Tuesday, January 26, 2016

የአባይ ፀሃዬ የለውበትም የት ያደርስ ይሆን?



ወዳጆች መቼም የዚህ ሀገር ነገር ግራና ቀኙ ጠፍቶዋል እንበል እንዴ? የፌዴራል ሹሞች የበታች ሹሞችን በፖለቲካ ውሳኔ በሚመጡ ጉዳዮ ጭምር እጃቸውን ወደታች መቀስር ጀምረዋል፡፡ ይህ ጉዳይ አዲስ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊትም አማርኛ ተናጋሪዎች ተለይተው ከመኖሪያቻው ሲፈናቀሉ፣ ተጠያቂ የተደረጉት “ጥቂት ኪራይ ስብሳቢ” የተባሉ የበታች ሹሞች ናቸው፡፡
አሁን ደግሞ የአዲስ አበባና በዙሪያ ያሉ ከተሞች የተቀኛጀ ማስተር ልማት ይዞት የመጣው ጦስ በቀላሉ የሚገላገሉት አይመስልም፡፡ ጎምቱ የሚባሉት ባለስልጣናትም ቢሆን ስህትት ከመስራት የሚያግዳቸው ኃይል ሊገኝ አልቻለም፡፡ የዛሬ ፅሁፌ መነሻ የሆነው ደግሞ አቶ አባይ ፀሃዬ በሚዲያ የሰጡት የመከላከያ መልስ እጅግ ስለአስገረመኝ ነው፡፡
ባጠቃላይ መንግሰት የሚባለው አካል እንደ አካል ይህ ጦሰኛ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ግራ አጋብቶታል፡፡ ግራ ተጋብቶ ግራ እያጋባን ይገኛል:: የአዲስ አበባ መሰተዳደር በግሉ ማስተር ፕላኑን ተግባራዊ ያደርጋል የሚል ዜና የሰማነው የኦሮሚያ/የኦህዴድ ሰራ አስፈፃሚ የተቀናጀ ማስተር ፕላኑን ተግባራዊ እንዳይሆን ውድቅ ባደረገ ማግስት ነው፡፡ አዲስ አበባ በተናጥል ማስተር ፕላኑን ተግባራዊ ሲያደርግ በዙሪያ ያሉት ከተሞች ላይ የሚያሰከትለው በጎም ሆነ አሉታዊ ተፅህኖ እንዴት እንደሚታይ የነገረን የለም፡፡ ለማነኛውም ይህን እናቆይ እና ለፅሁፌ መነሻ ወደ ሆነው ጉዳይ ልግባ፡፡
በእኔ እምነት በኦሮሚያ አካባቢ ለተነሳው ንቅናቄ ዋነኛው ነገር ቆስቋሽና አቀጣጣይ የነበሩት አቶ አባይ ፀሃዬ ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ኦቶ አባይ ፀሃዬ እጅ እና እግር የለሌለው ክስ በየደረጃው ወደሚገኙት የኦሮሞ ካድሬዎች ላይ አቅርበዋል፡፡ ወደዚህ ጉዳይ በዝርዝር ከመግባቴ በፊት ግን በዚህ ጦሰኛ ማስተር ፕላን ነገር ቆስቋሽና አቀጣጣይ ያልኩበትን ምክንያት ማስረዳት ይኖርብኛል፡፡
አቶ አባይ ፀኃዬ በአሁኑ ሰዓት ያላቸው ስልጣን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በፖሊሲና ጥናት ጉዳዮች ማማክር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እንደሚታወቀው ይህ ስልጣና በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የስልጣን ዘመን የነበረ አይደለም፡፡ ኦቶ አባይ ይህንንም ስልጣናቸውን የገለፁበት መንገድ ጠብ የሚፈልግ ካለ ወይም ከተገኘ ለጠብ የሚመች ነው፡፡ “ጠቅላይ ሚኒስትር የእለት ተእለት ስራ ስለሚበዛባቸው በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ እንደንስራ ተመደብን” ሲሉ በመጀመሪያ ያድረኩት የህገ መንግሰቱን አንቀፅ 79 መመልከት ነበር፡፡ ይህ ህገ መንግስት ካልተቀየረ በሰተቀር የፖሊሲ ጉዳዮችን ሸክም የሚወስድላቸው ሌላ ሰው መድበው እርሳቸው በሌላ የእለት ተዕለት ስራ መጠመድ አይገባቸውም ነበር፡፡ አቶ አባይ ፀሃዬ በዚሁ ስልጣናቸው መነሻ ባለፈው ሁለት ዓመት ግድም በኦሮሚያ በተለይ አምቦ አካባቢ በተነሳው ግርግር ማግስት ቆም ብሎ የነበረውን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ጉዳይ ከምርጫው በኋላ በአሸናፊነት መንፈስ ከኦህዴድ ካድሬዎች ጋር ባደረጉት ውይይት “ይህንን ፕላን በግዳቹ ትተግባራለችሁ ብለዋል የሚለው ነው”፤ ይህን አይሉም ሊባል የማይችለው የኦህዴድ ባለስልጣናትም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የነበራቸው አቋም ተግባራዊ ለማድረግ ምን እናድርግ? የሚለው እንጂ ተግባራዊ አናደርግም የሚል ሰለ አልነበረ ነው፡፡
ይህች በግድ የምትል ቃል እልህ አስገብታ ይህን ሁሉ እሳት የጫረች እንደሆነች መገንዘብ አያሰቸግርም፡፡ ከአቶ መለስ ዜናዊ እልፈት በፊት ኦሮሚያ በእጅ አዙር ይቆጣጠሩት እንደነበር፤ ለዚህም እንደ አለማየሁ አቶምሳ እና ሙክታር የመሰሉ የመለስ ቀኝ እጆች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ ሉሎችም አሉ፡፡ ከመለስ ዜናዊ ሞት በኋላ የኦሮሚያ ባለስልጣናት ከህውሃት ሰዎች ጋር ትከሻ መለካከት እንደጀመሩ ብዙ ማሳየዎች አሉ፡፡ አቶ አባይ ፀሃዬ ከመለስ ሞት ማግስት ጀምሮ ከአንገታቸው ቀና ካሉት ሰዎች አንዱ ቢሆኑም በኦሮሚያ ሰፈር የተፈጠረውን ትከሻ መለካካት ያጤኑት አይመስለኝም፡፡ይህን ትከሻ መለካካጽ ልብ ብለውት ቢሆን ኖሮ “በግዳችሁ ትተገብራላችሁ” የምትለው ጦሰኛ ቃል አትውጣም ነበር፡፡ በግድ ማርም ቢሆን አይጥምም!!!
