Sunday, March 29, 2015

ክርክር ሶስት- ግብርና እና ገጠር ልማት


“በ24 ዓመት አሁንም በአዝማሚያ ላይ ነኝ የሚለው ኢህአዴግ ……”
“የ1997 የምርጫ ክርክር ይደገም ……”
ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com; girmaseifu.blogspot.com
ተከራካሪዎች፤
አቶ ተፈራ ደርቤ እና ዶ/ር አብርሃም ተከስተ
አቶ ግርማይ አደራ እና ዐዐዐዐዐ
አቶ ትዕግሰቱ አወሉ እና አቶ ዮሃንስ አሰፋ
አቶ ግዑሽ ገብረሰላሴ እና ትዕግሰቱ ዱባለ
አቶ ጥላሁን እንዳሻው እና ሙላቱ ገመቹ
በመጋቢት 18 እና 19 2007 ለግንቦት ምርጫ የተደረገው “የምረጡኝ ክርክር” የተጀመረው በአቶ ተፈራ ደርበው በተመራው የኢህአዴግ ቡድን በግንባሩ ውስጥ በከባድ ሚዛኑ ህወሃት ተወካዮ ዶክተር አብርሃም ተከሰተ በመታገዝ ነበር የተገኘው፡፡ ተከራካሪዎቹ በኢህአዴግ በተተኪ መስመር የሚገኙ ቢሆኑም እንደ ወትሮ ሁሉ ኢህአዴግ የሚያቀርበው አዲስ ሀሳብ ለሚቀጥለው የስልጣን ዘመን ሊያቀርብ አልቻለም፡፡ እነዚህ የኢህአዴግን ሹሞች ልብ አውልቅ የሆነውን በእውሸት የተሞላውን የቁጥር ጫወታ ይዘው ብቅ ያሉ ሲሆን በዚህ ደረጃ ሊሞግታቸው የሚችል፤ አንድም ተቃዋሚ ነኝ የሚል ለማየት አልቻልንም፡፡ ኢህአዴጎች ከታቃዋሚዎች በላቀ ደረጃ ጎላ ያደረጋቸው የለበሱት ሱፍና የተጫሙት ጫማ ማብቅረቅ ሲሆን ተቃዋሚዎች አሁንም ከጀርባቸው ያስቀመጧቸው አማካሪ ተብዬዎች ምንም ያለመፈየድ ሳይሆን እንቅልፍ ሲያንጎላጃቸው ማየት ኢህአዴግ በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ምን ዓይነት ሰዎችን ወደፊት እያመጣ እና ወደፊትም እንደሚያመጣ አመላካች ነው፡፡ ከተቃዋሚ ጀርባ ለተቀመጡትም ሆነ በፊት መስመር ላሉት ደካማ ተቃዋሚዎች ተጠያቂው ኢህአዴግ እና የዘረጋው ስርዓት መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡
ኢህአደግ ለቀጣይ አምስት ዓምት በስልጣን እንደሚቆይ ቢያውቅም ይህን በትህትና ለገጠሩ ህብረተሰብ ያስተላለፉት ዶክተር አብርሃም ተከሰተ እና ቆጣ ቆጣ ሲሉ የነበሩት አቶ ተፈራ ደርቤ ናቸው፡፡ ለዚህም እንደማስረጃ ያቀረቡልን
·         60 ሺ በላይ የገጠር ልማት ሰራተኞች  እና የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች(በተቃዋሚዎች በትክክል ካድሬዎች ተብለው የተፈረጁት)፤
·         ድህነትን በ1988 ከነበረበት 48 ከመቶ ወደ 24 ከመቶ ዝቅ ማድረጋቸው፤ (በመቶኛ ቀነሰ ቢባልም በቁጥር ግን በ1988 ከነበረው ጋር ተቀራራቢ ነው፡፡)
·         መስኖ እና ሰፈራ በአርብቶ አደሩ አካባቢ ማስፋፋቱ፤
·         2.2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በግል ባለሀብት እየለማ መሆኑ (ይህ መረጃ በቅርቡ እየተነገረ ቢሆንም ኢትዮጵያዊያን በዚህ መስክ የሚያደርጉት ተሳትፎ በግልፅ የሚታይ አይደለም)
·         የመሰረተ ትምህርት እና ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት መስፋፋቱ፤ ወዘተ ሲሆን
በዚህ መነሻ አርሶ አደሩ ሀብት እያከባተ በመሆኑ ወደ ማንፋክቸሪንግ ዘርፍ እንሚገባ አሰረድተውናል፡፡ አህአዴጎች በዛሬው ክርክር የቀደሞ ሰርዓት መክስስ ዘዴያቸውን የገቱ ቢሆንም ተቃዋሚዎችን ማጣጣል በተለይ መድረክ ላይ ለመዝመት ተዘጋጅተው እንደመጡ አቀራረባቸው ያሳብቅ ነበር፡፡ አቶ ተፈራ ደርቤ በተደጋጋሚ ተቃዋሚዎች ከላይ የተዘረዘሩትን የኢህአዴግ ሰኬት በመቃወም መሬት ይሸጥ ይለወጥ በማለት አርሶ አደሩን በማፈናቀል ለጥቂት ባለሀብቶ የቆሙ መሆናቸውን ያረጋገጡበት ክርክር ነበር፡፡ አቶ ተፈራ ደርበው ከመድረክ ጋር ተከራከሩ ተብለው መመሪያ እንደተሰጣቸው በሚያሳብቅ ሁኔታ መድረክን መሬት ይሽጥ? ነው የምትሉት ወይስ ሌላ አማራጭ አላችሁ? እያሉ በተደጋጋሚ አንስተውታል፡፡ አቶ ጥላሁን እንሻውም እንዳሻቸው መልሰውላቸዋል፡፡
ከኢህአዴጉ ተወካይ ዶክተር አብርሃም ተከስተ ያነሱት ሀሳብ ግን ወደ 1997 ክርክር መልሶኛል፡፡ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ አቶ አዲሱ “ግብርና ሴክተር የእድገት ፍንጭ” እያሳየ ነው ሲሉ ለሰጡት አሰተያየት  “ከ14 ዓመት በኋላ ፍንጭ እየታየ ነው አትበሉን” በሚል የሰጣቸውን ምላሽ አሰታውሶኛል፤ በ2007 ክርክር ዶክተር አብርሃም ተከስተ የግብርና ፖሊሲው “የስራ አጥ ቁጥርን የመቀነስ አዝማሚያ” እያሳየ ነው ብለውን ከ24 ዓመት በኋላ አዝማሚያ ላይ እንደሆኑ ነግረውናል፡፡ በእኔ እምነት የግብርና ዘርፉ ይህን ሁሉ ጉልበት ይዞ መቀመጥ አይጠበቅበትም፡፡ በግብርና ዘርፍ ያለው ትርፍ ጉልበት ሊቀበል የሚችል ግብርና ያልሆነ ዘርፍ መፍጠር ያልቻለው ኢህአዴግ ሊከሰስበት የሚገባው ዋና ነጥብ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ 24 ዓመት ያልበቃው ኢህአዴግ ምን ሲሰራ ነበር ተብሎ አይጠየቅም፡፡ ብዙዎቹ ሚኒሰትሮች ከሁለተኛ ደረጃ፣ የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም ድህረ ምረቃ ትምህርት ሲከታተሉ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አንድ አንዶች ለሶሰተኛ ዲግሪ የሚሆን ጊዜ ነበራቸው፡፡ አበበ ገላው እየገዙ ነው የሚለውን ወደጎን እንተወው ከተባለ ማለት ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ያሉትም ማሰታወስ ያሰፈልጋል “እነዚህ ሰዎች ሀገር እየመሩ/እያሰተዳደሩ ሶሰተኛ ዲግሪ መያዛቸው ወይ ሰራቸውን እየሰሩ አይለም፣ ካልሆነም ትምህርቱ ቀሎዋል ማለት ነው” አሰተያየት ሰምቻለሁ፡፡ ቃል በቃል ባይሆንም፡፡
ለማነኛውም ኢህአዴግ መነሻ ሀሳቡንም፣ ማብራሪያውንም ማጠቃለያውን “በሚመጥነው” ደረጃ አቅርቦ ክርክሩን አጠናቆዋል፡፡ ከዚህ የጠነከረ ክርክር ቢያቀርብ ማን ከቁብ ሊቆጥርለት ነው፡፡ በእኔ ግምት ዶክተር አብርሃም ተከስተ በዚህ ክርክር ላይ ባልመጣው ሳይል የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ጠንከር ያለ ቁጥርና ቁጥር ነክ ጥያቄዎች በተለይ ደግሞ የመዋቅራዊ ሽግግር ጥያቄዎች እና ማክሮ ኤኮኖሚክ ነክ የሆኑ ለምሳሌ በውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ በግብርና ሴክተር የመሪነት ሚና ላይ ዝርዝር ሀሳቦች ለመመለስ በክርክሩ ላይ የተገኘ ይመስል ነበር፡፡ ዶክተር አብርሃም ተከስተ የክርክር ጊዜውን ለመግደል ዘና ብሎ ሲመልስ ላስተዋለ በእግር ኳስ ጫወታ እየመራ ያለ ቡድን ጎል ጠባቂ ጊዜ ሲያባክን የሚያሳየውን ባህሪ የሚያሰታውስ ነው፡፡
ለማነኛውም አቶ ተፈራ ደርቤ ያቀረቡት የመሬት ጉዳይ በህገ መንግሰት ውስጥ መግባቱ እና አሁን የሚከተሉት የመሬት ፖሊሲ መሰረቱ ኤኮኖሚያዊ ነው ብለው ቢዋሹም፣ ኢህአዴግ መሰረቴ ነው የሚለውን አርሶ አደር ለመቆጣጠር እንዲችል የተቀመጠ ፖለቲካዊ መሰረትነቱ መቼም ክዶት የማያወቅው ታውቆ ያደረ ጉዳይ መሆኑን የሚያስታውሳቸው አላገኙም፡፡ የዶክተር አብርሃም ተከሰተ ትህትና የተሞላበት የምረጡን ጥያቄም አማላይ ነበር፡፡

