Monday, July 28, 2014

የግል ሚዲያው “በፀረ ሽብር ህግ” ሊበላ ይሆን?

የመንግሰትን ቀጣይ እርምጃ የሚያሳዩ ተከታታይነት ያላቸው በግል ሚዲያዎች ላይ የሚደረጉ ዘመቻው ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ መልክቶች እየታዩ ነው፡፡ በቀጣይ ለሚቀርበው ዶክመንተሪ ተጋባዥ አንግዳ ሆኜ ለቆርጦ ቀጥሉ ኢቲቪ ቃለ ምልልስ እንደሰጣቸው ጥያቄዎቹ ደረስውኝ ተመልክቸዋለሁ፡፡ የጥያቄዎቹን ዝርዝር እንተወው እና ዓላማው ግን ባለፈው ከቀረበው ዘጋቢ ፊልም የተለየ ነገር የለውም፡፡ በነገራችን ላይ ባለፈው የቀረበውም ዘጋቢ ፊልም ላይ እንድሳተፍ ተጠይቄ እንደማይሆን ገልጨላቸው ነበር፡፡ ውሳኔዬ ትክክል መሆኑን ዘጋቢ ፊልሙን ካየሁ በኋላ ገብቶኛል፡፡ የዘጋቢ ፊልሞቹ ዋና ግብ “የኢህአዴግን አብዮታዊ ዲሞክራሲን መንገድ አምነው ያልገበሩ የግል የሚዲያ ተቋማትን ለማጥፋት ጥርጊያ መንገድ ማመቻቸት ነው፡፡” የግል ሚዲያውን ማጥፊያ መንገዶች ሁሉን አቀፍ ናቸው፡፡ በዋነኝነት ኤኮኖሚያዊ የሚባለው ሲሆን ይህም በምንም ሁኔታ ከመንግስት ወይም “ከልማታዊ ባለሀብቶች” ገንዘብ እንዳያገኙ ማድረግ ሲሆን ከአንባቢ የሚሰበሰቡትንም ገንዝብ ለእዕትመቱ ቀጣይነት እንዳይመች የሚቻለውን ቀዳዳ ሁሉ መዝጋት፤ ይህ የማይሳካ ቢሆን በአሰተዳደራዊ ዘርፍ እንዲወሰድ የተቀመጠው ፍርድ ቤትን በመጠቀም ጋዜጠኞችን ማስር ነው፡፡ ይህ በመጨረሻ የተቀመጠው አማራጭ የውጭ ሀይሎች የማይቀበሉትም ቢሆን መጠቀም ሲያስፈልግ መጠቀም ግድ ነው፡፡ ይህ ሃሳብ የኔ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ አይደለም፡፡ አቶ መለስ ዜናው አዘጋጅተውት ኢህአዴግ የሚባለው ፓርቲ እንደ መርዕ ተቀብሎት አሁን በአቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ የገዢነት ዘመንም የሚቀጥል የሟቹ ጠቅላይ ሚኒሰትር የራዕይ ክፍል ነው፡፡ ይህን ራዕይ አላስቀጥልም ሚዲያ በዓለም ተቀባይነት ባለው መስፈርት አራተኛ መንግሰት እንዲሆን አደርጋለሁ ይሉናል ብለን ብንጠብቅም ሊሆን የቻለ ነገር የለም፡፡
ለዚህም ማሳያው ባለፈው ሳምንት የቀረበው ዘጋቢ ፊልም ነው፡፡ ክሱም በቀጣይ ዝም ብሎ ተራ ክስ እንደማይሆን ምልክቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ዜጎችን አሸባሪ በማለት ክስ በመመስረት ታዋቂ የሆኑት ግለሰብ በዋና ተዋናኝነት የቀረቡበት ሲሆን ይህ ዘጋቢ ፊልምም ለቀጣይ ለሚያዘጋጁት ክስ መንደርደሪያ ሊሆናቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ በሽብርተኝነት የሚከሰሱ ሚዲያዎችና አምደኞች እንደሚኖሩ መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ እዚህ አካባቢ እስክንድር፣ ርዕዮት፣ ውብሸት ሰለባ የሆኑለት የግል ሚዲያ ተሳትፎና ሃሳብን የመግልፅ ነፃነት መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ ሀቃቢ ህጉ ከሰጡት አሰተያየት ሳይሆን ስንት ሰው ከሰው ወህኒ የወረወሩበትን አዋጅ ሰም በትክክል መጥራት አለመቻላቸው ነው፡፡ ለነገሩ “የሽብር ህጉ” እያሉ ሲጠሩት ትክክለኛ የተፃፈ ስሙ ባይሆንም እውነተኛ ምግባሩን ግን መግለፁን አልዘነጋሁትም፡፡ በተደጋጋሚ “የሽብር ህጉ” እያሉ ሲጠሩት አዘጋጁ ጋዜጠኛም አውቆ መሆን ይኖርበታል ይህን ክፍል ማስተካከል ያልቻለው፡፡ የውስጥ አርበኝነት ይሆን ብለን ታዝበን ከማለፍ አንባቢም ልብ ካላለው ለማስታወስ ብዬ ነው፡፡ ይህ “የሽብር” ያሉትን ህግ መቼ እንደምንገላገለው ባናውቅም ግብሩ ግን አሸባሪነት መሆኑ ተገልፆልናል፡፡
የብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ ቀደም ሲልም ከበላያቸው ለስሙ ኃለፊ የነበረ ቢሆንም በመሰሪያ ቤታቸው አድርጊ ፈጣሪ እንደ ነበሩ ታውቆ ያደረ ጉዳይ ነው፡፡ እርሳቸው ከሰጡት ውስጥ ድንቅ የሆነብኝ ግን 45 ሺ ታትሞ ሁለትና ሶሰት ሺ ነው የሚሸጠው የሚለው ክፍል ነው፡፡ ከዚህ ቀጣይ ያለው ነገር ግልፅ ነው፡፡ ክቡርነታቸው እንደነገሩን እነዚህ ጋዜጦች የሚደጉማቸው አንድ ኃይል አለ የሚል ነው፡፡ ይህ ሀይል ደግሞ ሀገሪቱን ለማተራመስ የሚሰራ መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ አምደኛ ሆኜ እንኳን አንድ መፅሄት በነፃ እንደማልወስድ እግረ መንገዴን ብነግራቸው ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ ቅዳሜ ሳልገዛ ካመለጠኝ እሁድ ከገበያ ላይ እንደማላገኝው ልባቸው ያውቀዋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለብሮድክሳት ባለስልጣኝ ሃላፊ ሁለት ሺ ኮፒ ለኢህአዴግ አባላትም እንደማይበቃ አልተረዱትም፡፡ በዚህ ክፍል አንባቢ እንዲረዳልኝ የምፈልገው አንድ እውነት ከሻቢያ፣ ከግብፅ፣ ከግንቦት ሰባት፣ ወይም አንድ የውጭ ሀይል የሚል ክስ ታሳቢ መደረጉ ነው፡፡ ክሱ ልክ መሆኑ አያስጨንቃቸውም ማንን ፈርተው ልክ እንዲሆን ይጨነቃሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ስንወያይ አንድ ወዳጄ ያለኝን ማንሳት ይጠቅማል፡፡ እነዚህ ሰዎች ቤተሰብ ዘመድ የሚባል የላቸውም ወይ? ይታዘበናል አይሉም ወይ? ነው ያለኝ፡፡ እኔም ደገምኩት አፈርኩ ለእናንተ ስል ብዬ፡፡
ለነገሩ እነዚህ ጋዜጦች በዚህን ያህል ዝቅተኛ ኮፒ የሚሸጡ ከሆነ መንግሰት የሚባል አካል ለምን ተሸበረ? ለምንስ ዘጋቢ ፊልም መስራ አሰፈለገው? ብለንም ልንጠይቅ እንገደዳለን፡፡ ሌላው ጥያቄ ደግሞ እነዚህ የውጭ የሚባሉ ሀይሎች የማይሸጥ ጋዜጣና መፅሔት ታትሞ ቢቀመጥ የሚያስቡተን ሀገር የመበተን ሴራ እንዴት ይሳካል ብለው ነው ድጋፋቸውን የሚቀጥሉት? ብለን ጠይቀን እንለፍ፡፡
ሌላው አስቂኝ ክስ ደግሞ “አሻጥረኛ አከፋፋዮች” የሚለው ነው፡፡ አቶ ሽመልስ ከማል አዲሰ ዘመን ከገበያ ልትወጣ የተቃረበችው በእነዚህ አሻጥረኛ አከፋፋዮች ሴራ እንደሆነ ምክር ቤት ቀርበው ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የኢዲስ ዘመንን ይዘት ማስተካከል ሲያቅታቸው የመጣላቸው ሰብብ አድርገን መውሰድ ያለብን አይመስለኝም፡፡ ዋናው ግብ አከፋፋዮችን በይፋ በማውገዝ ለቀጣይ እርምጃ ማዘጋጀት ነው፡፡ እነዚህ አከፋፋዮችን ማጥፋት ደግሞ የግል ሚዲያ ዕትመቶች ወደ ህዝብ እንዳይቀርብ ማድረጊያ ወሳኝ መንገድ ተብሎ እየታሰበ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የዚህ ክስ ተጋሪ የሆኑት አቶ እውነቱ በለጠ የኮሚኒኬሽን ሚኒሰቴር ዴህታ ናቸው፡፡ የአቶ ሽመልስን አሳበ በመጋራት በዘጋቢ ፊልሙ ላይ ተመሳሳይ ሃሳብ አንፀባርቀዋል፡፡ ሰለዚህ የመንግሰት ኮሚኒከሽን ሚኒሰትር መሰሪያ ቤት የግል ሚዲያውን የሚያሽከረክሩት ዋናኛ ሞተሮች “አሻጥረኛ አከፋፋዮች ናቸው የሚል ስምምነት ላይ መድረሱን መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ከዚያስ …… ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡
እነዚህ ከላይ የተቀሰኳቸው ሁለት የመንግሰት ተቋማት በግብ ከመስማማታቸው ውጭ የሚያቀርቡት ሃሳብ ግን ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል እንደሆነ አይረዱትም፡፡ በእነዚህ ሁለት የመንግሰት ተቋማት ውስጥ የግል ሚዲያውን በማጥፋት ዙሪያ ስምምነት አለ፤ ሁለቱም በየፈርጃቸው ግን ሊወስዱ ያሰቡት መንገድ የተለያየ እና የሚቃረን ነው፡፡ የብሮድካስት ባለስልጣን ዕትመቶቹ አይሸጡም፤ እነዚህ ሚዲያዎች በውጭ ሀይል ድጋፍና ዕርዳት ሀገር ለማፍረስ የሚሰሩት ይላል፡፡ የመንግሰት ኮምኒኬሽን መስሪያ ቤት ሃላፊዎች ደግሞ እነዚህ የግል ሚዲያዎች በከፍተኛ ደረጃ እንዲታተሙ እና እንዲሰራጩ የሚያደርጉት አከፋፋዮች ናቸው፡፡ የመንግሰት ልሳን እንዳይሽጥ በማድረግ ጭምር እያሉን ነው፡፡

