ግርማ ሠይፉ
|
ምርጫ 2012 …
|
ምርጫ 2012 የሚመለከቱ መጣጥፎች
|
|
ግርማ ሠይፉ
|
1/1/2012
|
ይህ ሠነድ በተለያዩ ጊዜዎች በመፅሔት ላይ የወጡ ናቸው፡፡
|
Contents
1 መግቢያ
ከዚህ በታች ያሉት ፅሁፎች በተለያየ ጊዜ የተፃፉ
ናቸው ምርጫ በሚመለከት እና ምን ማድረግ እንዳለብን የሚያሳይ ነው፡፡ እነዚህን ፅሁፎቸ ብቻ ለብቻ በራሳቸው ሊነበቡ የሚችሉ ናቸው፡፡
አንዱ ርዕስ ከሌላው ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ ሰለዚህ ከዚህ በፊት እነዚህን ፅሁፎች ለማንበብ እድል ያላገኛቸሁ ታነቡት ዘንድ
እዚህ ላይ አቅርቢያለሁ፡፡
2 የምርጫ ዋዜማ እንዴት ነው?
በአሜሪካን
አገር ለምርጫ አንድ ዓመት ሲቀረው፤ የምርጫ ዋዜማ ነው፡፡ እኛስ እንዴት ነን? በአሜሪካ በሥልጣን ላይ ያለው ፕሬዝዳንት፤ ቀጣይ
የምርጫ ዘመን የሚመለከተው ከሆነ ወይም ለቀጣይ ፓርቲው አባል ማሳለፍ ካለበት በርትቶ በምርጫ የሚሳተፍበት ዓመት ነው፡፡ ዘንድሮ
እንደምትታዘቡት ሪፐብሊካኖች ግራ ተጋብተዋል፡፡ ትራምፕ ለቀጣዩ ምርጫ የማይቀርብበት እድል ሊፈጠር ቢችል ሌላ ዕጩ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡
ይህ ዕጩ ደግሞ በደንብ በምርጫ ዋዜማው በሕዝብ መታየት ይኖርበታል፡፡ ይህ እየሆነ አይደለም፡፡ ዴሞክራቶች ከሂላሪ ክሊንተን ሸንፈት
በኋላ እዚህ ግባ የሚባል፣ ዓይነ ግቡ መሪ ማቅረብ የቻሉ አይመስሉም፡፡ ምክንያቱም በአሜሪካ ምርጫ ልዩ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር
አንድ ተመራጭ ፕሬዝደንት፤ የመድገም እድሉ ስፊ ነው፡፡ ሰለዚህ ብዙ ድካም አያስፈልገውም የሚል ታሳቢ ሊወሰድ ይቻላል፡፡ የዘንድሮ
ግን ልዩ ሁኔታ ነው፡፡ በመንበሩ ላይ ያሉት ትራምፕ ናቸው፡፡ ትራምፕ ደግሞ ልዩ ናቸው፡፡ ቢያንስ በታችኛው ምክር ቤት ይከሰሱ
የሚል ቀይ ካርድ ተሰጥቷቸዋል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ዴሞክራቶቹን ዓይነ ግቡ መሪ ማቅረብ አላስቻላቸውም፡፡ አሁንም የቀድሞ የኦባማ
ምክትል ፕሬዝዳንት ጆን ባይደን እና አዛውንቶ ሳንደርሰን ከፊት የሚታዩበት የምርጫ ዘመቻ ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ ዴሞክራቶቹ ከሃያ
በላይ ዕጩ ፕሬዝዳንት መሆን የሚሹ ሰዎች ቀርበው በጋዜጠኛ ሲፋጠጡ፣ ደጋፊ በሚሉት ፊት ተገኝተው ምን ይዘው እንደሚመጡ ሲደሰኩሩ
ከርመዋል፡፡ ይህ ፓርቲዎች የመጨረሻ ዕጩ የሚሉትን ወስነው ከተፉካካሪያቸው ጋር ወሳኝ ግጥሚያ እስኪጀምሩ፤ የማጣሪያው ጫወታ ይቀጥላል፡፡
እስከ ምርጫው እለት ያለው ሁሉ የምርጫ ዋዜማ ነው፡፡ ቢያንስ የዓመት የምርጫ ዋዜማ በሚዲያ እናያለን፡፡
ወደ
አገራቸን ፊታችንን መለስ ስናደርግ ደግሞ፣ ለምርጫ የቀረው ጊዜ አራት ወር ብቻ ነው፡፡ የምርጫ ዋዜማ የሚመስል ነገር ከፓርቲዎች
ሰፈር አይታይም፡፡ የገዢው ፓርቲ አመራሮች፤ ጠቅላይ ሚኒትሩን ጨምሮ ቦረና ድረስ ዘልቀው አትርሱን አለን ማለታቸው፤ ኢዜማ በአዲስ
አበባ፤ በባሕር ዳር፣ አዳማ እንዲሁም ሀወሳ ያደረገው ከሕዝብ ጋር የመገናኘት ሙከራ እንደ ፍንጭ ሊታይ የሚችል ነው፡፡ ለምርጫ
ፉክክር ያደርጋሉ የሚባሉት ፓርቲዎች ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆነ አይታወቅም፡፡ እንኳን እኛ ዜጎች አይደለንም ፓርቲዎችን ለመመዝገብ
አስፈላጊም ሲሆን ለመሰረዝ ማለትም የፓርቲዎችን ውልደትም ክስመትም ሲፈጠር ይህን ወሣኝ ኩነት እንዲከውን ሥልጣን የተሰጠው የምርጫ
ቦርድም የሚያወቀው አይደለም፡፡ በቅርቡ መመሪያ ቁጥር 3/ 2012 በሚል በብርቱካን ሚደቅሣ ፊርማ የወጣው መመሪያ ተግባራዊ ሲሆን
ቁርጡ ይለያል ተብሎ ይታመናል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የተደራጁ ፓርቲዎች ቢያንስ አሰር ሺ የፓርቲ አባላት ሊኖራቸው የግድ ይላል
ሰለሚል፤ ምን ያህል ፓርቲዎች በዚህ ደረጃ የሚፈለገውን መስፈርት አሟልተው ይመዘጋባሉ? የሚለው ጥያቄ አፍጥጦ ቀርቧል፡፡ ይህ ግዴታ
በምክር ቤት በፀደቀው አዋጅ ሕግ ከሆነ በኋላ በአጭር ጊዜ የሚለወጥ እንዳልሆነ እሙን ነው፡፡ ሕጉ ይህን በሚመለከትም ምንም የሽግግር
ጊዜ አልሰጠም፡፡ መመሪያ ቁጥር 3/2012 ይህን መመሪያው ከወጣበት ታህሣስ 25 ቀን ጀምሮ በሁለት ወር ጊዜ ማሟላት እንዳለባቸው
ገልፆ ማስታወቂያ አስንግሯል፡፡ ባሉበት በደብዳቤ እንዲደርሳቸውም ተደርጓል፡፡ ሰለዚህ የካቲት 25 ድረስ የምርጫ ተሳታፊዎች ይለያሉ
ተብሎ ይታመናል፡፡
ይህ
መመሪያ በቁጥር አንሰተኛ የሆነ ሕዝብ ያላቸው አንድ አንድ ብሔረሰቦችና/ሕዝቦችን እንወክላለን የሚሉ ግለሰቦችን የፖለቲካ ፓርቲ
ሆነው እንዲመዘገቡ እድል የሚሰጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ለዚህ የሚሆን ክፍተትም ፈጥሯል፡፡ በግሌ እነዚህ ግለሰቦች/ስብስቦች በሲቪል
ማህበር ካልሆነ በስተቀር ለፓርቲነት መብቃት የለባቸውም ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ የማያስችል ማህበራዊ
መሰረት ይዘው፤ የፖለቲካ ፓርቲ ሰርተፊኬት ብቻውን መያዝ ትርጉሙ ሰለማይገባኝ ነው፡፡ ለምሣሌ በመቶ ሺ ዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ያሉት
አንድ ሕዝብ በምክር ቤት ሊኖረው የሚችለው መቀመጫ ቢበዛ አንድ ነው፡፡ በምክር ቤት አንድ መቀመጫ ማግኘት ምንም የፖለቲካ ሥልጣን
አያስገኝም፡፡ ድምፅ ለማሰማት ከሆነ በሲቪል ማህበር መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ሰለዚህ እነዚህ ሰዎች አሁን የፖለቲካ ፓርቲነት
ሠርተፊኬት የሚያገኙ ከሆነ በአገራችን እስከ 83 የሚሆኑ የፖለቲካ ሰርተፊኬት ባለቤቶች ይኖራሉ ብለን መገመት እንችላለን፡፡
በአገር
አቀፍ ፓርቲ የሚመዘገቡት ቢያንስ አሰር ሺ አባላት የተጠየቁት ፓርቲዎች በእኔ ግምት ከአምስት ይበልጣሉ ብዬ ለማመን እቸገራለሁ፡፡
በግንባር ቀደምትነት አሁን የምናያቸው የብልፅግና ፓርቲ እና ኢዜማ ሁለቱ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ሶሰቱን መገመት ያስቸግራል፡፡ መድረክ ውሕድ
ፓርቲ አይደለም፤ በውስጡ የሚገኙት ህብረ ብሔራዊም የሆኑት አስር ሺ ማግኘት አንችልም ብለው ተናግረዋል፡፡ ለምሣሌ በፕ/ሮ በየነ
የሚመራው ፓርቲ ይህን ሸፍጥ ነው ብሎ በሚዲያ አውግዞታል፡፡ ሌሎቹ አራቱ (ዓረና፣ ኦፌኮ፣ ሲዳማና የአፋር ፓርቲዎች) የብሔር ድርጅቶች
ሰለሆኑ በቀላሉ ሊወጡት የሚችሉት ናቸው፡፡ ሰለዚህ እንደ ግንባር ካልሆነ በአገር አቀፍ ፉክክሩ ብዙም ትኩረት የሚስቡ እየሆኑ አይደለም፡፡
ውሕደት ደግሞ በመድረክ ሰፈር የሚታሰብ አይደለም፡፡ ለማንኛውም እንደ ሶሰተኛ እንውሰዳቸው ብንል እና ሌላ ተጨማሪ ሁለት ይመጣሉ
ብለን ብንገምት፤ በድምሩ አምስት ፓርቲዎች ይኖሩናል ማለት ነው፡፡ ሌሎቹ ቢበዛ በክልል ካልሆነም ለወረዳ ምክር ቤት ምርጫ ነው
የሚወዳደሩት የሚል እምነት አለኝ፡፡
በምርጫ
ዋዜማ እነዚህ አምስት ፓርቲዎች ምን እየሰሩ ነው? ምርጫስ የአማራጭ ማቅረብ ጉዳይ
አይደለም ወይ? አማራጭ ሳይዙ ምረጡኝ ብሎ ሕዝብ ፊት መቅብ ይቻላል?
ቢቻልስ ነውር አይሆንም? ብዙ ዜጎች የምርጫ ዋዜማ ጉዳይ ያሰስበናል፡፡ በምርጫው ዋዜማ የምናያቸው ነገሮች፤ ከምርጫ በኋላ ምን
እንደሚሆን ለማወቅ/ለመገመት ሰለሚረዳን ነው፡፡ በእኔ እምነት በቀጣይ ሁለት ወራት በአገር አቀፍ ደረጃ ለውድድር የሚበቁ አገር
አቀፍ ፓርቲዎች ተለይተው ይታወቃሉ፡፡ ዝግጅታቸውን ፓርቲ መሆናቸውን ካወቁ በኋላ ነው የሚጀምሩት ካልተባለ በስተቀር፤ በቀጣይ ቀሪው
ሁለት ወር ፕሮግራማቸውን ለህዝብ ለመንገር በቂ ጊዜ ይመስለኛል፡፡ አሁንም በእኔ እምነት ብዙ ፓርቲዎች እንደ አሜሪካኖቹ አንድ
ዓመት የምርጫ ዋዜማ ቢሰጣቸው፤ ዓመት ሙሉ የሚያወሩት ብቻ አይደለም፤ ዓመት ሙሉ ከቦታ ቦታ የሚዞሩበት አቅምም የላቸውም፡፡ ሰለዚህ
የተዘጋጁት ነገር ካለ፤ ለመራጩ ሕዝብ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ሊነግሩት የሚችሉ ይመስለኛል፡፡ የተዘጋጀ ነገር ከሌላቸው ለቀጣይ
ምርጫ መሰረት የሚጥሉበት ዕድል አድርገው መውሰድ ብልዕነት ይመስለኛል፡፡
ቀሪዎቹ በብሔረሰብ/ሕዝብ ስም ተደራጅተናል
ብለው የፖለቲካ ፓርቲ ሠርተፊኬት ለመውሰድ የተዘጋጁ ሁሉ ልብ ሊሉት የሚገባው ነገር፤ በእርግጥም እንቆምለታለን ለሚሉት (ሕዝቡ
ወክሉኝ እስኪል ድረስ) ሕዝብ የሚያስቡ ከሆነ፣ ትኩረታቸውን ሕዝቡ በሚኖርበት አካባቢ በማድረግ፤ ዜጎች የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ
ሊሆኑ የሚችሉበትን እድል መፍጠር ይኖርባቸዋል፡፡ አገር አቀፍ ፓርቲ የሚሆኑትም ቢሆን የእነዚህን ማህበረሰብ ወኪሎች ወደ ምርጫ
ስለሚያቀርቡ እነርሱ ላይ ጫና የሚፈጥሩበትን አካባቢያዊ ጉዳይ አተኩረው ቢሰሩ መልካም ነው፡፡ ነገሩ በቅጡ ገብቷቸው ወደ ሲቪል
ማህበርነት እስኪቀየሩ፣ ገንቡ ሚና ለመጫወት መትጋት የምርጫ ዋዜማ ተግባራቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
በምርጫ ዋዜማ በቅርቡ የምናየው
ከፍተኛ የሚዲያ ቅስቀሳ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ በእኔ እምነት አሁን ያሉት ሚዲያዎች የሚፈቅዱትን ቀዳሚ የምርጫ ቅስቀሳ ሰዓት
በተገቢ ደረጃ የተዘጋጀ ፓርቲ አላውቅም፡፡ ቀጣዩ ሁለት ወር እንደ ፓርቲ ሠርተፊኬት ለማግኘት ከሚደረገው እሩጫ ጎን ለጎን ሚዲያዎቹን
በቅጡ ለመጠቀም አቅም መገንባትን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ይመስለኛል፡፡ የእኛ የምርጫ ዋዜማ እንደ አሜሪካኖቹ ዓመት ሙሉ
ባይዘልቅ እንኳን፤ ለሁለት ወራት በበቂ ሚዲያዎች ተጠቅመው ለሕዝቡ ምን አማራጭ እንዳላቸው ማስረዳት ቢችሉ ብዙ ርቀት ልንጓዝ የምንችልበት
እድል ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በፊት ባለው ተመክሮ እጅግ ብዙ ፓርቲዎች ይህን ሚዲያ እድል መጠቀም ሳይችሉ መቅረታቸው ይታወቃል፡፡
በአዲሱ የፓርቲ ምዝገባ ሕግ እጅግ ብዙ አባላት ያሉት ፓርቲ፤ ከአባላቶቹ ውስጥ ለሚዲያ የሚሆኑ ሰዎችን የሚያገኝበት እድል ይፈጥርለታል፡፡
የምርጫ ዋዜማ ጉዳያችንን ለማጠቃለል
የኢትዮጵያ ምርጫ ዋዜማ የሚጀምረው ከሁለት ወር በኋላ ፓርቲዎች ሕጋዊነታቸው ሲረጋገጥ ይሆናል፡፡ ከዚያ በፊት ፓርቲዎቹ ብዙ የሚሰሩት
ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ ፓርቲዎች በበቂ ሁኔታ በምርጫው እንዲወዳደሩ ተገቢው ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱና
ዋንኛው ፓርቲዎቹ አማራጭ ፖሊሲዎቻቸውን እንዲሁም ይህን ፖሊሲያቸው የሚፈፅሙ ዕጩዎችን ለሕዝብ የሚያሳውቁበት እደል መፍጠር ነው፡፡
ሚዲያዎች ይህን ማድረግ ግዴታ የሚጣልባቸው ቢሆንም ብቻውን ይህን ማድረግ ግን ሥጋ ሰጥቶ ቢላ እንደ መከልከል የሚቆጠር ይመስለኛል፡፡
ሲቪል ማህበራት ሕበረቶች በመተባበር ፓርቲዎች ሚዲያዎችን ሊጠቀሙ የሚችሉበትን ስቱዲዮዎች እና ባለሞያዎች በማዘጋጀት የሚዲያ ፕሮዳክሽን
ድጋፍ እንዲሰጡ ቢደረግ መልካም ይመስለኛል፡፡ ምርጫ ቦርድ ለዚህ የሚሆን መጠነኛ ድጋፍ ለሲቪል ማህበራት ሊያደርግ የሚችልበት አቅም
አያጣም፡፡ ሴቶችን በምርጫ እንዲሳተፉ ለማበረታታት ሙከራ እያደረጉ ያሉ አካላት ለሴቶች ዕጩዎች የሚዲያ ፕሮዳክሽን ድጋፍ ስቱዲዮ
መገንባት አስቸጋሪ ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ አማራጭ ያላቸው ነገር ግን አማራጫቸውን ለማቅረብ የሚያስችል አቅም ያጠራቸውን ፓርቲዎች
በመደገፍ የምርጫ ዋዜማነችን ሠላማዊ እናድርገው፡፡
ቸር ይግጠመን…. መልካም የጥምቀት
በዓል ይሁንልን!!!
