የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኬሚስትሪው መቀየሩን ወይም በቀላሉ ሊቀየርበት
የሚችልበት ደረጃ ላይ መገኘቱን ሰንቶቻችን ገብቶናል፡፡ ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ምን አልባትም አንድነት ፓርቲ “ድንክ” ከመደረጉ
እና ለምር ፖለቲካ ሳይሆን ለፌዝ ፖለቲካቸው እንዲመጥናቸው ለማድረግ በደህንነት ተቋም ውሣኔ ከመተላለፉ በፊት የኢትዮጵያ ፖለቲካ
ፓርቲ ተበዬዎች በርዕዮተ ዓለም መስመር ለይተው ግብ ግብ ለመግጠም ሳይሆን ሁሉም ተባብሮ ህወሓት/ኢህአዴግ የሚባልን ሰይጣናዊ ሀይል
በማሰወገድ ቀጥሎም የፖለቲካ ምእዳር ማስተካከል ቀጥሎ ደግሞ እርስ በእርስ መወዳደር የሚል ነበር፡፡ በአንድ አንዶች አገላለፅ ትግሉ
“የነፃነት የፍትህና የዴሞክራሲ” ስለሆነ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ በተፃራሪ የቆመ ሁሉ ተባብሮ መስራት ይጠበቅበታል የሚል ነበር፡፡
ትክክልም ነበር፡፡
ተባብሮ መስራት እና ሕዝቡን ለነፃነቱ ቀናሂ በመሆን ጭቆና በቃኝ፣
ነፃነት ያስፈልገኛል፣ አማራጭ እፈልጋለሁ፣ ወዘተ እንዲል ማነሳሳተ ትክክለኛ የፖለቲካ ውሣኔ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር አንድነት ፓርቲ “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” በሚል “በፀረ ሸብር” ተብዬ ሕግ ላይ ያደረገው ዘመቻ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡
ሚሊዮኖች ለፖለቲካ ፕሮግራም ልዩነት እና ተመሳሳይነት ሳይሆን አፋኝ የሆነውን የህወሓት/ኢህአዴግን ሥርዓት እንቢኝ ያሉበት ነበር፡፡
በዚህ እንቅስቃሴ በብሔር የተደረጃው ብሔር ዘለል ከሆነው አደረጃጀት ጋር በጋራ ለመቆም ሙከራ አድርጓል፡፡ መድረክና አንድነት የነበራቸው
ግንኙነት ዓይነት፡፡ የግንኙነቱ ወጤት አሳዛኝ የነበረ ቢሆንም፡፡
ዛሬ ላይ ሆነን ስንመለከተው በአኔ እምነት ፖለቲካው ተቀይሯል፡፡
ወይም ሊቀየር የሚችልበት ደረጃ የደረሰ ይመስለኛል፡፡ ዶክተር አብይ የሚመራው ኢህአዴግ የመለስ ዜናውን የአብየታዊ ዴሞክራሲ/ልማታዊ
መንግሰት ተረኮች ወደ ጎን በማለት (በራሳቸው ቃል ለመጠቀም) ለተፉካካሪዎች ምቹ የፖለቲካ ምሕዳር የሚከፍቱ ከሆነ ጉዳዩ ኢህአዴግን
በማንኛውም መንገድ ይወገድ ከሚለው መስመር መላቀቅ ግድ ይለናል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ መሣሪያ አንስተው ይዋጣልን ያሉትም ቢሆኑ
የሚመለከት ስለሆነ መሣሪያውን አፈሙዝ አሰደፍቶ ወደ እስክሪብቶና ወረቀት ጫወታ ይቀየራል ማለት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የጫወታ ሕግ
ለጋራ አገራችን በፉክክር ማመን፣ ለሕዝብ ዳኝነት መቅረብ፣ ጀግንነት ማሸነፍ ሳይሆን መሸነፍን መቀበል የሚሆንበት
ይሆናል ማለት ነው፡፡ ጫወታው ተሸንፎ ጭምር ጀግና የሚኮንበት መሆን
ይኖርበታል፡፡
ይህ እድል አሁን በበር ላይ ቆሞ ያለ ይመስለኛል፡፡ ክፈት በለው በሩን
