ከአዲስ
አበባ የሐምሌ ጭጋግ ለመሸሸ ከምጠቀምባቸው አማራጮች አንዱ ከወሩ አጋማሽ ጀምሮ ድሬዳዋ መገኘት እና የቁልቢ ገብርኤልን በዓል ትሩፋት
መሻት ነው፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ በዚሁ ወር በጋምቤላ ለሶሰት ቀናት መገኘት በመቻሌ፤ የሐምሌን ጭጋግ ሽሽት በቆላዎቹ የሀገራችን
ክፍሎች የማደርገውን ቆይታ የተሳካ አድርጎታል፡፡ የነበረንን ጉዞ አጠናቀን እግራችን ጋምቤላን ከመልቀቁ፤ በመዥንገር እና “ደገኞች” በሚባሉት ነዋሪዎች መካከል መፈጠሩ የተሰማው ግጭትና ደም
መፋሰስ፣ ኢህአዴግ የዘራው የጎሰኝነት ፍሬ ማሳያ አንዱ ክፍል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ልብ በሉ! ኢትዮጵያዊነታችን ጥላ ሆኖን
እንደልባችን መዘዋወር አንችልም፡፡ መጤ እና ነባር ተብዬ ፍልስፍና ነብስ ዘርቷል፡፡ በጋምቤላ ቆይታዬ የታዘብኩትን በሌላ ጊዜ ልመለስበት
እችላለሁ፡፡ ለዛሬው ግን በድሬዳዋ እና አካባቢው የታዘብኩትን ላካፍላችሁ፡፡
በቁልቢ በዓል ላይ የሙስሊሙ
እና የክርስቲያኑን አብሮነት ስመለከት፣ ለምን ይህን አብሮነት እና ሰላም የሚጠሉ ሰዎች ይፈጠራሉ? የሚል ጥያቄ ያጭርብኛል፡፡ ጥያቄዬውን
ተከትሎ የሚመጣልኝ መልስ ደግሞ፤ በግላቸው ባላቸው ችሎታና አቅም የማይተማመኑ ነገር ግን ሰልጣን እና ጥቅም የሚሹ ወይም ደግሞ
በአንድ አጋጣሚ ይህን ጥቅም ቀምሰው ጥቅም ያናወዛቸው “ልሂቃን” እና የአካባቢ ተወካይ ነን የሚሉ ግለሰቦች፤ በቡድን መብት ስም
የሚፈጥሩት ውዥንብር እንደሆነ ግልፅ ሆኖ ይታየኛል፡፡ እንግዲህ በሀገራችን ሰላም የሚሰጠን፣ ለእነዚህ ጥቅም ላናወዛቸው ግለሰቦች፣
ልጓም ሲበጅ ነው ብዬም አምናለሁ፡፡ ይህን አብሮነታችንን ሰኞ ዕለት በነበረው የሙስሊሞች በዓል በድሬዳዋ ከተማ ተገኝቼ ተመልክቼዋለሁ፡፡
በቡድን መብት ስም ስልጣን ላይ ያሉት ወገኖች ግን ይህ ሰላም ዘላቂ እንዲሆን የሚሹ አይመስሉም፡፡ እናስተዳድረዋለን በሚሉት ከተማ
እዚህም እዚያም የሚፈጥሩት ችግር፣ ሙስሊሙን እና ክርስቲያኑን የከተማ ነዋሪ እያማረረው ነው፡፡
ድሬዳዋ በቅርቡ የከተሞች ቀንን
እንደምታስተናግድ እየተሰማ ነው፡፡ ከተማዋን ለማስዋብ በሚል ሰበብ በመንገድ ላይ የሚገኙ አጥሮች ቀለም እንዲቀቡ ቀጭን መመሪያ
ተላልፏል፡፡ የመመሪያው መቅጠን ደግሞ መመሪያ አውጪውን አካል ትዝብት ላይ ጥሎታል፡፡ መመሪያው፣ “የሚቀባው የቀለም መለያ ቁጥር፣
የቀለም ቀቢውን ስልክ ቁጥር እና ስሙን ጨምሮ” እንደሚያስተላልፍ ያዛል፡፡ የሚገርም ጊዜ ላይ ደርሰናል ማለት ነው፡፡ ይህ ቀጭን
ትዕዛዝ የደረሳቸው አንድ ባለሆቴል ሰውዬ “ቀለሙን አስቀባለሁ እነርሱ ላዘዙኝ ቀለም ቀቢ ግን አስቀብቼ መመሪያ አውጪዎቹ ኮሚሽን
አይበሏትም” ነበር ያሉኝ፡፡ ህዝብ እንዲያስተዳድሩ በተለያዩ አጋጣሚዎች ቦታ የያዙ ሰዎች፣ ይህን ያህል የማሰቢያ አቅላቸውን የሚያስት
