Friday, May 20, 2016

የአሰፋ ጫቦ “የትዝታ ፈለግ” መፅኃፍ እኔ እንደገባኝ…



የአቶ አሰፋ ጫቦን “የትዝታ ፈለግ” መፅኃፍ እያነበብኩ ተመችቶኛል ብዬ ፌስ ቡክ ላይ ሃሳቤን ባሰፍር፡፡ ለራሴም ለአቶ አሰፋም የሰድብ ምርት ማምረት ቻልኩኝ፡፡ እስኪ እግዜሩ ያሳያችሁ እኔ አንብቤ ተመቸኝ ማለት ሌላው ተመችቶታል ማለቴ ተደርጎ እንዴት ይወሰዳል፡፡ እጅግ ብዙ ሰው የአቶ አሰፋ ጫቦ መፅኃፍ ብሎም ሃሳቡ ላይመቸው የሚችል እንደሚኖር እገምታለሁ፡፡ በምሳሌ ላስረዳ ጋምቤላ ሄጄ ወባ ያዘኝ ብል፤ ጋምቤላ የሄደ ሁሉ ወባ ይይዘዋል ማለት፡፡ እንዴት ነው ታዲያ የእኔ በወባ መያዝ ውሸት የሚሆነው፡፡ እባካችሁ እየተሰተዋለ ለማለት እና የአቶ አሰፋ ጫቦ መፅኃፍ ሊያስደሰተኛ የቻለበትን ሲከፋም ከአቶ አሰፋ ጫቦ ጋር ያለኝን የሃሳብ አንድነት ለመግለፅ ልሞክር፡፡ መብቴን ልጠቀም፡፡
አቶ አሰፋ ጫቦ እስር ቤት ሆነው በግላቸው ግፍ የሚባለው (ቶርቸር) እንዳልደረሰባቸው በይፋ መስክረዋል፡፡ መቼም አሰር ዓመት ከስድሰት ወር በላይ መታሰር ግፍ አይደለም ብለው አይደለም፡፡ ከሌሎቹ ጋር ሲነፃፃር ለማለት ብቻ ነው፡፡ የሌሎችን ስቃይ ግን በደምብ አድርገው እንድንረዳ አድርገው በመፅሃፍ ውስጥ አሳይተውናል፡፡ በዚያ በግፍ ማጎሪያም ውስጥ ቢሆን በጎ ሰዎች ለማየት መቻሉን የአቶ አሰፋ መፅሃፍ ያሳየናል፡፡ እነዚህ በጎ ሰዎች ለበጎነት አጥር እንደሌለው የሚየሰተምሩን ናቸው፡፡
አቶ አሰፋ ጫቦ ከብዙዎች የሚለዩት ደርግን ለመመዘን የተጠቀሙበት ሚዛን አብዛኛው ደርግን ለመመዘን ከሚፈልግበት የተጭበረበረ የወያኔ ሚዛን በተለየ ነው፡፡ ይህ በደርግ ላይ የተጭበረበረ ሚዛን ይዞ የሚመዝነው ወያኔ ብቻ አይደለም- ኢህአፓም፣ መኢሶንም፣ ወዘተ ናቸው፡፡ በሚያስገርም ሁኔታ እነዚን የተጭበረበሩ ሚዛኖች ካልተጠቀመ ሁሉም ሰው ደርግ/ኢሰፓ ወይም የድሮ ስርዓት ናፋቂ የሚል ወይም አንድ ክቡድ የሆነ ተቀፅላ ይሰጠዋል፡፡ እግዜር ያሳያችሁ በዚህ ምክንያት ሁሌም በራሳችን ሚዛን ከመጠቀም ይልቅ ለጊዜውም ቢሆን አሸናፊ በሰጠን ወይም አሸናፊው በፈቀደልን ሚዛን እንድንጠቀም እንገደዳለን፡፡ አቶ አሰፋ ግን እንዲህ ይላል “እስር ቤት ሆኜም ሆነ፣ ከዚያም በፊት፣ ከዚያም በኋላም - ምን አቅብጦኝ ከደርግ ጋር ገጠምኩ- ብዬ አላውቅም፡፡ አምኜ እንጂ ወይ ምናምን ፍለጋ ወይ ሰው  ገፋፍቶኝ አሳስቶኝ አልገባሁም፡፡ በመሸ በጠባ ቁጥር በጥሼ የምቀጥለው ማተብ የለኝም፡፡” በማተቤ ልዳኝ ብለዋል፡፡ ይህ በእውነት ሊደነቅ የሚገባው የመርዕ ሰው መሆንን የሚጠይቅ ነው፡፡