ኢፍዴአግ  በአቶ ግርማይ አደራ በሚባሉ ሰው የተወከለ ሲሆን በረዳትነት የተገኘውን ለማወቅ እድል አላገኘንም፡፡ አቶ ግርማይ ጊዜው አይበቃም ቢሉም ሲጀምሩ ቀስ ብለው ተዝናንተው ሲጨርሱም ሁለት ደቂቃ አሰቀርተው ሲያጣቃልሉም ለጊዜ አጠቃቀም ምንም ግድ ሳይሰጣቸው ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ከእኝ ግለሰብ ልይዝላቸው የቻልኩት ነጥብ  መሬት ለኢትዮጵያን የዜግነት፣ የሀገር ባለቤትነት፣ የነፃነት መገለጫ ነው የሚሉት እና የማዳበሪያ ዕዳ ለመክፈል አዲስ አባባ ለልመና የሚመጡ አርሶ አደሮች መኖራቸውን ያስታወሱን መሆኑን ነው፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ በፅሁፍ የያዘውን በቅጡ የማያነብ፣ በቂ አይደለም ብሎ ካለው ጊዜ ውስጥ በመግቢያና በመውጫ ሠዓት ማባከን ምን ግምት እንደሚያሰጥ ተከራካሪው ያሰቡበት አይመስለም፡፡ ለማነኛውም ኢህአዴግ አቻውን አግኝቶዋል ማለት ይቻላል፡፡ በቃ ኢህአዴግ የሚመጥነው እንደ አቶ ግርማይ አደራ ያሉ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ ምርጫቸው ነው እና ማክበር አለብን፡፡ አቶ ግርማይ አርማው ጋሻና ጦር የሆነ እድር ቢኖራቸው ችግር የለኝም ነገር ግን እርሳቸውም ሆነ የእርሳቸው ፓርቲ በሚሰጡት አመራር በማጠቃለያ እንደነገሩን በምግብ እህል ራሷን የቻለች ኢትዮጵጰያ ሊዚያውም ተርፎዋት ኤክስፖርት የምታደርግ ሀገር አይሰሩልንም፡፡ ለኢትዮጵያዊ የቀረበለት ከዝንጀሮ ቆንጆ መረጣ ነው፡፡
“ድንኩ አንድነት” እንደ ተለመደው በትዕግስቱ አወሉ የተወከለ ሲሆን በረዳትነት የተመደበለት ደግሞ አቶ ዮሐንስ አሰፋ ነው፡፡ አቶ ትዕግሰቱ በቴሌቪዥን በክርክር የሰንብት ክርክሩን አድርጎ ሄዶዋል፡፡ እኛም ተገላገልን፡፡ ባለፈው ድንኩ አንድነት የአንድነት ፓርቲ ውስጥ አባል ያልሆነ ሰው ለክርክር ቀረበ ብለን ትንሽ ተንጫጭተን ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ በረዳትነት የመጣው አቶ ዮሃንስ አሰፋው ለጫጫታ መነሻ የሚሆን አወዛጋቢ ግለሰብ ነው፡፡ ዮሐንስ በወረዳ 24 ውስጥ፣ ገዢውን ፓርቲ ወክሎ ወረዳውን ሲያምሰ የነበረ ነው፡፡ የሴራው ማጠንጠኛም አስራት አብርሃም ነበር፡፡ ፓርቲው አምኖበት በከፍተኛ ሃላፊነት ላይ ያስቀመጠውን ሰው የወያኔ ተላላኪ ነው እያለ ውንጀላ ሲያደርግ፣ በአስራት አብርሃም ደረጃ አሰተዋጽኦ የሚያደርግ ከየትም ቢመጣ ችግር እንደሌለብን አሰርደቼው ነበር፡፡ ለነገሩ ፓርቲውን ለመፍረስ ከሚያሴሩት ጋር በግልፅ እንደሚሰራ እያወቅን በዝምታ ያለፍነው የውስጥ አርበኛ ነው፡፡ አሁን ደግሞ በአሰራት አብርሃም ቦታ ወረዳ 24 ዕጩ ሆኖ የቀረበ ሲሆን ለትዕግሱቱ አወሉ ቡድን በቂ አማካሪ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ከዚህ የተሻለ ከትዕግሱቱ ጎን ማግኘት አጉል ነው የሚሆነው፡፡ ትዕግስቱም የልኩን አማካሪ ኢህአዴግም የሚመጥነውን ተቃዋሚ አግኝተዋል፡፡
ትዕግሰቱ የአንድነትን የፖሊሲ አማራጭም ሆነ ዝርዝር የኢህአዴግን የአፈፃፀም ክፍተት በተሟላ ይዞ ሊቀርብ እንደማይችል ማንም ያውቃል፡፡ በድፍረት ግን “የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ በአሰቸጋሪ ሁኔታም ቢሆን አንድነትን ምረጡ” የሚል ቃል እንዴት ሊወጣው እንደቻለ አልገባኝም፡፡ ከሁሉም ያስገረመኝ ደግሞ “ኢህአዴግ የመሬት ፖሊሲ የምቀይረው በመቃብሬ ላይ ነው” ይላል በሚል የሰጠው አስተያየት ነው፡፡ ኢህአዴግ ለስልጣኑ ዋልታና ማገር ያደረገውን የመሬት ፖሊሲ በመቃብሬ አለ የሚለው ትዕግሰቱ አወሉ እልህ ምላጭ ያስውጣል በሚል መፈክር ከራሱ ሌላ አንድ ሌላ ድምፅ ለማግኘት ያልቻለበትን አንድነት ፓርቲን ከምርጫ ቦርድ እና ከገዢው ፓርቲ ጋር እርሱ በሚያውቀው መስመር ተመሳጥሮ ድንክ ያደረገ ግለሰብ፣ ታንክና ባንክ ለማዘዝ የሚያሰችል ስልጣን የሚያስገኝን የመሬት ፖሊሲ በመቃብሬ ላይ ቢባል ምን እንደሚያስገርም አልገባኝም፡፡ ትዕግሰቱ አወሉ ታንክና ባንክ የሚያዝ መንግስት ቢሆን ብዬ ሳሰበው ዘገነነኝ፡፡
አቶ ትዕግሰቱ አወለ በክርክሮች ሁሉ ቀና ብሎ የቴሌቪዥን ካሜራ ለማየት ማፈሩ ተገቢ ሆኖ ባገኘውም የሚያፍር ከሆነ ለምን ቴሌቪዥን ላይ እንደሚመጣ ነው የማይገባኝ፡፡ አንድነት አማራጭ እንዳለው ሰንድ ማሳየት ይቻላል ያለው ትዕግሰቱ የአንድነትን ፕሮግራመ በቅጡ ማንበብና መዘጋጀት ሳይችል (የምርጫ ማኒፌስቶ እርሱ ሊያገኘው አይችልም፣ ቢሮ ዕቃ በጉልበት ሲዘርፍ በአባላት ጭንቅላት የሚገኝ እውቀት ግን በእርሱ እጅ አልገባም) የዛሬ አምስት ዓመት የተዘጋጀውን ሰትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ለዚያውም በመግቢያ ላይ የተፃፈውን ሰለ ዜጎች ሰደት የሚያወራውን ክፍል ለግብርና ክርክር ይዞ ሲቀርብ፣ “የድንኩ አንድነት” ተወካይ መሪ አቶ ትዕግሰቱ ለመዘጋጀት ፈተና የሆነበት ምን ያህል የውስጥ ሰላም አጥቶ እንደሚገኝ የሚያሳይ ነው፡፡ አንድነት በየትም ቦታ ዜጎች ወደ ከተማ መምጣት ችግር ነው ብሎ አያውቅም፡፡ ይልቁንም ችግር ከሆነ እንደ ችግር የሚያየው ዜጎች ከመሬት ጋር ተጣብቀው በገጠር እንዲኖሩ መደረጋቸወ ነው፡፡
ሌላው ያስገረመኝ የጥርሶቹ ማለቅ ሲሆን (መለስ መላጣ ማለት ይቻላል፣ መንካት ግን አይቻልም ባለው መሰረት)፣ እንዴት ነው አሁን ያለው የገንዘብ ፍሰት ለዚህ የሚሆን እንጥፍጣፊ የለውም ወይ? የሚል ጥያቄ ጭሮብኛል፡፡ ከዚህ በፊት ጥርሳቸውን ያስተከሉ መሪዎች በፓርቲው ገንዘብ ነው እያለ እርሱ ሲያወራ ስለነበር ነው፡፡ ለማነኛውም “ሞያ በልብ ነው አንድነትን ምረጡ” ያለው ትዕግሰቱ በግሌ የወረዳ 8 ነዋሪ ከራሱ በስተቀር አንድም ድምፅ እንዳያገኝ በማድረግ እንዲያዋርደው በማክበር ጥሪ አቀርባለሁ፡፡ በሰፈሩ ያሉት እድሮችና የትዕግሱ የማሪያም ፅዋ ማህበርም ይህን እንዲያስተባብሩ እና ትዕግሰቱ ከራሱ በስተቀር አንድም ድምፅ እንዳያገኝ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን የኢህአዴግ ኮካዎች ማህበራዊ ማግለል ወንጀል ነው ይሉታል፡፡ በትዕግስቱ ላይ ማህበራዊ ማግለል ወንጀል የሚሆንበት ህግ ካለ ለመማር ዝግጁ ነኝ፡፡ መቼም ትዕግሰቱን በመወከል ታዛቢ ይኖራል ብዬም አላምንም፡፡ በተጨማሪ የአንድነት ደጋፊዎችም ትዕግሰቱ ከራሱ ሌላ አንድም ሌላ ድምፅ እንዳያገኝ ጠንክረው መስራት ይኖርባቸኋል፡፡ ይህን ሳናደርግ ብንቀር ሌሎች ትዕግሰቱዎች ለዚህች ሀገር እየጋበዝን መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ አንድነት ዋንጫ የሚያነሳው ትዕግሰቱና የትዕግሰቱ ቡድን ድምፅ ሲያገኝ ሳይሆን እነርሱ ተገቢውን ውርደት ሲከናነቡ ነው፡፡
ኢድአን አቶ ግዑሽ  ገ/ሥለሴ እና ትዕግስቱ ዱባለ  በተባሉ አባላቱ ተወክሎ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ አቶ ግዑሽ ገ/ሰላሴ በ2002 ምርጫ ወቅት መድረክ ሞቅ ያለ የምርጫ ስራ ላይ እያለ “ኢድአን ከምርጫ ወጥቶዋል” በሚል መድረክን ያመሱ ግለሰብ ናቸው፡፡ በምርጫ ወቅት የገዢው ፓርቲ ተቃዋሚዎችን የሚያዳክምበት መሳሪያ ናቸው፡፡ ከምርጫ በኋላ እዚህ ግባ በሚባል ፖለቲካ ውስጥ ጉልዕ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አይታዩም፡፡ አቶ ግዑሽ ካቀረቡት ክርክር ነጥብ አድርጌ የያዝኩላቸው “ … እሰከ መገንጠል መብት የሰጠ መንግሰት፣ ለአርሶ አደሩ መሬትን እሰከ መሸጥ ለምን መስጠት ፈራ” የሚለው ነው፡፡ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት እሰከ መገንጠል ስለተሰጠ የተገነጠለ የለም በሚል የሚከራከረው ኢህአዴግ አርሶ አደሩ እሰከ መሸጥ የሚደርስ መብት ቢያገኝ በመሬቱ ተጠቃሚ ከሆነ አይሸጠውም የሚል መርዕ እንዴት ሊገባው አልቻለም የሚል ነው፡፡ ተዋዋሚዎች ትንሽ ከሚሏት የክርክር ደቂቃ ሁለት ደቂቃ ያገኘው የአቶ ግዑሽ ረዳት አቶ ትዕግሰቱ ዱባለ ያገኛትን ሁለት ደቂቃ በቅጡ የሚረባ ነገር ሳይናገር ላብ በላብ ሆኖ ወጥቶዋል፡፡ ከእንቅልፉ ድባብ ተቀስቅሶ በመናገሩ የተቸገረ ነው የሚመስለው፡፡ ኢህአዴግ የመጨሻውን ማጠቃለያ መስጠቱን ዘንግቶ ለኢህአዴግ ጥያቄም አቅርቧል፡፡ ለማነኛውም በማጭድ ምልክት ዘመናዊ የግብርና መሳሪያ በድጎማ ማቅረብ አማራጭ አድርጎ ያቀረበልን ኢድአን ከቁም ነገር የሚቆጠር አማራጭ ነው ብለን ልንወሰደው እንቸገራለን፡፡ እንኳን ሌሎች እንዲመርጧቸው ልንደግፋቸው አይደለም የራሳቸው “ከተመረጥን” የሚለው ድምፅ ለመመረጥ እንዳልተዘጋጁ የሚያሳጣ ነው፡፡
መድረክ ተወክሎ የገባው በአቶ ጥላሁን እንዳሻው እና በአቶ ሙላቱ ገመቹ በሚባሉ አባላት ሲሆን፡፡ ኢህአዴግም ቢሆን በዋነኝነት ሊከራከረው የገባው ከላይ እንደገለፅኩት ከመድረክ ጋር ብቻ እንደሆነ ያስታውቅ ነበር፡፡ መድረክ በመጀመሪያ ሰድስት ደቂቃ አንዱን ደቂቃ ጊዜው ትንሽ ነው በሚል ጉንጭ አልፋ ክርክር ጊዜ ያባከነ ሲሆን፤ በተጨማሪ መልስ በሌላቸው ህገመንግሰታዊ ድንጋጌዎችና ትርጉም ጊዜውን እንዳባከኑት ይሰማኛል፡፡ በእኔ ግምት በመሃል የተቆረጠ በሚመስል ሁኔታ አምሰት ደቂቃ የሚሞላ ሀሳብ አልሰማንም፡፡ ኢቲቪ ኢህአዴግን የመከላከል መብቱን ተጠቅሞ የቆረጠው ሃሳብ እንዳለ መገመት ይቻላል፡፡ መድረክ በቀጣዩ በነበረውን ዘጠኝ ደቂቃም ቢሆን ኢህአዴግ ላቀረበለት ጥያቄ መልስ በመስጠት፣ ለምሳሌ በሚል የአቶ ጥላሁን እንዳሻው ትውልድ አቅራቢያ ቦታዎች ላይ የሚገኙ የመሬት መፈናቀልና የመሰረተ ልማት እጥረትን በመዘርዘር ለክርክሩ የሚመጥን ነበር ለማለት የሚያስቸገር ሃሳብ ሲያቀርቡ ነበር፡፡ በ2002 አቶ ጥላሁን እንዳሻው በተመሳሳይ ርዕስ ተከራካሪ የነበሩ ሲሆን ይህን ልምድ ይዘው በተሻለ የመቅረብ እድሉ ቢኖራቸውም ሊጠቀሙበት አልቻሉም፡፡ ከመድረክ ክርክር ነጥብ የሚወሰድ ከሆነ በልማት ሰራተኛ ስም የተሰገሰጉት ካድሬዎች ጉዳይ ሲሆን ኢህአዴጎች ይህን ከሰራተኞቹ ጋር ለማጋጨት ሊጠቀሙበት የሞከሩ ቢሆንም በልማት ሰራተኛ ሰም በገጠር የሚንከራተቱት ሰራተኞች ይህን ተጨማሪ ያለፍላጎታቸው የሚሰጣቸው ሰራ እንደማይወዱት ለሚያውቅ የኢህአዴግ መንገድ የሚሳካ አይመስለኝም፡፡ በክርክሩ የመጨረሻ ተከራካሪ መሆን ያለውን ከፍተኛ የማጥቃት እድል በማያሰፈልግ ሁኔታ ከረዳታቸው ጋር የተካፈሉት አቶ ጥላሁን ረዳታቸውም ምንም አዲስ ነገር ሳይነግሩን ክርክሩም እንዲያበቃ አደርገውታል፡፡
በእኔ እምነት ኢህአዴግ አሁንም ቢሆን መንግሰት ሆኖ ያከናወናቸውን ስራዎች ይህን ማድረግ የማይችሉትን ተቃዋሚዎች መክሰሻ አድርጎ ለማቅረብ ሲሞክር ከመስማት የበለጠ አሳፋሪ ነገር የለም፡፡ ይህ ማለት ግን ተቃዋሚዎች በያዘው ስልጣን ሊያከናውን ያልቻለውን፣ በተለይ ደግሞ ባለፈው አምስት ዓመት በግብርና ዘርፍ አሳካዋለሁ ብሎ ያላሳካቸውን ነጥቦች አንሰተው ደካማ መሆኑን ማሳየት አይችሉም ማለት አይደለም፡፡ ኢህአዴግ አሁን የሚሞግተን የግብርና ፖሊሲና ስትራቴጂ፤
·         ባለፉት 24 ዓመታት ይህችን ሀገር በምግብ እራሷን እንድትችል ባለማድረጉ የሚከሰሰበት ዋነኛ ነጥብ ነው፡፡ በሃያ አራት ዓመት አሁንም አዝማሚየ በሚባል ሁኔታ መሆናችን ተቀባይነት የለውም፤
·         በኢትዮጵያ ሀገራችን በገጠር የሚኖረው ህዝብ ባለፉት 24 ዓመታት ከነበረበት 85 ከመቶ ወደ 83 በመቶ ብቻ ነው ዝቅ ሊል የቻለው፡፡ ይህ ደግሞ በአፍሪካ ደረጃ ከተሜነት 50 ከመቶ በላይ በደረሰበት ወቅት እጅግ አሳፋሪ ሲሆን፤ ይህን እንደ ነጥብ አንሰቶ የሚሞግት ያለመኖሩ ከዚያ ይልቅ የገጠሩ ህዝብ ወደ ከተማ እየፈለሰ ነው የሚል ቅሬታ የሚያሰሙ ተቃዋሚዎች መኖራቸው የሚያሳዝን ነው፤
·         የከተሜነት ያለመስፋፋት፣ ዜጎች በገጠር ከመሬት ጋር ተጣብቀው እንዲኖሩ እያደረገ ያለው ደግሞ፤ ኢህአዴግ በውሸት ኤኮኖሚያዊ ምክንያት የሚለው ነገር ግን ፖለቲካው ምክንያት የሆነው መሬትን ህገመንግሰት ውስጥ መደንቀሩ ነው፤ ይህን ፖለቲካዊ የሆነ ጉዳይ ኤኮኖሚያዊ ነው ብለው ምንአልባት ከፓርቲው አቋም ውጭ የግብርና ሚኒሰትሩ ሃሳብ ሲሰነዝሩ የሚሞግታቸው አላገኙም፤
·         ኢህአዴግ መሬት መሸጥ መለወጥ የሚለውን ሃሳብ ሲያነሳ መሬት የሚገዙ ጥቂት የሚላቸው ዜጎች መሬቱን የሚገዙት ምርት ለማምረትና ለማትረፍ በዚህም ሀገራችንን በምግብ እህል ራሰን ከመቻል አልፎ ኤክሰፖርት ለማድረግ መሆኑ ቀርቶ ለቀብራቸው መሬት የሚገዙ ያሰመስለዋል፡፡ መሬቱን ሸጦ የሚፈናቀል አርሶ አደር ደግሞ በሌሎች አገልግሎት ዘርፍ የማይገባ፣ ከመሬት ጋር ብቻ ተጣብቆ እንዲኖር የተፈረደበት ያሰመስልብናል፡፡
ባጠቃላይ በእኔ እምነት የ1997 የግብር እና የገጠር ልማት ስትራቴጂ ክርክር በድጋሚ ይቅረብልን ብዬ ማጠቃለል መርጫለሁ!!!

