Sunday, March 29, 2015

ክርክር ሶስት- ግብርና እና ገጠር ልማት


“በ24 ዓመት አሁንም በአዝማሚያ ላይ ነኝ የሚለው ኢህአዴግ ……”
“የ1997 የምርጫ ክርክር ይደገም ……”
ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com; girmaseifu.blogspot.com
ተከራካሪዎች፤
አቶ ተፈራ ደርቤ እና ዶ/ር አብርሃም ተከስተ
አቶ ግርማይ አደራ እና ዐዐዐዐዐ
አቶ ትዕግሰቱ አወሉ እና አቶ ዮሃንስ አሰፋ
አቶ ግዑሽ ገብረሰላሴ እና ትዕግሰቱ ዱባለ
አቶ ጥላሁን እንዳሻው እና ሙላቱ ገመቹ
በመጋቢት 18 እና 19 2007 ለግንቦት ምርጫ የተደረገው “የምረጡኝ ክርክር” የተጀመረው በአቶ ተፈራ ደርበው በተመራው የኢህአዴግ ቡድን በግንባሩ ውስጥ በከባድ ሚዛኑ ህወሃት ተወካዮ ዶክተር አብርሃም ተከሰተ በመታገዝ ነበር የተገኘው፡፡ ተከራካሪዎቹ በኢህአዴግ በተተኪ መስመር የሚገኙ ቢሆኑም እንደ ወትሮ ሁሉ ኢህአዴግ የሚያቀርበው አዲስ ሀሳብ ለሚቀጥለው የስልጣን ዘመን ሊያቀርብ አልቻለም፡፡ እነዚህ የኢህአዴግን ሹሞች ልብ አውልቅ የሆነውን በእውሸት የተሞላውን የቁጥር ጫወታ ይዘው ብቅ ያሉ ሲሆን በዚህ ደረጃ ሊሞግታቸው የሚችል፤ አንድም ተቃዋሚ ነኝ የሚል ለማየት አልቻልንም፡፡ ኢህአዴጎች ከታቃዋሚዎች በላቀ ደረጃ ጎላ ያደረጋቸው የለበሱት ሱፍና የተጫሙት ጫማ ማብቅረቅ ሲሆን ተቃዋሚዎች አሁንም ከጀርባቸው ያስቀመጧቸው አማካሪ ተብዬዎች ምንም ያለመፈየድ ሳይሆን እንቅልፍ ሲያንጎላጃቸው ማየት ኢህአዴግ በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ምን ዓይነት ሰዎችን ወደፊት እያመጣ እና ወደፊትም እንደሚያመጣ አመላካች ነው፡፡ ከተቃዋሚ ጀርባ ለተቀመጡትም ሆነ በፊት መስመር ላሉት ደካማ ተቃዋሚዎች ተጠያቂው ኢህአዴግ እና የዘረጋው ስርዓት መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡
ኢህአደግ ለቀጣይ አምስት ዓምት በስልጣን እንደሚቆይ ቢያውቅም ይህን በትህትና ለገጠሩ ህብረተሰብ ያስተላለፉት ዶክተር አብርሃም ተከሰተ እና ቆጣ ቆጣ ሲሉ የነበሩት አቶ ተፈራ ደርቤ ናቸው፡፡ ለዚህም እንደማስረጃ ያቀረቡልን
·         60 ሺ በላይ የገጠር ልማት ሰራተኞች  እና የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች(በተቃዋሚዎች በትክክል ካድሬዎች ተብለው የተፈረጁት)፤
·         ድህነትን በ1988 ከነበረበት 48 ከመቶ ወደ 24 ከመቶ ዝቅ ማድረጋቸው፤ (በመቶኛ ቀነሰ ቢባልም በቁጥር ግን በ1988 ከነበረው ጋር ተቀራራቢ ነው፡፡)
·         መስኖ እና ሰፈራ በአርብቶ አደሩ አካባቢ ማስፋፋቱ፤