የጥቅም ግንኙነት እንዴት ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ማሰብ ይከብዳል፡፡ እንግዳ ሊመጣ ነው ቤት እናፅዳ ማለት የአባት ቢሆንም፣ በዚህ ደረጃ
መመሪያ ማቅጠን ግን ምክንያቱ ግልፅ ነው፡፡
የድሬዳዋ ከተማ በፅዳት እጅግ
ምስጉን እንደነበር ማንም ይመስክራል፡፡ ነበር ያልኩት ያለምክንያት አይደለም፡፡ አንደኛው ድሬዳዋ ውስጥ በአሁኑ ጉብኝቴ ከወትሮ
በተለየ የፅዳት መፈክሮች በብዛት መመልከቴን ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ በአጋጣሚ ወደ ጤና ቢሮ እና አካባቢው ጎራ ባልኩበት ጊዜ ከጤና
ቢሮ 50 ሜትር ርቀት በማይሞላ ቦታ ላይ መንገድ ዘግቶ የተከማቸውን ቆሻሻ እና በየውሃ መውረጃ የሚታየው ፍሳሽ ድሬዳዋን የሚመጥን
አለመሆኑን በመታዘቤ ነው፡፡ ወግ ደርሶን እኛም ድሮ ለማለት በቃን፡፡ ቆሻሻ የሚመጥነው ከተማ ባይኖርም፤ በፅዳት መፈክር ያበደችው
ድሬ አሁን ለከተሞች ቀን ለታሰበው ጽዳት ቀድመን እናቆሽሻት በሚል የተጠመደች ትመስላለች፡፡ በተለምዶ “ፋይናንስ” ተብሎ ከሚታወቀው
የከተማው አስተዳደር ምክር ቤት ከሚገኝበት መቶ ሜትር ርቀት ላይ አዲስ በሚገነባው ፍርድ ቤት ህንፃ አጥር ስር የተከማቸው ቆሻሻ
የአዲስ አበባን “ቆሼ” ያስታውሳል፡፡ ይህ እንግዲህ ከተማውን ለሚያስተዳድሩ አካላት ከእይታ ውጭ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ እነርሱ
ከቀለም ቀቢ የሚገኝ ኮሚሽን ላይ አፍጥጠው፤ የከተማውን ቆሻሻ የሚያነሳ ጠፍቶ የተለያዩ ሰበቦችን ይደረድራሉ፡፡
ድሬ ሲታሰብ የከዚራ ጥላውንም
ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ የድሬ ጥላ የነበሩት ዛፎች እየተመናመኑ፣ ቀድሞ የነበሩ ቤቶች እየፈረሱ፣ አዲስ ህንፃ በከዚራ ሊሰራ
የፈረሱ ቦታዎች ታጥረው ይገኛሉ፡፡ በአስደናቂ ፍጥነት የተጠናቀቀው የዳሽን ባንክ ህንፃም እንደተጠበቀው ለከዚራ ድምቀት አልሰጠም፡፡
ለአንድ የባጃጅ ሾፌር “ህንፃዎቹ ሲያልቁ ከዚራ ይደምቃል” የሚል አስተያየት ስሰጠው፣ የመለሰልኝ መልስ ይበልጡኑ አስገርሞኛል፡፡
ሾፌሩ፣ “በሲሚንቶ ክምር ከተማ አይደምቅም” ነበር ያለኝ፡፡ ‹‹እንዴት?›› ብዬ ጥያቄዬን ሳስከትል “ድሬዳዋ ፎቅ ሳይሆን ሰው
ነው የሚያስፈልጋት፤ ድሬዳዋ ማነው ፎቅ ላይ ወጥቶ የሚገበያየው?” ብሎ መልስ ሰጠኝ፡፡ ስለዚህ የድሬዳዋ ከተማ የነዋሪዎቿን ስነ-ልቦና
ያገናዘበ ግንባታ መሻቱን ተረድቻለሁ፡፡ ይህ ታዲያ የማን ኃላፊነት ነው? ብዬ ብቻዬን ስቆዝም፤ የባጃጅ ሾፌሩ በሀዘን ስሜት እንዲህ
አለኝ፤ “እነዚህ ሰዎች የድሮ ነገር አይወዱም፡፡ የነበረውን ባቡር ጣቢያ አፍርሰው ሌላ ይሰራሉ፤ ከዚራን አጥፍተው ሳቢያን እንዲለማ
ይፈልጋሉ፡፡ የድሮ ከዚራ እንዲኖር የሚፈልጉ አይመሰለኝም፡፡” በእውነትም ከዚራን ማፍረስ ለምን ቅድሚያ ተሰጠው? የሚል ጥያቄ ማንሳት
ያስፈልጋል፡፡
ከዚራን ከማፍረሱ ጎን ለጎን