አቶ አሰፋ ጫቦ ለሰዎች ምስጋና የሚሰጠው አብዛኛው ህዝብ ይወዳቸዋል በሃሳብ ከእኔም ጋር ይሰማማል በሚል አይደለም፡፡ “ህዝቡ” የሚባለው አይናችሁን ላፈር ያላቸውን በአደባባይ ያመሰግናለሁ፡፡ ከመንግሰቱ ኃይለማሪያም ጀምሮ፣ የደህንነት ሚኒሰትሩ ተሰፋዬ ወልደስላሴን ጨምሮ የማዕከላዊውን አርጋው እሸቱን በመፅኃፉ ያደንቃል፡፡ እነዚህ ሰዎች በኩራት የሰሩትን በጎ ነገር ይተርካል፡፡ በቦታው ደግሞ መዝገባቸውን ገልጦ ያሳየናል፡፡ ይህን በራስ መመራት ልንማርበት ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር ዶር በፍቃዱ ደግፌ በቀድሞ የኢሠፓ አባሎች የኢሠመጉ አባል ይሁነ አይሁኑ በሚለው ክርክር ወቅት የወሰደውን አቋም መሰረት አድርጎ (ሰበብ/ምክንያት) በግሌ ዛሬም/ወደፊት ለህውሃት እና ሀጋሮቹ የምመኘውን ደፋር ሃሳብ በመፅኃፉ ውስጥ አስቀምጦልኛል፡፡
የህወሃት/ኢህአዴግ ወይም ሌሎች ሀጋር ድርጅቶች በማነኛውም መንገድ ተሸንፈው ስልጣን ቢለቁ እነርሱ በሰፈሩት ቁና እንስፈራቸው የሚል እምነት ጨርሶ የለኝም፡፡ የቀደሞ የኢትዮጵያን ሠራዊት    “የደርግ ሠራዊት” እንዳሉት ሁሉ የአሁኑንም ሠራዊት “የህወሃት ሰራዊት” ብሎ ለመበተን በዝግጅት ላይ ያለ ካላ የአሰፋ ጫቦን ምክር ማዳመጥ ያለበት ይመስለኛል፡፡ የአሰፋ ምክር እንዲህ ይላል “የኢሠፓን ጉዳይ፣ እንዲያውም ማንኛውንም ሀገረ አቀፍ ጉዳይ ስንመለከት በተቻለ ከትልቁ ምስል አኳያ ማየት የሚሻል ይመስለኛል፡፡ ትልቁ ምስል ኢትዮጵያ ነች፡፡ ትልቁ ምስል ይህች ሀገር የጋራ ቤታችን ኢትዮጵያ ነች፡፡” …..  “ፖለቲካ ባዶ ህዋው ላይ የሚሰራ ትርዒት አይደለም፡፡ ዛሬ ያለንበት ሁኔታ የዛሬ መለኪያ፣ የነገውን መፍቻ ቁልፍ ይጠይቃል፡፡ የትላንትናውን ሙሉ ለሙሉ አውልቀን አንጥልም፡፡ ትምህርት እናገኝበታለን፡፡” የሚል ነው፡፡ በአሁኑ ሁኔታ ስንመዝነው አንዳንድ ሰው ከወያኔ/ኢህአዴግ ምንም ትምህርት አይገኝም የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ እንደዚህ የሚል ሰው በእኔ እምነት ኢህአዴግ ምንም ጥፋት አልሰራም ከማለት የሚተናነስ አይመስለኝም፡፡ ኢህአዴግ የሰራቸውን ሰህተቶች በሙሉ ነቅሰን አውጥተን መማር ይኖርብናል፡፡ ለመማር ደግሞ ጠርጎ አውጥቶ ጥሎ ሳይሆን አካቶ መሆን ይኖርበታል፡፡
አቶ አሰፋ ጫቦ የታናሽ ወንድሜን ባለቤት ሀገር ጨንቻን በፅሁፉ በደንብ አስጎብኝቶኛል፡፡ አሁን በራሴ ቁስቆሳም ቢሆን ለመጎብኘት ሰበብ ይሆነኛል፡፡ አርባ ምንጭን እና ሌሎች የገጠር ቀበሌዎችን በስራ አጋጣሚ አይቻለሁ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ጨንቻን አላየሁም እና ጥሩ ቅስቀሳ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ሌላ በትዝታ ፈለግ መፅኃፍ ውስት በተለይ ለእኔ ምርጥ ሆነው ያገኘሁት “ነፍጠኛ ማን ነው?” በሚል የኢትዮጵያችን የነፍጠኛፖለቲካ ትርጉም የገለፀበት አንዱ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ “ጎበዝ ….! ማውረድ እንዳያቅተን” በሚል ሰለ ኢህአፓው መሪ ዘርዑ ክህሽን የተፃፈው ነው፡፡ በሌሎቹ ላይ ሌሎች አሳብ እንዲሰጡበት ትቼ በነዚህ ላይ ብቻ አተኩራለሁ፡፡