·         2.2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በግል ባለሀብት እየለማ መሆኑ (ይህ መረጃ በቅርቡ እየተነገረ ቢሆንም ኢትዮጵያዊያን በዚህ መስክ የሚያደርጉት ተሳትፎ በግልፅ የሚታይ አይደለም)
·         የመሰረተ ትምህርት እና ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት መስፋፋቱ፤ ወዘተ ሲሆን
በዚህ መነሻ አርሶ አደሩ ሀብት እያከባተ በመሆኑ ወደ ማንፋክቸሪንግ ዘርፍ እንሚገባ አሰረድተውናል፡፡ አህአዴጎች በዛሬው ክርክር የቀደሞ ሰርዓት መክስስ ዘዴያቸውን የገቱ ቢሆንም ተቃዋሚዎችን ማጣጣል በተለይ መድረክ ላይ ለመዝመት ተዘጋጅተው እንደመጡ አቀራረባቸው ያሳብቅ ነበር፡፡ አቶ ተፈራ ደርቤ በተደጋጋሚ ተቃዋሚዎች ከላይ የተዘረዘሩትን የኢህአዴግ ሰኬት በመቃወም መሬት ይሸጥ ይለወጥ በማለት አርሶ አደሩን በማፈናቀል ለጥቂት ባለሀብቶ የቆሙ መሆናቸውን ያረጋገጡበት ክርክር ነበር፡፡ አቶ ተፈራ ደርበው ከመድረክ ጋር ተከራከሩ ተብለው መመሪያ እንደተሰጣቸው በሚያሳብቅ ሁኔታ መድረክን መሬት ይሽጥ? ነው የምትሉት ወይስ ሌላ አማራጭ አላችሁ? እያሉ በተደጋጋሚ አንስተውታል፡፡ አቶ ጥላሁን እንሻውም እንዳሻቸው መልሰውላቸዋል፡፡
ከኢህአዴጉ ተወካይ ዶክተር አብርሃም ተከስተ ያነሱት ሀሳብ ግን ወደ 1997 ክርክር መልሶኛል፡፡ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ አቶ አዲሱ “ግብርና ሴክተር የእድገት ፍንጭ” እያሳየ ነው ሲሉ ለሰጡት አሰተያየት  “ከ14 ዓመት በኋላ ፍንጭ እየታየ ነው አትበሉን” በሚል የሰጣቸውን ምላሽ አሰታውሶኛል፤ በ2007 ክርክር ዶክተር አብርሃም ተከስተ የግብርና ፖሊሲው “የስራ አጥ ቁጥርን የመቀነስ አዝማሚያ” እያሳየ ነው ብለውን ከ24 ዓመት በኋላ አዝማሚያ ላይ እንደሆኑ ነግረውናል፡፡ በእኔ እምነት የግብርና ዘርፉ ይህን ሁሉ ጉልበት ይዞ መቀመጥ አይጠበቅበትም፡፡ በግብርና ዘርፍ ያለው ትርፍ ጉልበት ሊቀበል የሚችል ግብርና ያልሆነ ዘርፍ መፍጠር ያልቻለው ኢህአዴግ ሊከሰስበት የሚገባው ዋና ነጥብ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ 24 ዓመት ያልበቃው ኢህአዴግ ምን ሲሰራ ነበር ተብሎ አይጠየቅም፡፡ ብዙዎቹ ሚኒሰትሮች ከሁለተኛ ደረጃ፣ የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም ድህረ ምረቃ ትምህርት ሲከታተሉ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አንድ አንዶች ለሶሰተኛ ዲግሪ የሚሆን ጊዜ ነበራቸው፡፡ አበበ ገላው እየገዙ ነው የሚለውን ወደጎን እንተወው ከተባለ ማለት ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ያሉትም ማሰታወስ ያሰፈልጋል “እነዚህ ሰዎች ሀገር እየመሩ/እያሰተዳደሩ ሶሰተኛ ዲግሪ መያዛቸው ወይ ሰራቸውን እየሰሩ አይለም፣ ካልሆነም ትምህርቱ ቀሎዋል ማለት ነው” አሰተያየት ሰምቻለሁ፡፡ ቃል በቃል ባይሆንም፡፡