በእኔ እምነት አሁን በኦሮሚያ አካባቢ የተነሳው በዋነኝነት “እምቢ ማስተር ፕላን” ተቃውሞ በኦሮሚያ በሚገኙ ኦህዴድ ካድሬዎች ቀጥተኛ ድጋፍ እንዳለው ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ድጋፋቸውን የሚሰጡበት መንገድ የተለያየ ቢሆንም፡፡ ኦህዴድ ዛሬ እንደ ከዚህ ቀደሙ በኢህአዴግ በሚቀመጥለት አቅጣጫ የኦህዴድ ካደሬዎችን አፍሶ እስር ቤት ማሰገባት የሚችል አይመሰለኝም፡፡ ዶክተረ ነጋሶ በአንድ ወቅት እንደነገሩን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ካድሬዎችን አባረው እና እስር ቤት አስገብተዋል፡፡ የዚያን ጊዜው ኦህዴድ አሁን ያለ አይመስለኝም፡፡ የአሁኑ ኦህዴድ ያለው እድል ካድሬዎቹን ተለማምጦ በስልጣን መቆየት ነው የሚኖርበት፡፡ ሰለዚህ አቶ አባይ እንዳሉት በግድ መተግበር ሳይሆን ማስተረ ፕላኑን መሰረዝ ነው፡፡
አቶ አባይ ፀሃዬ እራሳቸውን ሲቀጥልም እናት ፓርቲያቸውን ሕውሃትን ለመከላከል ብለው የሰጡት ምለሽ በእርግጥ ሌላ ዙር ቀውስ የሚጠራ ነው፡፡ ይህ የአባይ ፀሃዬ የለውበትም መልስ የት እንደሚያደርስ ግን አላውቅም፡፡ መልሳቸው ባጠቃላይ አሁን በኦሮሚያ አካባቢ የተነሳው ንቅናቄ መንስዔ “በኦሮሚያ የተለያየ እርከን የሚገኙ የኦህዴድ ሹሞች ሌቦች በመሆናቸው፣ ህዝቡ የሚጠይቀውን የመልካም አስተዳድር ምላሽ መሰጠት ባለመቻላቸው፣ ወዘተ” የሚል ነው፡፡ በዚህ የመከላከያ መልሳቸው በቀጥታ ላለመንካት የፈለጉት የኦህዴድ ከፍተኛ ሹሞችን ብቻ ነው፡፡ በእኔ እምነት ከወረዳ እሰከ ዞን ብሎም ክልል ድረስ ያሉት ሹሞች ሃላፊነት የተሰጣቸው በኦህዴድ ከፍተኛ ሹሞች ነው፡፡ በክስ ውስጥ ሊዘሏቸው ቢፈልጉም የበታቾቻቸውን መከላከል ወይም አብረው መከሰሳቸው መረዳት ግድ ነው የሚሆነው፡፡ የኦህዴድ ባለስልጣናት አቶ አባይ ፀሓዬን የሚጠይቁት ጥያቄ ያለ ይመስለኛል፡፡ ለማነኛውም አቶ አባይ ፀሓዬ ከግላቸው አልፈው ህውሃትም ሆነ ፌዴራል መንግሰት አሁን በተፈጠረው ጉዳይ አያገባውም ጉዳዩ የኦህዴድ እና የኦህዴድ ሾሞች ብቻ ነው ብለው እጃቸውን ለመታጠብ ሞክረዋል፡፡ ይህ በፍፁም የሚሳካ አይመስለኝም፡፡
በእኛ አረዳዳ ኦህዴድ የሚባል ፍጡር በኢህአዴግ በሚመራው ስርዓት ውስጥ የተለይ ነው ብለን አናምንም፡፡ ኦህዴድ የወሰዳቸው የግል ውሳኔዎች አሉ ብለን አናምንም ስለዚህ ሁሉም የኢህአዴግ አመራር አባሎች እና የፌዴራል መንግሰቱ ባለስልጣናት በዚህ ውሳኔ ውስጥ እንዳሉበት እናምናለን፡፡ ሰለዚህም አሁን አቶ አባይ ፀሃዬ ያቀረቡት መከላከያ ተቀባይነት የለውም፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት አንዳንዶቻችንም እንደምንስማማው የተቀናጀ ማስተር ፕላን በድፍኑ ክፋት የለውም፤ ክፋቱ የመጣው “በግድ ትተገብራላችሁ” የሚለው ማስፈራሪያ እና ጥቅም ካለው ማስገደድ እና ማስፈራራት ምን አመጣው? የሚለው እንደምታ ነው፡፡ ሰለዚህ ማርም ቢሆን በግድ ይመራል የምንለው!!!
