Monday, June 27, 2016

ለዲሞክራሲ ስርዓት ምን ዓይነት ፓርቲ ያስፈልገናል?



በሀገራችን የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበራት እንዲሁም የሚዲያ ተሳትፎ አጅግ ወሳኝ እንደሆነ ሁሉም ይረዳዋል ማለት ባይቻልም በተለይ የፖለቲካ ፓርቲ አባል አመራር የሆኑ ሰዎች ይጠፋቸዋል ብሎ የሚገምት ላይኖር ይችላል፡፡ እውነቱ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ሰዎች የሚሳተፉት በዋነኝነት በሀገራቸን የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያላቸውን መዋጮ በማስላት ሳይሆን ገዢውን ፓርቲ በማስወገድ ላይ ብቻ ያጣነጠነ ይመስላል፡፡ ይህንንም ማድረግ የሚፈልጉት ደግሞ በትርፍ ጊዚያቸው ከስራ መልስ ወይም በጡረታ ጊዚያቸው ነው፡፡ ይህን ሲያደርጉ ደግሞ የብዙ ወጣቶች ጊዜና ጉልበት መስመር ባልያዘ አቅጣጫ እንደሚመሩ አይረዱም፡፡ ለነገሩ የወጣቶችን ጊዜ በማባከን እና የወጣቶችን ፍሬያማ ጊዜ በከንቱ በማባከን ገዢውን ፓርቲ የሚወዳደር የለም፡፡ በሰራ እናገኛለን ተሰፋ እና እራሳቸውን ከደህንነት ስጋት ለመጠበቅ ገዢውን ፓርቲ በምሽግነት ስለሚጠቀሙበት፡፡ ይህም ቢሆን ገዢው ፓርቲ ይህን ስለሚያደርግ ተቃዋሚዎች የወጣቶችን ጊዜ ያለአግባብ ማባከን አለብን የሚል ክርክር ሊገጥሙ አይገባም፡፡
በእኔ እምነት የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሲኮን በተለይም አመራር ሲኮን በቀጣይ የመንግሰትን ስልጣን ለመያዝ መዘጋጀትን ይጠይቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዚህ ልክ እራሳቸውን ያዘጋጁ የገዢው ፓርቲም ሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ ከሰበሰባቸው ሰባት ሚሊዮን አባላት ምርጥ ብሎ አውጥቶ አመራሩን መቀየር ባለመቻሉ ያሉትን የጡረታ ጊዜ እያራዘሙ 25 ዓመት ሞልቶታል፡፡ አሁንም ቢሆን በገዢው ፓርቲም ሰፈር ከፊት መጥተው ተሰፋ የሚደረግባቸው አይታዩም፡፡
በተቃዋሚ ጎራ ይህን ወሳኝ የፖለቲካ አመራር እና የመንግሰት ስልጣን ቁርኝትን ባለመረዳት ፓርቲ የመሰረቱ እና ለመመስረት የሚራወጡ ሰዎች ግባቸው እንደ ከዚህ ቀደሙ የጡረታ ወይም ደግሞ ከሰራ መልስ ጊዜ ማሳለፊያ ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ ከዚህ በፊት ይህን ለማሳካት አንድነት ፓርቲ ያዘጋጀውን ስትራቴክ ሰነድ መሰረት አድርጎ የመድረክ አመራሮችን “ሻዶ ካቢኔ” እናቋቁም ብሎ ጥያቄ ሲያቀርብ በግልፅ ለፖለቲካ ስልጣን የምናደርገውን ትግል በድብቅ ማድረግ የለብንም የሚለውን የአንድነትን ግልፅ አቋም በድብቅ በውስጣቸው ባለ ሰውር የስልጣን ጥም (ማን የካቢነዊ መሪ ይሆናል?) ሳይቀበሉት እና ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በዚህም መነሻ አንድነት ያቀረበውን የስትራቲጂክ ፕላን ሰነድ ሳይቀበሉት ቀሩ፣ቀጥሎም አንድነትን ገፍትረው አስወጡት፡፡ ለነጉሩ አንድነትም በዚህ ትብትብ ውስጥ ድንክ ሆኖ አይቆይም ነበር፡፡
አሁን ደግሞ በድጋሚ ማሳካት የሚፈልገው ዓላማ ምን እንደሆነ የማይታውቅ ከአንድነት ፓርቲ ፍርስራሽ “ነፃነት” የሚባል ፓርቲ መመስረቱን ሰምተናል፡፡ ለምስረታው ከፍተኛውን ሚና ሲጫወት የነበረው አቶ ብሩ ቢርመጂ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይም የፓርቲው መሪ ሆኖ የተመረጠው ዶክተር ንጋት በእርግጥም የጃንሜዳ ልጅ ቢሆንም በሰሜን ሸዋነቱ በቀጣይ መድረክ ውስጥ ለሚታየው የአማራ ፓርቲ ክፍተት ማሟየ እንደሚሆን ግልፅ ነው፡፡
