Sunday, August 17, 2014

የግል ሚዲያዎች ክስ ለምን?


በዚህ የፋክት ዕትም ከ“ግል ሚዲያ” ውጪ ስለ ሌላ ነገር መፃፍ ትክክል መስሎ አልታየኝም፡፡ ይህን ሳስብ ደግሞ ባለፈው ዕትም በፋክት መፅሔት በከፊል የተነሳውን የኢህአዴግ የፖሊሲ ወረቀት “የዴሞክራሲ ሰርአት ግንባታ ትግልና አብዮታዊ ዲሞክራሲ” በሚል በመጋቢት 1999 ዓ.ም የወጣውን መሰረት ማድረግ ወሰንኩ፡፡ ከዚህ የፖሊሲ ወረቀት ውስጥም “ሚዲያና ዲሞክራሲ” በሚለው ንዑስ ርዕስ ላይ አተኩራለሁ፡፡ ለዚህም ምክንያቴ፣ አሁን መንግስት እንደሚለው እየወሰደ ያለው እርምጃ  ህግን የማስከበርና የህዝብ ጥያቄን የመመለስ ሳይሆን፤ በፖለቲካ ሰነዱ ላይ ያስቀመጠውን በግል ሚዲያዎች ላይ መወሰድ ያለበት ተከታታይ እርምጃ ክፍል መሆኑን በመጥቀስ ይህን የፖለቲካ ሰነድ አግኝተው ለማንበብ እድል ላልገጠማቸው አንባቢያን ማስረዳት ነው፡፡ ከዚያም በማስከተል ይህ ሰነድ፣ በፈለገው መንገድ ተተርጉሞ ህገወጦች ይለናል በሚል ነፃነታችንን አሳልፈን ለመስጠት አለመዘጋጀታችንን ይፋ ለማድረግ ነው፡፡ ነፃነት በነፃ አይገኝምና፡፡
ይህ የምርጫ 97 ዝረራ የወለደው የፖለቲካ ሰነድ ሚዲያን በሚዳስስበት ንዑስ ክፍል መግቢያ ላይ “ሚዲያ የዴሞክራሲ ስርአትን በመገንባት ረገድ ወሳኝ ድርሻ ካላቸው ተቋሞች አንዱ ነው” ብሎ የሚጀምር ቢሆንም፤ ዋና ግቡ ግን ሚዲያን እንዴት ማጥፋት እንደሚቻል የሚተነትን ነው፡፡ የሩዋንዳን እልቂት ፈጣሪ ሚዲያዎችን ፣ የምዕራባዊያንን የሚዲያ ተቋማትን እንዲሁም በአረቡ ዓለም ያሉትን አልዓረቢያና አልጀዚራን የመሳሰሉ ሚዲያዎችን በመጠቃቀስ “ኪራይ ሰብሳቢ ሚዲያዎች” የሚል ፅንሰ ሀሳብ ለማዋለድ በሚረዳ መልኩ “የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካ ኢኮኖሚ በልማታዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ በተሟላ መልኩ መተካት አለበት” ብሎ ይደመድማል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላ ኪራይ ስብሳቢ ሚዲያ ሲባል አቤት ማለት ይኖርብናል፡፡ ልዩነት ለዘላለም ይኑር ብለን የምንዘምር ሰዎች የኢህአዴግ “ልማታዊ ፖለቲካው ኢኮኖሚ”ን እንደ አንድ አስተሳሰብ መቀበል ብንችል እንኳን፣ ይህን አስተሳሰብ ለራሳችን ለማድረግ የምንቸገር ሰዎች አለን፡፡ ይልቁንም ከዚህ የተሻለ አማራጭ አለን ስንል፣ ይህ አስተሳሰብ በኢህአዴጎች ሰፈር “ኪራይ ስብሳቢነት” ቢሆንም በነፃነት ልናራምድ የምንችልበትን መድረክ ለመንፈግ፣ ይህ ሰነድ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡
የሚዲያ ነፃነትና የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታን በሚመለከት የፖለቲካ ሰነዱ  “ሚዲያውን በነፃነትና በጤናማ አኳኋን እንዲያድግ ማድረግ ለማንም ሲባል የሚሰራ ስራ ሳይሆን በአገራችን የዴሞክራሲ ስርአትን እውን ለማድረግ ተብሎ የሚከናወን በመሆኑ ለሌሎች የዴሞክራሲ ሰርአት ግንባታ ስራዎች ከምንሰጠው ትኩረት የማይተናነስ ትኩረት ለዚህም ስራ መሰጠት አለበት” ይላል፡፡ ይህን አባባል በጥሬው ስንመለከተው ምንም ክፋት የለበትም፡፡ ነገር ግን ምን ዓይነት ‹ነፃነት› እና ምን ዓይነት ‹ጤንነት› እንደሆነ ስንመረምር ችግሩን መረዳት ይቻላል፡፡ ኢህአዴግ ሌሎችንም የዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ማለትም የብዙኃን ማኅበራትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የህዝብ ምክር ቤቶች እንዲሁም የዳኝነት ስርዓቱን ምን ያህል ነፃነት እየከለከለ ጤና እንደሚነሳቸው ስንረዳ፣ ምን ዓይነት ነፃነትና ጤና እንደታዘዘልንም መረዳት ቀላል ነው፡፡ የግል ሚዲያውም ከላይ እንደገለፅኳቸው የዴሞክራሲ ተቋማት ሸፋፋ እንዲሆን የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንገኛለን፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግ ሚዲያውን እንደሌሎቹ የዲሞክራሲ ተቋማት ሙት እንዲሆን መፈለጉን እንረዳለን፡፡ በሙታን ውስጥ የሚገኝን ነፃነት እና ጤና የሚያውቁት ሙታኖች ብቻ ናቸው፡፡
ኢህአዴግ እንደ መንግስት የሚዲያውን አቅም መገንባት ሳይሆን እንዴት አድርጎ መዋጋት እንዳለበት በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ይህንንም ለማድረግ በፖለቲካ ሰነዱ ውስጥ የተቀረፀውም በአቅም ግንባታ ሞዴል ሳይሆን በውጊያ ሞዴል ነው፤ “ኪራይ ስብሳቢነትን መዋጋት” በሚል ርዕስ ነው የተቀመጠው፡፡ በዚህ ንዑስ ርዕስ ስር በዋነኝነት የተቀመጠው የውጊያ ግንባር “የሚዲያ አውታሮች ገቢና ወጪያቸውን በትክክል እንዲያስመዘግቡና በየጊዜውም ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግበት ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡” ይላል፡፡ ይህም የሚረዳው “በውጭ ሃይሎችና በፀረ ሰላም ድርጅቶች ፋይናንስ እንዳይደረግ በጥብቅ መከላከልና መቆጣጠር በጣም አስፈላጊ ይሆናል፡፡” በሚል ነው፡፡ ይህን በተመለከተ በግል ሚዲያዎች ላይ ማስረጃ ማቅረብ የተሳነው መንግስት በቴሌቪዥን በኩል ለሆዳቸው ያደሩ ሹሞችን እና ባለሞያ ነን የሚሉትን ሰብሰቦ በዘጋቢ ፊልም ‹‹መረጃ አለን፤ ከሚያትሙት አርባ አምስት ሺ፣ ሁለት ሺውን ብቻ ነው የሚሸጡት›› የሚል ፕሮፖጋንዳ ለመስራት ይዳክራል፡፡ ማስረጃ ማቅረብ ያልቻለ መንግሰት ‹መረጃ› እያመረተ ይገኛል፡፡ ወደፊት እነዚህ መረጃዎች በማስረጃ ደረጃ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ብለን ብንጠረጥር አስገራሚ አይሆንም፡፡ ለነገሩ ያቃጥሉት ነበር የሚል አዳፍኔ ምስክር ይጠፋል ብላችሁ ነው፡፡
