ፋክት መፅሄት በአንድ ቀን ቅዳሜ
ተነቦ የሚያልቅ እንዳልሆነ ይልቁንም አንድ አንድ ሰዎች ለሳምንት በቁጠባ እንደሚያነቡት አውቃለሁ፡፡ እኔም እንዲሁ ጥንቅቅ አድርጌ
ለመጨረስ ጊዜ ይወስድብኛል፡፡ አንዳንዴ ሳልጨርሰው ሳምንቱ ተመልሶ ሌላ ይዞ ይመጣል፡፡ ዛሬ ከፋክት መፅሔት ላይ ለማንበብ የቻልኩት
የዶክትር ነጋሶን “ውህደት፣ ምርጫና ዓመፅ” የሚለው ነው፡፡ ጠጠር ባለ አማርኛ ያቀረቡትን ፅሁፍ አንብቤ ማለፍ
የማልችላቸው ነጥቦች ገጠሙኝ፡፡ ለወዳጄ ዶክተር ነጋሶ ደውዬ ልነግራቸው እንደምችል እኔም እሳቸውም ያውቁታል፡፡ በዚህ ጉዳይ የግልፅነት
ችግር ሁለታችንም የለብንም፡፡ ነገር ግን ፅሁፉን ያነበበው ብዙ ሰው ሰለሚሆን ማስተካከያ ብዙ ሰው በሚያነበው መስመር እንዲሆን
ብዬ በማህበራዊ ድህረ ገፅ እንዲሆን ወደድኩኝ፡፡ ለዚህ አስተያየት የፋክት መፅሄትን ውድ ገፅ ማበከን ትርፋማ አይደለም የሚልም
የጎንዮሽ ታሳቢ አለው፡፡
አንዱ ቅሬታ ያለኝ “አንድነትና መኢአድ የፌዴራል ሰርዓቱን የሚቃወሙና
የሊብራል ፖለቲካ ሀሣብ ደጋፊ በመሆናቸው የተቀባይነት መሰረታቸውን ይገድበዋል፡፡” የሚለው ነው፡፡ ይህ መረጃም የተደረሰበትም ድምዳሜ
ትክክል አይደለም፡፡ አንድነትም ሆነ መኢአድ የፌዴራል ስርዓትን አይቃወሙም በቀድሞ ፕሮግራምም ሆነ በአሁኑ የውህዱ ፕሮግራመ በግልፅ
የተቀመጠው፣ ኢየትዮጵያ የሚያስፈልጋት የፌዴራ ሰርዓት መሆኑን፤ ፌዴራሊዝም በአንድ ጊዜ ተሰርቶ የማይጠናቀቅ መሆኑን፣ ኢትዮጵያ
ከቋንቋ በተጨማሪ ሌሎች የፌዴራል ክልሎችን ለማካለል የሚያስፈልጉ ተጨማሪ መስፈርቶች መኖራቸው ይጠቅማል የሚሉት ናቸው፡፡ ከዚህ
በተጨማሪ አሁን ያለው የእውሽት ፌዴራሊዝም የምር በተግባር መተርጎም አለበት ነው የሚሉት፡፡ ይህን እውነት ለዶክተር ነጋሶ ለማስረዳት
ሳይሆን መፅሄቱን የሚያነቡ ሰዎች ትክክለኛውን መረጃ እንዲያገኙ በማለት ነው፡፡ የአንድነት ድህረ ገፅ ላይ የፓርቲው ዝርዝር ፕሮግራም
ስለሚገኝ ፍላጎት ያለው ሊመለከት ይችላል፡፡ ሊብራል ፖለቲካ አሰተሳሰብ ደጋፊ መሆን ፓርቲዎቸን እንዴት አደርጎ አማራ እንደሚያደርጋቸው
እና ሌሎችን ብሔሮች እንደሚያስከፋቸው ሊገባኝ አይችልም እኔ አማራ አይደለመሁም የሊብራል ፖለቲካ አቀንቃኝ ነኝ፡፡ ይህ ሃሳባ ምንጩ
የመድረክ አባል ድርጅቶች ውህደትን በአደባባይ እንቢ ሲሉ እነሱን እሹሩሩ ማለት አለባችሁ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ አሁን ጫወታው
የተቀየረ ሰለሆነ ምርጫው የመድረክ አባል ድርጅቶች ነው፡፡
ሌላው ቅርታዬ ምርጫን በተመለከተ ያነሱት ሃሳብ ነው፡፡ ምርጫ የምንወዳደረው