 አቶ ብርሃኑ አዴሎ “በፀረ ሽብር አዋጅ” ዝግጅት ወቅት የነበራች የሞቀ እና ሰሜት የተሞላበት ተሳትፎ ታይቶ ለዘጋቢ ፊልም መቅረባቸው አንዱ ቢሆንም የሀቃቢ ህጉን በዘጋቢ ፊልም ላይ ያደረጉትን ንቁ ተሳትፎ ወስደን ጉዳዮን ስናየው በቀጣይ ክሱ “የሽብርተኝነት” እንደሚሆን መጠርጠር ብቻ ሳይሆን መዘጋጀትም ይኖርብናል፡፡ እግረ መንገዳቸው ግን አማረልኝ ብለው ያነሱትን የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ቋሚ አምደኛ መሆን ትክክልም ተገቢም እንዳልሆነ ለማስረዳት የሄዱበት ርቀት ነው፡፡ ዝም ብሎ ለማስታወስ ያህል በአዲስ ነገር ጋዜጣ የኢህአዴግ አባል የሆነ ቋሚ አምደኛ ነበር፡፡ ይህ ጋዜጣ ግን በመንግሰት ጥርስ ተነክሶበት ከገበያ የወጣ፤ ምርጥ ልጆቹም የተሰደዱበት ነው፡፡ በአቶ ብርሃኑ አዴሎ አመክንዮ ከሄድን ኢህአዴግና አዲሰ ነገር ግንኙነት ነበራችው ልንል ነው? እኔ በምፅፍበጽ ፋክት መፅሄት ላይ አባል የሆኑኩበትን ፓርቲ እያብጠለጠሉ ይፅፋሉ፤ በግሌ የፖለቲካ አቋሜንም ሆነ ማህበራዊ ብሎም ኢኮኖሚያዊ ምልከታዬን አሰፍራለሁ አቶ ብርሃኑን ጨምሮ ብዙ እንባቢዎች እንዳሉኝ ከሚደርሰኝ መረጃ አውቃለሁ፡፡ ይህ እኔ አባል የሆኑኩበት ፓርቲና ሚዲያውን ምን ያገናኛቸዋል፡፡ አንድ እውነት ግን አለ፡፡ ይህውም የህዝብ ሚዲያዎች በኢህአዴግ ታግተው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ እኩይ አስተሳሰብ ማረጋቢያ የሆኑ ሲሆን የተገፉት ደግሞ አማራጭ አሳቦችን ለማቅረብ አሁን የግል ሚዲያዎች ምቹ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ብዙ ሚሊዮን ተመልካች እንዳለው እናውቃለን፡፡ እድሉን ብናገኝ ከ20 ሺ ኮፒ በላይ በሳምንት ከማይታተሙ መፅሄቶች ይልቅ ኢቲቪን እንመርጥ ነበር፡፡ የተዘረፈው የህዝብ ሚዲያ ለህዝብ ጥቅም የሚውልበት ቀን እሰኪደርስ ግን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እንጠቀማለን፡፡ ይህ ምርጫ ሳይሆን ተገደን የገባንበት ነው፡፡ የግሉ ሚዲያ ለጊዜው የተገፉትን መወከሉ ስህተት የለበትም፡፡ ይልቁንም ሊበረታት የሚገባው ነው፡፡
ኢህአዴግ የህዝብ ውሳኔ የማይቀበል ፓርቲ እንደሆነ ዋነኛ ማሳያ ሊሆን የሚችለው አሁን በግል ሚዲያዎች ላይ የያዘው አቋም ነው፡፡ ያለምንም ጥርጥር አሁን በገበያ ላይ ያሉት ዕትመቶች በገበያ ላይ እንዲኖር የኑሮ ሸክሙን አቻችሎ በውድ ጋዜጣና መፅሄት የሚገዛ ህዝብ ነው፡፡ ይህ ህዝብ ደግሞ ለግል ሚዲያው የድጋፍ ድምፅ እየሰጠ መሆኑን መረዳት አለብን፡፡ የማይፈልገውን መፅሄት በገንዘቡ ገዝቶ ቤቱ የሚገባ ጅል አይደለም፡፡ አንዳንዱ መፅሄት ሲገዛ ለታሪክ ጭምር የሚቀመጥ ብሎ ነው፡፡ ኢህአዴግ በዚህ ጉልበቱ ይህን የህዝብ ድምፅ ሊያሸንፍለት የሚችል ሚዲያ ሊያዘጋጅ አልቻለም፡፡ ስለዚህ አሁን የያዘው መንገድ እነዚህን የህዝብ ድምፆች ለማፈን የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ነው፡፡ እነዚህ የህዝብ ድምፆች ደግሞ እንዲታፈኑ የተፈለገው ከቀጣይ ሁለት ሺ ሁለት ምርጫ ጋር ተዳምሮ ካደረበት ስጋት የሚመነጭ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ አሁን በቅርቡ የሚደረገው የደሞዝ ጭማሪ የግል ሚዲያዎችን ተገዢነት እንደሚጨምረው ይገመታል፡፡ ምክንያቱም ብዙ የመንግሰት ሰራተኞች ሊኖራቸው የሚፈልጉትን መፅሄት መግዛት ባለመቻላቸው በማንበብ ብቻ ተገድበው ነበር የሚል እምነት ስለአለኝ ነው፡፡
ቸር ይግጠመን



Monday, July 21, 2014

የተዓማኒነት ጉድለት ያለበት መንግሰት …..

