ህወሓትና የዜሮ ድምር ፖለቲካ
የዜሮ ድምር አስተሳሰብ የሚባለው በዋነኝነት
የሚገለፀው አንድ ሰው ወይም ቡድን አንድ ነገር ማግኘት ካለበት ሌላኛው ሰው ወይም ቡድን በተመሳሳይ ማጣት ይኖርበታል፡፡ አንደኛው
ቡድን ያገኘው እና አንደኛው ቡድን ያጣው ሲደመር ውጤቱ ዜሮ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ በኤኮኖሚክስ ሚዛኑን የጠበቀ
(Equilibrium Situiation) የሚባለው ዓይነት ነው፡፡ የዜሮ ድምር አስተሳሰብ ማለት
በሀገራችን “ፈጣሪ ከየት ያመጣል ከአንዱ ወስዶ ላንዱ ይሰጣል”
በሚል የሚገለፀውን የሚወክል ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ በመሰረቱ በስህተት የተሞላ ነው፡፡ ለዚህ ነው ሰዎች ካልሰረቁና ካላጭበረበሩ
የሚከብሩ የማይመስላቸው፡፡ እሴት መጨመር የሚባለውን የትልቁን ኬክ ታሪክ አለማወቅ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪ ሳይቀማ የሚሰጥ መሆኑንም
የዘነጉ ናቸው፡፡ በእምነትም በመደበኛ አስተምህሮም ስህተት ነው፡፡ ህወሓት በዚህ ፍልስፍና የሚመሩ ግለሰቦች ስብስብ ነው፡፡
የዜሮ ድምር አስተሳሰብ
በ“Game Theory” በተለይ በድርድር ወቅት አንዱን አስጥሎ አንዱ አግኝቶ ለመውጣት የሚደረግ ጥረት ስለሚሆን ተገቢ አስተሳሰብ
አይደለም፡፡ ይህ ማለት ግን በሁሉም ጊዜ ትክክል አይደለም የሚባል እንዳልሆነ ማወቅ ይገባል፡፡ ለምሳሌ የፓርላማ ወንበርን በተመለከተ
ለምርጫ በሚደረግ ውድድር አንዱ ፓርቲ ወንበር ካገኘ አንዱ ማጣቱ የግድ ነው፡፡ የምርጫ ውድድር ሲደረግ ሌላኛውን አሳጥቶ ራስ ለማግኘት
የሚደረግ ጥረት በመሆኑ ክፋት የለውም፡፡ ወንበሩ 547 እስከ ሆነ ድረስ እና የወንበር ቁጥር ለውጥ ካልመጣ በፓርቲዎች መሃከል
የሚደረግ ውድድር በዜሮ ድምር አስተሳሰብ የሚመራ ነው የሚሆነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ከአንዳንድ የምክር ቤት አባላት ጋር ስነጋገር
የፓርላማ ወንበራቸውን ለመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ መልቀቅ እንደሚኖርባቸው (አንዳንድ ሀገሮች በሚከተሉት የምርጫ ስርዓት እንዲህ
ዓይነት ውጤት እንደማይፈቀድ) ሲነገራቸው የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ነው ብለው ሌላ የቃላት ድሪቶ ከማምጣት የዘለለ መልስ የላቸውም፡፡
ኬኩ ውስን በሆነበት የዜሮ ድምር ጨዋታ የግድና የተፈቀደ ጨዋታ ነው፡፡ በእግር ኳስ ጫወታም ተመሳሳይ ነው፡፡ ሙሉ ነጥብ ለማግኘት
አንዱ መጣል አለበት፡፡
የህወሓት ሰዎች
እድሜ ዘመናቸውን በሙሉ በዜሮ ድምር አስተሳሰብ ተጠምደው፤አገራዊ ኬክ በማሳደግ ሳይሆን ያለውን በመቀማት ለዛሬው የመጨረሻ ቀናቸው
ደርሰዋል፡፡ ይህን ድርጊታቸውን በፖለቲካ፤ በኢኮኖሚ እና በማሕበራዊ መስክ አድርገን በፈርድ በፈርጁ ልናየው እንችላለን፡፡ የዛሬው
ርዕሴ ህወሓት በመሆኑ ነው እንጂ በአገራችን በተለይ የብሔር አደረጃጀት ያላቸው ቡድኖች በሙሉ ተመሳሳይ ነው፡፡ መነሻቸው ተበድለናል
የሚል ለቅሶ ሲሆን፤ መፍትሔው ደግሞ በተራቸው መበደልና መቀማት ነው፡፡
የህወሓት ፖለቲካ