የምርጫ ቦርድ እንዳይሰረዝን ብለን እንዳልሆነ ዶክትር ነጋሶ በትክክል ይረዳሉ፡፡ ነገር ግን ለዚህ ብለው የሚወዳደሩ እንዳሉ ይታወቃል፡፡
በአዲሰ አበባና ድሬዳዋ ምርጫ ወቀት አንድነት እንደ ፓርቲ ለመወዳደር ወስኖ ነገር ግን የመድረክ አባል ድርጅቶች በሙሉ በቂ ዝግጅት
ባለማድረጋቸው ላለመወዳድር ሰበብ ሲደረድሩ ዶክትር ነጋሶ እነሱን ደግፈው አንድነት ቢፈልግም መወዳደር ሳይችል ቀርቶዋል፡፡ በቀጣይ
ምርጫ አንድም የተለወጠ ነገር እንደማይኖር እርግጠኞች ብንሆንም ይልቁንም አሁን የምናየው አባሎቻቸን መታሰረ እየጀመሩ ቢሆንም፣
ለመወዳደር ግን ፍላጎት እንደሚኖራቸው ግምት አለኝ፡፡ ስለዚህ ምርጫ ቦርድ እንዳይሰርዛቸው እንጂ የሚችሉትን ያህል ውጤት ለማምጣት
እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ አሜሪካ ላቦራቶሪ ውስጥ ወይም በሌላ የምርምር ሰራ ላይ ሆነው ፓርቲ የሚመሩትም ሰዎች ምን እንደሚሉ በቅርቡ
የምናየው ይሆናል፡፡ በእኔ እምነት እነዚህ ሰዎች ከኢህአዴግ እኩል የሚታገሉት አንድነት ከመኢአድ ጋር የሚያደርገው ውህደት ከተሳካ
ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል ብዬ አሰባለሁ፡፡ ውህደቱ ባይሳካም አንድነት ከእነርሱ ጋር ሆኖ ከሚያገኘው ብዙ እጥፍ እንደሚሄድ ግን
ለማወቅ ነብይ መሆን አያስፈልግም፡፡
በመጨረሻም “በተቃዋሚ ትግሉ ውስጥ አሜሪካና ምዕራባዊያንን እንደመተማመኛ የመውስዱና ከህዝብ ባልተናነስ ወሳኝ ክፍሎች እንደሆኑ
አድርጎ የመመልከት አዝማሚያ አያለሁ” የሚል አስተያየት አለ፡፡ በሰጡት መደምደሚያ እሰማማለሀ፡፡ ዶክተር ነጋሶ እስከ ቅርብ
ጊዜ ድረስ የአንድነት መሪ ስለነበሩ ይህ አዝማሚያ አንድነት ውስጥም ነበር የሚል እንደምታ አንባቢ ከወሰደ ተሳሰተዋል ለማለት ነው፡፡
እኔ ከዶክተር ነጋሶ ጋር ፓርቲ በምንመራበት ወቅት ይህን አቅጣጫ በግልፅ ይዘን ሊያወያዩን የሚመጡ ማነኛቸውንም ሰዎች ኢትዮጵያ
ውስጥ የሚመጣ ለውጥ ካለ በህዝቡ ብቻ እንደሆነ አበክረን እናስረዳ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ነገር ግን መድረክ ውስጥ የውጭ ሰዎች
ላይ መተማመን አዝማሚያ ሳይሆን መርዕ እስኪመስል ድረስ እንዳለ ግን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በሀገር ውስጥ ከምናደርገው ጥረት ይልቅ
ተለማማጅ የፖለቲካ አታቼ ነን የሚሉ ፈረንጅ ጎረምሶች የበለጠ እንደሚሰሙ እነርሱም ያውቁታል፡፡ አንድነት በህዝብ ስለሚተማመን ነው
“የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” ብሎ ከህዝቡ ጋር ሲነቀሳቀስ የነበረው፡፡
No comments:
Post a Comment