ቸር ይግጠመን!!!!!!!

Sunday, March 22, 2015

ምረጫ ክርክር 2፡ “የፌዴራል ስርዓተ በኢትዮጵያ”-የግል ዕይታ

ተከራካሪዎች፤
·         ካሳ ተክለብርሃን እና አባዱላ ገመዳ                           ኢህአዴግ
·         በኃይሉ ሸመክት እና ደረጀ ጣሰው                         “ድንኩ አንድነት”
·         ተሾመ ወልደሐዋሪያት  እና ሰማቸውን ያልያዝኩት አዛውንት            መኢብን
·         ኤርሚያስ ባልከው እና ሰሙን ያልያዝኩት ወጣት                ኢዴፓ
·         አበባው መሃሪ እና አንድ ሰማቸውን ያልያዝኩት አዛውንት         መኢአድ                 
የሁለት ሺ ሰባት ምርጫ ክርክር ሁለተኛ ክፍል “የፌዴራል ስርዓተ በኢትዮጵያ” በሚል ነው፡፡ በዚህ ክርክር ዙሪያ ስናወራ አንድ ወዳጄ አንድ ቀልድ ቢጤ ነገረኝ፡፡ በዚሁ ቀልድ ብጀምረው ወደድኩ፡፡ በቅርቡ የእንግሊዝ፣ የአሜሪካ እና የኢትዮጵያ ምርጫ አስፈሚዎች ለልምድ ልውውጥ ተገናኝተው ነበር አሉ፡፡ የአንግሊዙ ተወካይ በቅድሚያ አሁን እኛ ምርጫ በብቃት አካሂደን በዚያው እለት ምርጫ ውጤት መግለፅ ችለናል ብለው የደረሱበትን ደረጃ ሲናገሩ፤ የአሜሪካው ተወካይ ደግሞ እኛ ደግሞ ውጤቱን በቀጥታ ማሰራጨት ችለናል ብለው ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ተወካይ (ፕሮፌሰር መርጊያ በቃና ይሁኑ አቶ ነጋ ዱፊሳ አልተገለፀም) ይህ ምን ያስገርማል ብለው በኩራት በእኛ ሀገር ውጤቱ ከምርጫ በፊት ይታወቃል ብለው አረፉት፡፡ የዘንድሮ ምርጫ የዋንጫው ባለቤት የታወቀበት ውድድር መሆኑ ከግንዛቤ እንዲያዝ እኛም እንደ ህዘብ እንደተረዳን ቀልዱ ያሰረዳል ብዬ አምናለሁ፡፡
በዛሬው ክርክር በእውነቱ ያዘንኩት በክርክሩ ፓርቲያችውን ወክለው ለቀረቡት ለአቶ ካሳ ተክለ ብርሃን እና ለአቶ አባዱላ ገመዳ ነው፡፡ በረጅም ዓመት በትጥቅ ትግል እንዲሁመ 24 ዓመት በመንግሰትነት የፖለቲካ አመራር ሲሰጡ የነበሩ ሰዎች የዚህ ሁሉ “ድካም” እና መስዋዕትነት ውጤት ዛሬ ከጎናቸው ሆነው በደህንነት መስሪያ ቤት ፈቃድ ያገኙ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ የደረሰበትን የፖለቲካ ደረጃ የማይመጥኑ የፓርቲ ወኪል ነን የሚሉ ሰዎች ጋር ያደረጉት ክርከር ነው፡፡ ማለት የፈለኩት ኢህአዴግ የዚህን ያህል የፖለቲካ ልምድ አለኝ እያለ ልኩ የዚህን ያህል የወረደ እንዲሆን በአንድነት እና በመኢአድ ፓርቲ ላይ ያደረገው ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ እንደ እነርሱ አባባል ለሰማዕታት ክብር ለመስጠት የሚያስችል ደረጃ ዲሞክራሲውን ሊያደርሱት አልተቻላቸውም፡፡ ህወሃት ትግል ከጀመረበት ቢቆጠር ከአርባ ዓመት በላይ ተደክሞ የተደረሰው እዚህ መሆኑ አሳፋሪ ነው የሚል የግል እይታ አለኝ፡፡
ለማነኛውም ወደ ክርክሩ ዝርዝር ስንገባ ካለፈው በተቃራኒ መጥፎውን የክርክር ጀማሪነት የወሰዱት “ድንኩን አንድነት” ወክለው የተገኙት አንድነትን በማፍረስ ቀንደኛ ተዋናይ የነበረው ደረጀ ጣሰው እና በኃይሉ ሽመክት የሚባል አንድነት ውስጥ የማላውቀው ወጣት ነው፡፡ በኃይሉ ሽመክትን በእውነት የት ወረዳ የተደራጃ አባል እንደነበር አላውቅም፡፡ ለማነኛውም ሁሉንም የማወቅ ፍላጎትም ሁኔታም የለኝም፡፡ እርግጡ ግን ለክርክር ካዘጋጀናቸው ሰዎች ውስጥ አልነበረም፡፡ አንድነትን ወክለው እንዲከራከሩ በዝገጅት ላይ የነበሩት የአንድነትን ፕሮግራም ጠንቅቆ ማወቅ የግድ ስለሚል ነው፡፡ ለዚህ ዋነኛው ማሳያ “የኮሚሽነር ጄነራል” ትዕግስቱ አወሉ “ድንኩ አንድነት” ፓርቲ ፕሮግራም ለውጥ ካለደረገ በስተቀር የአንድነት የፌዴራሊዝም አማራጭ “ጂኦግራፊ መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝም” የሚል አይደለም፡፡ በኃይሉ ስለ ፌዴራሊዝም ጎግል ሲያደረግ ስራ በዝቶበት የአንድነትን የፌዴራሊዝም ግልፅ አማራጭ ለማቅረብ አልቻላም፡፡ የበሀይሉን ለአንድነት ፓርቲ እንግዳነት የሚያሳብቀው ሌላው አንድነት “ሀብታሙ ሰዩም” የሚባል እሰረኛ የሌለው መሆኑ ነው፡፡ ደረጀ ጣሰው ከዚህ አንፃር  ጥቁር እንግዳውን በሀይሉ ሸመክትን በመራጃ ማቀበል እንዲረዳው የሚጠበቅ አይመስለኝም፡፡ በክርክር አብሮት ስለተገኘ ምሽት ክለብ ወሰዶ እስክስታ/ዳንስ ሊጋብዘው ይችል ይሆናል፡፡ ሌላው የበሀይሉን እንግዳነት የሚያሳየው “ራዕያችን ዋንጫ ነው” የሚለው የቃላት ግድፈት ዋንጫውን እንደ ምርጫ ምልክት የመረጥን ሰዎች በዋንጫው ዙሪያ ያደረግነውን ዝርዝር ውይይት ስለአላገኙት ዋንጫው ከምርጫ ውድድር ምልክትነት አልፎ “ራዕይ” እሰከመሆን የሚደርስ የቃላት ግድፈት ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡ ለማነኛም በኃይሉ ከፎረም የመጣ፣ በአንድነት ወጣቶች ውስጥ ራሱን የደበቀ የቀበሮ ባሕታዊ መሰለኝ፤ ለማነኛውም በሀይሉ ሊማር የሚችል ወጣት እንደሆነ ለመገንዘብ አልተቸገርኩም፡፡ አንድነትን ወክሎ ለክርክር ይመጥናል የሚባል ተከራካሪ አይደለም፡፡ ለ”ድንኩ አንድነት” ግን ከበቂ በላይ ነው፡፡ በሀይሉ የአንድነት አባል ከሆነ ወረዳውን እና የወርሃዊ ክፍያ የከፈለበትን ፌስ ቡክ ላይ ቢለጥፈው “ከፎረም” የመጣ ከሚለው ጥርጣሬ እተርፋለሁ፡፡
መኢብን በእርግጥ የመሳፍንት/መስፍን መኢብን ነው ወይ? ያስብላል፡፡ እኔ መሳፍንት/መስፍን የሚባል ግለሰብ የሚመራው ፓርቲ በሀገር ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚረዱ አባላት አሉ ብዬ አላምንም ነበር፡፡ ይህን ለማለት የሚያስደፍረኝ በግሉ የፈለገውን ከማለትና ከማድረግ አልፎ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በጠራራ ፀሃይ ከገዢዎች ጎን ተሰልፎ ሲዘልፍ ተው የሚለው አባል በፓርቲው ውስጥ መኖር አለበት ብዬ ስለማምን ነው፡፡ ለማነኛውም የመኢብን ተወካዮች በተደራጀ መልክም ባይሆን በዚህች ሀገር ያለውን ፌዴራሊዝም ዕፀፆች ለማሳየት ሙከራ አድርገዋል፡፡ ተከፋፍሎ የተሰጣቸው 19 ደቂቃ አንሶዋል ቢሉም በሁሉም ክፍሎች ግምሻ ላይ ሃሰብ አጥሮዋቸው ፈተና ውስጥ ሲገቡ ታዝበናል፡፡ ለማነኛውም ኢህአዴግ ከ24 ዓመት ወዲህ ያመጣው ኦሮሞ፣ ትግሬም፣ ሀዲያም፣ ወዘተ የሌለ መሆኑን በመግለፅ ይህ የኢህአዴግ የአፋዊ ፌዴራሊዝም ተቀባይነት የለውም ማለታቸው እውነት ነው፡፡ ይህ ግን በምንም መመዘኛ መኢብን የሚባል ፓርቲ ለምርጫ መቅረብ ያለበት ፓርቲ ነው ማለቴ አይደለም፡፡ ህዝብ ወክሎ ለምርጫ ለመቅረብ የሚያስችል የፓርቲ አቋም ያለው ፓርቲ ነው ብዬ ከምር ልወስደው አልችልም፡፡ የመሳፍንት ዓይነት ሰው የሚመራው ፓርቲ የፈለገ ጠንካራ ሰው ውስጡ ቢኖር የትም ሊደርስ አይችልም፡፡ እነዚህም ለክርክር የመጡ ሰዎች መሳፍንትን ያላስታገሱ እንኳን ሀገር፣ ቀበሌ ማስተዳደር የሚችሉ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ መሳፍንት የሚመጥነው ኢህአዴግ ስለሆነ ከተቀበሉት ፎርም ሞልቶ እዚያው ቢገባ የሚል አስተያየት መሰጠት ስህተት አይመሰለኝም፡፡
በዚህ ክርክር እንደ ኢዴፓ ውጤታማ ክርክር ለመከራከር የሚያስችል መረጃ ያለው ፓርቲ በግሌ አልገምትም ነበር፡፡ ለዚህ አስተያየቴ መነሻ  የኢዴፓው ልደቱ አያሌው መፅሃፍ ለማጣቀሸ የሚሆን እንደሆነ ስለማውቅ ነው፡፡ ለክርክሩ የቀረቡት ወጣቶች ግን ከልምድም ሆነ ከዝግጅት ማነስ አዚህ ግባ የሚባል ክርክር ማድረግና ነጥብ ማስቆጠር አልቻሉም፡፡ የልደቱን መፅሃፍ እንደ ማጣቀሻ ሳይሆን እንደ ቅዱስ መፅሃፍ ነው የወዱት፡፡ አሁን በኢዴፓ ውስጥ ፊቱን እየለመድነው የመጣነው ወጣት ኤርሚያስ ባልከው ያባከናቸውን ጊዜዎች ለጓደኛው/ከይቅርታ ጋር ሰሙን አልያዝኩትም/ ቢተውለት የተሻለ ይሆን ነበር ብዬ እገምታለሁ፡፡ ለማነኛውም ኢህአዴጎች ለኢዴፓ ባላቸው ቅን ልቦና እና አሁን ለክርክር የቀረቡት ሰዎች ተናዳፊ ያለመሆን ካልሆነ በስተቀር ኤርሚያስ ባልከው በተደጋጋሚ የኦሮሚያ መገንጠል በሚል በቀጥታ ከልደቱ መፅሃፍ የወሰደውን ሃሰብ እንደወረዳ እያቀረበ ለጥቃት እራሱን ሲያጋልጥ ነበር፡፡ ሰሙን ያልያዝኩት የኢዴፓ ተከራካሪ ህገመንግሰት ለማሻሻል አስቸጋሪ መሆኑ ግልፅ ሆኖ እያለ አሁን ኢዴፓ ባቀረበው ዕጩም ሆነ በሌላ መስመር ሊያሳካው የማይችለውን የህገ መንግሰት ማሻሻል ጉዳይ አንስቶ ጊዜ ሲያባክን ነበር፡፡ የዚህ ክርክር ፋይዳ የሚኖረው ለምርጫ ሳይሆን ለእውቀት በሚደረግ ክርክር ቢሆን ነበር፡፡ የኢዴፓው ተከራካሪ ሊብራል ዲሞክራሲ በሚከተሉ ሀገሮች ያለ ፌዴራሊዝም ተፈትኖ የወደቀ በሚል በኢህአዴግ የቀረበውን መሰረተ ቢስ ክስ ተፈትኖ የወደቀ ሳይሆን ተፈትኖ ያለፈ መሆኑ በደንብ ለማስረዳት ሞክሮዋል፡፡ ፈተና ያላለፈው እንኳን 70 ዓመት 24 ዓመት በቅጡ መቆም ያቃተወ ግራ ዘመም ሀገሮች ውስጥ ያለው ፌዴራሊዝም በተለይም አምሳያ የሌለው አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን ለዓለም ያበረከትነው ብለው የተመፃደቁበት ፌዴራሊዝም በእግሩ መቆም ያለመቻሉ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ፌዴራሊዝም ልዩ እያሉ የሚያሞካሹ ምሁር ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ አቶ ካሳ ተክለብርሃንም ሆነ ድርጅታቸው ኢሀአዴግ ሁሌም የሚያሰቡትን የሚነግሯቸው ምሁራን ስለሚመርጡ ነው፡፡
በኢዴፓ እምነት አሁን ያሉት ክልሎች ስልጣን ያላቸው ፌዴራል መንግሰት አባላት ሳይሆኑ፣ የሰራ ድልድል የተደረገላቸው ምድብ ሰራተኞች መሆናቸው ትክክለኛ ምልከታ ነው፡፡ በእኔ ዕይታ ለዚህ ማሳያ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ርዕስ መስተዳደር ከነበሩት ከአቶ ያረጋል አይሽሹም የተሻለ ማሳያ የሚገኝ አይመስለኝም፡፡ ከእርሳቸውም ሌላ በተፈለገ ጊዜ ከክልል ርዕሰ መሰተዳደርነት ተነሰቶ መጥቶ ወደ ፌዴራል መንግሰት የሚመጡበት ሁኔታ በተደጋጋሚ የታየ ነው፡፡ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒሰትራችን በብቃት ማነስ በሚል ከደቡብ ክልል መምጣታቸው፣ እርሳቸውን በብቃት ይተካሉ የተባሉት አቶ ሸፈራው ሽጉጤ ከመለስ ዜናው ሞት በኋላ ከክልል ርዕሰ መስተዳድረነት መነሳት፣ የጋምቤላው ርዕስ መስተዳድር ተነስተው ፌዴራል መስሪያ ቤት ቢሾሙም አድብተው ስደት መምረጣቸው፣ የድሬዳዋ የዙር አመራር፣ የሀረሪ ሀደሬዎችን ማዕከል ያደረገው የመንግሰት አሰያየም፤ ወዘተ እየተመለከትን በምን መመዛኛ የአንድ ፌዴራል አካል የሆነ የክልል መንግሰታት ናቸው ብለን ተጨፍነን ልንሞኝ አንችልም፡፡ የኢዴፓዎች መፈክር በተሳሳተ መስመርም ሆነው - “ዛሬም ይቻላል” የሚል ነው፡፡