3 የፖለቲካ ፓርቲዎች መቧደን ለቀጣይ ምርጫ ያለው እንደምታ
ምርጫው
የማይቀር መሆኑ እየተነገረ ባለበት ሰሞን፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተለመደው የደቦ ፀብና ገዢ ፓርቲውን ከመውቀስ ተላቀው፤ የገዢውን
ፓርቲ ፈለግ ተከትለው ለመሰባሰብ የወሰኑ ይመስላል፡፡ ይህ ትክክለኛ አካሄድ ይመስለኛል፡፡ ፓርቲዎች ከእርስ በእርስ መሻኮት ወደ
መተባበር ማጋደላቸው መልካም መሆኑን አስምረን፤ ምን ችግር ሊገጥማቸው ይችላል? ምን መልካም አጋጣሚስ አለው? የሚለውን ማየትም
ጠቃሚ ነው በማለት ይህን ፅሁፍ ጀምሪያለሁ፡፡
የገዢው
ፓርቲ ከምን ጊዜ በላይ ቆራጥ ውሣኔ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ ውሣኔው “የሚለየን
ሞት ነው!” የሚሉ የትግል አጋሮችን ሁሉ ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆን፤ ለመክፈል ቁርጠኝነት የታየበት የውዕደት ውሣኔ ነበር፡፡
ይህ ፅሁፍ በሚዘጋጅበት ወቅት ኦዴፓ፣ አዴፓ እና ደሕዴን የሚባሉ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የነበሩ ከስመዋል፡፡ ከምርጫ ቦርድ
መዝገብም መሰረዛቸውን የሚያረጋግጥ ይሁንታ አግኝተዋል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ሌሎች አምስት አጋር ድርጅቶች ለመክስም መወሰናቸው
እና በምርጫ ቦርድ ተቀባይነት ማግኘታቸው ዜና ነበር፡፡ የእነዚህ ሰምንት የፖለቲካ ድርጅቶች መክስም በተመለከተ ክርክር ያነሳ አካል
የለም፡፡ እነዚ ድርጅቶች ሕግ በሚጠይቀው መሰረት በፓርቲያቸው ከፍተኛ የሥልጣን አካል በጉባዔ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ ለጊዜው አምስቱን
አጋር ድርጅቶች ወደ ጎን አድርገን፤ ሰለ ሶስቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ጉዳይ ብንመለከት፤ የእነዚህ ድርጅቶች መክስም ሌላው
ውጤት ኢህአዴግ የሚባውን ድርጅት እልውና ማሳጣቱ ነው፡፡ ኢህአዴግ እንደ ግንባር ውዕደት ለመፍጠር መወሰኑን፤ ቀጥሎም በአባል ድርጅቶች
መካከል የሃሣብ ልዩነት መፈጠሩ የሰሞኑ አብዬ አጀንዳ ሆኖ መክረሙ ይታወቃል፡፡ ሕገ ደንባዊ አይደለም የሚሉ ንትርኮች በብዛት ሲነገሩ
ከርመዋል፡፡ አውነታው ግን ኢህአዴግ እንደ ግንባር ለውዕደት ባይወስን እንኳን፤ አባል ድርጅቶች በተለያየ ምክንያት አባልነታቸውን
ካቋረጡ፤ ኢህአዴግ በውዕደት ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገር አይደለም፤ መፍረስ የግድ እንደሚለው
ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ እነዚህ አባል ድርጅቶች ሕጋዊነቱ ላይ ምንም ጥያቄ በማያስነሳ መልኩ “መክሰማቸውን” አረጋግጠው፤ ለምርጫ ቦርድ አሳውቀው ተቀባይነት
አግኝተዋል፡፡
ከአሁን በኋላ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ፣
የኢህአዴግ ምክር ቤት ወይም ጠቅላላ ጉባዔ የሚባል ነገር ሊጠራ የሚችልብት አንድም ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡ የሌሉ ድርጅቶች
ግንባር ሊኖር አይችልም፡፡ ከአሁን በኋላ ተሰባስቦ ይህን ወሰነ የሚል መግለጫም የማንሰማ መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡ የኢህአዴግ አባል
ድርጅቶች ከነበሩት ሶስቱ፤ አጋሮቻቸውን አስከትለው ሌላ አዲስ ፓርቲ ለመመስረት መወሰናቸው በፓርቲዎቹ የውዕደት ሰምምነት ፊርማ
ተረጋግጧል፡፡ የምርጫ ሕጉ ፓርቲዎች ለመክሰም በጉባዔ ወስነው፣ ለውዕደት በፓርቲ መሪዎች ፊርማ ካረጋገጡ በቂ ነው፡፡ የአዲስ ፓርቲ
ምስረታ ባለመሆኑ ውዕደቱን ለመቀበል፤ ምርጫ ቦርድ ችግር የለበትም፡፡ አሁን በመሬት ላይ የሚታየው ችግር የኢህአዴግ መፈረስ፣ የአባሎችና
አጋሮች መክሰም (ህወሓትን ሳይጨምር) አይደለም፡፡ የብልጽግና ፓርቲ እልው መሆን ነው፡፡ የብልፅግና ፓርቲ የመመስራች የጋራ ጉባኤም
አላካሄደም፡፡ በጉባዔ የሚመረጡ የፓርቲ አመራሮች አልተመረጡም፡፡ በጨበጣ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች እየተባሉ የሚጠሩት ቀደም የኢህአዴግ
አመራሮች ናቸው፡፡ አጋር ድርጅቶች በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ምን ድርሻ አገኙ? ከቀድሞ በምን ይለያል? ቀመሩስ እንዴት ነው? መልስ
የሚሹ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ለማንኛውም ብልፅግና በሩን ገርበብ አድርጎ ህወሓትን እየጠበቀ መሆኑ ቢታወቅም፤ ህወሓት በሩን ዘግታ ሌላ
ሸሪክ እየፈለገች መሆኑ ፍንጭ ይታያል፡፡ ይሳካ ይሆን? ከባድ ጥያቄ ነው፡፡
ለብልፅግና ፓርቲ ምሥረታ ከባድ
የሚባለውን መስዋዕትነት በመክፈል፤ ብልፅግና ፓርቲ ካለበት የሕጋዊነት ከፍተት ጭምር ለዚህ ያደረሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤
መሰረታቸው ከሆነው ከኦሮሞ ማህበረሰብ ለመነጠል ከተለያዩ ቡድኖች ከባድ ፈተና እየገጠማቸው ነው፡፡ ወደ ሥልጣን ማማው ከፍ ለማለት
በማድባት ላይ በነበሩበት ዋዜማ ጀምሮ በነገር ሲጎነትላቸው የነበረው አክቲቪስት ጀዋር መሐመድ፤ የጠቅላዩ የብልፅግና መንገድ አልተዋጠለትም፡፡
ኦዴፓ የብልፅግና ፓርቲን እንዳይመሰርት/እንዳይቀላቀል፣ ካልሆነ ደግሞ እንዲከፈል በጥፍሩም በጥርሱም ሞክሮ ሳይሳካለት በመቅረቱ
ሌላ ሙከራ ላይ ይገኛል፡፡ ጀዋር መሐመድ በመሰረታዊነት የነበረው ዕቅድ ሁሉንም የኦሮሞ ፓርቲዎች በአንድ ላይ በማምጣት፤ ኦሮሚያ
ማንም የማይደርስባት የግል ግዛታቸው ማድረግ እና ይህን የተባበረ የኦሮሞ ድርጅቶች ሕብረት ደግሞ፤ ኢትዮጵያ የምትባለውን አገር
በሀያል ክንዱ ሥር ማድረግ ነበር፡፡ ለዚህም የእርሱ ሚና የአንጋሽነት እንዲሆን ማድረግ ነበር፡፡ ይህ ሊሳካ አልቻለም፡፡ በቁጥጥሬ
ሥር ናቸው ብሎ የሚያምናቸው የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴዎች ብቻ አይደለም፤ ከጠቅላላ ጉባዔውም ቢሆን ይህ ነው የሚባል ድጋፍ ማግኘት
ባለመቻሉ፤ ወደ ቀጣይ ዕቅድ መሸጋገሩን ይፋ አደርጓል፡፡ ባለፈው ሳምንት ከኦፌኮ ጋር አብሮ ለመስራት የወሰነ ሲሆን፤ ኦፌኮ ደግሞ
ከሌሎች የኦሮሞ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት እንዲሰማማ ተደርጓል፡፡ ይህ የኦሮሞ ፓርቲዎች መቧደን በኦሮሚያ ምርጫ ክልሎች የእርስ
በእርስ ሹኩቻውን ያስቀራል የሚል ሰፊ እምነት አለ፡፡ አሁን በጋራ ለመስራት ከወሰኑት ውጭ ያሉት የኦሮሞ ድርጅቶች አብዛኞቹ የህወሓት
ፍጡራን በመሆናቸው አሁን ብዙም ፋይዳ ያላቸው ሊሆኑ አይችሉም፡፡ አስገራሚ የሚሆነው ግን አሁን ኦፌኮና አብረው ለመስራት የተሰባሰቡት
“ኦነጎች” ብልፅግናን ለመግጠም በሚል የተሳሳተ ስሌት፤ ከህወሓት ጋር ከገጠሙ ነው፡፡ ይህ ስላቅ የሚሆን የገራፊ ተገራፊ ቅንጅት
የት እንደሚደርስ ጊዜው ሲደርስ የሚታይ ይሆናል፡፡
ሌላው ምርጫውን ለመሳተፍ ቡድን
የመሰረቱት ፓርቲዎች የልደቱ አያሌው-ኢዴፓ፣ የይልቃል ጌትነት-ኢሃን፣ እና ሕብር በመባል የሚታወቅ ጥምረት ሲሆኑ፤ የጥምረቱ አባላት
ማንነታቸው በግለፅ አይታወቅም፡፡ የእነዚህ ፓርቲዎች ጥምረት አገር አደጋ ላይ ነች ከሚል ድምዳሜ የተነሳ ሲሆን፤ በቀጣይ ምርጫ
በተለይ ከተሞችን አተኩረው እንደሚሳተፉ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች የመሰረቱት ቡድን፤ ከላይ ካነሳናቸው የቡድን አሰላለፎች ጋር
ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል ዓይነት አየደለም፤ ቢሆንም ግን ህወሓት የፌዴራሊስት ሀይል በማለት ለመስብሰብ ካሰበቻቸው አንድ አንድ
ፓርቲ ተብዬዎች መለየታቸውን አመላካች ሆኖ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በህወሓት እንደ ፌዴራሊስት ሀይል የሚቆጠሩት ፓርቲ ተብዬዎች ማረፊያ
ያጡ ይመስለኛል፡፡ ምንአልባት ህወሓት ጀዋር መሐመድን መዓከል አድርጎ ከሚመሰረተው የኦሮሞ ፓርቲዎች ጥምረት ጋር በጋራ መስራት
ካልቻለች፤ እነዚህን የሳምሶናይት ፓርቲዎች ልትጠቀምባቸው እንደምትችል የሚታወቅ ነው፡፡ ምክንያቱም የፌዴራሊስቶች ፎረም የሚባል
ስብስብ ባለፈው መቀሌ ላይ መመስረታቸው ይታወቃል፡፡ ሰለዚህ እንደ አስፈላጊነቱ በተጠሩበት የሚገኙ ስለሚሆን፤ ምርጫ እንደማያሻንፉ
ቢያውቁም ምርጫውን አስመልክቶ ትንሽ ገንዘብ ለማግኘት ከተቻላቸወም ቀውስ ለመፍጠር ሙከራ ያደርጋሉ የሚል ግምት መውስድ ይቻላል፡፡
እነዚህን ፓርቲ ተብዬዎች እንዴት አደርጎ በቀውስ አዙሪት ውስጥ እንዳይገቡ ማድረግ እንደሚቻል ማስብ ከባድ ነው፡፡ ይህን የምለው
ያለምክንያት አይደለም፤ በምርጫ ዋዜማ ላይ ሆነን የወጣን የፓርቲዎች እና የምርጫ ሕግ ተግባራዊ እንዳይሆን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ
ሙከራ ማድረጋቸው ለታዘበ፤ እነዚህ ፓርቲዎች በእርግጥም ሰለዚህች አገር ሠላም ያስባሉ ወይ? የሚል ጥያቄ ያጭራል፡፡
በነገራችን ላይ ኢዜማ የተለያዩ
እውቅና ያላቸው ፓርቲዎች ከስመው እንዲሁም በፓርቲ ምሥረታ ሂደት ላይ የነበሩ ስብስቦች ሂደቱን አቋርጠው የመሰረቱት አዲስ ፓርቲ
ሲሆን እንደ አንድ ሌላ ቡድን ሊታይ የሚችል ነው፡፡ ለምርጫው በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ስብስብ መሆኑን መመስከር እችላለሁ፡፡
ኢዜማ በተለያዩ አካባቢ የሚደረጉ ስብስቦችን በመልካም ጎናቸው የሚመለከታቸው ሲሆን፤ የምርጫ ውድድር በሃሳብ ሊሆን የሚችለው ከተወሰኑ
አማራጭ ይዘው ከሚቀርቡ ፓርቲዎች ጋር እንዲሆን ፍላጎት አለው፡፡ በኦሮሚያ አካባቢ አሁን ባለው የመስባሰብ አዝማሚያ ብልፅግና፣
ኢዜማ፣ የኦሮሞ ፓርቲዎች ስብስብ እንዲሁም አንድ ሁለት ተጨማሪ ፓርቲዎች ቢኖሩ በአምስት ቡድኖች መካከል የሚደረግ ፉክክር ይሆናል
ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህ ለመራጩም መደናገር ሳይፈጥርበት ሁሉም በሕዝብ የተሰጠውን ድምፅ ይዞ የሚወጣበት ሊሆን ይችላል የሚል እምነት
አለ፡፡ ሰለዚህ እነ ጀዋር የጀመሩት የማሰባሰብ ሂደት እጅግ ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ማስብ ይቻላል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ኦሮሚያ
የእኛ ብቻ ነች ከሚል ሰንካላ ሃሣብ መላቀቅ ከተቻለ ብቻ ይመስለኛል፡፡
በደቡብ አካባቢ የሚኖረው ሁኔታ
ከሁሉም የተለየ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ለአገራዊ ሥልጣን ምንም መሻቱ አይታይባቸውም፡፡ ትልቁ መሻት በዞን
ደረጃ ያለ ሲሆን፣ አብዛኞቹ አሁን የፓርቲ እውቅና ያላቸው ከአንድ እጅ ጣት የማይበልጥ የምክር ቤት መቀመጫ ያላቸው ናቸው፡፡ ሰለዚህ
በደቡብ አካባቢ ምርጫው ብልፅግና፣ ኢዜማ እና አንድ የዞን ወይም የወረዳ ተወካይ ፓርቲ ነው፡፡ በምሣሌ ለማስረዳት በኮንሶ ምርጫ
ክልል ሊወዳደር የሚችለው ብልፅግና፣ ኢዜማ እና የኮንሶ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ይሆናል ማለት ነው፡፡ የኮንሶ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት
ሌላ ቦታ ሄዶ ሊወዳደር የሚችልበት ምክንያት ያለ አይመስለኝም፡፡ በተመሳሳይ በአንድ አንድ የአማራ አካባቢዎች ውድድሩ ከዚህ የሚለይ
ላይሆን ይችላል፡፡ ለምሣሌ በቅማንት አካባቢ መወዳደር የሚችሉት የቅማንት ፓርቲ፣ አብን፣ ኢዜማ እና ብልፅግና ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ሌሎች ሁለት ተጨማሪ ፓርቲዎች ቢመጡ ሰድስት ፓርቲዎች አማራጭ ይዘው ይጋጠማሉ ማለት ነው፡፡ ይህ የፓርቲዎች መቧደን የሚሰጠን መልካም
እድል ነው፡፡ ፓርቲዎች በቁጥር አነስተኛ ሲሆኑ መራጩ ግራ ሳይጋባ ለመምረጥ እድል ያገኛል፡፡ ሰለዚህ የፓርቲዎች መቧደን ሊበረታታ
የሚገባው ተግባር ነው፡፡ ምርጫው በአማራጭ ላይ ሊመሰረት የሚችልበት እድል ይፈጥራል፡፡
ቸር ይግጠመን!!
4 የሽግግር መንግሥትን ያያችሁ!
