Wednesday, August 29, 2018

የፓርቲ የንግድ ተቋማት የወደፊት ዕጣ ፈንታ - የግል ምልከታ



የዛሬ ፅሁፍ መነሻ አቶ በረከት ስምዖን ጥረትን ከሃያ ሚሊዮን ብር መነሻ ወደ 11 ቢሊዮን አድርሼ ነው የለቀቅሁት የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ መግለጫ እነዚህን ተቋማት ምን ያህል የዘረፋ ድርጅቶች እንደሆኑ ከማሳየት ውጭ አንድም እነ በረከት እና ታደሰ ጥንቅሹን ታማኝ ናቸው የሚያስብል ቁምነገር አላየሁበትም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ብአዴን እነዚህ ድርጅቶች ከፓርቲ እጅ ወጥተው ወደ መንግሰት ይዛወሩ የሚል ውሣኔ መወሰኑንም ሰምተናል፡፡ ይህ በጎ ጅምር ግን ወደ መጨረሻው ትክክለኛው መንገድ መሄድ ይኖርበታል፡፡
በእኔ እምነት በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ድርጅቶች (በአራቱም አባል ድርጅቶች ማለቴ ነው) ወደ መንግሰት ይዞታነት ሳይሆን መዛወር ያለባቸው ወደ ግል ይዞታነት መዛወር ይኖርባቸዋል፡፡ ሰለዝውውሩ አማራጭ ከማቅረቤ በፊት ግን ለዚህ ዝውውር የሚሆን አንድ አንድ ሃሳቦችን ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡
ለምሣሌ ኤፈርት በእውነት የትግራይ ሕዝብ ድርጅት ነው? ይህ ከእውነት የራቀ ነው፡፡ በኢትየዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሴራ የሚሰራው የንግድ ተቋም በኤፈርት የሚመራው ነው፡፡ ይህ ድርጅት የትግራይ ሕዝብ ንብረት ነው እያሉ ሕዝቡን ላም አለኝ በሰማይ ሲያጓጉት ኖረዋል፡፡ ተሰፋው ተሰፋ ሆኖ የሚቀር ቢሆንም፣ እርግጠኛ የሆነ ነገርም አለ፡፡ እነዚህ ድርጅቶች በተወሰኑ የትግራይ አካባቢዎች የስራ እድል ፈጥረዋል፡፡ የህወሓት ካድሬዎች በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞ ይህን የሥራ እድል የሚቀርባቸው አድርገው የሚሰሩት ፕሮፓጋንዳ ማንኛውንም ወደ ሕጋዊነት የሚወስድ አማራጭ በሕዝብ ድምፅ ስም ማደናቀፋቸው የሚቀር አይደለም፡፡ ይህ ከግምት ውስጥ መግባት እና የሕዝብ ተጠቃሚነት ባለበት ሁኔታ ሁሉ የሕዝቡ ጥቅም ጉዳት ላይ እንደማይወድቅ ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ ይህ የተጠና የህዝብ ግንኙነት ሥራ ይፈልጋል፡፡ ምን ያመጣሉ በሚል እሣቢ ፈግጪው ፈግጠው ማለት አይገባም፡፡ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ በተለይ በእኛ አገር ሁኔታ በብሔር ፖለቲካ በሚናጥ ሲሆን እና አናሶች ከስልጣን ተገፋን ሲሉ ችግሩ የከፋ ሊሆን ይችላል፡፡
ሌላው ጉዳይ በተለይ በኦሮሚያ የሚታየው ድባብ ነው፡፡ በኦህዴድ ካድሬዎች ሰፈር የሚታየው ሰሜት ኤፈርትን ወደ ሕጋዊ ሥርዓት ማስገባት ሳይሆን ኦሕዴድም እንደ ሕወሓት ሌላ የኢኮኖሚ ኢምፓየር እንዲገነባ መገፋፋት ነው፡፡ ይህ ትክክለኛ አቅጣጫ አይደለም፡፡ የዚህ ሕገወጥነት የሚጀምረው የፖለቲካ ሥልጣን የያዙ ሰዎች ኢኮኖሚ መዘወር ሲጀምሩ የማሻጠር ጉዳዩም አብሮ ይፈጠራል፡፡ በረከት ሰምዖን  በአደባባይ እንደነገረን ሃያ ሚሊዮን፤ አሰራ አንድ ቢሊዮን የሚሆንበት አስማት ይፈጠራል ማለት ነው፡፡ ከአስማቶቹ አንዱ በሕገ ወጥ መንገድ የመንግሰት ንብረት ወደ ፓርቲ ንብረት ማዛወር አንዱ ሲሆን፣ ያለብቃት ትርፍ የሚያስገኝ አሰራር መዘርጋት ሌላው ነው፡፡ ሰራተኛ እንዴት እንደሚቀጥሩ አቶ በረከት የነገሩን ሚስጥር አሳፋሪ መሆኑን የምንታዘብ ያለን አይመስላቸውም፡፡ ዜጎች በውድድር ሳይሆን በክልል መንግሰት ዝርዝራቸው ቀርቦ እንዲመደቡ ይላካል ነው ያሉን፡፡ ይህ አቶ ሙሉጌታ ጓዴ የኤፈርትን ቅሌት በኢሳት ቀርበው ካስረዱን እውነት ጋር መሳ ለመሳ የሚገጥም ነው፡፡