ነፍጠኛ ለህወሃት፣ ነፍጠኛ ለመዐህድ፣ ነፍጠኛ ለኦነግ ወዘተ የራሳቸው የሆነ ትርጉም የሰጡት ሲሆን፡፡ በተለይ ነፍጠኛ ማለትና አማራ ማለት እኩል አቻ ትርጉም ያለው አስመስለው የሚያቀርቡትን የፖለቲካ ሸፍጥ አሰፋ ጫቦ በደንብ አፍታቶ አስቀምጦታል፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገራችን ሳያውቁ በስህተት አውቀው በድፍረት ለፖለቲካ ሸፍጣቸው ሲሉ የሚያደናግሩን እንደሆነ አስረድቶናል፡፡ አሰፋ በማጠቃለያው “ነፍጠኛ ማለት አማራ ብቻ ነው ማለት እምነት እንጂ እውነት አይደለም” ብሎ በመረጃ አስደግፉ አሳይቶናል፡፡ ዋነኛዎቹ የነፍጠኛ ፖለቲካ አቀንቃኞች የሆኑት የትግራይ ልሂቃን ትግራይ ነፍጠኛ የሌለባት ክልል ስትሆን የኦሮሞ ልሂቃን ደግሞ የኦሮሞ ልጆች ደግሞ በብዙ ቦታ ራሳቸው ነፍጠኛ እንደሆኑ እንድናውቅ አይፈልጉም፡፡ የአሰፋ ጫቦ መፅኃፍ በተለይ ሚንሊክ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ያደረጉት መሰፋፋት ነፍጠኛው የሸዋ ኦሮሞ መሆኑን የሚያሰረዳ ነው፡፡ ቀደም ሲልም ከ400 ዓመት በፊት ኦሮሞ ወደ ሰሜን ነፍጥ ይዞ መሄዱ ሳይዘነጋ ማለት ነው፡፡
መማር ከፈለገን አሰፋ ጫቦ ብዙ ያስተምረናል፡፡ ካወቅነውም ያስታውሰናል፡፡ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ አደሬ፣ ጉራጌ፣ ሶማሊ፣ አፋር፣ ወዘተ መሆን በምንም መልኩ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ጠብ እንደሌለበት፡፡ አሰፋ ጫቦ “እኔ ጋሞ ነኝ፡፡ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ሁለቱ ተጣልተው ለማስታረቅ ተቀምጨ አላውቅም፡፡ እረዳቸዋለሁ፡፡ የእኔ ቢጤ በሺህ የሚቆጠሩ አውቃለሁ፡፡ የማላውቃቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሉ፡፡” ይላል፡፡ እኔ አስፋ ጫቦ ከማያውቃቸው ከሚሊዮኖቹ አንዱ ነኝ፡፡ አቶ አሰፋ ይህን “ነፍጠኛ ማን ነው?” ለመፃፍ ሰባት ዓመት ከሰባት ጊዜ በላይ ወረቀት አውጥቶ እንደ ተወው ፅፎልናል፡፡ እኛም ሰባት ጊዜ ሰባ ሰባት ለመናገር ስንሞክር በአድማ ታፍነን ነበር፡፡ የአሰፋን መፅኃፍ ከወደድኩበት ምክንያት አንዱ የገባችሁ ይመስለኛል፡፡ እኔ ላደርገው ያልቻልኩትን የውስጤን ከተበው፡፡ በቃ ወደድኩት!!!
