Friday, November 27, 2015

ድርቅ በአንባገነን ስርዓት ችጋር ነው!!!




ግርማ ሠይፉ ማሩ
girmaseifu32@yahoo.com; www.girmaseifu.blogspot.com
“From Derge I to Derge II’ - ከደርግ አንድ ወደ ደርግ ሁለት የሚል ፅሁፍ ኢህአዴግ ሀገሪቱን በተቆጣጠረ ጥቂት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያን ሪቪው በሚባል መፅሄት ላይ ማንበቤ ትዝ ይለኛል፡፡ ፀሃፊ ፐ/ሮ ጌታቸው ሀይሌ ይመስሉኛል፡፡ ታዲያ  ደርግና ኢህአዴግ በዘወትር ውሎዋችን ጭምር ሲመሳሰሉብኝ ይህ ፅሁፍ ትዝ ይለኛል፡፡ የፅሁፉ ዝርዝር ይዘት በምን በምን እንደሆነ ባላስታውሰውም ብዙ ግን መመሳሰል እንዳለ ይገባኛል፡፡ አሁንም ይህን ትዝታዬን የቀሰቀሰው ዋነኛው ነገር የዘንድሮ እኛ ችጋር/ርሃብ የምንለው እነርሱ/ገዢዎቹ ደግሞ ድርቅ አለ፣ እናንተ የምትሉት ችጋር ግን የለም የሚሉት መሬት ላይ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ በእኔ እምነት በአምባገነን ስርዓት ውስጥ ድርቅ ርሃብ/ችጋር ሆኖ የዜጎች ህይወት እንደሚቀጥፍ እርግጠኛ ነኝ፡፡
በ1977 የነበረው ክፉ ቀን ዜጎችን እንደሚጨረስ መረጃ ያላቸው ሁሉ የዜጎች ህይወት እንዳይቀሰፍ ሲጮሁ የዚያነው “ደርግ” ባሕላችንን በድምቀት እንዳናከብር የኢምፔራሊስት ወሬ ነው እያለ፣ ሲፈልግም ሰምቶ እንዳልሰማ ጭጭ ብሎ አሁን የኢትዮ ኩባ ወዳጅነት ሀውልት፣ የጠቅላይ ሚኒሰትሩ ቢሮና አዳራሻ ያለበትን ህንፃ እና ሌሎችም በጊዜው ድንቅ የሚባሉ የልማት ስራዎችን/ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ፣ ቢራ ፋብሪካዎች፣ ወዘተ/ እየሰራ በጎን ደግሞ ለባሕሉ በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠር ህዝብ ለሰልፍ ማድመቂያ ስልጣና እያደረገ ነበር፡፡ ሰልፈኞችም ባህሉን በሚያደምቅ ሁኔታ የተለያየ አልባሳት እየተገዛላቸው ይለብሱ ነበር፡፡
በቅርብ ርቀት ግን ዜጎች የሚላስ የሚቀመስ አጥተው ተርበውና ታርዘው ምትክ የሌለው ህይወታቸውን ይነጠቁ ነበር፡፡ በወቅቱ የነፃ አውጪ ቡድንኖች ይህን ለማጋለጥ ደፋ ቀና ሲሉ ወደ ሀገር ውስጥ ለባህሉ የገባውን ውስኪ ቁጥር እንዲሁም  የገንዘቡን መጠን እያጋነኑ ለፕሮፓጋንዳ ጭምር ሲነግሩን ነበር፡፡ ደርግ ባህሉን ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ አክብሮ ሲጨርስ የፖሊት ቢሮው አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ ድርቁን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያሰችል ዕቅድ አለኝ በማለት - እግረ መንገዱንም “ተፈጥሮን በቁጥጥር ስር እናውላለን” የሚል መፈክር ይዞ ብቅ አለ፡፡ አስከትሎም ድርቁን ለማድረስ አማፂያን/ገንጣይ አስገንጣዮች/ ለህዝቡ እርዳታ እንዳይደርስ እንቅፋት እየሆኑ ነው ብሎ ለችግሩ የተገላቢጦሽ ምላሽ ይሰጥ ጀመር፡፡ /በነገራችሁ ላይ እነዚህ  ገንጣይ አስገንጣይ የተባሉት ኃይሎች እርዳታ እንዳይደርስ ሲያደናቅፉ አልነበረም የሚል አቋም የለኝም፡፡ ይህን ስለማድረጋቸውና የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት የሰሩትን ስራ የሚገልጥ የራሳቸው ኤግዚቢሸን ምስክር ነው፡፡/