በኢትዮጵያችን
የመንግሥት ሥልጣን መውጫና መውረጃው መንገድ ጠብመንጃ መሆኑን ሁሉም ያውቃል፡፡ ካልሆነ ደግሞ የተፈጥሮ ሞት መሪዎችን ሲጠራ ነው፡፡
ባለፉት መቶ ሃምሣ አመታት የዘመናዊ መንግሥት ምስረታ ታሪካችን፤ ነገስታቱም ሆኖ በሌላ ስያሜ አገሪቱን የተቆጣጠሩት ሰዎች እራሳቸው
ባወጡት ሕግ መሰረት እንኳን ለወራሾቻቸው ለማሸጋገር ሰኬታማ ጉዞ ያደረጉበት ሁኔታ የለም፡፡
በተፈጥሮ ሞት ሲሸኙ፤ አሰፍስፎ የሚጠብቀው በሚፈልገው መሰመር የሥልጣን ማማውን ይቆናጠጣል፡፡ የአቶ ሀይለማሪያም ደሣለኝ ወደ ሥልጣን
መምጣትም ይህንኑ የሴረኞች መንገድ የተከተለ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒሰትር መለስ ዜናዊን መሞት ተከትሎ በማግስቱ ኦቶ ሀይለማሪያምን
በዙፋኑ ላይ ቁጭ የሚያደርግ ሥርኣት አልተበጀም፡፡ በቀጣይም የሆነው ተመሳሳይ ነው፡፡ የአቶ ሀይለማሪያምን መልቀቅ ተከትሎ፤ አቶ
ደመቀ ቦታውን የሚወስዱበት ሕጋዊ ሥርዓት ያለመኖሩ፤ ለወደፊቱም እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ በእጃችን እንዳለ የሚያሳብቅ ነው፡፡ አቶ ሀይለማሪያም
ከሥልጣን መልቀቃቸውን ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር ነው ብሎ የሚያስቀን አይጠፋም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ጠቅላይ ሚኒሰትር አቶ ሀይለማሪያም
ደሣለኝ እየመጣ ያለውን የሕዝብ ግፊት/ሕዝባዊ ማእበል ተመልክተው በመንፍስ ቅዱስ ይሁን፣ በባለቤታቸው አመላካችነት፤ “ሥልጣን”
በቃኝ የሚመጣውን ለመቀበል ዝግጁ ነኝ ለማለት በመወሰናቸው፤ ለዚህች አገር ውለታ መዋላቸውን መመስከር እፈልጋሉ፡፡ በተጨማሪ ፕሬዝዳንት
መንግሥቱ ሀይለማሪያም በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ መቶ ታንኮችን አሰልፈው፤ ከተማውን አኬልዳማ የማድረግ እድል በእጃቸው እያለ፣
በማንም መካሪነትና ግፊት ይሁን፤ አገር ለቀው ለመውጣት በመወሰናቸው ባለውለታችን እንደሆኑ ይስማኛል፡፡ በአጠቃላይ የዘመናዊ መንግሥት
ታሪካችን የሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር የሌለበት መሆኑ ብቻ ሳይሆን አሁንም ቢሆን ይህን ለማድረግ በሚያስችል ቁመና ላይ ለመድረስ
ዝግጁነታችን ያጠራጥራል፡፡
አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም
ሆነ በቀጣይ ይሻሻላል ብለን በተስፋ የምንጠብቀው ካለ፤ ሥልጠና መያዣ መንገድ ምርጫና ምርጫ ብቻ እንደሚሆን ሁሉም ይስማማል፡፡
ምርጫ ማለት ደግሞ አማራጭ ቀርቦ፤ ሕዝቡ ይሆነኛል የሚለውን መምረጥ ሲችል ፤ የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ተክብሯል ልንል እንችላለን፡፡
“እንከን የለሽ” ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል የበለፀጉት አገራትን ማሳያ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ፕሬዝዳንት ትራም ምርጫ ለማጭበርበር
ከውጭ አገራት ጋር ተሻርከዋል በሚል መከራ ላይ ናቸው፡፡ “አንከን የለሽ” ምርጫ ብለው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ደም በደም
ያደረጉንን የ1997 ምርጫ በምንም የሚረሳ አይደለም፡፡ የአቶ መለስ ዜናዊና ጓዶቻቸው የታሪክ አካል ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ዛሬም ምርጫ
ማድረግ አለብን ሲባል እንከን ይጠፋዋል ከሚል መነሻ ሊሆን በፍፁም አይችልም፡፡ ሊፈጠሩ ይችላሉ የምንላቸውን ችግሮች ነቅሰን አውጥተን
ባናጠፋቸው፤ እንዴት እንቀንሳቸው? በሚለው ላይ መወያየት የሚያስፈልገን ወቅት ላይ እንገኛለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ምርጫ ለማካሄድ
ያሉብን እንከኖች በማጉላት፣ ለመፍትሔ ፍለጋ ሳይሆን በአቋራጭ ሥልጣን ለመያዣ፣ አድርጎ ለመጠቀም መሞከር፤ ነውረኝነት መስሎ ይስማኛል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ በሕዝብ ዘንድ
ያላቸው ተደማጭነት ምንም ያህል ይሁን፤ ለሚዲያ ቅርብ ሰለሆኑ እንዲሁም ደግሞ ሰሜት ቆስቋሽ ጉዳዮች ለሚዲያ ትኩረት ጠቃሚ በመሆኑ
ብቻ የሽግግር መንግስት ወይም የሽግግር ኮሚሽን ወይም የሽግግር ምክር ቤት ይቋቋም በሚል የተጀመረው ዘመቻ የት ያደርሳል? ብዬ
መጠየቅ እና መፈተሸ ፈልጊያለሁ፡፡ ይህን ሃሣብ ማንሳትና ማራመድ መብት መሆኑን አምናለሁ፤ አከብራለሁ፡፡ እኔም ይህን ለመፈተሽ
እና የግሌን ምልከታ ማካፈል መብቴ ነው ከሚል መነሻ ይህን ጉዳይ ለዛሬ ፅሁፌ መርጨዋለሁ፡፡
በአገራችን ኢትዮጵያ በውል የሚታወቅ
የሽግግር መንግስት ሰያሜ የተገኘው፤ ዘውጌ ብሔረተኞች በ19983 ግንቦት ወር በጦር ባገኙት ድል የአገሪቱን መዲና በተቆጣጡሩ ማግስት
የመሰረቱት መንግሥት ነው፡፡ ይህ በጦር የተገኘን ሥልጣን ቅቡልነት ለማስገኘት ሲባል የተደረገ የሽግግር ወቅት እንደነበር መቼም
የማይታባል ሀቅ ነው፡፡ በዚህ የሽግግር ወቀት አገርን በማንነት በመከፋፈል እና አገራዊ ምልከታዎችን እና ምልክቶችን አጥፍቶ በዘውጌ/በንዑስ
ብሔርተኝነት ለተደራጁ ሀይሎች የሕግና የመዋቅር ድጋፍ የሚሰጥ አደረጃጀት የፈጠረ፤ የሽግግር መንግስቱ አባል እንዲሆኑ የተፈቀደላቸው
ሁሉ ከተመልካችነት በዘለለ ይህ ነው የሚባል ፋይዳ ያልነበራቸው መሆኑን ስናውቅ፤ የሽግግር መንግሥት ናፍቆት ከየት እንደመጣ መገመት
ያስቸግራል፡፡ በሽግግር ወቅት የተረቀቀው ሕገ መንግሥት ለስሙ የህገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ቀጥሎ ደግሞ ጉባዔ የተሰየመለት ሲሆን፤
መቶ ስድስት አንቀፅ ከህወሓት ተልኮለት መቶ ስድስቱን አፅድቆ የወጣበት መሆኑን ለሚያውቅ ይህ የሽግግር ጊዜ ናፍቆት ለምን እንደሆነ
ሊገባው አይችልም፡፡ ደርግ ቆፍጣናና ነው፤ ሽግግር ብሎ አጃቢ አልጠራም፤ “ጊዚያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ” ተቋቁሟል ነው ያለው፡፡
በዓለማችን የተለያዩ አገራት፤ የእኛይቱን
ኢትዮጵያን ጨምር ከቅኝ ግዛት አሰተዳደር ወይም ከንጉሣዊ አገዛዝ ወደ ሪፐብሊክ ምስረታ ወይም በሕገ መንግሥት ወደሚመራ ሥርዓት
ለመሸጋገር “የሸግግር” ሂደቶችን አልፈዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉት “የሽግግር መንግሥት” የሚሉ ተረኮች በሙሉ ጉልበተኞች በሥልጣን
ላይ ያለውን አስወግደው፤ ለራሳቸው ሕጋዊነት ለማግኘት የሚጠቀሙበት መንገድ እንደሆነ ለመረዳት ይቻላል፡፡ ሰለዚህ አሁን አገራችን
ያለችበት ሁኔታ በሁሉም መመዘኛ አስቸጋሪ መሆኑን ሁሉም የሚያምን ቢሆንም፤ በሥልጣን ላይ ያለውን ሀይል ሳያስወግዱ በልመና የሽግግር
መንግሥት ይቋቋም ወይም ደግሞ ፈራ ተባ እያሉ “ግድ የለም እናንተ ሥልጣን ላይ ሆናችሁም ቢሆን፤ የሽግግር ኮሚሽን ይቋቋም” የሚል
ልመና ምላሹ ምን ሊሆን እንደሚችል አይገባኝም፡፡ አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን ቡድን/የብልፅግና ቡድን/ በጉልበት ማስወገድ የቻለ
ሀይል፤ የሽግግር መንግስት ምሰረታ ቢጠራ ለመካፈል ዝግጁ ነኝ፡፡
በዓለማችን አንባገነን ሥርዓቶች
በአንድ ወይም በሌላ መልኩ በጉልበት መወገድ ባልቻሉበት ወቅት፤ አንባገነኖችም ለራሳቸው መውጫ በር አበጅተው ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት
የሚሸጋገሩበት ተሞክሮ ለመረዳት መፅሃፍትን ማገላበጥ ይጠቅማል፡፡ የአሜሪካን ፖለቲካል ሳይንስ ማህበር በፈረንጆቹ አቆጣጠር
2013 ባወጣው ፅሁፍ “The Strength Concede: Ruling Parties and Democratization in Developing
Asia” በሚል በዳን ስታተር አና ጆሴፍ ዎንግ የተፃፈው የጥናት ፅሁፍ የእስያ አገራት እንዴት እንደተሻገሩ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም
መውጫ በር መሆኑን የሚያመላክት ማዕቀፍ ነው፡፡ አንባገነኖች በሕዝብ አመፅ ከመወገድ ሊታደጋቸው የሚችለው አንዱ መንገድ፤ እራሳቸውም
ባለድርሻ የሆኑበት ምርጫ ማካሄድና ውጤቱን መቀበል ነው፡፡ አንባገነኖቹን የሚቃወሙ ቡድኖችም ይህን ቀዳዳ ተጠቅመው ሥር እንዲተክሉ
የሚመክር ነው፡፡ ይህ ፅሁፍ ከወጣ በኋላ እንደ በርማ/ማይማር የመሳሰሉ አገሮች ተጠቅመውበት ውጤት አምጥተዋል፡፡ የሽግግር መንግስት
ሳይሆን “ነፃ ምርጫ” ማድረግ ነው የመረጡት መንገድ፡፡ በእኔ አምነት አገራችን አሁን ያለችበት ሁኔታ አንባገነኖች በከፈቱት ቀዳዳ
መጠቀም የሚያስችል ብልዕነት የሚጠይቅ እንደጂ፤ ጉንጭ አልፋ “የሽግግር ኮሚሽን” መጠየቅ አይመስለኝም፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አንበገነን
መንግሥታት ምርጫን በእኩል ምዕዳር ከማድረግ የተሻለ አማራጭ የላቸውም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የመንግሥትን ሥልጣን
ብቻ ሳይሆን ፤ገዢውን ፓርቲ ከታሪክ መዝገብ ላይ የሚፍቀው ውጤት ሊያመጣ ይችላል፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው ሀይል በስም ለውጥ በማታለል፤
ሕዝብን ከአሁን በኋላ በልማት ስም ለተጨማሪ የምርጫ ዘመን ሊመሩት/ሊገዙት እንደማይችሉ ሊረዱት ይገባል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ
እድል የሰጠው ኦ! ብሎ የወጣው ሕዝብ እንጂ አሁን የሽግግር ኮሚሽን/የሽግግር መንግሰት የሚጠይቁት ቡድኖች አይደሉም፡፡ እነዚህ
ቡድኖች ለቀጣይ ስድስት ወር በትጋት ሰርተው ለምርጫ ከተዘጋጁ እና ሕዝብ ይሁንታ ከሰጣቸው በቀጣዩ ምርጫ በሽግግር ከሚሽን አባልነት
ከሚያገኙት መቀመጫ የተሻለ በመንግሥት ባለድርሻነት ሕዝብ ሊወክላቸው ይችላል፡፡
አንድ በሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት
ተገፍትሮ ሳይወድቅ፤ ኑ! የሽግግር መንግስት እናቋቁም የሚልበት ምክንያት የለም፡፡ በቅርቡ በሱዳን የሆነውን በምሣሌ የሚያነሱ ሰዎች
ያስቁኛል፡፡ በሱዳን የሆነው ፕሬዝዳንቱ በወታደሩ ተፈንግሎ ማረፊያ ቪላ ሲገባ፤ ሲቨል ማህበራት የወታደር ፍንቀላ አንቀበልም ብለው
ጎዳና ወጡ፡፡ አፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ ሌሎች አካላት ፈንቃዩን አንቀበለም በማለት የሲቪል ማህበራትን ጥያቄ ደገፉ፡፡ ይህ አማራጭ
የሌለው የሸግግር ጥምር መንግሥት የሚፈልግ በመሆኑ፤ የጦር ሀይሉ ሁሉን ከሚያጣ ሊወስደው የሚገባ የመውጫ መንገድ መሆኑ እውነት
ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ይህን ሂደት በሽምግልና የተሳተፉበት በመሆኑ የተሞክሮ ችግር ሊኖርባቸው አይችልም፡፡ በእጃቸው
ያለውን ሥልጣን ከፈለጋችሁ ተወዳድረን በምርጫ ውስዱት ማለት ሳይበቃቸው፤ ከምርጫው በፊት እባካችሁ ኑ! እናንተ ምስኪን ተቃዋሚዎች
ሥልጣን እንጋራ ይላሉ ማለት የዋህ መሆን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ነባራዊ
ሁኔታ መንግሥትን ወጥሮ የያዘው ሕዝቡ ነበር፡፡ የሕዝቡ ግፊት መሰረት አድርጎ፤ በሕዝባዊ አመፅ ተወርውሬ ከምጣል ዴሞክራሲያዊ ምርጫ
አደርጋለሁ፤ ብሶት የፈጠሩ አፈናዎችን አነሳለሁ ብሎ መንግሥት ቃል ሲገባና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲጀምር፤ ሕዝቡ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡
ጥያቄው የሽግግር መንግሥት ቢሆን ኖሮ፤ ሕዝቡን ምንም ዓይነት ምድራዊ ሀይል አያስቆመውም ነበር፡፡ ሰለዚህ የሕዝብ ጥያቄ የፖለቲካ
አፈና እንዲቆም፤ ስብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፤ በሚፈጠረው ምቹ የፖለቲካ ምዕዳር የፈለገውን የፖለቲካ ፓርቲ ወደ ሥልጣን
የማምጣት ጥያቄ ነበር፤ አሁን ጥያቄው ይህ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ በምንም መልኩ ጥቂት ቡድኖቹን ወደ ሽግግር መንግሰት አምጥቶ በጫንቃው
ላይ ለማስቀመጥ አይደለም፡፡ ጎበዝ የሽግግር መንግስት ቢቋቋም ዝርዝሩ እንዴት ይሆናል ብላቸሁ ትገምታላችሁ? ተወያዩበት፤ እኔ ግን
የለሁበትም!!
ችር ይግጠመን!!
5 የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ፈልገው ምን አገኙ?
አገራችን ኢትዮጵያ ውስብስብ በሆነ የለውጥ ሂደት ውስጥ እያለፈች እንደሆነ
ብዙ ሰው ይገነዘባል ብዬ አምናለሁ፡፡ ጥቂቶች በለውጥ ጉዳይ ላይ ልዩነት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ በቅንብራዊ አስተሳሰብ ሀሁ ውጤታማ
የሆነ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው አምስት ታሣቢዎች ሲቀናበሩ እንደሆነ ያስተምረናል፡፡ እነርሱም፤ ራዕይ መሰነቅ፣ ክዕሎት መኖር፣ ተነሳሽነት፣ በጀት ማዘጋጀት እና የተግባር እቅድ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ
ፓርቲዎች ከእነዚህ ታሣቢዎች ውስጥ ምን ያህሉን በተሟላ ሁኔታ አድርገው ይንቀሳቀሳሉ? ምን ውጤት አገኙ? የሚለውን በዝርዝር መጠየቅና መልስ
መሻት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ያሉን የፖለቲካ
ፓርቲዎች በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ በመጨረሻ የሚገኙበት ሁኔታ ለለውጥ ስኬት ማድረግ ከሚገባቸው ውስጥ ባጎደሉት ታሣቢ ዓይነት
ሊሆን ይችላል፡፡ በዛሬ ፅሁፌ እነዚህ አምስት ታሳቢዎች በተራ በተራ በዝርዝር ለማሳየት አልሞክርም፡፡ ለመግቢያ ያህል ራዕይ የሌላቸው
ፓርቲዎች በውስብስብ የለውጥ ሂደት ምን ሁኔታ እንደሚገጥማቸው በማሳያነት አቅርቤ ወደ ፅሁፌ ዋና ጉዳይ እገባለሁ፡፡ ዋናው ጉዳይ
እጅግ ብዙ ፓርቲዎች ጫወታው ከመጀመሩ በፊት ከጫወታ ሜዳው የመውጣታቸው
ሀቅ ነው፡፡
በእኔ ግምገማ አሁን ባለው ሁኔታ ግራ የተጋቡ ፓርቲዎች የበዙበት ይመስላል፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ክዕሎት ያላቸው ጥቂት
ምሁራን ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ምሁራን ፓርቲ ለመመስረት የሚያስችል ተነሳሽነት የሚፈጥር ምክንያቶች የነበራቸው፤ እንዲሁም
እነዚሁ ልሂቃን ያላቸውን ተነሳሽነት በመመልከት ድጋፍ የሚያደርግላቸው ቡድን የተለያየ ሀብት ማስባሰብ ይችላሉ ተብሎ ይታመናል፡፡
በተጨማሪ የተግባር ዕቅድ አውጥተው የሚሰሩትን ነገር ሊያስቀምጡም ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ፓርቲዎች ግልፅ የሆነ ራዕይ የሌላቸው ሰለሚሆኑ ግራ የተጋቡ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ በግልፅ
ለመራጩ ህዝብ የሚያጋሩት ራዕይ የሌላቸው ፓርቲዎች፤ በወረቀት ላይ የሰፈረ ዕቅድና ይህን ዕቅድ ለመተግበር የሚያስፈልግ ሀብት ከየትም
ቢያገኙ፤ ግራ መጋባታቸውን ሊያስቀሩት አይችሉም፡፡ ለምን ራዕይ ሊኖራቸው አልቻለም? ብለን ስንጠይቅ፤ አሁን ባለንበት
ሁኔታ እነዚህ ፓርቲዎች ሕዝብ አንክሮ የተፋውን ቡድንተኝነት ወይም ደግሞ ከዚህ ቀደም እገሌ የሚባል ቡድን ነበር የሚገዛው በሚል
ትርክት፤ አሁን ደግሞ እኔ ተረኛ ነኝ የሚሉ ሰሜት ቀስቃሽ፤ ለጥቂቶች ተነሳሽነትን የሚፈጥሩ ጉዳዮችን አንገበው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው
ነው፡፡ ለአብዛኛው መራጭ ሕዝብ ተረኝነታችንን እወቅሉን ብለው ሊንቀሳቀሱ ሰለማይችሉ ብሎ መመለስ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ይህ ለሕዝብ
በይፋ የሚነገር ራዕይ ሊሆን ስለማይችል፡፡ ሰለዚህ እነዚህ ፓርቲዎች ግራ ተጋብተው ግራ የሚያገቡ መሆናቸው ይቀጥላል፡፡
በአገራችን የዚህ ዓይነት ፓርቲዎች በተለያዩ ቡድናዊ ፍላጎቶች የሚሰባሰቡ ጥቂት ሰዎችን ይዞ ጀማውን በአደባባይ ሊነግሩት
በማይችሉት የግል ፍላጎት ተተብትበው ግራ ተጋብተው ግራ የሚያጋቡ ሆነው እየቀጠሉ ነው፡፡ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በዝምታ ውስጥ
