርስ የምናየው ይሆናል ማለት
ነው፡፡ ሕዝቡ፣ ሕዝብ ጉሮሮ ላይ የሚቆም ከሆነ እጅን በራስ እጅ መቆርጥ ነው፡፡ ሕዝቡ ይህን አያደርግም ብለን ካመንን፤ በግለሰብ
ደረጃ ያለ ፉከራ አንዴት ጉሮሮዋችን ላይ ተቆመ የሚል ሰሜት አደረብን? በእርግጥ አየር አጥሮን ሳይሆን የሃሣቡን ባለቤቶች በተለይ “የሽግግር መንግሥት” ከመስከረም 30 በኋላ የሚሉትን
በሰበብ እንዲደፈቁልን የአንባገነንነት ድብቅ መሻታቸን አይደለም ብላችሁ ታምናላችሁ? ውድ አንባቢያን ይህን ፅሁፍ በምታነቡበት ወቅት፤
የኢትዮጵያ ሕዝብ በፌስ ቡክ ጥሪ፤ ኦ! ብሎ ወጥቶ እጁን በእጁ ይቆርጣል ብላችሁ ታምናላችሁ? ካልሆነ ይህን ጉዳይ ለምን ትንፋሽ
አጠረን ያስብለናል? ግድ የለም! መስከረም 30 ትንፋሽ አያጥረንም፡፡ አንሞትም! ኢትዮጵያም አትፈርስም፡፡
ኢትዮጵያ
አትፈርስም የሚለውን ተስፋ እያደረግን፤ ከመስከረም 30 በኋላ የሽግግር
መንግሥት ይሁን ወይም ሌላ አማራጭ የሚሉ ሰዎችን እንዲደፈቁ በግልፅም ይሁን በአደባባይ፡፡ በምክር ቤት ስብስባም ቢሆን መጠየቅ
ብናቆም ጥሩ ነው፡፡ ዛሬ ለዚህ ዓይነት የተለየ ሃሣብ አንባገነናዊ መፍትሔ ከጠየቅን እኛም ሌላ ጊዜ፤ የተለየ ሃሣብ ለማመንጨት
ፈራ ተባ ማለታችን አይቀርም፡፡ ከመስከረም 30 በኋላ በእርግጥ ሌሎች ብዙ ሥራዎች ይኖሩናል፡፡ ይህ ሕዝብ የእውነተኛ የሥልጣን
ባለቤት የየሚያደርገውን ምርጫ እናደርጋለን፤ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስፈልገን ጉልበት፣ አቅምና ሃሣብ በስጋት እንዳናባክን
መጠንቀቅ የግድ ይላል፡፡ ሕዝብ ወኪል እንዲሆኑት የሚፈልጋቸውን ፓርቲዎች ማየት ይፈልጋል፡፡ ፓርቲዎቸም ዓይነ ግቡ ለመሆን/ለመታየት
ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ቸር
ይግጠመን!!
እርቀታቸንን
እንጠብቅ!!