Thursday, September 4, 2014

የኢቲቪ ጥያቄዎች እና የእኔ መልሶች


በሰሞኑ ሰለ ግል ሚዲያው ትንሽ ለማለት ሞክሬ ነበር፡፡ የዚሁ ተከታታይ የሆነውን ይህ ፅሁፍ ደግሞ በዋነኝነት የአሁኑ የኢትዮጵ ብሮድካሰት ኮርፖሬሽን ለዘጋቢ ፊልም መስሪያ ብሎ ያዘጋጀውን ጥያቄ መሰረት አድርጌ አቀርብላችኋለው፡፡ ከጥያቄው መረዳት እንደምትችሉት ጥያቄዎቹ ለውንጀላ በሚያመች መልኩ የተዘጋጁ ሰለሆነ በግልፅነት ጥያቄውን ለመመለስ የሚሞኩሩ ሰዎች እንደ አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ መጠለፋቸው አይቀርም፡፡ ሚዲያ ብላችሁ አዲስ ዘመንን ስትከሱት ኢቲቪ ከሌላ ቦታ ካመጣው ጋር ቆርጦ ቀጥሎ ዘጋቢ ፊልም የግል ሚዲያውን ለመክሰስ ግብዓት ያደርጋችኋል፡፡ ይህን ለመከላከል ኢቲቪን በሩቁ ማለት ሳይሻል አይቀርም፡፡ ለዚህም ነው የቀረቡልኝን ጥያቄዎች ለኢቲቪ ብመልስ ምን ሊሆን እንደሚችል በምትረዱት ሁኔታ ከዚህ በታቸ የማቀርብላችሁ፡፡
ኢቲቪ እንደ መግቢያ በመጀመሪያ ያቀረበው ጥያቄ “ብሄራዊ ጥቅም ማለት ከኢትዮጵያ አንፃር መገለጫዎቹ ምንድናቸው?” የሚል ነው፡፡ የዚህ ጥያቄ ዓላማ በመጨረሻ ላይ ከሚቀርቡት ጥያቄዎች አንፃር ስታዩት የግል ሚዲያዎቹ እነዚህን ብሔራዊ ጥቅሞች እየተጋፉ ነው የሚል መደምደሚያ ለመስጠት እንዲመቸው ያቀረበው ነው፡፡ በእኔ እምነት በቅርቡ እየሰፋ የመጣውን ሀገር ማለት? የሚለው  ተጠየቅ መሬት ሲደመር ሰው (አንድ እና አንድ ሁለት እንደሚባለው) ማለት አይደለም፡፡ ለምሣሌ የዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ሀገር ማለት የእኔ ልጅን ልብ ይሏል፡፡ የመለስ ዜናውንም ሀገር ማለት ህዝብ ነውም የሚረሳ አይደለም፡፡ የዶክተር ሀይሉ ኃርሃያን የሀገር ልክፍት ግጥምም ትዝ ይለኛል፡፡ የዚህን ጥያቄ መልስ እንደ እልም ፈቺ፤ ለእልም ፈቺ እንተውው እና በእኔ እምነት ብሔራዊ ጥቅም ወይም የሀገር ጥቅም ማለት በአጭሩ የዜጎች ጥቅም ብዬ ነው የማስበው፡፡ የሀገረ ኢትዮጵያ ጥቅም የሚባል ነገር ሁሉ የኢትዮጵያዊያን ጥቅም ማለት ነው ብዬ ነው የምረዳው፡፡ ኢትዮጵያዊያኖች እንዴት ነው የሚጠቀሙት ብለን ወደ ዝርዝር ሰንገባ ደግሞ በሠላም ወጥቶ መግባት/መኖር፤ የሰውነት መብት መከበር፤ የህግ የበላይነት መኖር፤ ወዘተ ሲሆኑ መንግሰት እነዚህን ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስችለው መዋቅር እንዲኖረው ማደረግ ደግሞ የህዝቡ ዋነኛ ኃላፊነት ይሆናል፡፡ አንድ አንድ ሰዎች ጥቅም የሚባለውን ነገር ከራሳቸው በላይ ዘለግ አድርገው ማየት ስለማይችሉ ለልጅ ልጆች ሀገርን እንደ ሀገር አስጠብቆ ማለፍ የእነርሱ ድርሻ አይመስላቸውም፡፡ ለዚህም ነው ድንበር ማስከበርም፣ ዛፍ መትከልም፣ ወንዝ ተራራውም እንዲጠበቅ ማድረግ የመሳሰሉት አብይ ጉዳዩች ባለቤት ያጣሉ፡፡ ንቁ ዜጎች ግን ይህን በፍፁም አይዘነጉትም፡፡ ዛፉ ጥላው አድጎ ባይጠቀሙበት እንኳን ችግኝ መትከል ሀገራዊ ሃላፊነታቸው እንደሆነ ይረዳሉ፡፡ ድንበር ማስከበርም እንዲሁ ለልጅ ልጆቻቸው የሚተላለፍ መሆኑን ስለሚገነዘቡ ሀገር ቆርሰው አይሰጡም፡፡ ለኢቲቪ ይህን መልስ ብሰጠው የት ሰፈር እንደሚቆርጠውና ከምን ጋር እንደሚቀጥለው መገመት አያሰቸግርም፡፡
የኢቲቪ ተከታዩ ጥያቄ “የግል ፕሬሶች የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅሞች በማሰጠበቅ ረገድ ምን ያህል እየሰሩ ነው?” የሚል ሲሆን ከመጀመሪያው ጥያቄ ጋር ያለው ዝምድና ፍንትው ብሎ ይታያችኋል፡፡ በግሌ ለዚህ ጥያቄ ያለኝ መልስ “አንድም የግል ፕሬስ” የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ ለአሜሪካ፣ ለአውሮፓ፣ ለሀረብ ወይም ለሌላ አካል አሳልፎ ይሰጣል የሚል እምንት ሊኖረኝ አይችልም፡፡ በሀገራችን እንዳለመታደል ሆኖ መንግሰት የሚባለው አካል ከላይ የዘረዘርኳቸውን የህዝብ ጥቅሞች ማስጠበቅ ሲያቅተው እና ይህን ችግሩን በሌላ ማለከክ ሲፈልግ የግል ሚዲያዎቹ ቅርብ ሆኖ ያገኛቸዋል፡፡ ስለ መንግሰት በጎ በጎውን መዘመር እንጂ የመንግሰትን ኃላፊነት ያለመወጣት እና ደካማነት ሲነሳ “የሀገር/የህዝብ ጥቅም” ተነካ ብሎ ቡራ ከረዩ ማለት ይቀናዋል፡፡ እውነቱን ስንመለከተው ግን ጥቅም የተነካ ከሆነ ወይም ሊነካ ከሆነ የተነካው የሹሞች ጥቅም ነው፡፡ እርሱም እንደ ዜጋ ከሚያገኙት ሳይሆን በወንበር ተገን የሚዘርፉት ነው፡፡ የግል መልሴ ለኢቲቪ ይህ ነበር የሚሆነው፡፡