መንግሰት የሚባለው ነገር ምን እንደሆነ ግራ ገብቶኋቸው ግራ የሚያጋቡን የመንግሰት ኃላፊዎች ያሉበት ሀገር ውስጥ ነው የምንገኘው፡፡ በሃላፊነታቸው ደረጃ የሚመጥን ማስተካከያ ለመውሰድ አቅምም ፍላጎትም የላቸውም፡፡ የተሸከሙት ሃላፊነት መንግሰት ብለው ለሚያስቡት አንድ ግዑዝ ነገር ለአገልጋይነት እንጂ፤ እነርሱ የመንግሰት አካል እንደሆኑ አይረዱትም፡፡ ይህን እንድንል የሚያደርገን መንግሰታችን ብለን በኩራት ግብር የምንከፍለው፤ መንግሰታችን ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም አንዲገቡ የሚያደርግልን ተቋም ነው፤ ሀገራችን በልማት በልፅጋ ዜጎች የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ስርዓት ነው፣ ይህ ሁሉ ሆኖም ችግር ቢገጥመን በገለልተኝነት በፍትህ ስርዓት ዳኝነት የምናገኝበት ነው፤ ብለን ማመን ቢቸግረን ነው፡፡ እነዚህ የመንግሰት ሃላፊ ተብዬዎች እነርሱ የተጣለባቸውን ኃላፊነት መወጣት ሲያቅታቸው እኛ በእንድ ወይም በሌላ መንገድ ችግራቸውን በጠቆምናቸው ወደ ትክክለኛ ደረጃ ማደግ ትተው እኛ ወደ እነርሱ እንድንወርድ፣ እንድንዋረድ፣ ለሆዳችን እንድናድር ወደ ገደል ይጎትቱናል፡፡
እውነቱን ለመናገር የኢትዮጵያ መንግሰት የሚባለውን አካል ለመደገፍ፤ በህግ የተሰጠውን ተግባር አንዲወጣ ማገዝ እንደ ዜጋ መብቴ ነው ብቻ ሳይሆን እንደ ግዴታም የምመለከተው ነው፡፡ አሁንም የማደርገው ነገር ሁሉ የማድረገው በዚሁ መንፈስ ግዴታዬን ለመወጣት ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ የሚደረግለትን ድጋፍ መቀበል የማይችል መንግሰት ሆኖዋል፣ ልክ ጥሩ ምግብ ሲያጎርሱት እንደሚያስመልሰው በከፍተኛ ደዌ እንደተያዘ በሽተኛ፣ ወይም ቤት እንዲጠብቅ ጠላት ሲመጣ እንዲያነቃን ያሳደግነው ውሻ በተቃራኒው ቤተኛውን በሙሉ መናከስ እንደጀመረ ውሻ ሆኖዋል፡፡ መንግስት ምክር አይሰማም ብቻ ሳይሆን በተቃራኒው ምክር የሚሰጡትን ለማጥፋት በከፍተኛ ትጋትና ከፍተኛ በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ነው እየተሰማን ያለው፡፡ ይህ ድርጊቱ በቀጣይ ዜጎች ከመካሪነት ወጥተው ሀገርን ወደማይጠቅም አውዳሚ አማራጭ መስመር እንዲገፉ እንደሚያደርግ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ እሰከ አሁን የተገፉትን ሳይጨምር፡፡
ዛሬ የመረጥኩትን ርዕስ እንድመርጥ ያደረገኝ መንግሰት ሰሞኑን እያሳየ ያለው ባሕሪ ነው፡፡ መቼም መንግሰት የሚገለፀው በመንግሰት ሃላፊዎች ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ መንግሰትን የሚመሩት ግለሰቦችም ሆኑ አካላት በመንግሰት ሃላፊነት ላይ የሚመድቧቸውን ሰዎች በህዝብ ፊት እንዲቀሉ ማድረግ ያለባቸው አይመስለኝም፡፡ እነዚህ ግለሰቦች እንዲቀሉ ሲያደርጉ የሚቀሉት አበረው መሆኑን እንዲሁም መንግስት የሚባለውን ሰርዓት የሚመራው አካል ጭምር ነው፡፡ እራሱ የሾመውን አካል ጭምር ማለት ነው፡፡
ይህን ሀሳብ ያነሳሁት አቶ ጌታቸው ረዳ የተባሉ የጠቅላይ ሚኒሰትሩ ቃል አቀባይ “መንግሰት አቶ አንዳርጋቸውን አልተረከበም” ብለው በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ለህዝብ ይፋ አደረጉ፡፡ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል በመግለጫው “የየመን መንግሰት እንዲይዛቸው አደረግን የዚያኑ ዕለት ተረከብናቸው” አለ፡፡ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉ ጅግንነቱን ለመግለፅ የመንግሰት ቃል አቀባዩን ማዋረድ ለምን አስፈለገ? ከዚህ ቀደም እንደልምድ ሆኖ የመንግሰት ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ከፍተኛ ሹም የሆኑት አቶ ሽመልስ ከማል ሆን ተብሎ በሚመስል ሁኔታ እንዲህ ዓይነት ተቃርኖ ያለበት አሰተያየት እንደሚሰጡ ይታወቃል፡፡ በዚህ የተነሳም እኝህን ከፍተኛ የመንግሰት ሹም የሚያምን ለማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ ግለሰቦችን የማዋረድ ድርጊት መንግሰትን የሚጠቅመው እንዳልሆነ ግን ግልፅ መሆን አለበት፡፡ የመንግሰትን አቋም እንዲነግሩን የተመደቡ ሰዎች “አይታመኑም” ማለት አጭር እና ግልፅ በሆነ ቋንቋ “መንግስት አይታመንም” ማለት ነው፡፡ የተዓማኒነት ጉድለት ያለበት መንግሰት ሲመራን ደስ አይለንም፤ ለዚህም ነው መንግስት አንዲታመን የምንወተውተው፡፡ ይህ የምንሰጠው አሰተያየት በምንም መልኩ የሀገርን ገፅታ ማበላሸት ሳይሆን፤ ሀገራቸንን ወክለው የሚዋሹትን የመንግሰት ሹማምንት በመምከር ለሀገር ገፅታ ግንባታ መትጋት ነው፡፡ ብንዋሽም ለሀገር ገፅ ግንባታ ሲባል ዝም በሉን ከሆነ መርዕ አልባነት ስለሚሆን መስማት ቢቻልም መስማማት አይቻልም፡፡ ያለምግባባታችን ምንጩ በመርዕ ጉዳይ ያለመስማማት ነው፡፡
የመንግስ ተዓማኒነት የሚጎዱ ብዙ ድርጊቶች ማንሳት ቢቻልም፤ አሁን ደግሞ የፓርቲያችን አባል የሆነውን ሀብታሙ አያሌውን በምንም ምክንያት ቢይዙት መንግሰትን ለመማን በፍፁም ዝግጁ አይደለንም፡፡ መንግሰት ሁሌም እንደሚለው ክምር ማስረጃ አይደለም አንድ ገፅ ማስረጃ ያቀርባል ብለን አንጠብቅም፡፡ ይህን ለማለት የሚያሰደፍር በቂ ተሞክሮ አለን፡፡ ከብዞዎቹ አንዱ አንዱዓለም አራጌን ለእስር ያበቁበት መረጃ ነው፡፡ በህይወቴ ከደነገጥኩበት ቀን አንዱ አንዱዓለም አራጌ የታሳረ ዕለት ነው፡፡ ምከንያቱም የቀረበበት ክስ “ከግንቦት ሰባት” ከሚባለው “ሁሉን አቀፍ” የሚበል የትግል ስልት ከሚከተል በውጭ ሀገር ከሚገኝ ፓርቲ ጋር ግንኙነት አለው የሚል ስለ ነበር ነው፡፡ በወቅቱ አንዱዓለም አራጌ ላይ የሚያቀርቡትን መረጃዎች በጉጉት ነበር ስጠብቅ የነበረው፡፡ ነገር ግን አንድም ማስረጃ ሳይቀርብበት፣ አዳፍኔ ምስክሮችም እንደሰለጠኑት አሟልተው ሳይመሰክሩ የሰላማዊ ትግል ጓዳችን “በአሸባሪነት” ጥፋተኛ ነው ተብሎ እድሜ ልክ ተፈረደበት፡፡ ከዚያን ቀን ወዲህ ማንም ላይ ማስረጃ አለኝ ቢሉ ለማመን እቸገራለሁ፡፡ መንግሰት በሚፈፅማቻው ተግባራት ምክንያት ተዓማኒነቱን እየጎዳው ይገኛል፡፡ ቀበሮ መጣ እንደሚለው ውሽታም እረኛ ማለት ነው፡፡
በእኔ እምነት ከሳሾቹም ሆነ ፈራጆቹ የሰጡት ውሳኔ “ክምር ማስረጃ” አለን ያሉትን የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቃል ለማክበርና ለማስደሰት እንደነበር መጠራጠር አያሰፈልግም፡፡ እርሳቸውም ደስታቸውን ሳያጣጥሙት በተፈጥሮ ህግ ተለይተውናል፡፡ የቀረበውን ክምር ማስረጃ ታሪክ መዝግቦ ይዞታል ከሳሹችም ሆኑ ፈራጅች በታሪክ ፍርድ ፊት እንደሚቆሙበት ቅንጣት ያህል ጥርጥር የለኝም፡፡ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ አሁን በምንፅፈው፣ በምንናገረውም ሆነ ከዚህ በፊት በያዝነው አቋም ሁላችንም የታሪኩ አካል ነን፡፡ ሊፈርድብን ወይም ሊፈርድልን፡፡
