Monday, July 7, 2014

ሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛውና አብዮት

በቅርቡ የደሞዝ ጭማሪ አዋጁ ሲነገር በቦታው ነበርኩ፡፡ ማጨብጨብ አልወድም፡፡ ለምስማማበት ነገር ድጋፌን ለመስጠት እንኳን ቢሆን ሌላ ዘዴ ነው የምጠቀመው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ፤ በአፍሪካ አዳራሽ የደሞዝ ጭማሪውን ሲያበሰሩ ግን አጨበጨብኩ፡፡ ያጨበጨብኩት፣ የመንግስት ሰራተኛው፣ ከእጅ ወደ አፍ የሆነው ኑሮው፣ በሄድንበት ሁሉ እንደልባችን አገልግሎት እንዳንጠይቅ ከሚያደርጉን ገዳቢ ነገሮች አንዱ ስለሆነ የውስጥ ደስታዬ ከልቤ በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ የደሞዝ ጭማሪው ከመታወጁ ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ለአንድ መፅሄት በሰጠሁት ቃለ-ምልልስ ‹‹…ኢትዮጵያ ውስጥ አብዮት ሊጠራ የሚችለው ደሃውን ሕብረተሰብ እያመሳቀለው ያለው የኑሮ ውድነት፣ የመኖሪያ ቤት ዕጦትና ለመኖር ያለመቻል ነው፡፡ … መሃሉን ሲከለከል ዳር ወጥቼ እኖራለሁ ብሎ ከገበሬ ጋር ሲደራደርና ሲኖር ቤቱን ስታፈርስበት እና መፍትሔ ሲያጣ የመጨረሻው ቀን የአብዮት መነሻ ይሆናል፡፡ የመንግስት ሠራተኛው ለአብዮት መነሻ ዋና ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ልጁን ማስተማር ሳይችል ሲቀር፣ ከዛሬ ነገ ደሞወዝ ይጨመርልኛል ብሎ አንገቱን ደፍቶ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ ቀን በቃኝ ብሎ የተነሳ ዕለት ግን የአብዮት ገፊ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡” የሚል ነበር፡፡ ለማንኛውም መንግስት የሚመጣውን አብዮት ፈርቶ ይሁን አሊያም ችግሩን ተረድቶ የደሞዝ ጭማሪ አድርጓል፡፡
የደሞዝ ጭማሪውን ተከትሎ እየመጣ ያለው እና በመንግስትም ሆነ በግል ሚዲያዎች የሚራገበው ዋነኛው ጉዳይ የደሞዝ ጭማሪውን ተከትሎ ሊከሰት ስለሚችለው የዋጋ ንረት እና ስለ “ስግብግብ” ነጋዴዎች ተከታይ እርምጃ ነው፡፡ መንግስት እና የመንግስት ሚዲያዎች ያለውን መሰረታዊ ችግር ለመሸፋፈን የዚህ ዓይነት የፕሮፓጋንዳ ስራ ውስጥ ቢጠመዱ አይገርመኝም፡፡ ነገር ግን ምልዓተ-ህዝቡ መንግስት ለመንግስት ሰራተኛውን በቸርነቱ ያደረገውን የደሞዝ ጭማሪ “ስግብግብ” የተባለ ነጋዴ ሊዘርፈው ስለሆነ መንግስት አስፈላጊውን እንዲያደርግ ተማፅኖ ማቅረቡ ነው፡፡ ይህን ደግሞ የግል ሚዲያዎችም በእኩል መጠን ተቀብለው እያራገቡት መሆኑ እጅግ አድርጎ አሳስቦኛል፡፡
በሀገራችን ያሉ ነጋዴዎች እንዲህ ዓይነት የተደራጀ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አደረጃጀትም ሆነ ስነ-ልቦና  የላቸውም፡፡ ነጋዴ የሚባለው አንድ ነገር ቢነግድ ለሌላው ነገር ሸማች ነው (ዘይት ቢነግድ ጤፍ ይሸምታል)፡፡ ነጋዴ ከኑሮ ውድነት የሚጠቀም አይደለም፡፡ ሶሻሊዝም የሚባል ስርዓት ባመጣው ጣጣ የመደብ ልዩነት ፈጥረን እርስ በእርስ በጠላትነት እየተያየን በጋራ እንዳንቆም