ሶሰተኛው ጥያቄ “የግል ፕሬሶቹ መሰረታዊ የሆኑ የግለሰብ መብቶቸን በሚጋፋ መልኩ እየሰሩ ይገኛሉ ይባላል፤ በዚህ ላይ እርሶ ይስማማሉ ወይ?” የሚል ነው፡፡ እነዚህ የግል ፕሬሶች ማሰረጃ የሌለው  ነገር አትመው የግል መብት ነክተው ከሆነ በማስረጃ ፍርድ ቤት ማቅርብ ይቻላል፡፡ የግለሰብ መብት የሚሉት ግን ሹመኞቹን እንደሆነ መረዳት አይከብድም፡፡ አንድ አንድ ሹመኞች የህዝብ ማስተዳደሪያ የሆኑትን የሹመት ቦታዎች ሲረከቡ አብሮ የሚመጣውን የግል መብትና ነፃነት ገደብ ይዘነጉታል፡፡ የመንግሰት ንብረት ሲያስተዳድሩ በትክክል ካልተጠቀሙ ሚዲያው ይህን ለልጆቻቸው ብሎ ዝም ብሎ ሊያልፋቸው አይችልም፡፡ ይህ በመንግሰት ሹመኞች ላይ ብቻ ሳይሆን የህዝብ ህውቅናን ያገኘ ማነኛውም አይነት ታወቂነት ደረጃ ላይ የሚገኝ አርቲስት፣ ባለሀብት፣ ሯጭ፣ ወዘተ ሊሆን ይቸላል፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን የግል ሚዲያዎች የግለሰቦችን መብቶች ሊጥሱ የሚችሉበት ምክንያት የለም፡፡ ማንነቱ ስለማይታወቅ ሰው ቢፅፉ ማንም ሊያነብላቸው አይችልም፡፡ ትርፉ ኪሳራ ነው የሚሆነው፡፡ በእርግጥ እነዚህን የግል መብቶች ከላይ እሰከታች የሚጣሱት ጡንቻና መዋቅር ባለው መንግሰት ነው፡፡ መንግሰት ደግሞ እነዚህን ድርጊቶች የሚፈፅመው ለህዝብ ጥቅም ስል ነው ይላል፡፡ እኛ ደግሞ በህዝብ ስም መብታችንን አትጣስ እያልን ለትግል የወጣነው በግል ሚዲያ ላይ ሳይሆን በመንግሰት ላይ ነው፡፡
አራተኛው ጥያቄ “አሁን በገበያ ላይ ያሉት የግል ፕሬሶች የጋዜጠኝነትን መሰረታዊ የስነ ምግባር መርሆዎችን ጠብቀው በመሰራት ረገድ ምን ዓይነት አዎንታዊና አሉታዊ አስተያየት አለዎት?” የሚል ነበር፡፡ ይህ በተደጋጋሚ ጋዜጠኛ ነኝ የሚሉት ሁሉ የሚያነሱት ነጥብ ሲሆን ሰምምነት ተደርሶበት ሁሉም ሊገዛለት ይገባል የተባለ የሰነ ምግባር መርሆ ግን በዓለም ላይ የለም፡፡ አብዛኞቹ የሚስማሙበት ግን ጋዜጣኛ መርዕ ማድረግ ያለበት ነገር ካለ “ተጠያቂነቱን ለህዝብ” ማድረግ ነው፡፡ ይህም ማለት የህዝቡን የመረጃ ፍላጎት ማርካት ነው፡፡ ከዚህ ተከትሎ የሚመጡ የመረጃ ትክክለኝነት፣ግብረገባዊነት፣የመሳሰሉት ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ይህን ጋዜጠኛው ማሟላት ካቃተው ደግሞ ተጠያቂነቱ ለህዝብ ይሁን ካልን ፍርድ ሰጪውም ህዝብ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ህዝብ ዓይንና ጆሮ ሲከለክላቸው ከገበያ ይወጣሉ፡፡ ብሎም ይጠፋሉ፡፡ በዚህ ጊዜ “አከፋፋዮች” ናቸው እንዲህ የሚያደረጉት የሚል ክስ ውሃ አይቋጥርም፡፡ በውጭ ሀይል ግፊት ነው የሚለውም ክስ የትም የሚያደርስ አይሆንም ማለት ነው፡፡