እነዚህ ተቋማት አሁን መንግሥት የሚሰጣቸው ድጋፍ ሲቋረጥ የደም ስር እንደተቆረጠ የሚቆጠር ነው፡፡ ይሞታሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሀብት፣ ንብረት ከሁሉም በላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የስራ እድል ይዘው እንዳይሞቱ መንግሥት የተጠና እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ሳይሞቱ አገርና ሕዝብ በሚጠቅም ሁኔታ ወደ ሕጋዊ መስመር ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ በእኔ እምነት ሁለት አማራጮች አሉ፡፡ ሌሎችም ሊኖሩ ይችላሉ፤ ብቸና የሚባል ነገር አይደለም፡፡
አንደኛ አማራጭ፡ እነዚህ የሁሉም ፓርቲዎች ንብረቶች ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተዘረፉ ንብረቶች የተመሰረቱ እና ከምስረታ በኋላም በሕገ ወጥ መንገድ እንዲደልቡ የተደረጉ በመሆናቸው የፌዴራል መንግሰቱ ወደ ግል ይዞታ እንዲዛወሩ በማድረግ፤ ገንዘቡን ለክልሎች በቀመር መሰረት ማካፈል ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ አማራጭ አስቸጋሪ የሚያደርገው ከፍተኛውን ንብረት የያዘው ኤፈርት/ሕወሓት ፈቃደኝነት ያለመኖር ብቻ ሳይሆን፤ በህዝብ ዘንድ ሲነዛ የነበረው የትግራይ ሕዝብ ንብረት ነው የሚለው መሰረተ ቢስ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ ከዚህ ከላይ በጠቀስኩት መልክ በተፈጠረ ሥራ ለፍቶ ከማግኘት በላይ የተጠቀመው ነገር የለም፡፡ ዋንኛዎቹ ተጠቃሚዎች የፖለቲካ ሹሞቹ መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ የፖለቲካ ስልጣን በማንኛውም ሁኔታ ለመያዝ የሞት የሸረት ትግል የሚያደርጉትም ለዚህ የግል ጥቅማቸው ነው፡፡
ሁለተኛው አማራጭ፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ምክንያት ከትግራይ ሕዝብ ጋር መሰረት የሌለውም ቢሆን ቁርሾ የሚገባበት ሁኔታ ሳይኖር፤ እነዚህ ድርጅቶች በሙሉ በሸያጭ ወደ ግል ይዞታነት እንዲዛወሩ ተደርጎ፤ ከሽያጭ የሚገኘውን ገቢ ክልሎች ለበጀት ድጎማ እንዲጠቀሙበት እና ልዩ ልዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲገነቡበት ሊፈቅድ ይችላል፡፡ ይህ ወደ ግል የማዛውር ሂደት በዋነኝነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ችሮታ መሆኑ ታውቆ የተወሰኑ የፖለቲካ ልሂቃን እጅ እንዳይገባ የፌዴራል መንግሰቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግበት የሚገባ መሆን አለበት፡፡ ይህ አማራጭ ኢትዮጵያ አገራችን ትልቅና ከዚህ የላቀ ሀብት የማፍራት አቅም እንዳላት ማመን ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያዊያን ከእጥረትና እጦት አስተሳሰብ መላቀቃችንን የሚያሳይ ነው፡፡ በእኔ እምነት የተሻለ አማራጭ አድርጌም እወስደዋለሁ፡፡
ይህ የሚደረገው አሁን በፖለቲካ ፓርቲዎች ስም በሕገወጥ መንገድ ያሉትን ማስወገድ ብቻ ሳይሆን፤ ከአሁን በኋላ በአገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመሩት የንግድ ተቋም በምንም መልኩ መፈቀድ እንዳይኖርበት መሰረት ለመጣል ነው፡፡ አሁን የተቋቋሙትም በአፋጣኝ ወደ ሕጋዊ ስርዓት መግባት የግድ ይላቸዋል፡፡ እነዚህ ተቋሞች አሁን ያለው ሕገወጥ አሰራር ሲቆም መሞታቸው የማይቀር ነው፡፡ ሲሞቱ ደግሞ እጅግ ብዙ ሀብትና ንብረት ይዘው እንደሚሆን ግልፅ ነው፡፡ ሰለዚህ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ለማደግም ሆነ ለመሞት በእነዚህ ድርጅቶች እጣ ፈንታ ላይ ቆራጥ ውሣኔ በመወሰን በቀጣይ ለሚመጣው የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ስራ ሊያቀልለት ይገባል፡፡ ካልሆነ ቀጣዩ ጊዜ አገር ግንባታ ሳይሆን የጭቅጭቅ እና የንትርክ ከማድረግ አልፉ እናልፈዋለን የምንለውን የሰላም ማጣት አዙሪት በድጋሚ እንዳይገጥምን ያስፈራል፡፡


No comments:

Post a Comment