ግርማ
ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com
ሰሞኑን አቲቪ ደጋግሞ ያቀርበውን በ‹‹ቀለም አብዮት›› ዙሪያ የሚያውጠነጥነው
ዘጋቢ (ዶክመንተሪ) ፊልምን በጨረፍታም ቢሆን ያልተመለከተ አንባቢ መቼም እድለኛ መሆን አለበት፡፡ ስለምን ቢሉ? በብዙሀኑ ሕዝብ
‹ከሰዓት ውጪ እውነት አይናገርም› የሚባለው ይህ ጣቢያ፣ እንዲህ ሳይታክት ስለቀለም አብዮት ዘጋቢ ፊልም ማቅረቡን የተመለከተ ሰው
‹ምን ማለት ፈልገው ነው?› በሚል ማንሰላሰል፣ የጭብጡን ተቃራኒ ለመገመት መገደዱ አይቀርምና ነው፡፡ ዘጋቢ ፊልሙን ተአማኒነት
የሚያሳጣው ሌላው ገፊ-ምክንያት ደግሞ፣ የጉዳዩ ተንታኝ ሆነው ከቀረቡት ውስጥ ለታአማኒነት ቅርብ ያልሆነችው ሚሚ ስብሃቱ አንዷ
ሆና መቅረቧ ይመስለኛል፡፡ ይህ እንግዲህ ወጣቶቹ ተንታኞች
ልክ የሆነውንም ያልሆነውንም የግል ሃሳባቸውን ማቅረባቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የመንግስት ፖሊስን እንከን አልባ አድርገው በዘወርዋራ
ሊነግሩን ቢሞክሩም ልንቀበላቸው አንገደድም፡፡ መስማት፣ መስማማት አይደለምና፡፡
የዘጋቢ ፊልሙ ስህተት የሚጀምረው ሚዛናዊ ካለመሆኑ ላይ ነው፡፡ ይህም ሆኖ
እኔ የተረዳሁት አንድ ቁም ነገር ቢኖር ‹ኢህአዴግ በቀለም አብዮት ከስልጣን እውርዳለሁ› የሚል ከፍተኛ ሰጋት ውስጥ መውደቁን ነው፡፡
መቼም መነሾው ይህ ካልሆነ በቀር ‹በኢትዮጵያ የቀለም አብዮት ሊነሣ አይችለም› የሚል ዘጋቢ ፊልም በማዘጋጀት፣ አንድም ጉልበቱን
አያደክምም፤ ሁለትም የመንግስትን ሀብት አያባክንም ነበር፡፡
የሆነው ሆኖ በኢትዮጵያ ኢህአዴግ የሚፈራውን አብዮት ሊያመጡ የሚችሉ ነገሮች
አሉ ወይ? ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው ምላሽ በግሌ ‹‹አዎ!!!›› የሚል ይሆናል ብዬ አስባለሁ:: ይህን ያልኩበትን ምክንያት የፕሮግራሙ
ታዳሚ ወጣት “ምሁራን” እና “ጋዜጠኛ” ሚሚ ስብሃቱ ‹በኢትዮጵያ የቀለም አብዮት አይመጣም› ብለው ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ደጋፊ
ካደረጓቸው ውስጥ ጥቂት ነጥቦችን በማንሳት አስረዳለሁ፡፡ ‹‹ተንታኞቹ›› አብዮቱ ላለመነሳቱ ማሳያ ካደረጉት ዋና ዋና ነጥቦች ውስጥ፣
ብዙ የህብረተሰብ ክፍል ኑሮ እየተሻሻለ መምጣቱ፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ የዕድገቱ ተጠቃሚ ነን ብለው የሚያስቡ መሆናቸው፣
ወጣቱ ተስፋ ያለው መሆኑ፣ በኢትዮጵያ ከውጭ የሚጫን ዲሞክራሲ ቦታ ስለሌው… የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በእርግጥ ሚሚ ስብሃቱ የተጠቀሱት