ሰለሚገኝ የጥቂቶች ጩኽት ጎልቶ ሰለሚሰማ፤ ሁሉም ትንንሽ የሚጮኹ ስብስቦች ይዘው ለአብዛኘው ሕዝብ የሚያጋሩት ራዕይ ሳይስንቁ፤
ግራ ተጋብተው በምርጫ ዋዜማ ላይ ደርሰዋል፡፡ ቁምነገሩ ግን እነዚህ ፓርቲዎች ወደ ቀጣዩ የፖለቲካ ሂደት የሚሻገሩበት ሁኔታ በተግባራ
የማይሆንበት ሁኔታ እየመጣ መሆኑን ምልክት እያየን ነው፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለውጥ ለውጥ ሲሉ የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ውስብስብ ለውጥ ለፓርቲዎቹ ምን ይዞ
መጣ? ፓርቲዎቹ
ሲጠብቁ የነበረውን ለውጥ አሁን የተጋፈጡትን ዓይነት ውጤት ይዞ እንዲመጣ ይጠብቁ ነበር ወይ? የሚሉ እና ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች
መጠየቅና በዝርዝር መፈተሸ የሚያስፈልግ ጉዳይ ነው፡፡ የፖለቲካ ምዕዳሩ እንዲሰፋ ስንጮኽ የነበረን ሰዎች የፖለቲካ ምዕዳሩ በተወሰነ
ደረጃ መስፋት የሚታይበት ቢሆንም፤ ከምርጫ ጋር ተያይዞ እጅግ ብዙ መሻሻል የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉ የሚታመን ቢሆንም፤ የፖለቲካ
ምዕዳሩ እንዲሰፋላቸው እና በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ የሚጠበቁት የፖለቲካ ፓርቲዎች በቦታው እየታዩ አይደለም፡፡ ይህን በጎ ሁኔታ
ተጠቅመው አማራጭ ፖሊሲ አቅርበው መንግሥት ለመሆን ውድድር ያደርጋሉ ብለን ብንጠብቅም የአራዳ ልጆች “ወፍ የለም” የሚሉት ዓይነት
ነገር እየታዘብን፤ ይልቁንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጫወታ የሚወጡበት ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን እየተመለከትን ነው፡፡
በግልፅ አነጋገር በቀጣዩ ምርጫ የፓርቲዎች ቁጥር እንደሚቀንስ እየታየ ነው፡፡ ይህም የሆነው ፓርቲዎች ቢያንስ በአገር
አቀፍ ደረጃ ለመንቀሳቀስ አስር ሺ አባላት ማስፈረም እንደሚኖርባቸው አስገዳጅ ድንጋጌ የያዘ አዋጅ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ ነው፡፡
በዚህ አዋጅ መነሻ በምርጫ ቦርድ በወጣው መመሪያ መሰረት የተሰጠው የሁለት ወር የድጋሚ ምዝገባ የጊዜ ገደብ ባለፈው ዕረቡ መጋቢት
3/2012 ተጠናቋል፡፡ በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ የድጋሚ ምዝገባ መሰፈርት አሟልቶ ያልቀረበ ፓርቲ ከምርጫ ቦርድ የባህር መዝገብ
የሚሰረዝ ይሆናል፡፡ በቀጣዩ ምርጫም የሚሳተፍበት እድል አይኖረም፡፡ ይህን ፈታኝ አቀበት ወጥቶ ለሕዝብ አማራጭ የሚሆን ፓርቲ ማግኘት
ቀላል ጉዳይ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አስራር በተለይ የመንግሥት ይሁንታ ያላቸው “በተቃዋሚ ስም” የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች
ያለምንም ችግር፤ ይልቁንም የገንዘብ ጉርሻ አያገኙ ጭምር የሀሰት መድበለ ፓርቲ ማሳያ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ይህ ነገር እንደማይቀጥል
ምልክት የሚሆኑ ነገሮች ለመታዘብ ያለፈው ዓመት ኡኡታቸውን ማድመጥ አንዱ ነው፡፡
ከዚህ ጋር በቴያያዘ በምርጫ ሕጉ የተመለከተውን አነስተኛ የመስራች አባላት ቁጥር በሃሰት ፊርማ ለመሙላት ሙከራ ያደረገ
ፓርቲ ጉዳዩ ለፖሊስ ምርመራ የተመራ መሆኑን ከማህበራዊ ሚዲያ ተመልከተናል፡፡ በእኔ እምነት ይህ በወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑ እንደተጠበቀ
ሆኖ፤ ምርጫ ቦርድ ይህን ጉዳይ ቀደም ብሎ በግልፅ በተደጋጋሚ በሚዲያ ለፓርቲዎችና ለህዝቡ በመግለፅ ወደዚህ ጉዳይ እንዳይገቡ የመከላከል
ሥራ ከወር በፊት መስራት ነበረበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ባለመደረጉ ብዙ ፓርቲዎች በተጭበረበረ ፊርማ የጊዜ ገደቡ ማጠናቀቂያ ዋዜማ
ላይ በማቅረብ፤ የፓርቲ ምስረታውን ለማድረግ ዝግጅት ላይ የነበሩ ሲሆን፤ ይህ የማሕበራዊ ዜና ድንጋጤ ውስጥ ሲከታቸው እጃቸውን
እንደሚሰበስቡ ይጠበቃል፡፡ ይህ ድርጊታቸው ቁጥራቸውን ይቀንሰዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ሁለቱን ወራት የምር አባላትን በመመልመልና
ታዕማኒነት ያለው ሰነድ ለማቀረብ ሲሰሩ ሳይሆን ያሳለፉት፤ የምርጫ ቦርድ ለውይይት የሚጠራውን መድረክ በምክር ቤት የፀደቀውን ሕግ
እየተቃወሙ ምሣቸውን በቅንጡ ሆቴል በልተው ለመሄድ ሲጠቀሙበት እንደነበር ስንታዘብ ነበር፡፡
ፓርቲዎች ለውጥ ለውጥ ብለው ሲጮኹ ከርመው ለውጡ እንዲያመጣላቸው የፈለጉትን፤ በሽግግር መንግሥት ስም ሥልጣን ላይ
መውጣት የሚሰችል ውጤት ሊሆን አልቻለም፡፡ ይመጣል ብዬም አልጠብቅም፡፡ ወይም ደግሞ በግርግር በሚደረግ ምርጫ ምንም ድርጅት ባይሰሩ፤
በስሜት በሚደረግ ምርጫ፤ በስልጣን ማማ ላይ እንወጣለን ያሉ ራዕይ አልባዎችን ማስተናገድ የሚቸገር አካሄደ እየሆነ መሆኑ ለመታዘብ
አያስቸግርም፡፡ ይልቁንም ፓርቲዎቹ ዕልውናቸው አደጋ ላይ መውደቁን እየተመለከትን ነው፡፡ አንዳንዶቹ ይህን በግልፅ ሲናገሩት ለማድመጥ
ችለናል፡፡ የፓርቲዎች ዕልውና ማጣት አሳሳቢ ጉዳይ ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች ጋር በግሌ አልስማማም፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች እልውናቸውን
ማረጋገጥ ያለባቸው፤ በያዙት ራዕይ እና ራዕያቸውን ለህዝብ የማጋራት ብቃት ላይ ብቻ ነው መመስረት ያለበት፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻሉ
ከጫወታ ቢውጡ የዕልውና ማጣት ሳይሆን፤ ለመድበለ ፓርቲ ሰርኣት ዕልውና ሲባል ቦታ መልቀቅ ሰለሚኖርባቸው፤ ለዚሁ የተከፈለ መስዋዕትነት
ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
በመጋቢት 3/2012 የጊዜ ገደብ ምርጫ ቦርድ የተለየ ሁኔታ ካልፈጠረ በስተቀር፤ በአማካይ በሁሉም ክልሎች ሁለት ሁለት
ፓርቲዎች ቢኖሩ 22 ክልላዊ ፓርቲዎች ይኖራሉ ተብሎ ቢገመት እና አራት አገር አቀፍ ፓርቲዎች ቢኖሩ በአጠቃላይ ሃያ ስድስት ፓርቲዎች
ብቻ ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ አሁን አሉ ከሚባሉት መቶ ስልሣ በላይ “የፓርቲ ስሞች” ወደ ሃያ ስድስት ግፋ ቢል ሰላሣ
ፓርቲዎች ቢኖሩ የፓርቲዎች የፖለቲካ ምዕዳር ይስፋ ጥያቄ የመጨረሻ ውጤት የመጀመሪያው ምዕራፍ መጀመሩን የምንመለከትበት ሳምንት
ነው ማለት ነው፡፡ በግሌ ሰላሣ ፓርቲዎቸ አይደለም፤ አስራ አምስት ፓርቲዎች በትክክል መስፈርት አሟልተው ከተመዘገቡ ትልቅ ነገር
ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ትንሣኤ መቃራቡን የሚያሳይ ጥሩ ምልክት አድርጌ እወሰደዋለሁ፡፡ ይህ እንዳይሆን ለማጭበርበር እና በተጭበረበረ
ሠነድ አሁንም ከጫወታ ላለመውጣት የሚደረጉ ሙከራዎችን፤ ምርጫ ቦርድ ያለምንም ይቅርታና ይሉኝታ ወደ መስመር ማስገባት እንዳለበት
ማስታወስ የግድ ይመስለኛል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ምርጫ ቦርድ ሸብረክ
ማለት ከጀመረ፤ የቦርዱ አባላት ለታሪክ የተቀመጡበትን ቦታ ያረክሱታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህን የሚያደርጉ ናቸው ብዬም ለመጠርጠር
የሚያስችል ምንም ምክንያት የለኝም፡፡
ሲጠቃለል በኢትዮጵያ እንደ አሸን የፈሉ ፓርቲዎች ለህዝብ ጥቅም ሲባል ቁጥራቸው የሚቀንስበት እድል የተፈጠረ መሆኑን፤
በዚህ መነሻ የፖለቲካ ምዕዳሩ በፖሊሲ ጉዳዮች ክርክር ለሚያደርጉ ፓርቲዎች መልካም እድል ይፈጥራል ተስፋ መፍጠሩን መካድ አይቻለም፡፡
የተፈጠረው መልካም ዕድል ብቻ ሳይሆን ፈተናም ያዘለ መሆኑን አውቆ መንቀሳቀሰም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ፈተናው እነዚህ ጥቂት ፓርቲዎች
አሁን የተስፋፉትን ሚዲያዎች በአግባቡ ተጠቅመው ለሕዝቡ በቂ መልዕክት ማስተላለፍ የሚያስችል አቅም አላቸው ወይ? የሚለው ነው፡፡ ይህን ፈተና
መወጣት ደግሞ ፊርማ እንደማስባሰብ ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ የተጭበረበረ ሃሳብ ይዞ በሚዲያ በአደባባይ መቅረብ ዳገቱ ቀላል አይደለም፡፡
6 የሕዝብ ብዛት ቆጠራና እና ምርጫ ምን እና ምን ናቸው?
የምርጫ
ሠሌዳ መውጣቱን ተከትሎ፣ ምርጫ መካሄድ የለበትም የሚሉ ቡድኞች ጩኽት ይቀንሳል የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ መሰረት ያለው ግምት ነው፡፡
የምርጫው ሴሌዳ ሳይወጣ የዚህ ዓይት ግፊቶች ምናልባት ምርጫው ሊራዛም የሚችልበት እድል ሊፈጥሩ ይቻላሉ ከሚል መነሻ ሊሆን ይችላል፡፡
ከአሁን በኋላ ሰለ ምርጫ ይራዘም ማውራት መራጮን ከማዘናጋት ውጭ ፋይዳ የሚኖረው አይመስለኝም፡፡ ምርጫው ይራዘም ባዩች፤ የተለያዩ
ዓላማ እንዳላቸው ቀደም ባለው መጣጥፌ በዚሁ መፅሄት ላይ መክተቤን አስታውሳለሁ፡፡ አሁን የህዝብ ቆጠራን ማድረግ አለመቻላችንን
እንደማሳያ አድርገው ምርጫ አይደረግ የሚሉት ቡድኖች፤ ችግራቸው ምንድነው? ብለን ሰናደምጣቸው
የሚያነሱት ጉዳይ፤ መንግሥት ሠላም ማስከበር አልቻለም፤ ከዚህም በላይ
አገራዊ መገባባት የለም፡፡ የሕዝብ ቆጠራ ማድረግ ባልተቻለበት ሁኔታ እንዴት ምርጫ ሊካሄድ ይችላል? ሰለዚህ ምርጫው ተራዝሞ የሸግግር ባይሉም እነርሱ ያሉበት ሸግግር የሚመራ አካል እንዲኖር ይፈልጋሉ፡፡ ምርጫው ተካሄዶ በሕዝብ
ይሁንታ የተመረጡ ፓርቲዎች ወደምንፈልገው የዴሞክራሲ ሥርዓት ይውሰዱን የሚለውን ሃሣብ ያጣጥላሉ፡፡ ምክንያቱም እነርሱ በራሳቸው
ሚዛን አዋቂና ታዋቂ እንጂ፤ ይህን ሕዝብ በድምፁ ሊያረጋግጥላቸው የሚያስችል የፖለቲካ ቁመና ማለትም ፓርቲ የላቸው፡፡ አዲሱ የምርጫ፣
የፓርቲዎች ምዝገባና ሥነ ምግባር አዋጅ ደግሞ እነዚህን ቡድኖች ወደ ሕዝቡ እንዲቀርቡ አስገዳጅ ሁኔታ ማስቀመጡ አልተመቻቸውም፡፡
የቋንጅ ሥር ቁስል የሆነባቸው ይመስለኛል፡፡
ለማንኛውም እሰኪቀየር ድረስ ገዢ
በሆነው ሕገ መንግሥት እና በቅርቡ በወጣው አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት የሕዝብ ብዛት ቆጠራና ምርጫ እንዴት እንደተጋመዱ
ብቻ ሳይሆን ለግጭት መንስዔ ጭምር እንዲሆኑ ተደርገው እንደተሰሩ እንመልከት፣
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት
አንቀፅ 103/5
“የሕዝብ ቆጠራ በየአስር ዓመቱ ይካሄዳል፡፡ በውጤቱም መሰረት የምርጫ ክልሎችን አከላል
የምርጫ ቦርድ በሚያቀርበው ረቂቅ መሠረት የፌዴሬሸን ምክር ቤት ይወስናል፡፡
አንቀፅ 54/3
“የምክር ቤቱ አባላት ቁጥር
የሕዝብ ብዛትና በል ትኩረት ውክልና የሚሰጣቸው አናሳ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ቁጥር መሠረት በማድረግ 550 የማይበልጥ ሀኖ ከዚህ
ውስ አናሳ ብሔረሰቦች ከሃያ የማያንስ መቀመጫ ይኖረቸዋል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይደነገጋል፡፡
የኢትዮጵያ የምርጫ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር
አዋጅ 1162/2011
አንቀፅ 13/1/ሀ
“ለምርጫ
አፈፃፀም ዓላማ የክልል መንግሥታት ድንበር እንደተጠበቀ ሆኖ አገሪቱ የወረዳ አሰተዳደርን መሠረት በማድረግ የሚከፋፈሉ፤ በሕዝብ
ቆጠራ ውጤት መሠረት ማስተካከያ ሊደረግላቸው በሚችሉ ቋሚ የምርጫ ክልሎች ትከፋፈላለች፤፤”
ከዚህ
በላይ ለመግቢያነት የተጠቀሱት አንቀፆች በአገራችን ኢትዮጵያ ምርጫና ፖለቲካን አሰመልክቶ ውሳኔ የሚሰጥባቸው የሕግ መሰረቶች ናቸው፡፡
አንቀፅ 103/5 በሁሉም ዘንድ በደንብ የሚታወቅ አንቀፅ ነው፡፡
በዚህም መነሻ ብዙ ፖለቲከኞች የሕዝብ ቆጠራ ተካሄዶ በድጋሚ የምርጫ አከላል እንዲደረግ ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህም ገፊ ምክንያታቸው ባለፈው
የምርጫ ክልል አከላል ወቅት ያለአግባብ ትርፍ የወሰደ ወይም ደግሞ የሚገባውን ያላገኘ ክልል አለ በሚል የሚነሳ ቅሬታ አንዱ ነው፡፡
በወቅቱ በነበረው የሕዝብ ቆጠራ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሌና ትግሬ እንደ ቅደም ተከተላቸው የሕዝብ ብዛት ቢኖራቸውም፡፡ ትግራይ
38 መቀመጫ ሶማሌ 23 መቀመጫ በማግኘታቸው ይህ አከላለል ፍትሓዊነት ይጎድለዋል የሚሉ አሉ፡፡ የሶማሌ ክልል የሚገባውን ባለማግኘት
ቅሬታ አቅርቧል፡፡ ከአከላል በኋላ በተደረጉ የህዝብ ቆጠራቸው ውዝግብ የተፈጠረ ሲሆን ለውዝግቡ ዋንኛው መንስዔም በሕዝብ ቁጥር
ልናገኘው የምንችለውን ኤኮኖሚያዊ/በጀት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ተጠቃሚነትም አጥተናል፡፡ በደል ተፈፅሞብናል የሚሉ ናቸው፡፡ ይህ
ቅሬታ የገዢው ፓርቲ ሙሉ ለሙሉ በሚቆጣጠረው ፓርላማም የተደመጠ ድምፅ ነበር፡፡
አንቀፅ 103/5 የሕዝብ ቁጥርን በዘላቂነት ለፖለቲካ ሥልጣን መያዣ ዋንኛ መሰፈርቶች ውስጥ እንደ አንዱ
አድርጎ በማስቀመጡ በአገራችን የቤተሰብ ምጣኔ ለማካሄድ የመንግሥት/በተለይ የክልል መንግሥታት ቁርጠኝነት እንዳይኖራቸው ብቻ ሳይሆን
በቀጣይ በሚደረግ የምርጫ ወቀት ከፍተኛ ወንበር ለማግኘት እንዲቻል፤ በሕዝብ ቁጥር ማሳደግ ውድድር ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው አሳዛኝ
ምናልባትም አሳፋሪ ሀቅ ነው፡፡ አንድ የሕገ መንግሥት አንቀፅ አገር በኤኮኖሚ ልማት ከምታስመዘግበው
በላይ የሕዝብ ብዛት እንዳይኖራት ለማቀድ የማትችልበትን ድንጋጌ ይዞ ሲወጣ፤ ይህን በግልፅ ለመቃወም የማንነት ፖለቲካ አሸማቃቂ
ሲሆንብን አስገራሚ ነገር ነው፡፡ የቤተሰብ ምጣኔን በአግባቡ ሊይዝ ፍላጎት የሌለው የፌዴራል መንግሥት በሕዝብ ቁጥር በመጨመር የፖለቲካ
ትርፍ የሚሹ የክልል መንግሥታት አገር አዘቅት ይዘው እንደሚወርዱ ሳይታለም የተፈታ ሀቅ ነው፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒሰትር መለስ
ዜናዊ “የሚወለድ ልጅ አፍ ብቻ ሳይሆን ሁለት እጅ ይዞ ጭምር ነው” በማለት ቡራኬ መስጠታቸውንም መዘንጋት አይገባም፡፡
ሌላኛው አንቀፅ 54/3 የምርጫ
ክልሎች ቁጥር እና ተመራጮች ቁጥር 550 እንደማይበልጥ በግልፅ ይደነግጋል፡፡ ይህን ድንጋጌ ከአንቀፅ 103/5 ጋር ተጋምዶ ሲታይ፤
የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ለአገር ሠላም ሳይሆን የጠብ ምንጭ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ እነዚህ አንቀፆችን ተግባራዊ ለማድረግ
ቢሞከር በክልሎች መካከል እየተከሰተ ካለው የሕዝብ ቁጥር መጨመር ሸኩቻ በተጨማሪ የፖለቲካ ወንበር ላለማጣት ግልፅ ሸኩቻ ውስጥ
የሚያስገባ ነው፡፡ ለምሣሌ አዲስ አበባ ከተማ በውልደት ምጣኔ የሚመጣ እድገት ባይኖራም፤ ከሁሉም የአገሪቱ ከተሞች በሚመጡ ዜጎች
ቁጥሩ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ሰለዚህ የፖለቲካ ወንበር ይሰጠን የሚል ጥያቄ እንዲያነሳ የሚገፋፋ ነው፡፡ የሶማሌ ክልል ተመሳሳይ ጥያቄ
ማንሳቱ የሚታወስ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 54/3 ባለበት ሁኔታ ከትግራይ ምናልባትም ከኦሮሚያ ጭምር ወንበር መቀነስ ምን
ማለት የፖለቲካ ጦርነት እንደሆነ ለመገንዘብ አያስቸግርም፡፡ በቁመታችን እና በወርዳችን ልክ የፖለቲካ ሥልጣን ይሰጠን የሚለው ግልፅ
መፈክር የሕዝብ ቁጥር እንጂ ሌላ ምንም የረባ ነገር የለውም፡፡ ይህ የፌዴራል መቀመጫ ከ550 አይበልጥም የሚል ድንጋጌ፣ በሕዝብ
ቆጠራ መነሻ ድልድል ይደረጋል ከማለቱ ጋር ግጭት ቀስቃሽ ድንጋጌ መሆኑን መረዳት አንዱ ሆኖ፤ ይህን ድንጋጌ እንዴት እናሻሽል ወደሚል
መሄድ ይኖርብናል፡፡
የምርጫ ቦርድ አዲስ ባወጣው አዋጅ
ቁጥር 1162/211 ይህን ችግረ በቅጡ የተገነዘበው ይመስለኛል፡፡ ለዚህም ሲባል በዚሁ አዋጅ አንቀፅ 13/1/ሀ ላይ “..
