Tuesday, October 13, 2015

ኢህዴግ በሚጠራው መድረክ አለመገኘት ማንን ይጠቅማል? ግርማ ሠይፉ ማሩ

girmaseifu32@yahoo.com, www:girmaseifu.blogspot.com
ቅጥ አንባሩ የጠፋው የኢትዮጵያችን ፖለቲካ በዋነኝነት የሚጎድለው ልክ ያልሆነን ነገር ልክ አይደለም ማለት ያለመቻል ነው፡፡ በግል አስተያየት ልክ አይደለም ብሎ መቆም ደግሞ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ የተሳሳተ ውሳኔ ባለቤቶች በድጋሚ ጥፋታቸውን በጥፋት ለማረም ሌላ ስህተት ይደግማሉ፡፡ አሰተያየትን በአሰተያየት ለመመለስ ይከብዳቸዋል፡፡ የዚህ ደግሞ ዋነኛው ሰለባ የተቃዋሚው ጎራ ነው፡፡ ለነገሩ አሁን ይህ ነው የሚባል ተቃዋሚ አለ ባይባልም፤ ያሉትም ቢሆኑ ከልምድ የሚማሩ ዓይነት ሆነው አልተገኙም፡፡
ለዛሬ ፅሁፌ መነሻ የሆነኝ አንድ ሰሙ “የአንዳርጋቸው ፅጌ ብርሃን” በሚል የብዕር ሰም የሚከተለውን መልዕክት በፌስ ቡክ ገፄ የውስጥ መልዕክት ማስቀመጫ
“ግርማ ካሳ (ልብ በሉ እኔ ግርማ ሠይፉ ነኝ) ወረድክብኝ በጣም። ተፈጭቶ ተቦክቶ ተጋግሮ ሊበላ የቀረበውን ነገር ድጋሚ ወፍጮ ቤት ይሂድ ብለክ እየተከራከርክ ነው። 24 አመት ሲያታልል የኖርን መንግስት ዛሬ 25ኛው አመት ላይ ሆነክም እንዴት አልገባክም? ስንት አመት ነውሚፈጀው እንዳንት አይነት ሰዎችን ለማብሰል? ተወያየተክ ምን ታተርፋለክ ? ወያኔ ተቃዋሚዎችን  ሚፈልገው ለተራ ፕሮፖጋንዳው ሊጠቀምባቸው እንጂ ለነሱ ሀሳብ ጆሮ ለመስጠት አደለም። መንግስት እራሱ ያወጣውን ህግ ጥሶ ያሰራቸውን የፓርቲ አባሎችን ለማስፈታት ከወያኔ ጋር ስብሰባ መቀመጥ አያስፈልግም። እንዲምታስብ ከሆነ ከአልም ሁሉ ተለይተክ ከሀይለማርያም ደሳለኝ ብቻ የተሻልክ ጅላጅል ነክ ማለት ነው። ወያኔ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተጻፈውን ድብዳቤ ልብ ብለክ አንብበከዋል ? እንዲ የሚል አርፍተ ነገር አለበት። "በሀገራችን የሚገኙ ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች "እንደ መላው የሀገራችን ህዝቦች " እያለ ይቀጥላል። ሲጀመር ወያኔ እነዚ ፓርቲ ብሎ የሚያውቃቸው ድርጅቶች ከህዝብ ተለይተው ያሉ እና የህዝብ ድጋፍ የሌላቸው አርጎ ነው የጠራቸው። ፀረ ህዝብ አርጎ ነውሚስላቸው። አንደ ህዝብ አካል አርጎ አይቆጥራቸውም አያከብራቸውም። አንዳንተ ዓይነት አሟሟቂ ሰው ነው ወያኔሚፈልገው።ኢቢሲን አሟሟቂ”
የሚል መልዕክት አስቀመጠልኝ፡፡
መልዕክቱ የተፃፋው በዚህ ጉዳይ አስተያየት ለሰጠው ወዳጄ ግርማ ካሣ ይመስላል ነገር ግን  የተላከው ለእኔ በእኔ አድርሻ እና እኔን በዓይነ ልቦናው እየሳለ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ በእኔ እይታ ደግሞ የግርማ ካሣን ሃሳብ መደገፍ ብቻ ሳይሆን በግል ለደወሉሉኝ አቋሜን ገልጬ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ  ግን ሚዲያ ላይ ወጥቶ አስተያየት መስጠት ብፈልግም፤ ብዙ ምቾት አልተሰማኝም ነበር፡፡ ለማነኛው የዚህ አሰተያየት ሰጪን ሃሳብ መነሻ አድርጌ የግሌን አስተያየት ላቅርብ፡፡
