ዛሬ እንድ
ፍልስፍና ብጤ አስኝቶኝ ነው ለመፃፍ የተነሳሳሁት፡፡ የወታደራዊ እና/ወይም አንባገነናዊ መንግሰታት መገላጫ በመኖሪያ አካባባያቸው
ይገለፅ እንደሆን በሚል፡፡ ከዚህ ቀጥዬ
የማነሳቸውን የወታደር መኖሪያዎች እና የቤተ መንግሰት ሁኔታን ይመለከታል፡፡ ዘወትር እነዚህን ግቢዎች ባየኋቸው
ቁጥር የሚመጣብኝ አሳብም ስለሆነ ነው፡፡ ለነገሩ የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ አዲስ አይደለም፡፡ የኢኮኖሚክስ ትምህርት መጀመሪያ የሆነው
አንድ በላተኛ፣ አንድ አቅራቢ፣ አንድ ገበያ የሆነው ከአንድ ሰው ጀምሮ፣ ወደ ቤተሰብ እና ሀገር የሚያድገው ሞዴል ተፅህኖሞ ሊሆን
ይችላል፡፡ ነገሮችን ከቀላል በመነሳት ወደ ውስብሰብ ደረጃ ለማጥናት ይረዳል የሚል እምነትም አለኝ፡፡
በወታደራዊ
አገዛዝ ውስጥ የሆኑ ሀገሮች መጨረሻቸው እንዴት እንደሚሆኑ መረዳት የሚፈልግ ሰው በቦሌ መንገድ ከቦሌ ወሎ ሰፈር አደባባይ ከመድረሳችን
በፊት በሚገኘው የመጨረሻ መታጠፊያ ላይ የሚገኘውን የፌዴራል ፖሊስ የ ”ቪ.አይ.ፒ ጥበቃ” ማረፊያ መመልከት ነው፡፡ ይህ ቤት በደርግ
ጊዜ የከፍተኛ ባለስልጣን መኖሪያ እንደነበር የሚነገር ሲሆን፣ ዘመናዊ ቪላ እንደነበር ግን ብዙዎቻችን ምስክር ነን፡፡ ይህ ቪላ
በአሁኑ ወቅት በአይናቸን እያየነው ፈራርሶ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሶዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የብሎኬት አጥር እና በፍፁም ለአካባቢው የማይመጥን የቆርቆሮ
ግንባታ ተደርጎበታል፡፡ ህገወጥ ግንባታ የሚባለው እነሱን አይመለከትም፡፡ በአጠቃላይ ይህ ጊቢ ከነበረበት ደረጃ አሁን ወዳለበት
ደረጃ የወረደው በእኔ እምነት የወታደር መኖሪያ በመደረጉ ነው፡፡ አንዲት ሀገርም በወታደራዊ አስተዳደር ውስጥ ስትወድቅ እንደዚህ
እንደምትወርድ ማሳያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ አሁን በግቢው ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ይህ ቤት ቀደም ሲል ምን ይመስል እንደነበር ስለማያውቁ
ይህ የምሰጠው አስተያየት ሊገርማቸው ይችላል፡፡ እጅግ የሚያሳፍር ነው፡፡ ኪራይ ቤቶች ይህን ቤት በቅጡ መዝግቦ መያዙንም እጠራጠራለሁ፡፡
በእኔ እምነት ይህ ቤት አሁን ባለው የከተማ የሊዝ ዋጋ ቢሸጥ ለአዲስ አበባ ከተማ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች
ደረጃውን የጠበቀ ፅ/ቤት ሊሰራ የሚችል ገንዘብ ሊያስገኝ ይችላል፡፡ በተመሳሳይ በከተማው ውስጥ ከግለሰቦች ተወርሰው ለፖሊስ ማረፊያ
የተደረጉ ቤቶችን መመልከት ተመሳሳይ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ለምንድነው ግን ከመሻሻል ይልቅ ወደኋላ መሄድ የሚቀናን? የእነዚህ
ቤቶች አያያዝ ወታደራዊ መንግሰት ሀገርን እንዴት አድርጎ እንደሚያቆረቁዝ ማሳያ ይመስለኛል፡፡
ከላይ ወታደራዊ መንግሰት መገለጫ
ያልኩትን ሞዴል ለማሳየት የሞከርኩ ሲሆን፡፡ የአንባገነን መንግሰታት ደግሞ መገለጫ ሊሆን ይቸላል ብዬ ያልኩትን ላካፍላችሁ፡፡ በአጋጣሚ
ሆኖ በቀን አንድ ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትራችን ፅ/ቤት በጀርባ መግቢያ በር ማለፌ አይቀርም፡፡ በፕሬዝዳንቱ መኖሪያ ደግሞ በመኪና
ብቻ ሳይሆን በእግር ጉዞ ምክንያትም በሳምንት አንድ ሁለቴ አልፋለሁ፡፡ እነዚህን ጊቢዎች ስትመለከቱ መታዘብ የምትችሉት በጊቢያቸው
ያደገውን ሙጃ ሳር ብቻ ሳይሆን የንፅህና ጉድለቱን ጭምር ነው፡፡ እነዚህ መሪዎቻችን የሚኖሩበት ጊቢ በዚህ ደረጃ የቆሸሸ እንዲሆን
ሲፈቅዱ የሚመሩትን ሀገር እንዴት አድርገው ገነት ሊያደርጉት እንደሚችሉ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ ከእነዚህ ጊቢዎች የሚወጣው ፍሳሽ
መንገድ አቋርጦ የሚሄድ ሲሆን አስፋልቶቹን
እና የእግረኛ መንገዶቹን አበላሽቶ ስንመለከት ማዘናችን የማይቀር ነው፡፡ እርገጠኛ ነኝ መሪዎቹ የሚሄዱባቸው አካባቢዎች ምንጣፍ