እናላችሁ ዛሬ የዚያን ጊዜ ነፃ አውጪዎች የደርግን ቦታ ይዘው ከሰላሳ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈፅሙ ማየት አንዴ ብቻ ሳይሆን ሲደጋግሙት መስማትና ማየት ህሊና ማቁሰሉ አይቀርም፡፡ ብአዴን የሚባል የኢህአዴግ እህት/ወንድም ድርጅት 35 ዓመት ሞላኝ ብሎ ደርግን በሚያስንቅ ሁኔታ ሲጨፍር ሲደንስ ከርሞ፣ ጭፈራውን ቢያንስ በአደባባይ ያለውን እንደጨረሰ ስብሰባ ቢጤ ተቅምጠው ችግሩ አሳስቦናል ብለው በዜና ሰማን፡፡ እነዚህ ሰዎች የፕሮፓጋንዳ ሰዎቻቸው ከኢሠፓ ካልመጡ በሰተቀር እንዲ ዓይነት መመሳሰል ከየት ይመጣል ብዬ ልገምት፡፡ ለዚህ ነው ከደርግ አንድ ወደ ደርግ ሁለት የሚለው ፅሁፍ ከሃያ ዓመት በኋላ ትዝ ያለኝ፡፡ ይህ ፅሁፍ ያለው ሰው ጀባ ቢለን ከድሮ ጀምሮ ያለውን መመሳሰል ልናይበት እንችላለን፡፡ አንባገነን ሰርዓት ሄዶ አንባገነን ሰርዓት ቢመጣም ድርቅ ርሃብ እንዳይሆን ማድረግ አይችልም፡፡
ኢትዮጵያ ሀገራችን ማንም በስልጣን ላይ ቢመጣ በአሁኑ ጊዜ መወዳደሪያ ነጥብ አድርጎ መቅረብ ያለበት ስልጣን በያዘ በአምስት ዓመት ውስጥ ዜጎች በፍፁም ችጋር ውስጥ እንደማይገቡ የሚያረጋግጥ መሆን አለበት የሚል አቋም አለኝ፡፡ ሌሎች የልማት ስራዎች ሁሉ ይህን ለማረጋገጥ እገዛ የሚያደርጉ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ሃያ አራት ዓመት በግብርና መር ፖሊስ ሲመራ የኖረ መንግሰት ለተከታታይ አሰር ዓመት በሁለት አሃዝ እድገት አስመዝግቢያለሁ እድገቱ በአብዛኛው የተገኘው ከግብርና ነው ሲል የከረመ የፖለቲካ መሪ ዛሬ “ኤሊኖ” የሚባል ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የተፈጥሮ ችግር ገጥሞን ነው ቢሉን የምንሰማቸው አይሆንም፡፡ ፕሮፓጋንዲሰቶቹ “ተፈጥሮ በቁጥጥር ስር እናውላለን” የምትለዋን መፈክር ረስተውት ይመስለኛል እንጂ የሰሞኑ መግለጫ ሁሉ የደርግ ጊዜ መግለጫ ነው የሚመስለው፡፡
በዚሁ አጋጣሚ ጉደኛው “ኢቢሲ - የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን” ድርቁ የእኛ ብቻ አይደለም ሀብታሞቹም ሰፈር ጎራ ብሎዋል ለማለት ይመስላል፣ የደቡብ አፍሪካ “አርብቶ አደሮች” ችግር ላይ መሆናቸውን ለማሳየት ሙከራ አድርጎዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካዎቹ አርብቶ አደሮቹም ሆኖ ከብቶቹ እንዴት ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሆኑ ግን በደጋፊነት የቀረበውን ፊልም ተመልክተን  ግምት የምንወስድ አይመስላቸም፡፡ ንቀውናል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ገበሬዎች በድርቁ ምክንያት የመኖ እጥረት ስለሚፈጠር መኖ ቢኖርም በድርቁ መነሻ ዋጋው ውድ ስለሚሆን ብዙ ከብት ያላችሁ ብትሸጡ ይሻላል የሚል የባለሞያ ምክር ነው የተሰጣቸው፡፡ ይህም በገበያ ላይ ከሚፈለገው በላይ አቅርቦት ስለሚጨምር የከብት ዋጋ መቀነሱ ሀቅ ነው፡፡ ይህ ከእኛ አርብቶ አደሮች ጋር እንዴት እንደሚገናኝ አልገባኝም፡፡ የገባው ካለ ቢያስረዳኝ ደስታውን አልችለውም፡፡