በዚህ ክርክር የመኢህአድ ተወካይ አቶ አበባው መሐሪ አንድ ሀቅ ተናግረዋል፡፡ ህዝቡን በዚህ ምርጫ ምረጡን እና እንዲህ እናደርጋለን ብለው እስከመጨረሻው ለማሳሳት አልሞከሩም፡፡ በስተመጨረሻም ቢሆን በግልፅ ያሉተ “ምረጡን እና ምክር ቤት ከገባን ወክለን እንከራከርላችኋለን” ነው፡፡ ለወጉም ቢሆን መንግሰት እንሆናለን አላሉም፡፡ በዚህ አባባላቸው የኢህአዴግን ቀጣይ መንግሰትነትን አምነው ተቀብለውታል፡፡ በክርክሩ ከአንድ ፖለቲከኛ በማይጠበቅ ደረጃ የሰሩት ስህተት እና አቶ አባዱላንም ያሳሳቱት “ህዝቡ በአሰር ብር እንዳይታለል” በሚል የሰጡት አስተያየት ነው፡፡ አቶ አበባው መሃሪ በምድር ላይ ያለውን ሀቅ ገዢው ፓርቲ በኢኮኖሚ ደካማ የሆኑተን ዜጎች በተለያየ መንገድ እንደሚያማልል ለመግለፅ ነው፡፡ ይህን ሀሳብ በቅጡ መግለፅ ካልቻሉ በዚህ ደረጃ ባይሉት ጥሩ ነበር፤ አቶ አባዱላም ይህን በዚሁ መንፈስ ከህዝብ ጋር ለማጋጨት ባይሞክሩ ጥሩ ነበር፡፡ ይህን የአቶ አበባው መሃሪን ስህተት ተከራካሪው አቶ ሬድዋን ሁሴን ወይም ሽመልስ ከማል ቢሆኑ ኖሮ አንድ ዶክመንተሪ የሚወጣው ስድብ ይገጥማቸው ነበር፡፡ አሁንም ኢህአዴግ በቀጣይ በኢቲቪ በሚያቀርበው ዶክመንተሪ ከህዝብ ጋር በሚያጋጭ መልኩ ቅስቀሳ አይደረግባቸውም የሚል እምነት የለኝም፡፡ ለማነኛውም “ከፍትፍት እና ከእሳት” ምርጫ ቀርቦዋል አሰበህ ምረጥ ብለው ክርክሩን አጠናቀዋል፡፡
አቶ አበባው መሃሪ በአማካሪነት ያመጧቸው አዛውንት አስተያየት ካልሰጡ ለምን እንዳደከሟቸው አይገባኝም፡፡ አሁንም እንዚህ ጎምቶ የሀገር አዛውንቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛ ተዋናይ ለመሆን የሚያደርጉትን ፍላጎት ለመግታት ካልተቻለ በቀጣይ ዋነኛ ተዋናይ የሚሆነው አዲስ ትውልድ እንዴት እድል እንደሚያገኝ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ አቶ አበባው መሀሪም ቢሆን በዚህ ክርክር ደረጃውን የጠበቀ የቀድሞውን መኢህአድ ወክለው ሊቀርቡ አልቻሉም፣ ወደፊትም አይችሉምና በጊዜ ቢያስቡበት ጥሩ ነው የሚል ምክር መለገስ አለብኝ፡፡ አንተን ብሎ መካሪ የሚልም ቢኖር ማለቴ ነው፡፡
ኢህአዴግ ባለፈው እንዳልኩት አዲስ ሀሳብ ሆነ አዲስ ሰው እንደሌለው አሁንም በድጋሚ አሳይቶናል፡፡ ፌዴራሊዝምን በሚመለከት ኢህአዴግ እየደጋገመ ሲናገረው ለራሱም እውነት እየመሰለው የመጣው አሁን የተዘረጋው ፌዴራሊዝም ስርዓት ባይኖር ይህች ሀገር ትበታተን ነበር የሚለው ነው፡፡ መሳሪያ ይዘው ይህችን ሀገር ሲቆጣጠሩ እነርሱ እንደ ፈለጉ ካላደረጓት ይህችን ሀገር ለመበታተን ፍላጎት ነበራቸው የሚባል ከሆነ እውነት ነው፡፡ እነሱ ስልጣን ሲይዙ እኛ በህይወት ያለን ምስክሮች ሀገራችን ቋንቋን በዋነኝነት መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝም ካልመጣ እንበታተናለን ብለን ተማምለን አናውቅም፡፡ ልክ ነው ህውሃት ለመገንጠል ሃሳብ ነበረው፣ ኦነግም እንደዚሁ የነፃ ኦሮሚያ ሀሳብ እሰከ አሁን አልተወም፡፡ ኦነግ እንደ ድርጅት ይህን ሀሳብ ባይተወውም መሪዎቹ እነ ሌንጮ ለታ ለአርባ ዓመት በኦነግ ሰም የተከፈለውን መሰዋዕትነት እንዴት እንደሚያወራርዱት ሳናውቅ፤ የመገንጠል ሀሳቡን ትተውት አዲስ አበባ ገብተዋል የሚል ወሬ ነፍስ ዘርቶዋል፡፡
ኢህአዴግ የሚባል ድርጅት ይህችን ሀገር ካልመራ ሀገር ትበተናለች ሰላም የሚባል ነገር የለም የሚባል ቅጥ ያጣ ሟርት ምንጩ ምን እንደሆነ ባይገባኝም፤ ይህን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ደጋግመው ሲያወሩት ለራሳቸውም እውነት እየመሰላቸው መጥቶዋል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ልዩ በሆነ ሁኔታ ብዙ ቋንቋ እንዳለ አድርገው የሚነግሩን ለምን እንደሆነ እሰከ አሁን ለማንም ግልፅ አይደለም፡፡ በሌሎች የዓለም ሀገራት ብዙ ቋንቋ ብዙ ባሕል እያለም ተፋቅሮ መኖር የሚባል ነገር፣ ሀገር የሚባል የጋራ ቤት መስራት እንደተቻለ በፍፁም እንድናውቅ አይፈልጉም፡፡ በአንድ ቋንቋ እየተናገሩም በሰለምና በፍቅ መኖር አቅቷቸው በጎሳ እየተቧደኑ መገዳደል እንደሚቻል በቅርብ ያለች ሀገር ሶማሌ መፍረስ እንዳለም እንደምናውቅ አያውቁም፡፡ ስለዚህ ኢህአዴጎች ተጨፈኑ ላሞኛችሁ እያሉን ነው የሚገኘው፡፡ ይህንኑ መፈክር ነው አሁን ከ24 ዓመት በኋላ ይዘው ለምርጫ ክርክር የቀረቡት፡፡ ለዚህ ነው አዲስ ነገር የላቸውም የምለው፡፡
ለማነኛውም አስገራሚ ሆኖ ያገኘሁት የመከራከሪያ ነጥብ ከአቶ አባዱላ የቀረበው ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ወደ ትጥቅ ትግለ የገባው በቋነቋ መናገር ሲከለከል፣ ባህሉን ማሳደግ ሲያቅተው ነው የሚለው ነው፡፡ ይህ ክርክር በተለይ አቶ አባዱላ ገመዳ ላይ የሚያምር ሆኖ አላገኘሁትም፡፡  ልክ እንደ ትግራይ ልጆች ይህን ብለው ከአዲስ አበባ የኦሮሞ ልጆችን አደራጅተው ቢሄዱ ይህን ሃሳብ ልናከብረው እንችል ነበር፡፡ ለደርግ ሰራዊት ለመዋጋት ወታደር ሆነው በጦር ሜዳ ተማርከው፤ በምርኮ ወቅት ባገኙት የብሔርተኝነት ምክር በሰማኒያዎች መጀመሪያ ጀምረው ባደረጉት የጠመንጃ ትግል አማርኛ አስጠልቶኝ ነው ጫካ የገባሁት የሚመስል አሰተያየት ውሃ አልቋጥር ብሎኛል፡፡ ኢህአዴግ ፌዴራሊዝምን የመረጠው ብዝዓነትን ለማስተናገድ የቻለ ስርዓት ባለመኖሩ ነው ይሉናል፡፡ ይህ ባይሆን ልንበተን ነበር ሲሉን እኔ የሚገባኝ ግን ሊበትኑን ጫካ የነበሩት ግን እነርሱ ራሳቸው መሆናቸው ነው፡፡
ለማነኛውም ሁሉም የሚስማሙበት እኛም ቤታችን ሆነን ሰምምነታችንን የምንሰጥበት ጉዳይ ኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሰርዓት ብቸኛውም አማራጭ የሚለውን ትተን ጥሩ አማራጭ ነው በሚለው ሰምምነት ያለበት መሆኑን ነው፡፡  ሰምምነት የሌለበት እና በህዘብ ይሁንታ ሊታረም የሚገባው ደግሞ ምን ዓይነት ፌዴራሊዝም? የሚለው ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአንድ ጊዜ ተሰርቶ የሚያልቅ ሳይሆን ህዝቦች በሂደት እያዳበሩት የሚሄዱት በዓለም ላይ ያለ የአስተዳደር ዘይቤ ነው፡፡ ፌዴራሊዝም በህዘብ ብዛትና በመሬት ሰፋት እኩል የሆኑ የፌዴራል ግዛቶች የሚያዋቅሩትም አይደለም፡፡ አንድ ዓይነት ቋንቋም ሰለሚናገሩ በአንድ የፌዴራል ክልል ውስጥ መሆን አለባቸው የሚል ፎርሙላም አይሰራም፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያሉት ክልሎች መቼም ቢሆን በራሳቸው መንግሰት ሆነው የራሳቸው የተለየ የአስተዳደር ዘይቤ የመሰረቱበት ሁኔታ ሰለአልነበረ፤ በኢትዮጵያ የሚያስፈልገው ምርጥ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያመጣ እና በተለይ ደግሞ ዜጎች ባልተማከለ አስተዳደር ፍትህና መልካም አስተዳደር የሚያገኙበት፣ በሀገሪቱ ፖለቲካ በቀጥታ ለመሳተፍ የሚያስችል ብቻ ሳይሆን የአካባቢያቸውን ልዮ ሁኔታ ያገናዘበ የእድገትና የፖለቲካ ተሳትፎ ለማደረግ ነፃነት የሚሰጥ ነው፡፡ ይህን ያገናዘበ የፌዴራል ሰርዓት ቢያንስ፤
·         የተለያዩ ህጎች በፌዴራል ክለሎች በሚገኙ መንግሰታት መካከል ሊኖር ይቸላል፡፡ ለምሳሌ የሞት ፍርድን ቀድመው የሚያስቀሩ ክልሎች ሊኖሩ ይችላሉ፤
·         ኦሮሚያን የመሰሉ ትልልቅ ክልሎች ውስጥ ለምሳሌ ቦረና ጅማ የመሳሰሉት አካባቢዎች የገዳ ስርዓት ሞዴል የክልል አስተዳደር እንዲኖር የሚያደርግ አሰራር፤
·         መሬትን ለኤኮኖሚ ጥቅምና ለክልሉ ፈጣን ልማት ሲሉ በነፃ ለኢንቨስትመንት ማቅረብን ጨምሮ ታክስ ክፍያን በተለያየ ምጣኔ ማስከፈል፤
·         የሰለጠነ የሰው ኃይል ወደ ክልላቸው ለመሳብ ሲባል የሚወሰዱ የተለያዩ እርምጃዎች ለምሳሌ የክፍያ ሰርዓት እና የሰራ ቋንቋን ከአንድ በላይ ማድረግ፤ወዘተ
በግልፅ የሚታዩ ልዩነቶች ሊሆኑ ይቸላሉ፡፡
የሁለት ሺ ሰባት ምርጫ አማራጭ ባይኖርም ወጪን ይዞ ገዢውን ፓርቲ ለማንገስ በሁሉም መስክ እየተውተረተረ ይገኛል፡፡ እኔም ሰራ እንዳልፈታ ያለኝን የግል ዕይታ ወርውሪያለሁ፡፡ ሁሉም ላይስማማ ቢችልም ተመዝግቦ እንዲቀመጥ በሚል ያሰፈርኩትን ሀሳብ ተወያዩበት፤ ኢህአዴግ ለውድድር የተዘጋጀበት ዐውድ ግን በእውነት አሰደማሚ እንደሆነ ይቀጥላል፡፡ ይህም ፍርሃቱን ካልሆነ ምን ሊያሳይ እንደሚችል አልገባኝ ብሎ አለሁኝ፡፡