በነገራችን ላይ ተጠያቂነት የሚባለው ነገር አቶ አባይ ፀኃዬ ከሃያ አራት ዓመት የስልጣን ዘመን በኋላም እንዴት ሊረዱት ተሳናቸው? ለምን ይህን የሚያክል ሀገራዊ ውሳኔ ወደ ወረዳና ዞን ሹሞች ሊወረውሩት ፈለጉ? ሌላው ደግሞ በኦሮሚያ አለ የሚሉት “መሬት መሸጥ፣ የመልካም አስተዳድር እጦት፣ ሙስና፣ ወዘተ እኛን አይመለከትም፡፡ ሕዝቡ የጠየቀው ትክክለኛ ጥያቄ ነው መልስ መስጠት ሲያቅታቸው አባይ፣ ሕውኃት፣ ፌዴራል” ይላሉ ብሎ ከሃላፊነት መሽሽ ይቻላል ወይ?ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ በእኔ እምነት አሁንም ቢሆንም ማስተር ፕላኑ ተተግብሮ ውጤት ቢገኝ ጭብጨባውን ለመውሰድ ወደኋላ እንደማትሉት ሁሉ በዚህ መነሻ ለተነሱት መሰረታዊ የመልካም አስተዳድርና የነጻነት ጥያቄ መልስ መስጠት ካቃታችሁም ተጠያቂነቱንም አብራችሁ መሆን ይኖርበታል፡፡ በመጨረሻ አቶ አባይ ፀሃዬ የኦህዴድ የበታችና የመካከለኛ አመራር ላይ ክስ አቅርበዋል፡፡ እነዚህ የኦህዴድ አመራሮች በድርጅት መስመር ሄደው ይህ ክስ በይፋ ይነሳልን፣ ስናስፈፅም የነበረው ከፍተኛ አመራሩ የሰጠን መመሪያ ነው ማለት አለባቸው፡፡ ካለበለዚያ ደግሞ በጋራ ጥያቄያቸውን በኢህአዴግ ፎረም ላይ አቅርበው ሊገማገሙበት ይገባል፤ የአቶ አባይ የግል ከሆነም ግለ ሂስ እንዲያወርዱ ማድረግ አለባቸው፡፡ መቼም ኢህአዴግም ሆነ ኦህዴድ ስልጣን መልቀቅ ስለማይወዱ ብዬ ነው ከስልጣን ይውረዱ ያላልኩት፡፡ ስልጣኑን በግድ እስኪለቁ ግለ ሂስ ያውርዱ ለማለት ነው፡፡
ቸር ይገጠመን!!!


Sunday, January 17, 2016

የዶ/ር መረራ የቡዳ ፖለቲካ እና መቀበል ያቃተው መራራ እውነት



ዶክተር መረራ “የኢትዮጵያ የታሪክ  ፈተናዎች እና የሚጋጩ ሕልሞች” በሚል አዲስ መፅኃፍ አስነብቦናል፡፡ በአንድ ጋዜጣ ላይ የዶክተር መረራ ከዮኒቨርሲቲ መሰናበት ያመጣው አንድ በጎ ጎን መሆኑን አንብቤያሁ፡፡ እኔም በዚህ እስማማሀለሁ፡፡ ብዙ የሀገራችን ፖለቲካኞች ጋዜጠኛ መቅረፀ ድምፅ ይዞ በሚጠይቃቸው ጥያቄ መልስ ከመስጠት የዘለለ ብዕርና ወረቀት አገናኝተው የሚያምኑበትን የፖለቲካ መስመር እና በግላቸው ያላቸውን ምልከታ ማካፈል ይቸግራቸዋል፡፡ የዶክተር መረራ ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ ለንባብ ያበቃው መፅኃፍ ጋር ይህን መፅኃፍ ሲጨመርበት ቢያንስ በፖለቲካ መስመሩ ላይ ግልፅ መረዳት እንዲኖረን ያደርጋል፡፡ ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ ግን በዋነኝነት ዶክተር መረራ አውቆ የሚዘላቸው አንድነትን የሚመለከቱ ጉዳዮች ሲሆኑ እግረ መንገዴን ከመፅኃፉ የተረዳሁትን ለማካፈል ጭምር ነው፡፡
ዶክተር መረራ በእኔ መረዳት ዛሬም መኢሶን ነው፡፡ በተቻለው መጠን መኢሶን በመከላከል እና ዋናውን ጥፋት በደርግና ኢህአፓ ትከሻ ላይ ሲጭን ነው የሚታየው፡፡ መቀበል ያቃተው መራራው እውነት መኢሶን ከደርግ ጋር ተባብሮ የደርግን ጡንቻ ማፈርጠሙ ከዚያም ተከትሎ ለተፈጠረው ጥፋት ድርሻውን ማንሳት እንዳለበት በግልፅ ሊያሳየን አለመቻሉ ነው፡፡ ድርሻ መውሰድ ስል ጥፋትን አምኖ ይቅርታ መጠየቅ እና ለእርቅ ዝግጁ መሆን ማለቴ ነው፡፡ በእኔ የፖለቲካ እሳቤ ውስጥ ሂሳብ ማወራረድ የሚል የለም፡፡
ዶክተር መረራ አሁን ኢትዮጵያ የምንላትን ሀገር ቅርፅ ያሲያዙትን ምኒሊክን ጀግንነት በጥያቄ ምልክት ውስጥ በማስገባት እና ከሶማሊያ ጋር አብረው ሀገር ሲወጉ ነበር የሚባሉትን “ዋቆ ጉታን” ጀግና እያደረገ በአክራሪ ኦሮሞ ብሔርተኞች ድጋፍ የመሻት ፍላጎቱን በመፅሃፉ ውስጥ ታዝቢያለሁኝ፡፡ ዶክተር መረራ ወደ መሃል እንምጣ እያለ ጥግ ጥጉን የሚሄድ መሆኑን ማሳያም ጭምር ነው፡፡ እንደሚታወቀው የዶክተር መረራ አብረን እንስራ እስከ “ግንባር” ብቻ ነው፡፡