ደግሞ በዚያ አካባቢ በብዛት በሚገኙት የኪራይ ቤቶች ውስጥ ያሉ ነጋዴዎች አስተዳደሩ ሌላ ስጋት ጋርጦባቸዋል፡፡ ቀደም ሲል ሲከፍሉት
የነበረውን በመቶዎች የሚቆጠር ኪራይ በመከለስ፤ ስምንትና አስር ሺ ብር እንዲከፍሉ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሰራ እንደሆነ በከተማው ይወራል፡፡
አንዳንዶች ከምርጫ በፊት ተግባራዊ ላያደርጉት ይችላሉ የሚል ተስፋ ቢኖራቸውም፤ የማይቀር ዕዳ ነው የሚሉት ያመዝናሉ፡፡ ለምን መንግስት
እንዲህ ያደርጋል ያልኳቸው አንድ ነጋዴ፤ “ለአባይ ግድብ ገንዘብ እስኪሞላ እኛ ማለቃችን ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተውኛል፡፡ ከዚህ
በተጨማሪም ነጋዴዎች በደረጃ ተመድበው የቦንድ ግዢ እንዲፈፅሙ፣ “የነጋዴዎች ተወካይ” የሚገኙበት ኮሚቴ ወስኗል የሚል መረጃ ደርሶኛል፡፡
ድሬዳዋ በመኖሪያ ቤት ችግር
ከሚጠቀሱ ከተሞች አንዷ እንደሆነች ይታወቃል፡፡ በድሬ ቀደም ሲል መንግስት ህጋዊ የመሬት እደላ በማቆሙ ምክንያት በችግር ተገፍተው
በህገ-ወጥ መንገድ የመኖሪያ ቤት ሰርተው ሲኖሩ የነበሩ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ወደህጋዊነት ከተቀየሩ በኋላ፤ መፍትሔ ይገኛል
ተብሎ ቢጠበቅም፣ የከተማው የመሬት አስተዳደር አሁንም የዘመቻ ስራው
አብቅቶ መደበኛ የቤት መስሪያ ቦታ የማይቀርብ በመሆኑ፣ በከተማው ዙሪያ አሁንም ህገ-ወጥ ግንባታዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው፡፡
ቀደም ሲል ለጥ ያለ ሜዳ የነበረው በምስራቅ በኩል የሚገኘው ወደ ሽንሌ መውጫ መንገድ፣ ያለ እቅድ በተሰሩ ጎጆዎች ታጉሮ የስደተኛ
መንደር ይመስላል፡፡ በፕላን የተጀመረች ጥንታዊቷ ከተማ ድሬ፤ ዛሬ በሃያ አንደኛው ክፍለ-ዘመን ያለፕላን በዘፈቀደ እየተለጠጠች
ትገኛለች፡፡ ድሬ ይህን ጉዷን በከተሞች ቀን ለሚታደሙት እንግዶች እንደማታስጎበኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ቀለም እየተቀቡ ያሉት የከተማው
ዋና ዋና መንገዶችም ለታይታ መሰራታቸው ያስታውቃል፡፡
መቼም ድሬዳዋ ሲነሳ የኢትዮ-ጅቡቲ
ምድር ባቡር ጉዳይ መነሳቱ አይቀርም፡፡ የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር እንዲሞት የተፈረደበት መሆኑ ግልፅ ቢሆንም፤ ለምን እንደሆነ
በውል ባልታወቀ ምክንያት ከድሬዳዋ ጅቡቲ አንድ ባቡር ማንቀሳቀስ ተጀምሮ እንደነበር በሚዲያ ሲራገብ ነበር፡፡ የድሬዳዋ ነዋሪም
አዲሱ ባቡር ስራ እስኪጀምር ድረስ በዚሁ ማዝገም ጥሩ ነው ብሎ ሲጠብቅ፣ በግለሰቦች ግጭት ምክንያት አሁንም እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ከመተሃራ በሰቃ ሀይቅ ጀምሮ ከመቶ ኪሎሜትር በላይ የሚሆን ሀዲድ ለማደስ፤ ከጣሊያን ኩባንያ ጋር በቢሊዮን የሚገመት