በዚህ መስመር አንድም ማስረጃ ማግኘት የተሳነው መንግስት፣ በቀጣይ በሚዲያ ተቋማት ላይ ከማስታወቂያ እና ከአንባቢ በሚገኝ ገቢ ላይ እርምጃ መውሰድን እንደ ዋነኛ የኢኮኖሚ ቁጥጥር ስርአት አድርጎ ይዞታል፡፡ አንባቢዎችም እንደምትረዱት የመንግስትና የግል ድርጅቶች ማስታወቂያ እንዳያወጡ ከፍተኛ ጫና በመዳረጉ አሁን ጥርስ የተነከሰባቸው መፅሔቶች ማስታወቂያ ሳያወጡ በመፅሃፍ መግዣ ዋጋ መፅሔት ለመሸጥ በመገደዳቸው መንግስት ወደ ሌላ እርምጃ ተሸጋግሯል፡፡ ሌላኛው እርምጃ ከሰሞኑ የተሰማው ክስ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ነውረኛ የፖለቲካ ሰነድ ጥርስ የተነከሰባቸውን የግል ሚዲያዎች የሚገልፃቸው ነውረኛ በሆነ አገላለፅ ነው፡፡ በኢህአዴግ ሰፈር መገበርም አያስከብርም፡፡ እነዚህ የግል ሚዲያዎች አብዮታዊ ዲሞክራሲን ባይቀበሉም የመንግሰትን ስትራቴጂ የተቀበሉ ኪራይ ስብሳቢዎች በማለት ይገልፃቸዋል፡፡ ለእነርሱም “በሕጉ መሰረት የሚሰሩ ጥገኞችን በተመለከተ ግን ለስራቸው የተመቻቸ ሁኔታ የመፍጠር አሰራር ልንከተል ይገባናል” በማለት ይሰድባቸዋል፡፡ በቅርቡ ለነዚህ ጥገኞች ምን ተጨማሪ ነገር እንደሚደረግላቸው የምናየው ይሆናል፡፡ እንደምታስታውሱት ለጥገኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጎማ ሲሰጣቸው፣ የሌሎቹ ፓርቲ አባላት ደግሞ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡
በኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር ያልገባ ሁሉ ህገወጥ እና ጤና የሌለው ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ በዲሞክራሲ፣ ሰላም እና ነፃነት ላይ የቆመ ደንቃራም አድርገው ይቦድኑታል፡፡ ህዝቡ ኢህአዴግ የሚያወራውን ይህን ሽብርና መዓት ወደ ጎን በማለት ኪራይ ሰብሳቢ ለሚላቸው የግል ሚዲያዎች መተማመኛው የፈለገውን ያህል ውድ ቢሆኑ፣ ተሻምቶ በመግዛት የአለንላችሁ መተማመኛ መስጠቱ አልተዋጠላቸውም፡፡ ሹሞቻችን ይህን የህዝብ መተማመኛ ተቀብለው ለመሄድ ፈቃዳቸው አይደለም፡፡ ይልቁንም ከህዝብ ውጭ አለቃ የለንም እያሉ በየመድረኩ የሚገዘቱ ሹማምንት፤ ህዝብን በሚንቅ መልኩ፤ ‹በህዝብ ጥያቄ መሰረት በግል ሚዲያዎች ላይ እርምጃ ወስደናል› ይሉናል፡፡ ህዝቡ እርምጃው ለምን ተወሰደ ሳይሆን የሚለው ለምን ዘገየ እያለ ነው፡፡ ህዝቡ፣ ህዝቡ፣ ህዝቡ እያሉ በመንግሰት ሚዲያ ላይ ቀርበው ይዘባበታሉ፡፡