ልብ በሉ የእኛ አርብቶ አደሮች ካሉት ከብቶች ግማሹን ሸጠው ቀሪውን የማትረፍ አማራጭ ላይ አይደሉም፡፡ ከብቶቹ በቁም ደርቀው የሚቀምሱት አጥተው በቆሙበት መውደቅ ነው፡፡ የእኛ አርብቶ አደሮቹ በሚያሳዝን ሁኔታ ለከብቶች አይደለም ለልጆቻቸው የሚሰጡት አጥተው ልጆችም እራሳቸውም ቀዬ ለቀው የመንግሰት እጅ የሚጠብቁት፡፡ ይህ ጉደኛ ቴሌቪዥን ታዲያ ምን ማለቱ ነው ማለታችን አይቀርም፡፡ ለማነኛውም በደርግ ጊዜም ተመሳሳይ ዜናዎች በቴሌቪዝን እንመለከት ነበር፣ በሀገራችን የዚህ ዓይነት ችግር ሲፈጠር የመጀመሪያ አይደለም በሚል በሚኒሊክ ጊዜ ጀምሮ የነበረን ክፉ ቀን ያስተዋወቁን እነዚሁ ጉደኛ የደርግ ፕሮፓጋንዲስቶች ነበሩ፡፡ በአሜሪካም ተመሳሳይ ችግር አለ ምን ያስገርማል ይሉን ነበር፡፡ በዓለም ላይ ድርቅ እንደሚኖር ማንም ያውቃል ልዩነቱ አምባገነኖች ባሉበት ብቻ ሀገር ድርቅ ችጋር እንደሚሆን የምንረዳ አይመስላቸውም፡፡
ዲሞክራሲያዊ መንግሰት ባለበት ሀገር  ድርቅ በሚኖርበት ወቅት ዋነኛው ችግር የዜጎች ህይወት አደጋ ላይ መውደቅ አይደለም፡፡ የምግብ ዋጋ መናር ትልቅ ጉዳይ ይሆንና መንግሰታት ይህን መቆጣጠር ካልቻሉና ዜጎችን የዋጋ ንረት ከሚፈጥረው ችግር ለመታደግ የሚያስችል የፖሊሲ እርምጃ ካልወሰዱ ስልጣናቸው አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡ የእኛ አምባገነኖች በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ነብሱ ከስጋው ልትለያይ እያጣጣረ ችግሩ በቁጥጥር ላይ ነው ይሉናል፡፡ ስልጣናቸውም ከሌላው ጊዜ በተለየ ይመቻቸው ሁሉ ይመስለኛል፡፡
ለማጠቃለል የትግራይ ርዕስ መሰተዳደር ቁንጮ አቶ አባይ ወልዱ የሰጡት መግለጫ ላሰታውሳችሁ እና ልሰናበት፡፡ አቶ አባይ ወልዱ እንዲህ ይላሉ “ችግሩ በጥቂት ቀበሌዎች ውስጥ ብቻ ነው፣ ይህ ችግር ደግሞ ከክልሉ አቅም የሚያልፍ አይደለም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ከፌዴራል መንግሰት ጋር በመሆን እርዳታ ማቅረብ ጀምረናል” የሚል ነው፡፡ ሀገራችንን የሚመሩት ሰዎች ሁለት መስመር አንዱ ከአንዱ ጋር የማይገጭ ማቅረብ  እንደማይችሉ ማሳያ ነው፡፡ ከክልሉ አቅም ውጭ አይደለም ብለው ደቂቃ ሳይቆዩ ከፌዴራል መንግሰት ጋር በመተባበር ይላሉ፡፡ በዚህች ሀገር ጋዜጠኛ ቢኖር አፋጦ ከስልጣኛቸው ሳያወርድ እይመለሰም ነበር፡፡ ምን ያረጋል ይህ አልሆነም፡፡ በመጡበት መንገድ መርጠው ይሆናል፡፡ እነርሱም መውረድ አልፈለጉም፡፡ እሰከዚያው ድረስ በዚህ ችግር መሃል እነዚህን ሰዎች መሪዎች ብሎ የተቀበለ ህዝብ ምርጫው ነው ብለን ምርጫውን ማክበር አለብን፡፡
ቸር ይግጠመን!!!!

No comments:

Post a Comment