የዶክተር መረራ የቡዳ ፖለቲካ ብሂል በሁሉም ጉዳይ ችግሮችን ወደሌሎች ማላከክ ባለብን አባዜ ጥሩ ገላጭ ቢሆንም፤ የዚህ የቡዳ ፖለቲካ ሰለባ ዋነኛው ግን ዶክተር መረራ መሆኑ ብዙ ማሳያ ማቅረብ ይቻላል፡፡ በተለይ መድረክ የሚባለውን ስብስብ አንዴም እንኳን ለሚፈጠሩት ችግሮች ኃለፊነት የሚወሰድ አካል አድርጎ አያቀርበውም፡፡ ዶክተር መረራ በሚመራው ድርጅት ውስጥም ያለውን ችግር ለማየት እና ለማስተካከል አይፈልግም፡፡
የዶክተር መረራ “የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎች እና የሚጋጩ ሕልሞቸ” የሚለው መፅኃፍ ይህች ሀገር ከፈታና የምትወጣው እና ህልሞች ቅዠት ሳይሆኑ አውን የሚሆኑት “የኦሮሞ ልኢቃን” እና “የአማራ ልሂቃን” የያዙትን ፅንፍ ሲተዉ እና መሃል መንገድ ላይ ሲገናኙ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ እኔ በፍፁም ያልገባኝ “የአማራ ልሂቅን” የሚባለው ፍረጃ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነት የሚያቀነቅኑት ለማለት ከሆነ ሌሎችም አማራ ያልሆኑ በዚህ ረድፍ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ወይም ደግሞ አማራ ማለት ኦሮሞ ያልሆነ ሁሉ ማለት እንደሆነ በግልፅ ሊነግረን ይገባ ነበር፡፡ ወጣም ወረደ እኔ በመሪነት ሁሉ የተሳተፍኩበትን አንድነት ፓርቲን በአማራ ልሂቀን የሚመራ ተብሎ ተፈርጇል፡፡ ስለዚህ ይህ መሰረታዊ ስህተት ሀገራችን ከፈተና እንድትወጣ የታዘዘላት የዶክተር መረራ መድሃኒት እንደማይሰራ የሚያመላክት ነው፡፡
ዶክተር መረራ የቡዳ ፖለቲካው ሰለባ መሆኑን በደንብ የሚያሳየው “ለአንድነት ሆዴ መቁረጥ የጀመረው፤ በ2205 ክረምት የድጋፍ ማሰባሰቢያ ስብሰባዎችን በአሜሪካ ለማካሄድ ተሰማምተን ከሄድን በኋላ እነ ግርማ ሠይፉ ሙሉ በሙሉ ባልገባኝ ምክንያት የጋራ እንቅስቃሴ እንዳናደርግ ባደረጉ ጊዜ ነበር፡፡ በጊዜው ለአንድነት መሪ ለነበረው ለዶ/ር ነጋሶም ምሬቴን ገልጨ ነበር፡፡ ምሬቴ ለዶ/ር ነጋሶም የገባው ይመስለኛል፡፡ ለማረም ግን አልቻለም፡፡….”  የሚል ክስ በገፅ 147 ላይ አስፍሮዋል፡፡ ተመሳሳይ ክስ በሌለሁበት በመድረክ ስብሰባ ላይ ሰሜን ጠርቶ እንዳቀረበ ሰምቻለሁ፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ የድጋፍ ማሰባሰቢያ ስብሰባዎችን በአሜሪካ ለማካሄድ ተሰማምተን የሚለው አውነት አይደለም፡፡ እኔም እርሱም በግላችን አሜሪካ እንደምንሄድ ሲታወቅ ከተቻለ በጋራ ስብሰባ ብናደርግ የሚል ሃሳብ አንሰተን ሙከራ እንድናደርግ በሚል “አዲስ ቪው ሆቴል” ተገናኝተን ተነጋግረናል፡፡ ሙከራ ደግሞ ሊሳካም ላይሳከም ይቸላል፡፡ ይህን ዶክተር ነጋሶ ለአንድነት ድጋፍ ሰጪዎች ገልፀውላቸዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ዶክተረ መረራ ዘወትር እንደሚያደርገው “የኦሮሞ ኮሚኒቲ” ለብቻው ሰብሰቦ ገንዘብ ያሰባሰብ ነበር፡፡ ይህ ገንዘብ ለመድረክ የሚገባ አይደለም፡፡ ከዚህ በሚተርፈው ጊዜ የአንድነት ድጋፍ ሰጪዎች ስብሰባ እንዲጠሩ ጥያቄ ቀረበላቸው፡፡ የአንድነት ድጋፍ ሲጪዎች በጣም በሰለጠነ ሁኔታ ስብሰባ አድርገው በቂ ዝግጅት ሳይደረግ ድንገት የዚህ ዓይነት ስብሰባ መጥራት እንደሚቸገሩ አስታወቁ፡፡ በወቅቱ ደግሞ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” በሚል አንድነት ለጀመረው ዘመቻ ድጋፍ እያሰባሰቡ ስለሆነ ተጨማሪ ሌላ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ለማድረግ ጊዜ እንደሚወስድባቸው ምክንያታቸውን ገለፁ፡፡ ይህን ለዶክተር ነጋሶም፣ለዶክተር መረራም ተነግሯል፡፡ ዶክተር መረራ ግልፅ ሆኖ ያልገባው ምን እንደሆነ አልገባኝም፡፡ የኦሮሞ ኮሚኒቲን ሰብሰቦ ለድርጅቱ ገቢ እየሰበሰበ፣ የአንድነትን ለመድረክ አድርጉት የሚለውን ዝግጅት ያልተደረገበትን ጥያቄ አንቀበልም ማለት ለምን እንዳሰከፋው አላውቅም፡፡ በግሌ ለመድረክ ገቢ ለመሰብሰብ ዝግጁ መሆኔን በተደጋጋሚ ገልጨለት እያለሁ ግን ለምን ሊከሰኝ እንደፈለገ አላውቅም፡፡
