Thursday, April 24, 2014

ለክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትር ሀይለማሪያም ያቀረብኩት ጥያቄዎች የሚከተሉት ሲሆኑ መልሶቹን ከኢቲቪ ጠብቁ



ሚያዚያ 15/ 2006
ክቡር ጠቅላይ ሚኒንስትር ከዚህ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ሳቀርብ በዚህ ሀገር ምንም ለውጥ አልተደረገም ከሚል ጨልመተኝነት ከመነሳት አለመሆኑን እንዲረዱልኝ እፈልጋለሁ፤
ሌላው በዚህ ሪፖርት ውስጥ እንደ ከዚህ ቀደሙ መሰረተ ቢስ የሆኑ ውንጀላዎች አማራጭ አለን ለምንል የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ባለማካተቱ እንደ በጎ ጅምር ወስጄ ማመስገን እፈልጋለሁ፤
ወደ ዝርዝር ጥያቄዎች እገባለሁ፤
1.   ሪፖርቱ የመጀመሪያ ፓራግራፍ “የትራንስፎርሜሽን አቅዳችን የተለጠጡ ግቦች የያዘ እና አፈፃፀሙም ከሞላ ጎደል በጥሩ መልኩ እየሄደ ያለ ሲሆን በዋናነት ለቀጣና ለሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርማሽን ዕቅድ ዘመን የተሻለ ልምድ የቀሰምንበት የህዝባችን እና የመንግስት የመፈፀም አቅም እየጎለበተ እንዲመጣ ያደረገ ሂደት ነው፡፡ ….. በቀሪው የትግበራ ጊዜም ርብርብ በማድረግ ያስቀመጥናቸውን ግቦች በማሳካት የህዝባችን ተጠቃሚነት የበለጠ እንደምናረጋግጥ እሙን ነው” ይላል፡፡ ከዚህ ውስጥ ሁለት ተቃራኒ ነገሮች ይታዩኛል አንደኛው ልምድ የተቀሰመበት ስለሆነ የተቀመጡት ግቦች በተሟላ ባይሳኩም ችግር የለም የሚል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ያስቀመጥናቸውን ግቦች እናሳካለን የሚል እንደምታ አለው፡፡ ጥያቄዬ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በዋና ዋና በሚባሉት መስኮች አሁንም ይሳካሉ ብለው ያምናሉ ወይስ ልምድ ተቀስሞበታል ብለን እንውሰድ?
ከዚህ ጋር በተያያዘ “ጥቂቶችን በተቀመጠው ግብ መሰረት አንደርስባቸውም ቢሆንም የተሻለ አፈፃፀም ደረጃ እንደምናደርሳቸው ለማየት ተችሎዋል” ሲባል ጥቂቶቹ ምን ምንድናቸው? ለምሳሌ
·         የባቡር መስመር ከታቀደው 2395 ስንት ኪሎ ሜትር ሰራ ይጀምራል?
·         ኢነርጂ ከታቀደው 10000 ሜጋ ዋት በእቅድ ዘመኑ መጨረሻ ሰንት ሜጋ ዋት ይኖረናል?
·         ከታቀዱት አሰር ሰኳር ፋብሪካዎች ስንቱ ማምረት ይጀምራሉ? (ከተቀመጠው ዕቅድ 2.2 ሚሊዮን ቶን ምን ያህል ያመርታሉ? ምን ያህሉ ወደ ውጭ ይላካል?)
·         የገጠር መንገድ ከተቀመጠው 71523 ኪሎ ሜትር ምን ያህሉ ይፈፀማል?
·         በጤና ዘርፍ ከታቀደው ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ምን ተሰፋ አለ?
ዝርዝሩን ለማሳጠር እነዚህ ጥቂቶች ናቸው ወይ? እነዚህ ሁሉ በጅምር ላይ ባሉበት ሁኔታ ልምድ ተቀስሞበታል ከሚል አልፎ እናሳካለን ብሎ ተሰፋ መሰጠት ተገቢ ነው ብለው ያምናሉ?
2.   ክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትር “ሪፖርቱ የአፈፃፀም ጉድለቶች መኖሩን ይጠቁማል”  ጥሩ ዕቅድ አቅዶ በአፈፃፀም ጉድለት ማሳየት መንግሰቶን ተጠያቂ ማድረግ የለበትም ብለው ያምናሉ? የመንግሰት ስልጣን መልቀቅና ተጠያቂነት ምን ግንኙነት አላቸው?
3.   በሀገራችን የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልፀዋል በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የስንዴ እና የሰኳር እጥረት እየተሰተዋለ ነው በዚህ ሁኔታ የዋጋ ንረቱ ሊያገረሽ የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ሰጋት አለ፡፡ የዕጥረቶቹ ምንጭ ምንድነው? ዋጋ ለማረጋጋት ከሚወሰደው እርምጃዎች አንዱ የስራ እድሎችን በማሰፋ የዜጎችን የገቢ አቅም ማሳደግ የሚል የተገለፀ አለ ይህ በተቃራኒው የዋጋ ንረት ይፈጥራል እንጂ ዋጋ አያረጋጋም፤ የሚፈጠረውን የዋጋ ንረት ለመቋቋም ተብሎ ቢስተካከል ጥሩ ነው፡፡