የሚያደርገን አስተሳሰብ ነው፡፡ የማይካደው ነገር የደሞዝ ጭማሪን ተከትሎ የሚመጣ የዋጋ ንረት አለ፡፡ የዚህ የዋጋ ንረት ዋነኛ ምንጩ ግን ደሞዝ ከተጨመረለት የመንግስት ሠራተኛ የመግዛት ፍላጎት ጋር የማይጣጣም የፍጆታ እቃዎች አቅርቦት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ የመንግስት ሰራተኛ በወር አራት ኪሎ ስኳር የሚያስፈልገው ቢሆን ቀደም ሲል በተፈጠረ የዋጋ ንረት፣ የገንዘብ የመግዛት አቅም መውረድ እና በሌሎች ብዙ ምክንያቶች የተነሳ ሁለት ኪሎ ብቻ ሲጠቀም ከነበረ፤ በደሞዝ ጭማሪ ምክንያት ወደ ቀድሞ አራት መመለስ ባይችል እንኳን ሶስት ኪሎ ለመግዛት ሊወስን ይችላል፡፡ የአንድ ኪሎ ስኳር ጭማሪ በአንድ ሚሊዮን ሰራተኛ ሲባዛ አንድ ሺ ቶን ስኳር ተጨማሪ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ስኳር በመደበኛውም ወቅት እጥረት ያለበት የሸቀጥ አይነት ስለሆነ ከደሞዝ ጭማሪው ጋር ተያይዞ የበለጠ ሊወደድ ይችላል፡፡ ይህ “የስግብግብ” ነጋዴ ሴራ ሳይሆን የገበያ ህግ ያመጣው ነው፡፡ ይህ በተመሳሳይ በሁሉም የፍጆታ እቃዎች ላይ የሚታይ ስለሆነ ወደ ሌላ ዝርዝር መግባት አያስፈልግም፡፡ ወደ ሌላ ወሳኝ የሆነ የመኖሪያ ቤት ዋጋ ጭማሪ እንለፍ፡፡
በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤትን እንደ አንድ የንግድ ዘርፍ ወስደው ቤት ሰርተው የሚያከራዩ ግለሰቦች አሊያም የንግድ ተቋማት እምብዛም የሉም፡፡ ያሉትም እጅግ አነስተኛ ከመሆናቸው በተጨማሪ ምንም ዓይነት የፖሊሲ ድጋፍ የሌላቸው፣ ከዚህም የተነሳ የዋጋ ቁጥጥር የማይደረግባቸው ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አብዛኛው ሰው በግቢው ውስጥ ያለው ትርፍ ቦታ ላይ ጎጆ እየቀለሰ ኑሮውን የሚደጉም ነው (አብዛኛው ጡረተኛ ወይም ደሞዝተኛ ነው)፡፡  አብዛኞቹ ቤት አከራዮች ደግሞ ኑሮዋቸውን መሰረት ያደረጉት ከቤት ኪራይ በሚያገኙት ገንዘብ ነው፡፡ ኑሮ ሲወደድባቸው አማራጭ የሌለው ቤት ተከራይ ላይ ዋጋ መጨመርን ብቸኛው አማራጭ አድርገው ይወስዱታል፡፡ ለዚህ ችግር ዋነኛው ምክንያት ዜጎች ቤት መስራት ባይችሉ እንኳን የተረጋጋ የቤት ኪራይ ተመን ሊኖር የሚችልበት ፖሊሲ የሌለው መንግስት በመኖሩ ነው፡፡ መንግስት፤ የመኖሪያ ቤት ሰርተው ለሚያከራዩ ባለሀብቶች ምቹ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫ ቢያስቀምጥ ሁሉም ሰው የግል የመኖሪያ ቤት ባለቤት የመሆን ፍላጎት የለውም፡፡ ይህ ችግር በአዲስ አበባ የከፋ ሲሆን በሁሉም አካባቢ በስፋት የሚታይ ነው፡፡ በከተማው ውስጥ የመኖሪያ ቤት ኪራይን ዋጋ የሚያንረው ደግሞ ራሱ መንግስት ነው፡፡ አቅርቦቱ እንዲሰፋ ምንም ዓይነት የፖሊስ አቅጣጫ ያላስቀመጠ መንግስት ይባስ ብሎ በከተማው ውስጥ በሊዝ እየሸጣቸው ያሉት መሬቶች፤ ዋጋቸው ወደፊት የመንግስት ሠራተኛ ብቻ ሳይሆን አንድም ሰው በከተማ መኖር እንደማይችል አመላካች ነው፡፡ ከምርጦቹ ውጭ ማለቴ ነው፡፡