ሌላው ዶክተር መረራ በመድረክ ውስጥ አነድነትን የአማራ ወኪል ለማድረግ የሚሰራውን ሸፍጥ (ኦፌኮ በኦሮሚያ፤ አረና በትግራይ፤ የፕ/ሮ በየነ ድርጅቶች በደቡብ) መታገል ሳይችል “አንድነት ከመድረክ ካልወጣሁ” ብሎዋል በሚል ይከሰናል፡፡ ይህን ሸፍጥ ግልፅ የሚያደርገው መድረክ በ2007 ምርጫ አንድም ዕጩ በአማራ ክልል ያለማቅረቡ ነው፡፡ እውነቱ አንድነት እንደ ፓርቲ ከመድረክ የመውጣት ጥያቄ አንስቶ አያውቅም፤ በግለሰብ ደረጃ የመውጠት ፍላጎት ያላቻው የሉም ማለት አይቻልም፡፡ አሁን ከመድረክ ጋር ለመስራት ሽር ጉድ የሚለው ሰማያዊ ፓርቲ መስራቾች ከአንድነት የወጡበት ምክንያቱ አንዱ የመድረክ ጉዳይ ነበር፡፡ አንድነት የነበረው ጥያቄ መድረክ የእውነት “ግንባር” ወይም “ውህድ” ፓርቲ ይሁን ነበር ጥያቄው፡፡ በግልፅ ዶክተር መረራ የውህደት ተቃዋሚ ሲሆን ሁሉም የመድረክ አባል ድርጅቶች አንድነት ላይ ያላቸው የጋራ ጥያቄ የገንዘብ ምንጫችን ይዋሃድ የሚል ነበር፡፡ በመጨረሻም አንድነት “በሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” በጀመረው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ከኢህአዴግ እኩል የተረበሹት የመድረክ አመራሮች አንድነትን ከመድረክ አግደው፣ እንደ ኢህአዴግ ይቅርታ ካልጠየቀ አይገባም ሲሉ የአንድነት አባላት ደግሞ መድረክ ሲታዘል ተንጠልጥሎ የቀረ ሰለሆነ ከጫንቃችን ይውረድ ብለው ወስነዋል፡፡ ይህ ደግሞ ተገቢ ውሳኔ ነበር፡፡
አንድነት ከመድረክ መልቀቅ ብዙም ሳይወራ አንድነት በሁለት ሺ ሰባት ምርጫ ላይ በያዘው ግልፅ አቋም መነሻ በስርዓቱ እንዲፈርስ ሲወሰን ከመድረክ ባንወጣ አንድነት ሳይፈርስ እንደሚቆይ እንረዳለን፡፡ ውሳኔያቸን ግን አሁን መድረክ እና አባል ድርጅቶቹ ባሉበት አቋም በፓርቲ ሰም ከመኖር ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ባሳየነው ቁርጠኝነት የበለጠ እንደሰታለን፡፡ አንድነት ከመድረክ ወጥቶም በግዛቸው ሸፈራው መሪነት ቢቀጥል መንግሰት ይህን አሳፋሪ እርምጃ አይወስድም ነበር፡፡ ምክንያቱም ባለበት የሚረግጥ ፓርቲ ማንም አይፈራውም፡፡ ግብ አስቀምጠን የምንሄድበትን አውቀን ስንሄድ ነው ፈተናው የመጣው፡፡ ዶክተር መረራ እንደፃፈው አንድነት የፈረሰው ከባለራዕይ ወጣቶች፣ ከሀረና፣ ከኦፌኮ፣ ወዘተ በመጡ አምስተኛ ረድፈኞች አይደለም፡፡ ከተለያየ ፓርቲ ወጥተው በተለይ ከብሄር ፓርቲ ለቀው አንድነትን የተቀላቀሉ ወጣቶች አንድነት ዶክተር መረራ እንደሚለው የአማራ ልሂቃን ሳይሆን የሁሉም ቤት መሆኑን በመረዳታቸው ነው፡፡ ይህን መራራ እውነት ደክተር መረራ መቀበል የግድ ነው፡፡ አንድነት የሁሉም ቤት መሆኑ ያስፈራው መንግሰት ያለምንም አፍረት አንድነትን ለማፍረስ የተነሳውም በተለይ በኦሮሚያ ስናደርገው የነበረው ያልተጠበቀ ንቅናቄ ጭምር ነው፡፡ አንድትን ለማፍረስ የተሰለፉት ሆዳሞች ደግሞ ከሁሉም ሰፈር የተሰበሰቡ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ የድርጅት ስራችን ክፍተት መሆኑን እናምናለን፡፡
በመጨረሻ ዶክተር መረራ የአምቦ ወጣቶች እሰኪነግሩት ተሸፍኖበት የነበረው አውነት “የከብት ሌባን የሚጠብቀው ባለቤቱ ነው፤የኮሮጆ ሌባን የሚጠብቀው ህዝብ ነው፡፡” የሚለው ነው፡፡ አንድነት ፓርቲ በ2007 ምርጫ እሳተፋለሁ ሲል በአደባባይ የተናገርነው “ምርጫ ቦርድን ቁጥር ደማሪ እናደርገዋለን” የሚል ነበር፡፡ አንድም ምርጫ ጣቢያ ላይ ድምፁን የሚጠብቅ ህዝብ ካለሰለፍን ብንሰረቅም አንጮህም ብለን ተነሰተን ነበር፡፡ አሁንም ዶክተር መረራ ዘግይቶም ቢሆን እንደተረዳው የኮሮጆ ሌባን ለመጠበቅ የሚቆም መረጫ በሌለበት ምርጫ ፌዝ ነው፡፡ ለመምረጥ የተመዘገበ፤ ለሚደግፈው ድምፅ የሚሰጥ፣ የሰጠውን ድምፅ በትክክል የሚቆጥር ህዝብ ሲኖር ምርጫ ወደዲሚክራሲ መሸጋገሪያ ይሆናል፡፡ ይህ እንዳይሆን የሚከለክል መንግሰት ደግሞ በሌላ መንገድ ወንበሩን ለመልቀቅ መረጧል ማለት ነው፡፡