…. ብለን እንገባ ወይስ በሩ ተከፍቷል ግቡ እንባል የሚለው እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ዶክተር አብይ አና ቡድናቸው በአፋጣኝ
መሳሪያ ያነሱትን ሀይሎች መሳረያቸውን አስቀምጠው በሕግ ወደሚመራ ጫወታ እንዲገቡ ጥሪ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ከፖለቲካ አሻጥር
ነፃ የሆነ ጥሪ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ወሳኝ የሆነ የፖለቲካ ጅማሮ ነው በሩ መከፈቱን ማብሰርና ግቡ ማለት ያስፈልጋል፡፡ በአገር
ቤት የምንገኝ አማራጭ አለን የምንል ደግሞ አማራጫችንን ይዘን ክፈት በለው በሩን ማለት ይኖርብናል፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ “ትግሉ
የነፃነት ነው” በሚል በርዕዮት ዓለም ይሁን በግብ ከማይመስለን ጋር ሁሉ መሞዳሞድ መቆም ይኖርበታል፡፡ ጫወታው በሃሣብ ብልጫ እና
በምናቀርበው አማራጭ ልዕልና የሚወሰን መሆኑን ተረድተን ለዚሁ መትጋት ይኖርብናል፡፡ አደረጃጀታችን ይህን የሚመልስ እንጂ የኢህአዴግን
አደረጃጀት የሚመጥን ቁጥር ፍለጋ አባላት በማግበስበስ ላይ የሚመሰረት መሆን የለበትም፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአሁን በኋላ መብት ተነክቷል ለነፃነትህ ተነስ ብሎ
ቀስቃሽ አይፈልግም፡፡ በየሰፈሩ እና መንደሩ ይህ ጉዳይ በጎበዝ አለቆች፣ በቄሮና ዘርማ እየተመራ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ
የፖለቲካ ፓርቲ አያስፈልግም፡፡ እደግመዋለሁ የፖለቲካ ፓርቲ አያስፈልግም፡፡ ለዚህ ጉዳይ ጠንካራ ሲቪል ማህበራት መኖር የግድ የሚልበት
ሁኔታ ይታየኛል፡፡ ጥያቄዎች በስርዓት እንዲቀረርቡ፣ ዜጎች የተለያዩ አማራጭ ማቅረቢያ ዘዴዎችን በየደረጃው እንዲጠቀሙ የሚያስተምሩ
ተቋማት ያስፈልጋሉ፡፡ ለሁሉም ጥያቄ መንገድ መዝጋት እሳት ማንደድ ተገቢ ሰላልሆነ ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ማንሳት ያለብኝ
በቅርቡ ወንድማችን በቀላ ገርባ በግፍ ከሚማቅቅበት እስርe ቤት ያስፈታው የመንግሰት ቸርነት ሳይሆን ቄሮ ያነደደው አሳት መሆኑ
ግልፅ ሆኖ ሳላ ትልቁ ሰው በቀለ ገርባ ግን ዛሬም ይህ አማራጭ ብቸኛው አማራጭ ያለመሆኑን ይስብካል፡፡ የዚህ ዓይነት በመርዕ ላይ
ያሉ ሰባኪዎች ያስፈልጉናል፡፡ እስክንድር ነጋ “ፕሮፌሽናል እንቢተኞች” በሚል የጠራቸው የእርሱ ዓይነቶቹን መብት ተሟጋቾች የአስቸኳያ
ጊዜ አዋጅ ምናቸውም እንዳልሆነ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመብቱ፣ ለነፃነቱ፣ ወዘተ የጀመረውን እንቅስቃሴ እስከመጨረሻው መቀጠል
ይኖርበታል እያለን ነው፡፡ ይህ ሁሉ ግን የሚሆነው በሠላማዊ እንቢተኝነት ብቻ መሆን አለበት ብሎ እየሰበከን ነው፡፡ በእኔ እምነትም
እሳት ማንደድ የመጨረሻው አማራጭ መሆን ይኖርበታል፡፡ የህወሓት እጅ መስብሰብ ካቃተው እንቢታው ከበዛ፣ ዳተኝነት ካየለ ግን እሳት
ማንደዱ፣ መንገድ መዝጋቱ የግድ መሆኑን አምናለሁ፡፡ ያስፈልጋልም፡፡