የዛሬ ዓመት አካባቢ በደሴ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ለማስተባበር ከተመደበ ቡድን ጋር ተንቀሳቅሼ ነበር፡፡ ወቅቱ ደግሞ አንድ የሙስሊም የሀይማኖት አባት የተገደሉበት ነበር፡፡ በወቅቱ በደሴ ከተማ የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር አብዛኛው የከተማ ነዋሪ “የሀይማኖት አባቱን የገደላች መንግሰት ነው” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ በሰልፍ ላይ የተገኙ ሰዎችም “እየገደሉ ገደሉ አሉን” የሚል መፈክር በከፍተኛ ሰሜት እያሰሙ ቅሬታቸውን ሲገልፁ ነበር፡፡ በግሌ መንግሰት በዚህ ደረጃ ወርዶ በግለሰቦች ግድያ መጠርጠሩ ምቾት አልሰጠኝም፡፡ በተለያየ አጋጣሚ ያገኘኋቸውን የመንግሰት ሹሞች በዚህ ደረጃ መንግሰት መጠርጠሩ እንደሚያሳዝን አሁንም ቢሆን መስራት ያለባቸው የተቃዋሚዎች ስራ ነው እያሉ በአላስፈላጊ ፕሮፓጋንዳ ከሚጠመዱ፤ መንግሰትን በዚህ ደረጃ ለመጠርጠር ገፊ የሆነው ችግር ምንጭ ምን እንደሆነ እንዲመረምሩ አሳቤን አካፍያቸው ነበር፡፡ ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ  እኔንም ከአሽባሪና አክራሪነት ጋር ደምረው ልወደድ ባይ ጋዜጠኞች ዶክመንተሪ ፊልም ሰሩብኝ፡፡ ሀይ የሚል አልነበረውም ይልቁንም በተለያየ አጋጣሚ የማገኛቸው ኢህዴጎች የኢቲቪን ድራማ እያዩ እኔን መኮንን ነው የያዙት፡፡ እኔን በዚህ ደረጃ ከመጠርጠር እራሳቸውን መጠርጠር የሚቀላቸው ይመስለኛል፡፡ የእኔ ጥያቄ መንግስት ለምን በዚህ ደረጃ ይጠረጠራል? የመንግሰት ተዓማኒነት መጎደልን ለማሳየት ከዚህ የተሻለ ማስረጃ ማቅረብ ይከብዳል፡፡ እንዴት መንግሰት በግለሰብ ግድያ ይጠረጠራል? ሹሞቹ ግን ይህ አላሳፈራቸውም ቅድሚያ የሰጡት ለፕሮፓጋንዳው ነው፡፡
የተለያዩ ሀገሮቸን ለመጎብኝት እድል አጋጥሞኛል መንግስት ሊገድልህ፤ ሊያስገድልህ፤ በማጅራት መቺ ሊያስመታህ ይችላል ተብሎ የሚታመንባቸው ሀገሮች እጅግ ጥቂቶች ናቸው፡፡ የወደቁ ወይም በመውደቅ ላይ ያሉ መንግሰታት ናቸው፡፡ የሀገሬ መንግሰት እንዲህ እንዲሆን አልፈልግም፡፡ እንዲህ ዓይነት ግምት የሚሰጡ ሪፖርቶች ሲወጡ መንግትን ስለማልደግፍ ጮቤ አልረግጥም፡፡ ይልቁንም አዝናለሁ፡፡ በቅርቡ አንዲት ሴት መኖሪያ ቤቴ ድረስ መጥታ በከፍተኛ የመንግሰት ሹም ፆታዊ በደል እንደደረሰባት ነገረችኝ፡፡ ለነገሩ ጉዳዩ የግል ግንኙነት ከመሆኑ አንፃር ብዙም ፍርድ ቤት የሚያስኬድ ባሕሪ እንዳለው ባይገባኝም፤ የተነፈገ መብት አለኝ ካለች ፍርድ ቤት እንድትሄድ ነገርኳት፡፡ “ፍርድ ቤት ብሄድም ትርጉም የለውም፤ ይህን ማድረጌን ከሰሙ ያስገድሉኛል፤ አንተ በደንብ አታውቃቸውም አለቸኝ፡፡” ደነገጥኩ!! እውነት ነው ከሷ በላይ አላውቃቸውም፤ በግልፅ አንሶላ ተጋፋ ውስኪ ተራጭታ የሚያደርጉትን ታውቃለች፡፡ በመጨረሻም ከእኔ የምትፈልገው ነገር እኔ ላድርግላት እንደማልችል፤ እኔም ከመስመር አልፎዋል ያሉ ቀን ሊገድሉኝ፣ ሊያስገድሉኝ ካዘኑልኝ ደግሞ እስር ቤት ሊወረውሩኝ እንደሚችሉ አምኜ በድፍረት እንደምንቀሳቀስ ነገርኳት፡፡ ይህን ታሪክ ያነሳሁት መንግስት ከለላ የሚሰጠን ጠባቂያችን ሳይሆን ሊገድለን፣ አደጋ ሊያደርስብን የሚችል ነው ብለን ተዓማኒነት እንድንነፍገው ለምን ሆነ? ብዬ ለመጠየቅ ነው፡፡ የመንግሰት ተቃዋሚ ሆኖ አይደለም፤ መንግሰትን ከሚወክሉት ሹሞች ጋር ሲዳሩ መክረም እንደ ውለታ ተቆጥሮ ዋስትና አይሆንም፡፡ የፈለጉ ቀን ከህግ ሰርዓት ውጭ ማሰገደል የሚችሉ ናቸው፡፡ መንግሰትን የሚወክሉት ሹሞች፡፡ ግን ለምን አንዲህ ሆነ?
መንግሰት ለሚያደርጋቸው ነገሮች፣ ለሚወሰደው እርምጃ ተገማችነት አለመኖር ለተጠርጣሪነት እና ተዓማኒነት ጉድለት እንደሚያጋልጠው እርግጥ ነው፡፡ ይህን መከላከል ሲገባ ደግሞ ይህን የሚያጠናክሩ ድርጊቶችን በተደጋጋሚ ማየት መንግሰት ተዓማኒ አይደለም ብቻ አይደለም አንድ አንድ ሰዎች በድፍረት እንደሚሉት “መንግሰታዊ ውንብድና” ነው፡፡ ያሰገድሉናል የሚባል አቋም ሲያዝ ፍርድ ቤት አቅርበው አንዳለሆነ ግልፅ ነው፡፡ በአህአዴግ መንግሰት ከሁለት ሰዎች በላይ በህግ ውሳኔ በሞት የተቀጣ እንደሌለ እናውቃለን፡፡
ይህንን “የመንግሰትን ተዓማኒነት ጉድለት” የሚመለከት ፅሁፍ እያዘጋጀሁ ሳለ የግሌ አስተያየት እንዳይሆን የፌስ ቡክ ጓደኞቼ አስተያየት እንዲያዋጡ መጠየቅ ፈለጉህ፡፡ እንዲህም ብዬ በፌስ ቡክ ላይ ለጠፍኩ “እባካችሁ የመንግሰትን ተዓማኒነት ጉድለት የሚያሳይ አሳብ አዋጡ!! ከሌላችሁ በእውሽት ላይ የተመሰረተ ክስ ወይም ጠቅላላ አስተያየት ተቀባይነት የለውም፡፡ አመሰግናለሁ ……” የሚል ነበር፡፡ ተቀባይነት የሌላቸው አጠቃላይ አሰተያየቶችን ጨምሮ እጅግ ብዙ አስተያየት በአጭር ጊዜ ቀረበልኝ፡፡ በመሰረታዊነት ህገ መንግስቱን እና ህገ መንግሰታዊ ሰርዓቱን እንዲያከብሩ የሚጠይቅ ሲሆን፤ በግልፅ ምሳሌ ተደርገው ከተጠቀሱት ዋና ዋናዎቹ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ማግስት ባድመን አሰመልክቶ የተሰጠው መግለጫ፣ ዜጎች መንግሰት ላይ እምነት ቢኖራቸው በሚሊዮን ለምን ይሰደዳሉ?፣ ኢቲቪን ተመልከት፣ ፍርድ ቤቶች ምን እየሰሩ ነው፣ የደህንነት ተቋም ለማን ነው የሚሰራው? ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ነው ብለህ ታምናለህ? የሚሉና ከነአካቴው መንግሰት አለወይ? የሚሉት ይገኙበታል፡፡ አሰተያየቶቹ ሁሉንም የመንግስት አካላት የዳሰሱ ናቸው፡፡ መንግሰት ዜጎች በዚህ ደረጃ ተዓማኒነት እንዲነሱት ለምን ይተጋል ብለን መጠየቅ የለብንም ትላላችሁ?
ምኞቴ መንግሰታቸን ብለን የምናከብረው መንግሰት አንዲኖረ ነው፡፡ ግልፅ ነው በአሁኑ ስዓት የለንም እያልኩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሚገለፀው መንግሰትን ወክለው በሚታዩት ሹማምንቶች ባህሪና ተግባር ነው፡፡ የሀገርን ገፅታ ለመግንባት ከሊቅ እስከ ደቂቅ ኃላፊነት እንዳለብን እና ግዴታችን እንደሆነ ባምንም ይህን ከፍተኛ ኃላፊነት ግን ያለምንም ማወላወል በተግባር ሊያውል የሚገባው እና ሞዴል ሊሆነን የሚገባው መንግሰት ነው፡፡ መንግሰት ደግሞ በኃላፊዎቹ ይወከላል፡፡ የእኛ ተግባር ትክክለኛ ስራ ሲሰሩ ሞዴሎቻችን አድርገን መውስድና ትክክለኛ ተግባራቸውን ማስፋት፤ ካልሆነ ደግሞ ያልሆኑትን ናቸው ብለን መቀለድ ሳይሆን አትመጥኑንም ብለን መንገር ነው፡፡ ጆሮ ያለው ይስማ!!!!!