ቸር ይግጠመን!!!

Monday, January 4, 2016

ዝምታ ሰላም አይደለም!! ፕሮፓጋንዳም እድገት አይሆንም!!!




ሰሞኑን በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ተሳትፎ የሚያደርገው ሰው ጤና መሆኑን መጠራጠር የግድ ብሎኛል፡፡ አንዱ ውጭ ሀገር ሆኖ እንደእርሱ ካላቅራራህ ይለኛል፡፡ ሌላው ማንነቱ እንዳይታወቅ መሸጎ እየፃፈ ይፎክርና እንደ እኔ ፎክር ይለኛል፡፡ ለማነኛውም ሁላችንም እንደየ አቅማችን እና ችሎታችን፣ ምን አልባትም ድፍረታችን ያህል ለምናደርገው የነፃነት ትግል ክብር ብንሰጣጥ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ፈሪ መሆንም እኮ መብት ይመስለኛል፣ ሰው ለምን ትፈራለህ ለምን ይባላል!! ባይሆን ፈሪ እንደ እኔ ፍሩ ሲል ነው አይ ሊባል የሚገባው፡፡ በእኔ እምነት የዚህች ሀገር የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሊወሰን የሚገባው በሃሰብ ክርክር እና በዚሁ በሚገኝ የበላይነት ብቻ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህም ነው ሁሉም የማይሰማማበት ቢሆን እንኳን የእኔ ሃሳብ ይህ ነው ብዬ ለመግለፅ የምወደው፡፡ ይህን አካሄድ ያለመውደድ መብት ቢሆንም የእኔን ውደድ ብሎ ማስገደድ አይቻልም፡፡ ይህን ከሰሞኑ የፌስ ቡክ የፅሁፍ ምልልሶች መነሻ አድርጌ ካልኩኝ፤ ለዛሬ ፅሁፍ መነሻ ያደረጉት ደግሞ ለአንድ ሳምንት በምክር ቤት ወጉ እንዳይቀር “ሲመከርበት” የከረመው የሁለተኛው ዙር የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እና የሰሞኑ “የተቀናጀ ማስተር ፕላን እንቢ” በሚል መነሻ በኦሮሚያ አካባቢ የተቀሰቀሰው ንቅናቄ፣ በጎንደር የተፈጠረው ግጭት እንዲሁም ድርቅ መነሻ ሆኖ የተከሰተው ርሃብ እንደምታ ምን ሊመስል እንደሚችል በአጭሩ የግል እይታዬን ለማስቀመጥ እሞክራለሁ፡፡
ገዢዎቻችን አፍረት የሚባል ነገር እንደሌለባቸው የሚያስታውቀው የመጀመሪያውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በስኬት ማጠናቀቃቸውን ሲነግሩን አፋቸውን አንኳን ጎልደፍ ያለማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን በምክር ቤት ውስጥ ለተሰበሰቡት እጅ በማውጣት ደሞዝ ለሚከፈላቸው ሳይሆን በሚዲያ ለሚከታተላቸው ህዝብም ያላቸውን ንቀት የሚያሳይ ነው፡፡ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽኝ ዕቅድ በዋነኝነት ከተቀመጡት ግቦች የተሳከ የሚባል አንድም ነገር የለም እንዳይባል (ጥራት በሌለው ትምህርትና ጤና የቁጥር ስኬት መኖሩ አይካድም)፣ ከዚህ በስተቀር መብራት 10 ሺ ሜጋ ዋት ብለው ሶሰት ሺ ያለመድረሳቸው፣ ባቡር 2395 ኪ.ሜ ታቅዶ እሰከ አሁን ስራ ያልጀመረውን የአዲስ አበባ ድሬዳዋን ብንወስድ 700 ኪሎ ሜትር እንደማይሞላና ይህም ዕቅዱ የውሸት ህዝብ ማማለያ እንደ ነበር ነው፡፡ በግብርና ዘርፍ በብዙ ሚሊዮን የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል የተባለው እቅድ የተያዘለት፣ የተገላቢጦሽ መንግሰት በውጭ ምንዛሬ ሰንዴ መግዛት ውስጥ መግባቱ ይታወቃል፡፡ ባለፈው አምሰት ዓመት ከፍተኛ የእድገት ምጣኔ አስመዝግቦዋል የተባለው ግብርና ነው ብለው ሚሊየነር አርሶ አደር ብሎ መሸለሙን ሳይጠናቀቅ በድርቅ ተሳቦ 15 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ የሚላስ የሚቀመስ ማጣቱ መሬት የያዘ አቅ ነው፡፡ እነዚህ ለማሳያ የቀረቡት እና ሌሎችም እራሳቸው ያመኑት የውጭ ንግድ ዘርፍ ያለመሳካት ተጨምሮ ከወረቀትና ፉከራ ያላለፈው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በስኬት አጠናቀናል ይሉናል፡፡ ይህ እቅድ አልተሳካም የሚሉት ምን ቢሆን እንደነበር ግን ሊነግሩን አልቻሉም፡፡  ቢሆንም በስኬት ተጠናቋል እያሉን ነው፡፡ በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትምህርት አግኝተንበታል ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን እቅዱ ግን ለትምህርት መቅሰሚያ ነው አላሉንም ነበር፡፡