ብር የወጣበት ፕሮጀክት አንድም ጥቅም ሳይሰጥ ተጠናቋል፡፡ ይህ ሁሉ የሀገር ሀብት እንዲባከን የተደረገበት ምክንያት ተድፈንፍኖ
መቅረቱ ግን በዚህች ሀገር ተጠያቂነት እንደሌለ ጉልህ ማሳያ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ድሬዳዋ መስመር አግልግሎት መስጠት ካቆመ ብዙ
ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን፤ የባቡር ሀዲዶቹም አልፎ አልፎ መሬት ውስጥ እየተቀበሩ ቀሪዎቹም እየተዘረፉ እንደሚገኙ የድርጅቱ ሰራተኞች
በምሬት ይናገራሉ፡፡
የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት
በህግ እስከአሁን ባይፈርስም፣ ሰራተኞቹን በሙሉ ተረክቦ ያለስራ ደሞዝ የሚከፍለው የብረታ ብረትና ኢንጂነርኒግ ኮርፖሬሽን ነው፡፡
ይህ ኮርፖሬሽን ለምን እዚህ ግቢ ውስጥ ገባ ለሚለው ጥያቄ ብዙ መላ ምቶች ቢኖሩም፣ ብዙዎች የሚሰጡት ምላሽ በኢትዮ-ጅቡቲ ምድር
ባቡር ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኘው ለመቶ ዓመት የተከማቹ ብረታ-ብረቶች እና ሌሎች ማሽኖች ያለምንም ስርዓት የሚገኙበት መሆኑ ይጠቀሳል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከሚከፍለው ደሞዝ ጋር ሲነፃፀር የሚገኘው ጥቅም ከፍተኛ ስለሆነ መግባቱ አያስገርምም የሚሉት ይበዛሉ፡፡ በዋነኛነት የሚያነሱት
ጥቅሙም እንደተቋም ለድርጅቱ ተገበያይቶ ሳይሆን ለህገ-ወጥ አሰራር የተመቸ መሆኑን ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ በሀገር ውስጥ የወዳደቁ ብረታ-ብረቶቸን
ከመንግስት ተቋማት ያለምንም ውድድር ይሰበሰብ እንደነበረና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለከፍተኛ ሙስና የተጋለጠ ነው በሚል ከፀረ ሙስና
ኮሚሽን በቀረበ ሪፖርት መነሻ፤ ከመንግስት ተቋማት ግዢ እንዲያቆም መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑንም እንደማግኔት ብረት ይስባል
ይሉታል፡፡
ድሬዳዋ ለደረቅ ወደብ ዋነኛ
ተመራጭ ብትሆንም፣ እስከ አሁን ድረስ በጊዜያዊነት ካልሆነ በቀር የደረቅ ወደብ አገልግሎት እንድትሰጥ አልተደረገም፡፡ በከተማ ምስረታ
ታሪክ ረዥም ዕድሜ ያካበተችው፣ በአንፃራዊነት የተሻለ አገልግሎት መስጠት የምትችለው ድሬዳዋ ተዘላ፤ “ሞጆ” የደረቅ ወደብ እንድትሆን
መመረጧ ድሬዎችን ያስገርማቸዋል፡፡ በተለይ የጅቡቲ ድሬዳዋ ምልልስን በማፋጠን፣ ከፋተኛ ጭነት የሚጭኑ መኪኖችን ውጤታማነት ለማሳደግ
እና በሀገር ውስጥ የስርጭት ስራ ላይ የሚሳተፉ መካከለኛ የጭነት መኪኖችን ተሳትፎ ለማጎልበት የሚረዳው የድሬዳዋ ደረቅ ወደብ አገልግሎት
ለምን ችላ እንደተባለ ምላሽ የሚሰጥ የለም፡፡ መልሱ፣ ‹‹አቦ ድሬ ባለቤት የላትም!›› የሚል ነው፡፡ በድሬ የደረቅ ወደብ ግንባታ