የሥርዓቱ ‹‹ውጤታማነት›› ማሳያዎችና መልሳ በመናፍቃውያን ቋንቋ ‹‹በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ችግር ቢኖር እንኳን ዲሞክራሲያዊ ምርጫ
በየአምስት ዓመቱ ስለሚደረግ፣ ህዝቡ አብዮት ማካሄድ ሳያስፈልገው በምርጫ መሪዎችን ያስወግዳል›› ብላ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚንስትር
አባባል አስታውሳናለች፡፡ እነዚህን ነጥቦች በዋነኝነት መንግስት በፈረንጆቹ አቆጣጠር ሰኔ 2013 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት መሰረት
አድረጌ አብራራለሁ፡፡
‹‹የህብረተሰብ ኑሮ ተሻሽሏል›› የተባለውም ሆነ፣ ‹‹ሁሉም የህብረተሰብ
ክፍል ተጠቃሚ ነኝ ብሎ ያምናል›› የሚለው መደምደሚያ ከየት እንደመጣ ባላውቅም፤ እኛ በኢትዮጵያ የምንኖር ዜጎች ይህ መንግስት
ለጥቂቶች በምቾት ላይ ምቾት ሲጨምር፣ ለድሆች ግን የመከራ ኑሮ እየሆነባቸው እንደሆነ በየዕለቱ የምናየው እውነታ ነው፡፡ ይህን
መረዳት የሚፈልግ የአዲስ አበባ ነዋሪ ቦሌን ሳይሆን፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከቀድሞ አራተኛ ክፍለጦር ጀርባ ወይም ከለገሀር መሽዋለኪያ
ጀርባ ሴት እህቶቻችን በልቶ ለማደር ምን እየሰሩ እንደሆነ ማየት ይችላል፡፡ ይህ ግን ድሆች የነበሩ ጥቂቶች ፍርፋሪ አልወደቀላቸውም
እንደ ማለት አይደለም፡፡ ከላይ የጠቀስኩት የመንግስት ሪፖርት በግልፅ የሚያሳየው በከተማ ከሚኖሩ በዝቅተኛ የገቢ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በ1997 ዓ.ም (እ.ኤ.አ በ2005
ዓ.ም) ከነበራቸው ፍጆታ 1533፣ ከሰባት ዓመት በኋላ በ2003 ዓ.ም (እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም) ወደ 1279 ዝቅ ማለቱን ነው፡፡
ይህ እውነት በገጠርም ተመሳሳይ ነው፡፡ በተቃራኒው በከፍተኛ የገቢ ደረጃ ላይ የሚገኙት ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት ከፍተኛ እድገት
ያሳዩ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ወቅት በ1997 ዓ.ም ከነበሩበት 17141 ወደ 21962 እድገት አሳይተዋል፡፡ እነዚህ ቁጥሮች የሚነግሩን
ይህች ሀገር የድሆች ሳትሆን፣ የጥቂት ቅምጥሎች መቀማጠያ መሆኗን ነው፡፡ መቼም አብዮት የሚያስነሳው በድህነት አረንቋ የተዘፈቀው
ማሕበረሰብ እንጂ፣ ቅምጥሎቹ እንዳልሆኑ የኢቲቪ ዘጋቢም አልዘነጋውምና መዘርዘር አያስፈልግም፡፡
ይህን መከራከሪያ የሚያጠናክረው በዜጎች መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት በ1987