በመጨረሻ የቀረበው ጥያቄ “የፖለቲካ ፓርቲዎችና ፕሬስ አንዱ በሌላው ላይ ያላቸው አዎንታዊና አሉታዊ ተፅህዕኖ እንዴት ይታያል?” የሚል ነው፡፡ የዚህ ጥያቄ ዓላማ የግል ፕሬሶቹ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ልሣን ሆኑ የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ ነው፡፡ በእውነቱ ግን ሁልጊዜ ፕሬስ  “የWatch Dog - የህዝብን ጥቅም የመጠበቅ” ስራውን መዘንጋት የለበትም - ፓርቲዎች በየተራ ስልጣን የሚይዙ ስለሆነ የፕሬስ ይሁንታን ለማግኘት መጣጣራቸው አይቀርም፡፡ ተገቢም ነው፡፡ በእኛ ሀገር ገዢው ፓርቲ “የህዝብ/የመንግስት” የሚባሉትን ሚዲያዎች ጠቅልሎ የያዘና መረጃም የማይስጥ ስለሆነ፤ የግል ሚዲያዎች ደግሞ በመንግሰት በኩል የተነፈጉትን መረጃ ለማግኘት እና የገዢው ፓርቲ ተግባርም ትክክል እንዳልሆነ ለማሳየት በተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ቢወግኑ ክፋት የለው፡፡ ለነገሩ መንግስት መረጃ እየሰጣቸውም ቢሆን መንግሰት መደገፍ የማይፈልግ የግል ሚዲያ ማቋቋም ነውር የለውም፡፡ ነውር የሚሆነው በመንግሰት ሚዲያ ገዢውን ፓርቲ ብቻ ማገልገል ነው፡፡ 

No comments:

Post a Comment