ሰሞኑን
በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ተሳትፎ የሚያደርገው ሰው ጤና መሆኑን መጠራጠር የግድ ብሎኛል፡፡ አንዱ ውጭ ሀገር ሆኖ እንደእርሱ ካላቅራራህ
ይለኛል፡፡ ሌላው ማንነቱ እንዳይታወቅ መሸጎ እየፃፈ ይፎክርና እንደ እኔ ፎክር ይለኛል፡፡ ለማነኛውም ሁላችንም እንደየ አቅማችን
እና ችሎታችን፣ ምን አልባትም ድፍረታችን ያህል ለምናደርገው የነፃነት ትግል ክብር ብንሰጣጥ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ፈሪ መሆንም እኮ
መብት ይመስለኛል፣ ሰው ለምን ትፈራለህ ለምን ይባላል!! ባይሆን ፈሪ እንደ እኔ ፍሩ ሲል ነው አይ ሊባል የሚገባው፡፡ በእኔ እምነት የዚህች ሀገር
የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሊወሰን የሚገባው በሃሰብ ክርክር እና በዚሁ በሚገኝ የበላይነት ብቻ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህም
ነው ሁሉም የማይሰማማበት ቢሆን እንኳን የእኔ ሃሳብ ይህ ነው ብዬ ለመግለፅ የምወደው፡፡ ይህን አካሄድ ያለመውደድ መብት ቢሆንም
የእኔን ውደድ ብሎ ማስገደድ አይቻልም፡፡ ይህን ከሰሞኑ የፌስ ቡክ የፅሁፍ ምልልሶች መነሻ አድርጌ ካልኩኝ፤ ለዛሬ ፅሁፍ መነሻ
ያደረጉት ደግሞ ለአንድ ሳምንት በምክር ቤት ወጉ እንዳይቀር “ሲመከርበት” የከረመው የሁለተኛው ዙር የእድገትና ትራንስፎርሜሽን
እቅድ እና የሰሞኑ “የተቀናጀ ማስተር ፕላን እንቢ” በሚል መነሻ በኦሮሚያ አካባቢ የተቀሰቀሰው ንቅናቄ፣ በጎንደር የተፈጠረው ግጭት
እንዲሁም ድርቅ መነሻ ሆኖ የተከሰተው ርሃብ እንደምታ ምን ሊመስል እንደሚችል በአጭሩ የግል እይታዬን ለማስቀመጥ እሞክራለሁ፡፡
ገዢዎቻችን አፍረት የሚባል ነገር
እንደሌለባቸው የሚያስታውቀው የመጀመሪያውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በስኬት ማጠናቀቃቸውን ሲነግሩን አፋቸውን አንኳን ጎልደፍ
ያለማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን በምክር ቤት ውስጥ ለተሰበሰቡት እጅ በማውጣት ደሞዝ ለሚከፈላቸው ሳይሆን በሚዲያ ለሚከታተላቸው ህዝብም
ያላቸውን ንቀት የሚያሳይ ነው፡፡ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽኝ ዕቅድ በዋነኝነት ከተቀመጡት ግቦች የተሳከ የሚባል አንድም
ነገር የለም እንዳይባል (ጥራት በሌለው ትምህርትና ጤና የቁጥር ስኬት መኖሩ አይካድም)፣ ከዚህ በስተቀር መብራት 10 ሺ ሜጋ ዋት
ብለው ሶሰት ሺ ያለመድረሳቸው፣ ባቡር 2395 ኪ.ሜ ታቅዶ እሰከ አሁን ስራ ያልጀመረውን የአዲስ አበባ ድሬዳዋን ብንወስድ
700 ኪሎ ሜትር እንደማይሞላና ይህም ዕቅዱ የውሸት ህዝብ ማማለያ እንደ ነበር ነው፡፡ በግብርና ዘርፍ በብዙ ሚሊዮን የውጭ ምንዛሬ
ያስገኛል የተባለው እቅድ የተያዘለት፣ የተገላቢጦሽ መንግሰት በውጭ ምንዛሬ ሰንዴ መግዛት ውስጥ መግባቱ ይታወቃል፡፡ ባለፈው አምሰት
ዓመት ከፍተኛ የእድገት ምጣኔ አስመዝግቦዋል የተባለው ግብርና ነው ብለው ሚሊየነር አርሶ አደር ብሎ መሸለሙን ሳይጠናቀቅ በድርቅ
ተሳቦ 15 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ የሚላስ የሚቀመስ ማጣቱ መሬት የያዘ አቅ ነው፡፡ እነዚህ ለማሳያ የቀረቡት እና ሌሎችም እራሳቸው
ያመኑት የውጭ ንግድ ዘርፍ ያለመሳካት ተጨምሮ ከወረቀትና ፉከራ ያላለፈው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በስኬት አጠናቀናል ይሉናል፡፡
ይህ እቅድ አልተሳካም የሚሉት ምን ቢሆን እንደነበር ግን ሊነግሩን አልቻሉም፡፡ ቢሆንም በስኬት ተጠናቋል እያሉን ነው፡፡ በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ
ትምህርት አግኝተንበታል ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን እቅዱ ግን ለትምህርት መቅሰሚያ ነው አላሉንም ነበር፡፡
ቀጣዩ ዕቅድ በሚመለከት በመጀመሪያው
የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ከነበረው ሁኔታ በተለየ በጅምሩ የታየው እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ደግሞ በኦሮሚያ እና በጎንደር
አካባቢ የዜጎችን ህይወት እስከመቅጠፍ የደረሰው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ሲሆን በመላ ሀገሪቱ የተከሰተውም ድርቅ መነሻ ያደረገው ርሃብ
አንዱ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ሲገለፅ የነበረወ ነገር “የፀጥታ/ዝምታ
መኖር፣ የሰላም ምልክት እንዳልሆነ” ነበር፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ነብስ ዘርቶ ያለው ቋንቋ መሰረት
ያደረገ ፌዴራሊዝም፣ እንዲሁም በተለያየ ወቅት የነበሩ የእርስ በእርስ ግጭቶች፣ አሁንም በሀገሪቱ ለመድበለ ፓርቲ እንዳይመሰረት
ገዢው ፓርቲ የዘጋው በር፣ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያሰችል ከተለያየ መሰመር የሚቀርቡ ብሔራዊ ዕርቅ ጥያቄዎች፣ ወዘተ ተገቢው
ምላሽ ያለማግኘታቸው በሀገራችን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት አስቸጋሪ እንደሆነም ተገልፆዋል፡፡ ዘላቂ ሰላም በሌለበት ደግሞ እድገት የሚባል ነገር ሊታሰብ የሚችል አይደለም፡፡ በቅርቡ በኦሮሚያ አካባቢ በተፈጠረው
እንቅስቃሴ ምክንያት ወደ ሀገር ውስጥ መዋለ ንዋይ ካፈሰሱት ግንባር ቀደም የሆነው የዳንጎቴ ሲሚኒቶ ፋብሪካ ላይ አንዣቦ ነበር
የተባለው አደጋ እና ሌሎች ችግርች ለሌለች በዚህ ሀገር ኢንቨስት ለማድረግ ለሚፈልጉ ኢንቨሰተሮች መልዕክቱ ምን ሊሆን እንደሚቸል
ግልፅ ነው፡፡ ከፍተኛ የውጭ መዋለ ንዋይ ፍላጎት ያላት ሀገራችን እሰከ አሁን ያለውን ያህል የውጭ ገንዘብ ለማገኝት በሚቀጥለው
አምስት ዓመት የምትችልበት ሁኔታ አይኖርም የሚል ግምት አለኝ፡፡ ይህ ደግሞ የሚሆነው የውጭ ኢንቨስተሮች መረጃ የሚያገኙት ከኢትዮጵያ
ቴሌቪዥን ሳይሆን ዓለም አቀፍ ባለሞያዎች ከሚሰጡት ትንታኔ ነው፡፡ መንግሰት እንደሚለው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የሚሰጡት
መግለጫ እና የሚያወጡት ሪፖርት ዋጋ ቢስ አይደለም፡፡ እነዚህ ባለሀብቶች የት ሀገር ቢሄዱ በሰላም እንደሚነግዱ እና የተሻለ ትርፍ
እንደሚያገኙ መረጃ የሚያገኙበት ምንጭ ነው፡፡
የውጭ ኢንቨስተሮች ብቻ አይደለም
ከአሁን በኋላ የሀገር ውስጥ ባለሀብትም ቢሆን ዘላቂ ሰላም በሌለበት ሁኔት ኢንቨት የሚያደርጉበት ሁኔታ እጅግ ዝቅተኛ ነው የሚሆነው፡፡
ከዚህ በፊትም ሲያደርጉ ከነበረው ያነሰ ይሆናል ማለቴ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም ቢሆን ቀላል የማይባሉ ኢትዮጵያዊያን ከሀገራቸው ውጭ
መስራትን በተለይ በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገሮች አካባቢ ምርጫቸው እንደሚያደርጉ ይታወቃል፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ደግሞ የበለጠ
ገፊ ነው፡፡ ባለፈው የገቢዎችና ጉምርክ ባለስልጣን ሹም በሙስና ሲታሰሩ ከሀገር ተገፍተው የወጡ ነጋዴዎች ያሳዩትን የደስታ ምንጭ
ትዝ ይለኛል፡፡ ትንንሾቹ ሲታሰሩ ለውጥ የሚመጣ መስሏቸው፡፡
በኢትዮጵያ ኢንቨስትምንት ውስጥ
መንግሰት እጁን በማስረዘም በከፍተኛ ደረጃ ኢንቨስትመንት ውስጥ ይሳተፋል፡፡ ይህ የመንግሰት ተሳትፎ ደግሞ መስረት ያደረገው ከውጭ