ከላይ ላነሳኋቸው ነጥቦች የመፍትሔው አቅጣጫ ቀላል ነው፡፡ በመንግስት ሠራተኛው የመግዛት ፍላጎት ሊንሩ የሚችሉትን መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች አቅርቦት ለጊዜውም ቢሆን ቀድሞ ከነበረው ያለመለወጥ፣ ይልቁንም በደሞዝ ጭማሪ የሚመጣውን ተጨማሪ ገንዘብ ወደ ቁጠባ ማዞር ዋነኛው መፍትሔ ነው፡፡ መንግስት 20 ከመቶ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለመንግስት ሠራተኞች ብቻ እጣ እንዲያወጡ የሚለው የህልም እንጀራ ለጥቂት እድለኞች ወይም ለስርዓቱ ጋሻ ጃግሬዎች መፍትሔ ሊሆን ቢችል እንኳን አዲስ ለሚመጡት ወጣት የሲቪል ሰርቪሰ ሠራተኞች ዘላቂ መፍትሔ የሚሆን ግን አይደለም፡፡ መንግስት በተመጣጣኝ ዋጋ የመኖሪያ ቤት ሰርተው በሽያጭም ሆነ በኪራይ ማቅረብ ለሚችሉ ባለ ሀብቶች፤ የቤት መስሪያ ቦታና መሰረተ-ልማት በነፃ ከማቅረብ ጀምሮ፣ ረዘም ያለ የግብር እፎይታ ጊዜ እንዲሁም ብድር እንዲያገኙ በማድረግ፣ ዘርፉ ለባለሀብቶች አዋጭ እንዲሆን ማድረግ ይኖርበታል፡፡ አሁን በመንግስት የተያዘው የፖሊሲ አቅጣጫ የውጭ ኢንቨስተሮችና ጥቂት ሀብታሞች በከተማው ማዕከል ላይ ቤት እንዲኖራቸው የሚያደርግ እንጂ የአብዛኛውን ዜጋ የተረጋጋ ኑሮ የሚያረጋግጥ አይደለም፡፡ አሁን የሚደረገው የደሞዝ ጭማሪም ሆነ የኮንዶሚኒየም ቤት ግንባታ ችግሩን በመሰረቱ አይቀርፈውም፡፡
ወደኋላ ልመልሳችሁ፡፡ የደሞዝ ጭማሪው በተበሰረበት ስብሰባ ላይ ተገኝቼ በጥናታዊ ፅሁፍ አቅራቢዎች የቀረቡትን ፅሁፎች አዳምጫለሁ፡፡ ዶክተር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ያቀረቡት ፅሁፍ የመንግስትን አቅጣጫ ያሳየ ስለሆነ በኢህአዴግ መነፅር የታየ ብለን ልናልፈው ብንችልም፣ የሲቪል ሰርቪስ ሠራኛውን በተመለከተ ከ1900 ዓ.ም በፊትና በኋላ የነበረውን ታሪካዊ ዳራ ያስቃኙን የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አገላለፅ፣ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በሲቪል ሰርቪስ ያገለገልን ሰዎችን የወረፈ ነበር፡፡ “ከኢህአዴግ መንግስት በፊት ያለው የሲቪል ሰርቪስ የመንግስት አገልጋይ እንጂ የህዝብ አገልጋይ አልነበርም” ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ እስከአሁን ባለኝ እውቀት እንደሚገባኝ መንግስት የህዝብ አገልጋይ እንደሆነ ነው፡፡ መንግስትን ማገልገል ደግሞ በተዘዋዋሪ ህዝብን ማገልገል ነው፡፡ በግሌ በደርግም ጊዜ ሆነ በኢሕአዴግ መንግስት ውስጥ ተቀጥሬ ስሰራ ህዝብን እያገለገልኩ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ በዚህም ኩራት ይሰማኛል፡፡ አንድም ቀን የደርግም ሆነ የኢሕአዴግ የግል አሽከር ነበርኩ ብዬ አላስብም፡፡ ይልቁንም አሁን ያለው መንግስት እራሱን ለህዝብ የቆምኩ ነኝ እያለ ቢመፃደቅም ቅሉ በተግባር ግን የህዝብ አገልጋይነቱን እየረሳ ዜጎች መንግስት ለሚባል የማይዳሰስና የማይታይ መንፈስ፤ በመንግስት ስም ለሚታዩ ግለሰቦች አገልጋይ እንዲሆኑ ፍላጎት አለው፡፡ ይህ የመንግስትና ህዝብ ክፉኛ መራራቅ፣ በሀገራችን ኢትዮጵያ የለውጥ ፈላጊውን ቁጥር እያበዛው፣ የመንግስትን ቁጥጥር ደግሞ ልክ እያሳጣው መጥቷል፡፡