4.   በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ከተሳኩት ግቦች አንዱ የሀገር ውስጥ ቁጠበን ማሳደግ ነው፡፡ ድሃው ህዝብ በአሁኑ ወቅት በተለያየ መንገድ እየቆጠበ ቢሆንም በቁጠባ ልክ ተጠቃሚ ነው ብለው ያምናሉ? ወይስ ታሪክ ለመስራት የተዘጋጀ ትውልድ ነው የሚል ነው የቁጠባው ዋና መርዕ? ከቁጠባ አንዱ የሆነው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ቤት ለማግኘት የሚቆጥቡት ገንዘብ አንዱ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የመጨረሳ እድለ ቢስ መቼ ቤት ያገኛል ብለው ያስባሉ?
5.   የመንግሰት ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ከዚህ የሚገኘውን ገቢ በሪፖርቱ እንደተጠቀሰው “ ከብክነት በፀዳ እና በግልፅ ቅደም ተከተል ጥቅም ላይ ለማዋል የጀመርነውን ጥረት አጠናክረን መቀጠል ያለብን ይሆናል” ይላል፡፡ ነገር ግን የዋናው ኦዲተሩ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት ከፍተኛ የህዝብ ሀብት ከህግና መመሪያ ውጭ ለብክነት እንደተጋለጠ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ እንዴት ይመለከቱታል? ከዚህ አንፃር የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ተግባሩን ለመወጣት የሚፈልገውን የመንግሰት ድጋፍ ለማድረግ በእርሶ በኩል ቁርጠኝነት አለ ወይ?
6.   በሪፖርቱ ገፅ 10 “ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማት ወደ ማኑፋክቸሪንግ ሽግግር ተሰፋ ናቸው” ይላል፡፡ ተሰፋ ያላቸው የትኞቹ ናቸው? መንግሰት አሰፈላጊው ድጋፍ እያደረገ ነው የተባለው ድጋፍ ምንድነው? ኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ ሊገቡ ያሰቡ ወይም የሚችሉ ድጋፍ የተደረገላቸው ጥቃቅን እና አነሰተኛ ተቋሞች ካሉ ቢገልፁልን?
7.   የግልገል ጊቤ 3 በሚቀጥለው ዓመት ውሃ ስለማይሞላ ሰራ አይጀምርም የሚል ዜና በሚዲያ እየወጣ ሲሆን ሪፖርቱ ግን በሚቀጥለው ዓመት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል ይላል፡፡ በእርግጥ በሚቀጥለው ዓመት ሰራ ይጀምራል? የኢነርጂ አቅርቦታችን በዚህ ዓይነት አዝጋሚ ሁኔታ ሆኖ ማኑፋክቸሪንግ ሴክተሩ ምን ተሰፋ አድርጎ ሊመጣ ይችላል?
8.   ከሱዳን ጋር የጋራ ኮሚሽን የመሪዎች ጉባዔ በካርቱም ተዳሄዱ 13 የትብብር ስምምነቶች ተፈርመዋል፡፡ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ ለሱዳን መሬት ሰጥታለች የሚል ዘገባ ቢያወጡም ክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትሩም ይህ የማይታሰብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ እኛም ባይታሰብ እንመርጣለን፡፡ ለግልፅነት ሲባል ሰምምነቶቹ ዝርዝር ለምን ይፋ አይደረግም?
9.   ከኤርትራ በስተቀር ከጎረቤት ሀገሮች ጋር መልካም ግንኙነት እየተፈጠረ እንደሆነ በሪፖርቱ ተገልፆዋል፡፡ ኤርትራን በተለመለከት በግለሰቦችም ሆነ በቡድን ደረጃ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለመፍጠር ለሚያሰቡ ሰዎች የኢትዮጵያና የኤርትራን ህዝቦች ለጋራ ጥቅም በሚያሰልፍ መልኩ መንግሰቶ ምን ድጋፍ ሊያደርግ ይችላል?
10. ሰፋፊ እርሻን በሚመለከት ከሶሰት ሚሊዮን ሄክታር በላይ ዝግጅት ተደርጎ ብዙ መሄድ እንዳልተቻለ ይታወቃል፡፡ የተሰጡትም መሬቶች ቢሆን ከውዝግብ የፀዱ አይደለም፡፡ በመርዕ ደረጃ በድንበር አካባቢ ያሉ መሬቶችን ለምሳሌ በጋምቤላ አካባቢ ያሉ መሬቶች ለውጭ ዜጎች መስጥት ወደፊት ከሀገር ሉዓላዊነት አንፃር ያለው ሰጋት ተገምግሞ ያውቃል? ይህን ስጋት ለማስወገድ በድንበር አካባቢ መንግሰት የኢትዮጵያዊያን ተሳተፎ እንዲጎለብት ምን ድጋፍ ያደርጋል?
በመጨረሻም ሪፖርቱ ማካተት ሲገባው ያላካተተው ምን አልባትም ስለ አልተሰራ የሚሆነው የፖለቲካ ምዕዳሩን በማስፋት ቀጣይ ምርጫን በእኩል ውድድር የሚደረግበትን ሁኔታ ለመፍጠር መንግሰቶ አድሎዋዊ ሆኖ ቀጥሎዋል ብለን መውሰድ እንችላለን፡፡ ገዢው ፓርቲ አሁንም በቀጣይ ያለ ምንም ተቀናቃኝ ለመቀጠል የመንግሰትን ጡንቻ መጠቀሙን ይቀጥላል ብለን እንድንወስድ የሚያስገድድ ስለሆነ ይህ ላለመሆኑ የሚሰጡን ማብራሪያ ካለ ቢገልፁልን?
አመሰግናለሁ፡፡
ግርማ ሠይፉ ማሩ
 

No comments:

Post a Comment