በመጀመሪያ ማነኛውም ግብዣ ላይ የተጠራ ሰው ግብዣ የሚሄደው በመከባበር ሰሜት መሆን አለበት፡፡ ጠሪ አክባሪ በሚል እንጂ ግብዣው ላይ ምን ድግስ አለ በሚል መሆን የለበትም፡፡ በእኔ እምነት ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገራዊ አጀንዳ ላይ ከዚህ በፊት ጥሪ ተደርጎላቸው የማያውቁ የፖለቲካ ፓርቲውች መድረክ፣ ሰማያዊ እና መኢህአድ ግብዣ ተደርጎላቸዋል፡፡ ለምሳሌ በመጀመሪያው የአምስት ዓመት ዕድገትና ትራንሰፎርሜሸን ዕቅድ እና በአባይ ግድብ ወቅት ጥሪ ስለ አልተደረገላቸው አልተጠራንም ሃሳባችንን መስጠት እና የጋራ ማድረግ አልቻልንም ሲባል ነበር፡፡ በዚህ ወቅት የፖለቲካ ምዕዳሩም ሆነ አጠቃላይ ሀገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ተመሳሳይ ነበር፡፡ በዛን ጊዜ ተቃዋሚዎች አልተጠራንም ሲሉ የነበረው ተጠርተው ለመቅረት አይመስለኝም፡፡ ተገኝተው ሃሳባቸውን ለማካፈል ይመስለኛል፡፡
በእኔ እምነት አሁን በተደረገው ጥሪ መስረት ከላይ ሰማቸውን የጠቀስኩት ፓርቲዎች ተገኝተው የሚከተለውን ማከናወን ይችሉ ነበር፡፡ መጀመሪያ ያለፈው አምስት ዓመት ክንውን ሲቀርብ ከመነሻው ጀምሮ በጋራ ከተቃዋሚዎች ጋር በጋራ ለመስራት መንግሰት እርምጃ ባለመውሰዱ የእቅዱ ዋና ዋና ምሶሶ የሆኑት ተግባራት ያለመሳካታቸውን በተጨባጭ ማስረጃ ለማስረዳት እድሉን ሊጠቀሙበት ይችሉ ነበር፡፡ ለምሳሌ የባቡር ዝርጋታ ከታቀደው 30 ከመቶ ያለመሰራቱ፣ በኤሌትሪክ ሀይል በተመሳሳይ 20 ከመቶ እንኳን ያለመሳካቱ፤ በመንገድ በውጭ ንግድ፣ በዋጋ ማረጋጋት፣ በግብርና በተለይ በሰፋፊ እርሻ ወዘተ.. ያሉትን መሰረታዊ ችግሮች በማሳየት ለዚህ ዋነኛው ችግር በጋራ በመስራት ሊገኝ የሚችለውን ሀገራዊ ሀይል ወደ ጎን ማድረጋቸውን ለህዝብ ይፋ ማድረጊያ መድረክ ይሆን ነበር፡፡ በተለይ የአባይ ግድብን ገዢው ፓርቲ የፖለቲካ መጠቀሚያ እንዲሆን በማድረጉ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሊያደርጉ የሚችሉት ከፍተኛ አሰተዋፅኦ መገደቡን ለመናገር ከዚህ የተሻለ ትክክለኛ መድረክ የሚያገኙ አይመስለኝም፡፡ ይህንን መድረክ ለመጠቀም ባለመቻላቸው ትልቅ የፖለቲካ ኪሣራ ይመስለኛል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ገዢው ፓርቲ እራሱ ያመነውን የመልካም አስተዳደር መፍቻው ቁልፍ መንገድ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ እና በተለይ ደግሞ የሚዲያዎች ተሳትፎ መኖር ተዓማኒነት የሚጣልባቸው የፍትህ ስርዓት መሆኑን በሰብሰባው በሚፈጠሩ አጋጣሚዎች ሁሉ በማንሳት ዕቅዱ ያልተሳካው ይልቁንም ሙስና የተንሰራፋው ስርዓቱን የሚተቹ ጋዜጠኘኞችና አምደኞች በመታሰራቸው፣ እምነት የሚጣልበት የፍትህ ስርዓት ባለመኖሩ እንደሆነ አጋጣሚውን መጠቅም ይቻል ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዝግጅት አድርገው መሳተፍ እንጂ አድማ አድርጎ ከግብዣ በመቅረት ውጤት የሚገኝ አይመስለኝም፡፡ ይህ ትልቅ ሰህተት ይመስለኛል፡፡
ከዚህ ውይይት በማስከተል “የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም” በሚል ተረት ከገዢው ፓርቲ ጋር ተመራርቆ ለመውጣት ሳይሆን በቀጣይ ዕቅድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለያዩ ሀገራዊ አጀንዳዎች በምን መልክና ደረጃ ስንሳተፍ ይህ ዕቅድ ተግባራዊ ይሆናል በሚል መነሻነት የድርጊት መርዓ ግብር በመንደፍ የጋራ ኮሚቴ አቋቈሞ መውጣት፣ በተለይ የፖለቲካ ምዕዳሩ ለማስፋት የሚቻልበት መንገድ መቀየስ ሊሞከር የሚገባው ትልቅ ስራ ነበር፡፡ ይህ ከገዢው ፓርቲ ባህሪ አንፃር ተቀባይነት ባያገኝ እንኳን እንቢተኝነቱን ለማጋለጥ ይረዳ ነበር፡፡ እንደ ፓርቲ ሰርተፊኬት ይዞ ዓመት ከመቁጠር በዘለለ መንግሰት በተገኘበት ሁሉ እየተገኙ ድምፅ ማሰማት (ባይሰሙም መጮኽ) ግዴታቸው ነበር የሚል የግል አቋም አለኝ፡፡
