Saturday, December 19, 2015

የዲሞክራሲ መብት መሳሳት ጭምር ነው!!! ግርማ ሠይፉ ማሩ




ሰሞኑን በሀገራቸን ያለው ትኩሳት በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው በአብዛኛው ተማሪውን ያሳተፈው “እንቢ የተቀናጀ ማስተር ፕላን” በሚል የተነሳው ንቅናቄ ነው፡፡ ለዚህ ንቅናቂ መንሰዔ ናቸው በሚል የኦሮሚያ ክልል እና የፌዴራል መንግስቱ ከፍተኛ የኦህዴድ ሾሞች መግለጫ እየሰጡ ይገኛል፡፡ በእነሱ መግለጫ መሰረት ደግሞ ጥያቄው ከዚህም አልፎ የመልካም አሰተዳደር ጭምር መሆኑን አምነዋል፡፡ ሁላችንም እንደምናሰተውለው ኦህዴድ ውስጥ የሚታየው ከፍተኛ የተማረ የሰው ኃይል እጥረት ከተወሰኑ ሰዎች ውጭ ለማየት እድል አልሰጠንም፡፡ ይህ ባጠቃላይ በኢህአዴግ ውስጥ ያለ ችግር ነው፡፡ የዚህ ችግር ምንጭ ገዢው ፓርቲ የሚከተለው መስመር ለተማረ ቀርቶ ለሚያመዛዝን ሰው እንኳን ምቾት የሚሰጥ አለመሆኑ ነው፡፡ ኤርሚያ ለገሠ የሚባለው የቀድሞ ኢሕዴግ ሹም ሂሣብ ተምረህ እንዴት ኢህአዴግ ሆንክ? የሚል ጥያቄ እንደቀረበለት ሰምቻለሁ፡፡ ይህን ለዛሬ እንለፈው፡፡
ሰሞኑን በተፈጠረው ንቅናቄ ሁለት ጎራ ተፈጥሮዋል፡፡ አንዱ መንግስት ያወጣውን የተቀናጀ ፕላን እንደወረደ ደጋፊ ሲሆን ሌላው ደግሞ እንደወረደ ተቃዋሚ፡፡ ከዚህ ውጭ ሃሳብ መያዝ በሁለቱም መስመር “ፀረ ህዝብ” በሚል ያስፈርጃል፡፡ ይህ ፅንፍ ግን ፀረ ኃሳብ በመሆኑ፣ በእኔ እምነት ተቀባይነት የለውም፡፡ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የግሌን ሃሳብ ላክፍላችሁ የወደድኩት እዚህም እዚያም በፌስ ቡክ የሰጠሁትን ሃሳብ ለማጠናከር ጭምር ነው፡፡ በእኔ እምነት አሁን የተፈጠረው ችግር የኢህአዴግ እና በሽግግር ጊዜ ጀምሮ ኢህአዴግ ህገመንግሰቱን ሲያረቅ አባሪ ተባባሪ የነበሩ ቡድኖች የተከተሉት የፖለቲካ መስመር ችግር ውጤት ነው፡፡ ማለትም አሁን መንግሰት እተገብረዋለሁ የሚለው ዕቅድ ለማሳረፍ የሚፈልግበት የመሬት ፖሊስ አሁን እየተቃወመ የሚገኘው ኦነግ በዋነኝነት የተሳተፈበት የሽግግር ወቅት ሃሣብ ነው፡፡ የመድረክ አባል ድርጅቶች በሙሉ (የቀድሞ አንድነትን ሳይጨምር) የዚህ ፖሊሲ ደጋፊዎች ናቸው፡፡ አሁንም በፊት አውራሪነት የሚቃወመው የዶክተር መረራ ጉዲና ኦፌኮ ጭምር መሬት የመንግሰት መሆኑን ከምር ይደግፋል፡፡ በቅንፍ ውስጥ ኦሮሞው መሬት እንጂ ገንዘብ ስለሌለው እንዳይፈናቀል በሚል የተሳሳተ ታሳቢ ማለት ነው፡፡
የኦሮሚያ ርዕሰ መሰተዳድር እንዲሁም አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ በተከታታይ በሰጡት መግለጫ ህዝበ ካልተሰማማ “ይህ የተቀናጀ ማስተር ፕላን” ተግባራዊ አይሆንም የሚል ቃል ሰጥተዋል፡፡ ይህን ቃል ሲሰጡ በተለይ ለአባዱላ ጋዜጠኛው ተገዳችሁ ነው ወይ? ስትላቸው አዎ የመረጠን ህዝብ ቢያስገድደን ምን አለበት ብለው መልስ ሰጥተዋል፡፡ ይህን መልስ ወድጄዋለሁ፡፡ በፌስ ቡንክ ቋንቋ ላይክ አድርጌዋለሁ፡፡ ከአሁን በኋላ ታዲያ ይህን ማሰገደድ በመቀጠል አንድ ደረጃ ከፍ በማድረግ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚኖሩ የኦሮሚያ ልጆች ገበሬ ሆነው እንዳይቀሩ፤ ከከተሜነት ትሩፋት እንዲቋደሱ መሬታቸው አሁን ከሚባለው የመጠቀም መብት ከፍ እንዲል የመሸጥና መለወጥ መብት እንዲጨምር የፖሊሲ/ህገ መንግሰታዊ ማሻሻያ/ እንዲደረግ መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በለገጣፎ አካባቢ አንድ ካሬ ሜትር ቦታ ከስምንት ሺ ብር በላይ መንግሰት መሸጡን ሰምተናል፤ ሰለዚህ መንግሰት ቢያንስ ከገበሬው በአንድ ሺ ብር ለመግዛት መዘጋጀት ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ ካልሆነም መንግሰት ማስተር ፕላኑን ሰርቶ መሰረተ ልማቱን ይዘርጋ ለማልምታ የሚፈልግ ደግሞ ከገበሬው ጋር ተደራድሮ ይግዛ፡፡ መቼም ይህቺ የኒዎ ሊብራል አስተሳስብ የምትዋጥ አትመስለኝም፡፡ ጉዳዩ ግን ይህው ነው፡፡ የተቀናጀ ማስተር ፕላን የሚቃወሙ ወገኖች በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ አርሶ አደሮች ባሉበት ሁኔታ እንዲቆዮ ከሆነ በእርግጥ የአስተሳሰብ በሸታ ያለበት መሆን አለበት፡፡
ሌላው  መነሳት ያለበት ጉዳይ እና ለገዢው ፓርቲም ግልፅ መደረግ ያለበት “ውይይት ተደርጎ ህዝቡ ካመነ ብቻ ነው የሚተገበረው” የሚለው የርዕሰ መስተዳድሩ ፈራ ተባ እያሉ የሰጡት መግለጫ እና አፈ ጉባዔው በተመሳሳይ ፈራ ተባ ሲሉ የገለፁት ጉዳይ ነው፡፡ በኢቲቪ የርዕሰ መሰተዳድሩን መግለጫ ተከትሎ በተያያዘ ዜና በሚል የኢህአዴግ ዝቅተኛ ሹሞች “ይህ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ለአርሶ አደሩ ጠቃሚ ነው” በሚል መንፈስ በተቃውሞ የቆሙ ፀረ -ሰለም እና ፀረ-ህዝብ መሆናቸውን ሲገልፁ ነበር፡፡ ኦህዴድ/ኢህአዴግ ከዚህ በፊት ባለው ታሪካቸው አቶ አባዱላ እንደሚሉት አሳምነው ሳይሆን አስገድደው በመስራት ነው የሚታወቁት፡፡ አስገድደው እንደተመረጡም ረስተውት በተደጋጋሚ የመረጠን ህዝብ ሲሉ ሰው ይታዘበናል ማለት የተዉ ይመስላል፡፡ ሰለዚህ ህዝቡን ለማሳማን ኢህአዴግ ያመነበትን ማስተር ፕላን ይጠቅምሃል ተቀብል ሳይሆን፤ ውይይት ሲባል ለማሳመን ብቻ ሳይሆን ለማመንም ተዘጋጅቶ መሄድን ይጠይቃል፡፡ በነገራችን ላይ በብዙ መስፈርት ጠቃሚ መሆኑ ግንዛቢ ኖሮ ቢሆን እንኳን በማነኛውም ተራ ምክንያት አልቀበልም ካለ ይህን ለመቀበል ኢህአዴግ መዘጋጀት ያስፈልገዋል፡፡ ዲሞክራሲ ማለት መሳሳት ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ የተቀናጀ ማሰተር ፕላኑ በግልፅ ባልታወቀ ይዘቱ ጠቃሚ መሆኑ ቢታመን እንኳን አሁን ባለው የመሬት ፖሊሲ ቢተገበር የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርገው ከመሬቱ ከሚፈናቀለው አርሶ አደር ይልቅ ሌላውን ክፍል ነው የሚል አስተሳሰብ በፍፁም ውድቅ ሊደረግ የሚችል ምልከታ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው አሁን የተፈጠረው ችግር መሰረታዊው መንሰዔው ህገ መንግሰታዊ መሰረት የያዘው የዜጎችን ንብረት ማፍራት መብት የሚፃረራ የመሬት ባለቤትነት መብት ነው የምለው፡፡ ሰለዚህ ትግላችን መሆን ያለበት ዜጎችን ባለሀገር የሚያደርግ የመሬት ፖሊስ እንዲኖረን በሚያስችል ሁኔታ ህገ መንግሰታዊ ማሻሻያ መጠየቅ ነው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በዚሁ ጥያቄ መነሻነት አብዮት እንዲነሳ የሚፈልጉ መኖራቸው አንዱ የሚታወቅ ነገር ነው፡፡ ይህ መንግሰት በሰላማዊ መንገድ ለውጥ እንዲመጣ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እየተሳነው መሆኑን እረዳለሁ፡፡ ይህ ማለት ግን ኢህአድጋዊያንን ሊጠርግ የሚመጣ አብዮት ሰለማዊውን ዜጋ እንደማይበላ ማረጋገጫ ሰለሌለኝ አብዮትን አልወዳትም፡፡ በቅርቡ የታተመውን የቀድሞ የደርግ ከፍተኛ ሹም የነበሩት ፍስሃ ደስታ “አብዮቱና ትዝታዬ” በሚል የፃፉትን መፅሃፍ እያነበብኩ አብዮቱ እንዴት አድርጎ ዜጎችን ሲቀረጥፍ እንደነበር ሳነብ ዳግም አብዮት የሚያሰኝ ነገር አልታየኝም፡፡ ገዢው ፓርቲ መሪዎች ይህን የሚያክል ጥራዝ ለማንበብ ጊዜም ሆነ ሞራል ባይኖራቸው እንኳን የዚህን መፅሃፍ መጨረሻ ክፍል ማጠቃለያውን አንብበው ለብሔራዊ ዕርቅ ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ እፈልጋለሁ፡፡ እዚሁ መፅኃፍ ላይ አንባገነኑ መንግሰቱ የሚሰጠወን መክር አልሰማ ብሎ በመጨረሻ ደቂቃ ላይ ቢወራጭም መፍትሔ ሊያመጣ እንዳልቻልም፡፡ ኢህአዴግም እድሉን ቢጠቀምበት ጥሩ ይመስለኛል፡፡
በሀገራችን ያሉ ተቃዋሚዎች አብዛኞቹ በሚያሳዝን ሁኔታ የሚገኙ መሆናቸው የሚያጋልጠው የሰሞኑን ክስተት አስመልክተው የሚሰጡት መግለጫ በፍፁም ፓርቲያቸው ቆሜለታለሁ ከሚለው መርዕ ጋር የሚሄድ አለመሆኑ ነው፡፡ እነዚህን ፓርቲዎች ይህን አስታካው ህዝቡን ወደ ለውጥ እንዲመሩ አንድ አንድ ግለሰቦች/ቡድኖች ጥሪ እስከ ማቅረብ ደርሰዋል፡፡ እንኳን ሊመሩ መሪ የሚያስፈልጋቸው ደንባሮች እንደሆኑ ግን መግንዘብ ያልቻሉት ጥሪ አቅራቢዎቹ ናቸው፡፡ ለማነኛውም አብዮት እንደ ቱኒዚያው ቡሃዚዝ አይነቱ በሚጭሩት ትንሽ ጉዳይ ነገር ግን ሁሉም በሚሳተፍበት ሁኔታ ሊነሳ እንደሚችል ባምንም፤ አሁን ባለው ያልተቀናጀ ሁኔታ ባልጠራ መንገድ እብዮት መጥራት ሀገርን አደጋ ላይ ሊጥል ይቸላል የሚል የግል እምነት አለኝ፡፡ ይህ ግን በፍፁም አንባገነኖችን እሺ ብለን  እንገዛ ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ የሰሞኑ ጥያቄ በመሰረታዊነት በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ በኦሮሚያ አርሶ አደሮች መፈናቀል የለባቸውም የሚል ነው፡፡ በተመሳሳይ በከተማ ያለም ነዋሪ ተገቢ ካሳ ሳይከፈለው በልማት ሰም መነሳት የለበትም ማለት ይኖርብናል፡፡ በሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች በከተማ ማሰፋፋት ስም እየተነሱ ያሉ ሰዎች ተገቢ ካሳ ሊያገኙ ይገባል ማለት ይኖርብናል፡፡ በዚህ መንፈስ ጥያቄው ከተነሳ በከተማም በገጠርም ያለነው በጋራ ለመቆም እድል ይስጠናል፡፡
በመጨረሻ በመላው ሀገሪቱ ጥያቄያቸውን በተለያየ መንገድ ያቀረቡ ወጣቶች ህይወት በአንባገነኖች ጥይት እንዲቀሰፍ እርምጃ የወሰደው መንግሰት ከሃያ ዓመት በኋላም ግጭቶችን በጉልበት እንጂ በሰላማዊ መንገድ ለመቆጣጠር አቅም እንደሌለው ማሳያ ነው፡፡ እነዚህ ግድያዎች ደግሞ በፍፁም የሚረሱና የሚተዉ አይደሉም፡፡ የሞቱት ሁሉ በኢትዮጵያ ለለውጥ የተሰዉ ሰማዕታት ናቸው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ገዢው ፓርቲና መንግሰት ዜጎች ጥያቄ የማቅረብ መብታቸውን በመጋፋት በቁጥጥር ስር ውሎዋል የሚለው ቀረርቶ እና በምናብ ከሚስላቸው ፀረ-ህዝብና ፀረ-ሰላም ጋር የሚፈጥረው ምናባዊ ቁርኝት ድክመቱን ከማጋለጥ ውጭ ማንንም ግርታ ውስጥ እንደማይከት ማወቅ አለበት፡፡ አሁን በሚዲያ የምናያቸው የህዝብ አደረጃጀት ብሎ የሚሰበሰባቸው የፎረም አባለት የሚነግሩትን ከመስማት መታቀብ እና ትክክለኛውን የችግር ምንጭ ተቃዋሚ ከሚላቸው ቢያዳምጥ ይሻለዋል፡፡
ቸር ይግጠመን!!