እንደሚሆኑ እና ሀገሩ ሁሉ እንደዚሁ እንዲመስላቸው እንደሚፈለግ፡፡ በእነዚህ ጊቢዎች አጥር ተጠግቶ መሄድ ግን አይቻልም፡፡ እሳት
የሚተፋ ጠብመንጃ ያነገቱ ሰዎች ውክቢያ ይከተሎታል፡፡ ይህች ሀገር እነዚህን ጊቢዎች በንፅህና ለመያዝና ለተመልካች ማራኪ ለማድረግ
አቅም የላትም ቅድሚያ የምንሰጠው ሌላ ነገር አለን ሊሉን አይችሉም፡፡ በእኔ እምነት የእነዚህ ትልቅ የሀገር ገፅታ ግንባታ የሚገለፅባቸው
ጊቢዎች በሙጃ ተውጠውና ንፅህናቸው ተጓድሎ ከጊቢው አልፎ ሌሎችን ያበላሹበት ምክንያት በውስጡ ያሉት መሪዎች መገለጫ ነው፡፡
ለንፅፅር እንዲሆን ሁልጊዜ በቴሌቪሽን
የምንመለከተውን የባራክ ኦባማን ቤተመንግሰት ልብ ይሏል፡፡ ማንም መጠራጠር የሌለበት በተግባርም እንዲሁ ግልፅ እና ንፁህ ማራኪ
ነው፡፡ ውጭ ከሚገኘው ክፍት አጥር እስከ ቤቱ ድረስ ያለአንድ ግርዶሽ ፅድት ብሎ ይታያል፡፡ በቅርቡ ሰላም የሚነሱ ጠብመንጃ የታጠቁ
ሰዎች አይታዩም፡፡ ይህ ማለት ጥበቃ አይካሄድም አይደለም፡፡ ለዚህም ፅሁፍ መነሻም የሆነኝ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጊቢ በአንድ ሰው
መደፈሩን (አጥር ዘሎ መግባት) አስመልክቶ የግቢው የፀጥታ ሃላፊ ከስልጣን መልቀቅ ነው፡፡ ለምን እንደ ኢትዮጵያ ቤተመንግሰት ጠባቂዎች
አላስፈራራችሁም በሚል አይደለም፡፡ ወደፊትም ጊቢውን ማጠር እንደመፍተሄ አይወሰድም፡፡ እንደወትሮ ለህዝብ ዕይታ ክፍት ይሆናል ጥበቃው
ግን በስርዓት ይጠናከራል፡፡ የህዝብ መብት በማይነካ መልኩ፡፡ በእኛ ሀገር አንድ ሰው አምልጦ ቢገባ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት
ቀላል ነው፡፡ ግንባሩን በጥይት ይባላል፡፡ በዚህም ምክንያት የቤተ መንግሰት የጥበቃ ኃለፊ የሚወስደው አንድም ኃላፊነት አይኖርም፡፡ ከኃላፊነት ይለቃልም ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ይህ ነገር በእኛ ሀገር ስልጣን እንጂ ተጠያቂነት የሚባል ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው፡፡
ተረኛ ጠበቂው ግን ዘሩ ተጣርቶ ከአንዱ ድርጅት ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ መከራውን ይበላል፡፡ ኦሮሞ ከሆነ ኦነግ፣ አማራ ከሆነ
ግንቦት 7፣ ወዘተ. ….
ልጅ ሆኜ በቢቢሲ የሰማሁት ነገር
ታወሰኝ፡፡ ጋዜጠኛው ዲሞክራሲ የሌለባቸው መንግሰታት ሰር ያሉ ሀገራትን በምን እነለያለን? የሚል ጥያቄ ያቀረበለት አንድ የፖለቲካ ተንተኛ እነዚህ ሀገራት በአብዛኛው “ዲሞክራቲክ”
የሚል ቅጥል አላቸው ሲል ሰምቻለሁ፡፡ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ …….፡፡ ለምሳሌ የእኛን ጉድ ብንመለከት “የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራቲክ
ሪፐብሊክ” እንደሚለው ማለት ነው፡፡ በተግባር ዲሞክራሲም ፌዴራሊዝምም እንዳልሆነው ማለት ነው፡፡ እኔ ደግሞ ዛሬ የምለው ሀገራት
ዲሞክራት መሆናችው እና አለመሆናቸው የሚለየው በቤተመንግሰት ጊቢ አያያዝና ጥበቃ ሰርዓታቸው ነው ቢባልም ሊያስኬድ ይችላል ነው፡፡
ይህን ሞዴል ወደሌላ አፍሪካ ሀገር ሰፋ አድርጎ የሚያየው ቢገኝ በንፅህና የሚጠበቅ ቤተ መንግሰት እና ለህዝብ ግልፅ የሆነ ቤተ
መንግሰት ያላቸው ሀገሮች የተሸለ ዲሞክራቲክ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡ አስተሳሰብ በአካባቢ ከሚኖር ሁኔታ ሊመነጭ ይችላል፡፡ አካባቢውንም እንዲህ
እንዲሆን የሚፈቅዱት ውስጡ የሚገቡት ሰዎች ናቸው፡፡ ለነገሩ ቤተ መንግሰትን ለማስተዳደር ኃለፊነት የሚሰጣቸው ሰዎች የሚመረጡበት
መስፈርት እኮ …….
ሁለት ሺ ሰባት የቤተመንግሰት
ጊቢውንም ሆነ ከዚያ ውጭ ያለውን አስተዳደር የምንሻሽልበት እንዲሆን እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል፡፡
መልካም አዲሰ ዓመት ….መልካም
መስቀል ….መልካም …..
ቸር ይግጠመን!!!!!
No comments:
Post a Comment