ሌላው ኢህአፓን በሚመለከት ብዙ ኢህአፓ የነበሩ ወደጆቼ ድርጅቱ አመሰራረቱና አመራሩ በደንብ መፈተሸ አለበት፣ ይህ ማለት በቆራጥነት ለነብሳቸው ሳይሳሱ ለትግሉ ቆመው የነበሩትን መክዳት ሳይሆን፣ ትክክለኛው መድረሻው ግብ ሳይታወቅ ምን አልባትም “የኤርትራን ነፃ ሀገርነት” ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የውስጥ እሳት እንዲሆኑ ወንድሞቻችን እህቶታችን ተማግደው አለመሆኑን ይጣራ ስንል የሚሰማን አናገኝም፡፡ ሁሌም ሰለ ኢህአፓ ጅግንነት፣ ተራራ አንቀጥቃጭ ትውልድነት ብቻ ይነገር የሚል ሰሜት አለው፡፡ ንፅፅሩም ከደርግ ጋር ብቻ ሆኖ ሰው በላው ደርግ በላቸው በሚለው አንድ መስመር ፕሮፓጋንዳ እንድንዋኝ እየተደረግ ነው፡፡ በእውነት እንመልከት ከተባለ የዘርዑ ክህሸን መሰመር ከሻቢያ “የኤርትራ ነፃ ሀገር” መሆንን ከመፈፀም ያለፈ ግብ ነበረው ብለን እንድናምን የሚያደርግ ነገር ጠፍቶብናል፡፡ ልብ ወለድ በሚል ቢሆንም “የሱፍ አበባ” በሚል የተፃፈው መፅኃፍም ከዚህ የተለየ እንዲገባኝ አያደርግም፡፡ ለማነኛውም የብሔር ብሔረሰብ ጥንቅሩን ያልጠበቀውን የኢሕአፓ አመራር ከጅምሩ ስናይ በእርግጥ እነዚህ ሰዎች የተደራጁት ሻቢያና ወያኔ እንዲጠናከሩ መሰመር ለማበጀት ነው? የሚል ጥያቄ ያጭራል፡፡ አሁንም በጅምላ ፍረጃውን ትተን በግልፅ እንወያይበት የታሪክ ሰዎች ከፕሮፓጋንዳው ወጥተው፣ በዚሁ መስመር በተሰራው ሚዛን ሳይሆነ፤ በምሁራዊ እይታ እንዲገመግሙት መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ የታጋይ ደም ይጮሃል በሁሉም መስመር ያለ ነው፡፡ በነጭም በቀይም፣ በሌሎቹም የእርስ በእርስ ጦርነቶች፡፡
ይህ የግል አስተያየቴ እንደሆነ ታውቁ በመጨረሻም መፅኃፉ ውስጥ የተፃፉት የተለያዩ ፅሁፎች የተፃፉበት ቀን በጣም የተለያየ በመሆኑ ምክንያት የተፃፉበት ቀን ቢያንስ ዓመተ ምህረቱ ቢገለፅ ጥሩ ይመሰለኛል፡፡ ሌላው ደግሞ ብዙ ቦታ በዚህ ጉዳይ ወደፊት እፅፋለሁ እየተባለ ታልፎዋል፡፡ ለፀኃፊው ጉዳዮቹን ለማስታወስ ከመርዳት ወጭ በአሁኑ ሰዓት መፅኃፉ ውስጥ ያላቸው ፋይዳ አልታየኝም፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሚታዩት የዓመት ምህረት ስህተቶች መታረም ይኖርባቸዋል፡፡
አቶ አሰፋ ጫቦ በማመሰገን ቸር ይግጠመን እላለሁ፡፡



No comments:

Post a Comment