..የክልል መንግሥታት ድንበር እንደተጠበቀ ሆኖ ….” የሚለውን ሀረግ
በመክተት፤ ክልሎች የአንዱን ወንበር አንዱ ይወስዳል የሚለውን ስጋት ለጊዜውም ቢሆን ለማስወገድ ጥረት አድርጓል፡፡ የሕገ መንግስቱ ድንጋጌ በሕዝብ ቁጥር መሠረት የምርጫ ክልል ሽግሽግ ያደርጋል የሚለውን ጉዳይ፤ ክልሎች ያላቸውን የምክር
ቤት መቀመጫ በክልሉ ውስጥ ለማደላደል እንዲችሉ ብቻ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ይህ የምርጫ ቦርድ አካሄድ አሁን ባለው ሁኔታ
ማስተንፈሻ ቢሆንም፤ የሕዝብ ቆጠራን መሰረት አድርጎ ምርጫ ቦርድ በሚያቀርበው ረቂቅ መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይወስናል የሚል
በመሆኑ፤ ጉዳዩን በክልሎች ድንበር ማጠሩ የሕግ መሰረት የሌለው መሆኑን አውቀን መግባት ይኖርብናል፡፡
ከላይ በመግቢያዬ ላይ ለማሳየት
እንደ ሞከርኩት፤ አንድ አንድ ፖለቲከኞች የሕዝብ ቆጠራው ሳይካሄድ ምርጫውን ማካሄ እንዴት? የሚል ጥያቄ በማንሳት ቀጣዮን የፖለቲካ
ሂደት ለማወሳሰብ ጥረት እንደሚያደርጉ ጠቀስ አድርጊያለሁ፡፡ እርግጥ ነው የሕዝብ ቆጠራ ማካሄድ ያልተቻለው በፖለቲካ ጉዳይ እንደሆነ
ሊካድ አይችለም፡፡ የሕዝብ ቆጠራው የምር የሕዝቦችን መብት ለማስከበር ከሆነ መሆን ያለበት በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ የቅይጥ ብሔረተኞች
በምን ያህል ቁጥር አሉ? የሚለው ትልቅ ቦታ ሊይዝ ይችል ነበር፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የሕዝብ ቆጠራ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች
ያላቸውን የተጋነነ ቁጥር ማሳያ እንዲሆን የሚፈልጉ ብዙ ናቸው፡፡ ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን ቆጠራው ተጭበርብሯል ወደሚል አላስፈለጊ
ግጭት ውስጥ የሚከቱ ናቸው፡፡ አንድ በደቡብ የሚገኝ ብሔሮች የእኛ ብሔር አስር ሚሊዮን ይሞላ ሲሉ ማድመጥ የብሔር በሸታትን ለማረዳት
ትልቅ ምሣሌ ነው፡፡
የሕዝብ ቆጠራ ማድረግ ያልተቻለው
በቴክኒካል ጉዳይ ቆጥሮ ሪፓርት ማድረግ ባለመቻሉ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ደረጃ ችግር የሚፈጥር ሀይል አለ ተብሎ አይታመንም፡፡
ይህ ጉዳይ ዛሬ ቆጠራ ማካሄድ ያልቻለች አገር ምርጫ እንዴት ማካሄድ ትችላለች ወደሚል ተገቢ ያልሆነ ንፅፅር ውስጥ እንድንገባ የሚፈልጉ
አሉ? በእኔ እምነት የሕዝብ ቆጠራው ያልተካሄደው ሪፖርቱ ሲወጣ በምርጫው ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍ ሰለሆነ ነው፡፡ በቀጣይ የሕዝብ
ቆጠራ ከመካሄዱ በፊት፤ በብሔር ማንነት የሚገኝ የፖለቲካም ሆነ የኤኮኖሚ ልዩ ጥቅም እንደማያስገኝ ተረጋግጦ እንዲሆን፤ በፍርሃት
እራሳቸውን ወደ አንዱ ብሔር አዳብለው የነበሩ ቅይጥ ማንነት ያላቸው ዜጎች በነፃነት ቅይጥ ማንነት መምረጥ መብታው እንደሆነ በማስገንዘብ
መሆን ይገባዋል፡፡
የሕዝብ ቆጠራ ውጤት ከምርጫ ጋር
ሊኖረው የሚገባው ቀጥታ ግንኙነት፤ በምርጫ ጣቢያ ማደራጀት ወቅት በሚኖረው የግብዓት አቅርቦት ነው፡፡ አንድ ተወዳዳሪ ምን ያህል
ሰዎች ይወክላል? በምርጫ ክልሉ ምን ያህል መራጮች ይኖራሉ? መራጮች ሳይቸገሩ፣ ምርጫ እንዲያካሂዱ እንዴት ተደርጎ የምርጫ ጣቢያ
ይደራጅ የሚለው ነው፡፡ በመራጮች ምዝገባ እና በድምፅ መሰጫ ቀን ያሉት ቀናት በዋናነት ይህን ለማወቅ እና ተገቢውን የመራጭ ሰነድ
ለማዘጋጀት ይረዳል፡፡ ከዚህ በዘለለ በየአስር ዓመት ሕዝብ እየቆጠሩ የተለያ የምርጫ ክልል ማደራጀትና ከአንዱ ወስዶ ለአንዱ የመስጠት
ሃሣብ በፍፁም ሊወገድ ይገባል፡፡ ህወሓቶች ለዚህ ሲባል እንኳን ሕገ መንግሥት ይሻሻል እንደሚሉ አልጠራጠርም፡፡ የሕዝብ ቆጠራውን
ከፖለቲካ ማጋመድ የምናቆምበት ጊዜ አሁን ነው፡፡
7 የሕገ መንግሥት ክሽፈት ተከትሎ ይህ ቢሆንስ?
ዛሬ
ወትሮ ከማደርገው በተለየ የማምንበትን የራሴን ምልከታ ላጋራችሁ አይደለም፡፡ ፈረንጆች (Devil Advocate) የሚሉትን ዓይነት
ገፀ ባህሪ ይዜ ለመጫወት ፈልጊያለሁ፡፡ ዘወትር በግል ካለኝ አመለካከት የቢሆን ግምቶች ሳስቀምጥ መመዘኛዎች አሉኝ፡፡ የመሆን እድል
ብቻ ሳይሆን ሊተገበሩ የሚችሉ መሆናቸውን ከሚዛን አስገባለሁ፡፡ ጉዳዮችን ለተዓምር እና መለኮታዊ ኃይል መስጠት አልፈልግም፤ አማኒ
ብሆንም “ግመሌንም አስራለሁ፤ በፈጣሪም አምናሁ!” ከሚለው አርብቶ አደር ጎራ የምመደብ ነኝ፡፡ ከመፀኃፍ ቅድሱ ታሪኮች የአልዓዛር
ሞትና መነሳት፤ ጌታ ከሰራው ተዓምር ይልቅ፤ የአልዓዛር እህቶች ሚና እና የድርሻቸውን መወጣት አስፈላጊነት ያስተማረበት መንገድ
ከሚመስጣቸው ክርስቲያኖች አንዱ ነኝ፤ ቁጭ ብለው መና ከሚጠብቁት ጎራ የሌለሁበት መሆኔ ቢያንስ ለራሴ አሳምኜዋለሁ፡፡ የዛሬ ሚናዬን
ለመጫወት የፈለኩትም የማቀርባቸውን ቢሆኖች ሳላውቃቸው ቀርቼ ሳይሆን፤ የማይሆኑ ስለሆኑብኝ ነው፡፡ ግን ቢሆንስ ….. ዛሬ የማቀርባቸው
ቢሆኖች በምንም ሁኔታ የእኔ አቋም አይደሉም፡፡ በሌሎች ጫማ ሆኜ ነው የምፅፈው …
የመጀመሪያው ቢሆን ሕገ መንግሥታዊ ክሽፈት
ተከትሎ፤ ማለትም አሁን ሕገ መንግሥቱ ምላሽ ሊሰጣቸው ያልቻሉ ግልፅ ጉድለቶቹን እያሳየ መሆኑ አንዱ ነው፡፡ ሌሎች ጉድለቶቹ እንደተጠበቁ
ሆኖ መሻሻል እንዳለበት ታምኖ ያደረ ጉዳይ መሆኑ ሳይዘነጋ ለማለት ነው፡፡ የአሁኑ ግልፅ ክሽፈት አገራችን በቀጣይ የመስከረም ወር
መጨረሻ ሣምንት ሰኞ በኋላ ለይስሙላም ቢሆን የተመረጠ መንግሥትና የመንግሥት አካላት አይኖራትም፡፡ በዚህ መሠረት በሚፈጠረው ክፍተት
አገር መንግሥት አልባ ይሆናል፡፡ ይህ እንዳይሆን ደግሞ የተለያዩ ሀይሎች ያሉበት “የሆነ ስም ያለው” መንግሥት መመሰረት አለበት፡፡ ይህን አካሄድ መንግሥት የማይቀበለው ስለሆነ፤ የዚህ ሃሳብ አቀንቃኞች ሕዝባዊ
ጥሪ ያቀርባሉ፤ ያልተመረጠ መንግሥት በሥልጣን መቆየት የለበትም ለዚህ የሚሆን “የሽግግር፣ ባላደራ፣ የልሂቃን፣ ወዘተ…” የሚባል
መንግሥት ይቋቋም ብንልም እንቢ ስላላ “ሕዝብ ሆይ ወጥተህ፤ ይህን መንግስት ከሥልጣን አስወግድ፡፡” የሚል ጥሪ ሊያቀርቡ ይችላል፡፡
ጥሪው ምን ሊሆን እንደሚችል አላውቅም፤ ነገር ግን ሕዝብ በሽግግር ይሆን በሌላ ስም በሚጠራ መንግሥት የስልጣን ባለቤት እንደማይሆን
የታወቀ ሲሆን፤ ለሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት በሚል ጥሪ እንደማይኖር ይታወቃል፡፡ ለማንኛውም ለሕዝብ ጥሪ ይቀርባል፤ ቢሆንስ እያልን
አይደል?
እንደ
መሸጋገሪያ፤ ባለፉት ሁለት እና ሶሰት ዓመታት በፊት ሕዝብ ኦ! ብሎ የወጣው፡፡ መንገድ እየዘጋ ከታንክና መሳሪያ እስከ አፍንጫው
በታጠቀ የፌዴራልና የክልል ታጣቂዎች ጋር የተጋጠመው ብዙ ምክንያት ነበረው፡፡ አርግጠኛ መሆን የሚቻለው ጠሪዎቹን አምኖ አይደለም
ኦ! ብሎ የወጣው፡፡ በየሰፈሩ ወላጆች ልጆቻቻቸውን፤ ወጣቶች ወንድምና ቤተሰባቸውን፤ በአገር ባለ እስር ቤት ሁሉ የተለያየ ስያሜ
እየተሰጠ በእስር የሚማቅቁ መሆኑ፤ በአገራቸው መኖር አቅቷቸው የካድሬ መጫወቻ መሆን በቃን! ብለው ለሞት ቆርጠው በመነሳታቸው ነው፡፡
በዚህ መነሳሳት ላይ ያለን ሕዝብ ማንም፣ ለምንም ቢጠራው ሰበብ ፈልጎ መውጣቱ የግድ ነበር፡፡ “እንኳን እናቴ ሞታ፤ እንዲሁም አልቅስ
አልቅስ ይለኛል፡፡” የሚለውን ብሂል ማስታወስ ነው፡፡
በዛሬው
ቢሆን ግን ሕዝቡ ኦ! ብሎ ይወጣል ብለን እንመን፡፡ ምክንያት ባይኖረውም ጠሪዎቹ በሽግግር መንግሥት ለመሳተፍ ያቀረቡትን ጥሪ፤
መንግሥት ባለ መቀበሉ የቀረበ ጥሪ መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ጥሪውን ተቀብሎ ሕዝቡ ኦ! ብሎ ይወጣል፡፡ መሣሪያ የታጠቀው መንግሥት
ሕዝቡን በዓለም ላይ በተለመደው፤ በስብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ እንደማይመልሰው ይታወቃል፡፡ ምላሽ የሚሰጥበት መንገድ፤ አጅግ ቡዙ ዜጎች የህይወት መስዋዕትነት
የሚያስከፍል ይሆናል፡፡ ተከትሎም ለሕዝብ እልቂት ምክንያት የሆኑ የዚህ ጥሪ አቅራቢዎች ወደ እስር ቤት ይገባሉ፡፡ መንግሥት ይህን
ሁኔታ ለማረጋጋት በሚል በወሰደው አርምጃ፤ ከዜጎች ጋር ደም ይቃባል፡፡ በዚህ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ የሚታሰብ
ሰለማይሆን ወታደርና ደህንነት የሚሳተፍበት የይስሙላ ምርጫ ይደረግና ገዢው ሀይል በሥልጣን ይቆያል፡፡ ይህ ቢሆን፤ በአገራችን ሊሆን
የሚችል አንድ ጉዳይ ነው፡፡ ጠሪውም ማንም ሳይሆን የፖለቲካ “ልሂቃን” የሚባሉ ናቸው፡፡ ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ የፖለቲካ
“ልሂቃኑን” የሚሰማው ሕዝብ መኖር የግድ ነው፡፡ በአገራችን ለሌላ ብዙ ዓመታት የሚቆይ አንባገነን ሥርዓት ሊመጣ የሚችልበት አንዱ
መንገድ ነው፡፡ ይህ የቢሆን ትንተና ነው፡፡ ጎበዝ ይህ ነገር አይሆን ይመስላችኋል?
ሌላኛው ቢሆን ደግሞ ከላይኛው ቢሆን ጋር ሊገናኝ የሚችል ይሆናል፡፡ በአገር የተፈጠረ ሕገ መንግሥታዊ
ክሽፈት ተከትሎ አሁን በብልፅግና ፓርቲ ሥር የተሰለፉት ስምንት ክልሎች እና ሁለት የከተማ መስተዳድሮች (በሕገ መንግሥቱ ላይ ድሬዳዋ
የሚባል ከተማ መስተዳደር የለም፡፡)በጋር መቆም ቢያቅታቸው የሚል የቢሆን ትንተና መስራት ይቻላል፡፡ መቼም የዚህ ዓይነት ቢሆን
ለመቀበል በጣም አስፈላጊ ሁለት ነገሮች አሉ፤ አንደኛው የአብዲ ኢሌ ዓይነት አቅላቸውን የሳቱ የክልል መሪዎች እና ተከታይ፤ እንዲሁም
ይህን የሚቀበል የክልል ሕዝብ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ደረጃ ኢትዮጵያዊነቱን ጠልቶ አገር ብትገነጣጠል ስንት ክልል ሊኖረን
ይችላል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል፡፡ መንግሥት ይህን ጉዳይ ዝም ብሎ ይመለከተዋል የሚል የዋህ ሊኖር አይችልም፡፡ መንግሥት ይህን ጉዳይ
አጢኖ፤ አገር ከሚፈርስ በማንኛውም መንገድ አገር የማስቀጠል ፕሮጀክት በሚል ውሣኔ አንባገነን ነኝ ባይልም በአገር ፍቅር ስም አንባገነን
ተግባራትን እንደሚያደርግ መታወቅ አለበት፡፡ ይህ አንባገነን የመሆን ውሣኔ ለመወሰን “እድል” ይስጠዋል፡፡ ክልሎች ነፃና ሉዓላዊ ነን፤ በሚል ፈሊጥ ነፃ አገር ለመመስረት የሚወስዳቸውን መንገድ ሲመርጡ በመቶ ሺዎች ወታደር ያለው መንግሥት
በዝምታ “አንቀፅ 39” እያሉ የከሸፈ ሕገ መንግሥት ሲጠቅሱ ዝም ሊል አይችልም፡፡ ሰለዚህ በዚህ መንገድ የሚሄዱ አንድም ሁለትም
ይሁኑ ወይም ከዛ በላይ እብድ ክልሎች ቢመጡ መንግሥት ባለ በሌለ ሀይሉ ይገጥማቸዋል፡፡ ይህ ቢሆን ከላይ እንዳየነው አንባገነን
ሥርዓት ብቻ ሳይሆን እጅግ ብዙ የሚባል የህይወት መስዋዕተነት በዚህ መንገድ በመረጡ ክልሎች ሰበብ ሊፈጠር ይችላል፡፡
ሌላው ቢሆን መንግሥት የሽግግር ይሁን ሌላ
ስያሜ ያለው መንግሥት ለመቀበል ፈቃደኛ ቢሆንስ የሚለው ነው፡፡ በቢሆን ትንተና የማይሆን ነገር የለም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ
ከመቶ ሃምሳ በላይ ፓርቲዎች በእኩልነት መንፈስ ሁለት ሁለት ተወካዮች በአንድ ወር ውስጥ መርጠው እንዲልኩ፤ ሁሉም ብሔሮች ያለምንም
አድለዎ አንድ አንድ ተወካዮች መርጠው እንዲልኩ፤ ሁሉም የሀይማኖቶ ድርጅቶች አንድ አንድ ተወካይ እንዲልኩ፤ የወጣት የሴቶች ተወካዮች
እንዲሁ እንዲያደርጉ፤ በተለይ ፋኖ፣ ቄሮ፣ ኤጄቶ፣ ወዘተ ተወካዮች እንዲልኩ፣ ወዘተ በአዋጅ ይነገራል፡፡ የሌሎቹን ወደ ጎን አደርገን
የፖለቲካ ፓርቲዎችን ስንወሰድ እና ይህን ጉዳይ ለምርጫ ቦርድ እንዲያስፈፅም ሥልጣን ቢሰጠው፡፡ መቶ ሃምሳዎቹ ፓርቲዎች ሁለት ውክልና
ሰለማይበቃቸው ለሁለትና ሶስት በመከፋፈል ሶስት መቶ ይደርሳሉ፡፡ ይህን በቅጡ ማስተካክል የሚቻልበት ሁኔታ ሰለማይቻል፤ ለአንድ
ወር የተሰጠው ጊዜ ሰለማይበቃ ይልቁን ይህ የፓርቲዎች ውክልና ፓርቲዎችን ያላቸው የትግል ተመክሮ፤ በሕዝቡ ያላቸውን ተቀባይነት
በቅጡ ያገናዘበ ባለመሆኑ፤ ገዢው ፓርቲ ሊያጣላን አቅዶና አውቆ ያደረገው አሻጥር ነው በሚል ተግባራዊ ሳይሆን ይቀራል፡፡ ተግባራዊ
አይሆንም ማለትም አንዱ ቢሆን መሆኑ ነው፡፡
በተመሳሳይ የሌሎቹን ውክልና በተመለከተ
ማውራት ሁሉ ይቸግራል፡፡ ቄሮን ብንወሰድ ከወለጋ፣ ከሸዋ፣ ከባሌ፣ ከአርሲ፣ ከጅማ፣ ከጉጂ፣ ከየት ነው ሊወከል የሚችለው፡፡ ፋኖ
ወኪል ላክ ቢባል፤ የጎንደር፣ የጎጃም፣ የወሎ፣ የሸዋ፣ ወዘተ ከየት አካባቢ ያለ ወጣት ወክሎ ሊልክ ነው፡፡ አረ ጉድ ነው፤ ይህም
ተግባራዊ አይሆንም ግን አንዱ ቢሆን ነው፡፡
እጃችንን ደጋግመን እንታጠብ!