Friday, November 27, 2015

ድርቅ በአንባገነን ስርዓት ችጋር ነው!!!




ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com; www.girmaseifu.blogspot.com
“From Derge I to Derge II’ - ከደርግ አንድ ወደ ደርግ ሁለት የሚል ፅሁፍ ኢህአዴግ ሀገሪቱን በተቆጣጠረ ጥቂት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያን ሪቪው በሚባል መፅሄት ላይ ማንበቤ ትዝ ይለኛል፡፡ ፀሃፊ ፐ/ሮ ጌታቸው ሀይሌ ይመስሉኛል፡፡ ታዲያ  ደርግና ኢህአዴግ በዘወትር ውሎዋችን ጭምር ሲመሳሰሉብኝ ይህ ፅሁፍ ትዝ ይለኛል፡፡ የፅሁፉ ዝርዝር ይዘት በምን በምን እንደሆነ ባላስታውሰውም ብዙ ግን መመሳሰል እንዳለ ይገባኛል፡፡ አሁንም ይህን ትዝታዬን የቀሰቀሰው ዋነኛው ነገር የዘንድሮ እኛ ችጋር/ርሃብ የምንለው እነርሱ/ገዢዎቹ ደግሞ ድርቅ አለ፣ እናንተ የምትሉት ችጋር ግን የለም የሚሉት መሬት ላይ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ በእኔ እምነት በአምባገነን ስርዓት ውስጥ ድርቅ ርሃብ/ችጋር ሆኖ የዜጎች ህይወት እንደሚቀጥፍ እርግጠኛ ነኝ፡፡
በ1977 የነበረው ክፉ ቀን ዜጎችን እንደሚጨረስ መረጃ ያላቸው ሁሉ የዜጎች ህይወት እንዳይቀሰፍ ሲጮሁ የዚያነው “ደርግ” ባሕላችንን በድምቀት እንዳናከብር የኢምፔራሊስት ወሬ ነው እያለ፣ ሲፈልግም ሰምቶ እንዳልሰማ ጭጭ ብሎ አሁን የኢትዮ ኩባ ወዳጅነት ሀውልት፣ የጠቅላይ ሚኒሰትሩ ቢሮና አዳራሻ ያለበትን ህንፃ እና ሌሎችም በጊዜው ድንቅ የሚባሉ የልማት ስራዎችን/ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ፣ ቢራ ፋብሪካዎች፣ ወዘተ/ እየሰራ በጎን ደግሞ ለባሕሉ በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠር ህዝብ ለሰልፍ ማድመቂያ ስልጣና እያደረገ ነበር፡፡ ሰልፈኞችም ባህሉን በሚያደምቅ ሁኔታ የተለያየ አልባሳት እየተገዛላቸው ይለብሱ ነበር፡፡
በቅርብ ርቀት ግን ዜጎች የሚላስ የሚቀመስ አጥተው ተርበውና ታርዘው ምትክ የሌለው ህይወታቸውን ይነጠቁ ነበር፡፡ በወቅቱ የነፃ አውጪ ቡድንኖች ይህን ለማጋለጥ ደፋ ቀና ሲሉ ወደ ሀገር ውስጥ ለባህሉ የገባውን ውስኪ ቁጥር እንዲሁም  የገንዘቡን መጠን እያጋነኑ ለፕሮፓጋንዳ ጭምር ሲነግሩን ነበር፡፡ ደርግ ባህሉን ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ አክብሮ ሲጨርስ የፖሊት ቢሮው አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ ድርቁን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያሰችል ዕቅድ አለኝ በማለት - እግረ መንገዱንም “ተፈጥሮን በቁጥጥር ስር እናውላለን” የሚል መፈክር ይዞ ብቅ አለ፡፡ አስከትሎም ድርቁን ለማድረስ አማፂያን/ገንጣይ አስገንጣዮች/ ለህዝቡ እርዳታ እንዳይደርስ እንቅፋት እየሆኑ ነው ብሎ ለችግሩ የተገላቢጦሽ ምላሽ ይሰጥ ጀመር፡፡ /በነገራችሁ ላይ እነዚህ  ገንጣይ አስገንጣይ የተባሉት ኃይሎች እርዳታ እንዳይደርስ ሲያደናቅፉ አልነበረም የሚል አቋም የለኝም፡፡ ይህን ስለማድረጋቸውና የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት የሰሩትን ስራ የሚገልጥ የራሳቸው ኤግዚቢሸን ምስክር ነው፡፡/
እናላችሁ ዛሬ የዚያን ጊዜ ነፃ አውጪዎች የደርግን ቦታ ይዘው ከሰላሳ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈፅሙ ማየት አንዴ ብቻ ሳይሆን ሲደጋግሙት መስማትና ማየት ህሊና ማቁሰሉ አይቀርም፡፡ ብአዴን የሚባል የኢህአዴግ እህት/ወንድም ድርጅት 35 ዓመት ሞላኝ ብሎ ደርግን በሚያስንቅ ሁኔታ ሲጨፍር ሲደንስ ከርሞ፣ ጭፈራውን ቢያንስ በአደባባይ ያለውን እንደጨረሰ ስብሰባ ቢጤ ተቅምጠው ችግሩ አሳስቦናል ብለው በዜና ሰማን፡፡ እነዚህ ሰዎች የፕሮፓጋንዳ ሰዎቻቸው ከኢሠፓ ካልመጡ በሰተቀር እንዲ ዓይነት መመሳሰል ከየት ይመጣል ብዬ ልገምት፡፡ ለዚህ ነው ከደርግ አንድ ወደ ደርግ ሁለት የሚለው ፅሁፍ ከሃያ ዓመት በኋላ ትዝ ያለኝ፡፡ ይህ ፅሁፍ ያለው ሰው ጀባ ቢለን ከድሮ ጀምሮ ያለውን መመሳሰል ልናይበት እንችላለን፡፡ አንባገነን ሰርዓት ሄዶ አንባገነን ሰርዓት ቢመጣም ድርቅ ርሃብ እንዳይሆን ማድረግ አይችልም፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራችን ማንም በስልጣን ላይ ቢመጣ በአሁኑ ጊዜ መወዳደሪያ ነጥብ አድርጎ መቅረብ ያለበት ስልጣን በያዘ በአምስት ዓመት ውስጥ ዜጎች በፍፁም ችጋር ውስጥ እንደማይገቡ የሚያረጋግጥ መሆን አለበት የሚል አቋም አለኝ፡፡ ሌሎች የልማት ስራዎች ሁሉ ይህን ለማረጋገጥ እገዛ የሚያደርጉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ሃያ አራት ዓመት በግብርና መር ፖሊስ ሲመራ የኖረ መንግሰት ለተከታታይ አሰር ዓመት በሁለት አሃዝ እድገት አስመዝግቢያለሁ እድገቱ በአብዛኛው የተገኘው ከግብርና ነው ሲል የከረመ የፖለቲካ መሪ ዛሬ “ኤሊኖ” የሚባል ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የተፈጥሮ ችግር ገጥሞን ነው ቢሉን የምንሰማቸው አይሆንም፡፡ ፕሮፓጋንዲሰቶቹ “ተፈጥሮ በቁጥጥር ስር እናውላለን” የምትለዋን መፈክር ረስተውት ይመስለኛል እንጂ የሰሞኑ መግለጫ ሁሉ የደርግ ጊዜ መግለጫ ነው የሚመስለው፡፡
በዚሁ አጋጣሚ ጉደኛው “ኢቢሲ - የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን” ድርቁ የእኛ ብቻ አይደለም ሀብታሞቹም ሰፈር ጎራ ብሎዋል ለማለት ይመስላል፣ የደቡብ አፍሪካ “አርብቶ አደሮች” ችግር ላይ መሆናቸውን ለማሳየት ሙከራ አድርጎዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካዎቹ አርብቶ አደሮቹም ሆኖ ከብቶቹ እንዴት ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሆኑ ግን በደጋፊነት የቀረበውን ፊልም ተመልክተን  ግምት የምንወስድ አይመስላቸም፡፡ ንቀውናል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ገበሬዎች በድርቁ ምክንያት የመኖ እጥረት ስለሚፈጠር መኖ ቢኖርም በድርቁ መነሻ ዋጋው ውድ ስለሚሆን ብዙ ከብት ያላችሁ ብትሸጡ ይሻላል የሚል የባለሞያ ምክር ነው የተሰጣቸው፡፡ ይህም በገበያ ላይ ከሚፈለገው በላይ አቅርቦት ስለሚጨምር የከብት ዋጋ መቀነሱ ሀቅ ነው፡፡ ይህ ከእኛ አርብቶ አደሮች ጋር እንዴት እንደሚገናኝ አልገባኝም፡፡ የገባው ካለ ቢያስረዳኝ ደስታውን አልችለውም፡፡
ልብ በሉ የእኛ አርብቶ አደሮች ካሉት ከብቶች ግማሹን ሸጠው ቀሪውን የማትረፍ አማራጭ ላይ አይደሉም፡፡ ከብቶቹ በቁም ደርቀው የሚቀምሱት አጥተው በቆሙበት መውደቅ ነው፡፡ የእኛ አርብቶ አደሮቹ በሚያሳዝን ሁኔታ ለከብቶች አይደለም ለልጆቻቸው የሚሰጡት አጥተው ልጆችም እራሳቸውም ቀዬ ለቀው የመንግሰት እጅ የሚጠብቁት፡፡ ይህ ጉደኛ ቴሌቪዥን ታዲያ ምን ማለቱ ነው ማለታችን አይቀርም፡፡ ለማነኛውም በደርግ ጊዜም ተመሳሳይ ዜናዎች በቴሌቪዝን እንመለከት ነበር፣ በሀገራችን የዚህ ዓይነት ችግር ሲፈጠር የመጀመሪያ አይደለም በሚል በሚኒሊክ ጊዜ ጀምሮ የነበረን ክፉ ቀን ያስተዋወቁን እነዚሁ ጉደኛ የደርግ ፕሮፓጋንዲስቶች ነበሩ፡፡ በአሜሪካም ተመሳሳይ ችግር አለ ምን ያስገርማል ይሉን ነበር፡፡ በዓለም ላይ ድርቅ እንደሚኖር ማንም ያውቃል ልዩነቱ አምባገነኖች ባሉበት ብቻ ሀገር ድርቅ ችጋር እንደሚሆን የምንረዳ አይመስላቸውም፡፡
ዲሞክራሲያዊ መንግሰት ባለበት ሀገር  ድርቅ በሚኖርበት ወቅት ዋነኛው ችግር የዜጎች ህይወት አደጋ ላይ መውደቅ አይደለም፡፡ የምግብ ዋጋ መናር ትልቅ ጉዳይ ይሆንና መንግሰታት ይህን መቆጣጠር ካልቻሉና ዜጎችን የዋጋ ንረት ከሚፈጥረው ችግር ለመታደግ የሚያስችል የፖሊሲ እርምጃ ካልወሰዱ ስልጣናቸው አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡ የእኛ አምባገነኖች በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ነብሱ ከስጋው ልትለያይ እያጣጣረ ችግሩ በቁጥጥር ላይ ነው ይሉናል፡፡ ስልጣናቸውም ከሌላው ጊዜ በተለየ ይመቻቸው ሁሉ ይመስለኛል፡፡
ለማጠቃለል የትግራይ ርዕስ መሰተዳደር ቁንጮ አቶ አባይ ወልዱ የሰጡት መግለጫ ላሰታውሳችሁ እና ልሰናበት፡፡ አቶ አባይ ወልዱ እንዲህ ይላሉ “ችግሩ በጥቂት ቀበሌዎች ውስጥ ብቻ ነው፣ ይህ ችግር ደግሞ ከክልሉ አቅም የሚያልፍ አይደለም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከፌዴራል መንግሰት ጋር በመሆን እርዳታ ማቅረብ ጀምረናል” የሚል ነው፡፡ ሀገራችንን የሚመሩት ሰዎች ሁለት መስመር አንዱ ከአንዱ ጋር የማይገጭ ማቅረብ  እንደማይችሉ ማሳያ ነው፡፡ ከክልሉ አቅም ውጭ አይደለም ብለው ደቂቃ ሳይቆዩ ከፌዴራል መንግሰት ጋር በመተባበር ይላሉ፡፡ በዚህች ሀገር ጋዜጠኛ ቢኖር አፋጦ ከስልጣኛቸው ሳያወርድ እይመለሰም ነበር፡፡ ምን ያረጋል ይህ አልሆነም፡፡ በመጡበት መንገድ መርጠው ይሆናል፡፡ እነርሱም መውረድ አልፈለጉም፡፡ እሰከዚያው ድረስ በዚህ ችግር መሃል እነዚህን ሰዎች መሪዎች ብሎ የተቀበለ ህዝብ ምርጫው ነው ብለን ምርጫውን ማክበር አለብን፡፡
ቸር ይግጠመን!!!!