እውነቱን ለመናገር በቁጥር እስከ ሃያ የሚደርሱ የፓርቲ አባላትን (ለምሳሌ ሶስቱ ፓርቲዎች 60 አባላትን) በአንድ መድረክ ላይ እንዲገኙ የተሰጠን እድል ያለመጠቀምን ያክል ደካማ ውሳኔ አይታየኝም፡፡ እያንዳንዳቸው ሁለት ደቂቃ መልእክት ቢያስተላልፉ የሁለት ሰዓት መልዕክት በመንግሰት ጆሮ ላይ ማስቀመጥ ይቻል ነበር፡፡ እነዚህን አጋጣሚዎች በእስር የሚማቅቁ ጓዶቻችንን በማንሳት ልንዘክራቸው ይገባ ነበር፡፡ አሸባሪ ያሏቸውን “ጀግኖች” ብለን ልናወደስ የምንችልበት መድረክ ያለመጠቀም በምን መመዘኛ ልክ እንደሚሆን አይታየኝም፡፡
ገዢው ፓርቲ ከአሁን በኋላ ለማነኛውም ዓይነት ውይይት ሳይጠራ ዳተኛ ቢሆን ሰበብ አግኝቷል፡፡ ቢጠሩም አይገኙም ይልቁንም በሚጠሩበት መድረክ ከመገኘት ይልቅ ውጪ ሆነው መግለጫ በማውጣት ላይ ይገኛሉ ብሎ ለሀጋሮቹ ማስረጃ ያቀርባል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከኢህዴግ መንግስት ባልተናነሰ ካድሬ የሆኑ የአሜሪካን እና አውሮፓ ህብረት ድጋፍ ሰጪዎች ይህን ለመስማት እና ለማመን ብዙ አይቸገሩም፡፡
በእኔ አረዳድ ፓርቲዎቹ በግብዣው ላይ ተገኝተው በምን ጉዳይ አተኩረው እንደሚናገሩ እንዴት አድርገው የፖለቲካ ጥቅም እንደሚያገኙበት መካሪ አላገኙም፣ በውስጥም በቅጡ አልመከሩበትም፡፡ የሚያሳዝነው እነዚህ ፓርቲዎች የአሜሪካ ኤምባሲ ለስዕል ኤግዚቢሽን ምረቃ ቢጠራቸው በግብዣው ላይ ይገኛሉ፡፡ የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባል ሊያነጋግራችሁ ይፈልጋል ቢባሉ ይገኛሉ፡፡ መገኘት ብቻ ሳይሆን አነጋገሩን ብለው ዜና ይሰራሉ፡፡ እንግዲህ አንባገነኑ ኢህአዴግ ዲሞክራት እሰኪሆን ጠብቀው ለመወያየት ከሆነ ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ ባለፈው ፕሬዝዳንት ኦባማ ጉብኝት ሲያደርጉ ለግንኙነት በሚመቸው የእራት ግብዣ ላይ ላለመገኝት ወስነው በብዙ ሜትር ርቀት በቴሌቪዥን በተሻለ ለመከታተል በሚቻልበት የአዳራሽ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ሲወስኑ ዝም ማለታችን አበጃችሁ ያልን የመሰላቸው መሪዎች፤ ይህንንም ግብዣ ለፖለቲካ ጥቅም ማዋል አለመቻላቸውን ዝም ማለት ተገቢ አይደለም ለማለት ሲባል የቀረበ አስተያየት ነው፡፡ በእኔ እምነት በሰላማዊ ትግል በሀገር ውስጥ ለመንቀሳቀስ የወሰነ ማንኛውም አካል መንግሰትን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እያገኙ መልዕክት ማስተላለፍ ተገቢ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ እና መንግሰት በሚጠሩት ማንኛውም ስብሰባ ላይ ላለመገኘት መወሰን የሚጠቅመው ገዢውን ፓርቲ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ሃሣብ ያለው በመቅረት የሚገኘውን ጥቅም ቢያስረዳኝ፣ በተለይ አሁን በተደረገው የሁለተኛው የእድገት እና ትራነስፎርሜሽን እቅድ ለመወያየት በተደረገው ጥሪ ላይ ያለመሳተፍ ያስገኘውን ጥቅም ለሚያስረዳኝ ለመማር ዝግጁ መሆኔን እገልፃለሁ፡፡ በደፈናው ገዢውን ፓርቲ እውቅና መንፈግ የሚል መልስ ግን አልቀበልም፡፡ በሀገር ውስጥ ሆኖ በዚሁ መንግሰት ስር እየተዳደሩ እውቅና መንፈግ የሚባል ፖለቲካ አይገባኝም፡፡
ቸር ይግጠመን!!!!