ርቀታችንን እንጠብቅ!
ቸር ይግጠመን!
8 አገር አቀፍ ውይይት ለምን?
በአገራችን
ኢትዮጵያ በተለያዩ ሰያሜዎች እየተጠራም ቢሆን የሰለምና የእርቅ ኮንፈረስ ተደርጎ ከስምምት ላይ መድረስ ይኖርብናል የሚል ገዢ ሃሳብ
እየተንጸባረቀ መኖሩ ይታወቃል፡፡ ቀደም ጠቅላይ ሚኒሰትር አብይ አህመድና እና ጓዶቻቸው የተጣላ በሌለበት እርቅ የለም፡፡ የአገር
ጉዳይ የባልና ሚስት ጉዳይ አይደለም በሚል ፌዞች በማጣጣል ሲያልፉት እንደነበር ይታወቃል፡፡
በ2010 በአገራችን የተፈጠረውን “የለውጥ” ሰሜት ተከትሎ የሠላምና እርቅ ኮሚሽን በኢትዮጵያዊው ካቶሊካዊ ፓፓስ ሰብሰቢነት መንግሥት
መሰየሙ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ወደፊት መሻገር ከፈለግን ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ ቀድሞ የሚደረግ ማንኛውም
ዓይነት የፖለቲካ ውሣኔዎች እና እንቅስቃሴዎች ውጤታማነታቸው ያጥራጥራል የሚሉ ኃይሎች ብዙ ናቸው፡፡ ዛሬም “ኮቪደ 19” ተከትሎ በተፈጠረ የሕዝቦች እንቅስቃሴ መታገድ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ
ተከትሎ ተፋዞ የነበረው የፖለቲካ ሸኩቻ ሞቅ ደመቅ ብሎ እንደተጀመረ እየታዘብ ነው፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሀይሎች በተለያየ
ስያሜ ይጥሩት እንደጂ የአገር አቀፍ ውይይት አስፈላጊነት ላይ ስምምነት ያለ ይመስለኛል፡፡ ልዩነቱ ያለው አገር አቀፍ ውይይት ለምን?
የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ አገር አቀፍ ውይይት ብዙ አጀንዳዎች ይዞ እንዲጀመር እና በውይይቱ መፍትሔ በጋራ እንዲፈለግ የሚል ሃሣብ
አለ፡፡ ይህ አካሄድ ምን ያህል? በምን
ያህል ጉዳዮች? ስኬታማ ሊሆን እንደሚችል
መገመት አይቻልም፡፡ እስኪ የተወሰኑ የአገር አቀፍ ውይይት (ናሽናል ዳይሎግ) አጀንዳ የሚሆኑ ጉዳዮችን እያነሳን ፍተሻ እናድርግ፡፡
8.1 ለሰላምና እርቅ
ዜጎች
በተቋሰለ ልብ ውስጥ ሆነን በጋራ ልንሰራ አንችልም፤ ይህን ቁስል ሊያክም የሚችል እንቅስቃሴ መደረግ ይኖርበታል የሚሉ ብዙ ሰዎች
አሉ፡፡ ይህ ጉዳይ የግለሰቦች ብቻ አይደለም፡፡ የተወሰኑ ሰዎችን በሽምግልና አንተም ተው አንተም ተው በሚል የሚፈታ አይደለም፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በእርሳቸው የፈጠሩት መቋሰል መታከም የሚችልበት መንገድ ማስፈለጉ ይታመናል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በእርሳቸው ካላቸው በለይ፤ እነኚሁ ፖለቲከኞች ለፖለቲካ
ጥቅማቸው ሲሉ፤ በአገራችን የሕዝብ ለሕዝብ ልዩነቶች ዘርተዋል፡፡ በዚህም መነሻ፤ አንዱ ብሔር ሌላኛውን ብሔር ጨቁኖ ከፍተኛ በደል
አድርሷል በሚል ተረክ ውስጥ የምንኖር ነን፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ለፖለቲካ ፍጆታ ከምናውላቸው
በስተቀር በአደባባይ አቅርበን መፍትሔ ልንፈልግለት ፍላጎት ያለን አይመስልም፡፡ ወይም ደግሞ በዚህ ጉባዔ ላይ አንዱ አንዱን ካላንበረከኩ
እና ይቅርታ ካላስጠየቅሁ በሚል እሰጥ-አጋባ ለለየለት ጦርነት የምንዘጋጅበት መድረክ ሊሆን ይችላል፡፡
በአገራችን ኢትዮጵያ፤ ዜጎቿ በሠላም
መኖር ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ ሠላም መደረግ ያለበት ውይይትና እርቅ በጣም ያስፈልገናል፡፡ አስቸጋሪው ነገር በዳይና ተበዳይ ተለይቶ
ባልታወቀበት፤ ይህ የሰላምና እርቅ ጥያቄ ለዜጎች ሠላም ለማስፈን ሳይሆን ለፖለቲካ ጥቅም ለማዋል የምንሄድበት ከሆነ፤ ይህ የምናስበው
እርቅና ሠላም ያመጣል ከሚባለው እርቅና ሠላም፤ ይልቅ ለሌላ የብጥብጥ አዙሪት ሊዳርገን ይችላል፡፡ በተለይ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚደረጉ
ውይይቶች በታሪክ ስም በሚነገሩ ተረኮች ላይ የሚሆንበት እድሉ ሰፊ በመሆኑ ስምምነት የሚደረስበት አንድም መለኮታዊ ኃይል፡፡ በአሰማት
ሊመጣ የሚችል የውይይት አጀንዳም ማቅረብ ተሰብሳቢዎቹ አሰማታዊ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ የሚሰበሰቡት ፖለቲከኞች ደግሞ ለመለኮታዊ
ተዓምራት መገለጫነት የምንጠረጥራቸው አይደሉም፡፡ አስማትም ይሰራሉ ብለን አናምናቸውም፡፡
በግሌ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሰላምና
እርቅ አጀንዳ የሚኖራቸው ሚና ታሪካዊ እንዲሆን ከፈለጉ፤ በፓርቲዎች መካከል የብዙ ዜጎችን በተለይ ወጣቶች ሕይወት ያስከፈለውን
የእርስ በእርስ ትግል በሚያደርጉበት ወቅት ለተፈጠረው ስህተት በጋራ ሆነው የእርስ በእርስ ስምምነታቸውን በመግለፅ፤ ከደፈሩ ሕዝቡን
ይቅርታ ቢጠይቁት ነው፡፡ ውይይት ጀምረው ከውይይቱ የሚመጣን ውጤት የሚጠብቅ የፖለቲከኞች የውይይት መድረክ፤ በደረቅ ሳር ላይ ክብሪት
እንደመጫር የሚቆጠር ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነት ውይይት ማን? ምንያህል ገደለ? አስገደለ? የሚለው ሂሣብ ማወራረድ ከሆነ ውጤት አያመጣም፡፡
የሚደርሱበትን መደምደሚያ ላይ ተስማምተው እዛ መደምደሚያ ላይ በሚደርሱበት አካሄድ ላይ ውይይት መጀመር ከተቻለ፤ የተሻለ ውጤት
መጠበቅ ይቻላል፡፡ ሁሉም ኃይሎች ለአገራቸው ከነበራቸው የለውጥ መሻት የተሳተፉበት መሆኑን እኛ እናምናለን፡፡ ይቅርም እንላለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ እነዚህ ኃይሎች ተሰብስበው ይቅርታ ባይጠይቁንም፤ ይቅርታ ሰጥተን የምንሻገር መሆኑንም ማሳሰብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡
8.2 የሽግግር መንግሥት ምስረታ
የፖለቲካ
ፓርቲዎች ለአገራዊ ውይይት የሚቀመጡበት አንዱ አጀንዳ “የሽግግር መንግስት ምስረታ” ወይም በሌላ ስያሜ ያለውን መንግሥት ቀይሮ
በውይይት የሚቀመጡ ሰዎች፤ ከተቻለ ከተወሰኑ ሌሎች ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ደባልቆ፤ በድርድር ሥልጣን የሚይዙበት መንገድ ነው፡፡ ይህ ይሳካል ብሎ ለአገራዊ ውይይት አጀንዳ
ማቅረብ በራሱ መብት ሊሆን ቢችልም፤ ውሃ የሚቋጥር ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም በዓለም ታሪክ ውስጥ የሽግግር መንግስት ምስረታ
ከሚጠሩት መሰረታዊ ጉዳዮች አንዱና ዋንኛው የመንግሥት አቅም ማጣት እና ነገሮች ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ መሆናቸው ነው፡፡ የአገራችንን
ሁኔታ ስንገመግም፤ የዶክተር አብይ አህመድ መንግስት ከመምጣቱ በፊት፤ በጠቅላይ ሚኒሰትር ኃይለማሪያም ደሣለኝ የስልጣን ማገባደጃ
ዋዜማ የሽግግር መንግስት ለመመስረት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች ይታዩ ነበር፡፡ የፖለቲካ አመራሩ በጣም ተዳክሞ ነበር፡፡ አቶ ኃይለማሪያም
የሆነ መንፈስ ቅዱስ አመላክቷቸው ይሁን ወይም የውጥረቱ መብዛት ወደ ሽግግር ሳይሆን፤ በውስጥ ወደሚደረግ ጥገናዊ ለውጥ መርተው
ለዶክተር አብይ አህመድ አስረክበውናል፡፡ ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ፤ ሕዝቡ ከተቃዋሚ ጋር ተባብሮ ኢህአዴግ አያስፈልገንም
በሚል ተቃውሞውን መቀጠል ሲገባው፤ ይህ ግን ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ይልቁንም ሕዝቡ በድጋፍ ሰልፍ ለዶክተር አብይ አህመድ መስጠቱ በአደባባይ
ሰልፍ ሲገልፅ ታይቷል፡፡ በተመሳሳይ ተቃዋሚዎችም፤ በሕዝቡ ያልተገደበ ድጋፍ ተገፋፍተው በተስፋ ድጋፋቸውን ሲያቀርቡ ነበር፡፡ በግሌ ባለኝ መረጃ ሕዝቡ በዶ/ር አብይ አህመድ መንግሥት ተስፋ ቆርጦ፤ ተቃዋሚዎች ተባብራችሁ መንግሥት መስርቱልኝ
የሚል ጥያቄ ያቀረበበት ሁኔታም፤ ፍላጎትም አይታየኝም፡፡ አንድ አንድ ተቃዋሚዎች ግን ቀጣዩ ምርጫ ላይ ምን እንደታያቸው ባለወቅንበት
ሁኔታ ተባብረን የሽግግር መንግስት እናቋቁም እያሉ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ውይይት ለማድረግ የገዢውን ፓርቲ እና በዚህ ጉዳይ የማያምኑ
ፓርቲዎችን አግልሎ ካልሆነ በስተቀር በጋራ ሊካሄድ አይችልም፡፡ ይህ ጉዳይ አጀንዳ ሆኖ በሁሉም ስምምነት ካልተደረሰበት አጀንዳ
ሊሆን የማይችል ነው፡፡
ይህ ፅሁፍ በምፅፍበት ወቀት፤ ያለው
መንግሥት እስከ ምርጫው ይቀጥል፤ የሽግግር መንግስት ቢያንስ ለሁለት ዓመት ይቋቋም፤ የባለሞያዎች ባላደረ መንግሥት ይቁም፤ ወዘተ
የሚሉ ሃሳቦች እየቀረቡ ነው፡፡
8.3 የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማቅረብ
ሕገ መንግሥት ማሻሻያ በማድረግ
ላይ አገራዊ ውይይት ማድረግ በጣም ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ሀይሎች የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ሃሣብ
ላይ ስምምነት እንዳለ ይታወቃል፡፡ በምን ያህል ዝርዝር? ሕገ መንግሥቱ ይሻሻል በሚለው ላይ ብቻ ሳይሆን፤ መቼ ነው መሻሻል ያለበት?
በሚለው ጉዳይ ላይ ውይይት ማድረጉ ጠቃሚ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሲሻሻል በምን ዓይነት ሥርዓት ይካሄድ የሚለው ላይ መነጋገር ይቻላል፡፡
ሕገ መንግሥቱ ተቀዶ ይጣል/ይታደግ፤ ከሚለው በፍፁም መነካት የለበትም እስከሚሉት ድረስ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳዮች የአጀንዳው
አካል እንደሚሆኑ ይታመናል፡፡ አሁን ባለው፤ በሕዝብ የተመረጡ የሕዝብ ወኪሎች በሚኖሩበት፤ ማለትም ከምርጫው በኋላ ሕገ መንግሥት
ይሻሻል የሚለው ገዢው ሃሳብ እየሆነ መምጣቱን የሚያሳይ ነው፡፡ ለዚህ ጉዳይ ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት ፖለቲከኞች ለአገራዊ ውይይት
ቢቀመጡ መልካም ጅምር ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ይመስለኛል፡፡
8.4 የአገራዊ ምርጫና የፖለቲካ ሀይሎች ተሳትፎ
በአገራችን የነበሩትን የይስሙላ
ምርጫዎች የፈጠሩብንን መጥፎ ተሞክሮዎች በሚያሰወግድ መልኩ ስምምነት ለመፍጠር አገራዊ የምክክር መድረክ እጅግ ጠቃሚ አጀንዳ ተደርጎ
ሊወሰድ ይችላል፡፡ ቢሆንም በዚህ አጀንዳ ላይ ስምምነት ሊደረስ የማይችልበት ሁኔታ የለም ማለት አይደለም፡፡ አንድ አንድ ሀይሎች
በምርጫ የሚያገኙትን ውጤት ከአሁኑ አስልተው፤ ምርጫ በሕዝብ ድምፅ ሳይሆን “በልሂቃን” ድርድር የሚሉ አሉ ወይም ደግሞ ከላይ ያነሳነው
“የሽግግር መንግስት” ለዚህ ጉዳይ ደንቃራ ሊሆን ይችላል፡፡ ምን አልባትም፤ ድርድሩ እነዚህ ኃይሎች ወደ መሃል ለመምጣት በሚያስችል
ጥበብ ሊካሄድ ይችል ይሆናል፡፡
የፖለቲካ ኃይሎች በአንድ ጉዳይ
ብቻ ውይይት ማድረግ ቢኖርባቸው፤ በቀጣይ ምርጫ በሠላም ተጀምሮ በሠላም እንዲጠናቀቅ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ምን ማድረግ እንዳለበት
ከስምምት ለመድረስ መሆን አለበት፡፡ በሕዝብ የተመረጠ የፖለቲካ ኃይል ቀጣዩን ጉዳዮች እንዴት እንደሚይዛቸው ጭምር በምርጫው ወቅት
አቅርቦ፤ ሲመረጥ ደግሞ የሚፈተንበት መሰረታዊ ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ለአገራዊ ውይይት አጀንዳ ቅደም ተከተል ማስቀመጥ እና
የቅድሚያ ቅድሚያ የምንሰጠው ለየትኛው እንደሆነ መለየት በራሱ ውይይት ይፈልግ ይሆን?
እጃችንን እንታጠብ!
እርቀታችንን እንጠብቅ!
ቸር ይግጠምን!
9 “ኮቪድ 19” እና ምርጫ በኢትዮጵያ
ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ የወቅት
የዓለም መነጋገሪያ የሆነው “ኮቪድ 19” በመባል የሚታወቀው ወረርሽኝ ነው፡፡ ዓለማችን እንደሆነች ለበሽታ ብርቅ የሆነች ይመስል፤
በሚዲያ ጡዘት የሞቀውን “ኮሮና ቫይረስ” በዓለም ላይ
ፕሮግራም የተያዘላቸው ከፍተኛ ኩነቶች እንዳልነበሩ እያደረገ ይገኛል፡፡ በዓለማችን ከፍተኛ ኩነት ተብሎ በየአራት ዓመቱ የሚከወነው
ኦሎምፒክ ጭምር መሰረዝ የሚያስችል ሀይል ያለው ወረርሽኝ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ኦሎምፒክ በዓለማችን ከሚደረጉ ትልቁ ምን አልባትም
ውድ ከሆኑ ከንውኖች አንድኛው ነው፡፡ ጃፓንን የሚያክል የዓለማችን ባለ ትልቅ ኢኮኖሚ፤ ከዘጠኝ ዓመት በፊት የደረሰባትን የኢኮኖሚ
ድቀት ለማካካስ መፍትሔ አደርጋ የተዘጋጀችበትን ኦሎምፒክ መሰረዙ አይቀሬ መሆኑ ተነግሯል፡፡ የኦሎምፒክ ችቦ አቀባበል ሥነ ሰርዓት
ይህን ከማመላት የሚዘል አልነበረም፡፡ ብዙ አገሮች ምርጫ የሚባለውን “ፖለቲካ ካርኒቫል” በቀላሉ በአንድ አጭር መግለጫ፤ ያለ ብዙ
ማብራሪያ እንዲዛወር አደርገዋል፡፡ ምንም ጫጫታ አልተሰማም፡፡ አንድ አንዶች ምንአልባት ከዚህ ፅሁፍ ይሆናል፤ አገራት ምርጫ ማራዘማቸውን
የምትሰሙት፡፡ ምክንያቱም በኮሮና ዘመን ምርጫ መግፋት ትልቅ ክስተት አይደለም፡፡ ይህ ግን በምስኪኗ አገራችን ኢትዮጵያ እንዲህ
ቀላል አይደለም፡፡
ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መከበር
አለበት፤ መገለጫውም በተቀመጠለት የጊዜ ሠሌዳ ምርጫ ተካሂዶ በምርጫ መንግሥት መመሰረት አለበት የሚሉ እና ምርጫ በምንም ሁኔታ
መካሄድ የለበትም፤ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ፖለቲካዊ ሁኔታ በአገሪቱ የለም በሚሉ ፅንፎች መካከል ሲካሄድ የነበረው መጓተት አሁን
ቢያንስ ማስቢያ ጊዜ የሚሰጥ ምክንያት ተገኝቷል፡፡ ይህም “ኮሮና ቫይረስ” የሚባል የመግደል አቅም ያለው ወረርሽኝ በዓለማችን ተከስቶ እኛም የዚሁ ክስተት ተጠቂዎች መሆናችን በመረጋገጡ ነው፡፡
በአገራቸን ኢትዮጵያ ምርጫ ሊገፋ
የሚችልበት ሁኔታ ኮሮና መፍጠሩን ከበቂ በላይ ማሳያ ማቅብ ይቻላል፡፡ በዝናብ እንዴት አደርገን ቀስቅሰን ነው ምርጫ የምንወዳደረው?