ባለፈው አጭር ክታቤ ኢትዮጵያ ስንት ፓርቲ ያስፈልጋታል ስል ጉዳዩን
ወደ ቁጥር አውርደውተ የነበሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ ጉዳዩ የቁጥር አልነበረም፡፡ ለሕዝብ ትከክለኛ አማራጭ ሊያቀርቡ የሚችሉ ምን ያህል
የተደራጁ ሀይሎች ያስፈልጋሉ? የሚል ነበር፡፡ ለምሣሌ በግሌ በብሔር ለመደራጀት ፈቃደኛ አይደለሁም፡፡ ሰለዚህ በአገራችን ከሰማኒያ
በላይ የብሔር ድርጅቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ መብታቸው ነው፡፡ በፌዴራል ደረጃ ሥልጣን ለመያዝ ግን አንድ ድርጅት በቂ ሊሆን የሚችልበት
ሁኔታ በኢትዮጵያችን የለም፡፡ ሰለዚህ ግንባር መፍጠር የግድ ይላል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ሁነኛው ምሣሌ በህወሓት የሚመራው ኢህአዴግ
ሲሆን፤ ሌላው አማራጭ ደግሞ መድረክ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ አሁን በውጭ የሚገኙ በብሔር የተደራጅ ሀይሎች ኢህአዴግን ወይም መድረክን
መቀላቀል ወይም ደግሞ የራሳቸውን ግንባር ፈጥረው መምጣት ወይም ደግሞ በክልል ደረጃ ለመሳተፍ ብቻ መወስን ይችላሉ፡፡ የዚህ ዓይነት ስንት ስብስብ ያስፈልጋል? ጥያቄው ይህ
ብቻ ነው፡፡
በብሔር መደራጀት የማንፈልግ “የሃሣብ ሰብስብ” እንዲኖር የምንፈልግ
ሰዎች ደግሞ አሁን በአገራችን ያሉትን ሰርተፊኬት ያላቸውን ፓርቲዎች ከቁም ነገር ወስደን ጫወታ ለመጀመር የሚቻልበት ሁኔታ እንደሌለ
የረጀም ጊዜ ግምገማችን ያሣያል፡፡ ከዚህ ውጭ ያለው አማራጭ ደግሞ በተዓምር ከላይ ዱብ ሊል አይችልም፡፡ ዶክተር አብይም ቢሆን ኢህአዴግን ከህወሓት
የአይዲዎሎጂ ቅርቃር አውጥቶ ለውድድር የሚሆን ቁመና ያለው ፓርቲ ማድረግ ትልቁ ሃላፊነቱ ሲሆን ይህን በአግባቡ ሲወጣ ሌላ ሀይል
የሚፈጠርበት ምዕዳር ይመቻቻል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ዶክተር አብይ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ መርዝ ከኢህአዴግ ካላስተፋልን
በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ አማራጭ የሚባል ነገር የምር የለም፡፡ ሰለዚህ ሌላ ሀይል መፍጠር አይቻልም፡፡ አማራጩ እሳት ማንደድ እና
ማስገደድ ብቻ ይሆናል፡፡ እሳት እንዳይነድ አማራጭ ሀይል እንዲፈጠር ደግሞ የዶክተር አብይ አመራር ከባድ ሃላፊነት አለበት፡፡ የእኛ
ደግሞ ሃላፊነት አማራጭ ሀይል መፍጠሩ ላይ ነው፡፡ ይህን ሀይል መፍጠር ደገሞ አሁን በፓርቲ ጥላ ሥር የሚገኙም ሆነ ከዚያ ውጭ
ሆነው በዚህች አገር የፖለቲካ ዕጣ ፋንታ ሃላፊነት አለብኝ የሚሉ ዜጎችን ሁሉ ይመለከታል፡፡ ያለበለዚያ ግን እንደ ከዚህ ቀደሙ
ህወሓት/ኢሕአዴግን በማውግዝ፤ የሕዝብ ጥያቄ የሚመልስ አማራጭ ሳይኖረን ከቆየን፤ ዘመኑን አልዋጀንም እና ዋጋ አይኖረንም፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም በክብር ትኑር!!!
ግርማ ሠይፉ ማሩ
ቅዳሜ ግንቦት 4/2010
No comments:
Post a Comment