ለማነኛውም ኢህአዴግ መነሻ ሀሳቡንም፣ ማብራሪያውንም ማጠቃለያውን “በሚመጥነው” ደረጃ አቅርቦ ክርክሩን አጠናቆዋል፡፡ ከዚህ የጠነከረ ክርክር ቢያቀርብ ማን ከቁብ ሊቆጥርለት ነው፡፡ በእኔ ግምት ዶክተር አብርሃም ተከስተ በዚህ ክርክር ላይ ባልመጣው ሳይል የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ጠንከር ያለ ቁጥርና ቁጥር ነክ ጥያቄዎች በተለይ ደግሞ የመዋቅራዊ ሽግግር ጥያቄዎች እና ማክሮ ኤኮኖሚክ ነክ የሆኑ ለምሳሌ በውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ በግብርና ሴክተር የመሪነት ሚና ላይ ዝርዝር ሀሳቦች ለመመለስ በክርክሩ ላይ የተገኘ ይመስል ነበር፡፡ ዶክተር አብርሃም ተከስተ የክርክር ጊዜውን ለመግደል ዘና ብሎ ሲመልስ ላስተዋለ በእግር ኳስ ጫወታ እየመራ ያለ ቡድን ጎል ጠባቂ ጊዜ ሲያባክን የሚያሳየውን ባህሪ የሚያሰታውስ ነው፡፡
ለማነኛውም አቶ ተፈራ ደርቤ ያቀረቡት የመሬት ጉዳይ በህገ መንግሰት ውስጥ መግባቱ እና አሁን የሚከተሉት የመሬት ፖሊሲ መሰረቱ ኤኮኖሚያዊ ነው ብለው ቢዋሹም፣ ኢህአዴግ መሰረቴ ነው የሚለውን አርሶ አደር ለመቆጣጠር እንዲችል የተቀመጠ ፖለቲካዊ መሰረትነቱ መቼም ክዶት የማያወቅው ታውቆ ያደረ ጉዳይ መሆኑን የሚያስታውሳቸው አላገኙም፡፡ የዶክተር አብርሃም ተከሰተ ትህትና የተሞላበት የምረጡን ጥያቄም አማላይ ነበር፡፡

ኢፍዴአግ  በአቶ ግርማይ አደራ በሚባሉ ሰው የተወከለ ሲሆን በረዳትነት የተገኘውን ለማወቅ እድል አላገኘንም፡፡ አቶ ግርማይ ጊዜው አይበቃም ቢሉም ሲጀምሩ ቀስ ብለው ተዝናንተው ሲጨርሱም ሁለት ደቂቃ አሰቀርተው ሲያጣቃልሉም ለጊዜ አጠቃቀም ምንም ግድ ሳይሰጣቸው ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ከእኝ ግለሰብ ልይዝላቸው የቻልኩት ነጥብ  መሬት ለኢትዮጵያን የዜግነት፣ የሀገር ባለቤትነት፣ የነፃነት መገለጫ ነው የሚሉት እና የማዳበሪያ ዕዳ ለመክፈል አዲስ አባባ ለልመና የሚመጡ አርሶ አደሮች መኖራቸውን ያስታወሱን መሆኑን ነው፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ በፅሁፍ የያዘውን በቅጡ የማያነብ፣ በቂ አይደለም ብሎ ካለው ጊዜ ውስጥ በመግቢያና በመውጫ ሠዓት ማባከን ምን ግምት እንደሚያሰጥ ተከራካሪው ያሰቡበት አይመስለም፡፡ ለማነኛውም ኢህአዴግ አቻውን አግኝቶዋል ማለት ይቻላል፡፡ በቃ ኢህአዴግ የሚመጥነው እንደ አቶ ግርማይ አደራ ያሉ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ ምርጫቸው ነው እና ማክበር አለብን፡፡ አቶ ግርማይ አርማው ጋሻና ጦር የሆነ እድር ቢኖራቸው ችግር የለኝም ነገር ግን እርሳቸውም ሆነ የእርሳቸው ፓርቲ በሚሰጡት አመራር በማጠቃለያ እንደነገሩን በምግብ እህል ራሷን የቻለች ኢትዮጵጰያ ሊዚያውም ተርፎዋት ኤክስፖርት የምታደርግ ሀገር አይሰሩልንም፡፡ ለኢትዮጵያዊ የቀረበለት ከዝንጀሮ ቆንጆ መረጣ ነው፡፡