ሲሉ የነበሩ ተቃዋሚዎች፤ እንዴት አድርገው በኮሮና ዘመን ምርጫ መወዳደር እንደሚችሉ መንገድ ማገኘት ሰለማይችሉ ምርጫው መራዘሙ
አይቀሬ ነው፡፡ ቀደም ምርጫው ይራዘም በክርምት አይሆንም ስለ ነበር ምክንያቱ አሁን ምርጫው ከክረምት በኋላ እንደሚሆን ለማወቅ
ነብይ መሆን አይጠይቅም፡፡ ኦሎምፒክን የሚያክል ትልቅ ዓለም አቀፍ
ክንውን፤ የጃፓን የኢኮኖሚ ማንሰራሪያን እድል ተደርጎ በእቅድ ሲከወን የነበረን ጉዳይ የገፋ ኮረኖ ቫይረስ፤ ምንአልባት ለብጥብጥ
መነሻ ሰበብ ለመሆን የተዘጋጀን የኢትዮጵያን አገር አቀፍ ምርጫ ቢገፋው ለምን ይገረመናል?
9.1 የኢትዮጵያ ምርጫ “በኮቬድ 19” ምክንያት መራዘሙ የግድ የሚሆንባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች፤
9.1.1 ምርጫችን በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ድጋፍ ጥገኛ መሆን፤
ቀደም የነበረው ምርጫ ቦርድ ላለፉት
25 ዓመታት አምስት ተከታታይ ምርጫዎችን ያካሄደ ሲሆኑ፤ ልምዱ ተቀምሮ ወደ ቀጣይ ለማሻገር በሚሆን መልኩ የተደራጀ አልነበረም፡፡
ይልቁንም ለአዲሱ ምርጫ ቦርድ አቅም ሳይሆን መጥፎ ሰም አስቀምጦለት መቆየቱ የጎለ ነበር፡፡ በዚህ መነሻ አደረጃጀት ይሁን አሰራር፤
በአጠቃላይ ከሕግ ማዕቀፍ እስከ ዝርዝር ተግባራት መከለስ የግድ የሚል ነበር፡፡ በአገር አቀፍ የሚቀመር ልምድ ያለማዳበራችን ደግሞ
ከውጭ እንድናማትር የግድ የሚለን ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ሰለዚህ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ከነበረበት የአቅም ልምሻ ተላቆ፤ አገራዊ ተልዕኮዎን
በብቃት ይወጣ ዘንድ በዓለም አሉ የተባሉ የምርጫ ኤክስፐርቶችን በማሳተፍ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ እነዚህም ኤክስፐርቶች በዚህች
ደሃ አገር በጀት ሊከፈላቸው የሚችል ባለመሆኑ ከውጭ አገራት ከፍተኛ የበጀት ድጋፍ እየተገኘ ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም ለምርጫ
የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ግዢ እና ዕትመት ጭምር ከውጭ የሚከወን መሆኑን ሰምተናል፡፡ ዓለም በኮሮና ቫይረስ በሮቿን ጥርቅም አደርጋ
በዘጋችበት ወቅት ኢትዮጵያ ለምትባላ አገር ከፍታ ይህን የምትከውንበት አንድም ምድራዊ ምክንያት አይታየኝም፡፡ ብዙዎቹ የውጭ ባለሞያዎች
ለድጋፍ ወደ አገራችን የመጡ ቢሆንም የተለያዩ ድጋፎችን ደግሞ ከውጭ ከመጡበት እናት መስሪያ ቤት እንደሚያገኙ ይታወቃል፡፡ እነዚህ
ሰራተኞች በሙሉ ከቤታቸው እንዳይወጡ በተደረገበት፤ ከውጭ የመጡትም ቢሆኑ ወደ አገራችው እንዲመለሱ እየተመከሩ ባለበት ሁኔታ በተረጋጋ
መንፈስ ምርጫ ማዘጋጀት የሚቻልበት ሁኔታ የለም፡፡ ሰለዚህ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያለው የኮሮና ቫይረስ ሰርጭት ሁኔታ መስመር ሳይዝ የተረጋጋ የውጭ ድጋፍ ማግኘት ሰለማይቻል፡፡
በውጭ ድጋፍ ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ምርጫ መራዘሙ የግድ የሚል ይመስለኛል፡፡
9.1.2
በአገር ውስጥ ለምርጫ የተዘጋጁ ፓርቲዎች ለምርጫ ሥራ የሚያስችል ሁኔታ አለመኖሩ፤
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ፓርቲ የሚጠበቅባቸውን ተግባር እየከወኑ
ነው የቆዩት ብሎ በድፍረት መናገር አይቻለም፡፡ ይልቁንም ምርጫ እንዴት በሰበብ አስባብ ላለመሳተፍ “የእናቴ ቀሚስ” የሚል ሰበብ
ሲፈልጉ ነበር ቢባል ስህተት አይሆን፡፡ ለማንኛውም ግን ለምርጫ የተዘጋጁ ፓርቲዎች የሚከውኑዋቸው የተለያዩ ተግባራት ያሉ ሲሆን
በዋነኝነት ለውድድር በሚዘጋጁበት ምርጫ ክልሎች ቢሮ መክፈት፣ አባላትን ማደራጀት፣ ዕጩዎችን መመልመል፣ መራጮችን መቀስቀስ ማስተማር፣
ወዘተ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ ኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል ሲባል በሚጣሉ ገደቦች ጫና ይደርስባቸዋል፡፡
9.1.3
በምርጫ ክልል ቢሮ መክፈት፤
ሁሉም እንደሚረዳው በምርጫ ክልል ፓርቲዎች በዘላቂነት ቢሮ የሚከፍቱበት
ሁኔታ የለም፡፡ ፓርቲዎች አቅም ቢኖራቸው ይህ ቢሆን ክፋት የለውም፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ፓርቲዎች በየምርጫ
ክልሉ የምርጫ ዘመቻውን ለመምራት የሚያስችል ቢሮ መክፈት ብቻ ነው የሚፈልጉት፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው፡፡ በኮሮና
ቫይረስ ምክንያት ምርጫው በትክክል የማይታወቅ ከሆነ ፓርቲዎች ለተራዘመ አላስፈላጊ ወጪ የሚዳረጉ ሰለሚሆን የምርጫ ቢሮ መክፈት
ይቸገራሉ፡፡ ሰለዚህ ምርጫው ሠሌዳ ላይ የሚደረግ ለውጥ በውል ታውቆ ወደ እንቅስቃሴ መግባት ይቸገራሉ፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ
ፓርቲዎች ሥራቸውን መስራት ይቸገራሉ ማለት ነው፡፡
በምርጫ ክልል አባላት አባላት ማደራጀት፤
ፓርቲዎች በተለይ ሁኔታ የምርጫ ወቅትን ተከትለው አባላትን በስፋት ያደራጃሉ፡፡
ኮሮና ቫይረስ ማንኛውንም የሕዝባዊ ስብሰባዎች ማካሄድ የማያስችል ከመሆኑ አንፃር ፓርቲዎች ይህን ተግባር ከባድ ያደርግባቸዋል፡፡
በቂ አባላትን መመልመል ያልቻ ፓርቲ ደግሞ፤ በምርጫው ዕለት በቂ ታዛቢዎችን ማቅረብ የማይችል ሲሆን በምርጫው ቅስቀሳ ወቅትም በቂ
ፈቃደኛ የቤት ለቤት ቀስቃሾችን ማሰማራት አሰቸጋሪ ይሆናል፡፡ ሰለዚህ ይህ ባልተደረገበት ሁኔታ ምርጫ ማድረግ ትርጉም የሚኖረው
ፖለቲካዊ ተግባራ ሊሆን አይችልም፡፡
9.1.4
ዕጮዎችን መመልመል፤
ፓርቲዎችን ወክለው የሚወዳደሩ ዕጩዎች መለየት በዚህ ዓይነት አስቸጋሪ
ሁኔታ ከባድ ይሆናል፡፡ ዕጩዎች ሊያድርጉት የሚፈልጉት የምርጫ ቅስቀሳ ብዥታ ውስጥ ባለበት ሁኔታ ዕጩ የመሆን ፍላጎታቸው ይደበዝዛል፡፡
በዚህ ሁኔታ በቂ ዕጩ ቢገኝ እንኳን በበቂ ሁኔታ ተነቃቅቶ የሚያነቃቃ ሳይሆን “የግብር ይውጣ” ሊሆን የሚችልበት እድሉ ሰፊ ነው፡፡
ምርጫ ባልተነቃቃ የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩ እየተመራ ሲከወን ሰሜት አይሰጥም፡፡
9.1.5
መራጮችን መቀስቀስና ማስተማር ያለመቻል፤
መራጮችን መቀስቀስ ማስተማር በማይቻልበት ሁኔታ ምርጫ የሚባለው ነገር
ሊኖር አይደለም ሊታሰብ አይችልም፡፡ በቂ አማራጭ ቀርቦ ካልመረጡ ምርጫ ቀልድ ይሆናል፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታዎችን
ኮሮና ቫይረስ የማይቻል አድርጎታል፡፡ መራጮች ሰለ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያየ ሁኔታ መስማት ይችላሉ የሚል ታሳቢ ቢወሰድ እንኳን፤
መራጮች ወጥተው ለመምረጥ ፍላጎት በሚያጡበት የምርጫ ድባብ ውስጥ ምርጫ ትርጉም ማጣቱ አይቀሬ ነው፡፡
በአጠቃላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች “በኮቬድ 19” ድባብ ውስጥ ሆነው ምርጫ
መወዳደር አይችሉም፡፡ ምርጫ ቦርድም ቢሆን በዚህ ድባብ ውስጥ ሆኖ ምርጫ ለማወዳደር የሚችልበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ ሰለዚህ ምርጫው
“በኮቬድ 19” አስገዳጅነት ይራዘም እንላለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ “ኮቬድ 19” የገፋውን ምርጫ ሰሌዳ እንደ አንድ እድል
መጠቀም የሚችሉ፤ በዝግጅት ክፍተት የነበረባቸው ፓርቲዎች እንዳሉ ከግምት ማስገባት ይቻላል፡፡ እንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን
ወደ እድል የሚቀይሩ ግን ጥቂቶች ለዚህ ተሰጥኦ ያላቸው ብቻ ናቸው፡፡ በዚህ መስመር የሚገኝ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲ ከተገኝ እሰየው
የሚያስብል ነው፡፡ አሰቂኝ ነገር የሚሆነው ግን ኮሮና ቫይረስ ያስቆመውን/ያገተውን ምርጫ ሠሌዳ ለሌላ የግል ርካሽ ፖለቲካ መጠቀም
መፈለግ መኖሩ እንደማይቀር ስንገምት ነው፡፡
በግሌ ምርጫ መካሄድ አለበት ብዬ የማምን ቢሆንም፤ ማንም ይህን ምርጫ
የሚራዘምበት አሳማታዊ ምክንያት ካመጣ ቢራዘም ግድ የሌለኝ መሆኑን ደጋግሜ ገልጫለሁ፡፡ ምርጫ ከተራዘመ አይቀር ግን በሚኖረን ጊዜ
ኮኖና-ኮሮና ስንል ከርመን ወደነበርንበት ንትርክ ለመመለስ ሳይሆን፤ ቀጣዩ ምርጫ የእውነተኛ ዴሞክራሲ ማዋለጅ እንዲሆን ተጨማሪ
ጊዜ ወስደን በጎ ስራ የምንሰራበት እንዲሆን ምኞቴ ነው፡፡
ይህን በጎ ሥራ ለመስራት ምክክር
የሚጠይቅ ሲሆን፤ ምክክሩ አንዱ አንዱን በዝረራ አሸንፎ ለቀረርቶ የሚወጣበት ሳይሆን፤ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት እንዲሆን ማድረግ
የሚፈልግ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል አገራችንን እንወዳልን የምንል ከሆነ ለበጎ ስራ ማዋል ያለብንን ጊዜ፤ በተቃራኒው “የቱኒዚያ
እና የሱዳን ዓይነት ምስቅልቅል ተፈጥሮ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም የሚያስችል ሁኔታ የሚፈጥር ሕዝባዊ ንቅናቄ በተቀናጀ ሁኔታ
ሊያስተባብርና በመንግሥት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችል የተጽዕኖ ፈጣሪ ዜጐች ስብስብ መድረክ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአስቸኳይ መቋቋም
አለበት” ብሎ የአመፅ ጥሪ ማቅረብ ከእብደት የሚለይ ጥሪ ሊሆን አይችልም፡፡
እጃችንን በሣሙና መታጠብ አንዘንጋ!!
ቸር ይግጠመን!!
10 ኮቪድ 19 የሚፈጥረው የኢኮኖሚ ጫና እና መልካም አጋጣሚዎች!
ኮቪድ በዓለም ላይ የኤኮኖሚ ጫና
ያሳድራል? አያሳድርም? የሚል እስጥ አገባ የለም፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አንድ የዓለም አገር ይህን ጥያቄ ብቻውን ልታስተናግድ አትችልም፡፡
ጥያቄው የሚሆነው አገራት በኮቪድ 19 ምክንያት የሚደርስባቸው ጫና ምን ያህል ይሆናል? የሚለው ነው፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ ጫና
እንደሚያሳድር አውቀን የሚደርስውን ጉዳት በቅጡ “ገምተን” የመከላከያ አማራጮች የማንወስድ ከሆነ አደጋው የኮሮና ቫይረስ ከሚያደርሰው
አደጋ እጅግ የከፋ ይሆናል፡፡ አገሮች ኮቪድ 19 በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ጫና አቃለው ተመልክተው ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ መሆኑን
ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቻይና ቫይረስ እያሉ ሲያላግጡ እንዳልነበር ዛሬ የመስዋዕት በግ ፍለጋ
እያፈላለጉ ይገኛል፡፡ ግዴለሽነት የሚያስከፍለውን ዋጋ ግን እየከፈሉት ሲሆን መቆሚያው መቼ እንደሚሆን በውል አልታወቀም፡፡ የዓለም
አንደኛ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው አሜሪካ በዚህ ደረጃ ዋጋ ከከፈለች የእኛ የምስኪኖቹ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል ብሎ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡
በአገራችን የሚፈጠረውን ጫና እና
መወሰድ የሚገባውን ምላሽ ምን መሆን አለበት በሚል ሁለት ፅሁፎች ወጥተዋል፡፡ ይህን ፅሁፍ እየፃፍኩም በግብርና ላይ የሚያሳድረውን ጫና አንድ ቡድን እየሰራ እንደሆነ መረጃ ወጥቷል፡፡
ያገኘኋቸው ሁለት ፅሁፎች “Macroeconomic_Impacts_of_the_Corona_Virus_A_Preliminary_Assessment”
በሚል; CEPHEUS RESERCH AND ANYLITICS በሚባል የጥናት ቡድን በማርች 31/2020 ያወጣው አንዱ ሲሆን፤
“Economic and Welfare Effects of COVID-19 and Responses in Ethiopia: Initial
insights” በሚል በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ማህበር በኤፕሪል 2020 አጋማሽ የወጣው ሌላኛው ነው፡፡
የመጀመሪያው ፅሁፍ
ከቁጥጥር ውጭ ባልሆነ የቫይረስ ስርጭት፤ በኢኮኖሚያችን ላይ የሚከተሉት ጉዳቶች አይቀሬ ናቸው ይለናል፡፡ የሚያነሳቸው ነጥቦች
(የማክሮ ኤኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡) እነዚህ ነጥቦች በራሳቸው ስፋ ተደርገው ሊተነተኑ ይችላል፤
1.
አምስት በመቶ የአገር አቀፍ እድገት መቀነስ፤
2.
1.5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ይገባ የነበረው ይቀንስ፤
3.
ከ750 ሺ እስከ 1.5 ሚሊዮን ሥራዎች ችግር ላይ ይወድቃሉ፤
4.
ከ 27 -57 ቢሊዮን ብር የደሞዝ ገቢ ሊታጣ ይችላል፤
5.
መንግስት
አስከ ብር 90 ቢሊዮን (በ2.3 በመቶ የአገር ውስጥ ምርት) ለማህበረስብ ድጋፍ ሊያስፈልገው ይችላል፤ እና
6.