አንድነትን ገፍትሮ ያስወጣው የፕሮፌሰር በየነ አና የዶክተር መረራ መድረክ አሁን ለነፃነት ፓርቲ ምስረታ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የሚያሳየን ኢትዮጵያ የፓርቲዎች እጥረት ስለአለባት የዜጎችን የመደራጀት ዲሞክራሲያዊ መብት ለመደገፍ ካላቸው ቀና አመለካካት ሳይሆን መድረክ የኢህአዴግ “ፎርጅድ ኮፒነቱን” ለማሳካት የጎደለውን የአማራ ፓርቲ ለመሙላት ብቻ ነው፡፡ መድረክ በትግራይ ዓረና ለህውሃት፣ በኦሮሚያ ኦፌኮ ለኦህዴ፣ በደቡብ የፕሮፌሰር በየነ ፓርቲዎች እና የሲዳማው ድርጅት ለደህዲን የተዘጋጁ ሲሆን ለብአዴን ግን የአቻ ፓርቲ ችግር ነበረበት፡፡ ከዚህ በፊት አንድነትን በውስጠ ታዋቂነትም ሲከፋም በይፋ የአማራ ፓርቲ አድርገው ይፈርጁ ሰለነበር ከአንድነት መውጣት በኋላ ይህ ክፍተት “ፎርጅድ ኮፒ” ለመሆን እንኳን አላሰቻላቸውም፡፡ አሁን ግን የነፃነት ፓርቲ መምጣት ከመኢህአድም ሆነ ከሰማያዊ ጋር ያላቸውን ስር የሰደደ ጥላቻ አስወግደው ከመሻረክ ይህን የአንድነት ፍራሽ በማሰገባት ድሮ አንድነት ሊውጠን ነው ከሚለው ስጋታቸው ወጥተው እኩያቸው የሆነ ፓርቲ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል፡፡ ነፃነት ቢሮ የሌለው ማህተምና ፋይል በሰዎች መኖሪያ ቤት የሚገኝ፣ ይህ ነው የሚባል ድርጅታዊ ጥንካሬ የሌለው ፓርቲ ሰለሆነ ለመድረክ አባል ድርጅቶች የእኩዮች ጥምረት ይሆናል፡፡ “የፎርጅድ ኮፒ” ፕሮጀክት ክፍተትም ይሞላል፡፡ እንደሚታወቀው የፓርቲዎች ውህደት እኩል ሳይሆኑ በእኩልነት መንፈስ ይባላል፡፡
ለማነኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ እውነተኛ የዲሞክራሲ ስርዓት እንዲኖር ይፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ የሚሆነው አውነትኛ የድርጅት አቅም ያላቸው አማራጭ የሚሆኑ፤ ህዝቡ ቢመርጣቸው የመንግሰት ሃላፊነት ተረክበው ሊያስተዳድሩት የሚችሉ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይፈልጋል፡፡ በግሌ አንድ ፓርቲ መንግሰት ብሆን የካቢኔ አባሎቼ እነ እገሌ ናቸው ብሎ ብቃት ያላቸው 30 ሰዎች የሚያሳየኝ ካለ አባል ለመሆን ዝግጁ ነኝ፡፡ አንድነት ውስጥ ይህን ማደረግ ስለሚቻል ነበር ለፖለቲካ ስልጣን የምንሰራው፣ ይህ በገዢው ፓርቲ አልተወደደም፡፡ በገዢው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚ ነን በሚሉት ጭምር (ሰማያዊና መድረክን ጨምሮ) በተለይ ሰማያዊ በአንድነት ፍራሽ የሚጠነክር መስሎት ስለነበር፡፡ ነገሩ ግን የተገላቢጦሸ ነው የሆነው፡፡
አሁንም በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ስርዓት እንዲኖር ካስፈለገ፤ የሚፈጠረው ፓርቲ እንደ ኢህአዴግ አመራር የማይወጣው 7 ሚሊዮን አባል በመስብሰብ የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጥሩ አባላትን በማብዛት ሳይሆን ምርጦች የሚሰበሰቡበት፣ ለጥቅም ሳይሆን “ለአቅመ መስጠት” የደረሱ፤በአውቀታቸው እና ከራሳቸውና ከቤተሰባቸው አልፈው ለዜጎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ፍትህ የሚጨነቁ ብቻ ሳይሆን አማራጭ መፍትፈሔ የሚያቀርቡ፣ በየደረጃው ለፖለቲካ አመራር የሚሰባሰቡበት መሆን ይኖርበታል፡፡ ሰለዚህ መስጠት የማይችሉ ለአቅመ መስጠት እስኪበቁ በደጋፊነት መቆየት ይኖርባቸዋል፡፡ መረዳት ያለባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባልም ሳይሆኑ በዲሞክራሲ ስርዓት ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ በዚህ የሚጠቀሙት የኢህአዴግ አባለት ጭምር ስለሚሆኑ፡፡
በተመሳሳይ ጠንካራ ሚዲያ እና ሲቪል ተቋማት መኖር አለባቸው፡፡ አርዳታ ለማሰጠት እና ለራሳቸው የስራ እድል ለመፍጠር የተደራጁ ሲቪል ማኅበራት፣ በዕትመት ለመቆየት ለዘብተኛ የሆኑ ሚዲያዎች ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ፋይዳ የላቸውም፡፡ ይፍረሱ!!!!!

No comments:

Post a Comment