ግርማ ሠይፉ ማሩ
እንዴት በክብር መኖር እንዳለብን
የሚያስረዳ መፅሐፍ እያነበብኩ በክብር መኖር እንዳንችል ከሚያደርጉን ነገሮች አንዱ ሙስና መሆኑ የሚገልፀው ክፍል ስደርስ ከወቅቱ
የሀገራችን ሁኔታ ጋር እየተመሳሰለ ቢያሰቸግረኝ ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡ ስለ ሙስና ሲነሣ ብዙ ሠዎች በፀረ ሙስና እና ሰነ ሙግባር
ኮሚሽን የሚገኙ ሃላፊዎችን ጨምሮ የሚያነሱት በእኛ ሀገር ያለው ከአፍሪካ ለምሣሌ ናይጄሪያና ኬኒያ በአውሮፓም ሆነ
በኤዥያ ካሉት ብዙ ሀገሮች ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል እይደለም፤
የሚሉ አሉ፡፡ የኮሚሽኑ ሰራተኞችም በተለያየ መድረክ ይህን ሲያነሱ መሰማት የተለመደ ሆኖዋል፡፡ በእኔ እምነት ይህ መስመር በፍፁም
ተገቢ እንዳልሆነ ተገንዝቦ በእንጭጩ መቀጨት ያለበት እንደሆነ መረዳት ከሁሉም የሚጠበቀው መሆኑን ነው፡፡ ለዚህ ፅሁፍ መነሻ ያደረኩት
መፅሃፍ ስለሙስና የሚገልጸው ክፍል እንዲህ ብሎ ይጀምራል፤
“አንድ ሰው ወደ ቤቱ መግቢያ መንገድ ላይ እሾሃማ ቁጥቋጦ እየበቀለ
አይቶ ዝም ይላል፣ ጎረቤቶቹም እባክህ ይህ ነገር ልክ አይደለምና ንቀለው ቢሉትም በእጄ ብሎ ከመንቀል ዛሬ ነገ ሲል ቀን ቀንን
እየወለደ ቁጥቋጦውም እያደገ ሄዶ በአንደኛው ቀን ባለቤቱን ክፉኛ አቆስሎ ክፉኛ ጎዳው፤ ጉዳት የደረሰበት የቁጥቋጦ ባለቤት ጉዳት
ከደረሰበት በኋላ ቁጥቋጦውን ለመንቀል ቢሞክር ከአቅሙ በላይ ሆነ፤ ብቻውን የማይችለው አሰቸጋሪ ሆነበት ይላል ”
ከዚህ ምሳሌ የምንረዳው ተገቢ ያልሆኑ ነገሮች በወቅቱ ካልተወገዱ፤
እየጠነከሩ መጥተው ከአቅም በላይ እንደሚሆኑ …. አንድ አንዶቹ እንደ ሙስና ያሉት ደግሞ እነርሱ ሲጠናከሩ እኛን እያዳከሙ መሆኑን
ችግሩን የከፋ እንደሚያደርገው ነው፡፡ ሙስና እንደ እሾሃማው ቁጥቋጦ በአንድ አንድ ምን አገባኝ በሚሉና ግዴለሽ ሰዎች ይተከልና
ከአቅም በላይ ሆኖ በመጠናከር የዜጎችን እልውና የሚፈታተን ይሆናል፡፡ በመጨረሻም ትክክል እስኪመስል ድረስ በቤታችን ቤት ሰርቶ
በሚስቶቻችን እና በልጆቻችን ፊት ቢዝንሰ እያልን እስክናወራው ድረስ ማዕረግ ያገኛል፡፡
ለፅሁፌ መነሻ የሆነኝ መፅሐፍ ሙስና “እድል ፊት ያዞረችባቸውን፣ ተከላካይ የሌላቸውን እንዲሁም ለችግር የተጋለጡትን
ለመዝረፍ የተነሣ ሠይጣናዊ ፍላጎት” በሚል ይገልፀዋል፡፡ ብዙ ሰዎች እንዴት እንዲህ ያሉ ሰዎችን ሙስና አግኝቶ ይዘርፋቸዋል
ሊሉ ይችላሉ፡፡ በሙስና የሚሳተፉትን ተዋንያን ስንመለከት ጎቦ በመስጠት ሀብታሞች፤ ጎቦ በመቀበል ደግሞ ሹሞች እንደሆኑ የምንታዘብ
ሰዎች ይህ ትርጉም ምን ፍች አለው? የሚል ጥያቄ ብናነሳ ልክ ባይሆንም ተገቢ ነው፡፡ የሙስና ክፋቱም የሚጀምረው ከዚህ ዓይነት