ቀጣዩ ዕቅድ በሚመለከት በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ከነበረው ሁኔታ በተለየ በጅምሩ የታየው እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ደግሞ በኦሮሚያ እና በጎንደር አካባቢ የዜጎችን ህይወት እስከመቅጠፍ የደረሰው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ሲሆን በመላ ሀገሪቱ የተከሰተውም ድርቅ መነሻ ያደረገው ርሃብ አንዱ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ሲገለፅ የነበረወ ነገር “የፀጥታ/ዝምታ መኖር፣ የሰላም ምልክት እንዳልሆነ” ነበር፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ነብስ ዘርቶ ያለው ቋንቋ መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝም፣ እንዲሁም በተለያየ ወቅት የነበሩ የእርስ በእርስ ግጭቶች፣ አሁንም በሀገሪቱ ለመድበለ ፓርቲ እንዳይመሰረት ገዢው ፓርቲ የዘጋው በር፣ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያሰችል ከተለያየ መሰመር የሚቀርቡ ብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄዎች፣ ወዘተ ተገቢው ምላሽ ያለማግኘታቸው በሀገራችን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት አስቸጋሪ እንደሆነም ተገልፆዋል፡፡ ዘላቂ ሰላም በሌለበት ደግሞ እድገት የሚባል ነገር ሊታሰብ የሚችል አይደለም፡፡ በቅርቡ በኦሮሚያ አካባቢ በተፈጠረው እንቅስቃሴ ምክንያት ወደ ሀገር ውስጥ መዋለ ንዋይ ካፈሰሱት ግንባር ቀደም የሆነው የዳንጎቴ ሲሚኒቶ ፋብሪካ ላይ አንዣቦ ነበር የተባለው አደጋ እና ሌሎች ችግርች ለሌለች በዚህ ሀገር ኢንቨስት ለማድረግ ለሚፈልጉ ኢንቨሰተሮች መልዕክቱ ምን ሊሆን እንደሚቸል ግልፅ ነው፡፡ ከፍተኛ የውጭ መዋለ ንዋይ ፍላጎት ያላት ሀገራችን እሰከ አሁን ያለውን ያህል የውጭ ገንዘብ ለማገኝት በሚቀጥለው አምስት ዓመት የምትችልበት ሁኔታ አይኖርም የሚል ግምት አለኝ፡፡ ይህ ደግሞ የሚሆነው የውጭ ኢንቨስተሮች መረጃ የሚያገኙት ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሳይሆን ዓለም አቀፍ ባለሞያዎች ከሚሰጡት ትንታኔ ነው፡፡ መንግሰት እንደሚለው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የሚሰጡት መግለጫ እና የሚያወጡት ሪፖርት ዋጋ ቢስ አይደለም፡፡ እነዚህ ባለሀብቶች የት ሀገር ቢሄዱ በሰላም እንደሚነግዱ እና የተሻለ ትርፍ እንደሚያገኙ መረጃ የሚያገኙበት ምንጭ ነው፡፡
የውጭ ኢንቨስተሮች ብቻ አይደለም ከአሁን በኋላ የሀገር ውስጥ ባለሀብትም ቢሆን ዘላቂ ሰላም በሌለበት ሁኔት ኢንቨት የሚያደርጉበት ሁኔታ እጅግ ዝቅተኛ ነው የሚሆነው፡፡ ከዚህ በፊትም ሲያደርጉ ከነበረው ያነሰ ይሆናል ማለቴ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም ቢሆን ቀላል የማይባሉ ኢትዮጵያዊያን ከሀገራቸው ውጭ መስራትን በተለይ በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገሮች አካባቢ ምርጫቸው እንደሚያደርጉ ይታወቃል፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ደግሞ የበለጠ ገፊ ነው፡፡ ባለፈው የገቢዎችና ጉምርክ ባለስልጣን ሹም በሙስና ሲታሰሩ ከሀገር ተገፍተው የወጡ ነጋዴዎች ያሳዩትን የደስታ ምንጭ ትዝ ይለኛል፡፡ ትንንሾቹ ሲታሰሩ ለውጥ የሚመጣ መስሏቸው፡፡