Thursday, November 12, 2015

ፕሮፓጋንዳው ስብዓዊነት ይኑረው!!! ሰው እየሞተ ነው!! ቁጥሩን ቤቱ ይቁጠረው!!!



በሀገራችን ያለው ድርቅ ክብደት ከ1977ጋር የሚመሳሰል እንደሆነ የመንግሰት ሹም ከሸገር ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ምልልስ አረጋግጠዋል፡፡ ልዩነቱ ግን አሁን መንግሰት ይህን ለመቋቋም የሚያስችል አቅም አለን የሚልው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ አቅም ግን መሬት ላይ ወርዶ ስናየ ወኔ ብቻ ይመስላል፡፡ ከፕሮፓጋንዳ ያለፈ የፈረንጆቹን ደጅ እንዳይጠኑ የሚያደርጋቸው አይደለም፡፡
“ደርግ” በ1977 የነበረፈውን ድርቅ ለዓለም ይፋ አድርጎ የነበረ ሲሆን የዚያን ጊዜ በነበረው ቀዝቃዛ ጦርነት መነሻ በሁለቱ ጎራ በሚደረገው ፍልሚያ ግዳይ የሚጣልብት ወቅት ነበር፡፡ ደርግ ለዓለም ህብረተሰብ ጥሪ ባቀረበበት ወቅት የሶሻሊስቱ ተከታይ በመሆኑ ይህ ጎራ ይህን ድጋፍ የሚያደርግበት አቅም የሌለው ሲሆን ይህን ለማድረግ አቅም ያላቸው ምዕራባዊያን ግን ውጤቱን በደንብ ሳናየው ድጋፍ ላለመስጠት መቁረጣቸው ለችግሩ ክብደት አንዱ እንደ ነበር ለመረዳት ሊቅ መሆን አያስፈልግም፡፡ በተጨማሪ ለ1997 ድርቅ ተገቢው ምላሽ በምዕራባዊያን እንዳይሰጥ በወቅቱ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩት በተለይ ህወሃት እና ሻቢያ የተጫወቱት ሚና ቀላል የማይባል ብቻ ሳይሆን አሁን ላይ ሆነን ስናየው ሰብዓዊነትን ለፖለቲካ ጥቅም እንዳዋሉት ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ የኢህአዴግ መንግሰት ከምዕራባዊያኑ ጋር ያለው ቅርበት ከደርግ እንደሚሻል ስለሚታመን በተጨማሪ ህውሃትና ሻቢያ በዛን ጊዜ የሰሩትን ዓይነት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ለመስራት የሚችል ታጣቂ ሀይል ባለመኖሩ ችግሩን ለመቋቋም በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ መንግሰት አቅሙ የከብቶቹን ህይወት ለመታደግ ለምን አልተጠቀመበትም? ካልቻለ ደግሞ ምዕራባዊያኑ ድጋፍ ለማድረግ ከፈለጉ አሁንስ ቢሆን ከብቶቹ ሳይሞቱ እንዲደርሱልን ለምን አልተደረገም? የሚለው ጥያቄ ለማንሳት አርብቶ አድር መሆን አይጠበቅብንም፡፡
ሁሉም የሚረዳው አንድ ሀገር በድርቅ መቼም ቢሆን ሊጋለጥ ይችላል፡፡ ይህ በዓለም ላይ ተደጋጋሚ ክስተት እንደሆነ ማንም ያውቃል፡፡ ድርቅ ሲኖር ግን ይህን ድርቅ የሌላ ሶሰተኛ ሀገር ድጋፍ ሳይጠየቅ ለመፍታት አቅም መፍጠር መቻል ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ባላት ስነ ምህዳር ከዚህ የተሻለ ማድረግ እና ለሌሎች መትረፍ ይገባት ነበር፡፡ ይህ ደግሞ አሰማት ሳይሆን ሊተገበር የሚችል የሀገር ሉዓላዊነት መገለጫ ነው ብሎ የሚያምን መንግሰት ያስፈልጋል፡፡ ኤክስፖርት የሚደረግ ታንክ ሰራን በፍፁም በዚህ ወቅት ሊያኮራን የሚችል ስ አይደለም፡፡ አሁን የምንረዳው መንግሰት ችግሩን ሪፖርት አድርጊያለሁ ማለትን እንደመውጫ ቀዳዳ እየተጠቀመበት መሆኑን ነው፡፡
አሁን በመሬት ላይ ያለው ሀቅ በምግብ እና ውሃ እጥረት ከብቶች በብዛት እየሞቱ ሲሆን፤ መቼም እንደ እንሰሳቱ በብዛት ሰው እየሞተ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን አሁን በተፈጠረው ሁኔታ ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል የነበረባቸው የጤና ችግር አግርሽቶም ይሁን አዲስ ጤና መቃወስ ተፈጥሮ ህፃናት ብቻ ሳይሆን አረጋዊያንም ሆኑ ባለጡንቻው ጎልማሳ የሚሞቱበት ሁኔታ እንዳለ ግን መካድ አይቻልም፡፡ ከዚህ ስንነሳ በምግብ እጥረት ምክንያት ሞት የለም ብሎ ፈሊጥ፤ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ሁለት ህፃናት በቀን ይሞታሉ ያለው ለሌላ ዓላማ እና የሀገር ገፅታ ለማበላሸት ነው የተባለውን የመንግሰት ሹም መግለጫ ስንሰማ ከማፈር ውጭ ምን ልንል እንችላለን፡፡ የመንግሰት ሹሞቸ ፕሮፓጋንዳውን ጋብ አድርገው ሰብዓዊነት በመላበስ እየሞተ ያለውን ሰው መታደግ የግድ ነው፡፡ ስንት ሰው ሞተ ቤቱ ይቁጠረው፡፡
