የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ ቢሆኑ የሚሰሙት እና የሚያምኑት
በኢቲቪ ወይም በሌላ የመንግሰት መገናኛ ብዙዓን የተላለፈ ነገር ነው፡፡ ሌላው እውነተኛ የመረጃ ምንጫቸው ደግሞ
እንደ ትላንቱ (ጥር 28/2007) ጠቅለይ ሚኒሰትሩ ቀርበው እውነት ነው ብለው የሚነግሯቸውን ነው፡፡ ከዚህ ፍንክች ማለት ቢፈልጉም
አይፈቀድም፡፡ ይህ እውነት ሊሆን የሚችልበት እድል የሚኖረው በሚዲያ በኩል ከፖለቲካ ነፃ የሆነ የመረጃ ምንጭ መሆን ሲችል እና
ጠቅላይ ሚኒስትሩም የሚቀርብላቸውን መረጃ ከሰሩ የሚያጣሩ ቢሆን ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በተነገራቸው ደረጃ
እውነት ነው ያሉትን ለምክር ቤት አቅርበው፤ የራሳቸውን ፉከራ ጨምረው አስፈራርተውን ተሰናብተውናል፡፡ በዚያን ዕለት እውነት አለኝ
ብዬ በምክር ቤት የነበርኩ አንድ ሰው ግን የተረዳሁት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ
የሚመሩን እንዲያውቁ በተፈቀደላቸው መረጃ ልክ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከእውነት ጋር ያጋጫል፤ እኔ እርሳቸውን ብሆን በዚህ
ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትር ከምባል ስልጣን መልቀቅ እመርጣለሁ፡፡ ነጥቦቼን ላስቀም፤
በሁለት ቦታ ሁለት መቶና ሶስት መቶ ሰው ተሰብሰቦ ጉባዔ አካሄደ የሚሉት ማብራሪያ ውሽት ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ
የአንድነት ጠቅላላ ጉበዔ አባላት ቁጥር 320 ከሆኑ ሁለት ቦታ ላይ ሁለት መቶና ሶሰት መቶ ሰው ሊሰበሰብ አይችልም፡፡ ይህ ደግሞ
የፖለቲካ እውቀት ሳይሆን መደበኛ የሂሳብ እውቀት ነው የሚጠይቀው፡፡ ለዚህ ደግሞ መሀንዲሱ ጠቅላይ ሚኒሰትር የሚቸገሩ አይመስለኝም፡፡
ስለዚህ ትክክለኛ ጠቅላላ ጉባዔ ያካሄደው ማን እንደሆነ መርምሮ ውሳኔ መስጠት ያልፈለገው ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ምክንያቱም ከጀርባ
ሆኖ ለሳቸው መረጃ ለምርጫ ቦርድ ደግሞ መመሪያ የሚሰጥ አንድ አካል አለ፡፡ ስለዚህ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አይደለም ስንል ህንፃውን
ሳይሆን በህግ ከተሰጣቸው መተዳደሪያ ይልቅ በሌላ አካል መመሪያ የሚሰሩትን ሰዎች ነው፡፡ ይህን ማለት የሚያሰከስስ ከሆነ ለመከሰስ
ዝግጁ ነኝ፡፡ አሁን እንደገባኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሆኑ መረጃ ለማጣራት ፈቃደኛ ያለመሆኑ ሚስጥር እርሶም ትክክለኛ መረጃ የማግኘት
መብት ያሎት አይመስለኝም፡፡
ሌላው የሚያሳዝነው የተሳሳተ መረጃ ደግሞ የአንድነት አባላት ክፍፍል በውጭ እና በውስጥ የሚመራ የተባለው ነው፡፡
በውጭ የሚመራው ቡድን ውስጥ ደግሞ እኔም አለሁበት፡፡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አንድነትን መደገፋቸው ምንም ክፋት ባይታየንም
እኔ ያለሁበት አመራር ምርጫ መግባት ስንወስን በውጭ ያሉ የፈጠሩትን ጫጫታ፤ በተለይ ደግሞ የምናቀርባቸው እጩዎች ለምርጫ ውድድር
የሚያስፈልጋቸውን ወጭ ለመሸፈን የሚያስችል የግል የፋይናንስ ቁመና እና በሀገር ውስጥ ገንዘብ ለመሰብሰብ ያላቸው አቅም እንደ አንድ
መሰፈርት ያሰቀመጥን መሆኑ ያለመረዳት አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይነቃም የሚለውን ብሂል ከማስታወስ ባለፈ ምንም ማለት አይቻልም፡፡
ይልቁንም በፓርቲው ውስጥ የምንከሰሰው እና ምርጫ ቦርድ ደጅ የሚጠኑት የአንድነት አባላት በኢኮኖሚም ሆነ በትምህርት ለዚህ መሰፈርት
ስለማይመጥኑ ከዕጩነት ተገለልን የሚሉ ይገኙበታል፡፡ ዘወትር የሚቀርብብኝ ክስ ፓርቲውን የተማረና የሀብትም ሊያደርገው ነው የሚለው