“ድንኩ አንድነት” እንደ ተለመደው በትዕግስቱ አወሉ የተወከለ ሲሆን በረዳትነት የተመደበለት ደግሞ አቶ ዮሐንስ አሰፋ ነው፡፡ አቶ ትዕግሰቱ በቴሌቪዥን በክርክር የሰንብት ክርክሩን አድርጎ ሄዶዋል፡፡ እኛም ተገላገልን፡፡ ባለፈው ድንኩ አንድነት የአንድነት ፓርቲ ውስጥ አባል ያልሆነ ሰው ለክርክር ቀረበ ብለን ትንሽ ተንጫጭተን ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ በረዳትነት የመጣው አቶ ዮሃንስ አሰፋው ለጫጫታ መነሻ የሚሆን አወዛጋቢ ግለሰብ ነው፡፡ ዮሐንስ በወረዳ 24 ውስጥ፣ ገዢውን ፓርቲ ወክሎ ወረዳውን ሲያምሰ የነበረ ነው፡፡ የሴራው ማጠንጠኛም አስራት አብርሃም ነበር፡፡ ፓርቲው አምኖበት በከፍተኛ ሃላፊነት ላይ ያስቀመጠውን ሰው የወያኔ ተላላኪ ነው እያለ ውንጀላ ሲያደርግ፣ በአስራት አብርሃም ደረጃ አሰተዋጽኦ የሚያደርግ ከየትም ቢመጣ ችግር እንደሌለብን አሰርደቼው ነበር፡፡ ለነገሩ ፓርቲውን ለመፍረስ ከሚያሴሩት ጋር በግልፅ እንደሚሰራ እያወቅን በዝምታ ያለፍነው የውስጥ አርበኛ ነው፡፡ አሁን ደግሞ በአሰራት አብርሃም ቦታ ወረዳ 24 ዕጩ ሆኖ የቀረበ ሲሆን ለትዕግሱቱ አወሉ ቡድን በቂ አማካሪ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ከዚህ የተሻለ ከትዕግሱቱ ጎን ማግኘት አጉል ነው የሚሆነው፡፡ ትዕግስቱም የልኩን አማካሪ ኢህአዴግም የሚመጥነውን ተቃዋሚ አግኝተዋል፡፡
ትዕግሰቱ የአንድነትን የፖሊሲ አማራጭም ሆነ ዝርዝር የኢህአዴግን የአፈፃፀም ክፍተት በተሟላ ይዞ ሊቀርብ እንደማይችል ማንም ያውቃል፡፡ በድፍረት ግን “የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ በአሰቸጋሪ ሁኔታም ቢሆን አንድነትን ምረጡ” የሚል ቃል እንዴት ሊወጣው እንደቻለ አልገባኝም፡፡ ከሁሉም ያስገረመኝ ደግሞ “ኢህአዴግ የመሬት ፖሊሲ የምቀይረው በመቃብሬ ላይ ነው” ይላል በሚል የሰጠው አስተያየት ነው፡፡ ኢህአዴግ ለስልጣኑ ዋልታና ማገር ያደረገውን የመሬት ፖሊሲ በመቃብሬ አለ የሚለው ትዕግሰቱ አወሉ እልህ ምላጭ ያስውጣል በሚል መፈክር ከራሱ ሌላ አንድ ሌላ ድምፅ ለማግኘት ያልቻለበትን አንድነት ፓርቲን ከምርጫ ቦርድ እና ከገዢው ፓርቲ ጋር እርሱ በሚያውቀው መስመር ተመሳጥሮ ድንክ ያደረገ ግለሰብ፣ ታንክና ባንክ ለማዘዝ የሚያሰችል ስልጣን የሚያስገኝን የመሬት ፖሊሲ በመቃብሬ ላይ ቢባል ምን እንደሚያስገርም አልገባኝም፡፡ ትዕግሰቱ አወሉ ታንክና ባንክ የሚያዝ መንግስት ቢሆን ብዬ ሳሰበው ዘገነነኝ፡፡