Friday, September 25, 2015

የኢህአዴግ መንታ መንገድ

ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com
ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነኝ በእሁድ መስከረም 2/2008 ሪፖርተር ላይ የወጣው የኢህአዴግ የግንባርነት ጉዞና ቀጣይ ፈተናዎች በሚል የቀረበው ፅሁፍ ነው፡፡ ይህ ፅሁፍ ጠቅለል አድርጎ በሰንጠረዥ ያሰፈረው መረጃ ስለ ግንባሩ አባል ድርጅቶች አቻ ያለመሆን ብዙ የሚያስረዳ ሲሆን ለይሰሙላ በምክር ቤት የሚታየው መለያየት በዋና ዋና ወሳኝ ቦታዎች ላይ በእኩልነት ፍልስፍና እኩል ድምፅና እኩል ውሳኔ ሰጪ ወደ መሆን ቀይሮታል፡፡ ዛሬ ማንሳት የምፈልገው በእኔ እይታ በቀጣይ ግንባሩ ያለበት ፈተና በወሳኝ መልኩ ምን እንደሆነ የግል ምልከታዬን ማቅረብ እና በመጨረሻም ተቃዋሚዎች በዚህ መንታ መንገድ ላይ ሚናቸው ምንድነው? የሚለው ነው፡፡
ኢህአዴግ ይህችን ሀገር ሊገዛበት የሚችለው አደረጃጀት መስርቶ ላለፉት ሃያ አራት ዓመታት በስልጣን ላይ እንደቆየ ይታወቃል፡፡ ግንባሩን ከመሰረቱት ድርጅቶች በተጨማሪ ደግሞ በግንባሩ ሳንባ የሚተነፍሱ “አጋር” የሚባል ታርጋ የተለጠፈላቸው መኖራቸው ደግሞ እሙን ነው፡፡ ለማነኛውም ግን የግንባሩ አባል ድርጅቶች እና የአጋር ድርጅቶች ጥምረት ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ባይታወቅም፣ ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት በኋላ ደፍሮ ይህን ግንባር አፈርሶ ወይም አሳድጎ ወደ ውህድ ህብረ ብሔር ፓርቲ የሚያደርስ አቅም ያለው ቡድንም ሆነ ግለሰብ ማየት እየተቸገርን ነው፡፡ ይህ ግንባሩን መንታ መንገድ ላይ ሀገራችንንም ሰጋት ላይ የሚጥል ነው፡፡
በአብዛኛው በግንባሩ አባል ድርጅቶችም ሆነ በአጋር ድርጅቶች ውስጥ በአመራርነት ቦታ የያዙት ሰዎች በምንም መመዘኛ ሀገር ለመምራርት የሚያስችል የግል ብቃትና ስብዕና ያስመዘገቡ አይደለሙ፡፡ ይልቁንም አሁን የያዙትን ቦታ ያገኙት በተደራጁበት የብሔር/የጎሣ መዋቅር ወኪል በመሆን ነው፡፡ ግንባሩ ህብረ ብሔራዊ ፓርቲ ወይም ንቅናቄ ቢሆን ብቃት ዋነኛው መመዘኛ ሆኖ ሌሎች ተዋፅኦ የሚመለከቱ ጉዳዮች ተከታይ መስፈርት ስለሚሆኑ ብዙ ጥገኞች ይራገፋሉ፡፡
ቀጠዩ አምስት ዓመት ኢህአዴጎች ተቃዋሚው እንዳያንሰራራ አድርገው ህዝቡም ይህን በፀጋ ተቀብሎ የሚጠናቀቅ ከሆነ፣ የኢህአዴግ ተግዳሮት የሚጀምረው ሌላ ምርጫ ሲደረግ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ይሁን? የሚለው ነው፡፡ በእርግጠኝነት ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ከአጋር ድርጅቶች ለማግኘት የሚቻልበት እድል በፍፁም በግንባሩ መስመር ዝግ ነው፡፡ የግንባሩ እና የአጋሮች ግንኙነት ይህን አይፈቅድም፡፡ ይህች ሀገር ነች እንግዲህ ዜጎች እኩል ናቸው የሚባልባት፡፡ አፋር፣ ሶማሌ፣ አደሬ፣ ቤኒሻንጉል፣ ጋምቤላ፣ ወዘተ ሆኖ የጠቅቀላይ ሚኒትርነት ቦታ የሚያዝበት ስርዓት የለም፡፡ ግንባሩ ለአጋሮች መች የክልል ስልጣን አነሳቸው የሚል ትምክት ላይ እንዳለ አሁንም ያሳያል፡፡