አሳሳች ባህሪው ነው፡፡
በሙስና የተሰማሩት ሰዎች በቀጥታ ተጎጂዎች አይደሉም፡፡ እነርሱማ በሙስና
ከተመሰረተ ሰርዓት ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ለጊዜውም ቢሆን፡፡ ጉቦ በመስጠት ጥቅም ያገኙ ሰዎች የሰጡትን ጉቦ ለሌላ ጊዜ ጉቦ እንዲተርፍ
አድርገው በብዙ እጥፍ ለማስመለስ ዕዳውን የሚያስተላልፉት ዕድል ፊት ወዳዞረችባቸው፣ ተከላካይ ለሌላቸው እንዲሁም ለችግር ለተጋለጡት
ምስኪን ዜጎች ላይ መሆኑ ነው፡፡ በሀገራችን የሚታየው የኑሮ ውድነት ተሸካሚው ማን እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ጎቦ ተቀባይም
ሆነ ሰጪው ይህ የኑሮ ውድነት የምንለው መከራ አይመለከታቸውም፡፡ እነርሱ የመከራው ምንጭ ናቸው፡፡ በገበያ ላይ የአቅርቦት እጥረት
እንዲፈጠር አጭበርባሪ ጉቦ ይሰጣል፤ ሹመኛው ለዚህ የሚመች መመሪያ ያወጣል፣ ሸማች በዓለም ላይ በሌለ ዋጋ እንዲገዛ ይገደዳል፡፡
የሙሰኞቹ መከራ ሰክረው መትፋትና በስካር እየነዱ መሞት ነው፡፡
በዲሞክራሲያዊ ሰርዓት በበለፀጉ ሀገሮች እነዚህን ምስኪኖች የሚጠብቅ
የህግ ስርዓት አለ፡፡ እንዲህ ዓይነት ድርጊት ሲፈፀም በህግ ሰርዓት መፍትሔ ይሰጣል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር ህጎች ደካማን
እና ድሃውን ለማጥቃት የሚውሉ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ ጎልበተኞች የህግን አቅም የመደምሰስ አቅም አላቸው፡፡ ስልክ ተደውሎ ፋይላቸው
የሚዘጋና ከእስር ይፈቱ የሚባሉ ሠዎች እንዳሉ ስናስብ ይህ ጉዳይ ሊገርመን አይችልም፡፡
በመግቢያዬ ላይ እንዳነሳሁት ሙስና ዓለማቀፋዊ የሆነ፣ ያለና የሚኖር
በሚል መንፈስ ከተውነው ልክ እንደ ካንስር ያለንን ማህበራዊ መሰተጋብር በልቶ ሀገርን የሚያጠፋ መሆኑን ተረድተን፣ ህግ እሰኪደርስልን
ድረስ የራሳችንን የመከላከያ መላ ማበጀት ያለብን ይመስለኛል፡፡ የእምነት ተቋማት አንዱ መንገድ ቢመስሉም በሀገራችን ሙስና ከመንግሰት
ሰርዓት አልፎ ወደ ቤተ ዕምነት ከገባ ቆይቶዋል፡፡ የማሪያም ቤተ ክርስቲያን እንዲሰራ የተመደበ ምዕመን እገረ መንገዱን የራሱን
ቤትም አዘንጦ ሰርቶ፤ ከየት አመጣህ ሲባል “ማሪያም ሰራቸው” እንዳለው
…. እየቆየን ስንሄድ ሁሉንም ገንዘብ ጠቅልሎ ወስዶ የማሪያምን ታቦት ጎዳና የሚያሳድር የቤተ ክርስቲያን አሰሪ ኮሚቴ
እንደማይኖረን እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡
እንደሚታወቀው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ “ዲሞክራሲያዊ መንግሰት” አለን