ቸር ይግጠመን!!!

Sunday, March 15, 2015

የምርጫ ክርክር አንድ፡ መድበለ ፓርቲ ሰርዓት እና ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት- በእኔ ዕይታ


ተከራካሪ  “ፓርቲዎች”
ኢህአዴግ፤   አቶ አሰመላሽ ገ/ስላሴ እና አቶ ሬድዋን ሁሴን (ዋና ተከራካሪ ማን እንደሆነ ባይነገርም ይታወቃል)
አትፓ፤      አቶ አሰፋው ጌታቸው
መድረክ፤    ዶር መረራ ጉዲና
ሰማያዊ፤    አቶ ይልቃል ጌትነት እና አቶ ዮናታን ተሰፋዬ
“አንድነት”፤  አቶ ትዕግሰቱ አወሉ
ከዚህ በታች የማቀርበው አስተያየት የግል ምልከታዬን ሲሆን፤ ሰዎች በተለያየ አረዳድ ሊኖራቸው እንደሚችል መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በዘንድሮ ክርክር አንድ ጥሩ ነገር የውይይት ቅደም ተከተል በተራ እንዲሆን መደረጉ ሲሆን ይህ ኢህአዴግ የተሳሳተ መረጃና መደምደሚያ ሰጥቶ አድማጭ እንዳያደናገር ቢያንስ እድል ፊቷን አዙራበታለች፡፡ የመጨረሻውን መልካም እድል ያገኘው “የድንኩ አንድነት” ተወካይ አቶ ትዕግሰቱ አወሉ ቢሆንም በሙሉ ልብ የሚያከራክር ልዕልና ባለመያዙ ይህን ዕድል አልተጠቀመበትም፡፡ ሁለም ፓርቲዎች ከዋና ተከራካሪ በተጨማሪ አንድ አማካሪ ይዘው የገቡ ሲሆን ከሰማያዊ ፓርቲ በስተቀር ሌሎቹ ዕድል ሳያገኙ ወጥተዋል፡፡ ምክር ስለመስጠታቸውም ተመልካቾች እርግጠኞች አይደለም፡፡ አቶ ትዕግሰቱ አወሉ ይዞት የመጣው ግለሰብ ግን ሊመክረው እንደማይችል እርግጠኛ ነኝ፡፡ አንድነትን ድንክ በማድረግ ለዋለው ውለታ በቴሌቪዥን እንዲታይ ብቻ ይመሰለኛል፡፡ የዚህን ያህል እንደ መግቢያ ካልኩ ይበቃኛል፡፡
ኢህአዴግ ለ2007 ምርጫ ክርክር አዲስ ሀሳብ ሆነ አዲስ ሰው እንደሌለው ያረጋገጠበት መድረክ ነበር፡፡ ኢህአዴግ አብዮታዊ ወይም ልማታዊ ዲሞክራሲ እያለ በተለያየ ስም የሚጠራውን መስመር (ርዕዮተዓለም ሊባል ስለማይቻል) የሚያስረዱለት ዋነኛውን ሰው አቶ አስመላሽ ገብረስላሴን፤ እንደ አሰፈላጊነቱ ያለምንም ይሉኝታ ሊሳደቡ የሚችሉትን የስድብ አባት የሆኑትን አቶ ሬድዋን ሁሴንን ይዞ በክርክር መድረኩ ላይ ተሰይሞዋል፡፡ ኢህአዴግ የተሰጠውን የመጀመሪያ 15 ደቂቃ አሁንም ደርግን በጣለበት ጀግንነት ሰሜት ውስጥ ሆኖ አውቀው ይሆን ሳያውቁ 24 ዓመትን እንደ 24 ስዓት እንድንቆጥር እያደረጉ (በዕለቱ 24 ዓመት ለማለት 24 ሰዓት ይሉ ነበር፡፡) የለመድነውን በመንግሰትነት የሰሩትን ሰራ በፍፁም ከተቃዋሚዎች ጋር ሊወዳደሩበት የማይገባቸውን ተግባር እያነሱ ሲጥሉ ጨርሰውታል፡፡ ለተቃዋሚዎች ምንም እውቅና ለመስጠት ሳይዘጋጁ እውቅና በመሻት ሰሜት ውስጥ ሆነው ኦሮጌ የሆነውን የመነሻ ሀሳባቸውን አቅርበዋል፡፡ የ2002 ክርክር በድጋሚ ቢቀርብ ለውጡ አቶ አሰመላሽ የተኳቸው ተከራካሪ ያለመኖር ብቻ ነው፡፡
ቀጣዩን መድረክ በቅድሚያ የተረከበው አዲስ ትውልድ ፓርቲ በመባል የሚታወቀው የአቶ አስፋው ጌታቸው የግል ፓርቲ ነው፡፡ የግላቸው መሆኑን መጠራጠር አያስፈልግም፡፡ የቅስቀሳ ፅሁፍ ከማንበብ ጀምሮ በማንኛውም ስብሰባ ላይ ብቸኛው ተወካይ የሆኑት እኚህ ሰው በእርግጥ ሰማቸው እንደሚለው ይህን ትውልድ አይወክሉም እንጂ፤በመጀመሪያው ዙር ለትውልድ ማፈሪያ በሚሆን ደረጃ ለክርክር ቀርበው አግኝተናቸዋል፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ ከተቃዋሚ ተብዬዎቹ የመጀመሪያ በመሆናቸው ደግሞ በቀጣይ ለሚከራከሩት ሰዎች ማፈሪያ በሚሆን አጀማመር የጀመሩትን ከፍ ለማድረግ አስቸጋሪ ሁኔታ እንደፈጠሩባቸው መረዳት ቀላል ነበር፡፡ በግልፅ ለታዘበ አቶ ይልቃል ጌትነት ከጎናቸው ሆነው ሲሸማቀቁ ላየ ሰው የአቶ አስፋው ጌታቸው የመከራከሪያ ነጥብም ሆነ መንገድ በሌሎች ተከራካሪዎች ላይ ጉዳት አላደረሰም ሊባል አይችልም፡፡ ከጎን ላሉት አይደለም ቤታችን ለተቀመጥን ለእኛም ማፈሪያ የነበረ ክርክር አጀማመር ነው፡፡
አቶ አስፋው ጌታቸው ለክርክር ስለተመረጠው አጀንዳ “የመድበለ ፓርቲ ስርዓትና ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች” ጉዳይ አንድ ቃል ሳይተነፍሱ ስለ አረንጓዴ ቀለም ትርጉም ከረባታቸውን እና በኪሳቸው የሸጎጡትን ብጣሽ ጨርቅ እያሳዩ የተሰጣቸውን ውድ ጊዜ አጠናቀውታል፡፡ ከአረንጓዴ ትንታኔ በተጨማሪ የነገሩን ነገር ቢኖር ከኢህአዴግ ጋር ግብ ግብ ለመግጠም እንደማይፈልጉ ምለው መገዘታቸው ብቻ ነው፡፡ በእኔ እምነት አቶ አስፋው ጌታቸውም ሆኑ ፓርቲያቸው እንደ ሰማቸው ይህን ትውልድ ሊወክሉ አይችሉም፡፡ አቶ አስፋው ጌታቸው በዚህ ውድ ጊዜ ውስጥ ስለ ግል የትምህርት ዝግጅትና ግላዊ ጉዳይ ለማውራት የወሰዱት ጊዜ በኢትዮጵያ ስለ አለው አስከፊ የሰብዓዊ መብታ ሁኔታ ለመናገር ድፍረት ማጣታቸው አሳዝኖኛል፡፡ ይህን አዲስ ትውልድ እወክላለሁ የሚል ፓርቲ የዞን ዘጠኝ በመባል እስር ቤት ያሉት ብሎገሮች እና ጋዜጠኞች እንዲሁም እነ ሀብታሙ አያሌው እና ሌሎች ትንታግ የዚህ ትውልድ ወኪሎች ማንሳት ነበረበት፡፡ ይህ ትውልድ ወኪል አጥቶ ሳይሆን ሁነኛ ወካዮቹ ቤታቸው በገዢው ፓርቲ ውሳኔ ወህኒ መሆኑ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ይህ ትውልድ በምንም ሁኔታ በአዲስ ትውልድ ፓርቲ እና በአቶ አስፋው ጌታቸው አይወከልም፡፡
አቶ ሬድዋን እና አቶ አሰመላሽ በሁለተኛው ክፍለ ጊዜ ባገኙት 20 ደቂቃ በጅምላ ተቃዋሚዎችን በተለይ ሰመያዊና መድረክ ላይ ያደረጉት ውረፋ አቶ አሰፋው ጌታቸውንም ያስቆጣቸው ይመሰላል፡፡ በመጀመሪያ ካቀረቡት የመነሻ ኃሳብ በእጅጉ በተሻለ ሁኔታ የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት የሌለው መሆኑ፣ ኢህአዴግ ርዕዮት ዓለም የሚባል ነገር የሌለው ብቻ ሳይሆን ከኮሚኒዝም እሰከ ነጭ ካፒታሊዝም የሚረግጥ በግለሰቦች ትርጉም የሚመራ ግንባር እንደሆነ አሰቀምጠዋል፡፡ በተለይ ድፍረት አጥተው በግልፅ አይናገሩት እንጂ በተቃዋሚዎች ውስጥ ካለው ክፍፍል በከፋ በኢህአዴግ ውስጥ ያለው የሃሳብ ልዮነት ለከፋ ክፍፍል የሚባቃ እንደሆነ ነገር ግን ስልጣን ላይ በመሆናቸው ግልፅ የሆነ መከፋፈል እንዳላሰዩ ገልፀዋል፡፡ በእኔ እምነት በኢህአዴግ ሰፈር ለመከፋፈል የሚሰጠው ምላሽ በጠብምንጃ የታገዘ እና ወደ ወህኒ የሚያስወረውር እንደሆነ መቀመጥ ነበረበት፡፡ ከዚህ ካመለጡ ደግሞ ሰደት ይሆናል፡፡
ዶክተር መረራ ጉዲና እሰከ ዛሬ ያለቸውን አውቀት ተጠቅመው እንደ ሁልጊዜ በተረጋጋ ሁኔታ በግልፅ በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት የሌለ መሆኑ በማሰቀመጥ ከርዕሱ ጋር ተዛማጅ የሆነ ጉዳይ አንስተዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ዶክተር መረራ በእኔ እምነት ከፖለቲካው ግንባር ቢለቁ የምመርጥ ቢሆንም ከቀረቡ ወዲህ ግን አዲስ ነገር ይዘው መመጣት አለባቸው የሚል እምነት አለኝ /ዛሬም የጥብቆ እና የሚኒሊክ አልጋ ምሳሌ ቢቀር እመርጣሁ/፡፡ ኢህአዴግ አብዮታዊም ወይም ዲሞክራሲያዊም ያለመሆኑን ያስረዱበት መንገድ ተመችቶኛል፡፡ ዶክተር መረራ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጉዳይ ሲነሳ አበክረው ሊያነሱት የሚገባ የነበረ ነገር ግን የዘነጉት ከጎናቸው ተወስደው በእስር የሚማቅቁትን አባላቶቻቸውን ነው፡፡ እነ በቀለ ገርባ፣ ኦልባና ሌሊሳ እና ሌሎች የኦሮሞ ልጆችን በሰም ጠርተው የሚደርሰብቻውን ግፍ ለህዝብ ማሳየት አልቻሉም፡፡ የኦሮሞ ልጆች ከምንጊዜውም በላይ እየደረሰባቸው ያለውን የሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ሊያሳዩን ሙከራ አላደረጉም፡፡ በኢትዮጵያችን በአሁኑ ጊዜ ከኦሮሞ ልጆች እኩል በደል የደረሰበት ያለ አይመስለኝም፡፡ ዶክተር መረራ ለፓርቲዎች ውህደት ጥያቄ ሲቀርብ ኦሮሞነታቸውን የሚያጎሉትን ያህል በሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ብሔረተኝነታቸውን ሊጠቀሙበት አለመቻላቸው ተገቢ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ለመራጮቻቸው በዚህ ርዕስ ጉዳይ ከዚህ የተሻለ ማሰረጃ ሊሰጥዋቸው የሚችሉበት አጋጣሚ ሊያገኙ የሚችሉ አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ ህገ መንግሰታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ሰልፍ የወጡ የአምቦ ዮኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ነዋሪዎች በጥይት የተሰጣቸው መልስ ትክክል ያለመሆኑን ለማስረዳት ከዚህ የተሻለ ጊዜ የሚያገኙ አይመስለኝም፡፡ መብቶችን ለመጠቀም ሁል ጊዜ የሚነሳው ጉዳይ ልክ መሆን አይኖርበትም፡፡
ኢህአዴግ በሁለተኛ ክፍለ ጊዜ ባደረገው ጉንተላ እጅጉን ተበሳጭተው መስመር ከሳቱት በዋነኝነት የሚጠቀሱት ዶክተር መረራ ናቸው፡፡ ተማሪያቸው የነበረው አወያይ ጋዜጠኛ እስኪያቋርጣቸው ድረስ መስመር ጥሰው ሄደዋል፡፡ ርዕሱ “መድበለ ፓርቲ፣ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያ መብቶች” ሆኖ እያለ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ ጉዳዮችን አንሰተው ጊዜያቸውን ጨርሰውታል፡፡ ከውይይት ርዕሱ ጋር የማይሄዱ ነጥቦችን ኢህአዴግ አማራጭ የላቸውም አለን ብለው አድማጭ ሊይዘው በማይችለው ደረጃ ዝርዝሩን ዘርግፈውት በተገቢው ሁኔታ የወከሉትን ግንባር ምልክት እንኳን ሳያስተዋውቁ አጠናቀዋል፡፡ ለሌላ ጊዜ ለክርክር የሚቀርቡ ተከራካሪዎች በወረቀት ላይ የታተመ የምርጫ ምልክት ይዘው መግባት የሚጠቅማቸው ይመስለኛል፡፡