ዓ.ም ከነበረው 0.34 በ2003 ዓ.ም ወደ 0.37 ከፍ ብሎ የመገኘቱ እውነታ ነው፡፡ በእርግጥ በ1997 ዓ.ም ከፍቶ 0.44
ደርሶ ነበር፡፡ እናም ይህ ልዩነት በግድ ከ40 በመቶ መብለጥ አለበት ካልተባለ በስተቀር ብዙ ዜጎች ከ1987 ዓ.ም በከፋ የኑሮ
ደረጃ ላይ መሆናቸው ለቀለም አብዮት ገፊ መነሻ ነው ብለን እንድንወስድ እንገደዳለን፡፡ ሪፖርቱም በማጠቃለያው ላይ የገለፀው ሃሳብ
እንዲህ ይላል፡-
“… መረጃዎች በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር መቀነሱን ቢያሳዩም፣ ስር የሰደደ ድህነትን የሚያሳዩት ጠቋሚዎች
የሚያሳዩት ከ1997 ጀምሮ ሰር የሰደደ ድህነት በአሳሳቢ ደራጃ ያለመቀነሱን ሲሆን፤ ይልቁንም ጭማሪ አሳይቷል፡፡”
በተጨማሪ
የሪፖርቱ ማጠቃለያ አሁን ያለው የድህነት ደረጃ በፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው አመላክቶ ዘላቂነት ያለው ሁሉን ያካተተ እድገት መምጣት
ይኖርበታል ይላል፡፡ ይህ ልክ ቢሆንም ይህን ሊያመጣ የሚችል የፖለቲካ አመራር የሚሰጥ ሰርዓት የግድ ይላል ብለን መጨመር እንወዳለን፡፡
እናም የእነዚህ ሁሉ ጣጣ-ፈንጣጣ መፍትሄ ሚሚ እንደምተቀልደው አሁን ባለው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሰርዓት ብቻ ሳይሆን፣ አብዮት በማስነሳትም
ሊሆን እንደሚችል መገመት ብልህ መሆን ይመስለኛል፡፡
በመጨረሻም አንድ ኮሽታ ሲሰማ ይህ ጥያቄ ከውጭ የሚጫን ዲሞክራሲ፤ በተለይ
የኒዎ ሊብራል አመለካከት ያላቸው ምዕራባዊያን የሚያደርጉት ግፊት ነው የሚለው ነገር ዛሬም ድረስ ግራ እንዳጋባኝ ነው፡፡ እንዲሁም
የለውጥ አራማጆችን ‹‹ተላላኪዎች ናቸው›› ማለቱም ውሃ የሚቋጥር አይመስለም፡፡ የሚያሳዝነው ጉዳይ ደግሞ ይህን አይነት ይዘት ያለው
ትንተና የሰጡት ወጣቶች፣ አለቃቸው ‹‹ኒዎ ሊብራሊዝም›› የለም ማለታቸውን ከመስማታቸው በፊት ለዘጋቢ ፊልሙ የተቀረፁ መሆኑ ነው፡፡
አቶ ስብሃት ነጋ ‹‹ኒዎ ሊብራሊዝም የሚባል ነገር የለም›› በማለት በጋዜጣ መግለጫ ሲሰጡ ማንበብ፤ እናት ፓርቲያቸው ‹‹የኒዎ
ሊብራል አራማጆች›› እያለ የሚከሰው በሌለ ነገር መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ኩነቱን ምፀት የሚያደርገው ደግሞ ይህን ምስክርነት አዛውንቱ
ታጋይ በአደባባይ እየሰጡ ባለበት ወቅት፣ ጓዶቻቸው በኒዎ ሊብራል ሃሳብ አራማጆች የሚመራ የቀለም አብዮት ከዛሬ ነገ ይነሳል በሚል
ፍርሃት መርበድበዳቸውን በገሀድ መመልከታችን ነው፡፡
ሌላው በፊልሙ ውስጥ የተመለከትነው የእነዚህ ወጣቶች አስተዛዛቢ ድምዳሜ፣