አቶ ትዕግሰቱ አወለ በክርክሮች ሁሉ ቀና ብሎ የቴሌቪዥን ካሜራ ለማየት ማፈሩ ተገቢ ሆኖ ባገኘውም የሚያፍር ከሆነ ለምን ቴሌቪዥን ላይ እንደሚመጣ ነው የማይገባኝ፡፡ አንድነት አማራጭ እንዳለው ሰንድ ማሳየት ይቻላል ያለው ትዕግሰቱ የአንድነትን ፕሮግራመ በቅጡ ማንበብና መዘጋጀት ሳይችል (የምርጫ ማኒፌስቶ እርሱ ሊያገኘው አይችልም፣ ቢሮ ዕቃ በጉልበት ሲዘርፍ በአባላት ጭንቅላት የሚገኝ እውቀት ግን በእርሱ እጅ አልገባም) የዛሬ አምስት ዓመት የተዘጋጀውን ሰትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ለዚያውም በመግቢያ ላይ የተፃፈውን ሰለ ዜጎች ሰደት የሚያወራውን ክፍል ለግብርና ክርክር ይዞ ሲቀርብ፣ “የድንኩ አንድነት” ተወካይ መሪ አቶ ትዕግሰቱ ለመዘጋጀት ፈተና የሆነበት ምን ያህል የውስጥ ሰላም አጥቶ እንደሚገኝ የሚያሳይ ነው፡፡ አንድነት በየትም ቦታ ዜጎች ወደ ከተማ መምጣት ችግር ነው ብሎ አያውቅም፡፡ ይልቁንም ችግር ከሆነ እንደ ችግር የሚያየው ዜጎች ከመሬት ጋር ተጣብቀው በገጠር እንዲኖሩ መደረጋቸወ ነው፡፡
ሌላው ያስገረመኝ የጥርሶቹ ማለቅ ሲሆን (መለስ መላጣ ማለት ይቻላል፣ መንካት ግን አይቻልም ባለው መሰረት)፣ እንዴት ነው አሁን ያለው የገንዘብ ፍሰት ለዚህ የሚሆን እንጥፍጣፊ የለውም ወይ? የሚል ጥያቄ ጭሮብኛል፡፡ ከዚህ በፊት ጥርሳቸውን ያስተከሉ መሪዎች በፓርቲው ገንዘብ ነው እያለ እርሱ ሲያወራ ስለነበር ነው፡፡ ለማነኛውም “ሞያ በልብ ነው አንድነትን ምረጡ” ያለው ትዕግሰቱ በግሌ የወረዳ 8 ነዋሪ ከራሱ በስተቀር አንድም ድምፅ እንዳያገኝ በማድረግ እንዲያዋርደው በማክበር ጥሪ አቀርባለሁ፡፡ በሰፈሩ ያሉት እድሮችና የትዕግሱ የማሪያም ፅዋ ማህበርም ይህን እንዲያስተባብሩ እና ትዕግሰቱ ከራሱ በስተቀር አንድም ድምፅ እንዳያገኝ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን የኢህአዴግ ኮካዎች ማህበራዊ ማግለል ወንጀል ነው ይሉታል፡፡ በትዕግስቱ ላይ ማህበራዊ ማግለል ወንጀል የሚሆንበት ህግ ካለ ለመማር ዝግጁ ነኝ፡፡ መቼም ትዕግሰቱን በመወከል ታዛቢ ይኖራል ብዬም አላምንም፡፡ በተጨማሪ የአንድነት ደጋፊዎችም ትዕግሰቱ ከራሱ ሌላ አንድም ሌላ ድምፅ እንዳያገኝ ጠንክረው መስራት ይኖርባቸኋል፡፡ ይህን ሳናደርግ ብንቀር ሌሎች ትዕግሰቱዎች ለዚህች ሀገር እየጋበዝን መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ አንድነት ዋንጫ የሚያነሳው ትዕግሰቱና የትዕግሰቱ ቡድን ድምፅ ሲያገኝ ሳይሆን እነርሱ ተገቢውን ውርደት ሲከናነቡ ነው፡፡