አቶ ይልቃል ጌትነት በአቶ አሰፋው ጌታቸው የክርክር ሂደት በግልፅ በሚታይ መልኩ የደረሰባቸውን መሸማቀቅ በዶክተር መረራ ዘና ያላ አቀራረብ ዱካኩ የተገፈፈላቸው ቢሆንም በቅድመ ክርክር ወቅት የነበረውን ነጥብ አምጥቶ ካለቸው ውድ ጊዜ ለመጠቀም መወሰናቸው እንደ ሁልጊዜውም አጋጣሚውን ለህዝብ ግንኙነት ስራ መጠቀም የፈለጉ ያስመስለዋል፡፡ ክርክሩ ላይ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት የለም ብሎ በግልፅ ያስቀመጡት አቶ ይልቃል የሰብዓዊ መብትን ለማቅረብ የሄዱበት መስመር ሰብዓዊና ዲሞክራሲያ መብቶችን  ለህዝብ በሚገባው ግልፅ ምሳሌ ከማቅረብ ይልቅ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያው መብቶችን በመቀላቀል ማቅረባቸው የዝግጅት እጥረት እንደነበረባቸው ለመረዳት አያስቸግርም፡፡ በሰው ፊት ለንግግር ሰንቀርብ ሀምሳ ከመቶ ዝግጅት መሆኑን አቶ ይልቃል የዘነጉት ይመስላል፡፡ ከዝግጅት አንፃር ተዝረክርከው ማስታወሻውን ወደፊት ወደኋላ ሲገልፁ የነበሩትን አቶ አስፋው ጌታቸውን ማንሳት ሳያስፈልግ ነው፡፡
አቶ ይልቃል በሁለተኛውም ዙር የተሰጣቸውን ጊዜ በአግባቡ ከመጠቀም ይልቅ የተሰጠው ጊዜ አንሰተኛ መሆኑን በሚገልፅ ቅሬታ ጊዜ ሲያባክኑ ነበር፡፡ በሁለተኛው ዙር አቶ ይልቃል ያስቆጠሩት ዋነኛ ነጥብ አቶ አስመላሽ ሰለ ሰመያዊ ፓርቲ ጠቅላላ ጉበዔ አጠራር አሰመልክቶ ያነሱት ነጥብ ነው፡፡ ይህ ነጥብ ኦቶ ይልቃል ከመረጃ እጥረት በሚል እወሰደዋለሁ ቢሉም ይህ የጠቅላላ ጉባዔ ጉዳይ ህወሃት/ኢህአዴግ ከምርጫ ቦርድ ጋር ለሰማያዊ ፓርቲ ከተቀመሙት መርዞች አንዱ እንደሆነ ሁሉም ማወቅ አለበት፡፡ አቶ አስመላሽ የሰማያዊ ፓርቲ ደንብ ጊዜ አግኝተው ሊያነበትም ሆነ ሊያስነብቡ አይችሉም፡፡ አንብበው ፓርቲ ማፍረሻ ቀዳዳ የሚያቀብሉ በምርጫ ቦርድ የተቀመጡ ወኪሎቸ አሉ፡፡ ለዚህ ቅብብል የሚሆን ደግሞ የተዘረጋ ህጋዊ የሚመስል መስመር እንዳለ ሁላችንም እናውቃለን፡፡  ለማነኛውም አቶ ይልቃል የነበረውን ጊዜ በርዕስ ጉዳዩ ላይ ብቻ አተኩረው በምድር ላይ ባለ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት አሰደግፈው መከራከር አልቻሉም፡፡ እንደ ዶክተር መረራ በኢህአደግ ትንኮሳ መበሳጨታቸው ቢታወቅም ለመረጋጋት ያሰዩት ጥረት ጥሩ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ዘመኑን የዋጀ ፓርቲ አይደለም እራሱን የሚያወዳድረው ከንጉሶች ወይመ ከደርግ ጋር ነው፣ መሻሻል የማይፈልግ ፓርቲ ነው፡፡ በሚል ያነሱት ነጥብ በኢትዮጵያ ህዝብ ሊያዝ የሚችል አንኳር ጉዳይ ነው - በምርጫ ካርድ ይሁን በህዝባዊ አመፅ ግልፅ ሆኖ አልተቀመጠም፡፡
የመጨረሻውን እድል ያገኘው የድንኩ “አንድነት” መሪ የሆነው አቶ ትዕግሰቱ አወሉ ነው፡፡ አቶ ትዕግሰቱ ከሌሎቹ በተሻለ የሰብዓዊ መብት ለመርገጥ ገዢው ፓርቲ እየተጠቀመበት ያለውን “የፀረ ሽብር ህግ” አንስቶ ለመሞገት ሞክሮዋል፡፡ በምንም መልኩ ግን አስተያየት ሊሰጥበት ያልቻለው ግን የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ጉዳይ ነው፡፡ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ትዕግሰቱ በትክክል ያውቀዋል፡፡ በኢህአዴግ ኢትዮጵያ ይህች ያገኛትን ቦታ በአባላት ይሁንታ ሳይሆን በተደራጀ ሾኬ እንዳገኛት ስለሚያውቅ መድበለ ፓርቲ ስርዓት የለም ሊል አልደፈረም፤ ቢያንስ በመግቢያው ንግግር፡፡ የሚገርመው ግን አሁንም “አንድነትን” ሲጠራ አፉ ይተሳሰራል፡፡ “እንደ አንድነት ማለትም እንደ እኛ አመለካከት” ሲል ውስጡ ያለው የአንድነት መንፈስ እንዳልሆነ ያሳብቃል፡፡ ትዕግሰቱ የአንድነትን አቋም በሙሉ ልቡ ሊናገር የሚችልበት የሞራል ልዕልና ላይ እንደሌለ በሚያሳብቅበት ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡፡
አቶ ትዕግሰቱ አወሉ ስለሚያቀርበው ሃሳብ ያለኝን የግል ንቀት ለመተው እየሞከርኩ ቢሆንም ለመያዝ የሞከርኩት ነጥብ የዲሞክራሲ ተቋማት የይስሙላ መሆናቸውን ገልፆ በተለይ ምርጫ ቦርድን ጠቅሶ መለወጥ እንዳለበት ሲናገር የበላበትን ወጨት ሰባሪ ቢያደርገውም እውነት መናገሩን ግን መካድ አይቻለም፡፡ ኢህአዴግ ህዝቡን አፍንጫህን ላስ የሚል ፓርቲ መሆኑን መግለፁም ትክክል ነው፡፡ በዚህ አስተያየቱ ኢህአዴግ ተጨማሪ እድል ባለማግኘቱ ምን እንደሚከተለው ማወቅ አይቻልም፡፡ ለማነኛውም ጌቶቹን በተለይ ምርጫ ቦርድ ታዛዥነቱን አይቶ በሰጠው ወንበር ሰሙን ጠርቶ መዝለፉ ሽርክናቻው አንድነትን ድንክ እሰከማድረግ ብቻ አስመስሎባቸዋል፡፡
የኢህአዴግ የምላሽ ወቅት ሰለባዎች እንደሚጠበቀውም ሰመያዊና መድረክ ነበሩ፡፡  የፈለገ ጠንካራ ተቃውሞ ቢያቀርቡም “አትፓ እና ድንኩ አንድነት” በኢህአዴግ አፍ ለዘለፋ አይፈለጉም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ድንኮች ምንም በማያመጣ መልኩ ተሰርተዋል ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ አንድነትን ድንክ በማድረግ ሂደት ዋነኛዎቹ ተዋናዮች የነበሩት ሁለቱም የኢህአዴግ ወኪሎች አንድ ጊዜ እንኳን አንድነትን ሳይዘልፉ ይልቁንም ጅምሩ ጥሩ ነው በሚል ማለፋቸው ሰራቸው ማጠናቀቃቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ የኢህአዴግ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት መገለጫ ተብለው የቀረቡልን ምሳሌዎች ግን ተጨፈኑ ላሞኛችሁ ነገር ነው፡፡ እነርሱም፤
·         አሁን 75 ፓርቲዎች በሀገራችን መኖራቸው የመድበለ ፓርቲ መገለጫ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም አሁን ለክርክር የቀረቡት ፓርቲዎች መኖር ዋናኛ ማሳያ ነው፡፡ እንደ ኢህአዴግ በፓርቲ ምዝገባና ቁጥር የመድበለ ፓርቲ ቢለካ እውነት ነበር፡፡ በወረቀት የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዳለ ሳይካድ በተግባር ገን የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዲኖር የማይፈቅደው ኢህአዴግ ጉንጭ አልፋ ክርክር ያቀርባል፡፡ እምነታቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው ብለው እንዲጠፉ እየሰሩ ለእርዳታ ሰጪዎች ፍጆታ የፓርቲነት ሰርተፊኬት በማደል የመድበለ ፓርቲ ስርዓት አለ ብለን እንድናምን ይፈልጋሉ፡፡ በአሜሪካን ሀገር በዋነኝነት ሁለት ፓርቲዎች መኖራቸው ዲሞክራሲ ያለመኖሩ ማሳያ ነው እንደማለት ነው፡፡ የኢህአዴግ ጉንጭ አልፋ ክርክር፡፡
·         ለምርጫ ውድድ የቀረቡ ዕጩዎች ሌላኛው የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ማሳያ አድርገው ኢህአዴጎች አቅርበዋል፡፡ ማንም እድሉን ሊሞክር ለምርጫ ዕጩ ሆኖ እራሱን ማቅረብ ለመድበለ ፓርቲ ስርዓት ማሳያ እንዴት ሊታይ እንደሚችል አቶ አሰመላሽ እና አቶ ሬድዋን ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ ይህ በቅርቡ የመጣ የመድበለ ፓርቲ ስኬት መገለጫ ነው፡፡
·         ለምርጫ ማስፈፀሚያ የተመደበው በጀት ደግሞ ሌላው የመድበለ ስርዓት ስለመኖሩ ማሳያ ተድረጎ ነው የተብራራልን፡፡ አስገራሚው ነገር ከተመደበው ገንዘብ አብዛኛውን የሚወሰደው ገዢው ፓርቲ መሆኑ እየታወቀ፤ ፓርቲዎች በምርጫ ሰሞን በሚያገኙት በዚህ ገንዘብ የመድበለ ፓርቲ ስርዓትን ለማጠናከር ምን ሊያደርጉበት እንደሚችሉ ማሰረዳት አይችሉም፡፡ ተመደበ የተባለው ገንዘብ ዋነኛው ወጪ ከ45 ሺ በላይ ለሚሆኑ ምርጫ አስፈፃሚዎች አበል ሲሆን፤ ለአንድ ዕጩ ተወዳዳሪ ብር 500 በማይደርሰበት ሁኔታ ይህ ገንዘብ እንዴት እንደሚጠቅም ኢህዴጎች ሊያስረዱን አይችሉም፡፡
·         በጣም ያስገረመኝ አንዱ መከራከሪያ “የመድበለ ፓርቲ በሊብራል ዲሞክራሲ በሚያራምዱ ሀገሮች ለብሔር ብሔረሰቦች የማይፈቅድ ነው” የሚልው ነው፡፡ ኢትዮጵያን የተለየች የብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ አድርጎ ለማሳየት የሚደረገው የተሳሳተ ነገር አሁንም ቅጥ ያጣ ይመስላል፡፡ በዓለም ላይ አሉ የሚባሉ ብሔሮችና ብሔረሰቦች በሙሉ የሚኖሩባት ሀገር አሜሪካ ውስጥ በፈለጉት ቡድን ለመደረጃት አንድም ጥያቄ እንደማይቀርብ የምናውቅ አይመስላቸውም፡፡ ሊብራል ዲሞክራሲን ያለ ስሙ ሰም እየሰጡ የራሳቸውን የፖለቲካ መስመር አንዴ አብዮታዊ ሌላ ጊዜ ልማታዊ ዲሞክራሲ እያሉ ሊያደናብሩን ይፈልጋሉ፡፡ ይህ የብሔርና ብሔረሰብ ፖለቲካ ጉዳይ ሲነገር የሚያስታውሰን አንድ ነገር “ለምለሚቱ ሀገሬ” የሚለው ነገር ነው፡፡ በሌሎች ሀገራት ሳር የማይበቅል፣ ወተት ማር የማይገኝበት፣ ወዘተ ይመስለን የነበረው ዓይነት አሳሳች ምሳሌ ነው፡፡