ግንባሩን መስቀለኛ መንገድ ላይ የሚያቆመው ወሳኙ ጉዳይ ቁልፍ የሚባለው ስልጣን በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ቦታ አሁንም ቢሆን ለግንባሩ አባል ድርጅቶች አለመዳረሱ ነው፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒሰትር ያለምንም ይሉኝታ ከሃያ ዓመት በላይ ስልጣኑን ጠቅለለው በመያዛቸው እና ድንገት ጉዳዩን ፈር ሳያሲዙት በሞት መለየታቸው፤ አሁን ላሉት የግንባሩ እኩዮች ትከሻ ለመለካካት በር የከፈተ ሲሆን ፈተናውም ከባድ ሆኖባቸዋል፡፡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትር የሚል ማዕረግ እስከ መስጠት የደረሰ፡፡ በዘጠነኛ የግንባሩ ድርጅታዊ ጉባዔው ግንባሩ አንድ ውሳኔ አሳልፎዋል፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ በሌሉበት የተካሄደ በመሆኑ ድርጅቱን ከሁለት ዙር በላይ አንድ ሰው አይመራውም የሚል አቋም ለመያዝ ብዙ አልተቸገሩም፡፡ አቶ መለስ ቢኖሩ በእጅ አዙር ልክ አልነበሩም እንደማለት ስለሚሆን የሚደፍረው አይገኝም ነበር፡፡ ከዚህ ስንነሳ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ከዚህ አምስት ዓመት በኋላ የድርጅቱም ሆነ የሀገሪቱ መሪ የሚሆኑበት እድል ዜሮ የሆነ ይመስለኛል፡፡ እኔ እንደሚገባኝ “የአክሱም ሀውልት ለወላይታ ምኑ ነው?` በሚባልበት ድርጅት ውስጥ በአቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒሰትርነት የደቡብ ንቅናቄ አባላት ሁሉ ይደሰታሉ ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ በብሔር ፖለቲካ ስልጣን ለሚፈልጉ ስብስቦች የሀይለማሪያም ደሳለኝ ከወላይታ ጠቅላይ ሚኒሰትር መሆን ለሲዳማ፣ ለጉራጌ፣ ለጋሞ፣ ወዘተ ምኑ ነው? ይህ የሚያሳየው ይህ ቦታ ለደቡብም ንቅናቄ ደስታና እርካታ አልፈጠረም ማለት ነው፡፡ ቢሆንም አሁን ባለው የግንባሩ ቀመር ደቡብ ድርሻውን አግኝቶዋል እንበል …. ልክ ባይሆንም ….
ዋናውን ወንበር ጠባቂ ቀሪ የግንባሩ ደርጅቶች “የአማራው” ብአዴን እና “የኦሮመ” ኦህዴድ ናቸው፡፡ የኦሮሞ ብሔረተኞች ለላንቲካ ከሚሰጠው የፕሬዝዳንትነት ቦታ በላይ ይገባናል የሚል ቅሬታ አላቸው፡፡ ይህ ከባድ ጥያቄ ባለበት ጊዜ በሚቀጥለው ዙር የጠቅላይ ሚኒሰትርነት ቦታ ለአማራ መስጠት በግንባሩ ውስጥ ጡዘት ይፈጥራል የሚል የግል ግምት አለኝ፡፡ ጡዘቱ ከኦህዴድ ብቻ ሳይሆን ከህወሃት ጭምር የሚመጣ ይመስለኛል፡፡ አማራ/ነፍጠኛ በደለህ ተብሎ ሲዋጋ የነበረው የትግራይ ብሔረተኛ መልሶ ለአማራ ዋናውን ቁልፍ የስልጣን ቦታ ይስጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ስለዚህ በቀጣይ ኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒሰትር የመሆን እድሉ የሚታወቀው የፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ አንድ የስራ ዘመን ከቀጣዩ ምርጫ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ሲጠናቀቅ ቦታውን ለአማራ እንዲሰጥ በማድረግ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒሰትር ኦሮሞ እንዲሆን ሊደረግ ይቻላል፡፡ ይህ ኦህዴድ ከአሁን ጀምሮ ዝግጅት ያደረገበት እንደሆነ የሚሳካ የቤት ስራ ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ነገር