Sunday, December 16, 2018

የሁለት ዘጋቢ ፊልሞች ወግ


ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ በታህሣስ 2 ቀን 2011 ዓ.ም ምሽት በተለያዩ ሚዲያዎች የቀረበው በህወሓት/ኢህአዴግ መንግሰት የደረሰውን የስብዓዊ መብት ጥስት የሚያሳይ ቅንጭብ ዘጋቢ ፊልም ከቀረበ በኋላ፣ ከዘህ በፊት በሚቴክ ዙሪያ የቀረበውን የዘረፋ ዘጋቢ ፊልም ጨምሮ ትክልል አይደለም የሚሉ፤ በተለይ ይህ ድርጊት የትግራይ ሕዝብን አንገት ለማስደፋት በአብዬ መንግሰት የሚደረግ ሴራ ነው በሚል በንዴት የጦፉ ሰዎች ጉትጎታ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች እኔም እንደነርሱ በንዴት እንድጦዝ እና ተባባሪ ሆኜ የዘጋቢ ፊልሙን እንዳወግዝ የቀረበልኝ ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ የቀረበልኝ ደግሞ ከዚህ ቀደም በህወሓት/ኢህአዴግ የሚሰሩ ዘጋቢ ፊልሞች “ዜጎችን በሀሰት ለመወንጅል ይጠቀምበት ነበር፡፡” በሚል በአደባባይ እንዲሁም በምክር ቤት አቅርበው በነበረው አቤቱታ መነሻ ነው፡፡

እውነት ነው ህወሓት/ኢህአዴግ ተከሳሾችን በፍርድ ቤት ብይን ሳይሰጥ ወንጀልኛ አድርጎ አሸባሪ ብሎ ይፈርጅ ነበር፡፡ ከሁሉም የሚከፋው ደግሞ በሕገ መንግሰት አንቀፅ 19/5 “ የተያዙ ሰዎች በራሳቸው ላይ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችል የአምነት ቃል እንዲሰጡ ወይም ማናቸውንም ማስረጃ እንዲያምኑ አይገደዱም፡፡ በማስገደድ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነት አይኖረወም፡፡” የሚለውን ሕገ መንግሰታዊ የስብዓዊ መብት ድንጋጌ በመተላለፍ ተጠርጣሪዎችን በዘጋቢ ፊልም ውስጥ ቆርጦ እየቀጠለ በሚያስገባው ሀሰተኛ የቪዲዮ ምስል እራሳቸውን እንዲወነጅሉ እና በራሳቸው ላይ ማስረጃ እንዲሆኑ በሀስት ያደርግ ነበር፡፡ ከሁሉም የሚከፋው ደግሞ የእወሸት ማስረጃዎችን እያቀረቡ ለዶክመንተሪ ግብዓት ማድረግ በግልፅ ሲሰሩ የነበሩ አስከፊ የዘጋቢ ፊልም ትውስታችን ናቸው፡፡ ይህ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው የዘጋቢ ፊልም ታሪካችን ነው፡፡ የዚህን ዓይነት ዘጋቢ ፊልም አለማውገዝ ነውር ነው፡፡