በመጨረሻም በክርክሩ የነበሩ ተቃዋሚ እና “ተቃዋሚ ተብዬ” ፓርቲዎች በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባት ውይይት ሲደረግ በቅርብ ርቀት በአንድነት ላይ የተፈፀመውን የመንግስታና ለመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባት ለማጠናከር መቆም ያለበትን ምርጫ ቦርድ ሴራ በምሳሌ አንስተው ለመሞገት ያለመሞከራቸው፤ በተለይ መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ የአንድነት ድንክ መሆን እነሱን ከፍ ማድረጉን በግልፅም ባይሆን በውስጣቸው የፈጠረላቸውን ደስታ የሚያሳይ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ አንድነትን ድንክ በማድረጉ ብቻውን እንዳልተጠቀመም ማሳያ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ የሚችለውን በመምረጥ አንፃር በጣም ተሳክቶለታል፡፡ በዚህ ፅሁፍ ለአንድነት ፓርቲ አመራሮች እግረ መንገዴን የማስታውሳቸው ዘወትር በነበሩን ስብሰባዎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለማስተባበር ስንደክም ከእኛ ይቅር ስንል የነበረው ለእነዚህ ፓርቲዎች መሆኑን ማስታወስ ይኖርብኛል፡፡ በተለይ ሰማያዊ ፓርቲን አስመልክቶ አንድነት ፓርቲ ውስጥ የነበረንን ልበ ሰፊነት ሳስበው በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ ለምን አደረግነው የሚል ቁጭት የለብኝም፡፡
አንድነት ፓርቲ በዚህ ክርክር ውስጥ ቢኖር ኖሮ በመጀመሪያ ከኢህአዴግ እኩል ሁሉንም ለመከራከር እድል ነበረው ፓርቲ ይሆን ነበር፡፡ ምክንያቱም 450 ዕጩዎች ለፌዴራል ምክር ቤት እና 1200 የማያንሱ የክልል ምክር ቤት ዕጮዎች ስለሚያቀርብ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ለመከራከር ሊመጡ የሚችሉትን ትንታግ የአንድነት ወጣቶች ሳሰብ እንባ እየተናነቀኝ ነው፡፡ የዛሬ አምሰት ዓመት የዚህን ተመሳሳይ ክርክር አንድነትን ወክሎ  የተከራከረው ምን አልባትም በዚህ ክርክር መነሻ ቂም ተይዞበት የነበረው፣ ዛሬ በወህኒ የሚገኘው አንዱዓለም አራጌ ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ ክርክሩ ከመደረጉ በፊት በዚህ ጉዳይ ላይ በሚኖረው 6 ደቂቃ የመነሻ ኃሳብ ልናነሳ የምንችለውን ቢያንስ 12 ነጥብ ይዘን እንገባ ነበር፡፡ ወይም 10 ነጥብ እና በቀሪው ሁለት ደቂቃ ለህዝብ ውይይት ሊጭር የሚችል ሃሳብ የሚነሳበት ይሆን ነበር፡፡ ሁለተኛው ዙር ዘጠኝ ደቂቃ በዝርዝር ህገ መንግሰታዊ ድንጋጌዎችን አሰመልክቶ ኢህዴግ የሚሰራቸውን የክርክር ፋውሎች ለህዝብ የምናጋልጥበት ይሆን ነበር፡፡ ለዚህ ነው በ2007 ኢህአዴግ የሚችለውን መርጦዋል የምንለው፡፡
ለማጠቃለል ተቃዋሚዎች በኢህአዴግ ትንኮሳ ተገፍተው በመድበለ ፓርቲ እና በሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ዙሪያ ትኩረት ሰጥተው ለመከራከር አልቻሉም፡፡ ክርክሩን በኢህአዴግ ሜዳ ላይ ለማድረግ ማተኮር የነበረባቸው “ህገ መንግሰት” ላይ የተዘረዘሩትን መብቶች እያነበቡ በተግባር የገጠመውን ፈተና በማቅረብ ህዝቡ እነዚህን ጉዳዮች ገዢው ፓርቲ የአፈፃፀም ችግር ናቸው ቢልም በመርዕ የማያምንባቸው መሆኑን እራሱ ኢህአዴግ ከፃፋቸው የፖሊሲ፣ሰትራቴጂና የርዕዮታለም ትንተና መፅሃፉች ጋር እያጣቀሱ ማስረዳት ነበረባቸው፡፡ የህገ መንግሰቱ ምዕራፍ ሶሰት ክፍል አንድ ከአንቀፅ 14 -28 የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን በማየት በተግባር የገጠሙትን ፈተናዎች፤ ምዕራፍ ሶሰት ክፍል ሁለት ከአንቀፅ 29-44 ዲሞክራሲያዊ መብቶቸን በማየት የገጠሙትን ፈተናዎች በዝርዝር መተንተን ይቻል ነበር፡፡ በዚህ መስመር ክርክሩ ቢደረግ ኢህአዴግ ሊከራከር የሚችለው ህገመንግሰቱን ለማዘጋጀት ህይወትና ደም ተከፍሎበታል ከሚል ፉከራ ውጭ ለምን በተግባር ላይ እንደማያውላቸው ሊያስረዳ አይችልም ነበር፡፡ ምንም በቂ ምክንያት ሊኖር አይችልም የሚል እምነት አለኝ፡፡
ቸር ይግጠመን!!!!