አንድም ሰው በድርቅ አልሞተም የሚል መግለጫ የሰጡትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም ቢሆኑ አሁን የተፈጠረው ሁኔታ ከላይ እንደገለፅኩት ቀደም ሲል በአካባቢዎቹ የኖረው ችግር ላይ ሲታከል ሰዎች እንደሚሞቱ መገንዘብ አቅቷቸው ሳይሆን ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ የተደረገ መሆኑን ማውቅ ግድ ይለናል፡፡ በዚህ ፕሮፓጋንዳ ማፈራችን እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡ የምናፍረው ደግሞ ከ30 ዓመት በኋላ ድርቅን ለመቋቋም የሚችል ህብረተሰብ ሊገነባ የሚችል ስርዓት መመስረት ያለመቻላችን ነው፡፡ ይህን መንግሰት ዛሬም ስህተቱን “በኤሊኖ” ክስተት አሳቦ በስልጣን እንዲቆይ የፈቀድነው እኛው ነን፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራችን በምንም መመዘኛ አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በፈለገ የተራዘመ የተፈጥሮ ችግር ጊዜ ቢሆን እንኳን ምግብ ለመለመን የማትችል ሀገር ለማድረግ የሚያስችል ፖሊሲና ሰትራቴጂ የሌለው መንግሰት እንዳይኖር ማድረግ ካልቻልን ምርጫው የራሳቸን ነው፡፡ ምን ማለት ነው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ እኛ ከላፈቀድን መሬትን በቁጥጥሩ ስር አድርጎ፤ ሴፍቲኔት በሚባል የመንግሰት ድጎማ ስር ህዝቡን በተራዘመ ሰንፍና እንዲኖር በማድረግ በአምስት ዓመት በሚመጣ የይስሙላ ምርጫ ካርድ አግኝቶ አገዛዙን ለማራዘም የሚፈልግ መንግሰት ይህን ዓይነት ሰርዓት ሊዘረጋ አይችልም፡፡ እንዲህ ሲያደርገን እንቢ ብለን መከላከል ምርጫው የእራሳችን ይሆናል ማለት ነው፡፡
በተለጠጠ ዕቅድ ተሰፋ ውስጥ (የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ልብ ይሏል) የከተማ ነዋሪውን ሸምቶ ለማብላት የውጭ ሀገር የሰንዴ ገበያን አማራጭ ያደረገ መንግሰት፤ በሀገር ውስጥ በእርሻ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ዘመናዊ ገበሬዎች እርሻ መሰሪያና ሌሎች ግብዓቶች ድጎማ አድርግ ሲባል ነፃ ኢኮኖሚ ነው ይለናል፡፡ አንድ በዘመናዊ እርሻ ለመሰማራት የሚፈልጉ ዘመናዊ ገበሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰበሰቡት ስብሰባ ላይ ከጎኔ ቁጭ ብለው የነገሩኝ አስደማሚ ነገር “መንግሰት ሰንዴ ለመግዛት በጨረታ የሚያባክነው ጊዜ እና ገንዘብ ለእኛ ድጋፍ ቢያደርግ ለጨረታ ከሚባክነው ጊዜ ባነሰ በሀገር ውስጥ ሰንዴ ለማምረት እንችላለን” የሚል ነው፡፡ ይህን ሀቅ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ለግብርና ሚኒሰትሩ የኪራይ ስብሰቢዎች ወሬ ነው የሚሆነው፡፡ ግብርና መር ስትራቴጂና ፖሊሲ ብለው ምግብ በሀገር ውስጥ ማሟላት ሳይችሉ ለዘላለም ሊገዙን ሲፈልጉ እሺ ብለን አለን፡፡
ለማነኛው ኢትዮጵያ ሀገራችንን ምድሯ “በኤሊኖ” ክስተት ይሁን በሌላ “ድርቅ” ጎብኝቷታል፡፡ ይህ ድርቅ አድጎ ደግሞ ዜጎችን ህይወት ቀሰ በቀስ እየወሰደ ነው፡፡ ይህን “ችጋር” ለመቋቋም ዜጎች በጋራ መነሳት ይኖርብናል፡፡ ፈረንጆቹ ይህ ውጤት እንዲቀለበስ ከልብ ከፈለጉ አንድም ሰው ሳይሞት ሊደርሱ የሚያስችል ሰርዓት አላቸው ነገር ግን የሰጡት ድጋፍ ህይወት አድን መሆኑ እንዲታወቅ ችግሩ እስኪሰማን ብዙ ሀይወት መጥፋቱ በሚዲያ ታይቶ ቅሰቀሳ እስኪደረግ ሊዘገዩ ይችላሉ፡፡ በዚህ መሃል ምትክ የሌለው የሰው ልጅ ህይወት ያልፋል፡፡ ይህ እንዳይሆን መንግሰት አሁን ከጀመረው ተራ ፕሮፓጋንዳ ወጥቶ ወደ ቀጥተኛ ህዝቡን ያሳተፈ ምላሽ እንዲሰጥ ማድረግ ይኖርበታል፡፡


Tuesday, October 13, 2015

ኢህዴግ በሚጠራው መድረክ አለመገኘት ማንን ይጠቅማል? ግርማ ሠይፉ ማሩ



girmaseifu32@yahoo.com, www:girmaseifu.blogspot.com
ቅጥ አንባሩ የጠፋው የኢትዮጵያችን ፖለቲካ በዋነኝነት የሚጎድለው ልክ ያልሆነን ነገር ልክ አይደለም ማለት ያለመቻል ነው፡፡ በግል አስተያየት ልክ አይደለም ብሎ መቆም ደግሞ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ የተሳሳተ ውሳኔ ባለቤቶች በድጋሚ ጥፋታቸውን በጥፋት ለማረም ሌላ ስህተት ይደግማሉ፡፡ አሰተያየትን በአሰተያየት ለመመለስ ይከብዳቸዋል፡፡ የዚህ ደግሞ ዋነኛው ሰለባ የተቃዋሚው ጎራ ነው፡፡ ለነገሩ አሁን ይህ ነው የሚባል ተቃዋሚ አለ ባይባልም፤ ያሉትም ቢሆኑ ከልምድ የሚማሩ ዓይነት ሆነው አልተገኙም፡፡
ለዛሬ ፅሁፌ መነሻ የሆነኝ አንድ ሰሙ “የአንዳርጋቸው ፅጌ ብርሃን” በሚል የብዕር ሰም የሚከተለውን መልዕክት በፌስ ቡክ ገፄ የውስጥ መልዕክት ማስቀመጫ