ኢድአን አቶ ግዑሽ  ገ/ሥለሴ እና ትዕግስቱ ዱባለ  በተባሉ አባላቱ ተወክሎ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ አቶ ግዑሽ ገ/ሰላሴ በ2002 ምርጫ ወቅት መድረክ ሞቅ ያለ የምርጫ ስራ ላይ እያለ “ኢድአን ከምርጫ ወጥቶዋል” በሚል መድረክን ያመሱ ግለሰብ ናቸው፡፡ በምርጫ ወቅት የገዢው ፓርቲ ተቃዋሚዎችን የሚያዳክምበት መሳሪያ ናቸው፡፡ ከምርጫ በኋላ እዚህ ግባ በሚባል ፖለቲካ ውስጥ ጉልዕ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አይታዩም፡፡ አቶ ግዑሽ ካቀረቡት ክርክር ነጥብ አድርጌ የያዝኩላቸው “ … እሰከ መገንጠል መብት የሰጠ መንግሰት፣ ለአርሶ አደሩ መሬትን እሰከ መሸጥ ለምን መስጠት ፈራ” የሚለው ነው፡፡ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት እሰከ መገንጠል ስለተሰጠ የተገነጠለ የለም በሚል የሚከራከረው ኢህአዴግ አርሶ አደሩ እሰከ መሸጥ የሚደርስ መብት ቢያገኝ በመሬቱ ተጠቃሚ ከሆነ አይሸጠውም የሚል መርዕ እንዴት ሊገባው አልቻለም የሚል ነው፡፡ ተዋዋሚዎች ትንሽ ከሚሏት የክርክር ደቂቃ ሁለት ደቂቃ ያገኘው የአቶ ግዑሽ ረዳት አቶ ትዕግሰቱ ዱባለ ያገኛትን ሁለት ደቂቃ በቅጡ የሚረባ ነገር ሳይናገር ላብ በላብ ሆኖ ወጥቶዋል፡፡ ከእንቅልፉ ድባብ ተቀስቅሶ በመናገሩ የተቸገረ ነው የሚመስለው፡፡ ኢህአዴግ የመጨሻውን ማጠቃለያ መስጠቱን ዘንግቶ ለኢህአዴግ ጥያቄም አቅርቧል፡፡ ለማነኛውም በማጭድ ምልክት ዘመናዊ የግብርና መሳሪያ በድጎማ ማቅረብ አማራጭ አድርጎ ያቀረበልን ኢድአን ከቁም ነገር የሚቆጠር አማራጭ ነው ብለን ልንወሰደው እንቸገራለን፡፡ እንኳን ሌሎች እንዲመርጧቸው ልንደግፋቸው አይደለም የራሳቸው “ከተመረጥን” የሚለው ድምፅ ለመመረጥ እንዳልተዘጋጁ የሚያሳጣ ነው፡፡
መድረክ ተወክሎ የገባው በአቶ ጥላሁን እንዳሻው እና በአቶ ሙላቱ ገመቹ በሚባሉ አባላት ሲሆን፡፡ ኢህአዴግም ቢሆን በዋነኝነት ሊከራከረው የገባው ከላይ እንደገለፅኩት ከመድረክ ጋር ብቻ እንደሆነ ያስታውቅ ነበር፡፡ መድረክ በመጀመሪያ ሰድስት ደቂቃ አንዱን ደቂቃ ጊዜው ትንሽ ነው በሚል ጉንጭ አልፋ ክርክር ጊዜ ያባከነ ሲሆን፤ በተጨማሪ መልስ በሌላቸው ህገመንግሰታዊ ድንጋጌዎችና ትርጉም ጊዜውን እንዳባከኑት ይሰማኛል፡፡ በእኔ ግምት በመሃል የተቆረጠ በሚመስል ሁኔታ አምሰት ደቂቃ የሚሞላ ሀሳብ አልሰማንም፡፡ ኢቲቪ ኢህአዴግን የመከላከል መብቱን ተጠቅሞ የቆረጠው ሃሳብ እንዳለ መገመት ይቻላል፡፡ መድረክ በቀጣዩ በነበረውን ዘጠኝ ደቂቃም ቢሆን ኢህአዴግ ላቀረበለት ጥያቄ መልስ በመስጠት፣ ለምሳሌ በሚል የአቶ ጥላሁን እንዳሻው ትውልድ አቅራቢያ ቦታዎች ላይ የሚገኙ የመሬት መፈናቀልና የመሰረተ ልማት እጥረትን በመዘርዘር ለክርክሩ የሚመጥን ነበር ለማለት የሚያስቸገር ሃሳብ ሲያቀርቡ ነበር፡፡ በ2002 አቶ ጥላሁን እንዳሻው በተመሳሳይ ርዕስ ተከራካሪ የነበሩ ሲሆን ይህን ልምድ ይዘው በተሻለ የመቅረብ እድሉ ቢኖራቸውም ሊጠቀሙበት አልቻሉም፡፡ ከመድረክ ክርክር ነጥብ የሚወሰድ ከሆነ በልማት ሰራተኛ ስም የተሰገሰጉት ካድሬዎች ጉዳይ ሲሆን ኢህአዴጎች