ግን ፕሬዝዳንት ሙላቱ በመንበሩ ላይ ከቀጠሉ ግን ካርታው በውድም ሆነ በግድ የፖለቲካ ጡዘቱን ለመሸከም ተዘጋጅቶ ግንባሩ ጠቅላይ ሚኒሰትርነቱን ለአማራ ያስረክባል ማለት ነው፡፡ ብዙዎች እንደሚገምቱት ሁሉም የግንባሩ አባል ድርጅቶች ይህ ወሳኝ የስራ አስፈፃሚ ቦታ ሳይደርሳቸው መልሰው ለህወሃት ይለቃሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ህውሃት አሁን ባለው ሁኔታ ከጠቅላይ ሚኒሰትርነት በመለስ ወሳኝ የሚባሉትን ቦታዎች ለማስከበር በትጋት የሚሰራ ይመስለኛል፡፡
ይህ ሁሉ ስንክሳር የመጣው ወግ በሌለው የብሔር ፖለቲካ የተደራጁ ቡደኖች የፈጠሩት ግንባር ቀጣይነት ያልታሰበበት ብቻ ሳይሆን ሌሎች አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲዎችም እንዳይጎለብቱ እየተደረገ በመሆኑ ነው፡፡ ግንባሩ ከዚህ ስንክሳር የሚወጣበት አንዱ መንገድ አጋሮቹን ጨምሮ የግንባሩ አባል ድርጅቶች በፖለቲካ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ፓርቲ/ንቅናቄ ለመሆን የመወሰን አቅም ሲፈጥር ለዚህም ሃሳብን ለማንሸራሸር እድል የሚፈጥር ውስጠ ዲሞክራሲ ሲኖረው ነው፡፡ ከዚህ ውጭ አንድ ቀን በስልጣን ጥም የሚነሳ የውስጥ ግጭት የሚያፈነዳው እሳተ ገሞራ ጦሱ ለእኛም ሊተርፍ ይችላል፡፡ ኢህአዴግ ይህችን ቀጣይ አምስት ዓመት ህዝቡን በልማት ስም ለማደናገር በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተውጦ በመስቀለኛ መንገድ ላይ መሆኑን ከዘነጋው ጦሱ ለብዙዎች የሚተርፍ ነው የሚሆነው፡፡ ዛሬ ኢህአዴግ የሚያስፈልገው አሁንም በጎጥ የሚሰበሰቡና ስልጣን የሚቀራመቱ ኪራይ ስብሳቢዎች ሳይሆን ከዚህ ቀደም አቶ ተፈራ ዋልዋ አቅርበውት የነበረውን እና ብቻቸውን ድምፅ የሰጡለት የአዋሳ ጉባዔ ሃሳባቸውን አቧራውን አራግፎ የሚያነሳ ጎበዝ ነው፡፡ ይህ ሃሳብ ደግሞ እነ ሀብታሙ አያሌውን የመሰሉ ምርጥ ወጣቶች ተሰፋ አስንቆ ኢህዴግ አባል እንዲሆኑ ያደረገ ነው፡፡
ኢህአዴግ ይህን እርምጃ እንዲወስድ የምንመክረው ፓርቲ ከሀገር በላይ መሆኑን በማሰብ እና በእነርሱ ዝርክርክነት የሚመጣው ጦስ ለእኛም ስለሚተርፍ ነው፡፡ ግንባሩ በዚህ መስመር እራሱን ከቃኘ ሌሎች በህብረ ብሄራዊ አደረጃጀት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲደራጁ ፍርሃትና ብርክ አይዘውም፡፡ከሌሎች ጋር ለመወዳደርም ቢሆን ድፍረት ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስብዕናቸው የተፈተኑ ሰዎች በተቃዋሚም ሆነ በገዢ ፓርቲ ውስጥ ጎልተው እንዲወጡ ማድረግ የሚያስችል ስርዓትም የሚፈጠረው ይህን መስቀለኛ መንገድ መሻገር ከቻለ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ስርዓት በሃሳብ የተሻሉ ሰዎች ወደ መድረክ የሚመጡበት እንጂ በጎጥ በኮታ ሹመትና ጥቅም የሚሰባሰቡበት እንዳይሆን ገደብ ያበጃል፡፡