የሚል መንግሰታት “ሙሰኛ ዲሞክራሲ” ያላቸው ናቸው፡፡ የዚህ ዓየነቶቹ የተደራጁ ዘራፊዎች ሲሆኑ ህዝቡን በማሸበር ሀገር የሚገዙና
የሚዘርፉ ናቸው፡፡ መገለጫቸውም “መንግሰታችን ዜጎችን ለመርዳት ዝግጁ ነው” ይላሉ፡፡ የሚገርም ነው፡፡ መንግሰት ዜጎችን ሊያገለግል
የሚቀመጥ መሆኑ ቀርቶ ህዝብን ሊረዳ የተቀመጠ አድርገው ይመፃደቃሉ፡፡ ድሃ ህዝብ ሀብታም መንግስት በሚል የፃፍኩትን ልብ ይሏል፡፡
በቅርቡ ደግሞ ኢህአዴግ ካድሬዎችን ሲያስመርቅ አንድ “ተመራቂ” ያለው ለዚህ ሁነኛ ማስረጃ ይሆናል፡፡ ይህ ወጠጤ ካድሬ ያስተማሩትን ነው የተናገረው “እኛ ከፊት ሆነን ህዝቡን ከኋላ አሰከትለን
ልማታችንን እናፋጥናለን” ነው ያለው፡፡ እሱ ብሎ ከፊት መሪ - እንዴት አድርጎ እንደናቁን ነው የሚያሳየው፡፡ ይህን አባባል ለጦር
ሜዳ ውሎ ቢሆን አይለውም፡፡ ህዝቡን ከፊት አስቀድሞ ነበር ከኋላ ሊመራ የሚፈልገው፡፡ ዜጎች የዚህ ዓይነት ወጠጤ እንቢ ካላልን
… በመግቢያ ላይ ያነሳናት እሾሃማ ቁጥቋጦ በጊዜ ባለመነቀሏ ያሰከተለችውን ጉዳት እንደሚያስከትሉ መጠርጠር የለብንም፡፡ እኛ እየተዳከምን
እነርሱ እየፈረጠሙ ሲሄዱ፤ አቅም ሲዳከም የማይነቀሉ አረሞች ይሆናል፡፡ ወንጀል ከመስራትም አይመለሱም፡፡
በሙስና በተዘፈቀ ሰርዓት ውስጥ ህጎች በህዘብ ስም የግል/የቡድን ጥቅም
ለማረጋገጥ ይዘጋጃሉ፡፡ ይህንንም ለማስፈፀም ሙሰኞችና ብቃት የሌላቸው ሰዎች በቦታው ይመደባሉ፡፡ በዚህ መነሻም የህዝብ ሀብትና
ንብረት ይመዘበራል እንዲሁም የዜጎች መብት ይረገጣል፡፡ ከዚህ ሁሉ ሊታደገን ይገባ የነበረው የፍትሕ ሰርዓት በተቃራኒው እነዚህን
ህጎች ለመተግበር ይተጋል፡፡
የዚህ ሁሉ ውጤት እሴት የሌለው ማህበረሰብ መፍጠር ሲሆን በእንደዚህ
ያለ ማህበረስብ በሙስና የሚገኝ ሀብት የሚያስከብርና በህብረተስብ ዘንድ ከፍተኛ ቦታ የሚያሰጥ ይሆናል፡፡ ለጊዜውም ቢሆን ሙስና
የሀብት መንገድ ሲሆን ሀቀኝነት ትርጉም ያጣ ሊመስል ይችላል፡፡ በክብር መኖርም አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ ይህ እንዲሆን ሙስና ዓለማአቀፋዊ
ነው እያሉ የሚያስተኙን በዝተዋል እና ነቅተን ውጊያ መግጠሚያው ጊዜ አሁን ነው፡፡
የማህበራዊ እሴቶች መውረድ የሚጀምሩት ሙስና ተቀባይነት ሲያገኝ እና
ሙሰኞች በዚህ ምክንያት ምንም ዓይነት ማህበራዊ መድሎሆ እና መገለል የማይደረግባቸው ከሆነ ነው፡፡ ሙሰኞችን ከማህበራዊ ኑሮ ማግለልና
መፀየፍ ሰዎች እራሳቸውን ከሙስና ለማራቅ ከሚያግዙ መንገዶች እንዱ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ሲሾም ያልበላ ሲሻር
ይቆጨዋል፤ ገንጥሎ ወጣ፤ ከሀብቶች ጀርባ ወንጀል አለ፣ ወዘተ ተቀባይነት ያገኙ ይመስላሉ፡፡ ሁሉም እንደሚረዳው ሙስና በራሱ ግብ