በነገራችን ላይ በሚሊዮን የሚቆጠር የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኛ ሰራዊት ጥያቄ ደሞዝ ይጨመርልኝ ብቻ አልነበረም፤ አይሆንምም፡፡ ይህ ሰራዊት በአንፃራዊነት የተማረ እና በከፍተኛ ደረጃ የተማረው ደግሞ በዚህች አገር በሚኖር ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለወንበር/ለሹመት እራሱን የሚያጭ ነው፡፡ ሹመቱ ቢቀር በቴክኖክራትነት ያገባኛል የሚል እና ወሳኝ በሆነ መልኩ ጫና ፈጣሪ ነው፡፡ ይህን ሊያደርግ የሚችልበት የስራ ሁኔታ እና ነፃነት እንዲኖር ፍላጎት አለው፡፡ ይህን ለማድረግ በሚያስችል መልኩ እስከ ዛሬ የተንቀሳቀሰ ባይሆንም፤ በቀጣይ በሚኖሩ የሰላማዊ ትግል ስልቶች ወሳኝ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይገመታል፡፡ ቀጣዩ ምርጫ ቢያንስ የምርጫን ካርድ በነቂስ በመውሰድ እና ቤተሰቦቹን በምርጫ እንዲሳተፉ በማስተባበር የህዝብ ወገንተኝነቱን እና ለህዝብ እንጂ ለግለሰቦች አገልጋይ እንዳልሆነ የሚያሳይበት አንድ ወሳኝ ኩነት ነው፡፡ ይህ ማለት የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኛው ተቃዋሚ ፓርቲን ይምረጥ ማለት አይደለም፡፡ አሁን ባለው የስራ ላይ ነፃነት ደስተኛ ከሆነ ኢህአዴግንም መምረጥና ማስመረጥ መብቱ ነው፡፡

ይሁን እንጂ በሀገራችን ኢትዮጵያ ለውጥ የማይፈልግ ሰው ካለ፣ እርሱ አሁን ካለው ስርዓት ያለአግባብ በሚያገኘው ጥቅም የታወረ መሆን አለበት፡፡ ለውጥን ከመፈለግ አንፃር ሌላው ቀርቶ የስርዓቱ ዋነኛ ተጠቃሚ ናቸው የሚባሉት ስልጣን ላይ ያሉትም ቢሆኑ እንደሚፈልጉ ይታወቃል፡፡ ይህን የሚጠራጠር ካለ እርሱም የመረጃ ክፍተት ያለበት መሆን አለበት፡፡ ችግሩ ለውጡ እንዴት ይምጣ የሚለው ላይ መሆኑ ነው፡፡ በገዢነት ወንበር ላይ የተደላደሉት፣ ለውጡ በፍፁም ቃሊቲ የሚያወርዳቸው እንዲሆን አይፈልጉም፡፡ ይህ ደግሞ ትክክለኛ አስተሳሰብ ነው፡፡ ቃሊቲ ሳይወርዱ እንዴት ለውጥ ይምጣ የሚለው ግን በሁላችንም በኩል መልስ ያልተገኘለት ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ ጥያቄውን ከባድ ያደረገው ደግሞ በተቃዋሚ ጎራ እነዚህን ገዢዎች ቃሊት ካላወረደ እንቅልፍ የማይወስደው የመኖሩን ያህል፤ በገዢዎችም ሰፈር ሁሉም በተቃዋሚ ሰፈር የሚገኝ እነርሱን ቃሊቲ ለማውረድ የሚሰራ የሚመስላቸው መሆኑ ነው፡፡ ይህ ተቀራርቦ ካለመወያየት እና ካለመረዳዳት የሚመጣ ሲሆን፤ በይሆናል እና በመላምት ለሀገር ግንባታ ሊውል የሚችል የሰው ኃይል እና ገንዘብ እርስ በእርስ በአይነ-ቁራኛ ለመጠባበቅ እያዋልን እንገኛለን፡፡ የሰሞኑን የደሞዝ ጭማሪ አንዳንዶች ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል የተሰጠ “ጉቦ” ብለውታል፡፡ ለጊዜው በደሞዝ አነሰኝ ሊመጣ የሚችለው አብዮት ትንሽ ሊዘገይ ቢችልም ሌሎች ግፎችና ግፉዓን በሞሉበት ሀገር አብዮት ሳይኖር ለውጥ እንዲመጣ መስራት ይኖርብናል፡፡

No comments:

Post a Comment