“ግርማ ካሳ (ልብ በሉ እኔ ግርማ ሠይፉ ነኝ) ወረድክብኝ በጣም። ተፈጭቶ ተቦክቶ ተጋግሮ ሊበላ የቀረበውን ነገር ድጋሚ ወፍጮ ቤት ይሂድ ብለክ እየተከራከርክ ነው። 24 አመት ሲያታልል የኖርን መንግስት ዛሬ 25ኛው አመት ላይ ሆነክም እንዴት አልገባክም? ስንት አመት ነውሚፈጀው እንዳንት አይነት ሰዎችን ለማብሰል? ተወያየተክ ምን ታተርፋለክ ? ወያኔ ተቃዋሚዎችን  ሚፈልገው ለተራ ፕሮፖጋንዳው ሊጠቀምባቸው እንጂ ለነሱ ሀሳብ ጆሮ ለመስጠት አደለም። መንግስት እራሱ ያወጣውን ህግ ጥሶ ያሰራቸውን የፓርቲ አባሎችን ለማስፈታት ከወያኔ ጋር ስብሰባ መቀመጥ አያስፈልግም። እንዲምታስብ ከሆነ ከአልም ሁሉ ተለይተክ ከሀይለማርያም ደሳለኝ ብቻ የተሻልክ ጅላጅል ነክ ማለት ነው። ወያኔ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተጻፈውን ድብዳቤ ልብ ብለክ አንብበከዋል ? እንዲ የሚል አርፍተ ነገር አለበት። "በሀገራችን የሚገኙ ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች "እንደ መላው የሀገራችን ህዝቦች " እያለ ይቀጥላል። ሲጀመር ወያኔ እነዚ ፓርቲ ብሎ የሚያውቃቸው ድርጅቶች ከህዝብ ተለይተው ያሉ እና የህዝብ ድጋፍ የሌላቸው አርጎ ነው የጠራቸው። ፀረ ህዝብ አርጎ ነውሚስላቸው። አንደ ህዝብ አካል አርጎ አይቆጥራቸውም አያከብራቸውም። አንዳንተ ዓይነት አሟሟቂ ሰው ነው ወያኔሚፈልገው።ኢቢሲን አሟሟቂ”
የሚል መልዕክት አስቀመጠልኝ፡፡
መልዕክቱ የተፃፋው በዚህ ጉዳይ አስተያየት ለሰጠው ወዳጄ ግርማ ካሣ ይመስላል ነገር ግን  የተላከው ለእኔ በእኔ አድርሻ እና እኔን በዓይነ ልቦናው እየሳለ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ በእኔ እይታ ደግሞ የግርማ ካሣን ሃሳብ መደገፍ ብቻ ሳይሆን በግል ለደወሉሉኝ አቋሜን ገልጬ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ  ግን ሚዲያ ላይ ወጥቶ አስተያየት መስጠት ብፈልግም፤ ብዙ ምቾት አልተሰማኝም ነበር፡፡ ለማነኛው የዚህ አሰተያየት ሰጪን ሃሳብ መነሻ አድርጌ የግሌን አስተያየት ላቅርብ፡፡
በመጀመሪያ ማነኛውም ግብዣ ላይ የተጠራ ሰው ግብዣ የሚሄደው በመከባበር ሰሜት መሆን አለበት፡፡ ጠሪ አክባሪ በሚል እንጂ ግብዣው ላይ ምን ድግስ አለ በሚል መሆን የለበትም፡፡ በእኔ እምነት ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገራዊ አጀንዳ ላይ ከዚህ በፊት ጥሪ ተደርጎላቸው የማያውቁ የፖለቲካ ፓርቲውች መድረክ፣ ሰማያዊ እና መኢህአድ ግብዣ ተደርጎላቸዋል፡፡ ለምሳሌ በመጀመሪያው የአምስት ዓመት ዕድገትና ትራንሰፎርሜሸን ዕቅድ እና በአባይ ግድብ ወቅት ጥሪ ስለ አልተደረገላቸው አልተጠራንም ሃሳባችንን መስጠት እና የጋራ ማድረግ አልቻልንም ሲባል ነበር፡፡ በዚህ ወቅት የፖለቲካ ምዕዳሩም ሆነ አጠቃላይ ሀገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ተመሳሳይ ነበር፡፡ በዛን ጊዜ ተቃዋሚዎች አልተጠራንም ሲሉ የነበረው ተጠርተው ለመቅረት አይመስለኝም፡፡ ተገኝተው ሃሳባቸውን ለማካፈል ይመስለኛል፡፡
በእኔ እምነት አሁን በተደረገው ጥሪ መስረት ከላይ ሰማቸውን የጠቀስኩት ፓርቲዎች ተገኝተው የሚከተለውን ማከናወን ይችሉ ነበር፡፡ መጀመሪያ ያለፈው አምስት ዓመት ክንውን ሲቀርብ ከመነሻው ጀምሮ በጋራ ከተቃዋሚዎች ጋር በጋራ ለመስራት መንግሰት እርምጃ ባለመውሰዱ የእቅዱ ዋና ዋና ምሶሶ የሆኑት ተግባራት ያለመሳካታቸውን በተጨባጭ ማስረጃ ለማስረዳት እድሉን ሊጠቀሙበት ይችሉ ነበር፡፡ ለምሳሌ የባቡር ዝርጋታ ከታቀደው 30 ከመቶ ያለመሰራቱ፣ በኤሌትሪክ ሀይል በተመሳሳይ 20 ከመቶ እንኳን ያለመሳካቱ፤ በመንገድ በውጭ ንግድ፣ በዋጋ ማረጋጋት፣ በግብርና በተለይ በሰፋፊ እርሻ ወዘተ.. ያሉትን መሰረታዊ ችግሮች በማሳየት ለዚህ ዋነኛው ችግር በጋራ በመስራት ሊገኝ የሚችለውን ሀገራዊ ሀይል ወደ ጎን ማድረጋቸውን ለህዝብ ይፋ ማድረጊያ መድረክ ይሆን ነበር፡፡ በተለይ የአባይ ግድብን ገዢው ፓርቲ የፖለቲካ መጠቀሚያ እንዲሆን በማድረጉ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሊያደርጉ የሚችሉት ከፍተኛ አሰተዋፅኦ መገደቡን ለመናገር ከዚህ የተሻለ ትክክለኛ መድረክ የሚያገኙ አይመስለኝም፡፡ ይህንን መድረክ ለመጠቀም ባለመቻላቸው ትልቅ የፖለቲካ ኪሣራ ይመስለኛል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ገዢው ፓርቲ እራሱ ያመነውን የመልካም አስተዳደር መፍቻው ቁልፍ መንገድ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ እና በተለይ ደግሞ የሚዲያዎች ተሳትፎ መኖር ተዓማኒነት የሚጣልባቸው የፍትህ ስርዓት መሆኑን በሰብሰባው በሚፈጠሩ አጋጣሚዎች ሁሉ በማንሳት ዕቅዱ ያልተሳካው ይልቁንም ሙስና የተንሰራፋው ስርዓቱን የሚተቹ ጋዜጠኘኞችና አምደኞች በመታሰራቸው፣ እምነት የሚጣልበት የፍትህ ስርዓት ባለመኖሩ እንደሆነ አጋጣሚውን መጠቅም ይቻል ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዝግጅት አድርገው መሳተፍ እንጂ አድማ አድርጎ ከግብዣ በመቅረት ውጤት የሚገኝ አይመስለኝም፡፡ ይህ ትልቅ ሰህተት ይመስለኛል፡፡