በኢትዮጵያ ኢንቨስትምንት ውስጥ መንግሰት እጁን በማስረዘም በከፍተኛ ደረጃ ኢንቨስትመንት ውስጥ ይሳተፋል፡፡ ይህ የመንግሰት ተሳትፎ ደግሞ መስረት ያደረገው ከውጭ መንግሰታት እና ዓለም አቀፍ አበደባሪዎች ከሚገኝ ብድር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በሀገር ውስጥ የተፈጠረው ህዝባዊ እንቅስቃሴ በግልፅ ወጥቶ ከመታየቱ በፊትም ሀገሪቱ ያለባት የብድር ጫና ከፍተኛ መሆኑን ሪፖርት እያደረጉ እና ጥንቃቄ እንዲወሰድ ሲመክሩ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እንደከዚህ ቀደሙ ከፍተኛ ብድር ይስጣሉ የሚል ግምት መውሰድ የዋህነት ነው፡፡ ይልቁንም ይህ አጋጣሚ ተጠቅመው ብድሮቹን ከማግኘት በፊት አንድ አንድ የማሻሻያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ግፊት ያደርጋሉ፡፡ አሁን በግልጽ እያየነው ያለው እውነትም ዜጎች በረሃብ አደጋ ላይ ሆነው እያለ እርዳታው በቁጥ ቁጥ የሆነበት ሁኔታ በምግብ እራሳችንን ችለናል የሚለውን መንግሰት ከወገቡ ጎንበስ ብሎ እስኪለምን ድረስ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በቅርቡ እንደሰማነው ፉከራ ከሆነ ደግሞ መንግስት በራሱ አቅም እርዳት እንደሚሰጥ ነው፡፡ ወጤቱን አብረን የምናየው ይሆናል፡፡
የረሃቡን ጉዳይ ካነሳን “ኤሊኖ” ወቅታዊ ክስተት ስለሆነ ማለፉ አይቀርም ጥሎት የሚሄደው ጠባሳ ግን በእንድ እና ሁለት ዓመት የምንወጣው አይደለም፡፡ ለእድገትና ትራንሽፎርሜሽን እቅድ ትግበራ 15 ሚሊዮን ህዝብ ከዚህ ውስጥ ከግምሻ በላይ የሚሆነው አምራች ዜጋ ምንም ሚና የለውም ሊባል አይችልም፡፡ ይህ ህዝብ ለህድገት እሴት ከመሆን ይልቅ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የመቋቋሚያ ጊዜው ነው የሚሆነው፡፡ የጠፉበትን እንሰሳት ተክቶ ወደ ትርፍ እና ቁጣባ ለማምራት በዚህ አምስት ዓመት ውስጥ አይችለም፡፡ ይህ ደግሞ በእድገት ላይ የራሱ ጫና ይኖረዋል፡፡ መንግሰት ይህም ሆኖ ግን እድገታችን እንደተለመደው በአስማት በሁለት አሃዝ አድጎዋል ማለቱ አይቀርም፡፡ የነብስ ወከፍ ገቢያችንም እንዲሁ ይጨምራል፡፡
ሰለዚህ ቀጣዩ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አሁን ሀገሪቱ ካለችበት ያልተረጋጋ ሁኔታ፣ አዚህም እዚያም የሚከሰቱ ግጭቶች እና ግጭቶቹን መንግሰት የሚፈታበት ሀይልን መሰረት ያደረገ አካሄድ ለሀገሪቱ እጅግ አስፈላጊ የሆነው የውጭ ኢንቨስተምንት በሚጠበቀው ያህል ሊመጣ አይችለም፡፡ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችም ቢሆኑ ተሳትፎዋቸው በአጭር ጊዜ ውጤት ከሚያመጡ ንግዶች ሊዘል አይችልም፣ ቢኖርም በተለመደው አዲስ አበባ እና አካባቢዋ ብቻ ይሆናል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁን ከፍተኛ አደጋ ጋርጦ ያለው የዜጎች የሚላስ የሚቀመስ ማጣት አጠቃላይ ሀገራዊ አቅምን በሚፈትን መልኩ ለልማት የሚውልን ገንዘብ ወደ እለት ደራሽ እርዳት እንዲውል ከማድረጉም በላይ አጭር ለማይባል ጊዜ የሚቀጥል የማቋቋሚያ ወጪን ይጠይቃል፡፡ እነዚህ በቀጣይ ፈታኝ ሁኔታዎች ሲሆኑ በተለይ በተፈጠረው ህዝባዊ እንቅሰቃሴ ሀገር አለን፣ መንግሰት አለ ብለው በሰላም ሃሳባቸውን ለመግለፅ ወጥተው ሳይመለሱ የቀሩ ዜጎች ደምና ህይወት በተራ የፎረም ፕሮፓጋንዳ ሰብሰባ በሚሰጥ የአቋም መግለጫ የሚፈወስ አይደለም፡፡ በዚህች ሀገር ህዝብን ያማከለ ልማትና እድገት እንዲኖር ካሰፈለገ፣ ዜጎች ሃሳባቸውን በመግለፃቸው የህይወት መሰዋዕትነት መክፈል ማቆም ይኖርባቸዋል፡፡ ለእሰከ ዛሬው የተከፈለው መሰዋዕትነትም ተገቢውን ማካካሻ በማድረግ ብሔራዊ እርቅ እንዲሰፍን መስራት ይኖርብናል፡፡ ሀገራችን የጋራችን ሃሳባችን የግላችን ነው፡፡
ቸር ይግጠመን!!!!!!!