ቸር ይግጠመን

Sunday, July 13, 2014

ምንም ቢሆን ኢኮኖሚያችን በሁለት አሃዝ ማደጉ ይቀጥላል!!!

“የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት” በያዘነው ሳምንት መጀመሪያ በህግ የተፈቀደለትን ሰማኒያ ከመቶ ጊዜ አጠናቆ ተዘግቷል፡፡ ስራውን እንጂ ግዜውን አላልኩም፡፡ በቀረው 20 ከመቶ በሚሆነው ጊዜ ባለፉት አራት ዓመታት ያከናወናቸውን ዓይነት ተመሳሳይ ተግባራት ያከናውናል ብሎ መጠበቅ አይቻልም፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት ኢህአዴግ፣ በገዢነት በማንኛውም መንገድ ሊቀጥል እንደሚችል እርግጠኛ ቢሆንም፤ አንዳንድ የምክር ቤት አባላት ግን መቀጠል አለመቀጠላቸውን የሚያረጋግጡበት ግልፅ የሆነ አሰራር ባለመኖሩ ስጋት ላይ እንደሚወድቁ ስለማውቅ ነው፡፡ ይህ ስጋት ካሁኑ መታየት ጀምሯል፡፡ ስለዚህ አብዛኞቹ የምክር ቤት አባላት፣ አሁን በቀጣይ ዕጣ-ፋንታቸው ላይ የሚወሰነውን የሚጠባበቁበት እና በግላቸውም ቢሆን አማራጭ የሚመለከቱበት ጊዜ ነው፡፡
እነዚሁ የምክር ቤት አባላት የአራተኛውን ዓመት ጊዜ ለማጠናቀቂያ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቀረቧቸው ከደርዘን የሚበልጡ ጥያቄዎች መካከል፤ ገዢው ፓርቲ ያቀደውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማሳካት ክፍተት እንዳለበት ማሳለቁ አያቋርጥም፡፡ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡትም መልስ ‹‹ያሉትን ችግሮች ተቀብሎ ቢሆንም›› በሚል ማገናኛ ቃል በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ መሰረት ዕድገት አስመዝግበናል የሚል ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ አንድ አንድ ነጥቦችን አንስተን እንመልከት፡፡
መንግስት፣ በዘመቻ ከሚሰራቸው የኮንስትራክሽን እና ሌሎች ግንባታዎች ጋር በተያያዘ እየተፈጠሩ ያሉ እድሎች ወደፊት ዘላቂ ሊሆኑ የሚችሉት፤ በምርቱ ዘርፍ የግል ባለሀብቱ ሲሳተፍ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ ዘርፍ ግን በሚፈለገው መጠን የስራ እድል ሊፈጥር በሚችል ሁኔታ እየተስፋፋ እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቀብለውታል፡፡ ይህም ቢሆን የሀገራችን ኢኮኖሚ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሰረት በሁለት አሃዝ ማደጉን ግን አላቋረጠም፡፡ የምርቱ ዘርፍ የስራ እድል ቢፈጥርም ባይፈጥርም፣ ኢኮኖሚያችን ማደጉን ለነገሩ ኢትዮጵያዊያን አስማተኞች ሳንሆን አንቀርም፡፡ ስራ ቢኖረንም ባይኖረንም በልተን/ቀምሰን ማደርና ጠዋት ለስራ-ፈትነት አርፍዶ መንቃት የለመድን ይመስለኛል፡፡
መንግስት የደሞዝ ጭማሪ ማድረጉን ተከትሎ፤ ስግብግብ ነጋዴዎች ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንደማይገባቸው በተደጋጋሚ ከመገለፁ በተጨማሪ አሁን የሚመጣ የዋጋ ጭማሪ ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት እንደሌለው እንድናምን እየተነገረን ነው፡፡ የኢኮኖሚክስ “ሀሁ” እንደሚነግረን ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ማለት የአቅርቦትና ፍላጎት ያለመጣጣም ሲሆን፣ የኢኮኖሚክሱ “አቦጊዳ” ደግሞ እነዚህ ሁለቱን የሚያሳልጠው የገንዘብ አቅርቦት ተመጣጣኝ አለመሆን እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ክፍተት መኖሩን አምነው፣ ይህ ክፍተት የሚዘጋው፣ የበለጠ የከፈለ ያገኛል በሚለው መርህ መሆኑን እርሱት እያሉን ነው፡፡ ይህ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ካልሆነ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩም ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክንያት ለምን ሌላ እንደሚፈልጉ ለእኔ ግልፅ አይደለም፡፡ የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር መንግስት በመሰረታዊ ዕቃዎች ላይ  ድጎማ በማድረግ ዋጋ እንደሚያረጋጋ የነገሩን፣ በቂ አቅርቦት በሌለበት ድጎማ ዋጋ እንደማያረጋጋ ለማወቅ የኢኮኖሚ ሊቅ መሆን አይጠይቅም፡፡ በዚህ ጊዜ የሚኖረው በኮታ ማደል ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለጥቁር ገበያ እና ለከፍተኛ ዋጋ ንረት መንገድ ይከፍታል፡፡
ለማንኛውም በደሞዝ ጭማሪ ምክንያት በሚፈጠር የዋጋ ንረት ሃላፊነቱን የሚወስዱት “ጥቂት ስግብግብ ነጋዴዎች” ስለሆኑ፤ እነሱን ለመታገል በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቀመጠው አቅጣጫ “ተደራጁ” የሚል ነው፡፡ በእኔ እምነት የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር፣ አሁን ባለው ሁኔታ የሚያዋጣ ስላልሆነ በየመስሪያ ቤታችን የዋጋ ንረትን በጋራ ለመቆጣጠር መደራጀት ሊኖርብን ነው፡፡ ይህን ኃላፊነት ግን ለምን አሁን ያለው የአንድ ለአምስት አደረጃጀት አይረከበውም? ይህ አደረጃጀት፤ አንደኛ መንግስት በትክክል መደጎሙን ይከታተላል፤ እግረ-መንገዱንም ከ“ስግብግብ ነጋዴዎች” ጋር ግብይት እንዳናካሂድ አድማ ለማድረግ ይጠቅመናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ “በነፃ ገበያ” ስርዓት ዋጋ ጨመርክ ተብሎ ማሰር ስለማይቻል ነው አድማ ማድረግን ያመጣሁት እንጂ አብዮት ለመቀስቀስ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ የሚያስጠይቀው በሸማቾች ህግ ሳይሆን በፀረ-ሽብር ህግ ነው፡፡
መንግስት፣ በዕቅድ ደረጃ ስምንት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከውጭ ንግድ ለማግኘት አቅዶ ሊሳካለት አልቻለም፡፡ ለዚህም ዋና ዋና የተባሉት እና በመንግስትም እንደችግር ከተጠቀሱት ውስጥ ቡና ማልማት ከሚችለው መሬት አንፃር ከሃምሳ በመቶ በታች፣ ከምርታማነት አንፃር ገና አንድ ሶሰተኛው አካባቢ ላይ መሆናችን ነው፡፡ በዕቅድ ዘመኑ የቅባት እህሎች ለማምረት ወደ ተግባር እንደሚገቡ የታሰቡት ክልሎች ወደ ስራ ያለመግባታቸው፤ የገቡት የአማራና የትግራይ ክልልም ቢሆኑ፣ ምርታማነታቸው ከሃምሳ በመቶ በታች መሆናቸው ታውቋል፡፡ ከላይ እንደገለፅኩት የምርት ዘርፉ ገና ያልተጀመረ መሆኑ፣ በማዕድን ዘርፍ የወርቅ ዋጋ መቀነስ ብቻ ሳይሆን በባህላዊ አምራቾች ሊገኝ የታሰበው ያለመሳካቱ፣ እንዲሁም እጅግ ብዛት ያላቸው የንግድ ሰርዓት ማነቆዎች በመኖራቸው ምክንያት ዕቅዱ አልተሳካም፡፡ ይህን የሚያህል ሀገራዊ ዕቅድ ባልተሳካበት ሁኔታ፣ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለማሳካት አንድ መድህን ግን አልጠፋም፡፡ ይኽውም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለዘመዶቻቸው የላኩት ገንዘብ ከዕቅድ በላይ ተሳክቷል፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን የሀገሪቱ አጠቃላይ እድገት በሁለት አሃዝ ከማደግ የከለከለው አንድም ምድራዊ ሀይል አልተገኝም፡፡ የውጭ ምንዛሬ ግኝታችን ከስልሣ በመቶ በታች ቢሆንም እድገታችን ግን ካቀድነው ፍንክች አላለም፡፡
የአንድ ሀገር እድገት የሚለካው ዜጎች በትምህርት በሚያገኙት ክህሎት እና ይህንንም ክህሎት እሴት ለመጨመር ሲያውሉት እንደሆነ ይታመናል፡፡ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ግብ ከትግራይ ክልል በስተቀር ያለመሳካቱ ጉዳቱን ያዩበት አቅጣጫ ምቾት ሰጥቶኛል፡፡ ልጆች ትምህርት ቤት በሚሄዱበት ወቅት ከትምህርት ገበታ ከተገለሉ ለጉልበት ብዝበዛ የሚጋለጡበት ሁኔታ እንዳለ አስረድተውናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ያለ እድሜ ጋብቻ እና ሌሎች ማህበራዊ ችግሮች ውስጥ የሚወድቁ መሆኑን ደምረን ስናየው፤ የዚህ እቅድ በሀገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ጉልህ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በትምህርት ዘርፍ ወደ ስልሳ ሁለት ከመቶ ለማድረስ የታቀደው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋን ያልተሳካ መሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢታመንም፤ በእድገታችን ላይ አንድም ነጥብ ለመቀነስ ግን በቂ አይደለም፡፡
መንግስት፣ በገጠር ከተሞች እና ማዕከላት ለማስፋፋት አቅዶት የነበረው የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም፤ በባለሞያ ዕጥረት እና አንዳንድ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ ባለመቻሉ እንደታሰበው ሊሄድ እንዳልቻለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አምነዋል፡፡ መቼም የመብራት አስፈላጊነት ጨለማን ለማስወገድ ብቻ ሳይሆን መብራት በሚገባላቸው አካባቢዎች የሚፈጥረውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ታሳቢ በማድረግ ጭምር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አንዳንድ ሰዎች መብራት በሌለባቸው አካባቢዎች የወሊድ ምጣኔም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡ በእኛ ሀገር ግን ይህ እቅድ በታሰበው መጠን ባይሳካም፣ አጠቃላይ እድገታችን ላይ ምንም ጫና የለውም፡፡ ለዚህም ይመስላል በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በሁለት አሃዝ ያደግነው፡፡

የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አራተኛ ዓመት ማገባደጃ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ አንድ የቱሪዝም ምክር ቤት ተመስርቷል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በክልሎችም፣ በክልል መስተዳድሮች የሚመራ የቱሪዝም ምክር ቤት እንዲያቋቁሙ ከስምምነት ተደርሷል ብለውናል፡፡ በቱሪዝም ዘርፍ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ሀብት ለመጠቀም አቅጣጫ የሚያሳይ የተባለለት ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትራችን ገለፃ መሰረት ኢትዮጵያ በቱሪዝም ሴክትር ያላትን አቅም የሚያህል አንድም የአፍሪካ ሀገር የለውም፡፡ ሆኖም ግን ይህን ልንጠቀም እንዳልቻልን ይስማማሉ፡፡ ይህን ባናደርግም ግን እድገታችንን ከሁለት አሃዝ ማን ሊያወርደው ይችላል? የሀገር እድገት በእምቅ ሀብት ሳይሆን በተግባር ላይ በዋለ ምርት የሚለካ ቢሆንም፣ ‹‹ወይ ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ›› የሚሉት ሹሞች ግን ‹‹አድገናል›› እያሉን ነው፡፡
የምክር ቤት አባላት ካቀረቡት ጥያቄ አንዱ ‹‹የኦዲት ሪፖርትን መሰረት ያደረገ ተጠያቂነት  ለምን አይኖርም?›› የሚል ነበር፡፡ ክቡርነታቸው መልስ ሲሰጡ ዋናው ነገር ሪፖርት አቅራቢ መስሪያ ቤቶች ያለውን እውነት ማሳየታቸው ነው ብለውናል፡፡ ሌላው በሂደት የሚደረስበት ነው ማለታቸው ነው፡፡ ችግሮቹን ለመሸፈን የሚደረግ ጥረት ቢኖር አሳሳቢ ይሆን ነበር፡፡ ይህ አቅጣጫ መቼም የመንግስትን ሀብትና ንብረት ተገቢ ባልሆነ መስመር ለሚጠቀሙ ሰዎች፣ ጥሩ አረንጓዴ መብራት ይመስለኛል፡፡ ዘራፊዎቹ ዘረፋ ይቀጥላሉ፤ ሀብት ይባክናል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን የሀገሪቱን እድገት ከሁለት አሃዝ የሚያወርድ አይሆንም፡፡
በመጨረሻም በግሌ ያነሳሁት የግል ባንኮች ተሳትፎ በሚኖርበት ሁኔታ የማኑፋክቸሪንግን ዘርፍ ለማስፋፋት መንግስት ማበረታቻ ማድረግ ይኖርበታል የሚል ነበር፡፡ ለዚህ ጥያቄ የተሰጠው መልስ ለግል ባንክ የምንሰጠው ገንዘብ የለም የሚል ነው፡፡ የግል ባንኮች ገንዘብ መሰብሰብ ያለባቸው ከደንበኞች ቁጠባ ነው የሚል ሃረግም አክለውበታል፡፡ በግሌ ያቀረብኩት ሃሳብ፤ መንግስት ለግል ባንኮች ገንዘብ ይስጥ ሳይሆን፤ መንግስት ከግል ባንኮች የሚወስደውን ሃያ ሰባት በመቶ ያቁምና እራሳቸው ብድሩን  ለግል ሴክተር ይስጡ ነው፡፡ መቼም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ባይጠፋቸውም፣ አጠቃላይ አድማጩን ህዝብ ለማሳሳት በሚመስል መልኩ ጥያቄውን ወደሌላ አቅጣጫ መርተውታል፡፡ አሁንም የግል ተሳትፎ እንዲጎለብት የግል ባንኮች ተሳትፎ መኖር አለበት ብንልም አይሆንም ብለዋል፡፡ የግል ሴክተሩ ለኢኮኖሚው ሞተር ነው እያሉ ሞተሩ የሚነሳበትን ባትሪ በመንቀል እንዳይሰራ እያደረጉት ነው፡፡ የግል ሴክተሩ ቢሳተፍ ባይሳተፍ በሁለት አሃዝ ማደጋችን ግን ይቀጥላል፡፡
አንድ ጥያቄ አለኝ! መንግስት የዚች ሀገር እድገት ሊቀንስ የሚችለው ምን ምን ሁኔታዎች ሳይሳኩ እንደሆነ ሊገልፅልን ቢችል እኛንም ከመደናገር ያድነናል ብዬ አምናለሁ፡፡ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ውስጥ ይህ እቅድ እንዲሳካ ታሳቢ ተብለው የተቀመጡት ነገሮች በአብዛኛው በታሰበው መሰረት አልነበሩም፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን እድገቱ በታሰበው መሰረት ቀጥሏል …… የጉድ ሀገር!



Wednesday, July 9, 2014

ዶክተር ነጋሶ ፌዴራሊዝም አንድነት አይቃወምም

ፋክት መፅሄት በአንድ ቀን ቅዳሜ ተነቦ የሚያልቅ እንዳልሆነ ይልቁንም አንድ አንድ ሰዎች ለሳምንት በቁጠባ እንደሚያነቡት አውቃለሁ፡፡ እኔም እንዲሁ ጥንቅቅ አድርጌ ለመጨረስ ጊዜ ይወስድብኛል፡፡ አንዳንዴ ሳልጨርሰው ሳምንቱ ተመልሶ ሌላ ይዞ ይመጣል፡፡ ዛሬ ከፋክት መፅሔት ላይ ለማንበብ የቻልኩት የዶክትር ነጋሶን “ውህደት፣ ምርጫና ዓመፅ” የሚለው ነው፡፡ ጠጠር ባለ አማርኛ ያቀረቡትን ፅሁፍ አንብቤ ማለፍ የማልችላቸው ነጥቦች ገጠሙኝ፡፡ ለወዳጄ ዶክተር ነጋሶ ደውዬ ልነግራቸው እንደምችል እኔም እሳቸውም ያውቁታል፡፡ በዚህ ጉዳይ የግልፅነት ችግር ሁለታችንም የለብንም፡፡ ነገር ግን ፅሁፉን ያነበበው ብዙ ሰው ሰለሚሆን ማስተካከያ ብዙ ሰው በሚያነበው መስመር እንዲሆን ብዬ በማህበራዊ ድህረ ገፅ እንዲሆን ወደድኩኝ፡፡ ለዚህ አስተያየት የፋክት መፅሄትን ውድ ገፅ ማበከን ትርፋማ አይደለም የሚልም የጎንዮሽ ታሳቢ አለው፡፡
አንዱ ቅሬታ ያለኝ “አንድነትና መኢአድ የፌዴራል ሰርዓቱን የሚቃወሙና የሊብራል ፖለቲካ ሀሣብ ደጋፊ በመሆናቸው የተቀባይነት መሰረታቸውን ይገድበዋል፡፡” የሚለው ነው፡፡ ይህ መረጃም የተደረሰበትም ድምዳሜ ትክክል አይደለም፡፡ አንድነትም ሆነ መኢአድ የፌዴራል ስርዓትን አይቃወሙም በቀድሞ ፕሮግራምም ሆነ በአሁኑ የውህዱ ፕሮግራመ በግልፅ የተቀመጠው፣ ኢየትዮጵያ የሚያስፈልጋት የፌዴራ ሰርዓት መሆኑን፤ ፌዴራሊዝም በአንድ ጊዜ ተሰርቶ የማይጠናቀቅ መሆኑን፣ ኢትዮጵያ ከቋንቋ በተጨማሪ ሌሎች የፌዴራል ክልሎችን ለማካለል የሚያስፈልጉ ተጨማሪ መስፈርቶች መኖራቸው ይጠቅማል የሚሉት ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አሁን ያለው የእውሽት ፌዴራሊዝም የምር በተግባር መተርጎም አለበት ነው የሚሉት፡፡ ይህን እውነት ለዶክተር ነጋሶ ለማስረዳት ሳይሆን መፅሄቱን የሚያነቡ ሰዎች ትክክለኛውን መረጃ እንዲያገኙ በማለት ነው፡፡ የአንድነት ድህረ ገፅ ላይ የፓርቲው ዝርዝር ፕሮግራም ስለሚገኝ ፍላጎት ያለው ሊመለከት ይችላል፡፡ ሊብራል ፖለቲካ አሰተሳሰብ ደጋፊ መሆን ፓርቲዎቸን እንዴት አደርጎ አማራ እንደሚያደርጋቸው እና ሌሎችን ብሔሮች እንደሚያስከፋቸው ሊገባኝ አይችልም እኔ አማራ አይደለመሁም የሊብራል ፖለቲካ አቀንቃኝ ነኝ፡፡ ይህ ሃሳባ ምንጩ የመድረክ አባል ድርጅቶች ውህደትን በአደባባይ እንቢ ሲሉ እነሱን እሹሩሩ ማለት አለባችሁ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ አሁን ጫወታው የተቀየረ ሰለሆነ ምርጫው የመድረክ አባል ድርጅቶች ነው፡፡
ሌላው ቅርታዬ ምርጫን በተመለከተ ያነሱት ሃሳብ ነው፡፡ ምርጫ የምንወዳደረው የምርጫ ቦርድ እንዳይሰረዝን ብለን እንዳልሆነ ዶክትር ነጋሶ በትክክል ይረዳሉ፡፡ ነገር ግን ለዚህ ብለው የሚወዳደሩ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በአዲሰ አበባና ድሬዳዋ ምርጫ ወቀት አንድነት እንደ ፓርቲ ለመወዳደር ወስኖ ነገር ግን የመድረክ አባል ድርጅቶች በሙሉ በቂ ዝግጅት ባለማድረጋቸው ላለመወዳድር ሰበብ ሲደረድሩ ዶክትር ነጋሶ እነሱን ደግፈው አንድነት ቢፈልግም መወዳደር ሳይችል ቀርቶዋል፡፡ በቀጣይ ምርጫ አንድም የተለወጠ ነገር እንደማይኖር እርግጠኞች ብንሆንም ይልቁንም አሁን የምናየው አባሎቻቸን መታሰረ እየጀመሩ ቢሆንም፣ ለመወዳደር ግን ፍላጎት እንደሚኖራቸው ግምት አለኝ፡፡ ስለዚህ ምርጫ ቦርድ እንዳይሰርዛቸው እንጂ የሚችሉትን ያህል ውጤት ለማምጣት እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ አሜሪካ ላቦራቶሪ ውስጥ ወይም በሌላ የምርምር ሰራ ላይ ሆነው ፓርቲ የሚመሩትም ሰዎች ምን እንደሚሉ በቅርቡ የምናየው ይሆናል፡፡ በእኔ እምነት እነዚህ ሰዎች ከኢህአዴግ እኩል የሚታገሉት አንድነት ከመኢአድ ጋር የሚያደርገው ውህደት ከተሳካ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል ብዬ አሰባለሁ፡፡ ውህደቱ ባይሳካም አንድነት ከእነርሱ ጋር ሆኖ ከሚያገኘው ብዙ እጥፍ እንደሚሄድ ግን ለማወቅ ነብይ መሆን አያስፈልግም፡፡