አይደለም፣ ዋናው ግብ ሀብትና ስልጣን ብሎም ከዚህ የሚመነጨውን ጉልበትም ለመጨበጥ ነው፡፡ ይህም የፈለጉትን ወንጀል እንዲሰሩ ይገፋፋቸዋል፡፡
ሙስና እና ወንጀል የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ናቸው፡፡ በሀገራችን ሙስና የተጠረጠሩ ሰዎች ቤት የተገኙትን መሳሪያዎች ልብ ማለተ
የግድ ነው፡፡ ወፍ ሊያድኑበት አይደለም በቤታቸው መሳሪያ የሚያስቀምጡት፡፡ በሙስና ምክንያት የተፈፀሙ ወንጀሎችን ይዞ ለፍርድ ማቅረብ
በፍፁም አስቸጋሪ ነው፡፡ ሙሰኞችን የማስያዣውም ሆነ ለፍርድ ማቅረቢያውን መንገድ በገንዘብ ይገዙታል፣ በሃይል ይቆጣጠሩታል፡፡ ሙስና ከአሽባሪነት እኩል ወይም
የበለጠ አደጋ ያደርሳል ነገር ግን ሙስና የሚያደርስው ጉዳት በአሸባሪዎች እንደሚደርስ ጉዳት በግልፅ አይታይም፡፡ ለሚመለከተው ሁሉ
ተብሎ እንደተላከ ደብዳቤ ለሁሉም በተለይ ለምሰኪኑ ዜጋ በየቤቱ ይደርሳል፡፡
በአብዛኛው የሙስና ምንጭ የሚሆኑት ተግባራዊ ሊደረጉ የማይችሉ ህጎችና
በህጎች ውስጥ የሚቀመጡ ክፍተቶች ሲሆን ይህን የሚያደርጉትም ከዚህ ለመጠቀም የተዘጋጁ ሞራል የሌላቸው ሹመኞች ናቸው፡፡ በእርግጥ
በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ከፍተኛ የሰነ ምግባር ደራጃ ላይ የደረሱ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ ብልሹ ስነ ምግባር ያላቸውም መኖራቸውም ሀቅ
ነው፡፡ ልምዶች የሚያሳዩት ለሙስና የተጋለጡ ህጎች በበዙበት ሀገርም ቢሆን ከፍተኛ የሰነ ምግባር ደረጃን የሚተገብሩ ዜጎች ይገኛሉ፡፡
በተመሳሳይ ጠንካራ የህግ ስርዓት ባለባቸው ሀገሮችም ጥቂት ወረዳዎች መኖራቸው አይቀርም፡፡ ለማንኛውም አብዛኛው ሰው በህግ ሰርዓት
ማዕቀፍ ውስጥ እንደሚሆን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በጠንካራ ሰርዓት ውስጥ ሙሰኞች አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሲኖሩ፣ በሙስና በተዘፈቀ
ስርዓት ውስጥ ለክብራቸው የሚኖሩ ሰዎች መከራ ይገጥማቸዋል፡፡
ይህን ፅሁፍ በምሳሌ ብናሳርገው ጥሩ ነው፡፡ አንድ ንጉስ የሾመው ሚኒስትር
በሙስና መዘፈቁን ሰምቶ የማያዳግም መፍትሔ ብሎ ወደ ባህር ሄዶ የባህር ማዕበል የሚፈጥረውን እንቅስቃሴ እንዲቆጥር ይልከዋል፡፡
ይህ ልማደኛ ሙሰኛ እዛም ሄዶ ጎቦ ከጀልባ ቀዛፊዎች መቀበል ይጀምራል፡፡ ምክንያቱም መንግሰት የሰጠኝን የማዕበል እንቅስቃሴ የመቁጠር
ሃላፊነት በጀልባችሁ እንቅስቃሴ አወካችሁ በሚል ነው፡፡ ቃሊት የወረዱ ብዙ ሙሰኞች አሁንም ብዙ ነገሮችን በህገ ወጥ መንገድ እያደረጉ
እንዳለ በቅርቡ ቃሊቲ ጎራ ካለ ጓደኛችን ተረድቻለሁ፡፡
ቸር ይግጠመን!!!
No comments:
Post a Comment