ብሔራዊ ባንክ ብር 47 ቢሊዮን (1.3 የአገር ውስጥ ምርት)ለሚያስፈልጉ
ወጪዎች ፍላጎት ያስፈልገዋል፡፡
ሁለተኛው ፅሁፍ
በቤተሰብ እና በአንሰተኛ ቢዝነስ ላይ ያተኮሩ ጉዳዮችን (ማይክሮ ኤኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡) የአገር አቀፍ ምርት 2.2 - 9.9 በመቶ በሚደርስ ቅናሽ እንደሚያሳይ ግምቱን የሰጠ ሲሆን፤ ይህ በጣም በተጠናከረ
የመከላከል ስራ በሶሰት ወር ውስጥ በቁጥጥር ሰር ከዋለ በትንሹ እስከ 2.2 በመቶ ቅናሽ ይታያል፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ በስራ
እድል መቀነስና ስራ መቀዛቀዝ ብቻ ነው፡፡ ቫይረሱን ለመቆጣጠር የሚወስደው ጊዜ በተራዘመ ቁጥር ውስብስብነቱም እንዲሁ በመጨመር
በገጠርም በከተማም ያለው ድህነት በከፍተኛ ደረጃ ይባባሳል የሚል ግምት አለው፡፡ በዚህ መነሻ የአጠቃላይ ህዝቡ 50 ከመቶ ለከፋ
ድህነት ሊጋለጥ ይችላል በሚል ይደመድማል፡፡
ከእነዚህ ሁለት ፅሁፎች የምንረዳው ነገር ቢኖር አገራችን ኢትዮጵያ በኮቪድ
19 ጉዳት የሚያገኛት መሆኑን እና አጠቃላይ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከማናጋት ባሻገር ዜጎችን ለከፍተኛ ጉዳት እንዲሚያጋልጥ ነው፡፡
መንግሥትና አጠቃላይ ሕዝቡ ይህን በመረዳት ጉዳቱን ለመቀነስ ሁሉን አቀፍ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ፅሁፎቹ ይህን ለማድረግ
መሰጠት አለበት ያሉትን ምላሽ ምክረ ሃሳብ የሰጡ ሲሆን ወደ ምላሹ ዝርዝር ሳልገባ በግሌ የሚመስለኝን ሃሳብ ለመሰንዘር እሞክራለሁ፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት፤ ከዓለም ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋር ግንኙነት
እንዳላቸው ቢታመንም፤ እንደተጣበቁ መንታዎች በአንድ እትብት የሚተነፍሱ ግን አይደሉም፡፡ ይህ መሆኑ ብዙ ጊዜ የዓለምን የእድገት
ትሩፋት እንዳንካፈል የሚያደርገን ቢሆንም፤ በእንዲሀ ዓይነት ክፉ ጊዜ ደግሞ ጉዳቱ እንደ ትልልቆቹ አገሮች የከፋ የሚሆንበት መጠንም
ይቀንስልናል፡፡ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አሌ የማይባል ጉዳት እንደሚደርስ ከላይ በጥናት የተራጋገጠ ግምት ቢኖርም፤ ልንቋቋመው
የማንችለው የሚሆን ዓይነት አድረገን የምንወስደው ግን አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ምን አልባትም ለኢኮኖሚ መነቃቃት
የተለየ መንገድ ለማስብ ልንጠቀምብት እንችላለን፡፡
ለምሣሌ በኢትዮጵያ የባንክ ሴክተር ክሬዲት በመስጠት ከክሬዲት በሚሰበሰብ
የወለድ ገንዘብ የሚተዳደር አይደለም፡፡ አብዛኛው ገቢው ከሌሎች አገልግሎት ነው፡፡ ባንኮች በከፍተኛ ደረጃ ዲፖዚት/ቁጠባ ልንለው
እንችላለን/ ማሰባሰብ ከፍተኛ የስራቸው አካል ነው፡፡ የመንግሥት ባንክ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች በተናጥል ትርፍና
ኪሳራቸው ቢሰራ አብዛኞቹ ከሳሪዎች ናቸው፡፡ በተመሳሳይ የግል ባንኮችም የዚህ ዓይነት ሞዴል የሚከተሉ ናቸው፡፡ ትርፋቸው የሚገኘው
ከጥቂት ነጋዴዎች ጋር የሚያደርጉት የሥራ ግንኙነት ነው፡፡ ባንኮች በዋነኝነት ሚሊዮን ድሆች ከብር 1000(አንድ ሺ) እስከ
10000 (አሰር ሺ) ለክፉ ቀን ብለው የሚቆጥቡትን ገንዘብ፤ ለጥቂት ኢንቨስተሮች ማበደር ዋና ተግባራቸው ነው፡፡ ኮሮና ቫይረስ
እነዚህን ሚሊዮን ድሃዎች እና ጥቂት ኢንቨስተሮች የሚያገናኙትን ባንኮች አከርካሪ እንደሚሰብር መታወቅ ይኖርበታል፡፡
ድሆች ለክፉ ጊዜ ብለው ያስቀመጡትን በሙሉ የማውጣት ፍላጎት የሚኖራቸው
እና የባንኮችን ዲፖዚት/ተቀማጭ ባዶ የሚያደርጉትበት ሁኔታ ያለ ሲሆን፤ ተቀማጩን በብድር የወሰዱት ኢንቨሰተሮችም በተፈጠረው ሁኔታ
ብድር መክፈል ስለማይችሉ ባንኮች ከፍተኛ ችግር ላይ እንደሚወድቁ ይታመናል፡፡ ይህ ሁኔታ መንግሥት ጣልቃ በመግባት ዜጎች ገንዘባቸውን
ማግኘት የሚችሉ መሆኑን መተማመኛ በመስጠት፤ ነገር ግን ተቀማጫቸውን ጠርገው ከሚያወጡ “የክሬዲት አገልግሎት” በማስጀመር የባንኮችን
ስራ አንድ ደረጃ ከፍ ማድረግ የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ በአገራችን እንደምታውቁት ሁሉም ዜጋ ያለው “ዴቢት ካርድ” ብቻ
ነው፡፡ ኮሮና “ክሬዲት ካርድ” እንዲኖረ ሊያደርግ ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ካልሆነ ግን አሁን በተፈጠረው ሁኔታ የግል ባንኮች
የሰበሰቡትን የሕዝብ ገንዘብ ለመክፈል የሚችሉበት ሁኔታ በፍፁም አይኖርም፡፡
ሌሎች ብዙ መልካም አጋጣሚዎች በኮሮና ምክንያት ሊመጡ ይችላሉ፤ በሚፈጠሩት
መጥፎ ሁኔታዎች ብቻ ጭንቅላታችንን ወጥረን መጨነቅ ሳይሆን፤ መልካም አጋጣሚዎችን ማፍታታት እና ማየት ያስፈልጋል፡፡ ኮሮና በግልፅ
ካሳየን ነገር አንዱ አገራችን ኢትዮጵያ የብዙ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ሆና ዜጎቿን ለመቀለብ
የውጭ ጥገኛ መሆኗ ምን ያህል አስከፊና አሳፋሪ እውነት እንደሆነ ነው፡፡ ይህን ሁኔታ መቀልበስ የሚያስችል እና በምግብ እህል ሙሉ
ለሙሉ ራስን በአገር ውስጥ መቻል የሚባል ፖሊስ የግድ የሚለን መሆኑን ሁሉም ሊረዳው ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ በምንም ሚዛን ስንዴ ከውጭ
አምጥታ ዜጎች መቀለብ የለባትም፡፡ ይህን መልስ የማይሰጥ የፖለቲካ ሥርዓት መነወር ይኖርበታል፡፡
እጃችንን እንታጠብ!
ርቀታችንን እንጠብቅ!
አንድነታችንን እናጠናክር!
11 “ኮቬድ 19”፣ ምርጫ እና ሕገ መንግሥታዊ እውነት ….
ባለፈው
ፅሁፌ የኢትዮጵያ አገራዊ ምርጫ በምንም መመዘኛ ከኦሎምፒክ እንደማይበልጥ እና ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ ተገንጥሎ ምርጫ ማካሄድ አለብን
የሚል ተረት ተረት መቆም እንዳለበት የሚያሳስብ፤ ምርጫው ሊራዛም የሚችልበት በቂ ምክንያት እንዳለ ለማስረዳት ሞክሪያለሁ፡፡ ምርጫ
ቦርድ የእኔ ፅሁፍ በወጣ በአራተኛው ቀን መጋቢት 22/2012፤ ባወጣሁት የጊዜ ሠሌዳ መሰረት ምርጫ ማካሄድ እንደማልችል እወቁልኝ
የሚል ውሣኒያቸውን ለሚመለከተው ሁሉ አሳውቀዋል፡፡ መቼም ምርቻ ቦርድ አልችልም እያለ ትችላለህ ብሎ ክርክር ማድረግ አይቻለም፡፡
ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው ያስብለና፡፡ በተጨባጭ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ ምርጫ ቦርድ አልችልም ማለቱን ብዙዎች ትክክል መሆኑን እየገለፁ
ነው፡፡ እኔም በዚሁ ውሣኔ የምስማማ መሆኔን በአደባባይ ይመዝገብልኝ፡፡
ምርጫ
ቦርድ “በኮቬድ 19” ምክንያት በተፈጠረው አገራዊ እና ዓለማዊ ሁኔታ ምክንያት ምርጫ ማካሄድ በተያዘው የጊዜ ሠሌዳ ማካሄድ አልችልም
በማለቱ ፈተና ላይ የወደቀው ዋንኛው የአገሪቱ የፖለቲካና የሕግ ሠነድ የሆነው “ሕገ መንግሥቱ” ነው፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት ብዙ
ነገሮች ላይ ዝርዝር የሌለው ቢሆንም፤ በዝርዝር ሕጎች ይወሰናል የሚል ቀዳዳም አይሰጠም፡፡ ምርጫን በተመለከተ በተቀመጠው ድንጋጌ
መሠረት ማካሄድ ባይቻል ምን ማድረግ እንዳለበት አይናገርም፡፡ ምንም አይገርምም … ይህ ሰነድ በሰዎች የተዘጋጀ ነው፤ ሰዎች ደግሞ
የሰሩትን ሥራ በሂደት እየገመገሙ ማረም ይችላሉ፡፡ ይህ ሕገ መንግሥትም በአንቀፅ 105 ሕገ መንግስት የሚሻሻል ሠነድ መሆኑን ብቻ
ሳይሆን እንደ ልብ እንዳይሻሻልም ጭምር በማስብ ተንኮል ሁሉ ያዘለ አንቀጽ ደንግጓል፡፡ “ሕገ መንግስቱን ሰለማሻሻል” የሚል አንቀጽ 105 በግልፅ
ያለው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ተንኮል የሚያስብለው አንቀጽ 105/1 ሲሆን በዚህ አንቀጽ መሰረት የህገ መንግስቱ አንቀፅ 14 እስከ
44 እና አንቀፅ 104 እና 105 ማሻሻል አይቻልም በሚል ደረጃ የተቀመጠ ነው፡፡ ይህን ማድረግ እድል የነበረው ኢህአዴግ ሙሉ
በሙሉ የተቆጣጠረው ፓርላማ እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲሁም ሁሉም ክልሎች በኢህአዴግ መመሪያ በሚተዳደሩበት ቅድመ መጋቢት
2010 ዘመን ነበር፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ሊሻሻል የሚችለው በፖለቲካ ውሣኔ እና በሕዝበ ውሣኔ የሕገ መንግሥቱ ሠነድ
እንዳለ ለሕዝብ ይሁንታ ሲቀርብ ነው፡፡ ይህን በክፋት የታጀለ አንቀጽ ተወት አድርገን ወደ ዛሬው ፅሁፍ መነሻ የሆነው ክስተት እንመለስ፡፡
ምርጫ ቦርድ በወሰደው አቋም ምክንያት
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58/3 መሰረት “የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው፣ የሥራ
ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሒዶ ይጠናቀቃል፡፡” የሚለውን ድንጋጌ መፈፀም አይቻለም፡፡ ይህ
እውነት ሆኖ ተከስቷል፡፡ ይህን አውነት ተጋፍጦ መፍትሔ መፈለግ የግድ ይላል፡፡ ቀጣይ የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎች ይህን ነገር ከግምት
ማስገባት እንዳለባቸው የሚያነቃ ደውል ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ሌሎችም አንቀፆች እንደሚኖሩ እምነቴ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ እንዴት
እንፍታው የሚለውን የግሌን አማራጭ ከማቅረቤ በፊት ግን በዚህ ጉዳይ ዋንኛ ባለድርሻ አካላት ከሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች አቋም በጨረፍታ
ማየት አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡
ይህን ጉዳይ አስመልክቶ “ደርዝ”
ያለው ሃሳብ ይዘው ይፋ ያደረጉት “ኦነግ እና ኦፌኮ” ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉት ፓርቲዎች ምርጫው በነሐሴ ወር መጨረሻ ይካሄዳል ሲባል
ተገቢ አይደለም ብለው ክርክር አቅረበው ነበር፡፡ ምርጫ ቦርድ በሕገ መንግሥት በተቀመጠው ጊዜ ምርጫ ለማካሄድ እና ተገቢውን ዝግጅት
ለማድረግ ከዚህ የተሻለ ጊዜ የለኝም የሚል ምላሽ ሲሰጥ፤ መከራከሪያ አድርገው ያቀረቡት “ክረምት መሆኑ፣ ቢዘህ ምክንያት የአርሶ
አደሩና የኮሌጅ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተሳትፎ ይገድባል፣ ወዘተ” የሚል ነበር፡፡ አሁን በምርጫ ቦርድ ፈቃድ ሳይሆን በተፈጥሮ
አስገዳጅነት አገራዊና ዓለማዊ እውነታዎች መነሻ ምክንያት ከክረምቱ ተገፍቶ ወደ በጋው መዛወሩ ሲገለፅ፤ ተሸቀዳድማ ያቀረቡት ሃሳብ
ቀድሞም የሰጡት ሰበብ “ክረምት” እና ተመሳሳይ ምክንያቶች ከልብ እንዳልነበሩ የሚያሳብቅ ነው፡፡
እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ያወጡት
መግለጫ ከመስከረም በኋላ ምርጫም ባይኖር እንዴት አድረገን በሥልጣን ውሣኔ የሚሰጥበት ወንበር እናገኛለን የሚል መሆኑ ፍንትው ብሎ
ታይቷል፡፡ ይህ በእውነት ለትዝብት የሚጥል መሆኑን ለማወቅ የፖለቲካ ሊቅ መሆን የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ እርግጥ ነው፣ በተጭበረበረ ምርጫ፣ በሕዝብ አመፅ እና እንቢተኝነት ጥርሱ
ተነቃንቆ በይቅርታ እስከምርጫ እንዲቆይ ይሁንታ ያገኘ መንግሥት ሌላ ተጨማሪ ጊዜ ማግኘት አልነበረበት፡፡ ነገር ግን፤ አሁንስ
በቃ ከመስከረም በኋላ እኛም ለአጭር ጊዜም ቢሆን መንግሥት በሚሰራው ተግባር ድርሻ ይኑረን የሚሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች በምንም መመዘኛ
የሕዝብ ውክልና ያላቸው አይደሉም፡፡ በተጭበረበረ ምርጫ አይደለም፤ ለአባልነት አስር ሺ አባላት ለማስፈረም ምጥ የሆነባቸው ፓርቲዎች
ይበዙበታል፡፡ ሰለዚህ ቀጣዩ ምርጫ ለማካሄድ ፈጣን የተባለውን አማራጭ የጊዜ ሠሌዳ ተመካክሮ ከመወሰን ውጭ በአቋራጭ የመንግሥት
ሥልጣን ለመጋራት የሚደረግን ሃሣብ መጠየፍ ይገባል ብዬ በግሌ አምናለሁ፡፡ አማራጩ ምንድነው? የግል ምልከታዬን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ከገጣም
ሕገ መንግሥታዊ ክሽፈት ለመውጣት ሁለት አማራጮች መመልከት ይቻላል፡፡ ሁለቱም አማራጮች ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያላቸው ናቸው፡፡
የሞራል ጥያቄ ሊያስነሱ ቢችሉም ምርጫው የግድ ሲሆን መምረጥ የሚያስፈልግ ይመሰለኛል፡፡
አንደኛው አማራጭ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሊሆን ይችላል፤ ከላይ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ ያሉት ድንጋጌዎች እኩል ክብደት እንደሌላቸው በአንቀፅ
105 በግልፅ ተደንግጓል፡፡ አሁን ባለንበት ወቅት ፈተና ላይ የወደቀው አንቀጽ 58/3 የመሳሰሉት አንቀጾች ግን ሊሻሻሉ የሚችሉበት
ሁኔታ እንዳለ ከዚህ ቀደም የነበሩ ልምዶች ያሳያሉ፡፡ ለምሣሌ አንቀጽ 103/5 “የሕዝብ ቆጠራ በየአስር ዓመቱ ይካሄዳል፡፡ በውጤቱም
መሰረት የምርጫ ክልሎችን አከላለል የምርጫ ቦርድ በሚያቀርበው ረቂቅ መሠረት የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ይወስናል፡፡” የሚለው ድንጋጌ
ሊተገበር የማይችልበት ሁኔታ በመፈጠሩ በአንቀፅ 105/2 መሰረት ማሻሻል ተችሏል፡፡ ሰለዚህ አንቀጽ 58/3 በዚሁ መሰረት ላይሻሻል
የሚችልበት ምክንያት የለም፡፡ ነገር ግን የሞራል ጥያቄ የሚያስነሱ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
የሞራል ጥያቄ ያልኩት ጉዳይ የሚመጣው
አሁን ለውሣኔ የሚቀርበው አንቀጽ ውሣኔ የሚሰጡት የምክር ቤት አባላት በራሳቸው ጉዳይ ላይ መሆኑ ነው፡፡ ለተጨማሪ የስልጣን ዘመን
እንቆይ ለማለት፤ ተሰብስበው ውይይት ሲያደርጉ ክርክሩ ከግል ጥቅም አንፃር ወገንተኝነት ሊታይበት የሚችልበት እድል መኖሩን መካድ
አይቻልም፡፡ አሁን ያጋጠመንን ሁኔታ ግን “የኢትዮጵያ ምክር ቤት አባላት” ለሥልጣን ሲሉ በሴራ አመጡት ተብለው ሊታሙ ስለማይችሉ
ችግሩ የከፋ ላይሆን ይችላል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ችግር ከመስከረም
በኋላ በቁጥጥር ስር ባይውል ምን ማድረግ ይቻላል? ከዚህ ጋር ተያይዞ ወይም ሳይያዝ የተፈጥሮ ወይም ሰው ሰራሽ ችግር ቢገጥመነስ
ምን ይደረጋል? ከባድ ጥያቄዎች መሆናቸው የሚታወቅ ቢሆንም በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በሃላፊነት ሰሜት፤ ለአገርና ለመንግሥት
ጥቅም ሲል ይወስናል ብለን በጥንቃቄ መጠበቅ ነው፡፡ ሕዝብ ጥቅሙን የሚነካ ነገር ሲፈጠር ዝም አይልም የሚል ተስፋም አለ፡፡ በነገራችን
ላይ ምርጫ የሚደረገው ሕዝብ በመረጠው አካል/ፓርቲ እንዲተዳደር ነው፡፡ የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነት ማረጋገጫ ነው፡፡ ሰለዚህ ጉዳዩ
በዋነኝነት የሕዝብ ነው እንጂ የፓርቲዎች አይደለም፡፡ ሕዝብ ይህ የተፈጠረው እውነት የሌለ፤ ሕዝብን በመረጠው እንዳይተዳደር ለማድረግ
የተፈጠረ ልዩ ሴራ ብሎ ካመነ፤ ሆ! ብሎ ወጥቶ ያስቆመዋል፡፡
ከላይ የጠቀስኩት የሕገ መንግሥት
ማሻሻያ እንደ ከዚህ ቀደሙ በቀላሉ ሊገኝ የማይችልበት ሁኔታ መኖሩን መዘንጋት የለብንም፡፡ ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ሁለት ሶስተኛ
ድምፅ ይጠይቃል፡፡ በምክር ቤት የሚገኙት አባላት ይህን ላያደርጉ የሚችሉበት ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋንኛው ማሳያው በቅርቡ በኢትዮጵያ
ዜና አገልግሎት የቦርድ አባላት ማፅደቅ ወቅት የነበረው የድምፅ አሰጣጥ ነው፡፡ ሰለዚህ ሁለተኛው አማራጭ ምክር ቤቱን መበተን ነው፡፡ ይህ የሚሆን ከሆነ ሕገ መንግሥታዊው መውጫው መንገድ አሁን
አብላጭ ድምፅ የያዘው ብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤቱን በአንቀፅ 60/1 መሰረት በአብላጫ ድምፅ መበትን ይችላል፡፡ “ጠቅላይ ሚኒሰትሩ የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሄድ
በምክር ቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱ እንዲበተን ለማድረግ ይችላል፡፡” የሚል ድንጋጌ በመኖሩ የሚቻል ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን
ለማድረግ እና ለምርጫ ቦርድ በቂ ጊዜ መስጠት ከፈለጉ ደግሞ፤ ይህን ማድረጊያ ጊዜውን ወደ ነሐሴ መጨረሻ ወይም መስከረም አጋማሽ
ላይ ማድረግ ይችላሉ፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣው የሞራል
ወይም ደግሞ የተገቢነት ጥያቄ በመስከረም መጨረሻ ሳምንት ተጋብዞ ለሚበተን ፓርላማው አንድ ወር ወይም ከዚያ ያነሰ ጊዜ እንዳለው
እየታወቀ ይህን ማድረግ ተገቢ ነው ወይ? የሚለው ሊሆን ይችላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ተገቢውን አማራጭ ባለማቅረቡ አንድ ቀንም የቀረው
ምክር ቤት በሥራ ላይ ነው ብሎ መተርጎም ይቻላል፡፡ ሌላ አማራጭ ካለ ለውይይት ክፍት ነው፡፡
እጃችንን እንታጠብ!
አካላዊ ርቀት ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ
ጥግግትም እንቀንስ!
ሰላም ለአገራቸን እና ለሕዝባችን
ይሁን!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን አብዝቶ ይባርክ!
አሜን!
No comments:
Post a Comment