ለማንኛውም ከላይ እንደተረዳነው የኢህአዴግ የፖለቲካ ሰነድ የሚያስቀምጠው “ዋነኛው መቆጣጠሪያ መንገዱ ኢኮኖሚያዊ ስለሆነ … ልዩ ትኩረት ሰጥተን ልንረባረብበት ይገባል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በህገወጥ ሚዲያዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው የሚደረገው ሂደት በአስተዳደራዊ ገፅታው ብቻ ሳይሆን በፖለቲካው ገፅታው መታየት አለበት፡፡” በማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሰሞኑን እየተወሰደ ያለው እርምጃ በምንም መመዘኛ የግል ሚዲያዎቹ በሀገርና በህዝብ ላይ ሽብር በመፍጠራቸው ሳይሆን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ላይ በፈጠሩት ሽብር መነሻ ብቻ ነው፡፡ እርምጃውም ፖለቲካዊ በመሆኑ፣ ከቀጣዩ ምርጫ ጋር ተያይዞ በመጣ ፍርሃት የተነሳ ነው፡፡ ስለዚህ የግል ሚዲያዎች ለአብዮታዊ ዲሞክራሲ አንገብርም በማለታቸው “ህገወጥ” በሚል ሽፋን አስተዳደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩትም፣ ይህ አቅጣጫ የተቀመጠው በመጋቢት 1999ዓ.ም ከምርጫ 1997 ሽንፈት ማግስት ነው፡፡
ይህ ጉደኛ ሰነድ “አስተዳደራዊ እርምጃ ተገቢ መሆኑን ህዝቡና ከዚያም አልፎ ብዙሃኑ የሚዲያው ተዋንያን የሚቀበሉበት ሁኔታ መፍጠር አለብን፡፡” ይላል፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ፣ መንግስት ወገቡን ታጥቆ እርምጃው ተገቢ ነው እያለ የሚሰብክን፡፡ ይህን ድራማ ለመስራት የሚጋበዙትም ሰዎች ይህን መረዳት ያለመቻላቸው አስገራሚ ነው፡፡ ሰነዱ በመጨረሻም “ለውጭው አለም በዚህ ረገድ የምንወስዳቸውን እርምጃዎች ተገቢነት ለማስረዳት ጥረት ማድረግ ያለብን ቢሆንም ጋዜጠኞች በምንም አይነት ምክንያት መታሰራቸውን የማይቀበሉ ሃይሎች በርካታ በመሆናቸው እነዚህን ለማሳመን ከመንገዳችን ወጥተን መሄድ የሚጠይቀን መኖር የለበትም፡፡” ብሎ ያጠናቅቃል፡፡ አንድም ጋዜጠኛ፣ ጋዜጠኛ በመሆኑ አይታሰርም በሚል ድርቅ ብለው የሚከራከሩን ሹሞቻችን ጋዜጠኞችን ለምን እንደሚያስሩ ግን በሰነዳቸው ላይ በፅሁፍ አስቀምጠዋል፡፡ ጋዜጠኞች የሚታሰሩት በጋዜጠኝነታቸው ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው በያዙት አመለካከትም ጭምር ነው፡፡ ጥገኛ ለመሆን ባለመፍቀዳቸው እና ለነፃነታቸው በመቆማቸው ነው፡፡

እንግዲህ አስተዳደራዊውን እርምጃ ተከትሎ የሚመጣው  እስር መሆኑን ልብ ማለት አለብን፡፡ የዚያን ጊዜ ደግሞ ኢህአዴግ ከመስመር መውጣት ሳያስፈልገው “ጋዜጠኛ አላሰርንም፣ ጋዜጠኛ መሆን ወንጀል ለመስራት ሰርተፊኬት አይደለም” እያለ በመስመሩ ላይ ሆኖ ያላግጣል፡፡ ለማነኛውም በፖለቲካም ሆነ በጋዜጠኝነት ተሳትፎ የሚያደርጉ ሁሉ፣ የሚሳተፉት ይህ ጠፍቷቸው ሳይሆን ነፃነታቸው ከዚህ በላይ መሆኑን የሚረዱ በመሆናቸው ነው፡፡ ለነፃነት ሲባል ከእስርም በላይ ሞትን ለመቀበል የቆረጠን ሰው ማቆም እንደማይቻል መረዳት ግን ተገቢ እና አስፈላጊ ነው፡፡ይህን ፅሁፍ ለምታነቡ የኢህአዴግ አባላት አንድ ጥያቄ አለኝ፤ “ከጥገኝነት እና ከነፃነት” የቱ ይሻላል?

No comments:

Post a Comment