በእነርሱ የበላይነት ካልሆነ በስተቀር ልክ ሊሆን አይችሉም ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ከዳር እስከ ዳር በተንቀሳቀሰ
ሕዝባዊ ማዕበል የተመታው ህወሓት መራሹ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ፤ በመጋቢት 2010 ዳር እንዲይዝ ሲደረግ ህወሓት የጫወታውን
ሁኔታ አይቶ፤ ፖለቲካውን በጠቅላይነት ከመምራት በጋራ ወደ መምራት መውስድ አልሞከሩም፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ሁሉንም እድል
ቀስ በቀስ በመገፍተር መቀሌ መመሸግን መርጠዋል፡፡ የዜሮ ድምር አስተሳሰብ የተጫነው ህወሓት፤ በብልፅግና ውስጥ ሊኖረው የሚችለውን
ድርሻ ከጠቅላይነት በታች ለመቀበል ዳገት ሆኖበት፤ ሲሽኮረመም ከሁለት ዓመት በላይ ፈጅቶበታል፡፡ ባለፉት የሥልጣን ዘመን በረዳትነት
ጥፋት ሲፈጽሙ ከነበሩ ሀይሎች ጋር ጥፋቱን አጋርቶ ለእርምት በጋራ መቆም ፈተና የሆነበት የህወሃት ቡድን፤ በመጨረሻም ጠቅሎሎ መቀሌ
መግባትና መመሸግ አማራጭ አደረጉታል፡፡ ይህንንም ቢሆን አለን የሚሉትን የፖለቲካ ፍልስስፍና በትግራይ ምድር ሊያሳዩ የሚችሉበት
እድል ነበራቸው፡፡ ነገር ግን፤ “ያደቆነ ሠይጣን ሳያቀስ አይተውም” እንደሚባለው፤ በማዕከል ያለውን፤ ጥለውት የመጡትን ሥልጣን
እየጎመዡ “ባልበላው ጭሬ ልበትነው” በሚል ፈሊጥ የአገራችንን ፖለቲካ ቅርቃር ውስጥ ከተቱ፡፡ እኔ የማልመራት ኢትዮጵይ ብትንትኗ
ይውጣ የሚል መንገድ መረጡ፡፡
ህወሓት የፖለቲካ
የበላይነቱን ለማስረገጥ የሄደበት የመከላከያም ሆነ የደህንነት ተቋማትን በበላይነት መምራትና መቆጣጠር ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ከአንድ
የህወሃት የቀድሞ ከፍተኛ የጦር ሃላፊ ከነበሩ ጄነራል ጋር በነበረኝ ውይይት፤ በመከላከያም ሆነ በደህንነት በታችኛው መዋቅር የህወሓት
ተሳትፎ እያነሰ መምጣቱን፤ ይህም የሆነው ወጣቱ አሁን በዚህ ደረጃ ለመሳተፍ ፈቃደኛ እንዳልሆነ፤ በእነዚህ ወሳኝ ተቋሞች ላይ የትግራይ
ተወላጆች በዋነኝነት በትግል ወቅት ተሳታፊ የነበሩት መሆናቸው፤ ምንም ዓይነት ችግር ቢፈጠር ለትግራይ ሕዝብ ምንም ዋስትና እንደማይሰጡት
አስርድቶኛል፡፡ ይህ ግን በህወሓት ስብስብ ውስጥ ግንዛቤ ያገኘ ጉዳይ አልነበረም፡፡ የምታሰማራው ዋንኛ ሀይል ጠብመንጃና ታንክ
የያዘው እና እሳት የሚተፋው እንጂ ግፋ ቢል በወገቡ ሸጉጥ የታጠቀን ከፍተኛ ወታደራዊ ሹም ያለመሆኑን የህወሓት ሹሞች አልተረዱትም፡
የወታደራዊም ሆነ የፖለቲካ ሹሞቹ በፍፁም ፍቅረ ንዋይ በመታወራቸው የተነሳ፤ የአገር ሀብት አሳድጎ ድርሻን ለማግኘት ሳይሆን ያለውን
ጥሪት ሳያስቀሩ መቦጥቦጥ ላይ ሆነ፡፡ በመጨረሻም ጦርነት በጄኔራል ብዛት ማሸነፍ እንደማይቻል በህይወት ከተረፉ ሊያዩት በሚችሉበት
ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡
ህወሓት ፖለቲካ
ያለ ኤኮኖሚ የበላይነት ሊሆን እንደማይችል የተረዳ ቡድን ነው፡፡ ይህንንም በማንኛውም ሕጋዊና ሕገወጥ መንገድ ሲፈፅም እንደነበር
የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ በግሌ ህወሓት ከማዕከል ፖለቲካው ተገለለ ተብሎ፤ ከኤኮኖሚ ኢምፓየሩ ተፈንቅሎ ይውጣ ከሚሉት ወገን አልነበርኩም፡፡