እንደሚከናወን በአንድ ወቅት የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩት አቶ አባይ ፀሐዬ ሲናገሩ በአጋጣሚ በቦታው የነበርኩ ቢሆንም፤
ተመሳሳይ ቃል በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርም ተገብቶ እንደነበረ የከተማው ነዋሪዎች በቁጭት ያሰታውሱታል፡፡
ድሬዳዋ ለጅቡቲ ካላት ቅርበት
አኳያ ወደውጭ የሚላክም ሆነ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል ምርት ለሚያመርቱ
ኢንዱስትሪዎች መንደር ዝግጅት ደፋ ቀና ብትልም፤ በኢትዮጵያ ያለው የኢንቨስትመንት አየር ከአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ዙሪያ
ለመውጣት ገና ብዙ እንደሚቀረው ዋና ማሳያው ድሬዳዋ ነች፡፡ ድሬን ድሮ እና ዘንድሮ ስናያት እዚህም እዚያም ከበቀሉት ጥቂት ህንፃዎች
እና የኮብል ስቶን መንገዶች ውጭ፣ ለነዋሪው በሚመጥን ልክ የኢኮኖሚ እንቅሰቃሴ ማየት አይቻልም፡፡ ድሬ አሁንም በጊዜያዊነት የከተሞችን
ቀን ወይም ሌላ በዓልን ለማስተናገድ ከሚደረግ ሽር ጉድ ወጥታ ለዘላቂ የነዋሪዎች ተጠቃሚነት የሚሰራ አስተዳደር ያስፈልጋታል፡፡
ገዢው ፓርቲ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን
በኮሚቴ የሚያስተዳድራት ድሬዳዋ፣ ከሃያ ዓመት በላይ በቁልቁለት ጉዞ ውስጥ ለመገኘቷ ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ ይህ የቁልቁለት መንገድ
ደግሞ የተቀየሰው በገዢው ፓርቲ እና ሃላፊነት አለብኝ በሚለው የፌዴራል መንግስት አማካኝነት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ድሬዳዋ በህገ-መንግስት
የተቋቋመው የመንግስት መዋቅር አካል አይደለችም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ለምን በፌዴራል ከተማነት ተመደበች? ብሎ ቅሬታ ያለው ባይኖርም
ለእድገቷ የሚያስብላት የድሬዳዋ ልጅ የሌለ ይመስል፤ አባል ድርጅቶች ከክልሎቻቸው በሚመድቧቸው ካድሬዎች ውክልና መተዳደሯ፣ ከተማዋን
የሚመጥን ዕድገት ላለመምጣቱ አንዱ መንስዔ ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ በድሬዳዋ እና በሀረር የሚደረጉ ምርጫዎች በህዝብ ፍላጎት
ሳይሆን በድርጅታዊ አሰራር የሚወሰኑ መሆናቸውም ጉልህ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ከተማይቱ፣ ኦሮሞና ሱማሌ ተራ በተራ በከንቲባነት የሚያስተዳድሯት
ምስኪን ከተማ ነች፡፡ ለማንኛውም፣ የህዝብ ምርጫ እንዲከበር በዘር ሳይሆን በድሬዳዋ ልጅነት ወንበሩ ክፍት ይሁን፡፡ የድሬ ልጆችም
ለከተማቸው ራዕይ ሊኖራቸው እንደሚችል ጥርጥር የለውም፡፡ ዋናው ጭብጥ ግን፣ የድሬ ልጆች የግል ነፃነትን ለሚቀማው ኢሕአዴግ አባል
ለመሆን አለመመቸታቸው ነው፡፡
No comments:
Post a Comment