በመጨረሻም “በተቃዋሚ ትግሉ ውስጥ አሜሪካና ምዕራባዊያንን እንደመተማመኛ የመውስዱና ከህዝብ ባልተናነስ ወሳኝ ክፍሎች እንደሆኑ አድርጎ የመመልከት አዝማሚያ አያለሁ” የሚል አስተያየት አለ፡፡ በሰጡት መደምደሚያ እሰማማለሀ፡፡ ዶክተር ነጋሶ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአንድነት መሪ ስለነበሩ ይህ አዝማሚያ አንድነት ውስጥም ነበር የሚል እንደምታ አንባቢ ከወሰደ ተሳሰተዋል ለማለት ነው፡፡ እኔ ከዶክተር ነጋሶ ጋር ፓርቲ በምንመራበት ወቅት ይህን አቅጣጫ በግልፅ ይዘን ሊያወያዩን የሚመጡ ማነኛቸውንም ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመጣ ለውጥ ካለ በህዝቡ ብቻ እንደሆነ አበክረን እናስረዳ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ነገር ግን መድረክ ውስጥ የውጭ ሰዎች ላይ መተማመን አዝማሚያ ሳይሆን መርዕ እስኪመስል ድረስ እንዳለ ግን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በሀገር ውስጥ ከምናደርገው ጥረት ይልቅ ተለማማጅ የፖለቲካ አታቼ ነን የሚሉ ፈረንጅ ጎረምሶች የበለጠ እንደሚሰሙ እነርሱም ያውቁታል፡፡ አንድነት በህዝብ ስለሚተማመን ነው “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” ብሎ ከህዝቡ ጋር ሲነቀሳቀስ የነበረው፡፡ 

Monday, July 7, 2014

ሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛውና አብዮት

በቅርቡ የደሞዝ ጭማሪ አዋጁ ሲነገር በቦታው ነበርኩ፡፡ ማጨብጨብ አልወድም፡፡ ለምስማማበት ነገር ድጋፌን ለመስጠት እንኳን ቢሆን ሌላ ዘዴ ነው የምጠቀመው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ፤ በአፍሪካ አዳራሽ የደሞዝ ጭማሪውን ሲያበሰሩ ግን አጨበጨብኩ፡፡ ያጨበጨብኩት፣ የመንግስት ሰራተኛው፣ ከእጅ ወደ አፍ የሆነው ኑሮው፣ በሄድንበት ሁሉ እንደልባችን አገልግሎት እንዳንጠይቅ ከሚያደርጉን ገዳቢ ነገሮች አንዱ ስለሆነ የውስጥ ደስታዬ ከልቤ በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ የደሞዝ ጭማሪው ከመታወጁ ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ለአንድ መፅሄት በሰጠሁት ቃለ-ምልልስ ‹‹…ኢትዮጵያ ውስጥ አብዮት ሊጠራ የሚችለው ደሃውን ሕብረተሰብ እያመሳቀለው ያለው የኑሮ ውድነት፣ የመኖሪያ ቤት ዕጦትና ለመኖር ያለመቻል ነው፡፡ … መሃሉን ሲከለከል ዳር ወጥቼ እኖራለሁ ብሎ ከገበሬ ጋር ሲደራደርና ሲኖር ቤቱን ስታፈርስበት እና መፍትሔ ሲያጣ የመጨረሻው ቀን የአብዮት መነሻ ይሆናል፡፡ የመንግስት ሠራተኛው ለአብዮት መነሻ ዋና ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ልጁን ማስተማር ሳይችል ሲቀር፣ ከዛሬ ነገ ደሞወዝ ይጨመርልኛል ብሎ አንገቱን ደፍቶ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ ቀን በቃኝ ብሎ የተነሳ ዕለት ግን የአብዮት ገፊ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡” የሚል ነበር፡፡ ለማንኛውም መንግስት የሚመጣውን አብዮት ፈርቶ ይሁን አሊያም ችግሩን ተረድቶ የደሞዝ ጭማሪ አድርጓል፡፡
የደሞዝ ጭማሪውን ተከትሎ እየመጣ ያለው እና በመንግስትም ሆነ በግል ሚዲያዎች የሚራገበው ዋነኛው ጉዳይ የደሞዝ ጭማሪውን ተከትሎ ሊከሰት ስለሚችለው የዋጋ ንረት እና ስለ “ስግብግብ” ነጋዴዎች ተከታይ እርምጃ ነው፡፡ መንግስት እና የመንግስት ሚዲያዎች ያለውን መሰረታዊ ችግር ለመሸፋፈን የዚህ ዓይነት የፕሮፓጋንዳ ስራ ውስጥ ቢጠመዱ አይገርመኝም፡፡ ነገር ግን ምልዓተ-ህዝቡ መንግስት ለመንግስት ሰራተኛውን በቸርነቱ ያደረገውን የደሞዝ ጭማሪ “ስግብግብ” የተባለ ነጋዴ ሊዘርፈው ስለሆነ መንግስት አስፈላጊውን እንዲያደርግ ተማፅኖ ማቅረቡ ነው፡፡ ይህን ደግሞ የግል ሚዲያዎችም በእኩል መጠን ተቀብለው እያራገቡት መሆኑ እጅግ አድርጎ አሳስቦኛል፡፡
በሀገራችን ያሉ ነጋዴዎች እንዲህ ዓይነት የተደራጀ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አደረጃጀትም ሆነ ስነ-ልቦና  የላቸውም፡፡ ነጋዴ የሚባለው አንድ ነገር ቢነግድ ለሌላው ነገር ሸማች ነው (ዘይት ቢነግድ ጤፍ ይሸምታል)፡፡ ነጋዴ ከኑሮ ውድነት የሚጠቀም አይደለም፡፡ ሶሻሊዝም የሚባል ስርዓት ባመጣው ጣጣ የመደብ ልዩነት ፈጥረን እርስ በእርስ በጠላትነት እየተያየን በጋራ እንዳንቆም የሚያደርገን አስተሳሰብ ነው፡፡ የማይካደው ነገር የደሞዝ ጭማሪን ተከትሎ የሚመጣ የዋጋ ንረት አለ፡፡ የዚህ የዋጋ ንረት ዋነኛ ምንጩ ግን ደሞዝ ከተጨመረለት የመንግስት ሠራተኛ የመግዛት ፍላጎት ጋር የማይጣጣም የፍጆታ እቃዎች አቅርቦት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ የመንግስት ሰራተኛ በወር አራት ኪሎ ስኳር የሚያስፈልገው ቢሆን ቀደም ሲል በተፈጠረ የዋጋ ንረት፣ የገንዘብ የመግዛት አቅም መውረድ እና በሌሎች ብዙ ምክንያቶች የተነሳ ሁለት ኪሎ ብቻ ሲጠቀም ከነበረ፤ በደሞዝ ጭማሪ ምክንያት ወደ ቀድሞ አራት መመለስ ባይችል እንኳን ሶስት ኪሎ ለመግዛት ሊወስን ይችላል፡፡ የአንድ ኪሎ ስኳር ጭማሪ በአንድ ሚሊዮን ሰራተኛ ሲባዛ አንድ ሺ ቶን ስኳር ተጨማሪ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ስኳር በመደበኛውም ወቅት እጥረት ያለበት የሸቀጥ አይነት ስለሆነ ከደሞዝ ጭማሪው ጋር ተያይዞ የበለጠ ሊወደድ ይችላል፡፡ ይህ “የስግብግብ” ነጋዴ ሴራ ሳይሆን የገበያ ህግ ያመጣው ነው፡፡ ይህ በተመሳሳይ በሁሉም የፍጆታ እቃዎች ላይ የሚታይ ስለሆነ ወደ ሌላ ዝርዝር መግባት አያስፈልግም፡፡ ወደ ሌላ ወሳኝ የሆነ የመኖሪያ ቤት ዋጋ ጭማሪ እንለፍ፡፡
በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤትን እንደ አንድ የንግድ ዘርፍ ወስደው ቤት ሰርተው የሚያከራዩ ግለሰቦች አሊያም የንግድ ተቋማት እምብዛም የሉም፡፡ ያሉትም እጅግ አነስተኛ ከመሆናቸው በተጨማሪ ምንም ዓይነት የፖሊሲ ድጋፍ የሌላቸው፣ ከዚህም የተነሳ የዋጋ ቁጥጥር የማይደረግባቸው ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አብዛኛው ሰው በግቢው ውስጥ ያለው ትርፍ ቦታ ላይ ጎጆ እየቀለሰ ኑሮውን የሚደጉም ነው (አብዛኛው ጡረተኛ ወይም ደሞዝተኛ ነው)፡፡  አብዛኞቹ ቤት አከራዮች ደግሞ ኑሮዋቸውን መሰረት ያደረጉት ከቤት ኪራይ በሚያገኙት ገንዘብ ነው፡፡ ኑሮ ሲወደድባቸው አማራጭ የሌለው ቤት ተከራይ ላይ ዋጋ መጨመርን ብቸኛው አማራጭ አድርገው ይወስዱታል፡፡ ለዚህ ችግር ዋነኛው ምክንያት ዜጎች ቤት መስራት ባይችሉ እንኳን የተረጋጋ የቤት ኪራይ ተመን ሊኖር የሚችልበት ፖሊሲ የሌለው መንግስት በመኖሩ ነው፡፡ መንግስት፤ የመኖሪያ ቤት ሰርተው ለሚያከራዩ ባለሀብቶች ምቹ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫ ቢያስቀምጥ ሁሉም ሰው የግል የመኖሪያ ቤት ባለቤት የመሆን ፍላጎት የለውም፡፡ ይህ ችግር በአዲስ አበባ የከፋ ሲሆን በሁሉም አካባቢ በስፋት የሚታይ ነው፡፡ በከተማው ውስጥ የመኖሪያ ቤት ኪራይን ዋጋ የሚያንረው ደግሞ ራሱ መንግስት ነው፡፡ አቅርቦቱ እንዲሰፋ ምንም ዓይነት የፖሊስ አቅጣጫ ያላስቀመጠ መንግስት ይባስ ብሎ በከተማው ውስጥ በሊዝ እየሸጣቸው ያሉት መሬቶች፤ ዋጋቸው ወደፊት የመንግስት ሠራተኛ ብቻ ሳይሆን አንድም ሰው በከተማ መኖር እንደማይችል አመላካች ነው፡፡ ከምርጦቹ ውጭ ማለቴ ነው፡፡
ከላይ ላነሳኋቸው ነጥቦች የመፍትሔው አቅጣጫ ቀላል ነው፡፡ በመንግስት ሠራተኛው የመግዛት ፍላጎት ሊንሩ የሚችሉትን መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች አቅርቦት ለጊዜውም ቢሆን ቀድሞ ከነበረው ያለመለወጥ፣ ይልቁንም በደሞዝ ጭማሪ የሚመጣውን ተጨማሪ ገንዘብ ወደ ቁጠባ ማዞር ዋነኛው መፍትሔ ነው፡፡ መንግስት 20 ከመቶ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለመንግስት ሠራተኞች ብቻ እጣ እንዲያወጡ የሚለው የህልም እንጀራ ለጥቂት እድለኞች ወይም ለስርዓቱ ጋሻ ጃግሬዎች መፍትሔ ሊሆን ቢችል እንኳን አዲስ ለሚመጡት ወጣት የሲቪል ሰርቪሰ ሠራተኞች ዘላቂ መፍትሔ የሚሆን ግን አይደለም፡፡ መንግስት በተመጣጣኝ ዋጋ የመኖሪያ ቤት ሰርተው በሽያጭም ሆነ በኪራይ ማቅረብ ለሚችሉ ባለ ሀብቶች፤ የቤት መስሪያ ቦታና መሰረተ-ልማት በነፃ ከማቅረብ ጀምሮ፣ ረዘም ያለ የግብር እፎይታ ጊዜ እንዲሁም ብድር እንዲያገኙ በማድረግ፣ ዘርፉ ለባለሀብቶች አዋጭ እንዲሆን ማድረግ ይኖርበታል፡፡ አሁን በመንግስት የተያዘው የፖሊሲ አቅጣጫ የውጭ ኢንቨስተሮችና ጥቂት ሀብታሞች በከተማው ማዕከል ላይ ቤት እንዲኖራቸው የሚያደርግ እንጂ የአብዛኛውን ዜጋ የተረጋጋ ኑሮ የሚያረጋግጥ አይደለም፡፡ አሁን የሚደረገው የደሞዝ ጭማሪም ሆነ የኮንዶሚኒየም ቤት ግንባታ ችግሩን በመሰረቱ አይቀርፈውም፡፡
ወደኋላ ልመልሳችሁ፡፡ የደሞዝ ጭማሪው በተበሰረበት ስብሰባ ላይ ተገኝቼ በጥናታዊ ፅሁፍ አቅራቢዎች የቀረቡትን ፅሁፎች አዳምጫለሁ፡፡ ዶክተር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ያቀረቡት ፅሁፍ የመንግስትን አቅጣጫ ያሳየ ስለሆነ በኢህአዴግ መነፅር የታየ ብለን ልናልፈው ብንችልም፣ የሲቪል ሰርቪስ ሠራኛውን በተመለከተ ከ1900 ዓ.ም በፊትና በኋላ የነበረውን ታሪካዊ ዳራ ያስቃኙን የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አገላለፅ፣ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በሲቪል ሰርቪስ ያገለገልን ሰዎችን የወረፈ ነበር፡፡ “ከኢህአዴግ መንግስት በፊት ያለው የሲቪል ሰርቪስ የመንግስት አገልጋይ እንጂ የህዝብ አገልጋይ አልነበርም” ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ እስከአሁን ባለኝ እውቀት እንደሚገባኝ መንግስት የህዝብ አገልጋይ እንደሆነ ነው፡፡ መንግስትን ማገልገል ደግሞ በተዘዋዋሪ ህዝብን ማገልገል ነው፡፡ በግሌ በደርግም ጊዜ ሆነ በኢሕአዴግ መንግስት ውስጥ ተቀጥሬ ስሰራ ህዝብን እያገለገልኩ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ በዚህም ኩራት ይሰማኛል፡፡ አንድም ቀን የደርግም ሆነ የኢሕአዴግ የግል አሽከር ነበርኩ ብዬ አላስብም፡፡ ይልቁንም አሁን ያለው መንግስት እራሱን ለህዝብ የቆምኩ ነኝ እያለ ቢመፃደቅም ቅሉ በተግባር ግን የህዝብ አገልጋይነቱን እየረሳ ዜጎች መንግስት ለሚባል የማይዳሰስና የማይታይ መንፈስ፤ በመንግስት ስም ለሚታዩ ግለሰቦች አገልጋይ እንዲሆኑ ፍላጎት አለው፡፡ ይህ የመንግስትና ህዝብ ክፉኛ መራራቅ፣ በሀገራችን ኢትዮጵያ የለውጥ ፈላጊውን ቁጥር እያበዛው፣ የመንግስትን ቁጥጥር ደግሞ ልክ እያሳጣው መጥቷል፡፡
በነገራችን ላይ በሚሊዮን የሚቆጠር የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኛ ሰራዊት ጥያቄ ደሞዝ ይጨመርልኝ ብቻ አልነበረም፤ አይሆንምም፡፡ ይህ ሰራዊት በአንፃራዊነት የተማረ እና በከፍተኛ ደረጃ የተማረው ደግሞ በዚህች አገር በሚኖር ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለወንበር/ለሹመት እራሱን የሚያጭ ነው፡፡ ሹመቱ ቢቀር በቴክኖክራትነት ያገባኛል የሚል እና ወሳኝ በሆነ መልኩ ጫና ፈጣሪ ነው፡፡ ይህን ሊያደርግ የሚችልበት የስራ ሁኔታ እና ነፃነት እንዲኖር ፍላጎት አለው፡፡ ይህን ለማድረግ በሚያስችል መልኩ እስከ ዛሬ የተንቀሳቀሰ ባይሆንም፤ በቀጣይ በሚኖሩ የሰላማዊ ትግል ስልቶች ወሳኝ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይገመታል፡፡ ቀጣዩ ምርጫ ቢያንስ የምርጫን ካርድ በነቂስ በመውሰድ እና ቤተሰቦቹን በምርጫ እንዲሳተፉ በማስተባበር የህዝብ ወገንተኝነቱን እና ለህዝብ እንጂ ለግለሰቦች አገልጋይ እንዳልሆነ የሚያሳይበት አንድ ወሳኝ ኩነት ነው፡፡ ይህ ማለት የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኛው ተቃዋሚ ፓርቲን ይምረጥ ማለት አይደለም፡፡ አሁን ባለው የስራ ላይ ነፃነት ደስተኛ ከሆነ ኢህአዴግንም መምረጥና ማስመረጥ መብቱ ነው፡፡