ይህን ከሰራተኞቹ ጋር ለማጋጨት ሊጠቀሙበት የሞከሩ ቢሆንም በልማት ሰራተኛ ሰም በገጠር የሚንከራተቱት ሰራተኞች ይህን ተጨማሪ ያለፍላጎታቸው የሚሰጣቸው ሰራ እንደማይወዱት ለሚያውቅ የኢህአዴግ መንገድ የሚሳካ አይመስለኝም፡፡ በክርክሩ የመጨረሻ ተከራካሪ መሆን ያለውን ከፍተኛ የማጥቃት እድል በማያሰፈልግ ሁኔታ ከረዳታቸው ጋር የተካፈሉት አቶ ጥላሁን ረዳታቸውም ምንም አዲስ ነገር ሳይነግሩን ክርክሩም እንዲያበቃ አደርገውታል፡፡
በእኔ እምነት ኢህአዴግ አሁንም ቢሆን መንግሰት ሆኖ ያከናወናቸውን ስራዎች ይህን ማድረግ የማይችሉትን ተቃዋሚዎች መክሰሻ አድርጎ ለማቅረብ ሲሞክር ከመስማት የበለጠ አሳፋሪ ነገር የለም፡፡ ይህ ማለት ግን ተቃዋሚዎች በያዘው ስልጣን ሊያከናውን ያልቻለውን፣ በተለይ ደግሞ ባለፈው አምስት ዓመት በግብርና ዘርፍ አሳካዋለሁ ብሎ ያላሳካቸውን ነጥቦች አንሰተው ደካማ መሆኑን ማሳየት አይችሉም ማለት አይደለም፡፡ ኢህአዴግ አሁን የሚሞግተን የግብርና ፖሊሲና ስትራቴጂ፤
·         ባለፉት 24 ዓመታት ይህችን ሀገር በምግብ እራሷን እንድትችል ባለማድረጉ የሚከሰሰበት ዋነኛ ነጥብ ነው፡፡ በሃያ አራት ዓመት አሁንም አዝማሚየ በሚባል ሁኔታ መሆናችን ተቀባይነት የለውም፤
·         በኢትዮጵያ ሀገራችን በገጠር የሚኖረው ህዝብ ባለፉት 24 ዓመታት ከነበረበት 85 ከመቶ ወደ 83 በመቶ ብቻ ነው ዝቅ ሊል የቻለው፡፡ ይህ ደግሞ በአፍሪካ ደረጃ ከተሜነት 50 ከመቶ በላይ በደረሰበት ወቅት እጅግ አሳፋሪ ሲሆን፤ ይህን እንደ ነጥብ አንሰቶ የሚሞግት ያለመኖሩ ከዚያ ይልቅ የገጠሩ ህዝብ ወደ ከተማ እየፈለሰ ነው የሚል ቅሬታ የሚያሰሙ ተቃዋሚዎች መኖራቸው የሚያሳዝን ነው፤
·         የከተሜነት ያለመስፋፋት፣ ዜጎች በገጠር ከመሬት ጋር ተጣብቀው እንዲኖሩ እያደረገ ያለው ደግሞ፤ ኢህአዴግ በውሸት ኤኮኖሚያዊ ምክንያት የሚለው ነገር ግን ፖለቲካው ምክንያት የሆነው መሬትን ህገመንግሰት ውስጥ መደንቀሩ ነው፤ ይህን ፖለቲካዊ የሆነ ጉዳይ ኤኮኖሚያዊ ነው ብለው ምንአልባት ከፓርቲው አቋም ውጭ የግብርና ሚኒሰትሩ ሃሳብ ሲሰነዝሩ የሚሞግታቸው አላገኙም፤
·         ኢህአዴግ መሬት መሸጥ መለወጥ የሚለውን ሃሳብ ሲያነሳ መሬት የሚገዙ ጥቂት የሚላቸው ዜጎች መሬቱን የሚገዙት ምርት ለማምረትና ለማትረፍ በዚህም ሀገራችንን በምግብ እህል ራሰን ከመቻል አልፎ ኤክሰፖርት ለማድረግ መሆኑ ቀርቶ ለቀብራቸው መሬት የሚገዙ ያሰመስለዋል፡፡ መሬቱን ሸጦ የሚፈናቀል አርሶ አደር ደግሞ በሌሎች አገልግሎት ዘርፍ የማይገባ፣ ከመሬት ጋር ብቻ ተጣብቆ እንዲኖር የተፈረደበት ያሰመስልብናል፡፡
ባጠቃላይ በእኔ እምነት የ1997 የግብር እና የገጠር ልማት ስትራቴጂ ክርክር በድጋሚ ይቅረብልን ብዬ ማጠቃለል መርጫለሁ!!!

ቸር ይግጠመን!!!!!!!

No comments:

Post a Comment