ዛሬ ደግሞ በአገር ላይ የተደረገን ዘረፋ እና በዜጎች ላይ የተፈፀመን አጅግ ዘግናኝ ግፍ ለምን በጨረፍታ በሚዲያ ይቀርባሉ? የሚሉ ሰዎች ተነስተዋል፡፡ ህወሓትና የህወሓት ደጋፊዎች (አዲስ ገቢ ደጋፊዎችን ጭምር) የቀድሞ ዘጋቢ ፊልም መሰራቱ ሰህተት መሆኑን አምነው በዚህ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ይቅርታ ባልጠየቁበት ሁኔታ፤ ይልቁንም በዚህ በሀስት ዘጋቢ ፊልም ደጋፊነት የታሰሩ ዜጎች ወንጀለኞች ነበሩ ብለው እያመኑ፤ እነዚህ ሰዎች አሁን ከእስር የተለቀቁት በምዕረት ነው ከሚል አረዳድ ሳይላቀቁ፤ አሁን የሚሰራው ዘጋቢ ፊልም ትክክል አይደለም ለማለት ምን ሞራል እንዳላቸው አይገባኝም፡፡ የዚህ ዓይነት ዘጋቢ ፊልም ፍትህን በሚዲያ እንደመስጠት ነው ብለው ባደባባይ ሲጮኹም ትንሽ  እንኳን አፍረት ቢጤ አይሰማቸም፡፡ እነዚሁ ሰዎች ደግሞ ሕገ መንግሰት ይከበር በሚል ሰላማዊ ሠልፍ ሁሉ ጠርተው ይጮሃሉ፡፡ ሕገ መንግሰቱ በአንቀፅ 28/1 ላይ “ በአስገዳጅ ሰውን የመሰወር ወይም ኢሰብዓዊ የድብደባ ድርጊቶችን በፈፀሙ ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ አይታገድም፡፡ በሕግ አውጭም ክፍልም ሆነ በማንኛውም የመንግሥት አካል ውሳኔዎች በምሕረት ወይም በይቅርታ አይታለፉም፡፡” የሚለው በሕገ መንግሰቱ ውስጥ እንደሚገኝ የሚነግራቸው አላገኙም፡፡

እነዚህ የህወሓተ ደጋፊዎች የእኔ ቢጤ የቀደመውን የዘጋቢ ፊልም አጥብቀን ስንኮንን ለነበርን ሰዎች በሁለት መለኪያ የምንጠቀም መርህ አልባዎች አድርገው ሁሉ ይኮንኑናል፡፡ በአደባባይ ጭምር ሊከሱን ይዳዳቸዋል፡፡ የሚያስገርመው ደግሞ እነዚሁ ሰዎች አሁን ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የሚደረገው ጥረት ዝም ብሎ ቢሆን እና ለምን እንደታሰሩ ጉዳቸው በጨረፍታ ባይገለፅ መረጃ ይሰጠን ብሎ ለመጮኽ የሚቀድማቸው አይኖርም፡፡ ሰለዚህ በዚህ አጭር ፅሁፍ ማስተላለፍ የፈለኩት መልዕክት የእነዚህ ሁሉት ዘጋቢ ፊልምች ወግ የተለያየ መሆኑን ነው፡፡

በአገራችን ኢትዮጵያ ያለመታደል ሆኖ የዚህ ዓይነት ዘጋቢ ፊልም የመስራት አቅም ያለው መንግሰት በመሆኑ እና የግል ሚዲያዎች የምርመራ ጋዜጠኝነት ለመስራት የሚያስችል አቅም ማጣታቸው ይህን ጉዳይ እንደ አዲስ ክስተት እየተመለከትነው እንገኛለን፡፡ በማንኛውም አገር በአገር ሀብት ላይ ዘረፋ፣ በዜጎች ላይ የመብት ጥሰተ ተደርጎ ቢገኝ ሚደያዎች ሰጋ እንዳያ ውሻ ተረባርበው በተለያየ አቅጣጫ ትንተና ይስራሉ፡፡ ለሕዝብና ለመንግሰት ከፍ ሲልም ለዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ጉዳዩ እንዲደርስ ሌት ተቀን ይወተውታሉ፡፡ ይህን በማድረጋቸው ወንጀለኞች ይጋለጣሉ፣ ለወንጀል ከለላ የሚሰጡ መንግሰታትም መውጫ መግቢያ እንዲያጡ ያደርጋሉ፡፡ በመጨረሻ ወንጀለኞች ወደ ማይቀረው የፍትህ አደባባይ ይቀርባሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ፍርድ ቤቶች በሚዲያ የቀረበውን ሳይሆን በክሱ ወቅት የቀረበውን ተመልክተው ይበይናሉ፡፡ ተጠያቂነት ይስፍናል፤ ዘጋቢ ፊልሞች የመጨረሻ ግባቸው ተጠያቂነት እንዲሰፍን ነው፡፡ ዘጋቢ ፊልም ዜና እንደመስራት ቀላል አይደለም፡፡