Wednesday, March 4, 2015

“ኮሚሽነር ጄነራል” ትዕግሰቱ አወሉ ……

ብዙ ሰዎች ስለ እነ ትዕግሰቱ አወሉና ግብረ አበሮቹ መፃፍ ተገቢ አይደለም ይላሉ፡፡ ምክንያታቸውም ደረጃቸውን ከፍ ያደርገዋል የሚለው አንዱ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ከፍ ቢሉም ቢወርዱም እውነቱን ሰው አውቆት ፀሐይ ሞቆት መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሰለዚህ እፅፋለሁ፡፡ በቅርቡ የወጣ “የእኛ ፕሬስ ጋዜጣ ላይ አቶ ትዕግሰቱ በእርሱ ብሶ ቱግ ቱግ እያለ የሰጠውን ቅጥፈት የተሞላበት ቃለ መጠይቅ አይቼ ማለፍ አልቻልኩም፡፡ በዚህ ደረጃ ለሆዱ ያደረን ሰው ለምን ዋሸ ተብሎ አይጠየቅም ያሉ ሰዎች ቢኖሩም ውሸታም መባል አለበት ብዬ ስላመንኩ ይህችን አጭር ነገር ለማለት ወደድኩ፡፡ በነገራችን ላይ የኢህአዴግ ካድሬዎ ስለ ትዕግሰቱ ሲፃፍ ከሱ ይልቅ ይነዳቸዋል፡፡ በማህበራዊ ኑሮ እንዲገለል ለማድረግ ነው ይላሉ፡፡ በእኔ እምነት ትዕግሰቱን ከማህበራዊ ኑሮ ለማግለል ማህበረሰቡ የሚፈልገው የእኔን ምክር ሳይሆን የእርሱ ተግባር ነው፡፡ የሰራሁት ስራ ጥሩ ነው ካለ ማፈርም መገለልም የለበትም፡፡ ነውር ይዞ ግን ማህበረሰብ ውስጥ ለመቅረብ ስትሞክር ግን ዋጋ ያስከፍላል፡፡
ወደ ተነሳሁበት ርዕሰ ጉዳይ ስሄድ፤ በእኔ ግምት ጋዜጠኛው ብዙ ነገር ሊጠይቀው ተዘጋጅቶ ቢሆንም እንኳን ከትዕግሰቱ ጋር ከዚህ በላይ መነታረክ አያስፈልግም ብሎ ያቆመው ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ትዕግሰቱ ሰራው ትዕግሰት ነስቶት ጥያሰቄ ለመመለስ ዝግጁ አይደለም፡፡  አንድነትን ለማፍረስ እና አቶ ትዕግሰቱን ለማንገስ በተጠራው ስብሰባ ላይ የተሰበሰቡት ሰዎች የአንድነት አባላት ናቸው? ለሚል ጥያቄ ሲቀርብለት እኔ አባል አይደለሁም? የማነ አባል አይደለም? ብርሃኑ አመራር አይደለም? ብሎ ጋዜጠኛ ጋር መነታረክ መልስ ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ ነበሩ የተባሉት 193 ሰዎች ሰም ዝርዝር ማቅረብና አባላት መሆናቸውን ማስረዳት ነው፡፡ አቶ ትዕግሰቱ ሰማቸውን እየተጠራ አባል አይደሉም ወይ ያላቸው ሰዎች በቅጥረኝነት ከትዕግሰቱ ቀድመው የተሰለፉ ናቸው፡፡ ትዕግሰቱ ከኋላ ሆኖ ሲጫወት ከፊት ያጠቁ የነበሩ ናቸው፡፡ ከትዕግሰቱ ጋር ባደረኩት የስልክ ንግግር ለምን ወደፊት አትመጣም? ከኋላ ሆነህ ለምን ትረብሻለህ? ብዬ ስጠይቀው “ሞሪኖ ሜዳ አይገባም፡፡” ብሎ ነው የመለሰልኝ፡፡ አሁን ሲቀጥፍ እኔ ቅሬታ ያላቸውን ሰዎች የተቀላቀልኩት ጥር 3 ነው ይለናል፡፡ ከፈለክ ድምፅህን ማህበራዊ ድህረ ገፅ ላይ ልለጥፈው እችላለሁ፡፡
ትዕግስቱ አወሉ “የፖለቲካ ውሳኔ” ምን ማለት እንደሆነ አያውቅም፡፡ ምርጫ ቦርድ በህግም ሆነ በአሰራር ባልተሰጠው ስልጣን አንድን ፓርቲ ለእገሌ ሰጥቻለው ማለት እና በድፍረት መወሰን የፖለቲካ ውሳኔ ማለት ነው፡፡ ይህ ድፍረት የሚመጣው ደግሞ ህግን በጡንቻቸው ስር ባደረጉ ፖለቲከኞች ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ውሳኔዎች ፖለቲካዊ ውሳኔ ይባላሉ፡፡ ውሳኔው ፖለተካዊ አይደለም የሚባለው ህግና በመረጃ መሰረት ተደርጎ በፍርድ ቤት ሲወሰን ነው፡፡ ለአንባቢዎች ግልፅ እንዲሆን አንድ ምሳሌ ማንሳት ጥሩ ነው፡፡ ሁለት በጋራ ንግድ ያላቸው ሰዎች አለመገባባት ውስጥ ሲገቡ ንግድ ሚኒሰቴር ንግዱን ለእገሌ ሰትቸዋለሁ ብሎ እንደ መወሰን ነው፡፡ ይህ ደግሞ አልበቃ ብሎ ይህን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ ንግድ ሚኒሰቴር ፖሊሲ ማዘዘ ከቻለ ነው፡፡
የፖሊስ ነገር ከተነሳ ደግሞ በአቶ ትዕግሰቱ አወሉ ቃለ መጠይቅ ውስጥ አስገራሚ ነገር አንብቢያለሁ፡፡ “ፖሊሱንም ያቆሙኩት ከውሳኔው ከሁለት ቀን በኋላ ነው፡፡ ሁሌም ፖሊስ አለ፡፡ የዚያን ሰዓት ንብረት እንዳይጠፋ እንዲቆጣጠር ተደርጓል፡፡” የሚል ነው፡፡ አቶ ትዕግሰቱ ፖሊስ የማዘዝ ያህል ስልጣን እንዳለው አላውቅም ነበር፡፡ “ኮሚሽነር ጄኔራል” ትዕግሰቱ አወሉ ከፓርቲ ፅ/ቤት የወጡ ሁሉ እንዳይገቡ አድርጓል፡፡ በጥር መጨረሻ በምክር ቤት በነበረ ሰብሰባ ለአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ምርጫ ቦርድ ፖሊስ የማዘዝ ስልጣን ከየት አመጣ? በሚል ላነሳሁት ጥያቄ መልስ አልሰጡኝም ነበር፡፡ ለካ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳያውቁት ሌላ የፖሊስ አዛዥ የሆኑት አቶ ትዕግስቱ አወሉ ነበሩ፡፡
ሌላው አስገራሚ ነገር ንብረት እንዳይጠፋ የምትለዋ አስተያየት ነች፡፡ ሌባ እናት ልጇን አታምንም እንደሚባለው ነው፡፡ በፓርቲ ፅ/ቤት የነበርን የአንድነት ስራ አስፈፃሚ አባላት ሐሙስ በአስራ አንድ ሰዓት አካባቢ የምርጫ ቦርድን ነውረኛ ውሳኔ ከሰማን በኋላ  በማግሰቱ ጠዋት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ ከሰዓት በኋላ ደግሞ የብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ እንዲጠራ ወሰነን ወደ ቤታችን ገባን፡፡ ጠዋት ስራ አስፈፃሚ ተሰብሰቦ ከወሰናቸው ውሳኔዎች አንዱ በምርጫ ቦርድ ውሰኔ ፓርቲውን ለትዕግሰቱ አወሉ እንደማንሰጥ፣ ፍርድ ቤት ከወሰነ ግን ርክክብ እንዲፈፀም ርክክቡንም የፓርቲው ዋና ፀሃፊ ከኦዲትና ኢንሰፔክሽን ጋር ሆኖ በዝርዝር እንዲፈፀም ነበር፡፡ ይህ ውሳኔ የተላለፈበት ቃለ ጉባዔ ጠረጴዛ ላይ እንዳለ ለምሳ ወጥተን ስንመለስ “ኮሚሽነር ጄነራል” ትዕግስቱ አወሉ ያዘዟቸው ፖሊች የፓርቲውን ፅ/ቤት ወረውት አገኘን፣ ወደ ጊቢ መግባት ተከልክለን፤ በመጨረሻም መኪናችን በፖሊስ ተበርብሮ መኪናችንን ከጊቢ እንድናወጣ ተደረገ፡፡ በዕለቱ መኪናችን ጊቢ ውስጥ የነበረው እኔ፣ በላይ እና አቶ ተመስገን ዘውዴ ነበርን፡፡ እኛ ደግሞ ንብረታችንን አንዘርፍም፡፡
ሌላ አቶ ትዕግሰቱ ያነሳው ሰለ 2004 እና 2006 ደንብ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ እራሱን ከፍ ከፍ ለማድረግ ደንቡን ከአረቀቁት ሰዎች አንዱ ነበርኩ የሚለው ነው፡፡ ትዕግሱ ብሎ ደንብ አርቃቂ፡፡ የአንድነት ደንብ በ2006 መጠነኛ መሻሻሎች ብቻ ነው የተደረገበት፡፡ ይህም በብሔራዊ ምክር ቤት ተወሰኖ ያለቀ ጉዳይ ነበር፡፡ አቶ ትዕግሰቱ ግን የተሻሻሉትን አንቀጾች እንዲያስገባ ኃላፊነት ተሰጥቶት ሁለት ዓይነት ደንብ አባዝቶ እንዲሰራጭ ያደረገው እና በወቅቱ ለምራጫ ቦርድ እንዳይገባ ያደረገው እራሱ ነው፡፡ ይህም የሆነው በኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው አመራር ወቅት ነው፡፡ ተጠያቂውም ግዛቸው ነው የሚሆነው፡፡ ይህን ሳቦታጅ ሲሰራ የነበረው ደግሞ ከአዲስ አበባ ሰብሳቢነት ተነስቶ ከስራ አስፈፃሚም እንዲወጣ በመደረጉ ነው፡፡ እውነቱን የተናገረው አልህ ምላጭ ያስውጣል የሚለው ነው፡፡ እርሱ ሰራ አስፈፃሚ ውስጥ ካልገባ አንድነት በምርጫ ቦርድ ቅርቃር ውስጥ ቢሆን ትዕግሰቱ ግድ የለውም፡፡ ይህን አስነዋሪ ሰራውን ሰው የማያውቅ መስሎት “የፖለቲካ ሳቦታጅ” ብሎ ሰው ለመክስስ አፉን ሲከፍት ግን ትንሽም ከጭንቅላቱ ጋር ሰላም እንደማይፈልግ ያስታውቃል፡፡ ለሆዱ የሚያድርን ሰው እንዴት አድርጎ ለእውነት ቁም ተብሎ ይጠየቃል? ለምንስ ዋሽ  ይባላል? በግለጭ ውሸታም ከማለት በዘለለ፡፡
ሌላው ነጭ ውሸት ደግሞ ምርጫ ቦርድ የአንድነት አመራርን አላውቅም አለ የሚለው ነው፡፡ ምርጫ ቦርደ የአንድነትን አመራር አላውቅም ብሎ በግልፅ ደብዳቤ ፅፎ አያውቅም፡፡ ከምርጫ ቦርድ ጋር ያደረግናቸውን ደብዳቤ ልውውጦች መመልከት ይቻላል፡፡ www.girmaseifu.blogspot.com :: ልክ ነው ምርጫ ቦርድ በህዝብ ግንኙነት ሰራተኛው በኩል ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ባላቸው ግንኙነት የአንድነት አመራር እውቅና የለውም ብለው አውጥተዋል፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ ላይ ሆነን ስናየው ፍንትው ብሎ የሚታየን ሀቅ አንድነት ላይ ዘመቻ በይፋ የተከፈተው የዛን እለት እንደሆነ ነው፡፡ የዚያን ዕለት ጀምሮ ጫማቸው ስር ብንወድቅ አንድነትን ድንክ አድርገን በእጃችን ለማቆየት ይቻል ነበር፡፡ በእኛ እጅ አንድነት ድንክ ከሚሆን ደግሞ ለእርሱ የሚመጥን ሌላ ድንክ ትዕግሰቱ አወሉ ስለ አለ በዚህ ደረጃ መወዳደር አያስፈልገንም፡፡ በጭንቅላታችን ያለው የአንድነት አስተሳሰብ ግን ሁሌም አብሮን እንዳለ እርገጠኛ መሆን ያሰፈልጋል፡፡
አቶ ትዕግስቱ ሌላ አስቂኝ አስተያየት ሰጥቷ፡፡ “ተለጣፊ የሚሉን ሰዎች ምንጫቸውንም ስናስስ አሁን ካለው ስርዓት አሰተሳሰብ የወጡ ናቸው፡፡ እኛ በዚህ ሂደት ያለፍን አይደለንም፡፡” ይለናል፡፡ ገዢው ፓርቲ የሚከሰን የድሮ ስርዓት ናፋቂዎች በሚል ሲሆን ትዕግሰቱ ደግሞ የዚሁ ስርዓት ውላጆች ይለናል፡፡ ለማነኛውም ትዕግሰቱ ከየት ወዴት የሚል አጭር መድበል የሚያውቁህ ሰዎች እንዲፅፉ ከማስታወስ ውጭ ከሀሰብ- እሰከ አዲስ አበባ ያደረካትን የፖለቲካም ሆነ የማህበራዊ ጉዞህ የሚፈተሸ ሰው ይጠፋል ብዬ አልገምትም፡፡ በድህነትህ መቀለድ ስለማይገባ የኢኮኖሚ ጉዳይ ባይነሳ ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን ዳቦ መግዢያ ሲያጥርህ የደረሱልህን የፓርቲ አመራሮች የምትረሳቸው አይሆንም፡፡ በሰብዓዊነት እንጂ አንተን ለመግዛት እንዳልነበር ግን ልቦናህ ያውቀዋል፡፡
በመጨረሻም “ኮሚሽነር ጄኔራል” ትዕግስቱ አወሉ ስልጣንህን መከታ አድርገህ በፖሊስ መግቢያ መውጫ እንደማታሳጣን ተሰፋ በማድረግ አንድ ነገር ላንሳ፡፡ የኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ከስልጣን መውረድን በተመለከተ ከአንተ እና ከአስራት አብርሃ ማን ነበር በትጋት የሰራው? በተለይ በሴራ መንገድ፡፡ አሰራት አብርሃም ሆነ እኔ በግሌ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው እንዲመራን እንደማንፈልግ በግልፅ ኣቋም እንደያዝን ይታወቅ ነበር፡፡ ለዚህ ነበር በስራ አስፈፃሚ በማንኛም አማላጅ አንገባም ስንል አንተ ሰራ አስፈፃሚ ለመሆን እድል ያገኘኸው፡፡ ምክንያታችንንም በግልፅ አስቀመጠናል፡፡ ነገር ግን አንተ ግዛቸው በሚመራው ካቢኔ ውስጥ ሆነህ ውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋርም ሆነ በሀገር ውስጥ ካለን ሰዎች ጋር ምን ስትሰራ እንደነበር ኢ/ር ግዛቸውም ሆነ ሌሎች ሁሉ የሚያውቁት ሀቅ ነው፡፡ ብትክድ ግን ብዙ ማሰረጃዎች ይቀርብብሃል፡፡ በዚህም መነሻ ግዛቸው አንተን ማየት እንዴት እንደሚጠላ ታውቃለህ፡፡ የግዛቸው ፍቅር እንዲህ ካቃጠለህ፡፡ ምነው ዛሬ አትደውልለትም እና ሰራ አስፈፃሚ ሁነኝ አትለውም?
ለማነኛውም፤
·         ተሰብሰበው የተሰጡህን ለፖለቲካ ያልደረሱ ህፃናት ይዘህ የምታመጣውን ለማየት እንጓጓለን፡፡ መልካም እድል አይባልም እንደ አንተ ያለን ክፉ ሰው እግዜር ይገላግለን ከማለት ውጭ!!
·         የምርጫ ቦርድ መቅረብ የነበረበት ሪፖርት የዘገየበትን ምክንያት ካንተ ውጭ ሌላ ሰው ካለ በአሁኑ ስዓት ሊመሰክር የሚችለው ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ስለሆነ ጋዜጠኞች ይህን ጥያቄ እንዲያነሱ አሳሰባለሁ፤ ግዛቸው መልስ አልሰጥም የለሁበትም ሊል አይችልም፡፡ ከትዕግሰቱ ባለነስ ለአንድነት መፍረስ ተጠያቂ መሆኑን ማወቅ አለበት፡፡ እኛም ማስታወስ ይኖርብናል፡፡
·         አቶ ትዕግሰቱ ተመረጥኩ ያልክበትን ጉባዔ ተሳታፊዎች ዝርዝር መያዝና የአንድነት አባላት መሆናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለብህ መዘንጋት የለብህም፡፡ የአንድነት አባል አይደለም፤ ዝም ብለህ የምትፅፈው 193 የስም ዝርዝር እንደሌለህ እናውቃልን፡፡
·         2004 እና 2006 ደንብ እያልክ ማምታታት ማቆም አለብህ፡፡ የ2004 ደንብ ነው የሚገዛኝ ካልክ ደግሞ ኢ/ር ግዛቸውም ህጋዊ መሪ እንዳልሆነ መርሳት የለብህም፡፡ በተጨማሪ የአንድነት ፕሬዝዳንት የሚል ነገር የመጣው በ2006 ደንብ ሰለሆነ ሁሌም እራሰህን ከዚህ ማዕረግ አርቅ፡፡ አይመጥንህም፡፡
·         ፕሮፓጋንዳ ለመስራት ሰለማንፈልግ ነው እንጂ አዲስ አባለት ገብተዋል ያልከውን እናውቃለን፡፡ እነማን እንደሆኑ ዝርዝር ብታወጣ ጥሩ ነው፡፡ ከየትኛው ሰፈር ከተደራጀ ፎረም እንደመጡ ህዝቡ ያውቃልና፡፡
·         ሌላ ፓርቲ ለመግባት ሰለሞከሩት የአንድነት አባላት “ከሞራል አንፃር አይመከርም” ብለህ መምከር ሞክረሃል፡፡ ስለ ሞራል ለመምከር ለጊዜው ብቻ ሳይሆን ወደፊትም የሞራል ብቃት እንደማይኖርህ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ እልህ ምላጭ ያሱጣል ማለትህ ልክ ቢሆንም የዋጥካት ምላጭ ግን ጩቤ ሆና እንደምትዘለዝልህ መርሳት የለብህም፡፡ ከአሁን በኋላ ምንም ብትውጥ ሞራል የሚባል ነገር ሊኖርህ አይችልም፡፡
·         በመጨረሻም የካቢኔህን ዝርዝር እና የትምህርት ደረጃ ይፋ ብታደርግልን በእውነት አንድነትን ምን ያህል ድንክ እንዳደረከው ህዝቡ ይረዳል ብዬ ስለማምን ፈቃደኛ ከሆንክ ብታደርግልን፡፡ ዝርዝሩ ለማነኛውም ምርጫ ቦርድ ገቢ አድርግ ያለበለዛ ሌላ አንጃ አስነስተው ከስልጣን እንዳያወርዱህ
አበቃሁ፡፡ መልስህን በዝርዝር እጠብቃለሁ!!!!