የዋህ ሰለሆንኩ ሳይሆን ለዘላዊ መልካም ግንኙነት የሚል በቂ ምክንያት ሰለነበረኝ ነው፡፡ ህወሓት የትግራይ ሕዝብ ሀብት ነው በሚል
ከፍተና ፕሮፓጋንዳ የሰራበት ጉዳይ ነው፡፡ እውነቱ ግን የጥቂት የህወሓት ሹመኞች መፋነኛ የነበረ የኤኮኖሚ ኢምፓየር ነው፡፡ የኤፈርት
ንብረት በውርስ ቢሆን በሌላ መንገድ መቀማት፤ ከሚያመጣው ኤኮኖሚያዊ ጥቅም እና ፍትሓዊነት ይልቅ በትግራይ ተወላጆች ዘንድ ሊፈጥረው
የሚችለውን ቅሬት ከግምት በማስገባት ነበር የተለሳለሰ አቋም ለማራመድ የምሞክረው፡፡ ይህ ቅሬታ የሚያመጣው የመተማመን ጉድለት ለማስቀረት፤
ዘራፊዎች የዘረፉትን ሀብት ይዘው አርፈው እንዲቀመጡ የሚመር ቢሆንም ብዙዎች ፍላጎት አሳይተናል፡፡ ይህንንም በአደባባይ ተናግሬ
ነበር፡፡ በዜሮ ድምር አስተሳሰብ በሚመራ ፖለቲካ ይህ ሊሆን አልቻለም፡፡ ህወሓት ቀደም በዘረፋ መስርቶ በህገወጥ የገበያ ሥርዓት
ያደለባቸው ኩባንያዎች ወደ መስመር መግባት ሳይሆን፤ ይህን ሀብት ተጠቅመው አገር ማመስ፤ በዚሁ ሀብት ተጠቅመው እጅ ጠምዝዘው የፖለቲካ
ጥቅማቸውን ማስከበር የትግል ሥልት አደረጉት፡፡ ዛሬስ፤ እነዚህ ኩባንያዎች የባንክ ሂሣባቸው ታግዶ በሰሩት ወንጀል መነሻ የሚወረሱ
መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ከምሰረታው ጀምሮ የወንጀል ፍሬ የሆኑ የኤኮኖሚ አውታሮች፤ በይቅርታ ወደ ህጋዊ ሥርዓት ማስገባት
ያቃተው የህወሓት የዜሮ ድምር አስተሳሰብ ፖለቲካ አመራር፤ መጨረሻው በህግ አግባብ ተወርሰው ለህዝብ ጥቅም እንዲውሉ ማድረግ መሆኑ
እውን ሆኖዋል፡፡ ይህ የዜሮ ድምር አስተሳሰብ ፖለቲካ ውሳኔ ውጤት ነው፡፡
ከሁሉም የሚከፋው
ቀጣይ ጉዞዋችንን ፈታኝ የሚያደርገው በማህበራዊ ኑሮዎችን የተተከለው ነቀርሳ ነው፡፡ በማህበራዊ ዘርፍ የትግራይ ተወላጆችን በተለያዩ
አደረጃጀት በማቆራኘት፤ ሌላውን እንዲጠራጠሩ ህወሓት የሰራው ክፋት ከሁሉም የከፋው ሊሆን ይችላል፡፡ የትግራይ ልጆች ሰርተው በሚጠቀሙባቸው
ማህበረሰብ ውስጥ እራሳቸውን የተለያ አደርገው እንዲመለከቱ፤ ከሌላው የተለየን ነን የሚል የተሳሳተ ምልከታ እንዲይዙ በማድረግ ከፍተኛ
ቅሬታን ፈጥሯል፡፡ ዛሬ ተጋሩ ተለይቶ “ተጠቃ” ወይም “ሊጠቃ” ነው በሚል የሚነዛው ፕሮፓጋንዳ አደገኛነት ሊገነዘቡት አልቻሉም፡፡
ይህ የበሬ ወለደ ፕሮፓጋንዳ ከፖለቲካውም ሆነ ከኤኮኖሚው ጋር ካለው
በላይ ጉዳቱ የከፋ ነው፡፡ ምን አልባትም ለቀጣይ ከባድ ፈተና ሊሆንብን የሚችለው፤ ህወሓት በጥቂት የዘረፋ አባል በነበሩ አባላቶቹ
የተሳሳተ ምልከታ መነሻ የትግራይ ሕዝብ ሁሉ እንደነዚህ ሰዎች “ይሉኝታ ቢስ” አድርጎ የመመልከት ችግር ነው፡፡ በከተማ ለዘረፋ
የተሰማሩ የህወሓት አባላት እና ጋሻ ጃግሬዎች በፍፁም የትግራይን ህዝብ እንደማይወክሉ ለማመን ብዙ መስራት ይኖርብናል፡፡ ይህ በሁሉም
ወገን የጋራ ጥረት የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡ በምንም ዓይነት በማንነት የሚተላለፍ ክፋት የለም፡፡ የትግራይ ልጆች ኢትዮጵያ የመሰረቷት
አገር ነች፡፡ እኛ ያለ እነርሱ፤ አነርሱ ያለ እኛ ጎዶሎ ነን፡፡ ኢትዮጵያዊነት በጋራ ሰንሆን ከአክሱም እስከ ሶፎሞር፤ ከጎንደር
ካስል እስከ ድሬዳዋ ዋሻ ናቸው፡፡ ጀጎል የተጋሩም ነው፡፡
የዜሮ ድምር ፖለቲካ ከህወሓት ጋር ቻዎ ቻዎቸ…..
No comments:
Post a Comment