ነው፡፡ ይኼ ደግሞ በምንም የውጭ ጥገኝነትን የሚያሳይ አልነበረም፡፡
ለማነኛውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጥር 28 መልዕክታቸው ግልፅ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድን እና ፍርድ ቤትን በተግባር በሚያሳዩት
ሰማቸው ብንጠራቸው ለፍርድ እንደምንቀርብ ማስጠንቀቅ ነው፡፡ ደስ የሚለው የግል አስተያየቴ በሚል ነው የነገሩን፡፡ ይህን የግል
አስተሳሰባቸውን እንደ ቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የምር የሚወስድላቸው ከተገኘ ሰሞኑን ፍትህ ሚኒስትር ክስ መመስረት ይኖርበታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተሰጣቸው መረጃ ትክክል የሚመስለው የፍርድ ቤት ጉዳይ በሚመለከት ላነሳሁት ጥያቄ የሰጡት መልስ ነው፡፡ ነገር
ግን የፍርድ ቤቱ ም/ፕሬዝደንት ምርጫ ቦርድ አስተዳደራዊ ውሳኔ ባልሰጠበት ሁኔታ ክስ መመስረት አይቻልም ሲሉን፣ ምርጫ ቦርድ በፓርቲያችን
ላይ የተለያየ ህገወጥ ውሳኔ እየወሰነ የነበረ ሲሆን ከዚህም አንዱ የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት አልሰጥም፤ የጠቅላላ ጉባዔ ሪፖርት
መርምሮ ውሳኔ በወቅቱ አልሰጥም እያለ የነበረ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ የፍርድ ቤት ውሳኔ የተረዳነው ቁም ነገር ፍርድ ቤት ምርጫ ቦርድ
የሚሰጠውን የመጨረሻ ፖለቲካ ውሳኔ ያውቅ እንደነበረ ነው፡፡ የፖለቲካውን ውሳኔ የሚቃረን መረጃ መሰረት ያደረገ ውሳኔ እንዳይሰጥ
ከለላ እየተደረገ መሆኑ ግልፅ ሆኖዋል አሁን ባለንበት ሁኔታ፡፡ የሚገርመው አሁን ፍርድ ቤት ሲኬድ በአስተዳደራዊ ውሳኔ በፖሊስ
ሰራዊት የተቀማነውን አንድነት አትወክሉም ልንባል እንደምንችል ነው፡፡ ይህ ነው እንግዲ ነፃ ፍርድ ቤት ካላላችሁ ለፍርድ ትቀርባላችሁ
የምንባልበት ስርዓት፡፡
ጠቅላይ ሚኒሰትር ሀይለማሪያም ከመረጃ እጥረት ይሁን አውቀው በድፍረት ሊመልሱት ያልቻሉት “የምርጫ ቦርድ ህገ ወጥ አስተዳደራዊ ውሳኔ ለማሰፈፀም የፖሊስ ሀይል ማስማራትና ቢሮ የመዝረፍ
መብት ማን ነው የሰጠው?” የሚለውን ጥያቄ ነው፡፡ የአንድነት አባላት የሆኑ በበሩ እንዳያልፉ በፖሊሰና ደህንነት ኃይሎች ጥበቃ የሚደረግለት አዲሱ ሹም “የአንድነት ፕሬዝደንት” አቶ ትዕግሰቱ አጉሉ በሚዲያ ቀርቦ ምርጫ ቦረድ ለእኔ
ስጥቶኛል ብሎ የመሰከረውን ሀቅ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ምርጫ ቦርድ ምን ያድርግ ሊሉን አይችሉም፡፡ ምርጫ ቦረድ ኢህአዴግ እንዲያሸንፍ
የታዘዘውን ሁሉ መፈፀም ነው፡፡ በምክር ቤት መቋቋም ነፃነትን የሚያረጋግጥ ቢሆን ኖሮ…… ሌላ ጊዜ በዝርዝር እንመለስበታለን፡፡
ለማነኛውም ጠቅላይ ሚኒስትራችን እውነት ነው ተብሎ በተነገራቸው መረጃ ልክ ለምክር ቤት አባላት እና ለኢትዮጵያ ህዝብ
እውነት ነው ያሉትን አስተላልፈዋል፡፡ ከዚህ ውሳኔ የተረዳሁት እርሳቸው የሚመሩት ካቢኔ በዚህ ጉዳይ ውስጥ ከስረ-መሰረቱ እንዳልተሳተፈ
ነው፡፡ በመጨረሻ በግንባር የተገናኘን እለት የተረዳሁት ይህን ነበር፡፡ ነገር ግን ለማስተካከል አቅም ይኖራቸዋል ብዬ እምነት ነበረኝ፡፡
መረጃ በተሳሳተ ተሰጥቷቸው እንዳይሳሳቱም መረጃ ለመስጠት እና በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር በገቡልኝ ቃል መሰረት እንድንገናኝ ያደረኩት
ሙከራም ያልተሳካው የተለየ መረጃ ማግኘት ስለማይፈልጉ ሳይሆን ስለአልተፈቀደላቸው
ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ፡፡ ለዚህ ነው “ከእውነት ጋር ከሚጋጩ ስልጣን ቢለቁስ?” የሚል ሃሳብ መሰንዘር የፈለኩት፡፡
ቸር ይግጠመን!!!!!!
No comments:
Post a Comment