በኒዎ ሊብራል ምዕራባዊያን ግፊት ሊመጣ ይችላል ከሚሉት አብዮት ውጭ ያሉት ትንታኔዎች የሚያሳዩት አብዮት ማስነሻ ዋና ምክንያቶች በሙሉ ቁሳዊ ናቸው የሚል ነው፡፡ በዚህም እንቢ ለነፃነቴ ብሎ
አደባባይ የሚወጣ ጎበዝ የለም እያሉን ነው፡፡ ሁሉንም በራሳቸው ሚዛን ነው መለካት የፈለጉት፡፡ እነሱ ጠቀም ያለ ደሞዝ ስለሚከፈላቸው
የተባሉትን ወይም የተቀበሉትን ሃሳብ በማራመዳቸው፣ ሌላውንም ወደ እነርሱ ደረጃ አውርደው ለሆዱ ብቻ የሚኖር አድርገው ያዩታል፡፡
ይህ መነፅር ወድቆም ቢሆን መሰበር አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ለነፃነት ሲባል፣ ከካድሬ መንግስት ለመገላገል እንቢ ማለት ግድ የሚሆንበት
ጊዜ እንደሚመጣ መጠራጠር የለብንም፡፡ ለምሳሌ በህጋዊ መንገድ ተፈርሞ ያገኙትን ካርታ፣ ጉቦ ካልሰጡት መክኖል የሚልን መሃንዲስ፣
ፍርድ ቤት ቢወስዱትም ‹መመሪያ ነው› ብሎ ቢቀልድበት፤ ይህን መብትዎን ለማስከበር መሃንዲሱን ከቢሮ ጎትቶ ለማውጣት መፈለግ ብሎም
ወደ ተግባር መሸጋገር ፍትህ የሚሰጥ ፈጣሪ ነው የሚል ሀይማኖተኛ ካልሆነ በስተቀር ለፍትህ ሲባል መወሰድ ያለበት እርምጃ ነው፡፡
ይህ ብቻ አይደለም መንግስት ቴሌን በቁጥጥሬ ስር አድርጌ አገልግሎት እሰጣለሁ ብሎ አግልግሎት ሳይሰጥ ሲቀር፤ ይባስ ብሎም አግልግሎት
ሳይሰጥ ገንዘብ ሲቆርጥብን፣ ይህን ቅሬታችንን ለማሳየት ሀገሪቱን ወደ ሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤተ-መንግስት ተሰብሰበን ሄደን፣
ሞባይላችንን በተከበረው ጊቢያቸው ውስጥ ብንወረውረው፣ ብሎም ዋናውን ሚኒስትር ደብረ ፅዮንን ከኃላፊነቱ አንስተው፣ ለቦታው ሊመጥን
የሚችል ሰው ካልሾሙልን ቤታችን አንሄድም ብንል ምንም ክፋት የለውም፡፡ ሁሉም ሰው በደል ሲደርስበት፣ በዳዩን ለመቅጣት መነሳት
ከጀመረ አብዮት ይመጣል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ገፅታው፣ የቀለም ይሁን የፍራፍሬ በኋላ የሚወሰን ይሆናል፡፡
እነዚህ ገፊ ጉዳዮች አብዮት የሚጠሩ ከሆነ፣ አብዮት እንዳይመጣ መፍትሄው
ደግሞ በውሸትና ፕሮፓጋንዳ የተደገፈ ዘጋቢ ፊልም አለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በዓለማችን የኢህአዴግ አምሳያ አምባገነኖች መውጫ
መንገድ ያበጁበት ልምድ አለ፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰላምና ልማት ኢንስቲትዩት ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በድጋሚ
ባቀረበው የውይይት መድረክ ላይ የተነሱትን ነጥቦች ገዢው አምባገነን ፓርቲ/መንግስት ከአብዮት ማምለጫ አቋራጭ አድርጎ ሊጠቀምበት
ይችላል፡፡ ሆኖም በእንዲህ አይነት ችግርና መከራ የተተበተቡ ሀገራት ባለቀለም ይሁን የፍራፍሬ አብዮት ሳያካሄዱ ወደ ዲሞክራሲና