ይሁን እንጂ በሀገራችን ኢትዮጵያ ለውጥ የማይፈልግ ሰው ካለ፣ እርሱ አሁን ካለው ስርዓት ያለአግባብ በሚያገኘው ጥቅም የታወረ መሆን አለበት፡፡ ለውጥን ከመፈለግ አንፃር ሌላው ቀርቶ የስርዓቱ ዋነኛ ተጠቃሚ ናቸው የሚባሉት ስልጣን ላይ ያሉትም ቢሆኑ እንደሚፈልጉ ይታወቃል፡፡ ይህን የሚጠራጠር ካለ እርሱም የመረጃ ክፍተት ያለበት መሆን አለበት፡፡ ችግሩ ለውጡ እንዴት ይምጣ የሚለው ላይ መሆኑ ነው፡፡ በገዢነት ወንበር ላይ የተደላደሉት፣ ለውጡ በፍፁም ቃሊቲ የሚያወርዳቸው እንዲሆን አይፈልጉም፡፡ ይህ ደግሞ ትክክለኛ አስተሳሰብ ነው፡፡ ቃሊቲ ሳይወርዱ እንዴት ለውጥ ይምጣ የሚለው ግን በሁላችንም በኩል መልስ ያልተገኘለት ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ ጥያቄውን ከባድ ያደረገው ደግሞ በተቃዋሚ ጎራ እነዚህን ገዢዎች ቃሊት ካላወረደ እንቅልፍ የማይወስደው የመኖሩን ያህል፤ በገዢዎችም ሰፈር ሁሉም በተቃዋሚ ሰፈር የሚገኝ እነርሱን ቃሊቲ ለማውረድ የሚሰራ የሚመስላቸው መሆኑ ነው፡፡ ይህ ተቀራርቦ ካለመወያየት እና ካለመረዳዳት የሚመጣ ሲሆን፤ በይሆናል እና በመላምት ለሀገር ግንባታ ሊውል የሚችል የሰው ኃይል እና ገንዘብ እርስ በእርስ በአይነ-ቁራኛ ለመጠባበቅ እያዋልን እንገኛለን፡፡ የሰሞኑን የደሞዝ ጭማሪ አንዳንዶች ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል የተሰጠ “ጉቦ” ብለውታል፡፡ ለጊዜው በደሞዝ አነሰኝ ሊመጣ የሚችለው አብዮት ትንሽ ሊዘገይ ቢችልም ሌሎች ግፎችና ግፉዓን በሞሉበት ሀገር አብዮት ሳይኖር ለውጥ እንዲመጣ መስራት ይኖርብናል፡፡