ከዚህ በፊት በተለያየ አጋጣሚ እንደተናገርኩት በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለውን አውራ በሚል አውሬ የሆነውን ግንባር ለመገዳደር የሚችል ተቃዋሚ መኖር የግድ እንደሚል ጥርጥር የለኝም፡፡ ይህ ጠንካራ ተቃዋሚ በእኔ እምነት አሁን ካሉት ተቃዋሚ ነን በሚል ስርተፊኬት ይዘው ከሚንቀሳቀሱት ቡድኖች ውስጥ አይገኝም፡፡ ይህ ማለት ግን በእነዚህ ፓርቲዎች ውስጥ ለዚህ የሚሆን እርሾ የሚያበጁ በግለሰብ ደረጃ ሰዎች የሉም ማለት አይደለም፡፡ እንደ ስብስብ ግን የትኞቹም ቡድኖች በተለየ አደረጃጀት እራሳቸውን ለማፅዳት ቢያስቡ ከውስጥ በሚነሳ እሳት ጉልበትና ጊዜያቸውን መጨረስ ብቻ ነው ትርፉ፡፡ ይህ ደግሞ ተሰፋችንን ያርቀዋል፡፡ በቀጣይ ይህን ከባድ ሀገራዊ ሃላፊነት የሚወጣ ማንኛውም ቡድን ይፈጠራል የሚል ተሰፋ አለኝ፡፡ የዚህ ቡድን ሃላፊነት አባላቶቹ ለአቅመ መስጠት የደረሱ መሆናቸውን ማረጋገጥ የግድ ይለዋል፡፡ ሰጦታቸውም በቸርነት እንጂ ለጉራ እና ነገ በውለታው ምን አገኛለሁ በሚል ስሜት እንዳይሆን ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉም በላይ አባላቶቹ ለፖለቲካ መሪነት እራሳቸውን በቁርጠኝነት ያዘጋጁ እና  ሀገር የመምራት ሃላፊነታቸው በህዝብ ዘንድ ይሁንታ እንደሚያገኝ እርግጠኞች መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ማለት አባላቱ እራሳቸውን ከማሳመን አልፈው የህዝብ ታዓማኒነት ለማግኘት የማይቸገሩ እንደሆነ እርገጠኛ መሆን አለባቸው፡፡
ኢህዴግም መስመሩን ካስተካከለ ተቃዋሚ የሚሆን ቡድን ማግኘት ከቻለን ውድድሩ በተመሳሳይ ኪሎ እና በሃሰብ ልዮነትና የበላይነት ላይ ይሆናል፡፡ ይህን ተሰፋችንን እውን ለማድረግ ቁጭ ብለን በመቆዘም አይመጣም፤ ወይም ደግሞ ሌላ ነፃ አውጪ ቁጭ ብሎ በመጠበቅ፡፡ ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል፡፡
ቸር ይግጠመን

Thursday, August 20, 2015

ወጣቶቹን እየበላ ያለው ስርዓት …

ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com; www.girmaseifu.bolgspot.com
 ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ በቀጣይ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ የተመረጡ እና የተለመዱ ፊቶችን ስብስበው ጥያቄ ሲያቀርቡና ማብራሪያ ሲሰጡ ነበር፡፡ የእኔን ቀልብ የሳበው ግን አውቀውም ይሁን ሳያውቁት ወጣቶችን እየበላ ያለ ስርዓት ባለቤት እና መሪ መሆናቸውን የገለፁበት አስተያየት ከታዳሚው ሞቅ ባለ በተደጋጋሚ ጭብጨባ መታጀቡ ነው፡፡ ባለፈው የኦባማ ጉብኝት ወቅት ዲሞክራሲ ማላት ምርጫ በስላም ማጠናቃቅ ብቻ አይደለም፡፡ ጋዜጠኞችን አክቲቪሰቶችን እስር ቤት እያወረዱ አማራጭ ፖለቲካን እየከለከሉ ዲሞክራሲ የተሟላ አይሆኑም ብለው ሲሞልጯቸው በጭብጨባ ያጅቡ ነበር፡፡ ዛሬም ተመሳሳይ ነገር ነው የሆነብኝ፡፡
ይህን ፅሁፍ ከመለጠፌ በፊት ግን በእስር ላይ ያሉ ጓዶቻችን ከእስር እንዲፈቱ ፍርድ ቤት መበየኑን ሰምቻለሁ፡፡ ንፁህ ናችሁ ብሎዋቸዋል፡፡ ንፁህ ነበሩ እና አይገርምም፡፡ ይህን ማበረታታት አለብን፡፡ እነ አንዱዓለም፣ ናትናኤል፣ እስክንድር፣ ተመስገን ደሳለኝ ፣ ወዘተ መለቀቅ አለባቸው፡፡ ይህን ጥሩ እርምጃ ኦባማ ተቆጥቷቸው ነው እያሉ ከማንቋሸሽ ይህን እያጣጣምን ተጨማሪ መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ለማነኛውም ለቤተሰቦች ዕዳ ሆነው የነበሩት ታጋዮች ነፃ ወጥተዋል፡፡ ከቂሊንጦ!!! እንኳን ደስ ያላችሁ ደስ ያለን!!!