ከዚህ ውይይት በማስከተል “የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም” በሚል ተረት ከገዢው ፓርቲ ጋር ተመራርቆ ለመውጣት ሳይሆን በቀጣይ ዕቅድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለያዩ ሀገራዊ አጀንዳዎች በምን መልክና ደረጃ ስንሳተፍ ይህ ዕቅድ ተግባራዊ ይሆናል በሚል መነሻነት የድርጊት መርዓ ግብር በመንደፍ የጋራ ኮሚቴ አቋቈሞ መውጣት፣ በተለይ የፖለቲካ ምዕዳሩ ለማስፋት የሚቻልበት መንገድ መቀየስ ሊሞከር የሚገባው ትልቅ ስራ ነበር፡፡ ይህ ከገዢው ፓርቲ ባህሪ አንፃር ተቀባይነት ባያገኝ እንኳን እንቢተኝነቱን ለማጋለጥ ይረዳ ነበር፡፡ እንደ ፓርቲ ሰርተፊኬት ይዞ ዓመት ከመቁጠር በዘለለ መንግሰት በተገኘበት ሁሉ እየተገኙ ድምፅ ማሰማት (ባይሰሙም መጮኽ) ግዴታቸው ነበር የሚል የግል አቋም አለኝ፡፡
እውነቱን ለመናገር በቁጥር እስከ ሃያ የሚደርሱ የፓርቲ አባላትን (ለምሳሌ ሶስቱ ፓርቲዎች 60 አባላትን) በአንድ መድረክ ላይ እንዲገኙ የተሰጠን እድል ያለመጠቀምን ያክል ደካማ ውሳኔ አይታየኝም፡፡ እያንዳንዳቸው ሁለት ደቂቃ መልእክት ቢያስተላልፉ የሁለት ሰዓት መልዕክት በመንግሰት ጆሮ ላይ ማስቀመጥ ይቻል ነበር፡፡ እነዚህን አጋጣሚዎች በእስር የሚማቅቁ ጓዶቻችንን በማንሳት ልንዘክራቸው ይገባ ነበር፡፡ አሸባሪ ያሏቸውን “ጀግኖች” ብለን ልናወደስ የምንችልበት መድረክ ያለመጠቀም በምን መመዘኛ ልክ እንደሚሆን አይታየኝም፡፡
ገዢው ፓርቲ ከአሁን በኋላ ለማነኛውም ዓይነት ውይይት ሳይጠራ ዳተኛ ቢሆን ሰበብ አግኝቷል፡፡ ቢጠሩም አይገኙም ይልቁንም በሚጠሩበት መድረክ ከመገኘት ይልቅ ውጪ ሆነው መግለጫ በማውጣት ላይ ይገኛሉ ብሎ ለሀጋሮቹ ማስረጃ ያቀርባል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከኢህዴግ መንግስት ባልተናነሰ ካድሬ የሆኑ የአሜሪካን እና አውሮፓ ህብረት ድጋፍ ሰጪዎች ይህን ለመስማት እና ለማመን ብዙ አይቸገሩም፡፡
በእኔ አረዳድ ፓርቲዎቹ በግብዣው ላይ ተገኝተው በምን ጉዳይ አተኩረው እንደሚናገሩ እንዴት አድርገው የፖለቲካ ጥቅም እንደሚያገኙበት መካሪ አላገኙም፣ በውስጥም በቅጡ አልመከሩበትም፡፡ የሚያሳዝነው እነዚህ ፓርቲዎች የአሜሪካ ኤምባሲ ለስዕል ኤግዚቢሽን ምረቃ ቢጠራቸው በግብዣው ላይ ይገኛሉ፡፡ የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባል ሊያነጋግራችሁ ይፈልጋል ቢባሉ ይገኛሉ፡፡ መገኘት ብቻ ሳይሆን አነጋገሩን ብለው ዜና ይሰራሉ፡፡ እንግዲህ አንባገነኑ ኢህአዴግ ዲሞክራት እሰኪሆን ጠብቀው ለመወያየት ከሆነ ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ ባለፈው ፕሬዝዳንት ኦባማ ጉብኝት ሲያደርጉ ለግንኙነት በሚመቸው የእራት ግብዣ ላይ ላለመገኝት ወስነው በብዙ ሜትር ርቀት በቴሌቪዥን በተሻለ ለመከታተል በሚቻልበት የአዳራሽ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ሲወስኑ ዝም ማለታችን አበጃችሁ ያልን የመሰላቸው መሪዎች፤ ይህንንም ግብዣ ለፖለቲካ ጥቅም ማዋል አለመቻላቸውን ዝም ማለት ተገቢ አይደለም ለማለት ሲባል የቀረበ አስተያየት ነው፡፡ በእኔ እምነት በሰላማዊ ትግል በሀገር ውስጥ ለመንቀሳቀስ የወሰነ ማንኛውም አካል መንግሰትን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እያገኙ መልዕክት ማስተላለፍ ተገቢ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ጭምር ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ እና መንግሰት በሚጠሩት ማንኛውም ስብሰባ ላይ ላለመገኘት መወሰን የሚጠቅመው ገዢውን ፓርቲ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ሃሣብ ያለው በመቅረት የሚገኘውን ጥቅም ቢያስረዳኝ፣ በተለይ አሁን በተደረገው የሁለተኛው የእድገት እና ትራነስፎርሜሽን እቅድ ለመወያየት በተደረገው ጥሪ ላይ ያለመሳተፍ ያስገኘውን ጥቅም ለሚያስረዳኝ ለመማር ዝግጁ መሆኔን እገልፃለሁ፡፡ በደፈናው ገዢውን ፓርቲ እውቅና መንፈግ የሚል መልስ ግን አልቀበልም፡፡ በሀገር ውስጥ ሆኖ በዚሁ መንግሰት ስር እየተዳደሩ እውቅና መንፈግ የሚባል ፖለቲካ አይገባኝም፡፡
ቸር ይግጠመን!!!!