ዘጋቢ ፊልም ለመስራት እጅግ ብዙ ጋዜጠኞች በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ማለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሕይወት መስዋዕትነት የሚከፍሉ ጋዜጠኞ ብዙ ናቸው፡፡ በዚህ ዓይነት የዘጋቢ ፊልም ሥራ አልጀዚራን የሚያክለ ያለ አይመስለኝም፡፡ በሰውር ካሜራና የተለየ የሚስጥር ሰነዶችን በመፈተሸ ወንጀሎችን ያጋልጣሉ፡፡ ይህ በኢትዮጵያችን እንዲያብብ መትጋት ይኖርብናል፡፡

በእኔ እምነት ወንጀለኞ በምንም መስፈርት የሚወክሉት ብሔር ወይም ዓይማኖት አይኖርም፡፡ የሚወክሉት ቡድን ቢኖር የዘረፋ ኔትወርካቸውን ነው፡፡ አንድን ተጠርጣሪ በቁጥጥራቸው ሥር ካሰገቡ በኋላ የጣት ቀለበት፣ የአንገት አብል፣ ሞባይ የመሳሰሉ ውድ ዋጋ ያላቸውን ንብረቶች የሚቀሙ ዘራፊዎች ተራ ሌቦች እንጂ የአንድ ብሔር ወኪል ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ፈጣሪ ያሳያችሁ በሴትነት ክብር ለመኖር የማትፈልግ ውርጋጥ ሴት፣ ሴቶችን ልትወክል የምትችልበት አንድም የወል ሥም አይኖርም፡፡ ይህ ነውረኛ ድርጊት ዛሬ ሳይሆን ቀደም ሲል ህወሓት በዋና ሥልጣን መንበር ላይ በነበረበት ወቅት የቀረበ ሀቅ አሁን ግን በአደባባይ በመንግሰት ሚዲያ ጭምር መገለፁ ምን ነውር እንዳለው አልገባኝም፡፡ ይህ ድርጊት በመፅኃፍ ሠንዶ ካቀረበልን የግፉ ሰለባ የነበረው ሀብታሙ አያሌው እንዲህ ይላል፤

 “ሰለዚያ የስቃይ ማማ (ማዕከላዊ ማለቱ ነው) የቱን አንስቼ የቱን ልተው?  ያልሆንኩት ነገር የለም፤ ታዲያ! የሆንኩትን ብዬ የቱን የቱን ልፃፍ?  አያችሁ ያልሆንኩት ከሌለ ሁሉንም ሆኛለሁ፡፡ ሀሉም ሊፃፍ አይችልም፡፡ እንዲሁ ጊዜ እንዲፈታው እንደ ሙዚቃው ንጉሥ እንደ ጥላሁን ገሰሰ “ሆድ ይፍጀው” ማለቱ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ጠቅሶ ለማለፍ ያህል ግን  እነሆ ማዕከላዊን በጨረፍታ፤ ..” ይለንና፡፡ ከህወሓት ሰማይ ስር በሚል ካሳተመው መፅኃፍ ከገጽ 288-302 ዝርዝሩ ቅርቧል፣
ዘጋቢ ፊልሙ የዚህ ታሪክ ቅንጫቢ ነው፡፡ ሀብታሙ አያሌው ጊዜ  እንዲፈታው የተወው ጉድ እንግዲ፤ ጊዘው ደርሶ በታህሣስ 2 በተለያዩ ሚዲያዎች ለሕዝብ በይፋ ቀረበ፡፡ በፅሁፍ ተሰንዶ የተቀመጠን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለምን በቪዲዮ ቀረበ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝ፡፡ ዘጋቢ ፊልሙ ፍርድ ቤትን ያሳስታል ከተባለ፣ የሀብታሙ አያሌው መፅኃፍም ፍርድ ቤትን ሰለሚያሳስት ተሰብስቦ ይቃጠል፡፡ እረ ጎበዝ እየተስተዋለ፡፡
ግርማ ሠይፉ ማሩ

No comments:

Post a Comment