ወደ ተነሳሁብ ነጥብ ሰመለስ ጠቅላይ ሚንስትሩ ጉቦ የሚበላባቸው መስሪያ ቤቶች እንዳሉ ማወቅ ብቻ አይደለም ወጣቶችንም ጉበኛ አድርጎ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አስልጥኖ ወደ ተግባር እንደሚያስገባ በግልፅ ነግረውናል፡፡ በተጨማሪ ምንም ዓይነት የተሟላ ማስረጃ ቢኖረን ጉዳያችንን መጨረስ የማንችልባቸው የመንግስት ተቋማት እንዳሉም ጠቅላይ ሚኒስትራችን ጠንቅቀው ያውቃሉ እነዚህም ተቋሞች የሰለጠኑ አዲስ ምሩቃን ወጣቶች ስራ እንዲሰሩ ሲመደቡላቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት ጉዳይ ማለቅ እንደሌለበት ጠንቅቀው ይማራሉ፡፡ ይህንንም በተግባር ይፈፅሙታል፡፡ እነዚህ መስሪያ ቤቶች የመንግስት አገልግሎት መስጫ ነው፡፡
ባለጉዳይን በአግባቡ እና በስርዓት ያለማስተናገድ በእርሰቸው ቃል አመናጫቂና አንጓጣጭ መስሪያ ቤቶችም እንዲሁ የተመደቡላቸውን ወጣት ምሩቃን በፍጥነት ቀይረው ተገዶ አገልግሎት ፍለጋ የመጣውን ተገልጋይ ያመናጭቃሉ፣ ይሳደባሉ፡፡ ይህን ስስማ የጤና ባለሞያዎቻችን ወላዶችን በምጥ ወቅት ማን አርግዥ አለሽ አትጩሂ ሲሉ ተሰማኝ፡፡ ሌሎች የሚሉትን ፀያፍ ቃል ለዚህ ፅሁፍ ስለማይመጥን ዘልየው ነው፡፡
የሀገር ውስጥ ገቢ ኦዲተሮች እና ገማቾች በግብር ከፋይ ዜጎች ላይ ያላቸውን “ቬቶ ፓውር” ማወቅ ብቻ አይደለም፣ ጠቅላይ ሚኒስትረ ተሰፋ የቆረጡበት ሁኔታ ያለ የሚመስል አስተያየት ነው የሰጡት፡፡ ሂሳብ ሰርታችሁ ካልመጣችሁ እንደፈለጉ ያድርጓችሁ የሚሉን ይመስላል፡፡ ለአፋቸው እንኳን እነዚህን ልክ ማስገባት አለብን የሚል ተሰፋ አልሰጡንም፡፡ እኔ በግሌ የሀገር ውስጥ ኦዲተር ብሆን ስራ አቆም ነበር፡፡ ደግነቱ እግዜር አንድኖኛል፡፡ በእኛ ሀገር መስሪያ ቤቱ ሲሰደብበት ኃላፊነቱን የሚለቅ ባለስልጣን ስለሌለን ነው፡፡ እራሴ እለቅ ነበር ያልኩት፡፡
እነዚህን ሁሉ ወጣቶችን የሚበሉ መስሪያ ቤቶች የሚተዳደሩት በመንግሰት በጀት፣ በምርጫ አሸንፌ ስልጣን ያዝኩ በሚል መንግሰት በሚሾሙ የፖለቲካ ሾመኞች መሆኑን የዘነጉት ይመስላሉ፡፡ ይህን ለማለት ያስቻለኝ ደግሞ መፍትሄው የታጋይ ዜጋ መኖርና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ነው በማለት አስቀምጠው፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነት በተመለከት ጠንካራ ፓርቲና አመራር በመኖሩ ተገባራዊ ማድረግ ይቻላል በሚል አሹፈውብናል፡፡
ይህን ፕሮግራመ የተከታተልን ሰዎች ታጋይ ዜጎችን በእኔ ትርጉም እንቢ ሙሰኝነት ….. ያሉትን፣ የመልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የጮሁትን እና የዘመሩትን፣ መንግሰት ይህን ጉዳይ የማያውቅ ከሆነም እንዲገባው የጦመሩትን፣ የፖለቲካ ሙሰኝነት እንዲቀር እንቅልፉን አጥቶ ጋዜጣና መፅሄት በማዘጋጀት የሚተጉትን ጋዜጠኞችን እስር ቤት እያጎሩ እንዴት ታጋይ ዜጋ እንደሚፈራ አልታይህ አለኝ፡፡
ታጋይ ዜጋ እንዳይፈራ ዜጎችን አንገት እያስደፉ ፖለቲከኞች በሚፈነጩበት ሀገር ኪራይ ስብሳቢነት አንገቱን እንዴት እንደሚደፋ ማወቅ አይቻልም፡፡ ታጋዮችን አንገት አስደፍቶ ሌቦች ፖለቲከኞችን ቁርጠኞች ናቸው ማለት ፌዝ ነው፡፡
ታጋይ ዜጋ እናፍራ - ታጋይ የሆነ ዜጋ ጉቦ አይከፍልም በዚህ ጊዜ ኪራይ ስብሳቢነት ይደፈቃል ነው ብለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነገር ግን ጉቦ አልሰጥም የሚል ዜጋ ለማፍራት፣ ከፖለቲከና ዱላ የሚጠብቅ ሲቪል ማህበረሰብ፣ ጋዜጠኛ የግድ ይለናል፡፡ ፍርድ ቤት ያስፈልገናል፡፡ ያስቸገሩንን ወሰደን የምንገትርበት፡፡ የመርጊያ በቃናን ውሳኔ የሚያፀና ፍርድ ቤት አለን ብለን ጉቦ አንከፍልም በሉ ብለን እዝቡን ለጅብ አንሰጥም፡፡ መልዕክቴ ስርዓቱ ከፖለቲካ ሙሰና ከፀዳ እርገጠኛ ይሁኑ ሌሎች ሙስናዎች ተራ ናቸው፡፡ ለማነኛውም ይህ ወጣቶችን እየበላ ያለው የፖለቲካ ስርዓት ይገራልን፡፡
ቸር ወሬ ያሰማን!!!!! ዛሬ ደስ ብሎኛል ደስ ይበላችሁ!!!!