ልማት ሊሸጋገሩ የሚችሉት በስልጣን ላይ ያሉት
ፓርቲዎችና የሚመሩት መንግስት ወሳኝ (Decisive) እርምጃዎችን ለመውሰድ ሲቆርጡ ነው፡፡ ወሳኝ ከሚባሉት እርምጃዎች ደግሞ ዋነኛው
አማራጭ አለን ለሚሉ ፓርቲዎች እኩል የመወዳደሪያ (Level Playing Field) ሁኔታን ማመቻቸት ያካትታል፡፡ ይህ ወሳኝ እርምጃ
ግን በፍፁም ኢህአዴግ “ለተቃዋሚ” ተብዮዎች ገንዘብ መስጠቱ ወይሞ የኦሮሚያ ተቃዋሚዎች ከኦህዴድ ገንዘብ መጠየቃቸው ጋር የሚገናኝ
ተደርጎ መወሰድ እንዳሌለበት ማስገንዘብ እፈልጋለሁ፡፡
በውይይት ፕሮግራሙ ላይ ኢህአዴግ ሊያምነው ያልፈለገው እየተንፈራገጠም ሊያስጨብጥ
የፈለገው መንግስታችን ዲሞክራሲያዊ ነው የሚለውን ጭብጥ ነው፡፡ ህዝቡም ወሳኝ ሚናውን እየተጫወተ ነው የሚልም አለበት፡፡ ሞሀመድ
ጋዳፊ፣ መንግስቱ ኃይለማሪያም፣ ሆስኒ ሙባረክ… ወዘተ ‹ዲሞክራሲያዊ ነኝ› እያሉ ነው ወደ መቃብራቸው የወረዱት፡፡ ኢህአዴግም አንድ
አምባገነን ያስወገደ አምባገነን መሆኑን ረስቶ፤ አምባገነን ስላስወገደ ዲሞክራት ሊሆን እንደማይችል መረዳት የተሳነው ይመስላል፡፡
ይሁንና ኢህአዴግም ከዚህ ስሁት መንገዱ ወጥቶ ወሳኝ እርምጃዎችን ለመውሰድ ቁርጥ ውሳኔ ላይ ቢደርስ፣ በምንም ምክንያት ስልጣንን
አሳልፎ ከመስጠት ጋር መያያዝ የሌለበት መሆኑን ተገንዝቦ ከቀለም አብዮት እና እርሱን ተከትሎ ከሚመጣ ጦስ ለማምለጥ ዛሬውኑ የቤት
ስራውን ቢጀምር ዞሮ ዞሮ ዋነኛው ተጠቃሚ ራሱ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት የለውጥ መንገደን ተከትሎ የሚመጣ
ጦስ በኢህአዴግ ብቻ ተገድቦ የሚቀር አይሆንም፤ ለሁላችንም የሚተርፍ ነው፡፡ እናም እነዚህ ወሳኝ እርምጃዎች ስለውጤት (ምርጫ ስለማሸነፍ
ወይም ለተቃዋሚ ስልጣን ስለመስጠት) አለመናገራቸውን አምኖ በመቀበል መደላድሉን መፍጠር አለበት፡፡ ውጤቱ የሚወሰነው ኢህአዴግ የሚወስዳቸውን
ወሳኝ እርምጃዎች መሰረት አድርጎ ህዝቡ በነፃነት ወጥቶ በሚሰጠው ድምፅ ነው፡፡
በአሁኑ ሰዓት ኢህአዴግ ከሚያቃዠው የቀለም አብዮት የሚገላግለውን መንገድ
መምረጥ የግድ ይለዋል፡፡ አማራጭ አለን የሚሉ ፓርቲዎችም እነዚህን ወሳኝ እርምጃዎች በክብር ለመቀበል መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡
በዚህ ዓይነት የሚመጣ ምንም ዓይነት ዝቅተኛ ውጤት ወደ ጎዳና ነውጥ ሳይሆን ችግርን መርምሮ ወደተሻለ ደረጃ ለመሸጋገር በጋራ ሀገራዊ
ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት መዘጋጀት ነው፡፡ ይህችን ሀገር ከሶስተኛ አብዮት ለመጠበቅ ለሁሉም ልብና ልቦና ይሰጠው እላለሁ፡፡
ቸር ይግጠመን!!!