መንግሰታት እና ዓለም አቀፍ አበደባሪዎች ከሚገኝ ብድር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በሀገር ውስጥ የተፈጠረው ህዝባዊ እንቅስቃሴ በግልፅ
ወጥቶ ከመታየቱ በፊትም ሀገሪቱ ያለባት የብድር ጫና ከፍተኛ መሆኑን ሪፖርት እያደረጉ እና ጥንቃቄ እንዲወሰድ ሲመክሩ ነበር፡፡
በዚህ ሁኔታ ላይ እንደከዚህ ቀደሙ ከፍተኛ ብድር ይስጣሉ የሚል ግምት መውሰድ የዋህነት ነው፡፡ ይልቁንም ይህ አጋጣሚ ተጠቅመው
ብድሮቹን ከማግኘት በፊት አንድ አንድ የማሻሻያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ግፊት ያደርጋሉ፡፡ አሁን በግልጽ እያየነው ያለው እውነትም
ዜጎች በረሃብ አደጋ ላይ ሆነው እያለ እርዳታው በቁጥ ቁጥ የሆነበት ሁኔታ በምግብ እራሳችንን ችለናል የሚለውን መንግሰት ከወገቡ
ጎንበስ ብሎ እስኪለምን ድረስ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በቅርቡ እንደሰማነው ፉከራ ከሆነ ደግሞ መንግስት በራሱ አቅም እርዳት እንደሚሰጥ
ነው፡፡ ወጤቱን አብረን የምናየው ይሆናል፡፡
የረሃቡን ጉዳይ ካነሳን “ኤሊኖ”
ወቅታዊ ክስተት ስለሆነ ማለፉ አይቀርም ጥሎት የሚሄደው ጠባሳ ግን በእንድ እና ሁለት ዓመት የምንወጣው አይደለም፡፡ ለእድገትና
ትራንሽፎርሜሽን እቅድ ትግበራ 15 ሚሊዮን ህዝብ ከዚህ ውስጥ ከግምሻ በላይ የሚሆነው አምራች ዜጋ ምንም ሚና የለውም ሊባል አይችልም፡፡
ይህ ህዝብ ለህድገት እሴት ከመሆን ይልቅ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የመቋቋሚያ ጊዜው ነው የሚሆነው፡፡ የጠፉበትን እንሰሳት ተክቶ
ወደ ትርፍ እና ቁጣባ ለማምራት በዚህ አምስት ዓመት ውስጥ አይችለም፡፡ ይህ ደግሞ በእድገት ላይ የራሱ ጫና ይኖረዋል፡፡ መንግሰት
ይህም ሆኖ ግን እድገታችን እንደተለመደው በአስማት በሁለት አሃዝ አድጎዋል ማለቱ አይቀርም፡፡ የነብስ ወከፍ ገቢያችንም እንዲሁ
ይጨምራል፡፡
ሰለዚህ ቀጣዩ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን
እቅድ አሁን ሀገሪቱ ካለችበት ያልተረጋጋ ሁኔታ፣ አዚህም እዚያም የሚከሰቱ ግጭቶች እና ግጭቶቹን መንግሰት የሚፈታበት ሀይልን መሰረት
ያደረገ አካሄድ ለሀገሪቱ እጅግ አስፈላጊ የሆነው የውጭ ኢንቨስተምንት በሚጠበቀው ያህል ሊመጣ አይችለም፡፡ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችም
ቢሆኑ ተሳትፎዋቸው በአጭር ጊዜ ውጤት ከሚያመጡ ንግዶች ሊዘል አይችልም፣ ቢኖርም በተለመደው አዲስ አበባ እና አካባቢዋ ብቻ ይሆናል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁን ከፍተኛ አደጋ ጋርጦ ያለው የዜጎች የሚላስ የሚቀመስ ማጣት አጠቃላይ ሀገራዊ አቅምን በሚፈትን መልኩ
ለልማት የሚውልን ገንዘብ ወደ እለት ደራሽ እርዳት እንዲውል ከማድረጉም በላይ አጭር ለማይባል ጊዜ የሚቀጥል የማቋቋሚያ ወጪን ይጠይቃል፡፡
እነዚህ በቀጣይ ፈታኝ ሁኔታዎች ሲሆኑ በተለይ በተፈጠረው ህዝባዊ እንቅሰቃሴ ሀገር አለን፣ መንግሰት አለ ብለው በሰላም ሃሳባቸውን
ለመግለፅ ወጥተው ሳይመለሱ የቀሩ ዜጎች ደምና ህይወት በተራ የፎረም ፕሮፓጋንዳ ሰብሰባ በሚሰጥ የአቋም መግለጫ የሚፈወስ አይደለም፡፡
በዚህች ሀገር ህዝብን ያማከለ ልማትና እድገት እንዲኖር ካሰፈለገ፣ ዜጎች ሃሳባቸውን በመግለፃቸው የህይወት መሰዋዕትነት መክፈል
ማቆም ይኖርባቸዋል፡፡ ለእሰከ ዛሬው የተከፈለው መሰዋዕትነትም ተገቢውን ማካካሻ በማድረግ ብሔራዊ እርቅ እንዲሰፍን መስራት ይኖርብናል፡፡
ሀገራችን የጋራችን ሃሳባችን የግላችን ነው፡፡
ቸር ይግጠመን!!!!!!!
No comments:
Post a Comment